ተገኝ ብሩ
እንደ ማህበረሰብ ሣናውቅ የተላመድነው፤ እንደ አገር በብርቱ የፈተነን ጉዳይ ነው። ምክንያት አልባነት። በእርግጥ የበዙ አርቆ አሣቢዎች አስቆሙን እንጂ እኛ እስካሁን መመለሻ አልባ ሆነን መድረሻችን እንዳይታወቅ ሆነን በከፋን ነበር። ይህ ማህበራዊ ክፉ ልማዳችን ዛሬ በማረፊያ አምዳችን በማመልከት መፍትሄን ለመጠቆም አሰብንና ከሥሜት ርቀን ምክንያት የምንላበስበትን መድሀኒት እንፈልግ ዘንድ ለመጠቆም ብዕራችንን አነሳን።
እንደ ሕዝብ ልናወግዘው የሚገባን፤ ነገር ግን ቀስ በቀስ እየተላመድነው የመጣነው ማህበረሰባዊ ሥህተት ነው። ከምክንያት ርቆ በሥሜት መፍረድ፤ ከውይይት ተነጥሎ በክርክርና ውግዘት መጠመድ። እርግጥ አልደመድምም፤ ሌሎችም አሉ። የዚህች አገር መቆም ዋልታና ማገር የሆኑ ሩቅ አስበውና ነገን አሥልተው መልካም ነገር ላይ የሚያዘወትሩ እልፎች አሉ። እኛ ግን ከእነሱ ርቀናል ከእርነሱ በብዙ ተለይተናል።
በሥሜት የሚፈታ ችግር በግለት የሚገኝ መፍትሄ ያለ ይመስል ይህን መጥፎ ባህሪ ከእኛ ጋር እያጋባነው እንገኛለን። ምክንያትን መነሻው ያደረገ ትውልድ ቢሳሳት እንኳን ስህተቱን ለማረም ጊዜ አይፈጅበትም። በሥሜት የተለወሰ ውሣኔ በግለት የተወሠደ ርምጃ ደግሞ የሚያደርሰው ከባድ ፈተና ነው።
እንደኛ ቢሆን ተፈረካክሰን በየመንደራችን ከትመናል፤ ነገር ግን የእነሱ ሐሳብ በጎ የእነሱ መስከን መልካም ነውና ነገም እንደኛ ሣይሆን እንደነሱ እንቀጥላለን። አዎ ኢትዮዮጵያችን በብርቱና ቀና ልጆችዋ ወደፊትም ፈክታ ትቀጥላለች። ዛሬ የታመመችበት በሽታ ጊዜያዊና የሚሻር ነው። ውሎ አድሮ የሚድን፤ ከርሞ የሚከስም።
ብዙዎቻችን በሥሜት የምነፈርድ፤ በማን አለብኝነት የጀገን ሆነናል። ለችሮቻችን መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ ይበልጥ ችግር የምንደርብ፤ ውለን አድረን የሚብስብን ሆነናል። አውርቶ መግባባት ተነጋግሮ መተማመን ጠልተናል። ለእኛ የሚሆን መፍትሄ ከእኛው ከመፈለግ ይልቅ አሻግረን እናያለን። የራሣችን እንጂ የሌላውን የምንሰማበት ጆሮ ርቆናል። ታዲያ እንዴት መግባባት ይቻለን? ምክንያቱም ላለመግባባት ተግባብተናላ።
ጠዋት ላይ አንድ ጉዳይ ተነስቶ የጉዳዩ መልካምነት ይወራል። ሁሉም ተቀባብሎ የጉዳዩን ቅዱሥነት በአሉ አሉ ካንዱ ጫፍ ወዳንዱ ጫፍ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ያደርሣል። ከሰዓት ላይ ይኼው ጠዋት ቅዱሥ የተባለው ጉዳይ ወይም ግለሠብ ይረክሣል፤ ይንቋሸሻል፤ ይብጠለጠላል። ለዚህ አንድም ማሣመኛ ምክንያት ላንጠይቅ እንችላለን።
አንድን ጉዳይ ወይም ሰው ማወደስና ማንኳሰስ መነሻው ምክንያት አልባነት መሆኑ ትልቅ ማሣያ ነው። ስለሁኔታው ሣያውቁና በቂ ግንዛቤ ሣይኖር በአሉ መመራትን በተባለ መፍረድን ያስከተለው ውጤት ነው። ምክንያት አልባነት የእኛ ባህል እስኪመስል ድረስ ተላምደነዋል። ብደግ ብለን እንፈርጅና ከፍርጃው በኋላ ለምን ሥንባል ለፍርጃችን ምክንያት እናጣለን። ምክንያት ሆይ ከወዴት ተሠውረህ ይሆን? ሥሌት ጠፍቶን በሥሜት የምንነጉደው እስከመቼ ይሆን?
ምክንያታዊነት የሚመነዘር ትርፍ አለው። ሥሜት ደግሞ የማይለካ ኪሣራ፣ የማይቆጠር ውድመት አድርሽ ሥሜት ነው። ምክንያታዊ አስተሳሰብ የተላበሰ ትውልድ እያንዳንዱን ተግባርና ሀላፊነቱን በሚያስጠይቅ መልኩ ይወጣል። ከምክንያቱ በራቀና ሥሜትን በተከተለ መልኩ ደግሞ ተግባራትን ሲፈፅም አሊያም በሥሜት ሲወስን ከሀላፊነት በራቀ መልኩ ውድመቱ ከፍ ይላል። ለዚህም ነው ይኼን ማከም ይገባል፤ መታረምም ያለበት ክፉ ልማዳችን ነው የምንለው።
የሀገር ሐብት በብዙ መልክ ይለካል። በዜጎች አዕምሮ የሚለካ አምራችና በጥሩ መንፈሥ የተገነባ አመለካከቱና አተያዩ ቀና የሆነ ማህበረሰብ ግን ከሐብቶች ሁሉ ከፍ ያለ ሐብት ያለው ነው። በተቃናና ምክንያትዊ በሆነ አመለካከት የተዛነፈው ይቀናል፤ የተወላገደው ይስተካከላል።
ምክንያታዊ ትውልድ ለአገሩና ለወገኑ ቀናይ ነው። ሥሜትን የተላበሰና የማያሠላ ትውልድ ግን የእለቱን እንጂ የነገን አይመለከትም፤ የዛሬን እንጂ ነግ ምን ይሆናል የሚለው ትዝ አይለውም። ለዚህም ነው ለዚህ በሽታችን የሚሆን መድሀኒት እንፈልግ የምንለው። ለእንደኛ ዓይነት ታዳጊና ከዓለም በብዙ ርቆ የሚገኝ አገር ደግሞ ያላት ትልቅ ሐብት ዜጋ ነው።
በእያዳንዳችን ውስጥ የሚወድቀው አገር የመለወጥ ሀላፊነትና ህብረተሰብን የማገልገል ቀና ልቦና መነሻው ምክንያታዊ አስተሳሰብ ነው። ዜጎች በተቃና አመለካከት ከተገነቡ ደግሞ የአገር ግንባታና ብልፅግና ይቀርባል። እንደ ማህበረሰብ የተጋባብን በሥሜት መፍረድና ከምክንያት መራቅ ደግሞ መጪው ዘመናችንን አሥጊ ያደርገዋል። ምክንያቱም በሥሜት የሚፈጠር ችግር እንጂ የሚገነባ አገርና የሚለወጥ ህብረተሰብ ሊኖር አይችልም።
አንድ ወገን ወይም አካል መነሻና መድረሻው ያልታወቀ ታይቶና ተመርምሮም የማይጥም ሐሳብ ይዞ መሆን አለበት ብሎ ይነሣል። ለምን ነው የሚሆነው? እንዴትስ ይሁን? ተብሎ ሲጠየቅ የሚያስቀድመው ምክንያት ሣይሆን ሥሜት ነውና መሆኑን እንጂ ለምንና እንዴት መሆን እንዳለበት አይገደውም። የሚሆንበት እንጂ መሆን እንደሌለበት ማሠቢያ ጊዜ የለውም። አንድ ነገር የግድ እኔ ስለፈለኩት መሆን አለበት እንዴት ሊባል ይችላል ጎበዝ። በሥክነት ውስጥ ካልሆነ እንዴት በግለት ጉዳይ ይገደላል።
ሥሜታዊነት በገነነበት ምክንያት በጠፋበት እለት አቋም ያለው ይረገማል። ሐሳቡ ገዢ አመለካከቱና አተያዩ ትክክል ይሁን አይሁን አይመረመርም፤ ብቻ ስለምን እኛን ይቃወማል፤ ለምንስ ከኛ በተለየ ይቆማል ነው ጉዳዩ። ጭራሽ ለምን ተለየህ ተብሎ ሐሳቡ ሣይሆን የሐሳቡ ባለቤት ይዘመትበታል። የያዘውን ሐሳብ አቅርቦ ምን አልባትም ትክክለኛው የሱ መሆኑ እየታወቀም እንኳን በቃ ምንም ቢሆን የእሱ አይሆንም ተብሎ ይዘመትበታል። ይጥላላል፤ ይወገዛልም።
የግለሰቡ ትክክለኛነት አይጤንም፣ ምክንያቱም ዳኝነቱ የሚሰጠው በሥሜት እንጂ በምክንያት አይደለም። ለዚህ ነው መልካም አስተሳሰቦችን መመርመር፣ ጥሩ ልምዶችን መላመድ ያለብን። በሀገር ግንባታ ሂደት ወሣኙ እና ቀዳሚው ተግባርም ይኼ ነው። የበለፀገ እና ምክንያታዊ አስተሳሰብ የተላበሠ አዕምሮ አገርን ወደ ብልፅግና ማቃረብ ወደ ዕድገትዋ የምታደርገው ጉዞ ፈጣን እንዲሆን ማድረግ አይከብደውም።
ኢትዮጵያ ለኢትዮጵያዊያን ምቹ ትሆን ዘንድ ዜጎች ለአገራቸው ያላቸውን ፍቅርና ክብር በተግባር ያሣዩ ዘንድ ኢትዮጵያ በምክንያት የተገኘች ተሥባና ተጠብቃ የቆየች በምክንያት የምትቀጥል መሆኗን መገንዘብ ይገባል። በምክንያታዊነት የሚያምን ትውልድ ሁሌም ቀዳሚ ነው። አበቃሁ ቸር ይግጠመን።
አዲስ ዘመን መጋቢት 12/2013