ቦጋለ አበበ
የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ሊካሄድ ከአራት ወር ያልበለጠ ጊዜ ቀርቶታል፡፡ በርካታ አገሮች በዚህ ታላቅ የስፖርት መድረክ ውጤታማ ለመሆንና ሰንደቅ ዓላማቸው በዓለም ሕዝብ ፊት ጎልቶ እንዲታይ ለማድረግ በራቸውን ዘግተውና ድምፃቸውን አጥፍተው ዝግጅታቸውን አጧጡፈዋል፡፡ የአትሌቲክስ ስፖርት የዘወትር ተቀናቃኞቻችን ጎረቤት አገር ኬንያና ዩጋንዳ ጭምር አትሌቶቻቸው የሚሳተፉባቸው የስፖርት አይነቶችን ስብጥር አዛምደው ለኦሊምፒክ ተሳትፎ ወገብ ታጥቀው በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ በአንፃሩ በኢትዮጵያ በኩል የሚታየው ሁኔታ ከዝግጅቱ ይልቅ፣ ስፖርቱ በሚመለከታቸው አካላት መካከል የነገሰው ትርምስና ሽኩቻ ግራ የሚያጋባ ነው፡፡
ኦሊምፒክ በአራት ዓመት አንዴ በመጣ ቁጥር በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን መካከል ውዝግቦች ሲነሱ ማየት የተለመደ ቢሆንም፣ በዚህ ወቅት የአገሪቱን ስፖርት የሚመሩት ሁለቱ ትላልቅ አካላት ተባብረው ውጤት ለማስመዝገብ ጥረት ከማድረግ ይልቅ በሆነው ባልሆነው መቆራቆዛቸው ከስፖርትም ያለፈ ትርጉም እየተሰጠው ይገኛል፡፡ የሁለቱ ተቋማት ውዝግብ ካለፉት ጥቂት ዓመታት ጀምሮ እየተካረረ የመጣ ቢሆንም፣ ሁለቱ አካላት በተለያዩ መድረኮች ልዩነቶቻቸውን የፈቱ ወይም ወደ ጎን ትተው በጋራ ለመስራት የተስማሙ ሲያስመስሉ ቆይተዋል፡፡ የአገሪቱን ትልልቅ የስፖርት ተቋማት በሚመሩ ግለሰቦች መካከል መቃቃር ሲፈጠር አዲስ አይደለም፡፡ አሁን ሁለቱ አካላት የሚሻኮቱባቸው አጀንዳዎች ግን ከዚህ ቀደሞቹ አንፃር ጠንከር ብለው መታየታቸው በኦሊምፒኩ ውጤት ላይ ተፅዕኖ እንዳያሳድር ስጋት የሚፈጥር ነው፡፡
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እጅና ጓንት ሆነው በመሥራት ለአገር ክብርና ዝና ሊተጉ በሚገባበት በዚህ ወቅት አላስፈላጊ ንትርክ በመካከላቸው ሲቀጣጠል ‹‹ተዉ›› ባይ መጥፋቱ ችግሩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ አሁን ላይ ትኩረት ቅድሚያ ለሚያስፈልገው ቶኪዮ ኦሊምፒክ ማዋል ሙያዊ ብቻ ሳይሆን፣ የዜግነት ግዴታም ነው፤ በዚህ ወቅት አስተዳደራዊ አለመግባባቶችን እያባባሱ መካረርና መቧደን የኢትዮጵያን ኦሊምፒክ ተሳትፎ እንዳይጎዳው መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ከውጪ ሆኖ የሚታዘበው ሕዝብም ‹‹ምነው ፀቡን ከኦሊምፒኩ በኋላ ቢያደርጉት›› እስከ ማለት ደርሷል፡፡
ለኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሥራ አመራር ቦርድ
ዕጩ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ በትምህርት ዝግጅት ቢያንስ የመጀመሪያ ዲግሪና ቢያንስ አንድ ዓለም አቀፍ ቋንቋ መቻል የሚለው ቅድመ ሁኔታ በአባላቱ ዘንድ ሰሞንኛው ውዝግብ ለመፈጠሩ ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የካቲት 19 ቀን 2013 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ አዱላላ ሪዞርት ባካሄደው አስቸኳይ ጉባዔ፣ በዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) ይሁንታ ያገኘውንና ከላይ የተገለጸውን ቅድመ ሁኔታ ያካተተውን መተዳደሪያ ደንብ ያለምንም ተቃውሞ አፅድቆ የነበረ ቢሆንም፣ በዚህ አጭር ጊዜ ውስጥ በቅድመ ሁኔታው አማካይነት የተፈጠረው ውዝግብ ዘርፉ በምን ዓይነት ባለሙያዎች እየተመራ እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡
በአስቸኳይ ጉባዔ ወቅት ተሳትፈው ያለምንም ተቃውሞ የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው የምርጫ ማስፈጸሚያ መመሪያውን ጨምሮ መተዳደሪያ ደንቡ እንዲፀድቅ የተስማሙ ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች፣ የክልልና ከተማ አስተዳደር የስፖርት ኮሚሽነሮች፣ አመራሮችና ሌሎችም አባላት መልሰው በትምህርት ዝግጅትና ከዓለም አቀፍ የቋንቋ ክህሎት ጋር የተያያዘው የመተዳደሪያ ደንብን መቃወማቸው ትዝብት ውስጥ የሚከት መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ስፖርቱ በምን ዓይነት ሙያተኞች እንደሚመራ አመላካች ነው፡፡ አሁን ላይ ከዚህ ቅድመ ሁኔታ ጋር የተነሳው ውዝግብ መጀመሪያውኑ በቢሾፍቱው መድረክ መቅረብ ሲገባው፣ ደንቡ በከፊል ሳይሆን በሙሉ ድምፅ ከፀደቀ በኋላ ጉዳዩ እንደገና መነሳቱ ዘርፉ እየተመራ ያለው ለግል ጥቅም እንጂ ለስፖርቱና ለአገር ጥቅም ቅድሚያ በሚያሳቡ ግለሰቦች እንዳልሆነ ማሳያ ነው፡፡
‹‹የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በጣት የሚቆጠሩ ወራት ዕድሜ በቀረበት በአሁኑ ወቅት ሽኩቻውና ክርክሩ ምክንያታዊ ነው ተብሎ ቢታመን እንኳን ጊዜው አይደለም፡፡ ምክንያቱም በኦሊምፒክ መድረክ አትሌቲክስ ማለት ለኢትዮጵያ ‹‹አንድ ዓይን ያለው በአፈር አይጫወትም›› ነውና፡፡ የኦሊምፒክ ጉዳዩ የጋራ ጉዳይ እስከሆነ ድረስ ተቀራርቦ መነጋገር ሲቻል አመራሩ ጉዳዩን ወደ አላስፈላጊ ነገር ወስዶ መነታረክ ተገቢ ሊሆን አይችልም፡፡
ስፖርቱ ውስጥ ያለው ፖለቲካ ምንም ይሁን ምን ለመነታረክ ጊዜው አሁን አይደለም፡፡ ውዝግብ በሚፈጥሩት አጀንዳዎች የቱም አካል ትክክል፣ የቱም አካል ስህተት ሊሆን ይችላል፡፡ ሁለቱ አካላት በየትኛውም ጉዳይ እስኪወጣላቸው ለመነታረክ ከኦሊምፒኩ በኋላ በቂ ጊዜ አላቸው፡፡ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ውጤት እያሽቆለቆለ መምጣቱን በማስተዋል ቢያንስ ታላቁ አትሌት አበበ ቢቂላ በነገሰባት ቶኪዮ ከተማ ዳግም ታላቅ ውጤት ለማምጣት ሽኩቻው ቀርቶ ጥረትና ተነሳሽነት ሊኖር ይገባል፡፡ ካለበለዚያ ግን ዝቅተኛ የተባለውን ያለፈው ሪዮ ኦሊምፒክ አንድ የወርቅ ሜዳሊያ እንኳን በቶኪዮ ለማሳካት ብርቅ ሊሆንብን እንደሚችል ማሰቡ ተገቢ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብና አትሌቶች በኦሊምፒክ መድረክ መገለጫቸው ወርቅ ነው፡፡ ይህ ማለት ብርና ነሐስ በኦሊምፒክ መድረክ ያላቸውን ዋጋ ማጣጣል ሳይሆን ከነበርንበት ከፍታ የመውረድና ያለመውረድ ጉዳይ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ እንዳለፉት ዓመታት የአትሌቲክስም ይሁን የኦሊምፒክ ውጤት ሲያሽቆለቁል፣ የለመድነው አረንጓዴ ጎርፍ ሲደርቅ በጋራ ከመስራት ይልቅ በጭቅጭቅ ወርቃማውን ጊዜ በከንቱ ሰውቶ ‹‹ወርቅ ማምጣት ከባድ ነው፣ በብርና በነሐሱ ተፅናኑ እነሱም ቢሆኑ ቀላል አይደሉም›› የሚል ማስተባበያ መስማት አንፈልግም፡፡ ለውጤት መጥፋት የተለመዱ ምክንያቶችን ማድመጥ ሰልችቶናል፡፡ እዚያ ደረጃ ላይ ከመድረሳችን በፊት ዛሬ ልዩነቶችን ወደ ጎን ትቶ በአንድነት ነጭ ላባቸውን እያፈሰሱ ለሚዘጋጁት ስፖርተኞች ልፋት ትንሽም ቢሆን ግድ ሊሰጠን ይገባል፡፡ ምክንያቱም የአመራሩ መከፋፈልና መነቋቆር በአትሌቶቹ ዝግጅትም ይሁን ውጤት ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ተፅዕኖ ቀላል አይደለም፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም ሕዝብ ዘንድ በበጎ የምትነሳው በኦሊምፒክና በአትሌቲክስ ውጤቷ ነው፡፡ በተለይም አገር እንደ ወቅቱ አይነት የዲፕሎማሲ ችግር ሲገጥማት የዓለም ሕዝብ ሁሉ ትኩረት የሆነው የኦሊምፒክ መድረክ ገፅታን ከመገንባት አንፃር መልካም አጋጣሚ እንደሚሆን ግልፅ ነው፡፡ ኢትዮጵያም የቶኪዮን ኦሊምፒክ ለገፅታ ግንባታ እንደ ትልቅ እድል መጠቀም ትችላለች፡፡ ይህን እድል ለመጠቀም ደግሞ በኦሊምፒኩ የሚመዘገበው ውጤት የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ምክንያቱም ዓለም የሚከተለውም ይሁን ትኩረት ሰጥቶ የሚከታተለው አሸናፊውን ነውና፡፡ አሁን በየትኛውም አካል የሚነሳ ውዝግብ የስፖርቱን ውጤት ገደል ከመክተት ባለፈ ለአገር ብዙ ትርጉም ያላቸው እድሎችን ማምከኑ አይቀርም፡፡
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴም ሆነ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አሁን ላይ የትኩረት አቅጣጫቸው ሊሆን የሚገባው፣ ዓለም በጉጉት በሚጠብቀው ታላቁ የኦሊምፒክ መድረክ አገሪቱን የሚወክሉ አትሌቶች ላይ መከራከርና መነጋገር ነው፡፡ በአንፃሩ ነገን በማያሻግር ውዝግብ መጠመድ ተገቢ እንደማይሆን ውዝግቡ ውስጥ ያሉ ግለሰቦችም ቢሆኑ አይጠፋቸውም፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 14/2013