ኃይሉ ሣህለድንግል
ኮቪድ ወደ ሀገራችን ከገባ አንድ ዓመት አለፈው:: ያኔ በሽታው ወደ ሀገራችን መግባቱ የታወቀው አንድ ጃፓናዊ በበሽታው መያዙን ተከትሎ እንደነበር ይታወሳል:: ኮሮና በዓለም በተለያዩ ሀገሮች እያደረሰ የነበረውን ችግር እንዲሁም የኢትዮጵያ መንግስት ሁኔታውን በቅርበት እያጤነው መሆኑን ሲከታተሉ የቆዩት ኢትዮጵያውያን ይህን ዜና ሲሰሙ በእጅጉ ደንግጠዋል:: መደንገጣቸው በእርግጥም ትክክል ነበር::
በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ መንግሥት የጥንቃቄ እርምጃዎችን ደረጃ በደረጃ መውሰድ ጀምሮ ቀስ በቀስም እገዳ ማድረግ ውስጥ መግባቱ ይታወሳል:: ሕዝቡም የጤና ሚኒስቴርን ርቀታችሁን ጠብቁ ፣ ከቤት እንዳትወጡ ወዘተ የሚሉትን መረጃዎችና መመሪያዎች በማክበር ራሱንና ቤተሰቡን ለመጠበቅ ጥረት ማድረግ ውስጥ ገብቶ ውጤታማ ስራ ተሰርቷል::
በዚያን ወቅት የታየውን የመከላከል ስራ መለስ ብሎ ለተመለከተ በእርግጥም እጅግ የሚገርም ነበር:: በዚህ የመከላከል ስራ የተገኘውን ለውጥ የመከላከል ተሞክሮና ግንዛቤ በመያዝም ነበር ገደብ ተደርጎባቸው የቆዩ እንቅስቃሴዎች ወደ መደበኛው እንዲመለሱ የተደረገው::
ይህን አቅም አጎልብተን የመከላከል ስራውን ይበልጥ ውጤታማ ማድረግ ሲገባን ታጥቦ ጭቃ ሆነናል:: ያ የመከላከል አቅም የለም ማለት ይቻላል፤ ከፍተኛ መዘናጋት እየታየ ነው:: የበሽታው መስፋፋት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ደርሶ ባለበት በዚህ ወቅት ጥንቃቄው ደግሞ የዚያኑ ያህል የሳሳ ነው:: የአምናው ጥንቃቄ ለዘንድሮ ቢሆን ምንኛ ጥሩ በሆነ ነበር::
በየቀኑ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በየአስር ቀናቱ ተጨምቀው የሚወጡት መረጃዎች በእርግጥም በአሳሳቢ ደረጃ ላይ መገኘታችንን ያሳስባሉ:: በቀን በበሽታው ይያዙ የነበሩ ሰዎች ብዛት አንድ ፣ ሁለት ፣ሶስት አኀዝ እያለ ወደ አራት አኀዝ ገብቷል፤ለዚያውም በፍጥነት::
ከትናንት በስቲያ ደግሞ ይህ ሁለት ሺ ሃምሳ ሰባት ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል::ይህም ከተመረመሩት 100 ሰዎች 26 ወይም 25 ነጥብ 5 በመቶ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ያመለክታል። ይህን ያህል ሰው በበሽታው የተያዘው ደግሞ 8ሺ 55 ሰዎች ምርመራ ባደረጉት ሁኔታ ነው:: 600 ሰዎች በጽኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ተኝተው ህክምና እየተከታተሉ ናቸው :: ቫይረሱ የተገኘባቸው ብዛት 181 ሺ 869 ፣ አሁን ቫይረሱ የሚገኝባቸው ደግሞ 33ሺ 916 ደርሷል:: 2ሺ602 ዜጎቻችን ሕይወታቸውን አጥተዋል::
ሁኔታው በእጅጉ የሚያስፈራ መሆኑን ከእነዚህ መረጃዎች ብቻ መረዳት አያዳግትም:: ይህ ሁሉ መጪውን ጊዜ እጅጉን አሳሳቢ እንዲሆን አድርጎታል:: ለሚያስብ ሰው ፣የመረጃ ዋጋን ፣ የማሳሰቢያንና መመሪያን አስፈላጊነት ለሚገነዘብ ሰው በአሳሳቢ ሁኔታው ውስጥ መገኘታችንን መረዳት አያዳግተውም፤ ታዲያ መከላከል አለመሞከርን ምን አመጣው?
የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ በቅርቡ እንዳስታወቁት፤ በበሽታው የመያዝ ምጣኔ፣ በፅኑ ህክምና ላይ የሚገኙ የህሙማን ቁጥር እየጨመረ ነው። የፅኑ ህክምና ክፍሎች መሙላት፣ የመተንፈሻ መሳሪያዎች በህሙማን መያዝና የኦክስጅን እጥረት ሁኔታውን እንዲባባስ አድርጎታል::
የመከላከል ስራው በሚጠበቀው ደረጃ ተግባራዊ እየተደረገ አለመሆኑን ሚኒስትሯ ጠቅሰው፤ የቫይረሱ ሰርጭት ከቁጥጥር ውጪ ከመሆኑ በፊት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ግዴታቸውን እንዲወጡ ሚኒስትሯ ጥሪ አቅርበዋል::
አሁን በኮሮና ወረርሽኝ መከላከል ላይ በስፋት እየተሰራ ያለው በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ በመንግስታዊ ተቋማት፣ በአንዳንድ የግል ድርጅቶች፣ በትምህርት ቤቶች፣ በኢንዱስትሪዎች ነው:: አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ማስክ ላላደረገ አገልግሎት አይሰጡም:: በእነዚህ ተቋማት የመከላከል ስራው በስሱም ቢሆን እየተፈጸመ ነው::
የመንግስትና የግል ተቋማት ሰራተኞቻቸውን ወደ ስራ ቦታ የሚያስገቡት እጃቸውን መታጠባቸውን ወይም በሳኒታይዘር ማጽዳታቸውንና የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ ማድረጋቸውን እያረጋገጡ መሆኑ አንድ ትልቅ ነገር ነው:: ይህም ቢሆን በተጀመረው አግባብ እየተፈጸመ አይደለም::
ሌላው ከሞላ ጎደል ጥሩ እየተሰራበት ያለው የትራንስፖርት ዘርፍ ነው:: ማስክ ያላደረጉ ተገልጋዮችን ማሳፈር ተከልክሏል፤ አሽከርካሪዎች ተሳፋሪዎች ማስክ ማድረጋቸውን ሳያረጋግጡ ተሸከርካሪ ማንቀሳቀስ አይጀምሩም:: ማስክ ያላደረገ ተሳፋሪ አሳፍረው ቢገኙ በትራፊክ ፓሊስ ወይም በመንገድ ትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች ይቀጣሉ:: በዚህ ምክንያት ማስክ የመጠቀም ሁኔታ ጥሩ ሊባል የሚችል ነው:: ይህም ቢሆን ግን ቅጣት ተፈርቶ የሚፈጸምና ድብብቆሽ ጨዋታ የሚስተዋልበት ነው::
ከዚህ በተረፈ አብዛኛው ህብረተሰብ በሽታውን ለመከላከል ያደርግ የነበረውን ጥንቃቄ እርግፍ አድርጎ ትቶታል:: ሕዝቡ ኮሮናን አስመልክቶ የጤና ሚኒስቴርና የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሚያወጧቸውን መረጃዎች፣ መመሪያዎችና ማሳሰቢያዎች እንደ ዋዛ እየተመለከታቸው ነው:: ምነው አሁንስ ነጠላ ዜማ አደረጋችሁት የሚሉም ይስተዋላሉ፤ አሁንም ከፖለቲካ ስራ ጋር የሚያያይዙ ከንቱዎችንም እናገኛለን::
የአዲስ አበባ ከተማ ጎዳናዎች፣ የገበያ ስፍራዎች፣ በተለይ በአደባባይ በዓላት ወቅት የሚታዩ እውነታዎች ከምልክቱ በስተቀር ሀገሪቱ በሽታውን በመከላከል ላይ አለመሆኗን፤ በገሀድ በአደባባይ አይተናል:: የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ሲመረቁ፣ በየሰርጉ ፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት ጭምር በተገኙባቸው መድረኮች ሰዎችን ያለማስክ ተመልክተናል::
ከሻይ ቤት አንስቶ ያሉት ሆቴል ቤቶች፣ ካፌዎች፣ ስጋ ቤቶች ወዘተ ማስክ ሲደረግባቸው አይታይም፤ አስተናጋጆች ማስክ ካላደረጉ ሌላ ምን ማለት ይቻላል:: አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መሆናቸው ተዘንግቷል:: ሰው በሚበዛበት አካባቢ አትገኙ ስንባል ልጅ ይመስል የተከለከለ ነገር እንወዳለን:: እኛ ግን የሚያምረን እሱ ሆኗል:: ጎበዝ ችግር ውስ ጥ ነን::
ችግሩ ከአዲስ አበባ ወጣ ሲባል ደግሞ ይብሳል:: በቅርቡ በተለያዩ አጋጣሚዎች በአዲስ አበባ ሶስት በሮች ከ100 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዣለሁ:: በእነዚህ አካባቢዎች ከተሞች ማስክ ማድረግ የሚባል ነገር የለም:: ማስክ ያደረገ ከታየም መንገደኛ መሆን አለበት:: የእነዚህ ከተሞች ነዋሪዎች ማስክ ያደረገ ሲያገኙ አዲስ አበቤዎች መጡ ወይም አዲስ አበባ የሚሄዱ ናቸው ሳይሉ የሚቀሩም አይመስለኝም::
ቸልተኝነታችን በቀላሉ ከማንወጣው ማጥ ውስጥ እየተከተተን ነው:: ከዚህ የሚያወጣን አሁንም አንድ እና እንዱ መፍትሄ የጤና ሚኒስቴርን መረጃ መከታተልና መተግበር፣ መመሪያዎችንና ማሳሰቢያዎችን አክብሮ መንቀሳቀስ ብቻ ነው::
ሀገራችን የምትችለውን ሁሉ እያደረገች ነው:: የኮሮና መከላከያ ክትባት በሀገራችን ለመስጠት 2ነጥብ 2ሚሊየን ዶዝ ክትባት ወደ ሀገር ቤት ገብቶ ክትባት መስጠት ተጀምሯል:: እስከ መጪው ታህሳስ ድረስ ከሀገሪቱ ሕዝብ 20 በመቶው እንደሚከተቡ የጤና ሚነስቴር አስታውቋል::
ይህ ሁሉ ሆኖም ጥንቃቄ ማድረግ ወሳኝ ስለመሆኑ ሚኒስቴሩ አሳስቧል፤ የተከተቡት በሙሉ አስፈላጊውን የመከላከያ መንገድ ሁሉ እየተጠቀሙ መቆየት አለባቸው:: ይህ በራሱ የመከላከል ስራው አሁንም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያመለክታል::
በአገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች በኩል ያለው የመከላከል ስራ ጥሩ ነው:: ይህ ሁኔታ ከአዲስ አበባ ውጪም እየተሰራበት ከሆነ በማጠናከር ለውጥ ማምጣት ይቻላል:: መኖሩን ግን እጠራጠራለሁ:: በዚህ በኩል በየደረጃው ያለ ተቋም ተጠያቂ መሆን አለበት ::
ማስክ ላላደረጉ አገልግሎት አለመስጠትን የሚተገብሩት አገልግሎት ሰጪዎች ናቸው፤ ይህን ባያደርጉ ተቋማቱ ተጠያቂ ይደረጋሉ:: ይህ በትራንስፖርቱ ዘርፍ በተወሰነ መልኩ የሚታይ ቢሆንም ቁጥጥሩ ትራፊክ አለ የለም በሚል የተመሰረተ በመሆኑ ሊታረም ይገባል:: ለማናቸውም በእነዚህ ተቋማት ላይ ያለውን የመከላከል ስራ ማጠናከር ፣ሌሎች ሆቴሎች የገበያ መዳረሻዎች ሕዝብ በብዛት የሚሰበሰብባቸው ተቋማትና ስፍራዎች ማስክ ማድረግን የግድ እንዲሆን ማስገደድ ውስጥ መግባት ያስፈልጋል::
ኮሮናን የመከላከል ስራው በአዲስ አበባ ለዚያም በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አካባቢ የተወሰነ ነው:: የመከላከል ስራው በአዲስ አበባ ላይ ብቻ ማተኮሩ ብቻውን የሚፈለገው ለውጥ ላይ መድረስ አያስችልም:: የእንቅስቃሴ ገደብ መጣል ባያስፈልግ እንኳ የመከላከል ሥራው በመላው ሀገሪቱ በሚገባ መተግበር ይኖርበታል:: የእንቅስቃሴ ገደብ በሌለበት ሁኔታ አዲስ አበባ ላይ ብቻ ኮሮናን ለመከላከል መሞከር ከዚያ ውጪ ያለው የሀገሪቱ ክፍል ነገር አለሙን ሲተው መመልከት ታጥቦ ጭቃ መሆን ነው::
እንዳለፈው የመከላከል ስራ የጸጥታ አካላት የመከላከል ስራውን እንዲከተታሉና እንዲቆጣጠሩ ማድረግ ይገባል:: ሰው ራሱን ካልፈራ ሊፈራ የሚችለውን ማሰማራት ይገባል:: ከዚህ ጎን ለጎን በጎ አድራጊዎች በስፋት በመልመል ማሰማራት አንድ ጥሩ አማራጭ ነው እላለሁ:: ጎበዝ ታጥቦ ጭቃ ሆነናል፤ ከዚህ ለመውጣት እንረባረብ::
አዲስ ዘመን መጋቢት 11/2013