ራስወርቅ ሙሉጌታ
የሰውን ልጅ ለጭንቀቶች ከሚዳርጉ ነገሮች መካከል አንዱ ግዜን በአግባቡ ያለመጠቀም ልምድ ነው። በተፈጥሮ ህግ ግዜ ለሁሉም ሰዎች እኩል የተሰጠ ቢሆንም እኩል ጥቅም ላይ ሲውል ግን አይታይም። ይልቁንም አንዳንዶች ግዜን በአግባቡ መጠቀም ባለመቻላቸው አምራችና ውጤታማ ካለመሆናቸውም ባሻገር ለተለያዩ ጭንቀቶች ሲዳረጉ ይስተዋላል። ለመሆኑ ግዜን በአግባቡ እንዴት ልንጠቀምበትና ከጭንቀት ድነን ውጤታማ ልንሆን እንችላለን ስንል የማህበራዊ ልማትና አመራር ባለሙያ ከሆኑትና በቲቪ ዘጠኝ የክሊፍ ሞቲቬሽን ወይም አፋፍ ለመድረስ ዝግጅት አዘጋጅና አቅራቢ አቶ ዘላለም ይትባረክን አነጋግረን የሚከተለውን ማብራሪያ ሰጥተውናል።
ጊዜ በተፈጥሮና በፍጥረት ውስጥ በቀን እና በሌሊት በብርሃን መሄድና መምጣት ሲሰፈር ለሰው ልጅ ግን የሚያስብ ከመሆኑ ጋር በተያያዘ ጊዜ በሰዓት ወይም በወቅት ትርጉምና ሚዛን ተሰጥቶት ይሰፈራል። የሰው ልጅም ይህንን መስፈሪያ ተከትሎ የየእለት ስራውን የሚያከናወን ቢሆንም አንዳንዶች ያላቸውን ግዜ ከዘልማድ በዘለለ በሳይንሳዊ መንገድ እየተመሩ የሚንቀሳቀሱበትና የሚቆጣጠሩት ባለመሆኑ በውጥረትና በግዜ ማነስ ሰበብ በስራቸው ወጤታማ ካለመሆናቸው ባሻገር ለጭንቀትም ሲዳረጉ ይስተዋላል። በስራ መወጠር ማለት ከአንድ ድርጊትና ስራ ወደ ሌላው እየተገላበጡ ግዜን ማሳለፍ ሲሆን ውጤታማ መሆን ግን ጊዜን በጥበብ እያስተዳደሩ መጠቀም እንደማለት ነው፡፡
ጊዜን በትክክል ለመጠቀም የሚረዱ ብልሃቶች
ጊዜን ማስተዳደር ማለት ራስን ማስተዳደር እንደማለት ሲሆን የሰው ልጅ በክህሎት ወይም በተግባር የሚገለጥበትም ነው፡፡ስለዚህም በጥሩ የጊዜ አስተዳደር የተትረፈረፈ ጊዜ እንዲኖረን ብዙ ስራዎችን በአንዴ ለመስራት አለመሞከር፣ እምቢ ማለት መማር፣ የመጨረሻ ቀን መቁረጥና እረፍት መውሰድ ተመካሪ ብልሃቶች ቢሆኑም ጠቅለል አድርገን ግን እንዲህ እንመልከታቸው።
የጊዜን ተፈጥሯዊ ባህሪ መረዳት
ግዜ የሚያልፍ አላፊ መሆኑን፤ መጠቀሚያ እንደሆነ፤ ዳኛ ፈራጅ መሆኑን፣ ጊዜ በህይወት የምንገለጥበት ወይም ድርጊታችን ሁሉ የሚበቅልበት (የምንዘራበት የእርሻ ማሳን ይመስል የዘራንበትን ያንን ብቻ ሊያበቅልልን የሚችል እንደሆነ መገንዘብ አለብን፡፡ጊዜ ሰጭ፣ ነጣቂ፣ አብዥ፣ አሳናሽ ወዘተ ወይም ጊዜ ከተጠቀምንበት የሚያከብረን የሚያሳድገን እንደሆነ ለዚህም በእውነት ጊዜንና የጊዜ ተፈጥሮን መረዳት ስንችል ለጊዜ ዋጋ በመስጠት የተሰጠንን በጤናማ መንገድ መጠቀም እንድንችል አቅም እናገኛለን ማለት ነው፡፡ጊዜን መጠቀም ስንል ለምንፈልገው ሳይሆን ለሚያስፈልገን እንደፈቀድነውና በውጤቱ እንደምንረካበት ጊዜን ማዋል ማለት ነው፡፡ጊዜን ለማስተዳደር ደግሞ የሚከተሉትን መፈፀም የሚጠበቅብን ይሆናል።
ራስን ማሽነፍ መቻል
ራስን ማሸነፍ ስንል አንደኛ ስሜትን ማስተዳደርና ሃሳብን መምራት መቻል ማለት ነው፡፡በዚህ ውስጥም የፍቃድ ስልጣን ልጓምን መጨበጥ ስለምንችል ለሚያስፈልገን ቅድሚያ እየሰጠን መጠቀም የምንችልበትን ልምድ ማዳበር እንችላለን፡፡ ያለበለዚያ ስሜት መርና ሃሳብ ነድ ህይወት እየኖርን የፍቃድ ስልጣናችን ልጓም ከእኛ ውጭ ስለሚሆን ጊዜን በአግባብ ለመጠቀም አያስችለንም፡፡ምክንያቱም በስሜትና በሃሳባችን በድምሩ በራሳችን ስለምንሸነፍ ለምናየው፣ ለምንሰማው፣ በስሜት ለቀረበን፣ ለለመድነው፣ ለሚያዘናጋን ወዘተ ሃሳብ ተገዥ ስለምንሆን ጊዜያችን ይባክንብናል ማለት ነው፡፡ይህም ተሰፍሮ በተሰጠን በሚያልቀውና በተገደበው ጊዜ ውስጥ መስራት ያለብንን መስራት ስለማንችል ውጤታማ ያልሆነ ህይወት ለመምራት እንገደዳለን፡፡
ራሳቸውን ማሸነፍ የሚችሉ በሃሳባቸው ልዕልና በተገነባው አስተሳሰባቸው ተጽዕኖ ፈጥረው፣ አሻራቸውን አስቀምጠው የሚያልፉ ናቸው፡፡ይህንን ማድረግ የቻሉ ከራሳቸው አልፈው የአገር ታሪክ ሰሚ ወይም ዳር ተመልካች ከመሆን ይልቅ የሚችሉትን አድርገው የአገራቸው ታሪክ አንድ አካል ለመሆን ይበቃሉ፡፡
ውሳኔን መወሰን መቻል
መወሰን መቻል የሰው ልጅ ያለውን ግዜ አውቆ በአግባቡ እንዲያስተዳድረውና እንዲጠቀምበት ያስችላል። የማይወስን ሰው በራሱም ሆነ የሌሎች ጊዜ እንዲባክን የሚያደርግና የጊዜ ዋጋ ያልገባው ነው። ጊዜ በአግባቡ የማይጠቀሙ ሰዎች ዋነኛው መገለጫ በተሰጣቸው ግዜ ማድረግ ያለባቸውን አለማድረጋቸው ብቻ ሳይሆን «አልችልም» በማለት ውሳኔ መወሰን አለመድፈራቸው ነው፡፡ እንደነዚህ አይነት ሰዎች ስራን ፤ ራሳቸውን ብሎም አገርን ይበድላሉ፤ ብዙ ነገሮችንም ለብክነት ይዳርጋሉ። ለዚህም ነው የአመራር ሳይንስ መወሰን መቻልን የመጀመሪያ መስፈርት የሚያደርገው።ምክንያቱም ባለመወሰን ከሚደርሰው ጉዳት ይልቅ በመወሰን የሚደርስው ጉዳት ትንሽ ነው፡፡
በዚህ ረገድ የብዙዎች ችግር የሚመርጡትን አለማወቅ ሳይሆን የመረጡትን ወስነው በአቋም አለመጽናታቸው ነው፡፡አቋም ያለው ሰው ስለሚወስን የፀና፣ ስር የሰደደ፣ በራሱ የቆመ ስለሚሆን ለዓላማ በዓላማ የሚኖር ነው። ስለዚህ መወሰን መቻል ጊዜን በትክክል በመጠቀም ህይወትን ውጤታማና የክብር ማድረግ የሚቻል ሲሆን በስራ ቦታም ቢሆን በተሰጠ ጊዜና ሃላፊነት የድርሻችን በመወጣት ከራስ አልፎ ለሌሎች ለመብቃት ያስችላል፡፡በመጨረሻም ውጤታማ የግዜ ተጠቃሚ ለመሆን በእቅድና በጊዜ ሰሌዳ (መርሃ- ግብር) መስራት ይጠበቃል። በዚህም መቼ ነጻ ጊዜ እንዳለ ለማወቅ የሚረዳ ሲሆን ይህንንም በአጭር ግዜ ከፋፍለን በሶስት አይነት ማሰቀመጥ ይቻላል።
- የቀን መርሃ-ግብር ማዘጋጀት፤ ይህ በየቀኑ የምናደርገውን የምናሰፍርበት ሲሆን ማታ ላይ በመገምገም የሰራነውን ካልሰራነው እንድናውቅ ከማድረግ ባለፈ ቅድሚያ የምንሰጠውን እንድንለይ ያስችላል።
- ሳምንታዊ መርሃ-ግብር፤ በዚህ ላይ ሁሉንም እቅዶቻችንን የምናሰፍር ሲሆን በሳምንት ምን ያህል ጊዜ በስራ እንዳሳለፍን ስኬትና አጠቃቀማችንን የምንመዝንበትና የምንገመግምበትም ይሆናል።
- ወርሃዊ መርሃ-ግብር የጊዜ አጠቃቀማችንን ትልቁን ምስል የምናይበት ሲሆን ከጊዜም በላይ ራስን ለመገምገም የሚረዳ ነው፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 14/2013