የዛሬው የስኬት እንግዳችን ወጣት ሥራ ፈጣሪ ነው። ከሰሞኑ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና በጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር አስተባባሪነት በተዘጋጀው 13ኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬና ቅባት እህሎች ጉባዔ ላይ ከፍተኛ አፈፃፀም ካገኙና በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ከፍተኛ ደረጃ ከደረሱ ባለሀብቶች መካከል ወጣት ሥራ ፈጣሪ በሚል ልዩ ሽልማት አግኝቷል። ይህ ወጣት ሥራ ፈጣሪ አቶ ፍሬው ደሳለኝ ይባላል።
አቶ ፍሬው የላንፎስ ትሬዲንግ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር መሥራችና ሥራ አስኪያጅ ነው። እሱ እንደሚለው፤ ከልጅነቱ ጀምሮ አርክቴክት መሆን ይፈልግ ስለነበር ዩኒቨርሲቲ ሲገባም የመጀመሪያ ምርጫው ያደረገው የኢንጂነሪንግ የትምህርት ክፍልን ነው። እንዳሰበው ባይሆንም በሲቪል ኢንጂነሪንግ ትምህርቱን ተከታትሏል።
ከትምህርቱ በተጓዳኝም ከንግድ ጋር የተያያዙ መፅህፍትን በስፋት ማንበብ ያዘወትር ነበር።፡ እነዚያ መፅህፍትም ተፅዕኖ ይፈጥሩበትና ከሲቪል ኢንጂነሪግ ትምህርቱ በተጨማሪ ቢዝነስ ለማጥናት ወስኖ በቢዝነስ ትምህርትም ዲግሪውን አገኘ።
የልጅነት ህልሙ በነበረው የሲቪል ኢንጂነሪግ ትምህርቱን ከማጠናቀቁ በፊት ለአንድ ዓመት ያህል በግል ድርጅት ውስጥ ተቀጥሮ መሥራቱን የሚናገረው ወጣት ፍሬው፤ ከተመረቀም በኋላ ለተጨማሪ አንድ ዓመት በዚህ ሙያ መሥራቱን ያስታውሳል።
አሁን ወዳለበት የንግድ ሥራ ከመግባቱ በፊት በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ለአንድ ድርጅት በገዢ ሠራተኝነት ሠርቷል። ይህም ሥራ ስለ ላኪና አስመጪነት ሥራ በጥልቀት ለማወቅ እድል እንደሰጠው ይገልጻል።
ተቀጥሮ ከመሥራት በዘለለ ስለዘርፉ የተሻለ ግንዛቤ ለማግኘትም አሁንም መፅህፍትን ማገላበጡን፤ መጠየቅና ጥናት ማድረጉን አላቆመም። ይልቁንም በዘርፉ ለመሠማራት እየተሳበ በመምጣቱ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ከተለያዩ አካላት ልምድ ለመቅሰም ጥረት አደረገ። አስቦና አቅዶ ብቻ አልቀረም፤ በሽያጭ ሥራ ካገለገላቸው ድርጅቶች የሚያገኛትን ሽርፍራፊ ገንዘብ ለምንም ነገር ሳይጓጓ መቆጠቡን ያዘ። ይህን ያደርግ የነበረውም ወደፊት ለመድረስ ያሰበው ራዕይ እውን መሆን እርሾ ይሆነኛል ብሎ ስላመነ ነበር።
‹‹እኔ በመሠረቱ የግድ ስለሆነብኝ እንጂ ተቀጥሮ መሥራት አልወድም፤ ገና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለሁ ጀምሮ ተቀጥሮ ከመሥራት ይልቅ የራሴን ድርጅት ከፍቼ መንቀሳቀስ ነበር ህልሜ፤ ለዚህም ነው የማገኛቸውን ሳንቲሞች ሳይቀር አጠራቅም የነበረው›› የሚለው ወጣቱ፣ እንደ ንግድ ሰው ዩኒቨርሲቲ በገባበት ወቅትም በትርፍ ሰዓቱ ቋንቋ በማስተማርና ተማሪዎችን በማስጠናት እንዲሁም የተለያዩ ዲዛይኖችን በመሥራት ገንዘብ ለማግኘት ጥረት ያደርግ እንደነበር ያስታውሳል። ‹‹ተቀጥሮ መሥራት እውቀት ለማግኘትና ልምድ ለመቅሰም እንደሚያግዝ ስለማምን ለተወሰነ ጊዜ ተቀጥሬ መሥራት ነበረብኝ፤ ሥሰራም ልክ እንደራሴ ሥራ አድርጌ ነበር የምሠራው›› ሲል ያብራራል።
በወጣቶች የተመሠረቱ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ታሪክ ይስቡት እንደነበር የሚያስታውሰው አቶ ፍሬው ፤ በዓለም ላይ የሚታወቁና ሪቴል /ሸቀጦችንና አገልግሎቶችን በመሸጥ የንግድ ሥራ/ ላይ የሚሠሩ ድርጅቶችን ታሪክ በማጥናት ጊዜውን ያሳልፍ እንደነበር ይጠቅሳል።
ተቀጥሮ በሚሠራበት ጊዜ የተለያዩ አዳዲስ ሃሳቦችን በማምጣት የሚሠራበትን ተቋም ለማሻሻል ጥረት ቢያደርግም በሀገሪቱ ካለው የሥራ ባህልና ለወጣቶች ካለው ዝቅተኛ አስተሳሰብ የተነሳ ተቀባይነት ለማግኘት አለመቻሉን ያስረዳል። ይህም እንደማንኛውም ወጣት ተግዳሮት ሆኖበት እንደነበርና በዚህም ምክንያት የተሻለ ሃሳብ ቢኖረውም ድርጅቱን በሚመራው አካል መስመር ለመከተል ግድ ብሎት እንደነበር ያስታውሳል።‹‹እነዚያ መንገዶች ጊዜ ያለፈባቸውና አሁን ላይ እንደማይሰሩ ባውቅም ለውጥ እንድናመጣ ነባራዊ ሁኔታው አይፈቅድም ነበር›› ይላል።
በሌላ በኩል ለሠራበት የሚያገኘው ክፍያ ዝቅተኛ መሆንም ራሱን ችሎ ለመቆም ፈተና ሆኖበት እንደነበርም ያስታውሳል። ‹‹ሲቪል ኢንጂነሪንግ ተመርቄ ተቀጥሬ አገኝ የነበረው ብር 4ሺ500 ብር ብቻ ነበር ፤ ይህም ደግሞ ራሴን ለመቻል እንኳ የማይበቃ ነበር›› በማለት ይናገራል።
እነዚህ ሁሉ ገፊ ምክንያቶች ከልጅነቱ ጀምሮ የራሱን ኩባንያ ለሟቋቋም እንደረዱት ይገልፃል። በወጪ ንግድ ለመሰማራት ፍላጎት እያደረበት በመጣበት ወቅት ደግሞ ሌላ ፈተና ገጠመው፤ በንግዱ ሥራ ላይ እውቀትና ልምዱን በበቂ ሁኔታ ቢያካብትም የወጪ ንግድ ላይ ለመሰማራት ከፍተኛ ካፒታል የሚፈልግ መሆኑ ደግሞ ሌላ ፈተና ሆነበት።
‹‹እኔ የወጪ ንግዱን ዘርፍ ስቀላቀል የሰሊጥ ዋጋ አሁን ካለው ዋጋ ጋር ሲነፃፀር በጣም ዝቅተኛ ቢሆንም፣ ያንን ገንዘብ ለማግኘት ትልቅ ፈተና ሆኖብኝ ነበር›› ይላል። በመሆኑም ትላልቅ ዓለም አቀፍ ጉባዔዎችና አውደ-ርዕዮች ላይ በመሳተፍ በቀላል መንገድ ዘርፉን መቀላቀል የሚችልበትን መንገድ ማጥናት ያዘ።
አቶ ፍሬው የውጪ ንግዱን ከመቀላቀሉ በፊት ግን ዘርፉን የሚያንቀሳቀሱ አካላት ማን እንደሆኑ፤ የኢትዮጵያ ምርቶች መዳረሻ ሀገራት የት የት እንደሆኑ፤ ምን አይነት የጥራት መስፈርት ነው የሚጠይቁት በሚሉት ወሳኝ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ጥናት አድርጓል። ጎን ለጎንም ለተለያዩ ድርጅቶች ግዥ በመፈፀም እገዛ ያደርግ እንደነበርም ይናገራል። እነዚህ ድምር ጥረቶቹ ደግሞ የዓለም አቀፍ ገበያን ባህሪና ሁኔታ አበጥሮ ለመለየት አገዙት። ከዚህም ባሻገር የሚሳተፍባቸው መድረኮች የተለያዩ የውጭ ደንበኞችን ለማፍራት አስቻሉት። በእነዚህ ሥራዎቹ ያገኘውን ሁለት ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል በማድረግ የተለያዩ የጥራጥሬና የቅባት እህሎችን ወደ ውጭ መላክ ጀመረ።
ከሶስት ዓመታት በፊት በዚህ ሁለት ሚሊዮን ብር እና ሶስት ሠራተኞችን በመቅጠር ሥራውን የጀመረው ወጣቱ የንግድ ሰው፣ በአሁኑ ወቅት 20 ለሚደርሱ ሰዎች ቋሚ እና ከ100 ለማያንሱ ደግሞ በጊዜያዊነት የሥራ እድል መፍጠር ችሏል። የኩባንያውን ቅርንጫፎችም በአዲስ አበባ ከተማ ሶስት፤ አዳማ ከተማ ሁለት አድርሷል። በድምሩ በአምስት መጋዘኖች ያሉት ሲሆን በምርት ገበያና ከኮንትራት እርሻ የሚገኙ ሰብሎች ይከማቻሉ፤ በእያንዳንዱ መጋዘን ከ20 እስከ 30 ሰዎች ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ጥራት የማስጠበቅ ሥራ እንዲሠሩ ይደረጋል።
አቶ ፍሬው እንደሚለው፤ የድርጅቱ ምርቶች ዋና ዋና መዳረሻዎች በአውሮፓ ቤልጂየም፣ ጣሊያን፣ ቱርክ፣ ቡልጋሪያ፤ በመካከለኛው ምስራቅ የተባበሩት ኢምሬቶች፣ ሳዊዲ አረቢያ፣ ኦማን ፣ ጆርዳን እና እስራኤል ናቸው። ወደ ፓኪስታን፣ ህንድ፣ ቻይና ኢንዶኔዢያ ገበያንም ጨምሮ የኢትዮጵያ ጥራጥሬና ቅባት እህሎች ዘልቀው እንዲገቡ ማድረግ ችሏል። በአሁኑ ወቅት የደቡብ አፍሪካና መካከለኛው አሜሪካ ገበያንም ጭምር በተወሰነ መልኩ በመቀላቀል ላይ ይገኛል።
‹‹አብዛኞቹ ዓለም አቀፍ ገዢዎች ከአፍሪካውያን ጋር የመሥራት ፍላጎት የላቸውም›› የሚለው አቶ ፍሬው፤ ይህም የሆነበት ምክንያት አንድም ከጥራት ጋር በተያያዘ አፍሪካውያን ላይ ጥርጣሬ ያላቸው በመሆኑ እንደሆነ ይናገራል። ዋጋ ላይ ያላቸው ምልከታ ምክንያታዊ አይደሉም የሚል ግንዛቤ ስላላቸው እንደሆነ ያስረዳል።
በዚህ ምክንያትም አብዛኛውን ጊዜ በደላሎች ወይም አገናኞች አማካኝነት መሥራት እንደሚሹ ይጠቅሳል። ይህም በመሆኑ ትላልቅ ዓለምአቀፍ ኩባንያዎች የኢትዮጵያን ምርቶች ጥራት ቢያውቁም እንደ አጠቃላይ በአፍሪካ ላይ ባለው ጥቅልና የተዛበ እሳቤ ምክንያት በሚፈለገው ደረጃ የዓለምን ገበያ ሰብሮ ለመግባት አዳጋች ያደረገበት መሆኑን ያመላክታል።
ይህም ቢሆን ግን የድርጅቱ ምርቶች ዓለም አቀፍ ደረጃቸውንና ጥራት ጠብቀው እንዲላኩ ከፍተኛ ጥረት እንደሚያደርግ ይገልፃል። ‹‹የድርጅታችን መርሆም እኛ ገዢ ብንሆን የማንፈልገውን ምርት አንሸጥም የሚል በመሆኑ ጥራትን በሚመለከት ምንም አይነት ድርድር አናደርግም›› ሲል ያክላል። ከገበሬ የሚገዙትን ምርቶች ጥራት የጠበቁ ስለመሆናቸው ያጣራሉ፤ በማዘጋጃ መጋዘኖች እስከሚላኩባቸው ሀገራት ድረስ ደረጃና ጥራቱን ጠብቀው እንዲላኩ የሚያደርግ መሆኑን ያስገነዝባል። በዚህ ደረጃ ጥንቃቄ ማድረጉም የድርጅቱ ምርቶች በዓለም ገበያ ተፈላጊና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ምክንያት እንደሆነም አቶ ፍሬው ያምናል።
ሌሎች በዘርፉ የተሰማሩ ባለሀብቶችም ወደ ውጭ የሚልኩት ምርት የኢትዮጵያን ስም የሚያስጠራ እንደመሆኑ ከገበሬ ጀምሮ ምርቶች ሲሰበሰቡ፤ ሲታጠቡና ሲያዘጋጁ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ይመክራል።
የእሱ ድርጅትም ምርት ገዝቶ ከመሸጥ በዘለለ ለገበሬዎች ዘር እና በዘርፉ ለተሠማሩ አካላት የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመስጠትና በመደገፍ የበኩሉን ጥረት እያደረገ መሆኑን ያስረዳል። እንደሀገር የወጪንግዱ እንዲጎለብት ከተፈለገ በዋናነት የገበሬውን አቅም ማጎልበት እንደሚገባ ይናገራል። ‹‹በንግድ ላይ የተሠማራ የትኛውም አካል የቱንም ያህል ጥረት ቢያደርግ ምርቱን የሚያመርተውን የዘርፉ ዋነኛ ሞተር የሆነውን ገበሬ ካላገዝንና በቻልነው መጠን ካልደገፍነው የምንፈልገውን ውጤት ማምጣት አንችልም›› በማለትም ይገልጻል።
ድርጅቱ ወደ ውጭ የሚልካቸው ምርቶች መጠን ለማሳደግም ካፒታሉን በከፍተኛ ደረጃ ከፍ ለማድረግ እየሠራ መሆኑን ጠቅሶ፤ ‹‹ባለፈው ዓመት የጥራጥሬና ቅባት እህሎችን ወደ ተለያዩ ሀገራት በመላክ ወደ 14 ሚሊዮን ዶላር ለሀገር ማስገባት ችለናል›› ይላል። ዘንድሮም አምና ከተገኘው ከመቶ እጥፍ በላይ ለማግኘት እየሠሩ ስለመሆናቸውም ያመለክታል። ለዚህም ይረዳ ዘንዳ ጥራትን አጠናክሮ የማስቀጠልና የተሻለ የገበያ ተደራሽነት እንዲኖር ለማድረግ የሚያገኛቸውን እድሎች ሁሉ ተጠቅሞ እየሠራ እንደሆነ ያብራራል።
ሰሞኑን በተካሄደው የጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመሞች ዓለም አቀፍ ጉባዔ ላይም በጥራጥሬና ቅባት የወጪ ንግድ “Young and Immerging Exporeter›› በሚል ልዩ ዘርፍ መሸለሙ ትልቅ መነቃቃት የፈጠረበት መሆኑን አቶ ፍሬው ያመለክታል። ‹‹በተለይ ደግሞ ከእኔ ጋር የተሸለሙት አብዛኞቹ ኩባንያዎች በጣም የካባተ ልምድ ያላቸው ትላልቅ ድርጅቶች እንደመሆናቸው መሸለሜ ምንም አይነት ተግዳሮት ቢኖር ከተሠራ ማሳካት እንደሚቻል አስገንዝቦኛል›› ሲል ይናገራል። ወደፊትም የበለጠ በመሥራት የኢትዮጵያ ምርቶች እሴት ተጨምሮባቸው እንዲላኩን የዓለምን ገበያ ሰብረው እንዲገቡ ለማድረግ እያደረገ ላለው ጥረት ጥሩ ማበረታቻ እንደሆነውም ይጠቁማል።
የኢትዮጵያን የግብርና ውጤቶች በማቀነባበርና እሴት በመጨመር ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት ለመላክ አቅዶ እየሠራ መሆኑን ያመለክታል። ወጣቱ ሥራ ፈጣሪ ትላልቅ ፋብሪካዎችን፤ ማበጠሪያዎችን የመትከል እቅድ እንዳለው ጠቅሶ፣ በዚህም ለበርካታ ሥራ አጥ ወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር ሃሳብ እንዳለውም አመላክቷል።
ለዚህም እቅዱ መሳካት በተለይም የፋይናንስ ተቋማት ድጋፍ ወሳኝ መሆኑን ያምናል። ‹‹ ብዙ ጊዜ የእኛ ሀገር የፋይናንስ ተቋማት ትልቅ ትኩረት የሚሰጡት ረጅም ጊዜ በዘርፉ ለቆዩ ድርጅቶች ነው። እንደእኔ ላሉ ወጣት ሥራ ፈጣሪዎች ግን ብዙ ቢሮዎች ላይ ጥሩ ተቀባይነት አይታይም፤ በተለይም ባንኮች ለወጣቶች ገንዘብ ለማበደር ይፈራሉ፤ በመሆኑም ይህንን የቆየ አተያይ በማስወገድ ተባባሪ ሊሆኑ ይገባል›› ሲል አስገንዝቧል።
ማህሌት አብዱል
አዲስ ዘመን ኅዳር 14 ቀን 2017 ዓ.ም