አብርሃም ተወልደ
አንድ ጊዜ እንዲህ ሆነ አሉ፤ ሦስት ጓደኛሞች አብረው የሚሰሩ፤ በአንድ ወቅት ታዲያ ጓደኛሞቹ በመካከላቸው አለመስማማት ይከሰታል፤ ጠቡ ተካረረ፤ በእነሱ የሚፈታ ሳይሆን ቀረናም አስታራቂ አስፈለገ። አለመግባባታቸውን የሰማ አንድ ልባም ሰው ሊያስታርቃቸው ይወስናል፡፡
ይህ ሰው ጓደኛሞቹን በአንድ ላይ ከአስቀመጠ በኋላ አንዱ የሌላውን ችግር እንዲናገር ጠየቃቸው። እነሱም በሆዳቸው ያለውን አንድም ችግር ሳይቀር በዝርዝር ተናገሩ። አስታራቂው ቀጠለናም አንዳችሁ ያንዳችሁን ችግር እንደተናገራችሁ ሁሉ አሁን ደግሞ አንዳችሁ የሌላኛችሁን መልካም ነገር በዝርዝር ተናገሩ አላቸው። በዚህም አንደኛው የሌላኛውን መልካምነት እና በደጉም በክፉም ቀናት ያደረጉትን ቸርነት ዘረዘሩ፡፡
ጓደኛሞቹ አስታራቂው በፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ መሠረት ከልባቸው አውጥተው ከተናገሩት መካከል ከክፉው ይልቅ ደጉ በልጦ ተገኘ። እከሌ በደለኝ ከሚሉት ይልቅ ዋለልኝ የሚሉት በዛ። ይህን ሲገነዘቡም ድብልቅልቅ ያለ ጸብ ውስጥ ከመግባት ይልቅ ያለሌላ ተጨማሪ አስታራቂ ተቃቅፈው መሳሳም ውስጥ ገቡ። ማረኝ፤ ይቅር በለኝ ተባባሉ፡፡
ማንኛውም ሰው አንድን ጉዳይ በቅን ልቦና መመልከት ከቻለ የተደረገለት ተደርጎብኛል ከሚለው የበለጠ ሆኖ ያገኘዋል። ለእዚህ ግን ማድመጥ እና ማስተዋል ያስፈልጋል። የጎደለን ይሄ ነው። ለማዳመጥ ዝግጁ አይደለንም፤ ለማስተዋል ዕድል አንሰጥም። ይህን ሳስብ ደራሲ ከበደ ሚካኤል በግጥማቸው
«አሁን የት ይገኛል ቢፈልጉ ዞሮ መስማት ከማይፈልግ የባሰ ደንቆሮ» ያሉት ይታወሰኛል፡፡
ባለቤቱ ስጦታው መሆኗን መረዳት የተሳነው አንድ አዝማሪ ነበር። ባለቤቱ በጎ ብታደርግለትም አያመሰግናትም፤ ማመስገን አይደለም ሥራዋን በበጎነት ሊቆጥርላት አልቻለም። ከማመስገን ይልቅ ማጣጣል ይቀናዋል፤ አንዱንም ምክሯን እንክብካቤዋን አይቀበልም፡፡
ታዲያ ከዕለታት አንድ ቀን ጠዋት ላይ አንድ ነገር ሆነ፤ ይህ አዝማሪ ለባለቤቱ «ማታ በህልሜ መልአከ ሞት መጥቶ ዕዳ ከሜዳ አለብህ ሲለኝ አደረ።» ይላታል። ባለቤቱም «ይሄማ ባላጠፋኸው ጥፋት ቅጣት ይጠብቅሃል ማለቱ ነው። ስለዚህ አርፈህ እቤትህ ተቀምጠህ ይሄን ቀን ብታሳልፍ ይሻላል» ትለዋለች።
ባልም፤ «ምንም ሳላጠፋ ማን አባቱ ነው የሚቀጣኝ፤ እንዲያውም አሁኑኑ ነው የምወጣለት» ብሎ ተነስቶ ወደ ጫካ ሄደ። አንድ ትልቅ ዋርካ ስር ተቀምጦም ክራሩን እየመታ ማንጎራጎር ጀመረ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ አካባቢው በሁካታ ተናጠ። በርካታ ሰዎች በአዝማሪው ዙሪያ ተሰበሰቡ።
ግራ ተጋብቶ ይመለከታቸው ጀመር። እነዚህ ሰዎች ለካ በሬ የጠፋባቸው ኖረዋል። በሬውን የነዱት ወንበዴዎች አርደው በልተው ሲፈነድቁ ቆይተው ወደ ሰፈራቸው ተመልሰዋል። የተረፋቸውን ደግሞ እዚያው እዋርካው ስር ጥለውታል።
ግጥምጥሞሹ ያስገርማል፤ በአካባቢው ከተሰባሰቡት መካከል አንደኛው፡- «ይሄ ጥጋበኛ አዝማሪ በሬያችንን አርዶ በልቶ ጠግቦ ሲያበቃ፣ ይሄው ክራሩን እየመታ ዜማውን እያንቆረቆረ ፈንጠዝያውን ቀጥሏል። እንግዲህ ሌባ ተይዞ ዱላ አይጠየቅም» አለ። ሁሉም በአዝማሪው ላይ አንዳንድ ቡጢ አሳረፉበት። አዝማሪውም በጣም ተጎዳ።
ወደ ቤቱ ተመልሶም ለባለቤቱ የሆነውን ሁሉ ይነግራታል። ባለቤቱ «ውድ ባለቤቴ ሆይ እንኳንም ተረፍክ ብቻ፤ በህልምህ እኮ መላከ ሞት ዕዳ ከሜዳ ያጋጥምሃል ብሎ በግልጽ አማርኛ ነግሮህ ነበር። አንተ ግን አላዳመጥከውም። እኔም አርፈህ እቤት ተቀመጥ ብዬህ ነበር፤ አሻፈረኝ ብለህ ሄድህ፤ እንግዲህ ችግሩ ያንተው ነው። ለወደፊቱ የምትባለውን አዳምጥ፤ ሰው ሲነግርምህም በሚገባ አዳምጥ፤ ቢያንስ እኔ የነገርኩህን መስማት ነበረብህ» አለችው።
አየህ ባሻዬ! ይህንንም ያነሳሁት ለመውቀስም ሆነ ለማመሰገን መናገር ብቻ ሳይሆን ማድመጥ ተገቢ መሆኑን ለማመልከት ነው። ይህ ሰው ቢሰማ ያተርፋልም፤ ይተርፋልም። እጁ ላይ ያለውን ቢያውቅ/ባለቤቱን የምትለውን ቢሰማ/ ቢያመሰግን ለዚህ ሁሉ አደጋ ባልተጋለጠ ነበር፡፡
ማዳመጥ ትልቅ ዋጋ አለው። ሰው የሚነገረውን ማዳመጥ የማይፈልግ ወይም ለማዳመጥ ያልታደለ ከሆነ ክፉኛ የተበደለ ነው። ክፉና ደግን ለመለየት ማዳመጥ ከዚያም ውሳኔ ላይ መድረስ ትልቅ ዋጋ አለው፡፡
አለማዳማጥ ለጥሩ ሰው ክብር አለመስጠት ክብር ነፋጊውን ማዳመጥ የማይፈልገውን ዋጋ ያስከፍለዋል፤ ለዚያም የዘንድሮውን ዓይነት ዋጋ ፤ በአናት በአናቱ የሚጨምር ዋጋ ።
ሰዎች ለሰዎች የሚሰጡት ዋጋ የሚገባቸውን የማያህልበት ጊዜ ጥቂት አይደለም። ባል ሚስቱ ለምታደርገው በጎ ነገር እውቅናውን በተለያየ መንገድ የማይገልጽበት ሁኔታ ያጋጥማል፤ ሚስትም ለባሏ እንዲሁ። ይህ ትልቅ ጉድለት ነው። በብዙ በጎ ነገሮች መካከል በታየ አንድ ጥሩ ያልሆነ ነገር ሳቢያ የተሰራውን በጎ ነገር ሁሉ ጥላሸት መቀባትም አለ። ይሄ ደግሞ ከፉ በሽታ ነው።
ይህ ሁሉ መጥፎ ባህሪ ነው፤ አንድ ቀን ዋጋ ያስከፍላል። መጥፎ ባህሪን የሚሸከም ይጠፋና ቁጭት ውስጥ መግባት ይከተላል። ከዚህ ለመውጣት ሰዎችን ማዳመጥ፣ ዋጋቸውን በሚገባ ተረድቶ ማመስገን ይገባል። ምስጋናው ጥሩ ዘር ማለት ነው፤ ቀጥሎ ብዙ ሰዎችና ሥራቸው ይበልጥ ጥሩ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡
ምስጋና ለበለጠ ሥራ ያነሳሳል። ምስጋና ለሚገባው ሰው ምስጋና በወቅቱ አለመስጠት እጅጉን ይጎዳል። በጎ ነገር አድርገን መመስገን ሁላችንም እንፈልጋለን፤ የዚያኑ ያህል በጎ የሰሩትን ማመስገን አለብን፤ ማዳመጥም አለብን።
አንዳንድ ሰዎች ምስጋና ይፈልጋሉ፤ አንዳንዶች ደግሞ መስራታቸውን እንጂ ምስጋናውን አያስቡትም። ሰዎች ለሰሩት ለእያንዳንዱ በጎ ነገር ምስጋና ሊቸራቸው ይገባል። በጎ ሰሪዎችን እየፈለገን ምክንያት እየፈጠረን ማመስገን ይኖርብናል፤ ይህ ሲሆን ይጠነክሩልናል። ሌሎች ከስር ከሥራቸው ይከተሏቸውና ይበዙልናል፡፡
ፍቅራችን ድካማችን መጨነቃችን እንባችን በሌላ ሰው ሕይወት ውስጥ ስላመጣው በጎ ነገር መስማት እንፈልጋለን። እኛ መመስገን የምንፈልገውን ያህል ሌሎችም መመስገን እንደሚፈልጉ መዘንጋት የለብንም። ይህንን ባለመረዳታችን ምክንያት በሕይወታችን ከፍተኛ ሚና የሚጫወተውን «ምስጋና» ነፈግናቸው የተጎዱትን ቤቱ ይቁጠራቸው። በማመስገን ፈንታ ነቅፈናቸው ልባቸው የተሰበረም ጥቂት አይደሉም። መልካም ሰው በምስጋና የተሞላ ነው፤ ትልቅም ሆነ ትንሽ ያደረገልንን አናመስግን!!
አዲስ ዘመን መጋቢት 10/2013