አምራቾችን ያሰጋው የዶሮ መኖና ግብአት ዋጋ መናር

ኢትዮጵያ የሌማት ቱሩፋት መርሃ-ግብር ከጀመረች ወዲህ በተለይ በዶሮ እርባታ ዘርፍ ከፍተኛ እምርታ ማስመዝገብ ችላለች፡፡ እያንዳንዱ ክልል መርሃ-ግብሩን በመተግበርና በማስፋት ዜጎች በተመጣጣኝ ዋጋ ዶሮም ሆነ እንቁላል እንዲያገኙ የማድረጉ ጥረትም ስኬታማ የሚባል እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ያምናሉ፡፡ ምርቱ በመስፋቱ ምክንያት በሃገሪቱ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በተለይ የእንቁላል ዋጋ በእጅጉ ቀንሶ እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ የዋጋ መቀነሱ በልማቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንዳያሳርፍ ተሰግቶም ነበር፡፡

ይሁንና ካለፈው ክረምት ወዲህ ካጋጠመው የመኖ ዋጋ መጨመር ጋር ተያይዞ የእንቁላል ዋጋ ጨምሯል፡፡ ይህም አርቢዎች ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ ከመሆኑም ባሻገር የህብረተሰቡን የመግዛት አቅም እየተፈታተነው ይገኛል፡፡

ዝግጅት ክፍላችን ያነጋገራቸው ዶሮ አርቢዎች የመኖ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጨመሩ ምክንያት ለኪሰራ እየተዳረጉ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ ላለፉት አራት ዓመታት በዶሮ እርባታ ስራ ሲተዳደር የቆየው ወጣት ሰለሞን ጌታቸው እንደሚለው፤ የእንቁላል ዋጋ ለመጨመሩ የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም የመኖ ዋጋ መናር ግን አብይ ጉዳይ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት እሱም ሆነ ሌሎች አምራቾች ጥቂት ጭማሬ አድርገው ቢሸጡም ካለው ወጪ አንፃር ተመጣጣኝ ገቢ እያገኙ አይደለም፡፡

የመኖ ዋጋ ንረት ከዚህ በላይ እየጨመረ ከሄደ በርካታ አርቢዎችን ከስራ ሊያስወጣ ይችላል የሚል ስጋት ያለው ወጣት ሰለሞን፤ በዚህ ምክንያት በሚፈጠር የዋጋ ጭማሪ ህብረተሰቡ እንቁላልም ሆነ የዶሮ ስጋ በቀላሉ ማግኘት የሚችሉበት ሁኔታ ላይኖር እንደሚችል አስገንዝቧል፡፡ እንደ ሃገርም በጥሩ ሁኔታ ላይ የነበረውን የዶሮ ልማት ስራ ወደ ኋላ እንዳይጎትተው መኖ ልማት ላይ መንግስትም ሆነ የግሉ ባለሃብት በስፋት ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝቧል፡፡

ወይዘሪት ማህሌት ዮሐንስ በአለማ ካውዳይስ የእንስሳት መኖ ፋብሪካ የሽያጭ ባለሙያ ነች፡፡ እሷ እንደምትናገረው፤ ድርጅቱ ለዶሮ፣ ለወተት ላሞች፣ ለሚደልቡ በሬዎችና ለዓሳዎች እንደ የእድሜያቸው፣ እንደሚሰጡት የምርት መጠን የተለያዩ ዓይነት መኖዎችን ያመርታል፡፡ ድርጅቱ ላለፉት 15 ዓመታት የሚያመርታቸውን መኖዎች በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ ወኪሎቹ አማካኝነት ለተጠቃሚዎች በማድረስ ለዘርፉ እድገት የበኩሉን ሚና በመጫወት ላይ ነው፡፡

በተጓዳኝም በዘርፉ ለዓመታት የካበተ ልምድ ካለው የኔዘርላድ ኩባንያ ጋር በጥምረት እየሰራ መሆኑን ጠቅሳ፤ ‹‹መኖ ስናመርት በሃገር ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ የጥሬ እቃ ችግር ያጋጥመናል፤ ለአንድ እንቁላል ጣይ ዶሮ ከ15 በላይ ጥሬ እቃ ያስፈልጋል፤ እነዚህን ግብዓቶች በሃገር ውስጥ እንደልብ ማግኘት ስለማይቻል በዚያው ልክ የማምረት አቅማችንን ይገድበዋል ›› ትላለች፡፡

ሆኖም ከኔዘርላንዱ ኩባንያ ጋር በመተባበር የጥሬ እቃ እጥረቱ ምርት ላይ ጫና እንዳይፈጥር ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክታለች፡፡ ግብዓት እንደልብ አለመገኘቱ መኖ በስፋት የማምረቱን ስራ ፈታኝ እንዲሆን ማድረጉን ገልጸው፣ ችግሩ የማምረቻ ወጪያቸውን ከፍ እንደሚያደርገው አስታውቃለች፡፡

‹‹በሃገር ውስጥ ያለው የመኖ ግብአት ዋጋ ሲንር እኛ በምርታችን ላይ ዋጋ ለመጨመር እንገደዳለን፤ ያም ቢሆን በቻልነው አቅም ትንሽ ትርፍ አግኝተን አርቢዎችን ለማገልገል ነው የምናስበው›› በማለት ወይዘሪት ማህሌት ትናገራለች፡፡

እሷም በቅርቡ በመኖ አልሚዎች ላይ ቫት መጨመሩ ችግሩን ‘ከድጡ ወደ ማጡ’ አድርሶታል ባይ ነች፡፡ እንደ አጠቃላይ መኖ በስፋት ለማቅረብም ሆነ የዶሮ ርባታው ዘላቂ እንዲሆን ከተፈለገ የግብዓት እቅርቦቱ መሻሻል አለበት ስትል አመልክታ፤ በተለይ መንግስት ዘርፉ ለህብረተሰቡ ያለውን ጠቀሜታ በመገንዘብ የቫቱን ጉዳይ ዳግመኛ ሊፈትሽና አልሚዎችንም ሊደግፍ እንደሚገባ አስገንዝባለች፡፡

በአሜን እንስሳት መኖ ማምረቻ የምርት ጥራት ተቆጣጣሪ የሆኑት አቶ ድንቁ ወርቁ በበኩሉላቸው እንደሚናገሩት፤ ድርጅታቸው ከተመሰረተ ስድስት ዓመታት ብቻ ቢሆንም፣ ደረጃቸውን የጠበቁ የእንስሳት መኖዎችን በማምረት በ30 አከፋፋዮቹ አማካኝነት በመላው ሃገሪቱ ለሚገኙ አልሚዎች ተደራሽ ያደርጋል፡፡ በተለይም በየጊዜው የሚስተዋለውን የግብዓት ችግር በመቋቋምና መኖን በስፋት በማምረት የዋጋ መረጋጋት እንዲሰፍን የበኩሉን ጥረት በማድረግ ላይ ነው፡፡

‹‹ያም ቢሆን እንደማንኛውም መኖ አምራች ኢንዱስትሪ በሃገር ውስጥ ያለው የዋጋ አለመረጋጋት በስራችን ላይ ትልቅ ችግር እየፈጠረ ነው›› የሚሉት አቶ ድንቁ፤ ይህም በተለይም ጥሬ እቃ እንደልብ ካለማገኘትና ከዋጋ መናር የሚመነጭ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ‹‹በተለይ ካለፈው ሰኔ ወር ወዲህ ንግድ ሚኒስቴር ቫት እንዲጨመር ማድረጉ ትልቅ ጫና ፈጥሮብናል፡፡ በዚህ ምክንያት እኛም መኖ ላይ ዋጋ ለመጨመር ተገደናል›› ይላል፡፡ ይህንን ተከትሎም በሃገሪቱ ዶሮ አርቢዎችም የእንቁላል ዋጋ ላይ በመጨመራቸው የስራ መቀዛቀዝ እንደሚስተዋል አመልክተዋል፡፡

ከስድስት ወራት በፊት የእንቁላል ዋጋ ሰባትና ስምንት ብር ወርዶ እንደነበር አቶ ድንቁም አስታውሰው፤ ‹‹በዚያን ጊዜ ደግሞ መኖ ወደ አምስት ሺ ብር ነበር፡፡ ቫቱ ከተጨመረ ወዲህ እኛም ሆንና ሌሎች አምራቾች በመኖ ዋጋ ላይ ለመጨመር ተገደናል›› ይላሉ፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ ዶሮ አርቢዎች ከገበያ የሚወጡትና ልማቱም የሚስተጓጎልበት ሁኔታ እንደሚፈጠርም ያስገነዝባል፡፡ ከሁሉም በላይ ጭማሬው የሚያርፈው ተጠቃሚው ህብረተሰብ ላይ መሆኑን ጠቅሰው፣ ጉዳቱም የሚያመዝነው ህብረተሰቡ ላይ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

‹‹በእርግጥ መንግስት ዘርፉን ለማሳደግ፤ እኛንም ሆነ ዶሮ አርቢዎችን ለመደገፍ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ቢሆንም የቫቱን ጫና የሚረዳልን አላገኘንም›› በማለት ያመለክታሉ፡፡ ብዙዎቹ አርቢዎች መኖ አምራቾች ሆነ ብለው ዋጋ ይጨምራሉ ብለው እንደሚገነዘቡ ጠቅሰው፣ ሆኖም ግን መኖ አምራቹ ግድ ስለሆነበት ደንበኞቹን ላለማጣት ሲል ብቻ ያለምንም ትርፍ የሚሸጥበት ሁኔታ እንዳለም ይጠቁማሉ፡፡ በመሆኑም በተለይ ከግብዓት ጋር ተያይዞ በተለይ አኩሪ አተርና በቆሎን የመሳሰሉ ምርቶች በስፋት እንዲመረቱ ትኩረት አድርጎ መሰራት እንዳለበት አቶ ድንቁ ያስገነዝባሉ፡፡

ከውጭ የሚመጡ እንደቫይታሚን ያሉ ግብዓቶች ዋጋ በየቀኑ እየጨመረ መሆኑንም አንስተው፤ ይህንን ምርት በሃገር ውስጥ ለመተካት ጥረት መደረግ እንዳለበትም ይናገራሉ፡፡ በሌላ በኩል መንግስት በሌማት ትሩፋቱም ሆነ በሌላ የልማት መስክ ዘርፉን ለማሳደግ እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ እንደሆነ አመልክተው፤ ይህ ጥረቱ ስኬታማ ሊሆን የሚችለው በዋናነት የመኖ አቅርቦቱ ሲሰፋና በተመጣጣኝ ዋጋ ማቅረብ ሲቻል እንደሆነ ነው የጠቆሙት፡፡

‹‹ድርጅታችን እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን፣ ቄብ ዶሮዎችን እያሳደገ ይሸጣል፤ የመኖ ማቀነባበሪያም አለን›› በማለት የተናገሩት ደግሞ ሱፐር ሮቫን በተባለ የዶሮና መኖ አምራች ድርጅት ውስጥ ከፍተኛ የሽያጭ ባለሙያ ሆነው እያገለገሉ የሚገኙት ዶክተር ቢሊሱማ ሁሴን ናቸው፡፡ እንደእርሳቸው ገለፃ፤ ከተመሰረተ አምስት ዓመት የሆነውና ዋና ማዕከሉን በሃዋሳ ከተማ ያደረገው ድርጅታቸው የሚያመርታቸውን እንቁላል ጣይ ዶሮዎችንም ሆነ መኖዎች ለገበያ ያቀርባል፡፡ ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት 70 ሺ ዶሮ እንዲሁም 40 ሺ ጫጩት መያዝ የሚችል መጋዘን አለው፡፡ መኖ ደግሞ በሰዓት እስከ አምስት ወር ማምረት ይችላል፡፡ በአጠቃላይ ሃዋሳ ብቻ ለ98 ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ችሏል፡፡

‹‹መኖ ማምረት ከመጀመራችን በፊት መኖ ከገበያ እንገዛ ነበር፤ በየወቅቱ የመኖ ዋጋ የሚዋዥቅ በመሆኑ ምክንያት ስራችን ችግር ያጋጥመው ነበር›› ሲል ያስታውሳል፡፡ አሁን መኖ ራሳቸው እያመረቱ የሚጠቀሙ ቢሆንም የአኩሪ አተርና በቆሎ ዋጋ ሲጨምር የማምረቻ ወጪያቸውን እንደሚጨምር ጠቅሰው፣ ይህም ችግር በስፋት ለማምረት እንቅፋት መሆኑ እንዳልቀረ ያስረዳሉ፡፡ ‹‹ከሁሉም በላይ ደግሞ በመኖም ሆነ በእንቁላል ላይ ቫት በመጨመሩ ከፍተኛ ጫና አሳድሮብናል›› ሰሉ ያመለክታሉ፡፡ ልክ እንደ አቶ ድንቁ ሁሉ ጭማሬው ዞሮ ዞሮ በከፍተኛ ደረጃ የሚጎዳው ተጠቃሚውን በመሆኑ መንግስት አሰራሩን ሊፈትሽ እንደሚገባ ያስገነዝባሉ፡፡ ‹‹ከመኖና ዶሮ ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ከምግብ ነክ ነገሮች ላይ ቫት መነሳት አለበት፡፡ በተለይ መንግስት የተመጣጠነ ምግብ ለሁሉም ዜጋ ተደራሽ እንዲሆን እየሰራ ባለበት በዚህ ወቅት መኖና እንቁላል ላይ ቫት መጨመሩ በልማቱ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳደር ያላቸውን ስጋት እሳቸውም ጠቁመዋል፡፡

የግብርና ሚኒስትር ዶክተር ግርማ አመንቴ በቅርቡ በወቅታዊ የግብርና ጉዳዮች ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት፤ የዶሮ መኖን አስመልክቶ በቀረቡ ጥያቄዎች ላይ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ እንደተናገሩት፤ የሌማት ቱሩፋት ከተጀመረ ወዲህ የመኖ አቅርቦት ችግርን ለመፍታት ትልቅ ትኩረት ተሰጥሮ እየተሰራ ነው፡፡ ለዚህም በመንግስት ግልፅ አቅጣጫ የተቀመጠ ሲሆን፤ የመኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን በየክልሉ ተደራሽ ማድረግ ይገባል የሚል እምነት ተይዞ እየተሰራ ነው፡፡

‹‹እንደተባለው የመኖ ዋጋ ውድ እንዲሆን ካደረጉ ምክንያቶች መካከል የግብዓት እጥረቱ አንዱ ቢሆንም በተለይ ከዚህ ቀደም ማቀነባበሪያዎች ከአምራቹ በርቀት የሚገኙ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የትራንስፖርት ወጪ በራሱ ዋጋው እንዲንር ያደርገው ነበር›› ሲሉ ዶክተር ግርማ ያስረዳሉ፡፡ በሌላ በኩል ግን አብዛኛዎቹ የመኖ ግብዓቶች ሃገር ውስጥ የሚመረቱ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር አንድ ኮሚቴ ተቋቁሞ አነስተኛ እና መካከለኛ የመኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን ለማቋቋም ጥረት እየተደረገ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡

መቀነባበሪያዎች በየክልሉ ተገንብተው በእያንዳንዱ አካባቢ መኖ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ‹‹ለምሳሌ የሲዳማ ክልል በጀት መድቦ እንዲገነባለት ጠይቋል›› ሲሉ ይጠቅሳሉ፡፡ በጀት ያላቸው ሌሎች ክልሎችና ኢንተርፕራይዞች ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር በመሆን ወደ ማምረቱ ስራ እየገቡ መሆናውንም ተናግረዋል፡፡ በተጨማሪም በፕሮጀክቶች አማካኝነት ለዘርፉ ልማት ድጋፍ በማድረግ የመኖ ፋብሪካዎቹን ወደ አርሶአደሩ የማቅረብና በሃገር ውስጥ የማምረት አቅምን ለማሳደግ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡ ይህም አሁን የሚስተዋለውንና መኖን ለማጓጓዝ እየወጣ ያለውን የትራንስፖርትና ሎጅስቲክ ወጪ ለመቀነስ እንደሚረዳ ነው ያብራሩት፡፡

‹‹ይህ እንዳለ ሆኖ ግን መኖ ላይ የተጣለው ቫት በእኛ በግብርና ሚኒስቴር እሳቤ ከጀመርነው ልማት አንፃር ቢታሰበብት እና ቢታይ በሚል ከንግድ ሚኒስቴርም ሆነ ከሌሎች አካላት ጋር ውይይት ጀምረናል›› የሚሉት ሚኒስትሩ፤ ምክንያቱም ደግሞ አንዱ የድጋፍ መገለጫ የማምረቻ ወጪ መቀነስ የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በዋናነት ግን በተለይ እጥረት ያለው የተቀነባበረ መኖ ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ ‹‹ማቀነባበሪያዎችን በማስፋት ምርቱን ተደራሽ የማድረግ ስራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን›› በማለት አስገንዝበዋል፡፡

ማህሌት አብዱል

አዲስ ዘመን ኅዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You