በ60 ሺ ብር መነሻ ባለ 60 ሚሊዮን ብር ካፒታል

በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን ሶዶ ከተማ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝነት በመደራጀት የአንድ ቀን ጫጩቶችን በመረከብ የ45 ቀን ጫጩቶችን ለተጠቃሚዎች ያቀርባል:: የዶሮ ስጋና እንቁላል ልማትም ያካሂዳል።

በወተት ሀብት ልማት ላይም የተሠማራው ድርጅቱ በቀን ከ150 እስከ 200 ሊትር ወተት ያመርታል። የወተት ምርቱን ለአካባቢው ማኅበረሰብና ድርጅቶች ያቀርባል። በግብርናው ዘርፍ ላይ የሚሠራ የትምህርት ተቋም ከፍቶ በዲፕሎማ ደረጃ ትምህርትና ሥልጠና ይሰጣል።

ድርጅቱ ‹‹ኤግዞደስ ፋርም› ይባላል፤ የዚህ ድርጅት ባለቤቶች አምስት ቢሆኑም ድርጅቱ እንዲመሠረት ባለራዕይ በመሆን በ2002 ዓ.ም ከወላይታ ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ የእንስሳት ሕክምና ትምህርት ክፍልን የተቀላቀሉ 24 ተማሪዎች ይጠቀሳሉ። ተማሪዎቹ ዩኒቨርሲቲውን ከተቀላቀሉበት ጊዜ አንስቶ በዚያ እድሜያቸው ትምህርታቸውን ሲያጠናቅቁ ስለሚሠሩት ሥራ በእጅጉ ያስቡ ነበር። በወቅቱ ሕጋዊ ባይሆንም ማኅበር በመመሥረት በዚህ ጉዳይ ላይ በትኩረት መክረዋል።

የ«ኤግዞደስ ፋርም» ዋና ሥራ አስኪያጅና ከድርጅቱ ባለቤቶች አንዱ የሆኑት ተሻለ አላጋው (ዶ/ር) እንዳሉት፤ ተማሪዎቹ በተማሪነታቸው ይህን ያህል እንዲያስቡ ያደረጋቸው ደግሞ በወቅቱ የመንግሥት ሥራ ማግኘት ከባድ መሆኑና ሥራ አጥነት መንሰራፋቱ ነው።

ተማሪዎቹ ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ተመርቀው ቢመለሱ በአንድ ወረዳ ሊያስፈልግ የሚችለው የእንስሳት ሐኪም አንድ ብቻ እንደነበር ታያቸው። በወላይታ ዞን ያሉት ወረዳዎች ደግሞ 12 ብቻ መሆናቸውን ሲያስቡ ነገሮች ይበልጥ ዳገት ሆኑባቸው። እነሱ እስከሚመረቁ ድረስ በእንስሳት ሕክምና የሚመረቁ ተማሪዎች በርካታ ሊሆኑ እንደሚችሉ ሲያስቡም ያሉትም ቦታዎች ሊያዙ እንደሚችሉ ተገነዘቡ፡፡

ይህ ሁሉ ተጨባጭ ሁኔታ ተመርቀው የመንግሥት ሥራ ሊይዙ እንደማይችሉ አስቀድመው እንዲገነዘቡ አደረጋቸው። ሊሆን በሚችለው ሁሉ ተስፋ አልቆረጡም፤ ትምህርቱ ሰፊ መሆኑና በሙያቸው ብዙ ሊሠሩ እንደሚችሉ ሲገነዘቡ ስለመውጫው ወደ መምከር ገቡ።

በጉዳዩ ላይ ለሦስት ዓመታት የመከሩት ተማሪዎቹ፣ ሰፊ ውይይታቸው ሥራ የመፍጠር ሀሳባቸው አሸናፊ መሆኑን አሳወቃቸው። ከሦስተኛ ዓመታቸው አንስተው እያንዳንዱ ተማሪ ለተለያዩ ጉዳዮች ከቤተሰቡ ከሚላክለት ገንዘብ የተወሰነውን በየወሩ ማዋጣት ጀመረ፤ በየእረፍት ወቅታቸውም የገቢ ማስገኛ ሥራዎችን በግልም፣ በቡድንም በማካሄድ ገንዘብ ማጠራቀሙን ተያያዙት። እንደ ክረምት ወቅት ባሉት እረፍቶቻቸውም በጎች እየገዙ በማሞከትና በመሸጥ ገቢያቸውን ማሳደጋቸውን ቀጠሉ። በሦስት ዓመት ውስጥ ያጠራቀሙት ገንዘብ ተመርቀው ሲወጡ ባለ 60 ሺ ብር አደረጋቸው፡፡

በግላቸው ሥራ በመፍጠር ለመሥራት ሲመክሩ የነበሩት እነዚያ ባለራዕዮች ቁጥራቸው በተለያየ ምክንያት ቀንሶ ሁለት ብቻ ቀርተው ነበር፤ ዓላማቸው ግን እንደጸና ቀጠለ። የተቀሩት ሁለት ተማሪዎች እንደተመረቁ በትምህርት ቤት ያገኙትን የእንስሳት ሕክምና እውቀት፣ ሥራን በራስ በመፍጠር የመሥራት ሀሳብንና ያጠራቀሙትን ገንዘብ ምርኩዛቸው አድርገው ራዕያቸውን ለማሳካት ታጥቀው ተነሱ።

በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው በተመረቁበት ሙያ ለመሥራት እንደሚፈልጉ ለሚመለከተው የሶዶ ከተማ የመንግሥት አካል አመለከቱ። ሁለቱ ነባር የማኅበሩ አባላት ሌሎች ሦስት አባላትን አካተው ኢንተርፕራይዛቸውን ኤግዞደስ ፋርምን መሠረቱ።

ማመልከቻቸውም ተቀባይነት አገኘ። ይህ ሁሉ አቅማቸው፣ ጽኑ ፍላጎታቸውና ተነሳሽነታቸው፣ ብዙ ወጣቶች ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ሥራ ሲፈልጉ ዓመታትን በሚያሳልፉበት ሁኔታ እነሱ በዚህ ልክ ዝግጁ ሆነው መገኘታቸው የመንግሥት አካላትን በእጅጉ ማስገረሙን የድርጅቱ ሥራ አስኪያጅ ያስታውሳሉ። በአንድ ወር ውስጥም ሕጋዊ ማኅበር ሆነው፣ ብድርና ቦታም ተመቻችቶላቸው ሥራ መጀመራቸውን ተሻለ (ዶ/ር) ይናገራሉ።

እነ ተሻለ (ዶ/ር) መጀመሪያ ላይ ከብት ማድለብ ላይ ፕሮፖዛል ሠርተው ቢያቀርቡም፣ ይህን ሥራ ለመሥራት የሚያስፈልገው ገንዘብ ወደ አንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን ብር ሆነ፤ መንግሥት ደግሞ ይህን የሚያመቻቸው አልሆነም። ‹‹ለማኅበር እኛ የምንሰጠው ከ50 እስከ 100 ሺ ብር ብቻ ነው፤ በዛ ቢባል ደግሞ 150 ሺ ብር ነው›› የሚል ምላሽ ተሰጣቸው።

እናም የከብት ማድለቡን ፕሮጀክት መቀየር የግድ ሆነ፤ የከተማዋ ከንቲባ በአንድ ቀን ጫጩት ልማት እንዲሠሩ ያቀረቡላቸውን ሀሳብ ተቀብለው፣ የ300 ሺ ብር ብድር ተመቻችቶላቸውና ቦታም ተሰጥቷቸው በቀጥታ ወደ አንድ ቀን ጫጩት ልማቱ ገቡ።

ይህን ሥራ አሀዱ ብለው ሲጀምሩ አራት ሺ ጫጩቶችን ማስገባታቸውን ተሻለ(ዶ/ር) ጠቅሰው፣ በሂደት ከዚህም በላይ ጫጩቶችን ለኅብረተሰቡ እያቀረብን ነው፤ እኛም እንቁላል ጣይ ዶሮ እንዲሁም የሥጋ ዶሮ ማሳደግ ውስጥ ገባን ሲሉ ያብራራሉ።

የሚረከቧቸውን የአንድ ቀን ጫጩቶች በ45 ቀናቸው ላይ ይሸጣሉ። በአራት ሺ ጫጩት የተጀመረው ሥራ በአሁኑ ወቅት በአንድ ዙር እስከ 18 ሺ ጫጩት ወደ ማስገባት መሸጋገሩንም ይገልጻሉ።

በጫጩት፣ በእንቁላልና የሥጋ ዶሮ ልማቱ የሚገኘውን ምርት ከአካባቢዎቻቸውም አልፈው በተለያዩ ክልሎች በሰፊው እያቀረቡ እንደሚገኙም ጠቅሰው፣ በክልል ደረጃም በ45 ቀን ዶሮ አቅራቢነት ድርጅታቸው እንደሚታወቅም ገልጸዋል።

‹‹የኤግዞደስ ፋርም›› ልማት በዚህ ላይ ብቻ እንዳልተወሰነም ነው ዶክተር ተሻለ የሚናገሩት። የዶሮ ኩስም ሌላው የድርጅቱ ገቢ ማስገኛ በመሆን እያገለገለ መሆኑን ያስረዳሉ።

በሌላ በኩል የሚሠሩበት ቦታ ሰፋ ያለ መሆኑ ወደ ወተት ላም እርባታና ወተት ልማት እንዲገቡ አደረጋቸው። በሁለት ላሞች ሥራውን የመጀመረው ድርጅቱ፣ አሁን የላሞቹ ብዛት ወደ ሠላሳ ደርሷል። በዚህም ሰፊ የወተት ምርት እያገኙ ምርቱንም ለአካባቢው ማኅበረሰብ ያቀርባሉ።

በእንስሳት መኖ እና መገልገያ መሣሪያዎችን ለአካባቢው ከብትና ዶሮ አርቢዎች እያሰራጩ መሆናቸውንም ዶክተር ተሻለ ተናግረዋል። ‹‹እኛም ወደ ዶሮ ልማቱ ስንገባ በመኖ አቅርቦት ሳቢያ በጣም እንቸገር ነበር›› ሲሉ አስታውሰው፣ አሁን ከፋብሪካዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ከቢሾፍቱና አዲስ አበባ መኖውን በመረከብ ወደ አካባቢው እንደሚያመጡም ገልጸዋል።

የተቀናጀ ሥራ /ኢንቴግሬትድ የሆነ ነገር/ መሠራት እንዳለበት በማመንም ድርጅቱ ከፈራው ሀብትና ከሙያቸው ባሕሪ በመነሳት በ2014 ዓ.ም የክልሉን ትምህርት ዘርፍ የሚመራውን አካል ፈቃድ በመጠየቅ በግብርና ዘርፍ ላይ የሚሠራ ተቋም አቋቁመዋል። ተቋሙ እስከ ስምንት የሚደርሱ የትምህርት ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ሰፊ የትምህርትና ሥልጠና ሥራ በዲፕሎማ ደረጃ/ከደረጃ አንድ እስከ አራት የሚባለውን/እየሰጠ ይገኛል። በ2016 ዓ.ም ወደ 312 የሚደርሱ ተማሪዎችንም አስመርቋል።

አሁንም ተማሪዎችን በመቀበል የቀለም ትምህርቱን ከተግባራዊ ትምህርት ጋር በማቀናጀት ተማሪዎች እውቀትና ክህሎት እንዲጨብጡ ለማድረግ እንደሚሠራም ተሻለ (ዶ/ር) ጠቅሰዋል።

ከሌማት ትሩፋት ጋር የተያያዘ ሥራ በመሥራታቸው እጅግ በጣም መጠቀማቸውንም ተሻለ (ዶ/ር) አስታውቀዋል። በሌማት ትሩፋቱ መንግሥት ባስቀመጠው አሠራር መሠረት ኅብረተሰቡም ዶሮ ማርባት ይኖርበታል፤ ይህም የዶሮ ምርታችንን ቀጥታ ለመሸጥ የበለጠ ምቹ ሁኔታ ፈጥሮልናል፤ ሁኔታው የበለጠ እንድናመርት የሚያበረታታም ሆኖልናል ብለዋል።

ቀደም ሲል ዶሮ አርብተን በአርባ አምስት ቀናት ለመሸጥ ብዙ አካባቢዎች ላይ መንቀሳቀስ የግድ ይለን ነበር ያሉት ተሻለ (ዶ/ር)፣ የሌማት ትሩፋቱ ምርቶቻችንን ፍለጋ የኛን ክልል ጨምሮ በርካቶች ደጃችን እንዲመጡ እያረጋቸው ነው ሲሉም አስታውቀዋል።

እነ ተሻለ (ዶ/ር)ወደ ቀድሞ ከብት ወደ ማድለብ ሕልማቸው መመለስ በጣም ይፈልጋሉ። ‹‹እኛ እያካሄድናቸው በሚገኙ የልማት ሥራዎች ታዳጊዎች ነን። ገና በጣም መሠረታዊ ነገሮች ያስፈልጉናል። የወተት ልማት ማካሄድ ወይም ላሞችን ማርባት ብቻውን በቂ አይደለም፤ ለእነሱ የሚሆኑ ግብዓቶች ያስፈልጉናል፤ ያፈራነውን ሀብት በአጠቃላይ በዚያ ላይ እናውላለን›› ሲሉ አብራርተዋል።

በዶሮ ልማቱም እንዲሁ ለዘርፉ ሥራ የሚያስፈልጉትን በሙሉ ማሟላት ያስፈልጋል ሲሉ ጠቅሰው፣ ለትምህርት ቤቱም እንዲሁ ሰፋፊ ላቦራቶሪዎችን፣ የመማሪያ ክፍሎችን ለማደራጀት በራሳችን ገንዘብ ስለምንሠራ ያለንን ሀብት በሙሉ በቀጥታ መሬት ላይ የዋለ ነው። በመሆኑም ከብት የማድለብ ሥራውን አሁን ለማካሄድ እንቸገራለን፤ ፍላጎቱ ግን አለን ብለዋል፡፡

እሳቸው እንዳሉት፤ የከብት ማድለብ ሥራ ለራሱ ብቻ የሚሆን ሰፊ ቦታና ግብዓቶችን ይፈልጋል። ያለን ቦታ ግን ውስን ነው። የማድለቡ ሥራ የማስፋፊያ ሥራ ማካሄድን ይፈልጋል። ለራሱ ፕላን በማድረግ ለመሥራት እየታሰበ ይገኛል።

በዶሮና በወተት ልማት አንዱ ይገጥማል ተብሎ የሚታሰበው ችግር የገበያ እጦት እንደሆነ ይገለጸል:: ‹‹ኤግዞደስ ፋርም›› ግን የገበያ ችግር ጨርሶ የለበትም። እስካሁን ጫጩት ማምረት ውስጥ አልገቡም፤ ከሚያመርቱት እየገዙ ለ45 ቀናት እያቆየ ለገበያ እያቀረቡ ናቸው። ‹‹ጫጩት ጠይቀን ለማግኘት ረጅም ጊዜ እንጠብቃለን። እኛ በፈለግን ጊዜ ጫጩት ብናገኝ ኖሮ ብዙ ርቀት በተጓዝን ነበር ሲሉም ያመለክታሉ፡፡.

‹‹ኤግዞደስ ፋርም›› በወተት ሀብት ልማቱም በጣም እየተሠራ ስለመሆኑ ይገልጻሉ። እሱንም ለማስፋፋት ታስቦ በወተት ልማት ላይ ከሚሠራ ከኔዘርላንድ ከመጣ ድርጅት ጋር እየሠራ ነው።

‹‹ድርጅቱ ከመንግሥት ፈቃድ የምታገኙበት ሁኔታ ካለ ለወተት ማቀነባበር የሚያስፈልጉ ማሽኖችንና ግብዓቶችን በቀጥታ እንልክላችኋለን ብለውናል›› ያሉት ተሻለ (ዶ/ር)፣ በዚህ አይነት መንገድ ከሠራችሁ በጣም ጥሩ ደረጃ መድረስ ትችላላችሁ ሲሉም የድርጅቱ ባለሙያዎች ገልጸውልናል›› ብለዋል።

‹‹ኤግዞደስ ፋርም›› በቀን ከ150 እስከ 200 ሊትር ወተት ያመርታል። ምርቱም በአካባቢው ኅብረተሰብ በእጅጉ ይፈለጋል፤ አሁን ለትምህርት ቤት ምገባ ማቅረብ ጀምረናል፤ የኛ ምርት ብቻ ለዚህ በቂ አይደለም። ትላልቅ ሆቴሎችም ከኛ ለመግዛት ይፈልጋሉ፤ በዚህ ላይ የኛም ካፍቴሪያ ወተት ይወስዳል›› ሲሉም ወተቱ ምን ያህል ተፈላጊ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

በአካባቢው ብቻ ከፍተኛ የወተት ፍላጎት መኖሩን በመረዳታቸውም ጠቅሰው፣ ወደ 50 የሚሆኑ ተጨማሪ የወተት ላሞችን ለማስገባት መታቀዱንና ለዚህም ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።

እነ ተሻለ (ዶ/ር) ያሰቡትን ከማሳካት አልፈው በሁሉም የድርጅቱ ተቋማት በጊዜያዊና በቋሚ ሥራ ለ100 የማያንሱ ሠራተኞች የሥራ ዕድል ከፍተዋል። የድርጅታቸውም አጠቃላይ ካፒታል ከ60 ሺ ብር ተነስቶ ከ60 ሚሊዮን በላይ ደርሷል።

‹‹ኤግዞደስ ፋርም›› በእንሳሳት ዘርፍ የጀመራቸውን ሥራዎች ከጥናት ምርምር ጋር በማያያዝ ትልቅ ኢንስትቲዩት የመሆን ራዕይ አለው ሲሉ ጠቅሰው፣ ግብርናው ዘርፍ ላይ ዓለም ዛሬ ከደረሰበት ደረጃ ላይ መድረስ እንፈልጋለን ብለዋል።

በሀገሪቱ ደረጃውን የጠበቀ የግብርና ተቋም በመገንባት የግብርውን ዘርፍ አመራረት በቴክኖሎጂ ለመደገፍ አቅማቸውን አሟጠው ለመሥራት ድርጅቱ ሀሳቡ እንዳለው ጠቅሰው፣ ሰፊ ምርት በማምረት የኅብረተሰቡን ፍላጎት ማርካትም ራዕያቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

ድርጅቱ ማኅበራዊ ኃላፊነትን እየተወጣ መሆኑንም ይገልጻሉ። ምርቶቻችን ማኅበረሰቡን ማዕከል ያደረጉ መሆናቸው፤ የፈጠርናቸው የሥራ ዕድሎች፣ በኮሌጁ በሚሰጡ አጫጭር ሥልጠናዎች ዜጎች በቀጥታ በዚህ ዘርፍ እንዲሠማሩ ለማድረግ እየተከናወነ ያለው ተግባር ማኅበራዊ ኃላፊነትን መወጣት ናቸው ብለን እናስባለን ሲሉ ተሻለ (ዶ/ር) አስታውቀዋል።

ይህን ሁሉ የተሠራው ብዙ ተግዳሮቶች ታልፈው መሆኑን ጠቅሰው፣ የከብት ማድለብ ፕሮጀክታቸው ከፋይናንስ እጥረት ጋር ተያይዞ አለመሳካቱ አንድ ችግር እንደሆነ አመልክተዋል። ችግሩ ሌላ አማራጭ እንዲያዩ እንዳደረጋቸው አስታውቀዋል።

ለሥራችን ፈተና የሆነብን ትልቁ ችግር የካፒታል እጥረት ነው የሚሉት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ ይህን ችግር ለመፍታት ብድር መመቻቸት አለበት ይላሉ። አሁን ድርጅቱ የሚሠራበት ቦታ ሕጋዊ ሆኖ በስማቸው አለመመዝገቡንም እንደ ችግር ጠቅሰው፣ በርካታ ሀብት ያፈሰስንበት ይህ ቦታ በማኅበሩ ስም ቢሆን ሰፊ ገንዘብ አግኝተን ትልቅ ሥራ መሥራት እንችል ነበር ብለዋል።

ለዚህም ፕሮፖዛል አዘጋጅተን ከኛ የሚጠበቀውን ሁሉ አድርገን ከ2014ዓ.ም ጀምሮ ለመንግሥት አመልክተናል፤ ችግሩ እንዲፈታ በተደጋጋሚ መንግሥትንም ጠይቀናል ይላሉ። ይህ ችግር ቢፈታ ድርጅቱ ሰፊ የኢንቨስትመንት ራዕይ እንዳለውም አስታውቀዋል። ከ500 በላይ ሠራተኛ የመቅጠር አቅም አለን ሲሉም ጠቁመዋል፡፡

ለኢንተርፕራይዞች የተሰጠ ቦታ መልሶ የሚወሰድ ስለመሆኑ አሠራር እንዳለ ጠቅሰው፣ እኛ ግን በዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ አይደለንም፤ ትልቅ ድርጅት ነን፤ እኛ እነዚህ ሼዶች በሚተዳደሩበት መንገድ መተዳደር የለብንም፤ ሲሉ አመልክተዋል።

ኃይሉ ሣሕለድንግል

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥቅምት 30 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You