አዲሱ ገረመው
የመጨረሻው ክፍል
አሁን አፋር ገብተናል:: ረጅሙን የአፋር በረሃ ንዳድ እንቀምሰው ዘንድ ተስፈንጥረን ገብተናል:: የመንገዱ ግራና ቀኝ በወያኔ ተክል ታጅቧል:: አልፎ አልፎ የአፋር ብሔረሰብ ባህላዊ ቤቶች ይታያሉ:: ከውጭ ሲታዩ አሰራራቸው ይማርካል:: ይህን ንዳድ መቋቋም እንዲያስቸሉ ተደርገው ነው የተቀለሱት::
ከመኪናው ወርደን ቤቶቹን የማየት እድል ባይኖረንም የውጭው ውበት የውስጡን ጥሩ ገጽታ ያሳያል:: አንዳንዶቹ ቤቶች ቋሚ አይደሉም:: ዝናብና ጎርፍ በሚሆንበት ጊዜ ተነቅለው ሌላ ቦታ ይተከላሉ፤ አፋር ለከብቶቹ ሣር ፍለጋ ሲንቀሳቀስ ቤቶቹም ተነቃቅለው ይከተሉታል አሉ::
በረሃው የተለያዩ ገጽታዎችን የተላበሰ ነው:: የሰው አሰፋፈር እጅግ የተራራቀ ነው:: በአንድ መንደር የሚገኙት ቤቶች ውስን ናቸው::
መሬቱ አሸዋማና ድንጋያማ ነው:: የአካባቢውን የአየር ጠባይ ላላወቀ ሰው እጅጉን ይከብዳል:: ከሰማይ የሚመጣውን ንዳድ ተከትሎ ከፍተኛ ወበቅ አለ:: ወበቁ ጸሐይዋ ያስከተለችው ብቻ አይመስልም፤ ከከርሰ ምድር ጭምር የሚወጣም ነገር ያለ ያስመስለዋል:: መዳረሻችን የሆችውን ሠመራን ለማየት ይህን ሁሉ ፈተና ማለፍ ግድ ይላል::
ክልሉ በአንድ በኩል የተለየና ውብ የመሬት አቀማመጥ ሲኖረው በሌላ መልኩ ደግሞ እጅጉን ለኑሮ የሚከፋና በሙቀት ባህር ውስጥ ጠልቆ የሰመጠ ነው:: ሆኖም ሰውን ከማኖር አልቦዘነም:: ጠንካሮቹ የአፋር ማህበረሰብ አባላት በረሃው ምናቸውም አይደለም፤ እንዲያውም ከዚያ ወጥተው ሌላ አካባቢ መልመድ የሚከብዳቸው ይመስለኛል::
ሥፍራው ከፍተኛ የምድር ርደት አጋጥሞት የነበረ ስለመሆኑ አንዳንድ ቅሬቶች ይስተዋላሉ:: አልፎ አልፎ የሚያጋጥሙ ኮረብታ መሰል ጉብታዎች ከርቀት ሲታዩ የእርሻ መሬት ይመስላሉ፤ ለዚያም በትራክተር የታረሰ ሰፊ እርሻ:: ሆኖም ሙሉ በሙሉ ድንጋይ የተከመረባቸው ስለመሆናቸው በአይናችን ተመልክተናል:: ድንጋዮቹን ያየ ሰው “ እዚህ አካባቢ ድንጋይ የሚዘንበው ምን ወር ላይ ነው?” ብሎ መጠየቁ አይቀርም:: ያን ሁሉ ድንጋይ ፈንቅሎ አስፓልቱን የሰራው ኮንትራክተር ተዓምረኛ ነው::
በረሃውን ብዙም ሳናጋምሰው ከርቀት መኪናውን ለማስቆም የተዘጋጁ የፀጥታ አካላትን የተመለከተ ሰው “ወታደሮች ናቸው ተመልክቱ…” የሚል ድምጽ ከኋላዬ አሰማ:: አይኖቼ የመንገዱን ግራ እና ቀኝ በፍጥነት አሰሱ:: በቀላሉ ልለያቸው አልቻልኩም:: ምክንያቱም የደንብ ልብስ አልለበሱም:: በቅርቡ በአዲስ አበባ ምሽት ላይ አንፀባራቂ ልብስ ለብሰው ትራፊክ ፖሊሶች ነን ብለው አንዱን ባለ ራይድ መኪና ጉዳት አድርሰውበት የሄዱ ሌቦች ትዝ አሉኝ::
አካባቢው ጭር ያለ በመሆኑ ሽፍቶች ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ጥርጣሬ አደረብን:: እናም ከመኪናችን በተቃራኒ አቅጣጫ ወደ እኛ ፊታቸውን አዙረው መጡ:: መሣሪያ ይዘዋል:: መኪናውን እንዲቆም ምልክት ሰጡ:: ከመቅጽበት እጄ ላይ የነበረውን ሞባይሌን ወደ እነርሱ አቅጣጫ ለመደገን ሳነሳ፤ አጠገቤ የተቀመጠው ጎልማሳ እጄን አፈፍ አድርጎ ከመቀመጫው ጋር ጠፍንጎ ያዘኝ:: መልዕክቱ “ስታነሳ ቢያዩህ አለቀልን” አይነት ይመስላል:: “ጎመን በጤና” አልኩና ስልኬን ወደ ኪሴ ከትቼው የሚሆነውን መከታተል ጀመርኩ::
ተቆጣጣሪዎች ነን ባዮቹ መኪናው ውስጥ ገብተው ከየት እንደመጣንና ወዴት እንደምንሄድ ከጠየቁን በኋላ መታወቂያችንን እንድናሳይ አዘዙን:: የመኪናው በር አጠገብ የተቀመጠውን የአንድ ሰው መታወቂያ ብቻ አይተው ከጨረሱ በኋላ ወደ ሠመራ ከሆናችሁ ሰው ጭናችሁልን አድርሱልን ሲሉ ጠየቁን:: አስተባባሪውና ሹፌሩ እንደማይቻል ነገሯቸው:: የሚዲያ ሰዎች መሆናችንን ስላወቁ እንጂ ሊያስገድዱ እንደሚችሉ ከሁኔታቸው ያስታውቃል:: ጥቂት ከተነጋገርን በኋላ እንድናለፍ ፈቀዱልን::
እዚህ ጋር ሁለት ነገሮችን መታዘብ ችያለሁ:: አንደኛ ሕግ አስከባሪ ነኝ የሚል የትኛውም ሰው የደንብ ልብስ መልበስ ሲኖርበት እነርሱ ግን ይህን አላደረጉም:: አሽከርካሪው አልታዘዝም ብሎ ቀጥታ ቢነዳው ኖሮ ምን ችግር ሊፈጠር እንደሚችል መገመት አይከብድም:: ምናልባት ይህ አይነት ሁኔታ በሌሎች አካባቢዎችም ሊያጋጥም ስለሚችል የሚመለከተው አካል እርምት ሊወስድበት ይገባል::
ሕግ አስከባሪዎች እንዴት ሕግ ይጥሳሉ የሚለው ጉዳይ ደግሞ ሁለተኛው ትዝብቴ ነው:: ከልክ በላይ አትጫን ብሎ የሚቀጣ ተቆጣጣሪ ለራሱ ጥቅም ብሎ ከልክ በላይ እንድትጭን ስለምን ያስገድድሃል? “ማሞ ሌላ መታወቂያው ሌላ” አሉ:: ጎበዝ ሕግ ጊዜ፣ ሥልጣን፣ ገንዘብ አሊያም ጥይት ሊሽረው የማይገባ ነው እኮ:: ታዲያ ስንቶቹ ሕግ አስከባሪ ይሆኑ ይህን ተረድተው በአግባቡ አገልግሎት የሚሰጡት:: መልሱ ያለው ህሊናቸው ውስጥ ነው::
ጉዞአችን ቀጥሏል:: ሌላው አፋር ውስጥ በጣም የሚያስገርማችሁ ነገር የፍየልና የግመል ብዛት ነው:: መብዛቱ ብቻ አይደለም እኮ የሚገርመው፤ እንደመኪና አስፓልት መሐል ላይ ነው የሚሔዱት:: የመኪና ጥሩምባ ቢነፋባቸውም የተወሰኑት ቀስ ብለው ይለቃሉ፤ የተወሰኑት ደግሞ “መስሚዬ ጥጥ ነው” ይሏችኋል:: በተለይ የግመል ዋጋ እጅግ ውድ ከመሆኑ አንፃር አሽከርካሪዎች በጣም በጥንቃቄ ነው የሚነዱት:: አይበለውና አንድ መኪና ግመል ቢገጭ እንኳን የሚጠየቀው “መኪናው ላይ ስንት ትጨምራለህ?” ተብሎ ነው አሉ::
እንዲህ እንዲህ እያልን ተጓዝን:: የመኪና ጉዞ የማይስማማቸው ብዙ ሰዎች ስለነበሩ ፌስታሉም ከረዳቱ ወደ ሰዎቹ ተጋዘ:: እኔም ሁሉንም ነገር እየተከታተልኩ ውሃዬን ጎንጨት እያልኩ በረሃውን ገፋሁት::
በመንገዳችን ዳርቻ አንድ ነገር በተደጋጋሚ አየተናል፤ እርሱም ብጥስጣሽ የመኪና ጎማ ነው ፤ የበረሃውን ሙቀት መቋቋም ያልቻሉ ጎማዎች ቅሪተ አካል ከአዋሽ እስክ ሎጊያ ድረስ በብዛት ይታያል:: ይሄንን ሁሉ ተዓምር እያየን ሎግያ ከተማ ደረስን:: አሁን ከወበቅ! ! ከፀሐይ ንዳድ በትንሹም ቢሆን አረፍ አለን፤ ተንፈስስስስ አልን::
የምስራቁን የሰማይ ጥግ ይዞ ሲገሰግስ የሚታየው ግጥም ያለ ጥቁር ደመና የመሰለ ነፋስ ከዚህም ከዚያም ይነፍሳል:: ሎግያ ከጠበቅናት በላይ የደመቀች ከተማ ናት፤ ሙቀቱን አራግፍን እረፍት እናደርግ ዘንድ ናዝሬት ሆቴል ገባን፤ ሎግያ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጀምሮ እስከ ተራው ሰው ያለ ልዩነት እኩል የሚስተናገዱባትና የሚኖሩባት ናት አሉ:: በዚህች ከተማ “ባይኖርህም አትራብም፣ አትጠማም፤ ቢኖርህም ከማንም አትበልጥም፤ መንቀባረርም አያምርብህም” ይባላል::
አዲስ ዘመን መጋቢት 11/2013