Mኣr
በሰከነ አዕምሮ ከተመለከትነው መደገፍ መብት ነው። ልክ ማፍቀር መብትና ተፈጥሯዊ እንደሆነው ሁሉ መጥላትም እንደዛው ነው። ችግሩ ያለው የጠሉትን በሌላ፤ ሰብአዊ ባልሆነ መንገድ ካላስተናገድኩት ከተባለ ብቻ ነው። ይህን ላድርግ የሚል ካለ “ደርዝ አጣ” የምንለው ሲሆን ቀጥለንም “ደርዝ ይኑርህ እንጂ” በማለት ወደ ሰዋዊ ባህርይው እንዲመለስ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። ይህን ሁሉ ስንል ካልሰማን ያው በምናውቀው መንገድ “ምከረው ምከረው እምቢ ካለ መከራ ይምከረው” ብለን እናልፈዋለን።
በእስከ ዛሬው የዓለማችን የፖለቲካና ርዕዮተ ዓለም ሂደት ውስጥ በርካታ ሰው በላ ሥርዓታት ተከስተው ተሰናብተዋል፤ አረመኔ መሪዎች ተፈጥረው እንደየ አውሬነታቸው ደረጃና ባህርይ ሂሳባቸውን እየተቀበሉ፤ የቻሉትም እያወራረዱ ላይመለሱ አዝግመዋል። እነሆም በዓለም ታሪክ ውስጥም ዲያብሎሳዊ ቀመርና ተግባራቸው በአስተማሪያነቱ እንደ ዘለቀ ነው። ከእነዚህ ሁሉ ደግሞ ሂትለርና ፓርቲው አንዱና ዋናዎቹ ናቸው።
የአሁኗ ዓለም የሂትለርን አስተሳሰብና የሚከተለውን ርዕዮት የሚያስተናግድ ትከሻ እንደሌላት በሚገባ ይታወቃል። ይሁን እንጂ በአውሮፓና አሜሪከ እስከሁንም ድረስ የሂትለርን አቋም የሚደግፉና የርዕዮተ ዓለሙ አራማጅ የሁኑ ደጋፊዎች አሉ። ማንኛውንም አይነት ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን ተጠቅመው እንደ አንድ ሰላማዊና ተቃዋሚ ፓርቲ ይንቀሳቀሳሉ። “ይህን በማድረጋችሁ . . .” ተብለው ከማንም ጋር ንትርክ ገጥመው አያውቁም።
የአሜሪካን ፖለቲካ ስንመለከትም የምናገኘው ተመሳሳይ አይነት የመቃወምና የመደገፍ መብትን ሲሆን በይፋ ከምናውቃቸው ሁለቱ አውራ ፓርቲዎች ውጭ ሌሎች ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገሪቷ ይንቀሳቀሳሉ። ይንቀሳቀሱ እንጂ በህዝብ በኩል ያላቸው ተቀባይነት እዚህ ግባ ስለማይባል ተሳትፏቸውም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
ከእነዚህ ፓርቲዎች መካከል አንዱ ግራው ክፍል ሲሆን ከእነ አክራሪነትና አውዳሚነት አቋምና እምነቱ ጋር በነፃነት ይንቀሳቀሳል። የሚፈልግ ይወደዋል፤ የማይፈልገው ይጠላዋል፤ መሃለኛው ደግሞ እስከ መኖሩም ረስቶታል።
ይህን ሁሉ መንደርደሪያ እዚህ ለመገጥገጥ የተገደድነው ምናልባት እንስማማ እንደሆን በማለት ሲሆን እንድንስማማም በመሻት ጭምር ነው።
የጠ/ሚኒስትር አቢይን ወደ ሥልጣን መምጣት ተከትሎ ከታዩት ለውጦችና ከተከሰቱት ክስተቶች አንዱ የቀድሞው ህወሓት (ጁንታው) አባላት ወደ መቀሌ “ንካው” ማለታቸውና አስፈላጊውን የጦርነት ዝግጅት በማድረግ ህዳር 24/2013 ዓ.ም የሰሜን ዕዝ መከላከያ ላይ በአረመኔያዊ ሁኔታ ጭፍጨፋ ማካሄዳቸው፤ እሱንም ተከትሎ መንግሥት በወሰደው ሕግ የማስከበር ዘመቻ አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መደምሰሳቸው ነው። (እዚህ ላይ ማንሳት የተፈለገው ይህን አይደለም፤ የርዕሰ ጉዳያችን መነሻ መሆኑን ለመጠቆም ያህል እንጂ።)
በአሁኑ ሰዓት የጁንታው ደጋፊዎች በግልፅ እየተንቀሳቀሱ ነው። በማህበራዊ ሚዲያው ያለውን መንጋ እንኳን ትተን እዚሁ አጠገባችን በአካል ያሉትን እንኳን ብንወስድ ከአኳኋናቸው ጀምሮ አነጋገርና ሃሳብ አሰነዛዘራቸውን ጨምሮ ሁሉ ነገራቸው የጤና አይደለም።
“ይህች አገር ሰላም የምትሆን አይመስለኝም፤ ሰላም ካልሆነች ደግሞ ምንም አይነት እድገትም ሆነ ሌላ ነገር አይታሰብም።” ይሎታል ጠጋ ይልና። “ምንው ምን መጣ፣ ምን ተሰማ?” ሲሉት “ጦርነቱ መች ቆመ፣ መቀሌ አካባቢ የህወሓት ጦር እየተዋጋና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሠራዊት እየማረከ እኮ ነው፤ ለነገሩ ሂዱ ብሎ ለቋቸዋል።” በማለት የሀሰትና የተጋተውን ፕሮፓጋንዳ ያዥጎደጉደዋል።
ይህ መግለጫና ምንነቱ እንኳን በውል ያልገባው በቀቀን “አልሰማህም እንዴ የአሜሪካና አውሮፓ መንግሥታት በትግራይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል በማለት መግለጫ ማውጣታቸውን? ነገሩ እኮ ለአቢይ እየከበደ ነው የመጣው።” በማለት ሊያስረዳኝ መሞከሩን ያህል ግን ጨጓራ የሚልጥ ነገር የለም።
“ልክ ነህ። አሁንስ የት ይበሉ ታዲያ? ትግራይ ከማለት ሌላ አርባ ምንጭ ነው ወይስ አዲስ አበባ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈፀመ እንዲሉ ነው የፈለከው? ደግሞም ትግራይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈፅሟል እንጂ የትግራይ ህዝብ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈፅሟል የሚል ነገር የለበትም። ማን ማን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እንደ ፈፀመ ገና ተጣርቶ ለህብ አልተገለፀም። የተገለፀውና የሰማነው ነገር ቢኖር ትግራይ ክልል ለምሳሌ ማይካድራና አካባቢው) ውስጥ የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈፀሙን ብቻ ነው።” ተብሎ ሲነገረው ሁሉ ሁኔታው በሚፈልገው እንዳልሄደለት ቢያስታውቅበትም፤ ሰውየውና እሱን መሰል የጁንታው ደጋፊዎች “ዓይኔን ግንባር ያድርገው” ከማለት የሚመለሱ አይደሉምና ወያኔ ለዚህች አገር ያልሰራው ሥራ የለም፤ ይህ ሁሉ … በእሱ ነው። ዩኒቨርሲቲዎችን 50 ያደረሰው እኮ ህወሓት (ኢህአዴግ ማለቱም ቀረና) ነው። የደጋፊነታቸውን ጥግ አልፈው የድንዛዜያቸው ጠርዝ ላይ ሲደርሱ እንመለከታቸዋለን።
ሰሞኑን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ውስጥ ሲወጣ እኔ በበሩ ሳልፍ ያገኘሁትና የቆየ እውቂያ ያለን አንድ ሰው ያለኝ ለትዝብት ይሆን ዘንድ እዚህ ላሰፍረው ወደድኩ። እንዲህ ነበር ያለው “ሁኔታው ለፌደራሉ በጣም እየከበደው ነው የመጣው አሉ፤ ህወሓት የበላይነት እየያዘች ነው ይባላል።” እና የመሳሰሉትን ጁንታውን የማምለኪያ ቃላቱን ያለገደብ አፈሰሳቸው።
ከዚህ ሰው ጋር ያለን እውቂያ በመከባበር፤ እሱም ሆነ እኔ ስንናገር ተደማምጠን መነጋገር ላይ የተመሰረተ ነበርና ሲያወራል ከማዳመጥና የማውቀውን ከማካፈል ወደ ኋላ ማለት አልቻልኩም። በዚሁ መሰረትም “ጦርነቱ አልቋል ከተባለ እኮ ቆየ። ምን እያልከኝ ነው?” ስል ጠየኩት።
“አይምሰልህ። ሁሉንም ነገር ወደ ፊት የምታየው ይሆናል። ማን እንደሚያሸንፍና የበላይነቱን እንደሚይዝ ታያለህ” እያለ እሚያምነውም ሆነ የሚሰማው ያለ ይመስል እንደ ጉድ ያወራዋል፤ ጁንታውን እንደ ጉድ ይደግፈዋል – እስከ መደንዘዝ በሚያደርስ መለከፍ (አፍቃሬ ህወሓት) ተነድፎ፤ ከእሱም አልፉ ሌሎችን እስከመንደፍ በሚዘልቅ ትንታጉ።
ባጠቃላይ አይደለም ህወሓትን ማንንም መደገፍ የግለሰቡ ወይም ቡድኑ ምርጫ (ወይም መብት) ነው። በመግቢያችን እንዳለው ሂትለርም “Skin heads” የሚባሉ ደጋፊዎች አሉት። ደርዝ ያላቸው በመሆኑ እየደረሰባቸው ያለ፤ ወይም እያደረሱት ያለ ምንም አይነት ተፅዕኖ የለም። ስለዚህ በሀሰት፣ ምድር ላይ በሌለ ፕሮፓጋንዳ ህዝብን በማሳሳት ውጤት ላይ እደርሳለሁ ማለት ደርዝ ማጣት ብቻ ሳይሆን ላም አለኝ በሰማይ አይነት የእድሜ ልክ ማንጋጠጥን የሚያስከትል ነው።
የመጨረሻ ማጠቃለያችን የሚሆነው ሁላችንም ያለችን እችውና እቺው አገር ብቻ ነች። ክልል ተከፋፍሎ ቢሰጠንም ያለ እሷ፤ ግንዷ የሚሆን ነገር የለም። በመሆኑም ስናወራ እሷን ማዕከል አድርገን እንጂ የእሷን መፍረስ ማዕከል አድርገን አናውራ። እሷን ማዕከል አድርገን ካወራን የሁሉም ነገር እዳው ገብስ ነውና ብዙም አያሳስብም።
አዲስ ዘመን መጋቢት 10/2013