በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
(ክፍል አንድ)
የከሀዲው ትህነግ ርዝራዥና ዲያስፖራ ጭፍራ እንደ ቆሰለ አውሬ ደሙን እያዘራ ያገኘውን ለመንከስ እየዛከረ ነው። ባልጠበቀውና ባላሰበው መንገድ የበላይነት፣ የዘረፋ፣ የአፈና፣ የጥላቻና ሀገር የማፍረስ ፕሮጀክቱ ድንገት የእንቧይ ካብ ስለሆነበት ክፉኛ ተቆጭቷል። ጣረ ሞት ላይ ቢሆንም በሀሰተኛና የተዛባ መረጃ ማምሻም ዕድሜ ነው በሚል እየተፈራገጠ ነው። በስሁት ርዕዮት ዓለምና በፈጠራ ትርክት የካበው የእንቧይ ካብ ተንዷል። በእውኑም ሆነ በህልሙ ይሆናል ብሎ ባልገመተው የለውጥ ኃይሉና ሕዝባዊ ቁጣው ተናበውና ተመጋግበው ከ50 እስከ 100 ዓመት አገዛዝ ላይ የመቆየት የቀን ቅዠቱን አጨንግፈውታል። ታላቋን የትግራይ ሪፐብሊክ የመመስረት ሌላው ቅዠቱ ከንቱ ሆኗል። የአደጋ ጊዜ የመውጫ በሩ ከውጭ ተከርችሞበታል። ግራ ተጋብቷል። የሚይዘው የሚጨብጠው አጥቷል። ደመ ነፍሳዊ ሆኗል። አመክንዮና ተጠየቅ ድሮም አልነበረውም አሁንም እንደራቀው ነው። ማመዛዘኛው ይብስ ተበላሽቷል። የጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ታሪክ የማይረሳው፤ ትውልድ ይቅር የማይለው ክህደት እና በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው ጭፍጨፋና የጦር መሣሪያ ዘረፋ የዚህ ደመ ነፍሳዊነት ውጤት ነው።
‹‹ከፀሐይ በታች ህወሓትን የሚገዳደር ኃይል የለም። ይህን ማስጠንቀቂያ ችላ ብሎ የሚሞክር መቐሌ መቀበሪያው ትሆናለች። በመከላከያ ላይ መብረቃዊ ጥቃት ፈጽመናል። ከመንግሥቱ በላይ እስካፍንጫችን ታጥቀናል›› እያለ ሲፎክር፣ ሲያቅራራ፣ ሲፎልልና ሲሸልል እንዳልነበር በዘጠኝ ቀናት እንደ አሸዋ ላይ ሰቀላ ብትንትኑ ወጥቷል። ሁልጊዜም ከእያንዳንዱ ውድቀቱና ቀውስ ማግስት በጉያው ተጠባባቂ ደባዎችንና ሸሮችን በጉያው ይዞ የሚዞረው ከሀዲውና እፉኝቱ ትህነግ የፕሮፓጋንዳና የሕዝብ ግንኙነት ሌላ አውደ ውጊያ ከፍቷል። በለኮሰው እሳት ተቃጥሎ ዶጋ አመድ ከሆነ በኋላ የተረፈ የውሸትና የፈጠራ ትርክት ፍም አቀጣጥሎ ለጊዜውም ቢሆን ተስፈኞቹን ለማሞቅ ሌት ተቀን እየታተረ ነው። በተወሰነ ደረጃ ድካሙና ልፋቱ መና አለመቅረቱን እየታዘብን ነው።
ሀሰተኛ መረጃን እንደ ከሀዲውና እፉኝቱ ትህነግ የጦር መሣሪያ ያደረገ /ዌፐናይዝ/ ድርጅትም ሆነ ሀገር የለም። በዓለማችን እንደ ራሽያው የስለላ ተቋም ኤፍኤስቢ መረጃን እንደ ጦር መሣሪያ የተጠቀመ ወይም የሚጠቀም የለም ቢባልም የትህነግ ርዝራዥና የዲያስፖራ ጭፍራ ግን በገገማነትና በገልጃጃነት አሳምሮ ይበልጠዋል። ላለፉት 47 ዓመታት ርካሽ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሀሰተኛ መረጃን ከክላሹ መሳለመሳ በስፋት ተጠቅሟል። እንደሸሚዝ ከሚቀያይረው ርዕዮት ዓለም ይልቅ ለሀሰተኛና የተዛባ መረጃ እንዲሁም ለፈጠራ ትርክት መታመን ይቀለዋል። በውንብድናውም ሆነ በአገዛዙ ጥሩ አድርጎ ያረጋገጠልን ይሄን እኩይ ማንነቱን ነው። በሕግ ማስከበርና የህልውና ዘመቻውም ሆነ በኋላ ሆን ተብሎ በተዛባና በሀሰተኛ መረጃ የጸረ ኢትዮጵያ ፕሮፓጋንዳና የማጠልሸት ዘመቻውን በመደበኛና በማህበራዊ ሚዲያው እያፈራረቀና እያጃመለ ተያይዞታል። መደበኛውም ሆነ ማህበራዊ ሚዲያው በሀገር ቤትም ሆነ በውጭ በተጠና፣ በተቀናጀ፣ በተናበበና በተመጋገበ አግባብ መዋቅራዊና ተቋማዊ ሆኖ ይመራል።
ይህ ጸረ ኢትዮጵያ፣ ጸረ እውነትና ጸረ ፍትሕ የሕዝብ ግንኙነትና የሚዲያ ከፍ ሲልም የዲፕሎማሲ ደባና ሻጥር በሀገር ውስጥ በጌታቸው ረዳ ይመራ ነበር። አሁን ግን በበላይነት የሚዘውረውና የሚያሽከረክረው በምንደኛውና ጥቅሙ በተነካበት እብሪተኛና ማንአህሎተኛ /chauvinist / የትህነግ ርዝራዥና ጭፍራ ዲያስፖራ ነው። ለዚህ እንዲያግዘው ደግሞ፤«የትግራይ ወዳጅነት አገናኝ ቢሮ» (Tigray Friendship Liaison Office) በተሰኘ ተቋም አማካኝነት በቀድሞው ዲፕሎማት ወንድሙ አሳምነው እንደሚመራ መስፍን አማን የተባሉ ጸሐፊ በፍትሕ መጽሔት፤ 3ኛ ዓመት፣ ቁ111 ፣ ታኅሣሥ እትም ላይ፤ «ከወታደራዊ ሽንፈት ወደ ዲፕሎማሲያዊ ትንቅንቅ» በሚል ርዕስ ባስነበቡን ማለፊያ መጣጥፍ ተረድተናል። በመንግሥታቱ ድርጅት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም በጀኔቭ በመንግሥታቱ ድርጅት ሕዝብ ልማት ፈንድ ባልደረባው ዶ/ር ኪዳኔ አብርሃ ከአምባሳደር ብርሀነ ገብረክርስቶስ ጋር በመቀናጀት የአውሮፓውን የዲፕሎማሲና የዓለምአቀፍ ሚዲያውን እጅ ለመጠምዘዝ በተደረገው ርብርብ የአንበሳውን ድርሻ ወስደዋል። ከአትላንቲክ ማዶ በአሜሪካ ያለው ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ለአምባሳደር ፍስሐ አስግዶም በአደራ መሰጠቱን እኝሁ ጸሐፊ ጠቁመዋል። የቀድሞው ታጋይ ሙሉጌታ ገብረህይወት (ጫልቱ) ከመለስ ዜናዊ ወዳጅ አሌክስ ዲወል ጋር በመሆን የትህነግን ተስካር ለማሳመር እየባዘኑ ነው። የኦባማ የብሔራዊ ደህንነት የቀድሞ አማካሪና የአዲሱ የባይደን አስተዳደር ተሿሚ ሱዛን ራይስ፣ የአሜሪካ የልማት ተራድኦ (ዩኤስኤይድ) ዳይሬክተር ጌይል ስሚዝ፣ የሒውማን ራይትስ ዋች ኃላፊ ኬኔትስ ሮዝ ከእነ የማነ ኪዳኔ (ጀማይካ) ጋር በመሆን ዓለምአቀፍ ሚዲያውንና የሰብዓዊ መበት ተሟጋቾች ላይ ተጽዕኖ በማሳደር ሥራ ተጠምደዋል። በትግራይ ክልል የተካሄደውን የሕግ ማስከበር ዘመቻ ከዘር ማጥፋትና ማጽዳት ጋር ለማጣረስ እየኳተነ ያለው ሌላው ከሀዲ ዶ/ር መሀሪ ታደለ ነው። በዚያ ሰሞን በመደበኛውና በማህበራዊ ሚዲያው ስለወሬሳው ትህነግ ሽንጡን ገትሮ ሲሟገት የነበረው ማርቲን ፕላውት፤ የቢቢሲ የአፍሪካ አርታኢ ዊል ሮስ ቢቢሲ አማርኛንና ትግረኛን በትህነግ ካድሬዎችና ደጋፊዎች በመሙላት እና ኖርዌያዊው ሸተል ትሮንቮል እንደነ ቢቢሲ ባሉ ዓለምአቀፍ ሚዲያዎች በመቅረብ ለከሀዲው ትህነግ በመወገን የተዛባና የሐሰት መረጃ በመንዛት ትህነግ አፈር ልሶ እንዲነሳ እየማሰኑ ነው።
የቀድሞው ፓትርያርክ የአቡነ ጳውሎስ ልዩ ረዳት ስታሊን ገብረሥላሴ (ስምን መልዓክ ያወጣዋል እንዲሉ ፤ ጆሴፍ ስታሊን በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የሶቪየት ዜጎችን የጨፈጨፈ ሰው በላ ገዥ ነው ፤ ) ፣ አሉላ ሰለሞንና ዳንኤል ብርሀኔና ሌሎች የትግራይ ሚዲያ ሀውስ ሰዎች ደግሞ የሀገር ቤቱንና የውጭውን የትህነግን የፕሮፓጋንዳ ማሽን መካኒኮች ናቸው። የትግራይ ጦርነት ባህላዊ ጨዋታው ነው። ትግራዋይ ሁሉ ትህነግ ነው ሲሉ ካለማፈራቸው ባሻገር በሀገሪቱ ከተፈጸሙ ጭፍጨፋዎች ጀርባ እጃቸው አለበት። ከፍ ብዬ የጠቃቀስኋቸው የቀድሞ ታጋዮች፣ አምባሳደሮች፣ በዓለምአቀፍ ተቋማት የሚሰሩ፣ የውጭ ሀገር ዜጎች፣ አክቲቪስቶች በመማጸኛ ከተማው መሽጎ ከነበረው ከሀዲው የትህነግ ስብስብ እና አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው ሀገሪቱ ካሰማራቸው ጭፍራዎቹ ጋር በመቀናጀትና በመናበብ የፈጠራ ትርክታቸውን ከመለፈፋቸው ባሻገር የተዛባና ሐሰተኛ መረጃ በመደበኛውና በማህበራዊ ሚዲያው በመንዛት ሀገራችንን በጦር መፍታት ቢሳናቸው በወሬ ለመፍታት ሌት ተቀን እየተረባረቡ ነው። በዋናነት ትግራይ ሚዲያ ሀውስን (TMH )፣ ትግራይ ፈርስት ፣ አይጋ ፎረም፣ ትግራይ ፕሬስ፣ ቮይስ ኦፍ ትግራይ፣ ትግራይ ኦን ላይንና ሰሞኑን ደግሞ እንደአሸን የፈሉ ድረ ገጾችና ዩቲውቦች ሀሰተኛ መረጃውን ሌት ተቀን ያንበለብላሉ። እንደ ኦኤምኤን ያሉ የአጋሮቻቸውን መደበኛና ማህበራዊ ሚዲያዎችን በተውሶ ይጠቀማሉ።
ማህበራዊ ሚዲያዎችን አቀናጅቶ የሚጠቀመው በተለምዶ ዲጂታል ወያኔ በመባል የሚታወቀው የከሀዲው ትህነግ ጭፍራ በሺዎችና በአስር ሺዎች የሚቆጠር የፌስ ቡክ፣ የቲዊተር፣ የቴሌግራም፣ የኢንስታግራምና የዩቲውብ ሀሰተኛ አካውንት በመክፈት ጥላቻን፣ ልዩነትን፣ ዘረኝነትንና ልዩነትን የሚያቀነቅኑ የፈጠራ መረጃዎችን በመደበኛና በማህበራዊ ሚዲያዎች ያለዕረፍት ሌት ተቀን ይነዛሉ።
ለጊዜውም ቢሆን አምነስቲ ኢንተርናሽናልን፣ ሒውማን ራይትስ ዋችን፣ በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንን፣ በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ረድኤት ማስተባበሪያ አገናኝን /ዩኤንኦቻ/፣ የባይደንን አስተዳደር ፣ ዓለምአቀፍ ሚዲያውን፣ ወዘተረፈ በማሳሳት ግዳይ ጥለዋል። እውነትንና ፍትሕን ታቅፈን እንድንቀር አድርገዋል። ውሸት እውነትን፣ ጨለማ ብርሃንን ረቷል። ደካማው የኮሙኒኬሽንና የዓለምአቀፍ ግንኙነት ሥራችን ውድ ዋጋ አስከፍሎናል። ሉዓላዊነታችን ተደፍሯል። በፈተና ላይ የነበረው ለውጥ ጠልሽቷል። ዙሪያችንን ከበው አሰፍስፈው ሊውጡን ደጅ ቆመው ለሚጠብቁን እንደ ግብጽ ላሉ ታሪካዊና ወቅታዊ ጠላቶቻችን የልብ ልብ እንዲሰማቸው አድርጓል። እውነት ለመናገር እንደ ሀገር ወዳድ ዜጋ ያበግናል። ያብሰከስካል።
የትህነግ ርዝራዦችና ዲያስፖራ ጭፍራዎች ጊዜያዊ የፖለቲካና የዓለምአቀፍ ግንኙነት ትርፍ እስካገኙ ድረስ ሀገር ስሟ ቢጠፋ፤ ባፍንጫዋ ብትደፋ ጉዳያቸው አይደለም። በአክሱም ከጽዮን ማርያም ንግስ ሁለት ቀን በፊት 750 ሰዎች በጅምላ ተጨፈጨፉ፤ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት አባላት ንጹሐንን ገደሉ፤ አንድ ሴት ለ23 ተደፈረች፤ ወዘተረፈ የሚሉ በሰው ሰራሽ ክህሎት/artificial intelligence / የተቀነባበሩ ፍጹም እውነተኛ የሚመስሉ/deep fake/ ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በመልቀቅ ዓለምአቀፍ ማህበረሰብን እና ምዕራባውያንን በማደናገር በእንቅርት ላይ ቆረቆር ሆነውብናል። የአክሱምን የ«ዘር ማጥፋት» በቪዲዮ የሚያብራራው ቄስ ሲጣራ አንደኛ ቄስ አለመሆኑ ሁለተኛ በአሜሪካ የሎስአንጀለስ ነዋሪ ሲሆን በቅርብ ወደትግራይ ሄዶ እንደማያውቅ ተረጋግጧል። ለጊዜው የሀሰተኛ መረጃ ውርጅብኝ ዋጋ ቢያስከፍለንም ውሸትና ስንቅ እያደር ይቀላል እንዲሉ ቀስ በቀስ እውነቱ እየወጣ ነው። ትህነግ ላለፉት 27/30 ተቋማዊና መዋቅራዊ አድርጎ ጊዜውን ጠብቆ እንዲፈነዳ የቀበረው የጎሳ፣ የልዩነት፣ የጥላቻና የመጠራጠር ፈንጂ ሀገሪቱን እየናጣት፤ ሱዳን ሉዓላዊነታችንን ደፍራ መሬታችንን በወረረችበት እና በታላቁ የህዳሴ ግድብ የተነሳ ግብጽ እንደ ጎን ውጋት ቀስፋ በያዘችን ፈታኝ ሰዓት በሀሰተኛና ሆን ተብሎ በተዛባ መረጃ አሜሪካ የጸጥታው ምክር ቤት ባለወር መሆኗን ተጠቅማ ሀገራችንን ሆን ብላ ዜጎቿን በማስራብ መክሰሷ አልበቃ ብሏት የአማራ ልዩ ኃይል ከምዕራብ ትግራይ እንዲወጣ በመጠየቅ በውስጥ ጉዳያችን ጣልጋ ገብታለች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንተኒ ብሊንከን በየአጋጣሚው የሀገራችንንና የመንግሥታችንን ስም እያጠለሸ ነው።
ለዛሬ መጣጥፌን እዚህ ላይ እልባት ላድርግና በክፍል ሁለት መጣጥፌ በሀሰተኛ መረጃ የተከፈተብንን ዘመቻ ከዓለምአቀፍ ሚዲያውና ከመንግሥታቱ ድርጅት አንጻር ገፋ አድርጌ የማየው ሲሆን፤ የዜጎቻችን የዲሲ፣ የኒው ዮርክና ሌሎች ሀገራት ሀገር አድን ሰልፎችን አንድምታና የጠለሸውን ገጽታችንን ለማደስ ያግዙ ይሆናል ያልኋቸውን መላዎች አቀብላለሁ።
ሀገራችን ኢትዮጵያ በጀግኖችና በእውነተኛ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር !!!
አሜን።
አዲስ ዘመን መጋቢት 08/2013