የሆቴልና ጥምር ግብርና ኢንቨስትመንት ባለሀብቱ የቀድሞው መምህር

ሥራን አሐዱ ያሉት በመምህርነት ነው፤ በዚህ ሙያም ለ19 ዓመታት አገልግለዋል:: የሕግ ትምህርት በመማር የጥብቅና ሙያን ተቀላቅለው ለ13 ዓመታት የክስ መዝገቦችን አገላብጠዋል:: አጠቃላይ ግብርና በሚል የትምህርት መስክ የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝተዋል:: ኑሯቸውን ለማሻሻል አጥብቀው የሚተጉት እኚህ የዛሬው የስኬት ገጽ እንግዳችን ፓስተር ቦጋለ ወልደሃና ይባላሉ::

‹‹የትናንት ጥረትና ጉጉቴ ከትናንት ይልቅ ዛሬ የተሻለ እንዲሆን፤ ነገም ያማረና የሰመረ እንዲሆን በብዙ አግዞኛል›› የሚሉት ፓስተር ቦጋለ በሆቴል፣ በቡና ልማት፣ አዘጋጅነትና ላኪነት የተሰማሩ ባለሀብት ናቸው:: ኑሯቸውን ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ በሀዋሳ ከተማ ያደረጉት ፓስተር ቦጋለ፤ ተወልደው ያደጉት በሲዳማ ክልል፣ አርቤጎና ወረዳ ነው::

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአርቤጎና፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በይርጋለም ከተማ ተከታትለዋል:: ‹‹ትምህርት ለማንኛውም ችግር መፍቻ ቁልፍ ነው›› የሚል ጠንካራ እምነት ያላቸው በመሆኑ ለትምህርት ትልቅ ትኩረት ሰጥተው ተምረዋል::

ከትምህርት ያገኙት ዕውቀትና በመምህርነት ሙያ ያካበቱት ልምድ ሁሌም አብረዋቸው እንዳሉ አድርገው ያስባሉ:: በንባብ፣ በመማርና በማስተማር ሌባ የማይሰርቀውን ዕውቀት ማካበት የቻሉ ቢሆንም፣ በሚፈልጉት ልክ ሕይወታቸውንና ቤተሰባቸውን መምራት ሁሌም ይመኙ ነበር:: ለዚህም ነው ‹‹ሰው የደረሰበት ልድረስ፤ ኑሮዬን ላሻሽል›› በማለት በመምህርነት እየሠሩ የሕግ ከዚያም የግብርና ትምህርት ተከታትለዋል:: በሕግ ሙያ የጥብቅና ሥራ ሠርተዋል::

‹‹የትኛውም መንገድ በእውነትና በዕውቀት ከተመራ አዋጭ ነው›› የሚል ዕምነት ያላቸው ፓስተር ቦጋለ፤ የሕግ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላም ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በዓለም አቀፍ አመራር /International Leadership/ እንዳገኙ አጫውተውናል::

የቀሰሙት እውቀትና የያዙት ሥራ በሚያስገኝላቸው ለውጥ የማይወሰኑት ፓስተር ቦጋለ፣ ይበልጥ እለወጥበታለሁ ያሉትን ኢንቨስትመንት ደግሞ ፈልገው አፈላልገው ተቀላቅለውታል:: ፍለጋና ጥረታቸው ከሆቴል ኢንቨስትመንት ያደረሳቸው ፓስተር ቦጋለ፤ የመረጡት መንገድ ውጤታማ አደረጋቸው እንጂ ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ አላደረጋቸውም::

አብዛኛውን ጊዜያቸውን በመምህርነት ያሳለፉት ፓስተር ቦጋለ፤ ከጥብቅና ሙያቸው ጎን ለጎን ኢንቨስትመንት ላይ በመሰማራት ሆቴል መገንባት ሲያስቡ፤ ከራሳቸው ባለፈ ለሌሎችም የሥራ ዕድል ለመፍጠር በሚል መሆኑን ይናገራሉ::

ከኢንቨስትመንቱ መስክ የመጀመሪያ ምርጫቸውን በሆቴል ኢንቨስትመንት በማድረግ ሀዋሳ ከተማ መናኸሪያ አካባቢ የመጀመሪያውን ሜምቦ ሆቴል ገነቡ:: በወቅቱ አካባቢው ጫካ እንደነበርና ጫካውን መንጥረው፤ መንገድ አውጥተው፤ ሆቴሉን መገንባታቸውን ያስታውሳሉ:: በዚህ የተነሳም አሁንም ድረስ አካባቢው ‹‹ሜምቦ መንገድ›› በመባል ይታወቃል፤ በዚህም ደስተኛ ነኝ ይላሉ::

ከጥብቅና ሙያቸው ጎን ለጎን የጀመሩት የሆቴል ኢንቨስትመንት አዋጭና ተመራጭ መሆኑን ያረጋገጡት ፓስተር ቦጋለ፤ የጥብቅና ሥራቸውን በመተው ሙሉ ትኩረታቸውን በሆቴል ኢንቨስትመንት ላይ በማድረግ ጠንክረው ሠርተዋል::

ከመምህርነት ወደ ጥብቅና ሥራ፤ ከዚያም በሆቴል ኢንቨስትመንት የተሰማሩት ፓስተር ቦጋለ፤ የሆቴል ሥራቸውንም ይበቃኛል አላሉም:: ሆቴሉን ሊደግፍ ይችላል ወዳሉት የግብርናው ዘርፍ አመሩ:: ‹‹የግብርና ሥራ ያደግኩበት ነው›› የሚሉት ፓስተር ቦጋለ፤ ለሥራ ያላቸው ጉጉት፣ ጥንካሬና ብርታት ከገጻቸው ይነበባል::

ለእዚህም በትውልድ አካባቢያቸው አርቤጎና 10 ሄክታር መሬት ላይ ጥምር ግብርናን ዕውን አደረጉ:: በጥምር የግብርና ሥራቸውም ደን በማልማት፣ በእርሻ ሥራ፣ በከብት እርባታ፣ በቡና ልማትና ቡና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ሥራ ተሰማርተዋል::

ከመምህርነትና ከጥብቅና ሙያቸው ባሻገር ኢንቨስትመንትን ከጥምር ግብርና ያዋደዱት ፓስተር ቦጋለ፤ በሃይማኖታዊ ትምህርትም እንዲሁ በሀዋሳ ከተማ አንቱ የተባሉ አገልጋይ ናቸው:: ከሥራቸው ጎን ለጎን በሃይማኖታዊ ትምህርት /ቲዮሎጂ/ ወይም በሥነ-መለኮት የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ናቸው::

በጥምር ግብርናው በተለይም ቡናን ላይ ሰፊ ሥራ እየሠሩ ሲሆን፣ በግላቸው ከሚያለሙት ቡና በተጨማሪ ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጭምር ቡና ሰብስበው ለውጭ ገበያ ያቀርባሉ:: በዓመት በትንሹ 20ሺ ኬሻ የሚደርስ ስፔሻሊቲ ቡና አዘጋጅተው ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርቡ ይገልጻሉ::

በየዓመቱ የሚገኘው የቡና ምርት ከፍና ዝቅ ሊል እንደሚችል ጠቅሰው፣ በትንሽ መጠን ከፍተኛ ገቢ በሚገኝበት ስፔሻሊቲ ቡና ላይም ትኩረት አድርገው እንደሚሠሩ ይናገራሉ:: አካባቢውም ለዚሁ ምቹ መሆኑን ጠቅሰው፣ በግላቸው ከሚያለሙት ቡና በተጨማሪ የአካባቢው አርሶ አደሮች የሚያለሙትን ቡና በመረከብ ለውጭ ገበያ ያዘጋጃሉ::

ፓስተር ቦጋለ የአርቤጎና ጦጋ ደረቅ ቡና አምራችና አቅራቢ የኅብረት ሥራ ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ናቸው:: አካባቢው በስፔሻሊቲ ቡና የታወቀ መሆኑን ጠቅሰው፣ በ2020 ማህበሩ ስፔሻሊቲ ቡና በማቅረብ ሁለተኛና ሦስተኛ ወጥቶ ዓለም አቀፍ ተሸላሚ እንደነበር አስታውሰዋል::

ከመምህርነት ጀምሮ የነበራቸው ጥረት ፍሬያማ ሆኖ ዛሬ ላይ በጥምር ግብርና እንዲሁም በሆቴል ኢንቨስትመንት የተሰማሩት ፓስተር ቦጋለ፤ በመኖሪያ ከተማቸው ሀዋሳ ላይ በሚሠሩ የልማት ሥራዎችም ከፍተኛ ተሳትፎ ካላቸው የንግዱ ማኅበረሰብ መካከል አንዱ ሆነው ይጠቀሳሉ:: ለዚህም የሲዳማ ክልላዊ መንግሥት ሠላምና ፀጥታ ቢሮ በሀዋሳ ከተማና በዙሪያዋ በሚያስገነባቸውና እያስገነባቸው ባሉ ዘመናዊ የፖሊስ ጽ/ቤቶች ያላቸው አበርክቶ አንድ ማሳያ መሆኑን ይጠቅሳሉ:: ከተማዋ ውብ፣ ፅዱና አረንጓዴ እንድትሆን ማኅበረሰቡን በማስተባበር በኃላፊነት እየሠሩ መሆናቸውንም አጫውተውናል::

የኮሪደር ልማቱን ጨምሮ በሀዋሳ ከተማ በርካታ የልማት ሥራዎች እየተሠሩ መሆናቸውን ገልጸው፣ በተለይም በአሁኑ ወቅት በሁሉም አቅጣጫ የሚገነቡት የፖሊስ ጽ/ቤቶች ሙሉ በሙሉ በማኅበረሰቡ ተሳትፎ የሚሠሩ መሆናቸው ማኅበረሰቡ ለሠላም እየከፈለ ያለውን ዋጋ ያሳያል ይላሉ::

እሳቸው እንዳሉት፤ በየአካባቢው ያለውን ሥራ በኃላፊነት እየመሩ ካሉ የከተማዋ ባለሃብቶች መካከል አንዱ ናቸው:: በግላቸውም አንድ መቶ ሺ ብር ወጪ በማድረግ ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን ለእዚህ ዓላማ በማዋል ማዕከሉን እያስገነቡ ይገኛሉ:: እንዲህ አይነት ሥራ በሀዋሳ ከተማ ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር መስፋት አለበት ሲሉ አስገንዝበው፣ ሁሉም ሰው ለሀገሩ እንዲሠራም መልዕክት አስተላልፈዋል::

በሆቴል እና በጥምር የግብርና ሥራቸው በድምሩ 80 ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር እንደቻሉ የሚናገሩት ፓስተር ቦጋለ፤ 35 የሚደርሱ ሠራተኞች በቋሚነት ቀሪዎቹ ደግሞ በጊዜያዊነት የሚሠሩ እንደሆኑ ገልጸዋል:: የቡና ለቀማ ሥራ በርካታ ሠራተኞች የሚፈልግ መሆኑን ጠቅሰው፣ ቡና በሚደርስበት ወቅት በጊዜያዊነት የሚያሠሯቸው የሠራተኞች ቁጥር ከፍ እንደሚል አስታውቀዋል::

ከፈጠሩት የሥራ ዕድል ባለፈ ማኅበራዊ ኃላፊነትን በመወጣት ረገድ ጉልህ አበርክቶ እንዳላቸው ፓስተር ቦጋለ ገልጸዋል:: እሳቸው እንደሚሉት፤ በሚኖሩበት አካባቢ የተቸገሩ ሰዎችን በተለያየ መንገድ ያግዛሉ:: ለአብነትም በገጠር አካባቢ መጠለያ ላጡ መጠለያ በመሥራት፣ ለታረዙ በማልበስ፣ ለተራቡ በማጉረስና ወላጅ አልባ ሕጻናትን በመደገፍና በማስተማር ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ::

ማኅበረሰቡ በቻለው አቅም ያለውን ትርፍ ጊዜ በበጎ ሥራ እንዲያውልና የአካባቢውን ሠላም እንዲጠብቅ ያስተባብራሉ:: መንግሥታዊ ለሆኑ ጥሪዎችም እንዲሁ ምላሽ ይሰጣሉ:: በተለይም በትውልድ አካባቢያቸው አርቤጎና ላይ ከመንግሥት ጎን በመሆን የልማት ሥራዎችን እየሠሩ ይገኛሉ::

በጥምር ግብርና ሥራቸው ከከብት እርባታ ባለፈ ዘንድሮ ብቻ ሦስት ሺ እግር ቡና እንደተከሉ ፓስተር ቦጋለ አመልክተዋል:: አካባቢው ፆም ሲያድር የነበረ መሆኑን አስታውሰው፣ አኩሪ አተር፣ ቦሎቄ፣ እንሰት፣ ድንችና ሌሎች ሰብሎችን እያለሙ እንደሆነ ገልጸዋል::

እንደ ፓስተር ቦጋለ ማብራሪያ፤ ሀገር በቀል ዛፎችን በመትከልም ረዘም ያሉ ዓመታትን ያስቆጠሩ ሲሆን፤ በሦስት ሄክታር መሬት /ተራራ ላይ/ የተከሏቸው ሀገር በቀል ዛፎች በአሁኑ ወቅት ጥቅጥቅ ደን ፈጥረዋል:: ዛፎቹ የአፈር መሸርሸርን በመከላከል ረገድ ለአካባቢው ትልቅ አስተዋፅዖ እያበረከቱ ሲሆን፤ ከዚህ ባለፈም የዱር አራዊቶች ማደሪያ መሆን እንደቻሉ ተናግረው፣ እሳቸውም በአካባቢው ሞዴል አርሶ አደር እንደሆኑም ገልጸዋል::

በአርቤጎና የተከሉት ቡና ማዳበሪያ እንደማያውቅ ጠቅሰው፣ በከብቶች አዛባና በኮምፖስት ብቻ የሚለማ ኦርጋኒክ ቡና መሆኑን አስታውቀዋል:: ይህ በተፈጥሮ ማዳበሪያ ብቻ የሚያለማ ቡና ደግሞ በዓለም ገበያ እጅግ ተፈላጊና የተሻለ ገቢ እያስገኘ መሆኑን አመልክተዋል ::

‹‹የግብርና ሙያ በእጄ በመሆኑ ጥራቱን የጠበቀ ስፔሻሊቲ ቡና ላይ ትኩረት አድርጌ እየሠራሁ ነው›› ያሉት ፓስተር ቦጋለ፤ ቡናውን አድርቀው፣ አስፈልፍለው፣ አበጥረውና ለቅመው ለውጭ ገበያ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል::

በግላቸው ከሚያለሙት ቡና በተጨማሪ 127 ከሚደርሱና በማኅበር ከተደራጁ አርሶ አደሮች ጋር በጋራ ይሠራሉ:: እነዚህ አርሶ አደሮች ያለሙትን ቡና ገዝተው ደረጃውን በጠበቀ መንገድ አዘጋጅተው ለውጭ ገበያ ያቀርባሉ:: በግላቸው የሚያለሙት ቡና በመጠን ያነሰ ቢሆንም፣ በዙሪያቸው የሚገኙ አርሶ አደሮችን በመደገፍ ጥራቱን የጠበቀ ስፔሻሊቲ ቡና ማልማት እንዲችሉ የበኩላቸውን ጥረት በማድረግ ጥራቱ የተጠበቀና ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ይተጋሉ::

‹‹ሰው ራዕይ ካለውና በታማኝነት ለፍቶ ጥሮ ግሮ ከሠራ ስኬት ከእርሱ ጋር ነች›› የሚሉት ፓስተር ቦጋለ፤ ታማኝነት ውጤታማ ለመሆን ወሳኝ እንደሆነ ይናገራሉ:: እሳቸው እንዳሉት፤ ሀገሪቷ ብዙ ሃብት ያላት በመሆኑ ሰዎች አስበውና ጥናት አድርገው በታማኝነትና በጥረት መሥራት ከቻሉ ካሰቡት መድረስ ይችላሉ:: ‹‹እኔም ሰው የደረሰበት መድረስ አለብኝ:: ኑሮዬን ማሻሻልና መለወጥ አለብኝ በማለት ተስፋ ባለመቁረጥ በብዙ ጥረትና ድካም ዛሬ ላይ ደርሻለሁ›› ሲሉ ገልጸው፣ ሰዎች ተስፋ ሳይቆርጡ ብርቱ ጥረት ካደረጉ ስኬት ከእነርሱ ጋር እንደሆነች አመላክተዋል::

በዋናነት ከሚሠሩት የጥምር ግብርናና የሆቴል ኢንቨስትመንት ሥራ በተጨማሪ ሰዎችን ለመልካም ሥራ በማነሳሳት የሚታወቁት ፓስተር ቦጋለ፤ በቀጣይም ይህንኑ የማስቀጠል ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸውልናል:: በተለይም ለሀገር ሠላም በንቃት በመሳተፍ ትውልዱን መምከርና ወደ ቀናው መንገድ መመለስ ውስጣዊ ፍላጎታቸውና ቀጣይ ሥራቸው እንደሆነ አስታውቀዋል::

ፍሬሕይወት አወቀ

አዲስ ዘመን ህዳር 7/2017 ዓ.ም

Recommended For You