ወርቅነሽ ደምሰው
ትምህርት ቤቶች የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድ የሚያፈሩ እንደመሆናቸው መጠን ለተማሪዎች ብሩህ ተስፋን ስንቀው እንዲማሩ ለማድረግ ለመማር ማስተማሩ ሂደት ምቹ የሆኑ፤ ንጹህና ጽዱ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህንኑ እውን ለማድረግም በትምህርት ቤቶች ቅጥር ግቢና በአካባቢያቸው ያለውን ስፍራ ጽዱና ውብ ለማድረግ በየስፍራው የተለያዩ ጥረቶች በመደረግ ላይ ነው፡፡ በተለይ በመዲናዋ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች በኩል የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ለመፍታት የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ከግል ትምህርት ቤቶች እኩል ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ለማድረግ ከባለፈው ዓመት ጀምሮ መንግሥት በርካታ ወጪ በማውጣት ጥገናና እድሳት በማድረግ ምቹ ሁኔታ ሲፈጥር ቆይቷል፡፡
ከዚህ ባለፈም ተማሪዎች ትምህርትን በቅርበት እንዲያገኙ ለማድረግ ሁኔታዎች በማመቻቸት በርካታ አዳዲስ ትምህርት ቤቶች ተገንበተው ለኅብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ ይገኛል፡፡ እነዚህ ትምህርት ቤቶች ግንባታቸው በአጭር ጊዜ ተጠናቅቆ የመማር መስተማር ሂደት እንዲጀመሩ የተደረገ ሲሆን፤ ትምህርት ቤቶቹ ለእይታ ማራኪና ሳቢ ከመሆናቸው በላይ በርካታ ተማሪዎችን እያስተናገዱ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ግን በእነዚህ ትምህርት ቤቶች ከሚነሱ ችግሮች ውስጥ የግንባታ አለመጠናቀቅና የግብዓት አለመሟላት እንደ ችግር የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በቅርብ ግንባታው የተጠናቀቀው የቡርቃ ቦሪ የመጀመሪያ ትምህርት ቤት አዲስ እንደመሆኑ መጠን ከሞላ ጎደል እነዚህ ችግሮች ያሉበት ሲሆን፤ ከዚህ ከፍ ባለ ሁኔታ የመማር ማስተማሩ ሂደት አጣብቂኝ ውስጥ የሚከትት ችግር አጋጥሞታል፡፡
በዛሬው በፍረዱኝ አምዳችን በዚሁ በመዲናችን አዲስ አበባ ከተማ በቀድሞ የካ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13፤ በአዲሱ ክፍለከተማ ለሚ ኩራ ወረዳ 2 ውስጥ የሚገኘውን የቡርቃ ቦሪ የመጀመሪያ ትምህርት ቤትና አሶሳ አጸደ ሕፃናት ዘንድ ይወስደናል፡፡ በእነዚህ ትምህርት ቤቶች የመማር ማስተማሩን ሂደት አደጋ ላይ በመጣል እንቅፋት እየሆነ ያለው ትልቁ ችግር ምንድነው የሚለውን የሚያሳየን ይሆናል፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትና በአጸደ ሕፃናቱ መካከል ባለው አካፋይ መንገድ ላይ ያለው የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ጉዳይ የችግሩ መንስኤ ነው፡፡ በዚህ ቆሻሻ የተነሳ በርካታ ተማሪዎች ለጤና ችግር ከመዳረጋቸው ባሻገር ከትምህርት ገበታቸው በመቅረት ላይ መሆናቸው ይነገራል፡፡
የዝግጅት ክፍላችንም የተማሪዎች ወላጆች ጥቆማን ተከትሎ ትምህርት ቤቱ ድረስ በመገኘት የፍረዱኝ ባዮቹን ቅሬታ ለመመርመር ችሏል፡፡ በቅኝቱም የሚመለከታቸውን የትምህርት ቤቱ አካላት ያነጋገርን ሲሆን ፍርዱን ለእናንተው በመተው፤ የቅሬታ አቅራቢዎቹን እሮሮና ምሬት በማዳመጥ፣ ጉዳዩን የሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ጨምረን እንደሚከተለው ልናስቃኛችሁ ወደድን። መልካም ንባብ!
ጉዞ ወደ ትምህርት ቤቱ
የዝግጅት ክፍላችን የደረሰውን ጥቆማ ተከትሎ ወደ እነዚህ ትምህርት ቤቶች አቅንቶ ረቡዕ መጋቢት 1 ቀን 2013 ዓ.ም ቦታው ላይ ተገኝቶ ነበር፡፡ የቡርቃ ቦሪ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትና የአሶሳ አጸደ ሕፃናት ትምህርት ቤት ከመገናኛ -አያት – ጣፎ የሚወስደው መስመር ይዘው ሲጓዙ ወደ ጣፎ ከተማ መዳረሻ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ ትምህርት ቤቶቹ በግራና በቀኝ በኩል፤ ከመንገድ በላይና በታች በሰፊው ከተንጣለለው አያት ቁጥር ሁለት የጋራ መኖሪያ ቤቶች (ኮንዶሚኒየም) መሀል ተከበው የሚገኙ ሲሆን፤ በቀኝ በኩል ወደ ታች በሚወሰደው መንገድ ሁለተኛ በር በመባል በሚታወቀው የኮንዶሚኒየም መግቢያ በር በኩል በቀጥታ ወደ ታች ሲጓዙ ከ100 ሜትር ርቀት ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ በሁለቱም ትምህርት ቤቶች እጅግ ማራኪ የሆነ ገጽታ የተላበሱ ከመሆናቸው በላይ መንግሥት ይህንን የመሰለ ትምህርት ቤት በአጭር ጊዜ መገንባት በመቻሉ የሚያስመሰግነው ሥራ መስራቱን ማሳያ ናቸው፡፡ በሁለቱ መካከል ኮብልስቶን ንጣፍ ያለው መንገድ ያለ ሲሆን፤ ይህም ለአካባቢው ውበት ሰጥቶታል፡፡ ሆኖ ግን ይህን ሁሉ ውበት የሚያጠፋ አንድ ችግር ፍጥጥ ብሎ ይታያል፡፡ ለዓይን አስቀያሚ፤ ለአፍንጫ ሰንፋጭ የሆነ የቆሻሻ ክምር አካባቢውን በክሎት ይገኛል፡፡ ችግሩ በጣም አሳሳቢ የሚሆነው ደግሞ ቆሻሻው በአጸደ ሕፃናቱ በር አካባቢ መገኘቱ ነው፡፡ በገንዳው አካባቢ በጣም ብዙ የቆሻሻ ክምር ተከምሮ ይታያል፡፡ ቆሻሻው ላይ ደግሞ በርከት ያሉ ውሾች ወዲያና ወዲያ ሲሉ ይታያሉ፡፡
በትምህርት ቤቱ ደጃፍ የሚደፋው ቆሻሻ ከአካባቢው ኅብረተሰብ ብቻ የሚሰበሰብ ሳይሆን ከሌላ አካባቢ እየመጣ የሚከማች እንደሆን ነጋሪ ሳያስፈልግ መረዳት የሚያስችል ነው፡፡ በአጸደ ሕፃናት ቅጥር ግቢ ውስጥ ከሚገኙ የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ጋር ቆይታ አድርገን ስንወጣ በዚያው ቅጽበት የደረሱት የወረዳው ዋና ሥራ አስፈጻሚና ምክትል ሥራ አስፈጻሚው እንዲሁም የፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ ቆሻሻው በመሰብሰብ ላይ የተሰማሩትን ወጣቶች ሰብስበው በማወያየት ላይ እያሉ አገኘናቸው፤ እኛም የሕዝብ ጥያቄ ነውና እዚያው የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታ ላይ ሆነን ያንን ሁሉ ሽታ ተቋቁመን ቆይታ አድርገን ነበር፡፡ ሆኖም ግን ምንም እንኳን ማክስ ብናደርግም የቆሻሻ ሽታው አፍንጫ ሊበጥስ የሚደርስ መሆኑን ታዝበናል፡፡ በተለይ እኔ የዚያኑ ቀን ጀምሮ ለከፍተኛ ጉንፋን እና ለራስ ህመም በመዳረጌ እስካሁን አልቀቀኝም፡፡ ለሌላው የሥራ ባልደረቦቼ ጉንፋን ማትረፌ የማይካድ ነው፡፡ በዚህ አካባቢ ለደቂቃዎች በነበረኝ ቆይታ የቆሻሻ ሽታ ለዚህ ያህል ችግር ከዳረገኝ ለትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ምን ያህል ነው የሚለው ሳሰበው እጅግ ከባድ ነው፡፡
ከቅሬታ አቅራቢዎች አንደበት
የቡርቃ ቦሪ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትና የአሶሳ አፀደ ሕፃናት ትምህርት ቤት ርእስ መምህር አቶ ይስሐቅ ታምሩ እንደሚናገሩት፤ የትምህርት ቤቱ ግንባታ የተጠናቀቀው ባለፈው ዓመት በ2012 ዓ.ም ሲሆን ለመማር ማስተማሩ ዝግጁ ሆኖ የመማር ማስተማሩን ሥራ የጀመረው በ2013 ዓ.ም ሲሆን ከመስከረም ወር ጀምሮ የከተማ አስተዳደሩ ባወጣው የምዝገባ መርሃ ግብር መሠረት ተማሪዎች በመመዝገብ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡
በዘንድሮ ዓመት በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በአማርኛና በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ 1689 ተማሪዎችንና በአጸደ ሕፃናት በሁለቱም ቋንቋዎች 584 ተማሪዎች የተመዘገቡ ሲሆን፤ በአጠቃላይ በሁለቱም ትምህርት ቤቶች በአማርኛና በአፋን ኦሮሞ ቋንቋዎች 2273 ተማሪዎች በመመዝገብ የመማር ማስተማር ሥራው ተጀመረ፡፡ ትምህርት ቤቶቹ ከዚህ በተጨማሪም 130 የሚሆኑ መምህራንና የትምህርት ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ያሉት ነው፡፡ በትምህርት ቤቶቹ ትምህርት ደረጃ በደረጃ አንድ ሁለት እየተባለ የተጀመረበት ሁኔታ ቢኖርም በአጠቃላይ ትምህርት ከተጀመረ አንድ ወር የተቆጠረ መሆኑን ነው ርዕስ መምህሩ የሚናገሩት፡፡
ትምህርት ከተጀመረ በኋላ የመማር ማስተማሩ ሂደት በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል የሚሉት ርዕስ መምህሩ፤ ነገር ግን የመማር ማስተማር ሂደቱ የሚያውከው ትልቅ ነቀርሳ የሆነብን ጉዳይ በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እና አጸደ ሕፃናቱ በሚገኝበት ትምህርት ቤት መሀል ያለው የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ሽታ ችግር ነው:: ይህም የመማር ማስተማሩን ሥራ እጅግ አስቸጋሪና በጣም ከባድ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በትምህርት ቤቱ በኩል ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ ከስምንት ወር በፊት ከክፍለከተማ እስከ ትምህርት ቢሮ በተለያየ አቅጣጫ የተለያዩ አካላት እንዲያውቁት ለማድረግ የተቻለ ሲሆን፤ የከተማው ምክር ቤት፤ የከተማው ምክትል ቢሮ ኃላፊ፤ የክፍለከተማ አመራሮች በተለያየ ጊዜ ቦታው ድረስ በመምጣት አይተውት ነበር ይላሉ፡፡ ሆኖ ግን እስካሁን ችግሩ በነበረበት ያለና መፈታት ያልቻለ በመሆኑ በመማር ማስተማሩ ሂደት ትልቅ እንቅፋት ሆኗል፡፡
እንደ ርዕስ መምህሩ ገለጻ፤ በዚህ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ የተነሳ ብዙ ተማሪዎች በመታመማቸው ምክንያት ከትምህርት ገበታቸው ርቀው ቤታቸው እየቀሩ ሲሆን ፤ መምህራን እንዲሁ እየታመሙ ከሥራ የሚቀሩበት ሁኔታ መኖሩን ይገልጻሉ፡፡ በትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ በተለይ ከቀኑ ሰባት ሰዓት አካባቢ የቆሻሻው ሽታው መቆም ሆነ መቀመጥ የማያስችል ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በተለይ ቆሻሻው የአፀደ ሕፃናት ትምህርት ቤት በር አጠገብ እንደመገኘቱ መጠን ለሕፃናቱ እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ ወላጆች በየጊዜው የትምህርት ቤቱን በር እያንኳኩ እሮሮአቸውን እያሰሙ ነው ይላሉ፡፡
ሌላው በኩል ከሁለት ሳምንት በፊት የትምህርት ቤቱ የወላጅ ኮሚቴ አባላት ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጋር በመሄድ ችግሩን ለማሳወቅ ጥረት አድርገው እንደነበር ያስታወሱት ርዕስ መምህሩ፤ በወቅቱ ወላጅ ኮሚቴ አባላት ያገኙት ምላሽ በሦስት ቀን ውስጥ ቆሻሻ እንደሚያስነሳላቸው ተነግሯቸው ነበር የተመለሱት፡፡ ነገር ግን ቆሻሻውን የሚያነሳ አካል እንዳልተገኘ ይናገራሉ፡፡ በመቀጠልም ከሳምንት በፊት የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ኮሚቴዎች ተሰብሰበው ከተወያዩ በኋላ ግማሹ ለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ፤ ግማሹ የካ ክፍለከተማ የሄዱ ሲሆን፤ ለሚመለከታቸው አካላት ጉዳዩን በማስረዳት ማመልከቻ ደብዳቤ አስገብተው የተመለሱበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመዋል፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን ድረስ ችግሩ ሳይፈታ መልስ አልተሰጠውምና ምንም ዓይነት መፍትሔ ያልተገኘለት ሆኗል፡፡
‹‹ይህንን ችግር በተለይ በአጸደ ሕፃናት ትምህርት ቤት ላይ ትልቅ ተፅዕኖ የሚፈጥር በመሆኑ ለትምህርት ቤቱ ከፍተኛ ስጋት ነው፡፡ የሚመለከታቸው አካላት ለቆሻሻ ማጠራቀሚያው ሌላ ተቀያሪ ቦታ በመፈለግ የመማር ማስተማሩ ሂደት ሰላማዊ ወደ ሆነ ተማሪዎች በተረጋጋ መንፈስ የሚማሩበት ለማድረግ መስራት ይኖርበታል›› ብለዋል፡፡
የወተመህ (የወላጅ ተማሪ መምህር ህብረት) ኮሚቴ አባል መምህር የኋላሽት ኃይለማርያም በበኩላቸው፤ ቆሻሻው እንዲነሳና የተማሪዎቹ ጤንነት እንዲጠበቅ በርካታ ቦታዎችን ለማዳረስ መሞከራቸውን ይናገራሉ:: ክፍለ ከተማና ወረዳ ድረስ በመሄድ ጉዳዩን ማስረዳታቸውንና የአካባቢውን ማህበረሰብ የኮሚቴ አባላት በጋራ በመሆን መወያየታቸውን ይናገራሉ፡፡
መምህሩ እንደሚሉት፤ የአካባቢው ማህበረሰብ ኮሚቴዎች አባላቱን ባወያዩ ጊዜ እንደተረዱት ይህ ችግር አሁን ትምህርት ቤቱ ሲከፈት አፍጥጦ ወጣ እንጂ የቆየ ችግር ነው፡፡ የኮሚቴ አባላቱ እንደተናገሩት በተደጋጋሚ ይህ ቆሻሻ እንዲነሳላቸው ያመለከቱ ቢሆንም እስካሁን መፍትሔ አለማግኘታቸውን ነው፡፡ ይህ ትምህርት ቤት የመንግሥት አካል ስለሆነ ትምህርት ቤቱ የራሱን ጥረት ማድረግ ይጠበቅበታል ይላሉ፡፡ ከዚያም የትምህርት ቤት የወላጅ ኮሚቴ አባላትና የትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ በጋራ በመሆን የካ ክፍለ ከተማ ደብዳቤ ይዘን ሄደን ነበር፡፡ በወቅቱ የክፍለ ከተማው ምክትል ሥራ አስፈጻሚ ጋር በመወያየት ቆሻሻውን በሁለት ቀን ውስጥ እናስነሳዋለን ያሉ ሲሆን፤ እንዳሉትም ቆሻሻውን በሁለት ቀናት ጊዜ ውስጥ አስነስተውት ነበር፡፡ ሆኖ ግን በሦስተኛ ቀን ቆሻሻው ከሌላ ቦታ እየተጓጓዘ ተመልሶ መምጣቱን ቀጥሎ እንደገና ክምር ቆሻሻ ማጠራቀሙን ተያያዘው፡፡ በወቅቱ የተቀረፈው መጠነኛ የሆነ ችግር እንጂ ችግሩ ሙሉ በሙሉ ሳይቀረፍ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡
እንደ መምህር የኋላሽት ገለጻ፤ ቆሻሻው ሕፃናቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ የእእምሮ እንዲሁም የስነ ልቦና ችግር እያደረስ ነው፡፡ በተለይ በአጸደ ሕፃናቱ የሚማሩ ትናንሽ ሕፃናት ሊቋቋሙት የማይችሉት ሽታ በመግቢያ በር ላይ ይቀበላቸዋል፡፡ ይህንን ችግር ሁሉም የመንግሥት አካላት የሚያውቁት ነው፡፡ ‹‹ችግሩ የከተማ አስተዳደሩ ድረስ የሚታወቅ ቢሆንም እስካሁን ሊፈታ ያልቻለበትን ምክንያት ምን እንደሆነ ሊገባን አልቻልም፡፡ ከማህበረሰቡ ጤና ችግር አንጻር በአስቸኳይ ሊቀረፍ ሲገባው እስካሁን ምንም መፍትሔ ያልተበጀለት ነው›› ብለዋል ፡፡
እንደ ትምህርት ቤቱ ማህበረሰብ ፍላጎት ቆሻሻው ከዚህ ተነስቶ ወደ ሌላ ተቀያሪ ቦታ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ቆሻሻ የሚሰበስቡት ወጣቶች ክፍለ ከተማ ማህበራት ያደራጃቸው ስለሆነ ወረዳው የተሻለ ተቀያሪ ቦታ በመስጠት ማስነሳት የሚችልበት ሁኔታ መኖሩን ይናገራሉ፡፡ የዚህ የቆሻሻ ችግር ተደራራቢ ያደረገው ቆሻሻ የአካባቢው ኅብረተሰብ የሚጥለው ብቻ ቢሆን ኅብረተሰቡን በማሳመን የማስነሳት ሥራ መሥራት የሚቻል መሆኑን ጠቅሰው፤ ችግሩን ግን የባሰ ውስብስብ የሚያደርገው ቆሻሻው በእነዚህ ማህበራት ከሌላ በጣም ሩቅ ከሆነ ቦታ በመኪና ተጭኖ የሚመጣ መሆኑ ነው ፡፡
የወላጅ ኮሚቴ አባላቱ ቆሻሻውን ለማስወገድ ካስቀመጡት የመፍትሔ ሀሳቦች መካከል አንደኛው ቦታው እንዲታጠር ማድረግ ሲሆን፤ ሁለተኛው አማራጭ ሰላማዊ ስልፍ እንውጣ የሚል ነበር የሚሉት መምህሩ፤ እኛ ግን እንደ ትምህርት ቤት ሁለቱም አማራጮች መፍትሔ አይሆኑም ሕጉን ጠብቀን ለሚመለከተው አካል ማሳወቅ አለብን በሚል ነው እስካሁን የቆየው፡፡ እንጂ ማ ! ኅብረተሰቡ የሚያቀርበው ጥያቄ ብዙ ነው፡፡
እንደ መምህሩ ገለጻ፤ ትምህርት ቤቱ ሲቋቋም በዋናነት ዓላማው ለኅብረተሰብ አገልግሎት እንዲሰጥ ነው፡፡ አገልግሎት እንዲሰጥ ከተፈለገ ደግሞ ንጹህ አካባቢ መፍጠር ለማኅበረሰብና ለሕፃናት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡ የዚህ ትምህርት ቤት ሁኔታ ግን ከዚህ በተቃራኒው ሽታው በትምህርት ቤት ግቢ ብቻ የሚገደብ ሳይሆን ክፍሎች ውስጥ የሚሸት መሆኑ የመማር ማስተማሩን ሂደት እያወከ ነው፡፡ በተለይ ቀን ፀሐይ በሚሆንበት ጊዜ ሽታው በቀጥታ ክፍል ውስጥ ነው የሚመጣው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ልጆች እየተማሩ አይደለም፤ ጤናቸው እየተቃወሰ ነው ይላሉ፡፡ እስካሁን የባሰ ችግር አልገጠመንም እንጂ፤ የባሰ ችግር ቢገጥመን ተጠያቂ የሚሆነው ማነው ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡ ትኩረት ስላልተሰጠው ነው እንጂ፤ ይህንን በተለይ ለሕፃናት ጤና ጎጂ የሆነ ችግር የመንግሥት አካላት ተባብረው መቅረፍ የሚችሉት ጉዳይ መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡
የዚሁ ትምህርት ቤት ተማሪ ከሆኑት መካከል አንዷየስምንተኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው ኤፍራታ ደስታ ናት፡፡ ትምህርት ቤቱ ያለው ቆሻሻ በመማር ማስተማሩ ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረ እንደሆነ የምትናገረው ተማሪ ኤፍራታ በምንማርበት ጊዜ ለተለያዩ በሽታዎች እንድንጋለጥ እያደረገን ነው፡፡ ‹‹መጥፎ ነገር እየሸተተን መማር ይከብዳል፡፡ የቆሻሻው ሽታ በሚሸተን ጊዜ ትኩረታችን ሽታው ላይ ወይም ያንን ለመከላከል በመሆኑ ትምህርታችን ላይ ትኩረት ለማድረግ ይከብደናል›› የምትለው ኤፍራታ፤ ሽታ በጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ መሆኑ እየታወቀ መፍትሄ አለመሰጠቱ አግባብ እንዳልሆነ ትናገራለች፡፡
ኤፍራታ የቆሻሻው ሽታው በአብዛኛው ጊዜ ምግብ በሚመገቡበት ወቅት የሚሽት መሆኑን ገልጻ፤ አልፎ አልፎ ክፍል ውስጥ ሽታው እንደሚሸት ትናገራለች፡፡በዚህም የተነሳ ተማሪዎች ለጉንፋን እየተጋለጡ ነው:: አንድ ተማሪ ጉንፋን በሚያዝ ጊዜ የክፍሉ ተማሪዎች በሙሉ ሊዳርስ የሚችልበት ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን ጠቁማ፤ ከዚህም በተጨማሪ ለሌላ ተያያዥ በሽታ ተጋላጭ ሊያደርገን የሚችል በመሆኑ በትምህርት ቤት አካባቢ መጥፎ ጠረን ያለው እንዲሁም የተማሪዎች ትኩረት ሊስብ የሚችል ነገር መኖር የለበትም ስትል ትናገራለች፡፡ ለዚህ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶት ቢሰራ የመማር ማስተማሩ ሂደት የሚያወክ ችግር ቢያስወግድልን የተሻለ ይሆናል ብላለች፡፡
የአሶሳ አጸደ ሕፃናት ቅሬታ
የአሶሳ አጸደ ሕፃናት የቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት አስተባባሪ መምህርት ስንታየሁ ይመር የአጸደ ሕፃናት ትምህርት ከተጀመረ ሁለት ሳምንት እንደሆነ ይናገራሉ:: ሕፃናት እስካሁን ቤት እንዲቆዩ የተደረገበትና ትምህርቱ የካቲት ማለቂያ ላይ የተጀመረበት ዋንኛ ምክንያት ቆሻሻው መፍትሔ እስከሚበጅ መሆኑን ጠቁመው፤ ትምህርቱንም ስናስጀምር የሚመለከተው አካል መፍትሔ ይሰጠናል በሚል እምነት ነው፡፡ ሆኖም ግን ትምህርት ከተጀመረ በኋላም ማስተማር አዳጋች እየሆነ ነው፡፡ ሕፃናቱ ዛሬ መጥተው ነገ የማይደግሙበት፤ በሽታው ምክንያት የሚታመሙ ሲሆን፤ መምህራን ጉንፋን የሚያዙበት ውስብስብ ለሆነ የጤና ችግር እየተጋለጡ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
መምህራንና የግቢ ሠራተኞች በሙሉ ሥራ ከተጀመርበት ቀን ጀምሮ ታማሚ ሆነዋል የሚሉት አስተባባሪዋ፤ ትምህርት በመጀመሪያ ቀን መጥተው ታመው የቀሩ ሕፃናት መኖራቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ቆሻሻው የአጸደ ሕፃናት መግቢያ በር ላይ በመሆኑ ወላጆች ልጆቻቸውን ይዘው ሲመጡ በር ላይ ሸኝተው መመለስ ሲገባቸው ሽታ ስለማያስቆም ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ግቢ አስገብተው ስለሚመለሱ መማር ማስተማሩ ሂደት ላይ የራሱ ችግር እየፈጠረ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
አስተባባሪዋ እንደሚሉት፤ በሕግ መፍትሔ እስከምናገኝ ድረስ መማር ማስተማሩ መቆም ስለሌለበት እየታመምን፤ ልጆቹም እየታመሙ ቢሆን በችግር ውስጥ ሆነን ትምህርቱ እንዲቀጥል እያደርግን ነው፡፡ በአሁኑ ሰዓት ወላጆች ልጆቻቸው ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ ያስገደዳቸው ለልጆቹ ትምህርት ቤት መቅረት ስለማይፈልጉ እያስቸገሯቸው እንጂ አብዛኛው ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት መላክ እንደማይፈልጉ ተናግረዋል፡፡ ወላጆቹ ጉዳዩ ከትምህርት ቤት አቅም በላይ መሆኑን በመገንዘባቸው ተሰብሰበው ወደ ሚመለከተው አካል ሊሄዱ መዘጋጀታቸውን ነው የሚናገሩት፡፡
በአፀደ ሕፃናት ትምህርት ቤቱ በትምህርት ገበታቸው ላይ የተገኙት 350 ተማሪዎች ብቻ መሆናቸው ጠቁመው፤ ገና ወደ ትምህርት እየመጡ ያሉ ተማሪዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡ እንደ ትምህርት ቤት ያለውን ችግር ትምህርት ቤቱ የሚፈታው ሲሆን፤ ከትምህርት ቤቱ አቅም በላይ የሆነው ችግር የሚመለከተው አካል ሊፈታው ይገባል፡፡ በተለይ አሁን እየጨመረ ከመጣው የኮቪድ ቫይረስ አንጻር የመተንፈሻ ችግር ያለባቸው ሕፃናትና መምህራን በሽታው ምክንያት ተጋላጭ ይሆናሉ የሚል ስጋት እንዳላቸው ገልጸው፤ ለዚህም ከክፍለ ከተማ እስከ ወረዳ ያሉት የሚመለከታቸው አካላት ነገ ዛሬ ሳይባል በአስቸኳይ መፍትሔ ሊሰጡ ይገባል ብለዋል አስተባባሪዋ ፡፡
የአካባቢ ነዋሪና የአጸደ ሕፃናት መምህርት ሙሉዓለም በቀለ በበኩላቸው፤ ይህ ቆሻሻ የቆየና የአካባቢ ማህበረስብ ላይ ከፍተኛ የጤና ጉዳት ሲያደርስ የነበር መሆኑን ጠቁመው፤ አሁን ችግሩ ተባብሶ በተማሪዎች ጤና ላይ ጉዳት እያደረሰ ብዙ ተማሪዎች በጉንፋን እየታመሙ ከትምህርት ቤት የሚቀሩበት ሁኔታ መኖሩን ገልጸዋል፡፡ ወላጆችም በዚህ ሁኔታ ልጆታቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለማምጣት እየተቸገሩ ነው ያሉት መምህርቷ፤ በተለይ በፀሐይና በዝናብ ጊዜ ሽታው እጅግ የከፋ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ በተማሪዎችና በመምህራን ላይ ከዚህ የከፋ ጉዳት ሳይደርስ የሚመለከተው አካል ችግሩን በሚገባ ተገንዝቦ ሊፈታ እንደሚገባ ነው የሚናገሩት፡፡
የተደራጁት ወጣቶች ምላሽ
የአለማየሁ ሙሉጌታና ጓደኞቹ የደረቅ ቆሻሻ የህብረት ሽርክና ማህበር በሚል መንግሥት ያደራጃቸው ወጣቶች ኃላፊ የሆነው አቶ ዳዊት ዳንኤል እንደሚናገረው፤ እነሱን እዚህ ቦታ እንዲሰሩ ያደራጃቸው መንግሥት መሆኑን ገልጾ፤ ሆኖ ግን በተሰጣቸው ቦታ ላይ ትምህርት ቤት ተገንብቶ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ እዚህ ትምህርት ቤት የሚማሩት ተማሪዎች ደግሞ ልጆቻችን፤ እህቶቻችንና ወንድሞቻችን በመሆናቸው እኛም የእንጀራ ጉዳይ ሆኖብን እንጂ ሳናውቅና ሳንሳቀቅ ቀርተን አይደለም ይላል፡፡
እንደ ዳዊት ገለጻ፤ ከዚህ በፊት ከአንዴ ሁለት ሦስት ጊዜ ከዚህ ቦታ ተነስተን ሌላ ተቀሪይ ቦታ ላይ ተዘዋውረን ነበር፡፡ ሆኖ ግን እዚያ የተዘዋወርንበት ቦታ በርካታ ወጪ አድርገን ቆሻሻ ለመድፋት በመኪና ስናመጣ ሕዝብ እዚህ ጋ ቆሻሻ አትደፉም ብሎ እንዳበረራቸው ይናገራል፡፡
ቆሻሻ የሚያድር ከሆነ እንኳን ለተማሪዎቹ ለእኛም በሽታ ነው የሚለው ዳዊት፤ እኛ ከአርሶ አደሩና ከነዋሪው ኅብረተሰብ ጋር የማያጋጭ ነፃ የሆነ ቦታ ከተሰጠን የማንነሳበት ምክንያት የለም ባይ ነው፡፡ እኛ የተደራጀነው ለሥራ እስከሆነ ድረስ ወረዳው ከሁሉም ነገር ነፃ የሆነ ቦታ ከሰጠን ወዲያውኑ ከዚህ የምንለቅ ይሆናል ብሏል፡፡
የወረዳ ሁለት ምላሽ
በለሚ ኮራ ክፍለ ከተማ በወረዳ ሁለት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚና የትምህርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ማርቆስ ጳውሎስ እንደሚናገሩት፤ አሁን እዚህ ተገኝተን እያየን ያለው ይህ ቆሻሻ የመማር ማስተማር ሂደት በተለይም ሕፃናት እያወከ ስለሆነ ከኅብረተሰብና በዚህ ሥራ ላይ ተሰማርተው ከሚሰሩ ወጣቶች ጋር ተመካክረንና ተወያይተን መፍትሔ ለማስቀመጥ ነው፡፡ አሁን ከወጣቶቹ ጋር ባደረግነው ውይይት ስምምነት ላይ የደረሰነው ጊዜያዊ መፍትሔ በማስቀመጥ ቆሻሻው በየጊዜው እንዲነሳ ለማድረግ ነው ፡፡
እንደ አቶ ማርቆስ ገለጻ፤ አሁን ላይ እየሰጠን ያለው ጊዜያዊ መፍትሔ በቆሻሻ የተደራጁት ወጣቶች ደረቅና የበሰበሰ ቆሻሻ እንዲለዩ በማድረግ ቆሻሻውን በየቀኑ ከተቻለ በቀን ሁለት ጊዜ እንዲያስወገዱ የሚደረግ ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡ ቆሻሻ በሚቆይበት ልክ ሌላ ነገር ስለሚፈጥርና ቆሻሻው ከሌላ ቦታ የሚመጣበት ሁኔታ በመኖሩ ከሥር ከሥር እንዲያነሳ ማድረግ የሚገባ ሲሆን፤ ይህንን አሁኑ ለማስቆም አስቸጋሪ የሚያደርገው ቆሻሻው ለወጣቶቹ እንጀራ በመሆኑ ከሚመለከተው አካልና ከከተማ አስተዳደር ጋር ተነጋግሮ መፍትሔ ማበጀት የሚጠይቅ ነው፡፡ እስካሁን ችግሩ የቆየበት ምክንያት በመንግሥት በመሬት ባንክ ውስጥ ያለ መሬት እየፈለግን ስለሆነ እንጂ፤ ከዚህ በፊት ለመፍትሔ የሚሆን በርካታ ሙከራዎች አድርገን የአርሶ አደሩ የመሬት ጥያቄ ያለበት ቦታ በመሆኑ ሌላ አማራጭ ለመፈለግ ተገደናል ሲሉ ጠቁመው፤ ዘላቂ መፍትሔ እስከምናገኝ ድረስ ወጣቶቹ ደረቅና በስባሽ ቆሻሻ እየለዩ በየቀኑ እንዲያስወግዱ ማድረግ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
አሁን ያለው ችግር እጅግ አሳሳቢ በመሆኑ በሳምንት ጊዜ ውስጥ መፍትሔ ይፈልጋል ያሉት አቶ ማርቆስ የችግሩን ጥልቀት የተረዱት መሆኑንና እስካሁን የቆየበት ሁኔታ ወረዳው አዲስ ከመሆኑ አንጻርና በሰው ኃይልም ሆነ በግብዓት የተቀናጀና የተደራጀ ነገር ባለመኖሩ እንደተጓተተ ገልጸዋል፡፡ ወረዳ በፍጹም ይህንን ጉዳይ ችላ የሚለው አለመሆኑን ጠቁመው፤ የልጆቻችን ጉዳይ ስለሆነ በተቻለ መጠን በአስቸኳይ እንዲፈታ ለክፍለ ከተማ በማቅረብ የምንሰራ ይሆናል ብለዋል፡፡
እዚያ ኃላፊነት ከተመደቡ በኋላ አንድ ሳምንት እንደሆናቸው የሚናገሩት የለሚ ኩራ ወረዳ ሁለት ሥራ አስኪያጅ አቶ አዲስ አለማየሁ በበኩላቸው፤ ቅሬታውን ከሌሎች አመራሮች መስማታቸውን ገልጸው፤ ወደ ወረዳው እንደመጡ የደረቅ ቆሻሻ ማህበራትን ሰብሳቢ ጋር በማወያየት የችግሩን ጥልቀት በመረዳት መፍትሔ ፍለጋ ላይ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ አዲስ ገለጻ፤ ይህ ቆሻሻ ማከማቻ ቦታ በፊት በመንግሥት ካርታ ተሰጥቶት የነበረ መሆኑን ጠቁመው፤ ነገር ግን በኅብረተሰቡ ጥያቄ መሠረት መንግሥት ትምህርት ቤት እንዲገነባ አድርጓል፡፡ ይህ ሲደረግ ለዚህ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ የሚሆን ምትክ ቦታ አልተሰጠም ነበር ብለዋል፡፡ አሁን በቀረበው ቅሬታ እየሰጠን ያለው ሁለት ዓይነት መፍትሔ ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ዘላቂ መፍትሔ በመሬት ባንክ ያለመሬት ለመስጠት ያለመ ሲሆን፤ በጊዜያዊ መፍትሔ ቢያንስ እዚህ አካባቢ ላይ ቆሻሻ ማደር የለበትም፤ ቶሎ ቶሎ መነሳት አለበት በሚል ነው፡፡ በተጨማሪ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቦታ ዙሪያ ቶሎ ቶሎ መጽዳት አለበት የሚል አቅጣጫ
አስቀምጠናል፡፡ መሬቱ ተገኝቶ እስከሚሰጥ ድረስ የአርሶ አደር መሬት ቢሆን አርሶ አደሩን በማወያየት በጊዜያዊነት ከዚያ እንዲነሳ የሚያደርጉ መሆኑን ጠቁመው፤ የፅዳቱን ቀጣይነት በተመለከተ እንደ ሥራቸው አድርገው እንደሚከታተሉት ጠቁመዋል፡፡
አሁን ላይ ትልቁ ቅድሚያ የተሰጠው የትምህርት ቤት ጉዳይ ነው፤ ሌሎቹ ጉዳዮች በሂደት የሚፈቱ ናቸው ያሉት ኃላፊው፤ የጤና ጉዳይና የጽዳት ጉዳይ ለአንድ አካል የሚተው ጉዳይ ባለመሆኑ የሚመለከተው አካል ይህንን ችግር እንዲፈታ ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው አሳሰበዋል፡፡
የክፍለ ከተማው ምላሽ
የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፋኖስ ደቻሳ እንደሚናገሩት፣ ችግሩን በሚገባ የሚያውቁትና ኅብረተሰቡ በተደጋጋሚ ቅሬታ የሚያቀርብበት ጉዳይ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህንን ጉዳይ ከወረዳው ሥራ አስፈጻሚ ጋር በመሆን ሌላ አማራጭ ቦታ እየተፈለገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አሁን ላይ የወረዳ አስተዳደሩ በወሰደው እርምጃ ብዙ ቦታዎች ተገኝተው እንደነበር ጠቁመው፤ ነገር ግን የይገባኛል እና የካሳ ጥያቄ የሚነሳባቸው ቦታ በመሆናቸው እስካሁን ችግሩ እንዲዘገይ ሆኗል፡፡ አሁን ላይ እንደ አማራጭ አንድ ቦታ ተገኝቷል የሚሉት ኃላፊው፤ በዚያ ላይ ድርድር በማድረግ ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል ፡፡
ክፍለ ከተማው በትክክል በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ መግባት ከጀመረ ሦስት ወራት ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ ችግሩ የቆየና ከበፊት ሲንከባለል የመጣ እንደሆነም አመልክተዋል፡፡ ወረዳው ከክፍለ ከተማ ጋር ሆኖ አንድ አቋም ይዘን በመስራት ችግሩን እስካልፈታው ድረስ ልጆቹ መማር፣ ማቆም ብቻ ሳይሆን እዚያ አካባቢ ለመቆየት እራሱ አስቸጋሪ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ አሁን ግን ለጊዜው ከሥር ሥር እንዲነሳ እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፣ ዘላቂ መፍትሔው ላይ በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል ፡፡
በደረቅ ቆሻሻ የተደራጁት አካላት የሚያነሱት ቅሬታ እውነት ነው ያሉት ሥራአስኪያጁ፤ ለነዚህ አካላት የሚሰጠው ቦታ ትክክለኛነቱ ከተረጋገጠ በኋላ የሚተላለፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ችግሩ እኔ ሥራ ከጀመርኩበት ጊዜ ጀምሮ የሚነሳ ጉዳይ ሲሆን፤ ከክፍለ ከተማ ሆነ ከከተማ ጋር እንደ አጀንዳ አድርገን በየጊዜው የምናነሳው ጉዳይ ነው ያሉት ኃላፊው፤ የጉዳዩ አሳሳቢነት አጠያያቂ አይደለም፤ ስለዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ መፍትሔ ማምጣት እንችላለን በማለት ሃሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 08/2013