ታምራት ተስፋዬ
ኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለማሟላትና የኤሌክትሪክ አቅርቦትን ለማሻሻል ብሎም ሙሉ ለሙሉ ተደራሽ ለማድረግ የኃይል መሰረተ ልማቶችን በተለይም የአዳዲስ የማከፋፈያ ጣቢያዎችና ማስተላለፊያ መስመሮች በመገንባት ላይ ትገኛለች፡፡
የጊንጪ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ከእነዚህ ግንባታዎች መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡ እኛም ዛሬ በይፋ ስለሚመረቀው ጣቢያ አጠቃላይ መረጃ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ጠይቀናል፡፡
በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ከፍተኛ የኃይል ተሸካሚ መስመሮች እየተዘረጉና የሃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች እየተገነቡ ናቸው፡፡ በተለይ የሃይል ፍላጎታቸው ከፍተኛ የሆነ፣ የሃይል መቆረረጥ የሚያጋጥማቸው አካባቢዎች ላይ ትኩረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ የኢንዱስትሪ መስፋፋትን ተከትሎ ሃይል የሚፈልጉ በመሆኑ እነሱን ታሳቢ ያደረጉ ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን አቶ ሞገስ ነግረውናል ፡፡
የጊንጪ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ከእነዚህ ግንባታዎች መካከል ተጠቃሽ ነው፡፡ ለጊንጪ ከተማና ለአካባቢው ኃይል በአስተማማኝ ሁኔታ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችለው የጊንጪ ባለ 230/15 ኪሎ ቪልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የተጀመረው ነሐሴ ወር በ2008 ዓ.ም ነው፡፡ ግንባታውም ባሳለፍነው ዓመት ሐምሌ ወር ተጠናቋል፡፡
የማከፋፈያ ጣቢያው ከአዲስ አበባ በ83 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን በጊንጪ ከተማ የሚገኝ ነው ፡፡ ጣቢያው ሁለት ባለ 50 ሜጋ ቮልት አምፒር ትራንስፎርመሮች ተገጥመውለታል። እነዚህ ትራንስፈርመሮች እስከ 100 ሜጋ ዋት የመሸከም አቅም አላቸው፡፡
አቶ ሞገስ እንዳሉት፤ የፕሮጀክት ግንባታ በአጠቃላይ 8 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር ወጥቶበታል፡፡ ግንባታው ላርሰን ኤንድ ቱርቦ የተባለ የህንድ ኩባንያ ሲያከናውን ኤም ቪ ቪ ዲከን የተባለ የጀርመን እና ስዊዘርላንድ ኩባንያ ደግሞ የማማከር ሥራውን አከናውነዋል፡፡
ወደ ማከፋፈያ ጣቢያው የሚገባው ኃይል የተሳበው ከገፈርሳ ወደ ጌዲዮ ከተዘረጋው ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ላይ ነው፡፡ ጣቢያው ሁለት ጥንድ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ገቢ እና 10 ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች አሉት፡፡
እነዚህ ወጪ መስመሮችም ለጊንጪ ከተማ እና አካባቢው አስተማማኝ ሃይል የሚያስችሉ መሆናቸውን ያመላከቱት አቶ ሞገስ፣ በአሁን ወቅት ላሉትም ሆነ ወደ ፊት በአካባቢው ለመገንባት የታቀዱት አነስተኛም ሆነ ከፍተኛ ፕሮጀክቶች ብሎም ፋብሪካዎች የሃይል ፍላጎት ለማሟላት እንደሚያግዝ ነው ያብራሩት:: ‹‹በተለይም በቅርቡ ተግባራዊ የሚሆነው የወንጪ ልማት ፕሮጀክት ኤሌክትሪክ የሚያገኘው ከዚህ የሃይል ማከፋፋያ ጣቢያ ነው›› ብለዋል፡፡
‹‹እነዚህ የሃይል ማስተላላፊያ መስመሮችም ሆነ የማከፋፈያ ጣቢያዎች በመንግሥት ይገንቡ እንጂ ታሳቢም ሆነ ተጠቃሚ የሚያደርጉት የአገሪቱን ህዝብ ነው›› ያሉት አቶ ሞገስ፣ ህብረተሰቡ የተገነቡ የኤሌትሪክ ሃይል መሰረተ ልማቶችን እንደራሱ ሀብት ሊጠብቃቸው እንደሚገባ ያስረዳሉ፡፡
መንግሥትም ሆነ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል በእያንዳንዱ የገጠር ቀበሌ ሳይቀር የተዘረጉ የከፍተኛ ሃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን ሰው አቁሞ መጠበቅ እንደማይቻል ይናገራሉ። በመሆኑም ህብረተሰቡ ከፍተኛ ገንዘብ ወጪ ተደርጎባቸው የሚገነቡ የኤሌትሪክ ሃይል መሰረተ ልማቶች ላይ ዝርፊያ እንዳይፈፀም መከላከል እና ዝርፊያ የሚፈፅሙ ሲገኙም ለሕግ አካል መውሰድ እንዳለባቸው ነው አፅንኦት ሰጥተወ የተናገሩት፡፡
መረጃዎች እንደሚያመልክቱት በተሻሻለው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 381/2008 የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መስሪያ ቤትን ለማቋቋም በወጣው ደንብ መሠረት ተቋሙ የኃይል ማመንጫዎችን፣ የኃይል ማስተላለፊያዎችንና የኃይል ማከፋፈያዎችን የመገንባት፣ የጅምላ ሽያጭ፣ የተስማሚነት ጥናት፣ የዲዛይንና የቅየሳ ሥራ የማከናወን ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ተቋሙ ከ18 በላይ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን በማስተዳደር ላይ ይገኛል፡፡ ከነዚህም መካከል 14 ያህሉ ከውሃ ሲሆኑ እነሱም አባ ሳሙኤል (6.6 ሜ.ዋ)፤ ጊቤ 3 (1870 ሜ.ዋ)፤ በለስ (460 ሜ.ዋ)፤ ግልገል ጊቤ 2 (420 ሜ.ዋ)፣ ተከዜ (300 ሜ.ዋ)፣ ግልገል ጊቤ 1 (184 ሜ.ዋ)፣ መልካ ዋከና (153 ሜ.ዋ)፣ ፊንጫ (134 ሜ.ዋ)፣ አመርቲ ነሺ (95 ሜ.ዋ)፣ ጢስ ዓባይ (73 ሜ.ዋ)፣ ቆቃ (43.2 ሜ.ዋ)፣ አዋሽ 2 (32 ሜ.ዋ)፣ አዋሽ 3 (32 ሜ.ዋ)፣ ጢስ ዓባይ 1 ሜ.ዋ)፣ (14.4 ሜ.ዋ) በድምሩ ከውሃ 3814 ሜጋ ዋት ያመነጫል፡፡ ከንፋስ ደግሞ አዳማ 2 (153 ሜ.ዋ) እና አዳማ 1 (120 ሜ.ዋ) በድምሩ 324 ሜጋ ዋት በማመንጨት ላይ ሲሆን ቀሪው 104 ሜጋ ዋት ከአሉቶ ጂኦተርማልና ከዲዝል የሚመነጭ ነው፡፡
ኃይል ከማመንጨት ባሻገር የመነጨውን የኤሌክትሪክ ኃይል ወደ ብሔራዊ የኃይል ቋት ለማስተላለፍ የሚረዱ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያና ማከፋፈያ ጣቢዎች በመላ አገሪቱ ተገንብተዋል:: በአሁኑ ጊዜ ከ132 እስከ 500 ኪ.ቮ አቅም ያላቸው ከ19 ሺህ ኪ.ሜ በላይ የከፍተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ማከናወን ተችሏል፡፡ ከነዚህም መካከል ባለ 500 ኪ.ቮ የህዳሴ-ዴዴሳ-ሆለታ፤ ባለ 400 ኪ.ቮ የወላይታ ሶዶ II-አዲስ አበባ፤ ባለ 230 ኪ.ቮ የቆቃ-ሁርሶ-ድሬዳዋ፤ ባለ 230 ኪ.ቮ ሃላባ-ሆሳዕና-ግልገል ጊቤ 2-ጂማ-አጋሮ-በደሌ እና ባለ 230 ኪ.ቮ መቱ-ጋምቤላ ይገኙበታል፡፡
በተጨማሪም 199 የተለያዩ የቮልቴጅ መጠን ያላቸው የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ ሥራዎች ተጠናቀው አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ ሲሆን ባለ 500 ኪ.ቮ የዴዴሳና ሆለታ፣ ባለ 400 ኪ.ቮ የጊቤ 3፣ ባለ 230 ኪ.ቮ የሁርሶ፣ ጋምቤላ እና የመሆኒ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 11/2013