ለትውልድ የሚመጥን ከተማ፣ ለከተማው የሚመጥን ትውልድና የከተማ መሪን የመፍጠር ኃላፊነት

በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ባለው የኮሪደር ልማት ከተማዋን ለነዋሪዎቿ ለስራ፣ ለጎብኚዎቿና እንግዶቿ የምትመች ለማድረግ እየተሰራ ነው። ከተማዋ የሀገሪቱ መዲና ብቻ አይደለችም፤ የአፍሪካ ህብረት ዋና መስሪያ እና የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ ናት። የኮሪደር ልማቱ ይህን የከተማዋን ደረጃ የሚመጠን ግንባታ እየተካሄደ ይገኛል።

አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስና ውብ ማድረግን ያለመው ይህ ልማት፣ በመጀመሪያው ዙር የኮርደር ልማትም ይህን ማረጋገጥ ያስቻሉ ተጨባጭ ግንባታዎች ተካሂደው ወደ ስራ ገብተዋል። የከተማዋን ገጽታ በእጅጉ ያበላሹ መኖሪያ ቤቶች፣ የንግድ ቤቶች ተነስተው፣ ሰፋፊ የተሽከርካሪ መንገዶች ተገንብተዋል። የእግረኞች፣ የብስክሌት፣ የአካል ጉዳተኞች መንገዶች ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ ተገንብተዋል።

አረንጓዴ ስፍራዎች ፣ አደባባዮች፣ መጸዳጃ ቤቶች፣ ፋውንቴኖች፣ በእግራቸው የሚንቀሳቀሱ የከተማዋ ነዋሪዎች እንግዶችና ጎብኚዎች አረፍ የሚሉባቸው ስፍራዎችም ተገንብተው ከተማዋን ማድመቅ ጀምረዋል።

በመሰረተ ልማት ግንባታው የከተማዋን ገጽታ በእጅጉ አጉድፈው የነበሩ እንደ የኤሌክትሪክ፣ የውሃና ቴሌኮም መስመሮች ያሉት እንዲሁም የፍሳሽ ማስወገጃዎች በሙሉ በመሬት ውስጥ እንዲያልፉ ተደርጓል።

ከተማዋ ምሽትና ሌሊቱን ሙት ሆና ከኖረችበት ሁኔታ መውጣት ያስቻሏት የተለያዩ የመንገድ፣ የህንጻና የአጥር ላይ መብራቶች ተዘርግተዋል፤ በመንገዶቹ የደህንነት ካሜራዎች ጭምር የተካተቱ በመሆናቸው ከተማዋን በምሽትም በሌሊትም ያለስጋት ሊጓዙባት የምትችል ማድረግ እየተቻለ ነው።

የኮሪደር ልማቱ ምን ያህል ከተማዋን እየቀየረ እንዳለ ለመረዳት የከተማ አስተዳደሩ በየጊዜው የሚሰጣቸው መግለጫዎች፣ በየጊዜው የሚመርቃቸው የኮሪደር ልማቱ ግንባታዎች፣ የመገናኛ ብዙሃን መረጃዎች በሚገባ መከታተል ይበቃል። የልማቱ ቱሩፋቶች በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በሚደረግ እንቅስቃሴ ጎልተው የሚታዩ መሆናቸው እንዳለ ሆኖ ፣ አራት ኪሎን፣ ፒያሳን፣ ሰራተኛ ሰፈርን፣ ቦሌ መገናኛ መንገድን፣ ሜክሲኮ ሳር ቤት፣ ቄራ ጎተራ ወሎ ሰፈርን አራት ኪሎ መገናኛን በቀንም በምሽትም ተዟዙሮ በመመልከት ምን ያህል እንደተሰራ መረዳት ይቻላል።

በዚህ ከፍተኛ የስራ ባህል ለውጥ በታየበት የኮሪደር ልማት በሳምንት ሰባት ቀናት፣ በቀን ለ24 ሰአታት በተካሄደ ግንባታ፣ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት መፈጸም እንደሚቻል ማሳየትም ተችሏል።

ለሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማቱ ግንባታ የጸዱ አካባቢዎችን፣ ግንባታቸው የተጀመረ ፕሮጀክቶችን፣ ከተማ አስተዳደሩ በዚህ ምእራፍ ሊያካሂዳቸው ያቀዳቸው ፕሮጀክቶችም ሌሎች ልማቱ ምን ያህል እየሰፋ እንደመጣ የሚጠቁሙ ናቸው።

በዚህ በመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት የከተማዋ የተወሰኑ ኮሪደሮች የተሸፈኑ ሲሆን፣ አሁን ደግሞ በሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት በርካታ የከተማዋን ኮሪደሮች በልማቱ ለመድረስ ታቅዶና በቂ ዝግጅት ተደርጎ ወደ ትግበራ ተገብቷል። ለዚህ ልማትም ከመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት ተሞክሮ ተወስዷል።

ከመጀመሪያው ምዕራፍ የተወሰዱ ተሞክሮዎችን በመቀመርም በተሻለ የመሰረተ ልማት ስራዎች እንቅስቃሴ ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ ተገብቶ ከተማዋን መልሶ ለማደስ እና ለትውልዱ የምትገባ ዓለም አቀፍ ከተማ ለማድረግ የተጀመረው የኮሪደር ልማቱ ተጠናክሮ ቀጥሏል።

የሁለተኛው ምዕራፍ መዲናዋን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ለማድረግ የሚያሰችሉ ዘግጅቶች ተደርገው እና ዲዛይን ተዘጋጅቶ ነው ወደ ስራ የተገባው። በዚህ ምዕራፍ ቀጣይነት ያላቸው ስራዎች ቢኖሩም እስከ የካቲት ወር አካባቢ ዋና ዋና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎችንም ለማጠናቀቅ ፕላን ተደርጎ ወደ ስራ ተገብቷል።

በቅርቡ የተጀመረው የዚህ የሁለተኛው ምእራፍ የኮሪደር ልማት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት ባለፈው ሳምንት መካሄዱ ይታወቃል። በዚህ መድረከ ላይ ከንቲባ አዳነች አቤቤና ሌሎች ልማቱን የሚመሩ አካላት በሁለተኛው ምእራፍ የኮሪደር ልማት ላይ ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያና አቅጣጫ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ካነሷቸው የተለያዩ ጉዳዮች መካከል፤ በኮሪደር ልማቱ ሶስት አላማዎች ታሳቢ ተደርገው እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። በኮሪደር ልማቱ የሚሰሩት ለትውልድ የሚመጥን ከተማ፣ ለዚያ ከተማ የሚመጥን ትውልድ እና ከተማን የሚመራ ሰው መፍጠር ናቸው›› ሲሉ አመልክተዋል። “እየተገነባ የሚገኘው ለትውልድ የሚመጥን ከተማ፣ ለትውልድ የሚመጥን ሀገር ነው፤ መሰረተ ልማት ብቻ ሳይሆን ትውልዱም ስራ ይፈልጋል” ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳብራሩት፤ ሀገር ሲገነባ ሁልጊዜም በዚያ የነበሩ ሰዎች በቀላሉ ተቀብለውት ተስማምተው የሚሄዱበት ጉዳይ አይደለም። እንደዚያ ቀላል ቢሆን ሀገራችን ባልቆሸሸች ነበር። ይሄ የነዋሪዎች ባህሪ ብቻ ሳይሆን የሁላችንም ባህሪ ነው። ለምሳሌ ውጭ ሀገር ሲኬድ ከአምስትና ሰባት ሰዓት በረራ በኋላ ደውላችሁ ምን አለ ትላላችሁ። የራስ የራስ ነው ስለቆሸሸ ጥሩ ሀገር ስለሄድን የምንረሳው ጉዳይ አይደለም። የምታስታውሱት ሜክሲኮን፣ ፒያሳን፣ ምናምን ነው። የሰው ባህሪ ነው። ልክ እንደዚያው ካዛንቺስ ወይም አራት ኪሎ አካባቢ የነበረ ሰው ወጥቶ ለሚኩራ ሲባልም ተመሳሳይ ነው። ልምምድ የሚፈጥረው ጫና ነው። ሰው ከተለማመደው ነገር መላቀቅ ይቸገራል።

ከተማ ስንገነባ መጀመሪያ በራዕዩ እና ህልሙ ላይ መግባባት ላይ መደረስ አለበት፤ ከዚያም ሀገራቸውን የሚወዱ፣ ስለሀገራቸው ጥሩ የሚናገሩ፣ ሀገራቸውን በከፍተኛ ደረጃ የሚያስተዋውቁ ትውልዶች የሚፈጠሩበት ከተማ የገነባንለት ትውልድ ሲነሳ ነው። የምንገነባው ለትውልድ ከሆነ ያ የገነባንለት ትውልድ ሲነሳ ተመሳሳይ ቋንቋ እንሰማለን።

የዛሬ 26 ዓመት አዲስ አበባ ላይ ቢዞር በእርግጠኝነት የሚዞረው ትውልድ በሙሉ ሀገሩን የሚወድ፣ የሚጠብቅ ይሆናል። እኛ ቀድመን ነው ይህን እየፈለግን ያለነው፤ ቀድመን ከፈለግን አንችልም። ቀድመን ያንን አይነት መንፈስ በሀገራችን ላይ በከተማችን ላይ ማየት ከፈለግን አይሆንም። ያ እንዲሆን አሁን መልፋት ያስፈልጋል። በኋላ ያ ትውልድ ሲመጣ ደግሞ ልክ እንደ ሌሎች ሀገራት የራሱን ሀገር የሚወድ እና የሚያደንቅ ይሆናል።

የዛሬ 10 ዓመት የሆነ ሰው ቲኬት ቆርጦ ሌላ ሀገር ከሄደ በኋላ ለምን ቲኬት ቆረጥኩ ይላል፤ የኔ ሀገር ይሻላል፤ የኔ ሀገር መሰረተ ልማት ይሻላል፤ የኔ ሀገር መዝናኛ ቦታዎች ይመረጣሉ ለምን ይላል። እሱ ራሱ እየመሰከረ እያየ፣ እያነጻጸረ ይሄዳል። በመሆኑም ለትውልድ የሚመጥን ከተማ እና ሀገር መስራት ያስፈልጋል።

ሁለተኛው ደግሞ ለከተማው የሚመጥን ትውልድ መስራት ነው። በዚህም ከተማውን ብቻ ሳይሆን ትውልድም እንሰራለን። ለምሳሌ የብስክሌት መንገድ ሰርተንለት በእግሩ የሚሄድ ከሆነ ትውልድ አልተሰራም ማለት ነው። የእግረኛ መንገድ ሰርተንለት በአስፓልት መንገዱ ላይ የሚሄድ ከሆነ ትውልድ አልተሰራም ማለት ነው። የተዘጋጀለትን መሰረተ ልማተ በአግባቡ መጠቀም አይችልም።

ለአረንጓዴ ውበት ገንዘብ አውጥተን አፈር ውሃ አምጥተን ሳር አልብሰን ሳሩን እየረገጠ የሚሄድ ከሆነ ተውልዱ አልተሰራም ማለት ነው። መሰረተ ልማት ግን ተሰርቷል፤ ትውልዱ ግን አልተሰራም።

ልክ መሰረተ ልማቱ፣ ከተማውና ሀገሩ እንደተሰራው ሁሉ ትውልዱም ስራ ይፈልጋል። ትውልዱ የተሰራለትን ሀገርና የተሰራለትን ከተማ መጠበቅና መጠቀም ለማስቀጠል የሚችል እንዲሆን አድርገን ማዘጋጀት አለብን ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተው አስገንዝበዋል።

በዚህ ላይ ከፍተኛ ክፍተት ይታያል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሳር የሚረግጥ ሰው ሀገሪቱን የራሱ ሀገር አድርጎ ሳይሆን የሰው ሀገር ነው የተመለከተው ብለዋል። ሳር እየረገጠ የሚሄድ በሳይክል መንገድ ላይ በእግሩ የሚጓዝ የእግረኛ መንገድ እያለ በአስፓልት የሚሄድ በርካታ ሰው አለ። ይሄንን አስተሳሰብ እየቀየርን ለከተማዋ የሚመጥን ትውልድ መገንባት ሁለተኛው ስራ መሆኑን አመላክተዋል።

ሶስተኛው አንኳር ፍላጎት ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የጠቀሱት ከተማን መምራት የሚችሉ አመራሮችን መፍጠር የሚለው ነው። ባለፉት ዓመታት ከንቲባዎችን ከመሾም በዘለለ ከንቲባዎች ከተማቸውን መምራት ሳይሆን ከተማቸውን ማወቅ ሳይችሉ ይለቁ እንደነበር አስታውሰዋል።

ሰሞኑን በኮሪደር ልማት ምክንያት በየጉራንጉሩ ስትገቡ ነው የዜጎቻችን የኑሮ ሁኔታ እና ቤታቸውን፣ አዛውንቶች ያሉበትን ሕይወት ማየት የቻላችሁት ሲሉ የከተማዋን አመራሮች ገልጸው፤ ከዚህ በፊት አይታይም ነበር። ቢሮ በመቀመጥ ባለጉዳይ መጥቶ ያናግራችኋል፤ በዚህ ወቅት የባለጉዳዩን ህመምና ችግር ለመጋራት አዳጋች ይሆናል ሲሉ ተናግረዋል።

አሁን እየተፈጠረ ያለው አመራር ግን ቢያንስ ከተማውን በሚገባ የሚያውቅ፣ የከተማውን ችግር ለመፍታት የሚፍጨረጨር፣ በከተማ ውስጥ ያሉ እድሎችን የሚያይ፣ እዚህ ጋር ጨፌ ነው፤ እዚህ ጋ ተራራማ ነው፤ ዛፍ እተክላለሁ የሚለውን ቋንቋ መናገር የሚያስችለው ሁኔታ ተፈጥሯል፤ ይህም የሆነው ከተማ ውስጥ ገብቶ ማየት በመቻሉ ነው።

አዲስ አበባ ላይ የኮሪደር ልማቱን የምንመራው በተለየ መንገድ ነው። በየምዕራፉ በሀገር ውስጥም ጉብኝት ይደረጋል፤ ከሀገር ውጪም አመራሩ እንዲጎበኝ ይደረጋል። ዓላማውም ይሄ አመራር ከተማ ከሰራ በኋላ ለከተማ የሚመጥን ሰው ከሰራ በኋላ እሱን የሚመስል አመራሮች ይፈጥራል በሚል እሳቤ ነው ሲሉም አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳብራሩት፤ በሁለተኛው ምዕራፍ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጎንደር እና ቢሾፍቱ ተመድበዋል፤ ምክትል ከንቲባ ደሴና ሰመራ ተመድበዋል፤ ይህ የተመደባችሁበት መንገድ ለከተማው ልማት ብቻ ሳይሆን አመራር ለመፍጠርም ነው። በሌላውም ከተማን የሚመሩና የሚገነዘቡ ሰዎች መፍጠር እንዲቻል ነው። ለምሳሌ የከንቲባዋ ስራ ጎንደርና ቢሾፍቱ የከተማ መሪዎች ማገዝ ብቻ ሳይሆን የጎንደር እና ቢሾፍቱ ከንቲባዎች በአግባብ ከሰሩ ጉብኝት በማመቻቸት ወንጪንም ሊሆን ይችላል አዲስ አበባን ማሳየት ነው፤ ልክ እኔ ውጭ ሀገር አመቻችቼ እንደምልካችሁ ማለት ነው። አመራሩ እንደዚያ እየተፈጠረ እንዲሄድ ማድረግ ይጠበቅብናል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።

ከተሜነት አይቀሬ ነው፤ ተፈለገም አልተፈለገም አብዛኛው ማህበረሰብ ወደ ከተማ ይመጣል። ከተማን መምራት የሚችል ሰው መፍጠር ካልተቻለ እና ማዘጋጀት ካልተቻለ ደግሞ ከተማ ሳይሆን ሰዎች የሚሰባሰቡበት ችግርና የሌብነት ወንጀል የበዛበት ከባቢ እንፈጥራለን ብለዋል።

በኃይሉ አበራ

አዲስ ዘመን ህዳር 14/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You