ምህረት ሞገስ
ስም ተካዮች በሁለት መልኩ ይገለፃሉ። አንደኛው በመልካም ሁለተኛው በክፉ። ስም ትልቅ በጎ ነገር በማድረግ ይተከላል። አስገራሚው ነገር እጅግ በጣም የከፋ መጥፎ ነገር በማድረግም ስም ይተከላል። በጎ አድራጊ ስሙ ከመቃብር በላይ ለዘላለም እየተጠቀሰ ሲወደስ፤ ክፉ አድራጊው ዘላለሙን በተነሳ ቁጥር ሲረገም ይኖራል። ስሙ ከአገር አልፎ በዓለም ሊበተን ይችላል።
በዓለም ደረጃ ስማቸውን ከተከሉት መካከል ማዘር ትሬዛ ተጠቃሽ ናቸው። የማዘር ትሬዛ ቀዳሚ የአገልግሎት ዓላማ ዘር ቀለም ሳይለዩ በድህነት ምክንያት የሚቸገሩትን፣ መጨረሻቸው ከሞት በስተቀር ሌላ ምንም ዕድል የሌላቸውን፣ መጠለያ አጥተው መንገድ ላይ የወደቁትን መሰብሰብ፣ ሰዎች ከፈጣሪ የተሰጣቸው ሰብዓዊ ክብር እንዳይነካባቸው ወይም እንዳይነፈግባቸው መጠበቅ ነበር። ይህንንም በማድረግ በዓለም ደረጃ ስማቸውን ተክለዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በክፋት ስማቸውን በመትከል እየተወቀሱ ዘላለም ከሚረገሙት መካከል ቀንደኛው አዶልፍ ሂትለር ነው። አዶልፍ ሂትለር እ.ኤ.አ. ከ1933 ጀምሮ የጀርመን ቻንስለር እንዲሁም ከ1934 ጀምሮ ደግሞ የጀርመን መሪም ጭምር የነበረ ሰው ሲሆን፤ የሂትለር ዘረኛ አስተዳደር 6 ሚሊዮን የአውሮፓ አይሁዶችን እና 5 ሚሊዮን ሌሎች የተለያዩ አገራት ሕዝቦችን በገፍ አስጨርሷል።
ሂትለር ብዙዎች እንደሚያስቡት ቆሞ ቢደሰትም ሞቶ እረፍት የለውም፤ ነገር ግን ዛሬም ድረስ የሂትለርን የመሰለ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ‹‹የተለየን ዜጎን ነን›› ባዮች በክፉ ስማቸው ቢጠቀስ ምናለ? አይ ይቅርብን፤ እንግዲህ ሙት ወቃሽ መሆኑን አቁመን፤ ስለቆሙት እንወያይ።
ዘር እየቆጠሩ መግደል ለእንቶኔ መልካም መሥራት ሳይመስላቸው አልቀረም። በክፉ ስማቸውን እየተከሉ እንዳሉም የተገነዘቡ አይመስሉም። የማይካድራው ጭፍጨፋ የሚታወስ ሲሆን፤ አሁንም በመተከል እና በሌሎችም አንዳንድ አካባቢዎች የሚካሂዱ ማሳደዶች እና ግድያዎች መነሻቸው እንደሂትለር አይነት የዘቀጠ ‹‹የነጠረ ደም አለኝ›› የሚል የዘር አስተሳሰብ ውጤት ስለመሆኑ መካድ አያሻም።
ዘረኞቹ ስለሁሉም ሰው አያስቡም። የማንኛውም ብሔር ቢሆን የየትኛውም ሰው ጥቃት የእነርሱም ጥቃት ስለመሆኑ አያስተውሉም። በፍፁም አረመኔነት ሰው ማስገደል በተለይ ለኢትዮጵያውያኖች መከራ አይተው ያሳደጉትን ‹‹ይጦረኛል›› ብለው ተስፋ የጣሉበትን ወጣት መቅጠፍ የግፍ ግፍ ቢሆንም ሲፈፀም ታይቷል። በራስ ወዳድነት ጥግ በተፈፀመ ጥቃት ልጇን ያጣች እናት ጉንጯ ላይ የሚፈስ እንባ ጠፍቶ፤ ደረቅ ሃዘኗ በርትቶ ለሞት ሲዳርጋት ታይቶ ታልፏል።
ፖለቲከኞች ለአገር እና ለወገን ጥቅም ለመላው ህዝብ ክብር ከማሰብ ይልቅ በዘር ውስጥ ተወሽቀው፤ ለመላው ህዝብ ፍትህና እኩልነት ከመታገል ይልቅ መገነጣጠል ላይ ተንጠልጥለው አንድ የሆነችን አገር በማፍረስ ህልም ውስጥ እየኖሩ ጀሌያቸውን የሚያሰባስቡ የክፋት ስም ተካዮች ፖለቲከኞች ብቻ በሚል መታለፋቸው ያስቆጫል።
በጣም የሚገርመው ግን እነዚህ የክፋት ስም ተካዮች ቀድመው አስበውበት የገቡበት ነው ለማለት ትንሽ ያዳግታል። አንዳንዶች ከልጅነታቸው ጀምሮ ፖለቲካ እና ኤሌክትሪክ በሩቁ ብለው ሲሸሹ፤ ሌሎች ደግሞ በድፍረት የተፈጠሩኩት ‹‹ለሥልጣን ነው›› በሚል፤ (በእርግጥ ይህንን ቃል በቃል ላይሉት ይችላሉ)፤ የተፈጠርኩት ለፖለቲካ ነው ብለው ሲዳክሩ፤ የሚዳክሩትና ፖለቲካውን ሲያቦኩ የሚውሉት ለጊዜያዊ ምቹ ህይወት ብቻ የሚመስለን ብዙዎች ነን። ነገር ግን ከዛ በላይ ስማቸውን ለመትከል የሚዳክሩና ሲያቦኩ የሚውሉ ፖለቲከኞችም የትየለሌ ናቸው።
ፖለቲካውን በማቡካታቸው ሂደት ስማቸው በምን መልኩ እንደሚተከል ሳያስተውሉና ለዛም እርግጠኛ ሳይሆኑ በቀበሌም ሆነ በወረዳ በአንዱ ክፍል ሥልጣን ይቆናጠጣሉ። ያው ሥልጣኑ ከታች የሚጀምር ቢሆንም፤ በሥልጣናቸው ጎድሎብኛል ብለው የሚስቡትን የኢኮኖሚ ችግር በሙሉ በፖለቲካ ስም ያሟላሉ። ከዛ ደግሞ የሥልጣን ሥሯን ከያዙ ‹‹የነብር ጭራን ከያዙ…›› እንደሚባለው ይሆንባቸውና ተሟሙተው እየሸረቡ እና ከጎናቸው ያለውን የሚያሰጋቸውን በነገር ጉንጉን እየጠለፉ፤ ወደ ላይ ይንጠለጠላሉ። ጠለፋው ከግለሰብ ያልፍና ወደ ህዝብ ያድጋል፤ ምክንያቱም እነርሱ በምንም መልኩ ስማቸውን መትከል ይፈልጋሉና።
ህዝብ ሲጠለፍ አንድ ግለሰብ ሳይሆን፤ ብዙሃኑ ይጎዳል። የእነርሱ የሥልጣን እርካታን እስካረጋገጠ ድረስ አይከፋቸውም። ስም ተከላው በክፋት መሆኑ እያደገ ሲመጣ፤ ግለሰብን በነገር ግምገማ ራሱን አስተው እንደሚያልፉት ሁሉ፤ ህዝብንም በተለያየ መልኩ እያወናበዱ ግራ ያጋቡታል። መነሻቸው ከራሳቸው ጥቅም ያልዘለለ በመሆኑ፤ የህዝብ ጥቅም ብሎ ነገር አይታወሳቸውም፤ አፋቸው ስለህዝብ ጥቅም ቢናገርም ልባቸውና ተግባራቸው ግን በስግብግብነት ታውሮ ዝርፊያም ላይ ይዘምታሉ። ባለሥልጣን ማለት ከሕግ በታች መዋል ያለበት አንድ ሰው መሆኑን ጭራሽ ይረሱታል።
የሕዝብን ገንዘብ በመዝረፍ የዜጎችን ህይወት ከማክበድ በዘለለ፤ ማሳሰርና ማሰር፤ መግደልና ማስገደል የቀን ተቀን የህይወታቸው አካል ያደርጉታል። ከራሳቸው አልፈው ግብራበሮቻቸውን በአካባቢያቸው በመደርደር፤ በብልጠት የተጠቀሙበትን የነገር መስመርና የሥርቆት ጎዳና ለሌሎችም ያሳያሉ። ሕዝብ በርሃብ ቢራገፍ በጦርነት እየተቆላ ቢነጠፍ የዓይናቸውን ጉድፍ ያህል አይከብዳቸውም።
ፍትህ እና እኩልነትን አይሰብኩም። ዓላማቸው ሥልጣን ብቻ በመሆኑ ያመኑትን ተወላጅ ሰብስበው ‹‹እኛ የተለየን ዘሮች ነን። ወርቅ ዘሮች፤ ደማችን የነጠረ ነው›› ይላሉ። ደጋፊ የሚያሰባስቡት ልዩነት የሚፈጥሩት በዘር ነው። ሥልጣናቸው ላይ አንዳች ጥያቄ የሚነሳ ከመሰላቸው የተለየን ዘሮች በመሆናችን ከሌሎች መነጠል አለብን ይላሉ። ይህንን የመነጠል ጉዳይን የሚያነሱት ከራሳቸው ጥቅም አንፃር ብቻ ነው።
መነጠልና መገንጠልን የሚያነሱት ሌሎች ሥልጣን ቋማጮችም ጭምር ናቸው። የሆነው አካባቢ ሲነጠል ሥልጣን አገኛለሁ ብሎ የገመተ መነጠልና መገንጠልን ያቀነቅናል። ጥያቄው ቆሜለታለው በሚለው ህዝብ ላይ የበለጠ ድህነት፣ ስቃይና መከራን እንደሚያመጣና እንደማይጠቅም ቢገምትም፤ ሰው ያለሰው እንደማይኖር ቢታወቅም የእነርሱ ስግብግብነት ሚዛን ይደፋል። ድርን ያክል ስስ ነገር ሲያብርና ሲበዛ አንበሳ እንደሚያስር ከልጅነታቸው ጀምሮ ሲነገራቸው ቢቆይም፤ ልቦናቸው እያወቀ ህልማቸው ከሥልጣን ያልዘለለ በመሆኑ የትኛውንም መንገድ በመጠቀም ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ጥረት ያደርጋሉ። በጠመንጃ ጉልበት ሰው እያስበረከከ በመግደል ዘር እያጠፋ፤ አገር እየገፋ ስማቸውን በክፉ በመትከል እስከ መጨረሻው ይቀጥላል።
ዓላማቸው መነጠልን ማዕከል ሲያደርጉ ‹‹እኛ መገንጠል አለብን›› የምትሉት፤ በመገንጠል ውስጥ ህዝቡ ምን ያተርፋል? የሚለውንና ባለመገንጠል ምን ይገኛል? የሚለውን በመተንተን ተጨባጭ የህዝብ ጥቅም ልዩነቶችን ሳያስቀምጡ፤ ለሚያቀርቡት ሃሳብ በዘር የታጠሩ ሰዎች ድጋፍ ይሰጧቸዋል። አጨብጭቡ ሲባል ከማጨብጨብ በዘለለ በመነጠል ውስጥ ምን ጥቅም እናገኛለን? ምን እናጣለን? ለምን መነጠል አስፈለገና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በዘር የታጠሩት ሰዎች ጥያቄውን አያቀርብም። ሁላቸውም ዘረኞች የራሳቸውን እያሞካሹ፤ ይመፃደቃሉ። በእርግጥ አንዳንዱ ‹‹ተለይቶ ተጠቅተናል›› በሚል ስሜት በንፁህ ልብ ሲደግፍ ከበስተጀርባ የሚፈጠረው ችግር አይታየውም። በዚህ መልኩ ባለማስተዋል እንደጎርፍ ተግተልትሎ የሚነጉደው ብዙ ነው።
በዚህ ሁሉ ሁኔታ ውስጥ በተጨማሪ ባሉት ፖለቲከኞች ዘንድ ቀናነትና ለመልካም ሥራ ፅናት ባለመኖሩ ለውጥ ማምጣት አዳጋች ነው። በስንፍናው እና እርሱ የሌሎችን መብት በመግፈፉ ወይም ጥፋት በመፈፀሙ ሲጠየቅ ‹‹የእዚህ ብሔር ተወላጅ ስለሆንኩ ነው፤ ዛሬ ይህ ስለሆነ ነው›› ብሎ ደረቅ ሮሮ የሚቀርብ ከበዛ ከባድ ነው። በእርግጥ እንኳን ፖለቲከኛ አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን ቀርቶ፤ ማንኛውም ሰው ‹‹የእዚህ ብሔር ተወላጅ ስለሆንኩ ተጠቃሁ›› ባዩ፤ ‹‹መጠየቄ ተገቢ አይደለም›› ብሎ መከራከር መብቱ ነው። እኩል አልታየሁም ካለም ‹‹እኩል መታየት አለብኝ›› የሚል ጥያቄ ማቅረብ ይችላል።
ነገር ግን ሁሉንም ነገር በዘር መነፅር እያየ እያጣመመ ጀሌ ካስከተለ እና ፖለቲከኛው እንገንጠል ካለ ጉዳዩ ዞሮ ስምን በክፋት ከመትከል ጋር ይጣበቃል። እርሱ ብቻ ሳይሆን ደጋፊዎቹም እንደወንዝ ወራጅ ውሃ ዝም ብለው ከፈሰሱ፤ በምክንያት ካልተመሩ በክፋት ስም ተካዮች ሳቢያ አገር ፈረሰች ማለት ነው።
ህዝብን ማስተዳደር ቀላል አይደለም። አገር እንደተወጠረ ቆዳ ለመተር ተር አጣብቂኝ ውስጥ የገባችው እንኳን ህዝብን ቤተሰቡን በቅጡ የሚያስተዳደር በመጥፋቱ ነው። እርግጥ ነው፤ የልዩነት ግድግዳን አፍርሶ የአንድነት ድልድይ ከመሥራት ይልቅ ሜዳ ላይ የማይጠቅም ግንብ በመገንባትና፤ የሰዎች መቀበሪያ ጉድጓድ እየቆፈሩ አንድ የሆነውን ህዝብ ወደ ብሔርና ወደ ዘር፣ አልፈው ተርፈው ወርደው ወደጎሳ በማውረድ የተካኑ ሥልጣን ላይ የሰነበቱና ወደ ፊትም ሥልጣን እየፈለጉ ያሉ ሰዎች የበዙበትን አገር ማስተዳደር እጅግ ከባድ ነው።
ነገር ግን ዛሬም ቢሆን የክፋት ስም ተካዮች ህዝቡን በወረዳና በቀበሌ እየለዩ እርስ በእርስ እያነጣጠሉ እያገዳደሉ በቆፈሩት ጉድጓድ የሚቀብረውንና የሚቀበረውን ሰው የሚያደራጁ የክፋት ጥግ ፖለቲከኞች መኖራቸውን መካድ ከሃቅ መሸሽ ነው። እውነተኛ ፖለቲካ ዘር አያይም። የማንም ዘር ተወላጅ መጠሪያው የትኛውም ብሔር ቢሆንም በየትኛውም ዘር ላይ የሚፈፀም ጥቃት የሚያስቆጨውና የሚያንገበግበው ነው። ስለዚህ በመልካም ተጠርቶ ሞቶም ህያው ለመሆን መሰረታዊው መንገድ ስለሁሉም ጥቅም መቆም፤ የሁሉንም ጉዳት እንደራስ ጉዳት በመቁጠር ማንም ቢሆን እንዳይጎዳ ስለሁሉም መቆርቆር፤ ተቋማት ዘር ሃይማኖት ሳይሉ ለሁሉም እኩል እንዲያገለግሉ፤ የሞያ ማህበራት፣ የሃይማኖት ተቋማትና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ከፖለቲካ ነፃ እንዲሆኑና ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ መንገድ መጥረግ የቻለ እውነተኛ ፖለቲከኛ፤ ስሙን በመልካም ተከለ ማለት ነው።
ላለፉት ሃምሳ ዓመታት ስለእኩልነት የታገሉ፤ ለሥልጣን ያልታደሉ ተቆጥረው የማያልቁ ወጣቶች በፅናት ለፍትህና ለእኩልነት ሲሉ ተሰውተዋል። ታስረው እስር ቤት ከመወርወር አልፈው ህይወታቸው ሲያልፍ ህልማቸው እውን ሆኖ ሳያዩ፤ ድካማቸው አብሮ መክኗል። አሁን የሥልጣን ዕድሉን ያገኙ ፖለቲከኞቻችን ከሕግ በላይ ሳይሆን ከሕግ በታች ሆነው፤ ህዝብን አገልግለው ስለህዝብ በመቆም፤ ታግለው እነዛ የተሰው እልፍ ወጣቶች የቆሙለትን ዓላማ በማሳካት ስማቸውን በበጎ መትከል ይገባቸዋል። ዕድሉን በመጠቀም መልካም መሥራት በየዕለቱ ከሚሰጠው የህሊና እርካታ ባሻር በታሪክ እየተዘከሩ መወደስን የሚያስከትል በመሆኑ ሁሉም ፖለቲከኛ ከሥልጣኑ በላይ ለህዝብ ጥቅም ቅድሚያ ይስጥ!
ስለእውነተኛ የህዝብ ተጠቃሚነት የታገለ ፖለቲከኛ ዛሬ ስሙ ቢደበቅም ቆይቶ መታወቁና በህዝብ ዘንድ ከበሬታን የሚያገኝ መሆኑ ስለማይቀር ስለዕውነት በፅናት የምትታገሉ ፖለቲከኞች በርቱ። ኢትዮጵያ ፍትህ የሰፈነባት፤ ሁሉም በእኩልነት የሚጠቀምባት፣ ያደገችና የጠነከረች አገር እንድትሆን አደራ እንላለን! አሁንም ቢሆን በአንዳንድ አካባቢዎች የሚካሄድ ዘር ተኮር ግድያ እንዲቆም ትልቅ መስዋትነት ቢጠይቅም ማስቆም የግድ ነውና የንፁን ዜጎች ግድያ ይቁም። ዘረኞችና ክፉ አድራጊዎች ቀና በማለት ደረታቸውን ነፍተው የሚሄዱበት ጊዜ ያብቃ። ይህ እንዲሆን መላው ፖለቲከኛ እና ባለሥልጣን ግዴታውን ይወጣ፤ ክፉ አድራጊዎች ውሎ አድሮ አንገታቸውን አቀርቅረው መሄዳቸው አይቀርምና በህይወት ኖረው በግፋቸው አቀርቅረው ሲሄዱ ወደ ላይ እያየች የምትታዘባቸው መሬትም እነሱን ለመቀበል እምቢ ማለት ባትችልም፤ በምድሯ ላይ ያሉ ሰዎች ስግብግብና ዘረኛ ፖለቲከኞችን ሲወቅሱ ስለሚኖሩ አሁንም በማስተዋልም ሆነ ባለማስተዋል እንዲሁ አስበውትም ሆነ ሳያስቡት በተለያየ መልኩ ስማቸውን እየተከሉ ያሉ ፖለቲከኞች ሊያስተውሉ ይገባል እንላለን። ሰላም!
አዲስ ዘመን መጋቢት 9 ቀን 2013 ዓ.ም