አትሌቲክሱን ፈር የማስያዣ ጊዜው አሁን ነው

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራሮችና የስራ አስፈፃሚ አባላት የስልጣን ዘመን ሊጠናቀቅ አንድ ወር ብቻ ቀርቶታል፤ ፕሬዚዳንቷ ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ በህጉ መሰረት ለሶስተኛ ጊዜ መወዳደር አትችልም፤ የስራ አስፈፃሚ አባላትም የአራት አመት ስልጣናቸው ታህሳስ መጀመሪያ ላይ ያበቃል ተብሎ ይጠበቃል። ይህንንም ተከትሎ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ በመጪው ታህሳስ በስካይ ላይት ሆቴል ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል። የሚካሄደው ጠቅላላ ጉባኤና ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ከወዲሁ ትኩረት ስቧል።

የአትሌቲክሱን ህመም ተረድቶ ችግሩን በእውቀትና በስርዓት ሊቀርፍ የሚችል መሪና ስራ አስፈፃሚ ማን ሊሆን ይችላል? የሚለውም ጉዳይ አጓጊ ነው። ከወዲሁ እየታዩ የሚገኙ ውዝግቦችም አሳሳቢ ናቸው። ፌዴሬሽኑ ከሳምንት በፊት በዝግ ባደረገው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ከምርጫ ህግና ደንብ ጋር የተነሱ ጉዳዮች ጥያቄ ከመጫራቸው በተጨማሪ የሌላ ውዝግብ ምክንያት እንዳይሆኑ የስፖርት ቤተሰቡ ዘንድ ስጋት አሳድሯል።

በዋናነት ፌዴሬሽኑ በፅህፈት ቤት ኃላፊው ስም ተፈርሞ ለአስራ ሁለት ክልሎችና ለሁለት ከተሞች አስተዳደር ፌዴሬሽኖች በላከው ሦስት ገፅ ደብዳቤ ላይ ከፍተኛ ውዝግብን የሚፈጥሩ፣ የሀገሪቱን ስፖርቶች በበላይነት የሚመራው የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አሻሽሎ ካወጣው መመሪያ ጋር የሚጋጭ መስፈርት አውጥቷል የሚሉ ቅሬታዎች ተሰምተዋል።

“ማንኛውም የፕሬዚዳንትና የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆኖ በዕጩነት የሚቀርብ የሚከተሉትን መስፈርቶችና መመዘኛዎች ማሟላት ይኖርበታል” በሚለው ርዕስ ስር ንዑስ አንቀፅ “በ”ላይ “ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሰው በፕሬዚዳንትነት፣በተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንትነት፣ በምክትል ፕሬዚዳንትነትና በአቃቢ ነዋናይነት(በገንዘብ ያዥነት)ሊመረጥ አይችልም በሚል የተላለፈው መመሪያ የትውልደ ኢትዮጵያውያንን መብት የሚጋፋ የምርጫ መስፈርት በመሆኑ ሌላ ውዝግብ እንዳይፈጥርም ተሠግቷል።

“የስራ ዘመኑን የጨረሰ ስራ አስፈፃሚ በምርጫው መወዳደር አይችልም” የሚለው መመሪያም ሀገርን እንዳናገለግል የሚያደርግ ህገ-መንግሥታዊ መብትንም የሚጋፋ ነው በማለት ብዙዎች ተቃውመውታል። ሀገር አቀፍ የስፖርት ማህበራት ስለሚቋቋሙበት ሁኔታ ተሻሽሎ ከወጣው መመሪያ ቁጥር 907/2014 ጋር ተመሳክሮ የወጣ ነው? የሚል ቁልፍ ጥያቄ እንዲመዘዝም አድርጓል።

ከላይ በተጠቀሠው መሠረት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አሻሽሎ ባወጣው መመሪያ ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በተመለከተ አንቀፅ 46 ንዑስ አንቀፅ 2 ላይ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ከፕሬዚዳንትነትና ከምክትል ፕሬዚዳንትነት ውጪ በሌሎች የመመረጥና ሀገራቸውን የማገልገል መብት እንዳላቸው በግልፅ እያስቀመጠ ፌዴሬሽኑ እነማንን ከምርጫው ውጪ ለማድረግ አስቦ ይሄንን መስፈርትና መመዘኛዎችን ያወጣው? ለምንስ በህገ-መንግሥቱና በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተሻሽሎ በወጣው መመሪያ የተሠጣቸውን ሀገራቸውን በሙያቸውና በዕውቀታቸው የማገልገል መብት ለመንፈግ ፈለገ? የሚል ጥያቄ እንዲነሳበት እያደረገው ነው።

በሌላ በኩል ፌዴሬሽኑ በላከው ደብዳቤ ገፅ 2 በሦስተኛው አንቀፅ “ለመመረጥ የማያበቁ ሁኔታዎች” በሚል ንዑስ ርዕስ በተራ ቁጥር 4 ላይ “በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በፕሬዚዳንትነትና በስራ አስፈፃሚ ኮሚቴነት አገልግሎ የስራ ዘመኑን ያጠናቀቀ” አይመረጥም የሚለው አንቀፅ በተመሳሳይ ተቃውሞ እየገጠመው ነው።

የፌዴሬሽኑ የማህበራት ማደራጃም ሆነ ተሻሽሎ የወጣው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መመሪያ ቁጥር 907/2014 ላይ አንድ ሰው ሁለት የስልጣን ዘመን(ተርም)ብቻ ማገልገል እንደሚችል በግልፅ እየደነገገ፣ አንድ ተርም ያገለገሉትን ከውድድር ውጪ የሚያደርግ ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መመሪያ ጋር የሚጋጭ መስፈርት ማውጣቱ ብዙዎች ጣታቸውን ወደ ፌዴሬሽኑ እንዲቀስሩ ከማድረጉም በላይ ለማንሳት እንደተሞከረው ይሄንን የምርጫና የዕጩ መምረጫ መስፈርት የላከው እንደ ስራ አስፈፃሚ በጋራ መክሮበት ነው?

ሀገር አቀፍ የስፖርት ማህበራት ስለሚቋቋሙበት ሁኔታ ተሻሽሎ ከወጣው መመሪያ ቁጥር 907/2014 ጋር ተመሳክሮ የወጣ ነው? የሚል ምክንያታዊ ጥያቄን ደጋግመው እንዲያነሱ እያስገደደ ነው። አትሌቲክሱን ለመታደግ ከላይ የተነሱት ጥያቄዎች ከምርጫው በፊት መልክ መያዝ አለባቸው። የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እነዚህን ነቅሰን ያወጣናቸውንና ለውዝግብ የሚዳርጉ መስፈርቶችና መመዘኛዎች ላይ በፍጥነት እርምት በማድረግ ምርጫውና የምርጫው ሂደት ፍትሃዊና ከውዝግብ የፀዳ ሊያደርግ ይገባል።

በእግር ኳሱ ምርጫ ላይ ተደጋግሞ ይታይ የነበረውን የምረጡኝ ዘመቻን ብዙ ጊዜ በርካታ ሰዎች በማይወዳደሩበት አትሌቲክስ ለመከሰት አትሌት ስለሺ ስህን ፣ አትሌት ገ/እግዚአብሄር ገ/ማርያም ፣ አትሌት መሰረት ደፋር ፣ አትሌት አሰፋ መዝገቡ፣ አቶ ጌታ ዘሩና አቶ ቢኒያም ምሩጽ የረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ የስልጣን በትርን ለመረከብና የኢትዮጵያ ኩራት የሆነውን አትሌቲክስን ለመምራት ትልቅ ፍጥጫ ላይ መሆናቸው ተሰምቷል። አንዳንድ መረጃዎች ቁጥራቸው ከዚህም ሊጨምር እንደሚችል ይገልጻሉ። የሚመረጠው ሰው ማንም ይሁን ማን ስፖርቱን የሚጠቅም ሰው መሆን አለበት። አትሌቲክሱን ወደ ትክክለኛው መንገድ የሚመራው ሰው የሚሻበት ወቅት ላይ ይገኛልና።

ኢትዮጵያ የሚለው ታላቅ ስም ይበልጥ ጎልቶ የሚታይበትን፣ ባንዲራችን ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ የሚያደርገውን የአትሌቲክሱ ወንበር ላይ ይቀመጥ ይሆን? እነማንስ ይሄንን ውጤት ለማስጠበቅና ወደ ተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር በስራ አስፈፃሚነት ይመጡ ይሆን? የዚህን መልስ ለማወቅ እስከ ታህሳስ 13 መጠበቅ ግድ ይላል።

የሚመረጠው ፕሬዚዳንትም ይሁን ስራ አስፈፃሚ አባላቶቹ ቀላል ስራ እንደማይጠብቃቸው አውቀው ኃላፊነት የሚረከቡና የሚወጡ መሆን አለባቸው። ፈተናቸው ቀላል አይሆንም። ብንታደልና ቢሳካልን ኖሮ አስፈላጊውን ፕሮግራም በመዘርጋት ከታዳጊነት ጊዜያቸው ጀምሮ ተሰጥኦ (Talent) ያላቸውን አትሌቶች በመመልመልና ከታች ጀምሮ ፕሮፋይላቸውን ተከታትሎ በማሳደግ ለዓለም አቀፉ ውድድር ማድረስ የስፖርት ማህበራት ወግ ነበር። ይህን ማድረግ አልተቻለም።

ይባስ ብሎ የኢትዮጵያ ወጣቶች የስፖርት አካዳሚ ከፍተኛ ሀብት አፍስሶ ያሰለጠናቸውንና ለውጤት ያበቃቸውን አትሌቶች እንኳን ተቀብሎ በአግባቡ ወደ ቀጣዩ ምዕራፍ ማሸጋገር ዳገት ሆኖብናል። የሚመጣው አዲስ የአትሌቲክስ አመራር የመጀመሪያ የቤት ስራው መሆን ያለበትም ይህን ጉዳይ ፈር ማስያዝ ነው።

ይህም ካልሆነ እንኳን ምንም ሳናግዛቸው በግላቸው በየጫካውና በየተራራው ወጥተውና ወርደው የተሻለ ደረጃ ላይ የደረሱ አትሌቶችን ወደ ዓለም አቀፍ መድረክ ይዘን ለመሄድ ግልፅ እና ሁሉንም አትሌቶች በእኩል ደረጃ የሚዳኝ ከሁሉም በላይ ደግሞ ወቅታዊ ብቃት ያላቸውን አትሌቶች ለይቶ ለማውጣት የሚያስችል ወጥና ቋሚ መስፈርት ማዘጋጀትና በቁርጠኝነት መተግበርን የግድ የሚያደርግ መሪ መሆን አለበት። ቀደም ሲል ይህ አልሆንልን ብሎ ወይም ትኩረት ሳንሰጠው ቀርተን በተድበሰበሰ መንገድ መጓዛችን ለተዘበራረቀ አካሄድ ዳርጎን አንዱን ስናነሳና ሌላውን ስንጥል ስፖርቱ ወደ ትርምስ እንዲገባ ማድረጉን መዘንጋት የለብንም።

አንዳንድ ጊዜ ባለን የስራ አጋጣሚ ከኢንተርኔት በሚወሰድ መረጃ ብቻ በአካል የማይታወቅ አትሌት የብሄራዊ ቡድን አባል ሆኖ ሲካተት እንመለከታለን። ይህ በፍፁም ሳይንሳዊ አይደለም። ከዚህም በባሰ መንገድ ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ ዓለም አቀፍ ሚኒማ ማሟላት የሚያስችላትን ስርዓት አልዘረጋችም። በርካታ አትሌቶችን ተሸክማ ለሚኒማ ወደ ሌሎች የአውሮፓ ሀገሮች ትዞራለች። ኬንያ ይህን ማድረግ ችላለች። የተሻለ ወቅታዊ ብቃት ያላቸውን አትሌቶች መምረጥ የሚያስችላትን ውድድር በሀገር ውስጥ ታካሂዳለች። እኛ ግን ከዚህ ሁኔታ ለመውጣት ፍላጎት እንኳን ሳይኖረን ቆይተናልና አዲሱ አመራር ይህንንም ጉዳይ ኮስተር ብሎ ሊመለከተው ይገባል።

በፍፁም ከሳይንስ ጋር የማይተዋወቅና ዘመኑን የማይመጥን የአሰለጣጠን ዘዴን መከተላችን ሌላው ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ነው። ለዚህ ማሳያው ደግሞ አትሌቶቻችን በታላቁ የኦሊምፒክ መድረክ ፓሪስ ላይ ያሳዩት የአሯሯጥ ቴክኒክና ታክቲክ እንዲሁም የብቃት ደረጃ ነው። አሁንም አሰለጣጠናችን ሰዓት ይዞ ብቻ ደርሰህ ተመለስ አይነት ብቻ ሆኖ እንዳይቀጥል ዘመኑን የዋጀ ስርዓት የሚዘረጋ መሪ ያስፈልገዋልና ይታሰብበት። ወቅቱን የሚመጥንና ወደ ሳይንሱ የሚያስጠጋን ስር-ነቀል ለውጥ/Transformation/ ያስፈልገናል።

የቶኪዮው የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ሊካሄድ ወራቶች በቀሩበት በአሁኑ ወቅት የሚመረጠው ፕሬዚዳንት ስፖርቱን የማረጋጋት፣ የአትሌቶችን ስነ-ልቦና የሚደግፍ ስራ መስራት ፣ ብሄራዊ ቡድኑን ዳግም መመስረትና የማናጀሮችን እጅ መመለስ፣ ከምንም በላይ በየትኛውም አቅጣጫ የማይጎተት ለአንድ አላማ የቆመ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ውህደት በመፍጠር አትሌቲክሱን ከዘርና ከሃይማኖት ልዩነት ማጽዳት የሚጠበቅበትም ይሆናል።

ባለፉት አራት አመታት ፌዴሬሽኑን የመራችው ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ያሸነፈችውን ምርጫ ጨምሮ ወደ ኋላ የተካሄዱት ምርጫዎች ውድድር ያልነበረባቸውና ከጀርባ ባሉ አካሄዶች የሚጠናቀቁ ምርጫዎች እንደነበሩ ይታወቃል። የዘንድሮ ግን የምረጡኝ ግብግቦች የሚታዩበት ከመጋረጃ ጀርባ ምክክሮች የሚኖሩባቸው ይሆናሉ የሚል ስጋት አለ። የፖለቲካ አመራሮች፣ ባለሀብቶች ፣ ታዋቂ ሰዎች ተጽዕኖ ፈጠሪዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ እጃቸውን የሚያስገቡበት እንዳይሆን መጠንቀቅ ተገቢ ነው።

በፓሪስ ኦሊምፒክ የተገኘውን ደካማ ውጤት ተከትሎ እንደ ዋና ችግር ከታዩት ምክንያቶች መሃል ዋናው የብሄራዊ ቡድን መፍረስ ሲሆን፤ ይህን የማስተካከልና ቡድኑን ዳግም የመመለስ የማናጀሮች አሰልጣኞችና የአትሌቶች ባሎች ከፍተኛ ጫና የሚወገድበት ሁኔታን የመፍጠርና አትሌቲክሱን የማዳን ትልቅ ኃይል የሚይዝ ፕሬዚዳንትና ስራ አስፈጻሚ የሚመረጥበት እንዲሆን የመምረጫ ካርዱን የያዙ ተወካዮች ትልቅ ሀገራዊ ኃላፊነት እንደሚሆን የብዙዎችም እምነት ሆኗል።

አትሌቲክሱን የሚመሩ ሰዎችን በተመለከተ ስህተቱ የሚፈፀመው ምርጫው ላይ አይደለም። ችግሩ የሚጀምረው ስፖርቱን እንዲመሩ ከክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች ወዘተ ተወክለው ከሚመጡ ሰዎች ነው የሚጀምረው። ይህን ባለፉት በርካታ ዓመታት ምርጫዎች ላይ ታዝበናል። ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ስፖርቱን በፕሬዚዳንትነት ወይም በስራ አስፈፃሚ አባልነት እንዲያገለግሉ ወደ ምርጫ የሚልኳቸው አብዛኞቹ ሰዎች ማለት ይቻላል ከአትሌቲክሱ ጋር ምንም ግንኙነትና እውቀት የሌላቸው ናቸው። ብዙዎቹ ወይም የፖለቲካ ሹመኞች ወይም ቀደም ሲል ስፖርቱ ምን እንደሚፈልግ አቅሙ የሌላቸው ናቸው። ይህ እንደ አይናችን ለምናየው አትሌቲክስ ትልቅ ጉዳት ነው። ስፖርቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ውዝግቦች የሚናጠውም አንዱ ምክንያት ይህ ነው።

ስፖርቱን በመሪነት ለማገልገል ተወክለው ወደ ምርጫ የሚመጡ ሰዎች የግዴታ ስፖርተኛ ወይም ከዚህ ቀደም በስፖርት ያለፉ ይሁኑ ማለት አይደለም። ቢያንስ ስፖርቱ ምን ይፈልጋል፣ አሁን የተሳሳተው ነገር ወይም የስፖርቱ ችግር ምንድነው? የሚለውን ጉዳይ አውቀውና ተረድተው የማስተካከል አቅም እንዲሁም የመምራት ችሎታ ያላቸው ሊሆኑ ይገባል። ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የሚልኳቸው ተወካዮች እንዲህ አይነት ሰዎች መሆናቸውን የማረጋገጥ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ሊያውቁ ይገባል።

ስፖርቱን ለመምራት ተወክለው የሚመጡ ሰዎች ጋር ብቻ ግን አይደለም ችግር ያለው። በምርጫ ወቅት ድምፅ እንዲሰጡ ከክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና የተለያዩ ስፖርት ተቋማት የሚወከሉ ግለሰቦች ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው። ድምፅ የሚሰጡት ሰው ስፖርቱን ለማገልገል ተገቢ መሆኑን የማረጋገጥ አደራ እንዳለባቸው ማስታወስ ተገቢ ነው። ምርጫዎች ላይ ድምፆች እንደሚገዙና እንደሚሸጡ ለስፖርት ቤተሰቡ የተሸሸገ ጉዳይ አለመሆኑን ማደባበስ አያስፈልግም።

ስለዚህ ድምፅ ለመስጠት ተወክለው የሚመጡ ሰዎች በተቻለ መጠን በዚህ አይነት ቅሌት የሚታሙ አለመሆናቸውን ወካዮቻቸው ሊያጤኑ ይገባል። ለክልል ፌዴሬሽኖች ስልክ እየተደወለ ‹‹እከሌን እንዳትልኩ፣ እነ እከሌን ላኩ፣ እከሌ እኛ በህይወት እያለን መግባት የለበትም›› የሚሉ ለአትሌቲክሱ የማይበጁ ሽኩቻዎች እየተሰሙ መሆኑ ብዙዎችን በምርጫው ገና በጠዋቱ ተስፋ እንዳያስቆርጥ መታረም አለበት፡፡

ልዑል ከካምቦሎጆ

አዲስ ዘመን ኅዳር 16 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You