ይበል ካሳ
የዛሬ ስድስት ዓመት ከመንፈቅ አካባቢ በ2005 ዓ.ም የወጣው «አደጋን የሚቋቋም፣ አረንጓዴና ተደራሽ የከተሞች ልማት ፖሊሲ» ከጽዳትና ውበት ችግር እንዲሁም የአየር ንብረት ብክለት ጋር በተያያዘ ለኑሮ ምቹ አለመሆን ለከተሞች ዕድገት ዋነኛ ችግር መሆኑን አስቀምጧል። በዚህ ረገድ ፖሊሲው በተለይም «የኢትዮጵያ ከተሞች ችግሮችና የፖሊሲው አስፈላጊነት» በሚል በመጀመሪያው ክፍል ላይ «የልማት ችግሮች» በሚለው ንዑስ ርዕሱ ሥር ከዘረዘራቸው ስድስት ነጥቦች መካከል አንዱ የመዝናኛ ቦታዎች እጥረትና የአካባቢ ብክለት ችግር ነው። ሥርዓት ያለው ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃና የተከለሉ አረንጓዴ ቦታዎችና በቂ የመዝናኛ ማዕከላት የሌለው አከታተም ሰፍኖ ከመቆየቱም በአሻገር አብዛኞቹ ከተሞች በርካታ ያረጁ ሰፈሮች ያሉባቸውና በህገ ወጥ ግንባታ ደረጃቸውን ያልጠበቁ ቤቶች የተስፋፉባቸው መሆናቸውን ይጠቅሳል። ይህም ከተሞች ሥርዓት ያጡና የተበከሉ እንዲሆኑ በማድረጉ ለኑሮ ተስማሚ እንዳይሆኑ እያደረጋቸው በመምጣቱ እነዚህንና ሌሎች መሰል ችግሮችን ለመፍታት ፖሊሲው አስፈላጊ መሆኑን ያትታል።
በተለይም በደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻዎች አያያዝና አወጋገድ እንዲሁም ከከተሞች ጽዳትና ውበት አረንጓዴ ልማት ጋር በተያያዘ ከተሞች ያሉበት ነባራዊ ሁኔታ አሁንም ቢሆን ዝቅተኛ መሆኑን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴርና ከአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን የተገኙ መረጃዎች ያመላክታሉ። ከአራት ዓመታት በፊት «በከተሞች ጽዳትና ውበት ሥራዎች ላይ የተገኙ ውጤቶችና ተግዳሮቶች» በሚል ርዕስ በቀድሞው የአዲስ አበባ የአየር ንብረት ለውጥ መቋቋሚያ ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ተሾመ የተሰራ ጥናታዊ ጽሑፍ እንደሚለው ከከተሞች የሚወጡ ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻዎች በዘፈቀደ በየቦታው ይጣላሉ። በመሆኑም ከከተሞች የሚወጣው ቆሻሻ በአግባቡ ባለመያዙና ባለመወገዱ ከየቤቱ በሚወጡ ከፍተኛ የመበከል አቅም ባላቸው ደረቅ ቆሻሻዎችና ከጤና ተቋማትና ከኢንዱስትሪዎች በሚለቀቁ ፈሳሽ ቆሻሻዎች አማካኝነት አፈር፣ አየርና ውሃ እየተበከሉ በመሆናቸው የሰው ሕይወትና አጠቃላይ የአካባቢ ህልውና አደጋ ላይ ወድቋል። ይህም የከተሞችን ኑሮ አሳሳቢ እያደረገው መጥቷል።
አካባቢን በንጽህና አለመጠበቅ በኅብረተሰቡ ላይ የሚያስከትለውን የጤና ቀውስ በተመለከተ በተለያየ ጊዜ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሚሰሩ ጥናታዊ ጽሑፎች በበኩላቸው በአገሪቱ ከሚከሰቱ በሽታዎች መካከል ከስልሳ እስከ ሰማንያ በመቶ የሚሆኑት በአብዛኛው አካባቢ በአግባቡ ባለመጠበቁ ምክንያት በንጽህና ጉድለት የሚመጡ በሽታዎች መሆናቸውን ይገልጻሉ። በተለይም በከተሞች አካባቢ ቆሻሻ በየቦታው እየተጣለ በመሆኑ በአገሪቱ በከፍተኛ ደረጃ ኅብረተሰቡ እየታመመባቸውና እየሞተባቸው የሚገኙት አስር ዋና ዋና ገዳይ በሽታዎች እንደ ተቅማጥና የሆድ ትላትል የመሳሰሉ ከግልና ከአካባቢ ብክለት ጋር የተያዙ በሽታዎች ባለፉት ሦስት ተከታታይ ዓመታት የተደረጉ ጥናቶች ያመላክታሉ።
ከጽዳትና ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ተያይዞ በከተሞች አካባቢ እየተከሰተ ያለው ችግር በዋነኝነት ሁለት መሠረታዊ ምክንያቶች መሆኑን የሚያመላክቱት የጤና ሚኒስቴር ጥናቶች፡- እነዚህም ከኋላ ቀርነትና ከዕድገት ጋር የሚገናኙ ችግሮች ናቸው ይላሉ። ቆሻሻን በአግባቡ ማስወገድ ባለመቻሉ የሚፈጠረው የአካባቢ ብክለት ችግር ከኋላ ቀርነት ጋር የተያያዘ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ከፋብሪካዎችና ኢንዱስትሪዎች በሚወጡ በካይ ጋዞችና መርዛማ ፈሳሽ ኬሚካሎች አማካኝነት ከዕድገት ጋር ተያይዞ የሚመጣ ብክለት ነው። በመሆኑም በእነዚህ መሠረታዊ መንስኤዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ ከተሰራ ችግሩን ከስሩ ለመፍታት እንደሚያስችል ምክረ ሃሳባቸውን ያካፍላሉ።
በአጠቃላይ በቆሻሻና አካባቢ ብክለት በኩል ያለው ሁኔታ በበርካታ የሀገሪቱ ከተሞች ውስብስብ ችግሮችን እያስከተለ መሆኑን በጉዳዩ ላይ የሚሰሩ አካላት ሁሉ የሚስማሙበት ሃቅ ነው። በተለይ በአዲስ አበባ ያለው ደግሞ እየተባለ ካለው በላይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን መረጃዎች ያመላክታሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ ሥር ነቀል ለውጥ ማምጣት ካስፈለገ እንደ ሌሎች ጉዳዮች ሁሉ ለአካባቢ ጥበቃም ትኩረት እንዲሁም በከተማም ሆነ እንደ አገር የአካባቢ ደህንነትን ለማስጠበቅ ከከፍተኛ አመራሩ ጀምሮ የፖለቲካ አመራሩ ቁርጠኝነት አስፈላጊነትም በጉዳዩ ላይ የተሰሩ ጥናቶች በመፍትሔ ሐሳብነት ይጠቁማሉ።
በዚህ ረገድ ይህንን ሥራ የሚመራና በከተሞች ጽዳት፣ አካባቢ ጥበቃና አረንጓዴ ልማት ዙሪያ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ከስልጠና፣ ከክትትልና ድጋፍ፣ ከሕግ ማዕቀፍና ሥነ ዝግጅት አኳያ የተቀናጁ ሥራዎችን የሚሰራ «የከተሞች አየር ንብረት ለውጥ መቋቋሚያ ቢሮ» የሚባል አደረጃጀት በፌዴራል ደረጃ መቋቋሙም የሚታወስ ነው። ክልሎችም ይህንን ተከትለው የራሳቸውን አደረጃጀት በመተግበር ላይ ይገኛሉ። ለጉዳዩ የፖለቲካ አመራሩ ቁርጠኝነት አስፈላጊነት በተመለከተም ባለ ድርሻ አካላትን ከማሳተፍና የሕዝብ ንቅናቄ ከመፍጠር አኳያ «ጽዱ፣ ውብና አረንጓዴ ከተሞች ለህዳሴያችን» በሚል መሪ ሃሳብ በ2008 ዓ.ም በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መሪነት 3400 ሰዎች የተሳተፉበት የንቅናቄ ሥራ መሰራቱም በመልካም ጅምርነት የሚታይ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ያስታውሳሉ።
ከዚህ አኳያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ እንደ መንግሥት ብቻ ሳይሆን እንደ ግለሰብ ጭምር ለጉዳዩ የሰጡት ልዩ ትኩረትና እያከናወኗቸው ያሉ መጠነ ሰፊ ተግባራት በዘርፉ ትልቅ መነቃቃትን ከመፍጠሩም በአሻገር አመርቂ ውጤቶችንም ማስመዝገብ ጀምሯል። ይህም ከተሞች አሁን ካሉባቸው ችግሮች ተላቀው ለኑሮ የሚመቹ፣ ጽዱ፣ ውብና አረንጓዴ መሆን «ችግሩን ለመፍታት የከፍተኛ አመራሩ ትኩረትና ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው» የሚለውን የአጥኚዎች ምክረ ሃሳብ በከፍተኛ ደረጃ ወደ ተግባር እየለወጠ የሚገኝ በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከሚያስመሰግኗቸው ተግባራ መካከል በግንባር ቀደምነት እየተጠቀሰላቸው ይገኛል። በዚህ ረገድ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሃሳብ አመንጪነት በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወኑና እየተከናወኑ ያሉት ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክቶች የሀገሪቷን ገፅታ ከመገንባት ባለፈ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች ያሏቸውና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውቸውም የጎላ መሆኑን እየተመለከትን ነው።
ኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃን ጉዳይ ሕገ መንግሥታዊ አድርጋ፤ ፖሊሲ፣ ስልትና ፕሮግራም አዘጋጅታ በርካታ ተግባራትን እያከናወነች የምትገኝ አገር ናት። ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ በአስር ዓመቱ መሪ የልማት ዕቅድ ውስጥ ከተለዩ አብይ ምሰሶዎች ውስጥ አንዱም ነው። በመሆኑም የሙቀት አማቂ ጋዞችን ልቀት ለመቀነስና የአየር ንብረት ለውጥ ተፅዕኖን ለመቋቋም የሚያግዙ የኢኮኖሚ ልማቶች ያላቸው ሚና ከፍተኛ ነው። ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ የላቀ አስተዋፅኦ ያላቸው አረንጓዴ ልማቶችና አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት ቀዳሚ የሆነውን የቱሪዝም ዘርፉን በማዘመን ከዘርፉ ተጠቃሚ መሆን የሚቻልበትን ዕድል በመፍጠር ረገድ የሀገሪቱ መዲናና የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫ በሆነችው አዲስ አበባ የተከናወኑትና በመከናወን ላይ ያሉት ሸገርን የማስዋብ ሜጋ ፕሮጀክቶች የሚኖራቸው ፋይዳ በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ፕሮጀክቶቹ የአገሪቷን ገፅታ ከመገንባት ባለፈ ዘርፈ ብዙ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎችንም ማበርከት ይችላሉ። ኢትዮጵያ በያዘችው የአሥር ዓመት መሪ ዕቅድ ከቱሪዝም ዘርፉ ብቻ 23 ቢሊዮን ብር ለማግኘት ያለመች መሆኑ ይታወቃል። ለዚህም ሸገርን የማስዋብ ዓይነት ትላልቅ ፕሮጀክቶች ከፍተኛ ድርሻ ይኖራቸዋል ተብሎ ይታሰባል። ምክንያቱም የዓለም ሦስተኛዋ የዲፕሎማሲ ማዕከል በሆነችው አዲስ አበባ በተገነቡትና እየተገነቡ ባሉት ትልልቅ የመናፈሻ ፓርኮችና አረንጓዴ የከተማ ልማቶች ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ቱሪስት ወደ ሀገር ውስጥ በመሳብ ባህላዊና ቁሳዊ የሆኑ ባህሎችን ማሳየትና የቱሪዝም ገቢን ከፍ በማድረግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ መሆን የሚቻልበት ሰፊ ዕድል በመኖሩ ነው። ፕሮጀክቶቹ ለቱሪዝም ዘርፉ ከሚያበረክቱት አስተዋፅኦ በአሻገር ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠርም እንደቻሉ የሚያሳዩ መረጃዎች አሉ። በእንጦጦ አካባቢ እንጨት በመሸከም ኑሯቸውን ሲገፉ የነበሩ የበርካታ እናቶችን ሕይወት የሚቀይር ዕድል መፈጠሩም ለዚህ ጥሩ ማሳያ ይሆናል። ይህም ፕሮጀክቶቹ ከሚያስገኟቸው ዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዎች መካከል በዋናነት የሚጠቀስ ፋይዳ ነው። በዚህም የሥራ አጥ ቁጥሩን በመቀነስ ዜጎች እራሳቸውን በኢኮኖሚ መደገፍ የሚችሉበትን ሁኔታ ያግዛሉ። ዜጎች እራሳቸውን በኢኮኖሚ እያጎለበቱ ሲመጡ መንግሥትም ከዜጎች በሚሰበስበው ታክስ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚ እንደሚሆን እና ፕሮጀክቱ ለሀገሪቷ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ዘርፈ ብዙ መሆኑንም የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ያመላክታሉ።
ከዚህ በአሻገርም በዘርፉ ካለው ተሞክሮ አኳያ ኢትዮጵያ መስራት አትችልም የሚለውን በውጭ ዓለም ያለውን እሳቤ መቀየር የሚችልበት አስተሳሰብ እንደሚፈጥርም በጉዳዩ ላይ ለአዲስ ዘመን ሃሳበቸውን የሰጡት የኢኮኖሚክስ መምህሩ ዶክተር ወንዳፈራሁ ሙሉጌታ ያመላክታሉ። ለዚህም ስድስት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ፕሮጀክቶች ዕውን ሆነው ማየት በራሱ ኢትዮጵያ መስራት እንደምትችል በትልቅ ማሳያነት ያነሳሉ። በቀጣይ የታቀዱትን ፕሮጀክቶችም ማሳካት እንደሚቻልና የገቢ ምንጭ ለመፍጠር አቅም እንደሚሆኑም የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ይናገራሉ። ይህ በአዲስ አበባ የተጀመረው ሸገርን ማስዋብ ፕሮጀክት ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች የሚሰፋበት ሁኔታም ተፈጥሯል። ለአብነትም ከአዲስ አበባ ልምድ በመውሰድ የሃዋሳ ከተማም ሃዋሳን የማስዋብ ፕሮጀክት መጀመሩን በቅርቡ አስታውቋል። የጎንደር እና የአምቦ ከተማ ከንቲባዎችም በአዲስ አበባ ከተማ እየተሠሩ ያሉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀከቶችን መጎብኘታቸውና በእነርሱ ዘንድም ተመሳሳይ ተነሳሽነት እንደፈጠረባቸው መግለጻቸው ይታወሳል።
ከዚህ ሁሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ በአሻገር ደግሞ ጽዳትና ንጽህናን አካትቶ እየተተገረ የሚገኘው ሸገርን በማስዋብ የተጀመረው ከተሞችን የማስዋብ ፕሮጀክት ከፍ ያለ በራስ መተማመን ለመፍጠርና በዓለም ፊት በክብርና በኩራት ቀና ብሎ ለመሄድ ያስችላል። ከተሞቻችን ጽዱ ቢሆኑ ብሔራዊ ኩራታችን ይሆናሉ። ለአብነት የአፍሪካውያን መዲና፣ የበርካታ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ የሆነችው አዲስ አበባችን የእኛ ብቻ ሳትሆን የመላ አፍሪካውያንም መለያ ምልክት ተደርጋ ትቆጠራለች። ይሁን እንጂ አዲስ አበባችን ከስሟ፣ ከታሪኳና ከማዕረጓ ጋር የሚመጣጠን ንጽህና የላትም በሚል በሰፊው ስትታማ ኖራለች። ሃሜቱ እውነትም ነው። ምክንያቱም አሁንም ድረስ ከተማችን ላይ ቆሻሻ የትም ቦታ ይጣላል፣ በየአውራ ጎዳናው ሽንት ይሸናል፣ ደረጃውን የጠበቀ የፍሳሽ ማስወገጃ ሥርዓት የሌለ በመሆኑ በየአካባቢው ቱቦ እየፈነዳ የሚወጣው መጥፎ ጠረን የእኛንም ሆነ አክብረውን የሚመጡ ዓለም አቀፍ እንግዶቻችንን ያስቀይማል። የቆሻሻ አወጋገዳችንና የንጽህና አጠባበቃችን ሥርዓት ባለመያዙ ከከተማችን የሚወጣው መጥፎ ጠረን አካባቢያችን አይደለም እንዲሸት የሚያደርገው፤ ስማችንንም ያሸታል።
የአዲስ አበባ የማስዋብ ጉዳይ ከዚህም አልፎ ሌላ አንድምታ አለው። ምክንያቱም ቆሻሻ ከተማ ለአፍሪካውያን መቀመጫ አይሆንምና ዋና ከተማነቱ ለእኛ ይገባናል ተብሎ ክርክር ቀርቦብንም ያውቃል። ዳሩ በንጽህናችን ሳይሆን በአኩሪው ታሪካችን ማዕከልነታችንን አስጠብቀን ቀጥለናል። እናም በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ የአፍሪካውያን የኩራት ምንጭ የሆነችውን ታላቋን የነጻነት ከተማ አዲስ አበባን ለማስዋብ ቆርጠው መነሳታቸው ሸገርን የማስዋብ ብቻ ሳይሆን ለታላቋ አገር የሚመጥን ክብርና ስምን የማስቀጠል ጉዳይ ነውና ይበል የሚያሰኝ ነውና ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል እያልን የዛሬውን በዚሁ አበቃን። ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!
አዲስ ዘመን መጋቢት 9 ቀን 2013 ዓ.ም