አሥናቀ ፀጋዬ
የማዕድን ኢንዱስትሪ ለሀገር ከፍተኛ ዕድገት ሊያስመዘግቡ ከሚችሉ የምጣኔ ሐብት ዘርፎች መካከል አንዱ መሆኑ ይነገራል።የማህበራዊ አገልግሎት መሥጫ ተቋማት፣ ዘመናዊ የመኖሪያ ቤቶች፣ ትላልቅ መንገዶች፣ የፋብሪካ ግንባታዎች፣ የተለያዩ ሕንፃ ሥራዎች፣ የአየር ማረፊያዎች፣ የሃይል ማመንጫዎች፣ የመሥኖ ግድቦች፣ ዘመናዊ የእርሻ ግብዓት አቅርቦቶች ሁሉ ያለማዕድናት እውን አይሆኑም።ከዚህ አኳያም አብዛኛቹ የዓለማችን ሀገራት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥተው እየሠሩ ይገኛሉ።
በኢትዮጵያም ሠፊ የማዕድን ሐብት እንደሚገኝ በተደጋጋሚ የሚነገር ቢሆንም ጥናቶች ባለመካሄዳቸው ያለውን ሐብት በትክክል አውቆ ጥቅም ላይ ማዋል አልተቻለም።በዚህም ምክንያት የማዕድን ዘርፉ ለሀገሪቱ ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገት የሚፈለገውን ያህል አስተዋፅኦ እያበረከተ አይደለም።
የማዕድን ሐብት በሥፋት አለባቸው ከሚባሉ የአገሪቱ አካባቢዎች ውስጥ አንዱ በደቡብ ብሔር ብሄረሠቦችና ሕዝቦች ክልል የሚገኘው የጉራጌ ዞን ሲሆን፤ ልክ እንደሌሎቹ አካባቢዎች ሁሉ በዚህም ዞን ሠፋ ያለ ጥናት ባለመካሄዱ የማዕድን ሐብቱን አውቆ ጥቅም ላይ ማዋል አልተቻለም።
የጉራጌ ዞን ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ሀላፊ አቶ ፍሰሐ ዳምጠው እንደሚገልፁት በዞኑ በዋናነት ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚውሉ የኮንስትራክሽን ማዕድናት ይገኛሉ።ከኢንዱስትሪ ማዕድናት ውስጥም ፊልድ ስፓር አንዱ ነው። በጊቤ ተፋሰስ አካባቢ ባሉ ቢሽኬ፣ ኖሬ፣ እንሙርና ኢኒር እንዲሁም ከፊል ቸሃ ወረዳዎች ላይ የሚገኝ ሲሆን የድንጋይ ከሠል መኖሩም ተነግሯል፡፡
በዞኑ ምሥራቃዊ አካባቢ በተለይ በደቡብ ሶዶ ወረዳ ኬላ በሚባል ቦታ ሲልካ ሣንድ የተሠኘ ማዕድንም ይገኛል። በተመሣሣይ ኦፓልና ሌሎች የከበሩ ማዕድናትም በዚሁ አካባቢ እንዳሉ ተገምቶ ጥናቶች እየተካሄደባቸው ይገኛል። ከኮንስትራክሽን ማዕድናት ውስጥ ደግሞ አሸዋ፣ ገረጋንቲና ጥቁር ድንጋይ በዞኑ በሥፋት ይገኛል።
ሀላፊው እንደሚሉት እስካሁን ድረስ በዞኑ የማዕድን ሐብት ዙሪያ የተጠናው ጥናት በአብዛኛው በኮንስትራክሽ ማዕድናት ላይ ነው። በተለይ አምስት በሚሆኑ ወረዳዎች ላይ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚገኙ ተረጋግጧል።በሌሎች አካባቢዎች ላይ የኢንዱስትሪና የከበሩ ማዕድን ሐብቶች እንዳሉ ቢታወቅም በቂ ጥናት አልተደረገባቸውም።ወሣኝ የሆኑና የምጣኔ ሐብት ምንጭ ሊሆኑ በሚችሉ የማዕድናት ሐብት ላይ በደንብ አልተሠራም።ከዚህ አኳያም ከዲላ ዩኒቨርስቲ ጋር በመሆን ጥናት ለመጀመር መምሪያው ውል ተፈራርሟል።
ለኮንስትራክሽን ማዕድን ማውጣት ሥራ ዞኑ በሁለት መንገድ ፍቃድ ይሰጣል። በዋናነት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ በማተኮርና ከሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ ጋር በመሆን የባህላዊ ማዕድን ማምረት ፍቃድ ለወጣቶቹ ተሰጥቷቸው እንዲሠሩ፤ በሌላ በኩል ደግሞ መካከለኛ ባለሐብቶች በአነስተኛ ደረጃ ፍቃድ ተሰጥቷቸው በኮንስትራክሽን ማዕድን ማውጣት ሥራ እንዲሣተፉም ይደረጋል።
ከዞኑ ማዕድን ሐብት ጋር በተያያዘ ከሚታዩ ችግሮች ውስጥ አንዱ በዘርፉ በሚፈለገው ልክ ለወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር አለመቻል ነው። ለዚህ እንደዋና ምክንያት ሆኖ የሚጠቀሰው ቀደም ሲል በአንድና በሁለት ሰዎች ብቻ የተያዙ የማዕድን ማውጣት ፍቃዶችን በማሥለቀቅ በማህበር ለተደራጁ ወጣቶች ማሥረከብ አለመቻል ነው።
ከዚሁ ችግር ጋር በተያያዘ በዘርፉ ውስጥ ያሉ አመራሮች ቁርጠኝነት ችግርም አብሮ ይጠቀሣል።ዘርፉ በሚፈለገው ልክ ለወጣቶች የሥራ ዕድል እንዲፈጠር ከማድረግና ፍቃዶችን ከማሥተላለፍ አንፃር ውሥንነቶች ይታያሉ።አሠራሩን በመጠበቅ ወጣቶች ገንዘብ እንዲቆጥቡና ሐብት እንዲያከማቹ አድርጎና አሸጋግሮ ለሌሎች ወጣቶች የማዕድን ፍቃዶችን ያለመስጠት ችግሮችም አሉ።ይህም ችግር ሊመነጭ የቻለው ከሌሎች የቁጠባ፣ የሥራ ዕድል ፈጠራና ከሌሎች ተቋማት ጋር በቅንጅትና በትብብር መሥራት ባለመቻሉ ነው።
ሀላፊው እንደሚሉት በማዕድን ማውጣት ሥራ የተጎዱ ቦታዎችን መልሶ የማልማት ችግሮችም በዞኑ ይታያሉ። በሕግ ደረጃ በቅርቡ በተለይ በአነስተኛ ደረጃ የተሠማሩ ባለሐብቶች የመልሶ ማልማት ሥራ ለመሥራት የሚያሥችል ከትርፋቸው አምስት ከመቶ ቆጥበው ለማህበረሠብ ልማትና ለተጎዱ ቦታዎች ማልሚያ በዝግ አካውንት እንዲያስቀምጡ የሚያደርግ አሠራር ተዘርግቷል። ለዚህም መመሪያው በማዕድን ማውጫ ሥፍራዎች ላይ ጉዳት ከሚያደርሱ አነስተኛ ባለሐብቶች ጋር የጋራ መግባቢያ ሥምምነት ተፈርሟል።የጋራ ዕቅዶችም ተዘጋጅቷል።
በማዕድን ማውጣት ሥራ በተደራጁ ወጣቶች በኩል የሚታየውንና የማዕድን ማውጫ ቦታዎች የኛ ብቻ ናቸው ብሎ የመቁጠር የግንዛቤ ክፍተት ለመሙላትም የግንዛቤ ማሥጨበጫ መድረኮችን በመፍጠርና ሥልጠናዎችን በማመቻቸት ክፍተቱን ለመሙላት በመመሪያው በኩል ጥረት እየተደረገ ነው።
በዋናነት ደግሞ ይህን ሥራ በሚያስፈፅሙ ተቋማት በኩል የሚታየውን የቅንጅት ጉድለት ለማሟላት በዞኑ አስተዳዳሪ የሚመራ መድረኮች ተመቻችተዋል።በቅርቡም በጋራ በመገናኘት ከመምሪያው ሥር ያለው አቢይ ኮሚቴ አመራሩ እየመራው የቴክኒካል ኮሚቴ በማደራጀት እነዚህም ለመምሪያው ግብረ መልስ እየሰጡ የሚራበት አሠራር ተዘርግቷል።
ሀላፊው እንደሚገልፁት በጥናት አልተረጋገጠም እንጂ በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ በርካታ የከበሩ ማዕድናት እንዳሉ ይገመታል።ከዚህ አኳያም እነዚህን ማዕድናት ለማጥናት በቅርቡ ከዲላ ዩኒቨርስቲ ጋር ውል ታሥሯል።ይህም በዞኑ ያሉትን የከበሩ ማዕድናት በማውጣት በሥፋት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ተሥፋ አሣድሯል።ጥናቱን ለማጥናትም በዞን አቅም ብቻ የማይቻል በመሆኑ በዘርፉ የሠለጠኑ ባለሙያዎችና መሣሪያዎች ያሥፈልጋሉ።ለዚህም የክልሉ መንግሥት በዚህ ድጋፉን ቸሯል።ዩኒቨርስቲውም በቅርቡ ጥናቱን ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 13/2013 ዓ.ም