ኢትዮጵያ በወርቅ ማዕድን ሀብቷ ትታወቃለች፤ ይህን ማዕድን አልምቶ ተጠቃሚ መሆን ላይ ግን ብዙም አልተሰራባትም። ለእዚህ አንዱ ምክንያት ልማቱ እየተካሄደ ያለው በባሕላዊ መንገድ መሆኑ ነው። ወርቅ በአብዛኛው ሲመረት የኖረውም ሆነ እየተመረተ ያለው በእዚሁ በባሕላዊ መንገድ መሆኑ ይታወቃል።
ወርቅ ከባሕላዊ የአመራረት ዘዴ አለመላቀቁ ዜጎችም ሀገሪቱም ከእዚህ ወድ ሀብት የሚገባቸውን ያህል ተጠቃሚ እንዳይሆኑ አርጓቸው ኖሯል። ይህ ባሕላዊ አመራረት የወርቅ ሀብት እንዲባክን ከማድረጉም ባሻገር ምርቱ ለሕገወጦች ሲሳይ እንዲውል ሲያደርገውም ነው የቆየው።
መንግሥት ይህ ሀብት እንዳይባክን ተገቢውን ጥቅም እንዲሰጥ ለማድረግ መስራት ውስጥ ከገባ ቆይቷል። የወርቅ ማዕድኑ በአግባቡ ለምቶ ለዜጎችና ለሀገር ተገቢውን ጥቅም እንዲሰጥ፣ ሀገሪቱ ለተያያዘችው ልማት የፋይናንስ አቅም እንዲሆን፣ ለዜጎች የስራ አድል እንዲያስገኝ ለማድረግ በትኩረት እየሰራ መሆኑ ነው፡፡
በባሕላዊ መንገድ የሚካሄደው የወርቅ ልማት እንዲዘምን ለማድረግ ስልጠናዎችን በመስጠት፣ ቴክኖሎጂዎችን በማቅረብ፣ ወጣቶች በማሕበር ተደራጅተው ወደ ልማቱ እንዲገቡ በማድረግ ተሰርቷል፤ እየተሰራም ነው። በዚህም ለአያሌ ዜጎች የስራ እድል መፍጠር ተችሏል፤ በባሕላዊ መንገድ የሚያለሙትን ማሽነሪ ካላቸው ጋር በማስተሳሰር ልማቱ እንዲዘመን ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።
መንግስት ልማቱ ከዚህም በላቀ መልኩ እንዲካሄድ የወርቅ ልማቱን ለባለሀብቶች ክፍት አድርጓል። ይህን ተከትሎም ኩባንያዎች የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካዎችን እየገነቡ ያሉበት ሁኔታ ይታያል። እነዚህ ኩባንያዎች ወደ ስራ ሲገቡ በባሕላዊ መንገድ ከወርቅ የሚገኘውን የወርቅ መጠን በብዙ እጥፍ እንደሚያሳድጉትም ታምኖበታል።
ከእነዚህ ፋብሪካዎች አንዱ የሆነውና በጋምቤላ ክልል ዲማ በሚባለው አካባቢ የተገነባው ‹‹ኢትኖ ማይኒንግ›› የወርቅ ማምረቻ ፋብሪካ አንዱ ሲሆን፣ የፋብሪካው ግንባታ ተጠናቆ ከትናንት በስቲያ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተመርቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፋብሪካው ምርቃት ወቅት እንደተናገሩት፤ የዲማ ከተማ ከተመሰረተች ከ30 ዓመት በፊት ጀምሮ የወርቅ ግብይት ሲካሄድባት ቆይታለች። በአካባቢው የሚገኘው የወርቅ ማዕድን ለ30 ዓመታት ቢዛቅ ቢዛቅ ሊያልቅ አልተቻለም። ይህ የሚያመላክተው የጋምቤላ ክልል በተለይ ዲሞ በወርቅ ሀብት እጅግ ሀብታምና የደረጃ አካባቢ መሆኑን ነው፡፡
በአካባቢው ወርቅ በባሕላዊ መንገድ ሲወጣ የኖረ ሲሆን፣ እንዲህ አይነቱ የወርቅ ልማት አብዛኛው ወርቅ ለብክነት እንዲዳረግ በማድረግ ይታወቃል፤ የገበያ ሥርዓቱም ችግር ያለበት ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ወርቅ የሚመረትበት መንገድ በራሱ ከአንድ ቶን የወርቅ አፈር ሊገኝ የሚገባውን ያህል ወርቅ እንዳይገኝ የሚያደርግ ነው። ‹‹ጥቂት አግኝተን አብዛኛው እንዲባክን የሚያደርግ አሰራር ነው›› ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
ኢትኖ ማይኒንግ በዲማ አካባቢ ሥራ መጀመሩ በአካባቢው ሲባክን የኖረውን ወርቅ በአጭር ጊዜ በከፍተኛ ጥራትና መጠን ለማምረት እንደሚያስችል ገልጸዋል። ይህ ፋብሪካ ይዞት የመጣው እድል በመጀመሪያ ደረጃ ለዲማ አካባቢ ባሕላዊ ወርቅ አምራቾች ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው አመልክተዋል።
አምራቾቹ እስከ አሁን እንደሚያደርጉት ወርቅ በጥቂቱ እያወጡ ገበያ ማውጣት ሳይሆን ያልተጣራውን የወርቅ ምርት ወደ ኩባንያ በማምጣት እንዲጣራላቸው ቢያደርጉ ቀደም ሲል ያገኙት ከነበረው ወርቅ በእጥፍ ሊያገኙ እንደሚችሉም ጠቁመዋል። የወርቅ ዝውውሩን ሕጋዊ ማድረግ የሚያስችል መሆኑም ሁለተኛው ፋይዳው መሆኑን ገልጸዋል። ዲማ ላይ የወርቅ ሽያጭ ሕገወጥ በሆነ መንገድ ሲሰራ ብዙ ጊዜ በሕይወት ላይ አደጋም ያጋጥማል ሲሉ ጠቅሰው፣ ባሕላዊ አምራቾቹ ወርቁን ወደፋብሪካው የሚያመጡ ከሆነ ብዙ ወርቅ ማግኘት ብቻ ሳይሆን ዝውውሩም ሕጋዊ ስለሚሆን ትርፋማ ይሆናሉ ብለዋል።
የዛሬ 31 እና 32 ዓመት ገደማ የአካባቢው ወርቅ አምራች ወርቁን ወደ ከተማ ወስዶ ከሸጠ በኋላ ብሩን እዚያው ጨርሶ ሳይጠቀም ይቀር እንደነበር ጠቅሰው፣ አሁን ወርቁ ወደዚህ ፋብሪካ መጥቶ እንዲጣራ ከተደረገ አምራቾቹም፣ ወረዳውም ሀገርም በከፍተኛ ሁኔታ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡
‹‹በባሕላዊ መንገድ ወርቅ የምታመርቱ የዲማ አካባቢ ወርቅ አምራቾች የገበያ ማዕከላችሁ መሆን ያለበት ይሄ ፋብሪካ ነው›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበው፣ ፋብሪካው ይበልጥ ተጠቃሚ ስለሚያደርጋችሁ ሕገወጥ ከሆነው የግብይት ሥርዓት ወደዚህ ማምጣት ይኖርባችኋል›› ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት፤ ኢትኖ ማይኒንግ ይህንን ዘመናዊ ፋብሪካ ለመገንባት ሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ወስዶበታል። እንደዚህ አይነት ኢንቨስትመንት ለኢትዮጵያ የመጀመሪያው ነው። ፋብሪካው በውጭ የግሉ ዘርፍና በኢትዮጵያ ‹‹ሶቨርን ወርዝ›› በሚባል ድርጅት ትብብር የተሰራ ነው። በኢትዮጵያ ደረጃ በግሉ ዘርፍ እንደዚህ ያለ ዘመናዊ የወርቅ ፋብሪካ እስከዛሬ ኖሮ አያውቅም።
በሀገሪቱ ያሉት ፋብሪካዎች በሀገር ውስጥ ባለሀብቶችና በአብዛኛው በመንግስት ተጀምረው በኋላ ወደ ግሉ ዘርፍ የተሸጋገሩ ናቸው፤ ይሄኛው ከመነሻው ጀምሮ በግል ባለሀብት በግል ኢንቨስትመንት የተገነባ ፋብሪካ ነው።
ፋብሪከው በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ደረጃም በዘመናዊነቱ የተመሰከረለት /ሰርቲፋይድ የሆነ/ መሆኑንም ጠቅሰው፣ ከአንድ ቶን የወርቅ አፈር የምናመርተው የወርቅ መጠን በየትኛውም የአፍሪካ ሀገር ከሚመረተው ከፍ ያለ ነው›› ሲሉም የፋብሪካውን ዘመናዊነት ገልጸውታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳስታወቁት፤ የዲማ አካባቢ በወርቅ ምርት፣ በወርቅ ሀብት በእጅጉ ይታወቃል። እንደዚህ አይነት ዘመናዊ ፋብሪካ በባሕላዊ አመራረት ወቅት ለብክነት ይጋለጥ የነበረውን በርካታ ወርቅ ከብክነት በመታደግ ለገበያ እንዲወጣ በማድረግ ያግዛል። ይህ ፋብሪካ ገና ስራ መጀመሩ ነው፤ አቅሙ ስላለው በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ በሁለትና ሦስት እጥፍ ማደግም ይችላል። ፋብሪካው እንዲያድግ ለማድረግ የገበያ ሥርዓቱ ሰላም የሰፈነበት መሆን ይኖርበታል፡፡
‹‹ቀደም ሲል ታደርጉ እንደነበረው ሁሉ የዲማ አካባቢ ነዋሪዎች ይህን ፋብሪካ እንደግል ሀብታችሁ መጠበቅ ይኖርባችኋል። ይህ ፋብሪካ ከሌለ ይባክን የነበረውን ወርቅ ማግኘት አይቻልም። በሀገር ደረጃ ባለው ጥቅም ብቻ ሳይሆን፣ እያንዳንዱ ሰው በተዘዋዋሪ ከዚህ ምርት ስለሚጠቀም ፋብሪካውን መጠበቅና እንዲሰፋ ማድረግ የሁላችንም የጋራ ሥራ መሆን አለበት›› ብለዋል፡፡
‹‹ሁላችሁም እንደምታውቁት ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ከፍተኛ የማዕድን ሀብት ያላት ሀገር ናት፤ ይህ ሀብቷ ግን ባክኗል›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የቅርብና የሩቅ ጠላቶቻችን እነዚህን ምርቶቻችን ከለሙ፣ ኢትዮጵያ ካደገች፤ ኢትዮጵያ ከተለወጠች ስጋት ትሆንብናለች ብለው ስለሚያስቡ ወርቁም፣ ታንታለሙም፣ አይርን ኦሩም፣ ሊትየሙም ሁሉም አይነት ማዕድናት ያላት ሀገር ምንም እንደሌላት ሆና እስካሁን ቆይታለች›› ብለዋል።
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ከለውጥ በኋላ መንግሥት የማዕድን ዘርፍ ከፍተኛ ትኩረት ከሚገባቸው ዘርፎች አንዱ ነው በማለት በሁሉም ዘርፍ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ማድረግ ውስጥ ከገባ ቆይቷል። ‹‹ይህ ፋብሪካ የመጀመሪያችን እንጂ የመጨረሻችን አይደለም። በቅርቡ ተጨማሪ ፋብሪካዎችን እናስመርቃለን›› በማለት ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት፤ መንግስት ባለፋት ሁለትና ሦስት ዓመታት ከፍተኛ ሥራዎች ሲሰራ ቆይቷል፤ በዚህ ዓመት በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ እስከ 2 ቢሊዮን ዶላር ከወርቅ ብቻ ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ ነው። ይህም ቢሆን ኢትዮጵያ ካላት አቅም አንጻር ሲታይ በጣም ውስን ነው።
‹‹በርትተን ብንሰራ፣ ለጠላት መሳሪያ ባንሆን፣ የማዕድን ሀብታችንን ብንጠቀም፣ ሰላማችንን ብንጠብቅ ኢትዮጵያ ለማኝ ሳትሆን ሰጪ፣ የተቸገረች ሳትሆን የበለጸገችና ሌሎችን የምትረዳ ስለምትሆን ሀብቶታችንን፣ የሰው ኃይላችንን፣ ጉልበታችንን መጠቀም ይገባናል›› ብለዋል፡፡
እሳቸው እንዳስታወቁት፤ ሰላም በራሱ አንድ ሀብት ነው፤ ሰላምን መጠበቅና ሀብታችንን ለልማት ማዋልና ወደ ሚጠቅም ነገር መመንዘር የመንግሥትም የሕዝብም የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ተገንዝቦ መስራት ጠንክሮ መስራት ያስፈልጋል።
‹‹ይህ ጅማሮ ይቀጥላል፤ ጋምቤላ ይለማል፤ በሌሎች አካባቢዎች ያሉ ሀብቶች ሁሉ ይለማሉ፤ የኢትዮጵያን ብልጽግ እናረጋግጣለን›› ብለዋል። በግብርናም፣ በማዕድንም፣ በኢንዱስትሪም፣ በቱሪዝምና በቴክኖሎጂም ያሉን ሀብቶች ተስናስለው ሌሎች ዘርፎችን በማንቀሳቀስ የኢትዮጵያን ብልጽግና እውን እስኪያደርጉ ድረስ እንቅልፍ አይኖረንም ሲሉም አስገንዝበዋል። ለዚህ እንተባባር፣ እንበርታ፤ እንስራ ለለውጥና ለብልጽግና ለልማት በጋራ እንቁም›› ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
መረጃዎች እንዳስታወቁት፤ ኢትኖ ማይኒንግ የአኮቦ ሚኒራልስ ኩባንያ መጋቢ ሲሆን፣ በስካንዲኔቪያን ሀገራት መሠረቱን ያደረገ በኢትዮዽያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ በኩል ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በወርቅ ፍለጋ እና ማውጣት ስራ ላይ የተሰማራ ኩባንያ ነው።
ፋብሪካው የተገነባበት የጋምቤላ ክልል ዲማ አካባቢ ከፍተኛ የወርቅ ሀብት ክምችት ያለበት ነው። ባለፉት ሶስት አስርት ዓመታት አካባቢው በአነስተኛና ባሕላዊ የወርቅ ማዕድን ማውጣት ስራ ትታወቃለች።
ፋብሪካው በአካባቢው በከፍተኛ ደረጃ ወርቅ ማምረት ኢንቨስትመንት ስራ ተሰማርቶ እየሰራ ይገኛል። በአጭር ጊዜ ውስጥ አመርቂ እና ደረጃውን የጠበቀ የወርቅ ምርት እንደሚያስገኝ ታምኖበታል፤ ለሕገወጥ ተግባር ተጋልጦ የቆየው የወርቅ ማዕድን በአግባቡ እንዲለማና ለገበያ እንዲቀርብ በማድረግ ተገቢውን ምላሽ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።
ኢትኖ ማይንግ የማዕድን ፋብሪካ በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ትልቅ ወርቅ አምራች ኩባንያ ነው። ፋብሪካው በሰዓት 10 ቶን የወርቅ አፈር የሚፈጭ ሲሆን፣ በዓመት ደግሞ አንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ቶን አፈር ይፈጫል።
በእውቀትና ቴክኖሎጂ ሽግግር እስካሁን በሀገሪቱ ውስጥ ካሉ የማዕድን ፋብሪካዎች አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የሚስተካከለው እንደሌለም ተጠቁሟል። ይህ መሆኑ የአካባቢ ብክለት እና መሰል ተያያዥ ጥያቄዎችን የማያስነሳ ፋብሪካ እንዲሆን ያስችለዋል።
ለበርካታ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል የፈጠረ ነው። ግንባታው እየተካሄደ ባለበት ወቅት ብቻ ለ220 ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ፈጥሯል። ወደ ሥራ ሲገባ ደግሞ ከዚህ በላቀ ደረጃ የሥራ ዕድል ይፈጥራል።
በአንድ ወቅት በጋምቤላ ክልል ዲማ ወረዳ ተገኝተን የግንባታውን ሂደት በተመለክትንበት ወቅት ያነጋግርናቸው የኢትኖ ማይንግ የወርቅ ፋብሪካ ሳይት ማናጀር ኢንጂነር ወልደገብርኤል አረጋዊ ክልሉ ትልቅ የወርቅ ሀብት ክምችት እንዳለው ጠቅሰው፣ ይህም በወርቅ ማዕድን ልማቱ ብዙ መሥራት እንደሚያስችል ገልጸው ነበር።
እሳቸው እንዳሉት፤ ፋብሪካው ልማቱን የሚያካሂደው በ16 ኪሎ ሜትር ስኩየር ቦታ ላይ ሲሆን፣ ይህም ፋብሪካው ያረፈበት እና ወርቅ ፍለጋው የሚከናወንበት ስፍራን ያካትታል። የማዕድን ጥሬ እቃ ወይም ወርቅ ያዘለ አለት የሚወጣበት ስፍራ በጣም ምቹ እና ትልቅ ሀብት ያለበት ነው። በአካባቢው ያለው ወርቅ ያዘለ አለት በጣም ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው፣ ተፈላጊነቱም በዚያው ልክ መሆኑን ተናግረዋል።
በአካባቢው ከአንድ ቶን አፈር ውስጥ በአማካይ 22 ነጥብ 7 ግራም ወርቅ ማግኘት ይቻላል፤ የፋብሪካው በአካባቢው መገንባትም ይህን ሁሉ ታሳቢ አድርጓል። ለዚህም የሚውል ለየት ያለ ቴክኖሎጂ ሥራ ላይ ይውላል። የወርቅ ማዕድን አቅሙም ሆነ ያንን ለማውጣት የሚተከለው ፋብሪካ አቅም ለኩባንያው ብቻ ሳይሆን ለሀገሪቱ ከፍተኛ ፋይዳ አለው ሲሉ ተናግረዋል።
የቅርብ ጊዜ መረጃ እንዳመለከተው፤ በኢትዮጵያ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ከ517 ቶን በላይ የወርቅ ክምችት መኖሩ ተረጋግጧል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ዓርብ ኅዳር 13 ቀን 2017 ዓ.ም