መላኩ ኤሮሴ
ኃይል ለአንድ ሀገር ከሚያስፈልጉ ቁልፍ መሰረተ ልማቶች ውስጥ አንዱ ነው:: በተለይም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ታዳጊ አገራት አስተማማኝና ተመጣጣኝ የኃይል አቅርቦት ወሳኝ ነው:: በታዳጊ አገራት የኤሌክትሪክ ኃይል ለሰው ልጆች ህይወት መሻሻል አልፎ ተርፎም ህይወትን ሊያድን ይችላል:: በታዳጊ አገራት አስተማማኝ የኃይል ምንጭ መኖር ኢንዱስትሪ፣ ዘመናዊ ግብርናን፣ ህክምናን፣ ንግድን ጨምሮ እንዲሁም የተሻሻለ ትራንስፖርት ሥርዓትን ለማሳለጥ ወሳኝ ነው::
ኢትዮጵያ በታዳሽ የኃይል ምንጮች የታደለች መሆኗ በጥናቶች የተረጋገጠ ቢሆንም፤
ኢንተርናሽናል ፋይናንስ ኮርፖሬሽን የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ያወጠው መረጃ እንደሚያመላክተው፤ በሀገሪቱ ፀሐይ በምትጠልቅበት ጊዜ ከ10 ዜጎች መካከል ስምንቱ እንደ ምግብ ማብሰል ወይም ማጥናት ላሉት መሠረታዊ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች ጤናማ ያልሆኑ የብርሃን ምንጮች ለመጠቀም ይገደዳሉ::
እነዚህ የብርሃን ምንጮች በኬሮሲን የሚሰሩ ኩራዞች፣ የእንጨት እሳት እንዲሁ አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች በቀላሉ የማያገኙትን በድንጋይ የሚሰሩ የብርሃን ምንጮችን ያካትታሉ::
ኢትዮጵያ የዜጎቿን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት ብሎም ኢኮኖሚዋን ለማነቃቃት የተለያዩ ጥረቶችን ስታደርግ ቆይታለች:: ይሁን እንጂ ከተለያዩ የኃይል ምንጮች የሚመረተው የኃይል መጠን 5 ሺህ እንኳ አልደረሰም:: ዛሬም በርካቶች ከሀገራዊ የኃይል ሥርዓት ውጭ ናቸው:: እራትን በኤሌክትሪክ መብራት መብላት የቻሉትም 65 ከመቶ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። ቀሪው በባህላዊ መንገድ ብርሃን የሚያይ ካልሆነም ጨለማን በእንቅልፍ የሚያሳልፍ ነው።
ለዚህም ነው በኢትዮጵያ የኃይል አቅርቦት እና አማራጭ የኃይል ምንጭ ትኩረት የተሰጠው። ዛሬ ላይ የሀገሪቱ የኃይል ፍላጎት በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ ቢሆንም በዚያው ልክ የኃይል ፍላጎትን ለማሟላት የተደረጉ ጥረቶች የሚፈለገውን ያህል ውጤት አላስገኙም:: እየጨመረ የመጣውን የኃይል ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ እና የሚሰጠውን አገልግሎት ቀልጣፋ ለማድረግ የ10 ዓመታት ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል::
ፍኖተ ካርታው አቅምን ያገናዘበ ፍትሐዊ የኤሌክትሪክ ተጠቃሚነትና ተደራሽነትን ማረጋገጥ፣ የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ማሻሻል እንዲሁም አጠቃላይ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገትን ማፋጠን የሚያስችሉ አላማዎችን የያዘ ነው።
በ10 ዓመት ፍኖተ ካርታ መሰረት ሀገሪቱ የኃይል ፍላጎቷ ለማሟላት ለማልማት ለመጠቀም ከያዘቻቸው የኃይል ምንጮች የውሃ ኃይል፣ ነፋስ፣ ጂኦተርማል እንዲሁም የጸሐይ ኃይልን ያካትታሉ:: በዚሁ መሰረት አሁን እየተመረተ ያለውን ከ5 ሺህ ሜጋ ዋት በታች የሆነውን የኃይል መጠን ወደ 20 ሺህ ሜጋ ዋት የሚያድግ ሲሆን፣ ከፀሐይ ኃይል 1 ሺህ 700፣ ከውሃ 14 ሺህ፣ ከእንፋሎት 900 እንዲሁም ከንፋስ 2 ሺህ ሜጋ ዋት የሚደርስ ኃይል ለማምረት እየተሰራ ነው:: እስካሁን ድረስ በተለይም ከፀሐይ ኃይል አመንጭቶ በመጠቀም ረገድ በሀገሪቱ ጅምር እንቅስቃሴዎች አሉ::
ጥናቶች እንደሚያመላክቱት ኢትዮጵያ የተትረፈረፈ የፀሐይ ኃይል ሀብት አላት:: የፀሐይ ኃይልን ጨምሮ ሌሎች ታዳሽ ኃይሎችን በአግባቡ ጥቅም ላይ ብታውል ሀብቶቿ ከራሷ አልፎ ለውጭ አገራት በመላክ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ልታገኝ እንደምትችል መረጃዎች ያሳያሉ::
ኢትዮጵያ ከፀሐይ ኃይል ብቻ በቀን በአማካይ 5 ነጥብ 2 ኪሎ ዋት ሃወር ሜትር ስኩዬር የፀሐይ ጨረር ኃይል ታገኛለች:: በሕዝብ ጥግግት የሚታወቁት የሀገሪቱ ሰሜን፣ ማዕከላዊ እና የምዕራብ ደጋማ አካባቢዎች የፀሐይ ሀብቷ በአንፃራዊነት ዝቅተኛ ሲሆን የስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች እና ምዕራባዊ እና ምሥራቃዊ ዝቅተኛ ስፍራዎች ከፍተኛ ዓመታዊ አማካይ የፀሐይ ጨረር ኃይል ያገኛሉ:: ስምጥ ሸለቆ፣ ምዕራባዊ እና ምስራቃዊ ዝቅተኛ አካባቢዎች በቀን 6 ነጥብ… ኪሎ ዋት ሜትር ስኩየር የፀሐይ ኃይል ያገኛሉ::
ምንም እንኳን በአገሪቱ ውስጥ ብዙ የፀሐይ ኃይል ሀብቶች ቢኖርም እስካሁን ድረስ ለቴሌኮም አገልግሎት፣ ለመብራት፣ ለገጠር የውሃ ኃይል ማድረጊያ ለመሳሰሉ አገልግሎቶች እየዋለ ያለው የፀሐይ ኃይል መጠን 14 ሜጋ ዋት ብቻ እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ:: ይህ ጥቅም ላይ ሊውል ከሚችል የፀሐይ ኃይል አንፃር ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው እዚህ ግባ የሚባል አይደለም::
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከመደበኛ የኃይል (ግሪድ) አማራጭ ባሻገር እንደ ፀሐይ ኃይል ያሉትን የኃይል አማራጮችን በመጠቀም ኃይል አመንጭታ ስትጠቀም ቆይታለች:: ይህንን ስትጠቀም የኖረቺው ትላልቅ የኃይል ፍላጎቶችን ለማሟላት ሳይሆን ከኤሌክትሪክ አውታር (ግሪድ) ውጭ የሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ህዝቦችን የኃይል ፍላጎቶችን ለማሟላት ነው::
በለጋሾች ድጋፍ በመታገዝ በሀገሪቱ ሩቅ ገጠራማ አካባቢዎች የፀሐይ ኃይልን መሠረት ያደረጉ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የገጠሩ ህዝብ በተወሰነ ደረጃ ተጠቃሚ እየሆኑ ናቸው:: በተለያዩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እገዛ ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣ ሰዎች ቤታቸውን ለማብራት እና ንግዶቻቸውን ለማሳደግ ንፁህ እና ርካሽ የሆነ የፀሐይ ኃይል እየተጠቀሙ ይገኛሉ::
የተለያዩ ድርጅቶችም በፀሐይ ኃይል የሚሰሩ የብርሃን ምርቶች አምራቾች እና አከፋፋዮች ጋር አብሮ በመሥራት ከመደበኛው የኤሌክትሪክ ሥርዓት (ከግሪድ) ውጭ ለሆኑ የመብራት ምርቶች ገበያን ለመገንባት እና አጠቃቀሙን ለማስተዋወቅ እየሠሩ ናቸው:: የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከተለያዩ የውጭ ድርጅቶች ጋርም አብሮ ለመሥራት የስምምነት ፌርማ ተፈራርሟል::
የነዚህ ጥረቶች አንዱ አመላካች የሚሆነው ሰሞኑን በጋምቤላ ክልል በጆር ወረዳ ኡንጎጊ ከተማ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ነው:: በ25 ሚሊየን ብር ወጪ የተገነባው ይህ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከመደበኛው የኤሌክትሪክ ሥርዓት ርቀው የሚገኙትን ከአንድ ሺህ በላይ አባወራዎችን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተጠቁሟል::
ተመርቆ ወደ ሥራ የገባው ይህ ፕሮጀክት 175 ኪሎ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት ለግልና ለመንግሥት ተቋማት የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ የአካባቢውን የኤሌክትሪክ ኃይል እጦት ችግር ይቀርፋል ተብሏል::
የኡንጎጊ የሶላር የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሙከራ ትግበራ እየተገነቡ ከሚገኙ 12 የሶላር ሚኒ ግሪድ ኃይል ማመንጫዎች መካከል አንዱ ነው። የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ እንደተናገሩት በክልሉ ከፍተኛ የኃይል እጦት ችግር ይስታዋላል:: የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቱ በክልሉ የሚስተዋለውን የኃይል እጥረት ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ ሚና ይጨወታል:: ለአካባቢው ሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል::
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሽፈራው ተሊላ ተቋሙ የሀገሪቱን የኤሌክትሪክ ሽፋን ለማሳደግና ፍትሃዊ የኤሌክትሪክ አገልግሎትን ለሁሉም የሀገሪቱ ከተሞችና የገጠር መንደሮች ለማዳረስ በትኩረት እየሠራ ይገኛል ብለዋል:: ለዚህም የተለያዩ የኃይል ምንጮችን የማልማት ሥራ እየሠራ ይገኛል:: ከነዚህ የኃይል ምንጮች መካከል የፀሐይ ኃይል አንዱ ነው:: በተለይም ከዋናው የኃይል ቋት ርቀው የሚገኙ ህዝቦችን የፀሐይ ኃይልን በመጠቀም ኃይል ለማመንጨትና ተጠቃሚ ለማድረግ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው ብለዋል::
ከሀገሪቱ ህዝብ ውስጥ ከ35 በመቶ በላይ የሚሆነው የፀሐይ ኃይልን ከመሳሰሉ አማራጭ የኃይል ምንጭ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የኃይል ተጠቃሚ እንዲሆን ለማስቻል ርብርብ እየተደረገ ነው።
ከተለመዱት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች ጋር ሲነፃፀር የፀሐይ ኃይል ተደራሽነት፣ ዋጋ እና አስተማማኝነት እጅግ የተሻለ መሆኑን በዘርፉ የተካሄዱ ጥናቶች ይጠቁማሉ:: በተለይም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የፀሐይ ኃይል ከተለምዷዊ የኃይል አማራጮች ጋር ሲነፃፀር አንፃራዊ ጥቅሞቹ እየጨመሩ በመሆናቸው፣ ከፀሐይ ኃይል ለማመንጨት የሚያስወጣ ወጪ እየቀነሰ በመሆኑ፣ የፀሐይ ኃይል ጥራት እና አስተማማኝነት እየተሻሻለ በመምጣቱ እንዲሁም ከፀሐይ ኃይል ሥርጭት የቴክኖሎጂ ሞዴሎች እየተራቀቁ በመምጣታቸው አገራት የፀሐይ ኃይልን በስፋት ለአገልግሎት እያዋሉት ይገኛሉ::
ሀገሪቱ ያላትን የፀሐይ ኃይል በአግባቡ በመጠቀም የህዝቡን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጄክቶችን በስፋት ለመገንባት ጥረት ጀምራለች::
ታዳሽ የኃይል አቅርቦቶችን ለማጠናከር የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ትብብር እጅግ ወሳኝ በመሆኑ በመንግሥትና በግል የሽርክና ማዕቀፍ ውስጥ የሚሠሩ ሥራዎች ቅድሚያ ተሰጥቷቸዋል::
የኢትዮጵያ መንግሥት ዓለም አቀፍ በዘርፉ ከተሰማሩ እና የኃይል አመንጭ ከሆኑ ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመሥራት ውሎችን አስሯል:: ከነዚህ ድርጅቶች መካከል ኤ ሲ ደብሊው ኤ የተሰኘው የውጭ ድርጅት አንዱ ነው:: ድርጅቱ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ስምነት ተፈራርመዋል:: ድርጅቱ ኃይል እያመረተ የሚያቀርብ ይሆናል::
በተጨማሪም በመተሐራ 100 ሜጋ ዋት የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ለመገንባት እንቅስቃሴ የጀመረ ሲሆን ኢኒል ግሪን ፓወር የተሰኘ ድርጅት ጋር ውል ተደርሷል:: ሌሎች ፕሮጀክቶችንም በተለያዩ አካባቢዎች ለማስጀመር እንቅስቃሴዎች ተጀምሯል::
መንግሥት ከግል ድርጅቶች ጋር ሽርክና በማጠናከር በተለይም በሀገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ፣ ሀገራዊ የኤሌክትሪክ ሥርዓት ውጭ የሆኑ እና ዝቅተኛ የኤሌክትሪክ ፍጆታን ለሚፈልጉ ለገጠር ቤተሰቦች የፀሐይ ኃይልን እንደ መፍትሄ እንዲጠቀሙ ለማስቻል የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል::
አዲስ ዘመን መጋቢት 11/2013