ራስወርቅ ሙሉጌታ
ቤተሰብ የሚመሰረትበት የየራሱ ዓላማ ያለው ቢሆንም ብዙኃኑ የሶስት ጉልቻን ጉዞ ሀ ብሎ የሚጀምረው ልጅ ወልዶ አይኑን በአይኑ ለማየት ብሎም ልጆቹን በጤናና በፍቅር በማሳደግ ለወግ ለማዕረግ ለማብቃት በማሰብ ነው። ነገር ግን አንዳንድ ግዜ ሁሉም እንዳሰቡት አይሆንምና በተለያዩ ምክንያቶች ልጅን አሳድጎና አስተምሮ ለወግ ለማዕረግ ለማብቃት አቅቷቸው ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር የሌሎችን ድጋፍ የሚሹት እናቶች ቁጥር በርካታ ነው።
የዛሬ እንግዶቻችንም ቀን ጎድሎባቸው ችግር በችግር ላይ ተደራርቦባቸው የቤተሰባቸው ህልውና ለአደጋ በተዳረገባቸው ወቅት በ«ፍቅር ለህጻናትና ቤተሰብ ልማት በጎ አድራጎት ደርጅት ድጋፍ» ህይወታቸውን ያቀኑ ቤተሰቦቻቸውን ከመበተንና ለተለያዩ ችግሮች ከመዳረግ የታደጉ እናቶች ናቸው።
ወይዘሮ መልካም ቢያልፈው ትባላለች ነዋሪነቷ በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ በተለምዶ ቻይና ካምፕ የሚባለው አካባቢ ነው። ከአምስት አመት በፊት ነበር ልጆቿን አብልቶ አጠጥቶ ለማስተማር ሲያዳግታት ወደ ፍቅር ለህጻናትና ቤተሰብ ልማት በጎ አድራጎት ድርጅት ያቀናችው። በወቅቱም ድርጅቱ ተቀብሎ ሲያደርግላት የነበረው ድጋፍ ለአንዱ ልጇ የትምህርትና ሌሎች ቁሳቁሶችን ማሟላት ብቻ ነበር። መልካም በዚሁ የኑሮ ውጣ ወረድ ውስጥ እያለች ትንሿና ሁለተኛ ልጇም ለትምህርት በመድረሷና እሷም ሆነ ባለቤቷ ወጪዋን ለመሸፈን የሚገዳቸው በመሆኑ በድጋሚ ወደ ድርጅቱ በማቅናት ሁለተኛ ልጇም ተመሳሳይ ድጋፍ እንድታገኝ ታደርጋለች።
ይህም ሆኖ ግን መልካም ልጆቿን የማስተማር ብቻ ሳይሆን ቤቷንም በተገቢው መንገድ እንዳታስተዳድር የነበረባት የገቢ ችግር ቤተሰቧ የሚፈልገውን ሳያገኝ እንዲኖር አድርጓት ነበር። እናም ይህንን ችግሯን የተረዳው ፍቅር ለህጻናትና ቤተሰብ ልማት በጎ አድራጎት ድርጅት እሷንም ቤተሰቧንም ለማቃናት የብድርና ቁጠባ አገልግሎት ተጠቃሚ እንድትሆን ከመሰል ጓደኞቸች ጋር እንድትደራጅ ያደርጋታል። በወቅቱ ድርጅቱ ሀያ ሰባት ተደጋፊዎችን በመምረጥ ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር የሚያስችላቸውን አቅም እንዲፈጥሩ በማለት አደራጅቶ የመንቀሳቀሻ ካፒታል በማቅረብና ከቢሮ ጀምሮ ሌሎች መሰረታዊ ነገሮችን በሟሟላት ማህበር ያስመሰርታቸዋል።
«በተለያዩ ግዜያት በማገኘው የብድር አገልግሎት የራሴን ስራ እየሰራሁ ለቤተሰቤም የሚያስፈልገኝን እያደረግሁ እገኛለሁ» የምትለው ወይዘሮ መልካም ከዚያ በፊት የነበረውን የእሷንና የቤተሰቧን ሁኔታ እንዲህ ታስታውሳለች። «ከዚህ ቀደም ስኖር የነበረው በቤት ኪራይ በችግር ወስጥ ከእጅ ወደ አፍ በሚባል የኑሮ ደረጃ ነበር። ብዙ ነገሮች አይሟሉልኝም ነበር። ችግር ሲበረታብኝ የጉልበት ስራ ተሯሩጬ ስሰራ ነበር፣ በቀበሌ ከሴቶችም ጋር ተደራጅቼ ለመስራት ሞክሬ ነበር፣ ነገር ግን ምንም ጠብ የሚል ነገር ሳላገኝ ቆይቻለሁ። በአሁኑ ወቅት ግን ከራሴ አልፌ ለሌሎች የምተርፍ ለመሆን በቅቼያለሁ። እዚህ ድርጅት ውስጥ ባልታቀፍ ኖሮ በእጣ ያገኘሁትንም የጋራ መኖሪያ ቤት እድል ላልጠቀምበት እችል ነበር። ያ ማለት ደሞ በህይወት ውስጥ አንዴ የሚገጥም እድልን ማጣት ነው። በቤት ኪራይ መኖር በጣም አስቸጋሪ ነው። ኪራዩ እያደር የሚጨምር በመሆኑ እኔም ሆንኩ ቤተሰቦቼ ሁሌም ለሰቀቀን ሁሌም ለሀሳብ ተዳርገን ቆይተናል። አሁን ግን ማህበሩ ባደረገልኝ ድጋፍ ከቁጠባ ወስጄ ቅድመ ክፍያ ከፍዬ አከራይቼው ቆይቼ አሁን አድሼ ስለገባሁበት እኔም ቤተሰቦቼም እረፍት አግኝተናል። ለምኜ ከመክፈልም ታድጎኛል።
በአሁኑ ወቅት መንግስት ባወጣው የስራ እድል በመጠቀም የጽዳት ስራ እየሰራሁ ቢሆንም ጥቅሙ ከፍተኛ ስለሆነና ለብዙ ነገር ያበቃኝ ጓደኞቼንም ከብዙ ችግር የታደገ በመሆኑ እስካሁን የብድርና ቁጠባው አባልና ጸሐፊ በመሆን ከየካ አባዶ እስከ መካኒሳ እየተመላለስኩ እያገለገልኩም እየተጠቀምኩም እገኛለሁ። በድርጅቱ የልብስ ስፌት ትምህርት ስለሰለጠንኩ ወደፊት በዚህም መስክ ለመስራት እቅድ አለኝ ትላለች።
በአሁኑ ወቅት የነበረብኝን እዳዬን እየከፈልኩ ከልዩ ልዩ ተቀማጮች ውጪ አምስት ሺ ብር ተቀማጭ አለኝ ። ማህበሩ በአሁኑ ወቅት በአባላት ቁጥር ዘጠና ስምንት የደረሰ ሲሆን ካፒታሉንም ከሶስት መቶ ሺህ ብር በላይ ለማድረስ በቅተዋል። ሁለት ሺ ሁለት መቶ የነበረውን የብድር ጣሪያም አስር ሺ ለማድረስ በቅተናል። በአሁኑ ወቅት ሀያ ሺ ለማድረግ እየሰራን ሲሆን በአካባቢያችን ያሉ በርካታ ቤተሰቦች ተጠቃሚ ለመሆን በቅተዋል። እኔም ቤተሰቤም በተፈጠረልን ነገር ደስተኞች ነን።
ሌላዋ እናት ወይዘሮ አለም ተሾመ የሁለት ልጆች እናት ሲሆኑ ኑሯቸውንም ያደረጉት መካኒሳ በተለምዶ አሮጌው ቤተ ክርስቲያን በሚባል አካባቢ ነው። ወይዘሮ አለም አንደኛዋ ልጃቸው በነርቭ ህመም ምክንያት የጤና መጓደል ያለባት በመሆኑ እሷን ለማሳከም ብሎም የእለት ጉርሷን ለማሟላት ከጎዳና ላይ ልመና ጀምሮ በርካታ መስዋዕቶችን ሲከፍሉ ቆይተዋል። ያለፈውን አምስት ዓመት ግን አስፈላጊው እንክብካቤና ድጋፍ እየተደረገላቸው በመሆኑ ቢያንስ ለልጃቸው የሚያስፈልጋቸውን ነገር አያስቡም። ወይዘሮ አለም በተለይ የኮሮና ወቅት ሁሉም ነገር ሲጨልምባቸው ከእለት ጉርስ እስከ ህክምና የተለያዩ ድጋፎች ሲያገኙ የነበረው ከፍቅር ለህጻናትና ቤተሰብ ልማት በጎ አድራጎት ድርጅት እንደነበር ይናገራሉ። በተለይም የሁል ግዜ ራስ ምታት የሚሆንባቸው የቤት ኪራይ ለዛ ወቅት አንድ ሺ ሶስት መቶ ብር ሲከፈልላቸው የተሰማቸው ደስታ አሁን ድረስ ከእሳቸው ጋር እንደሆነም ይናገራሉ።
ወይዘሮ አለም አሁንም ቢሆን ልጆቻቸውን የሚደግፍላቸው ሌላ ረዳት የሌላቸውና ብቻቸውን የሚኖሩ በመሆኑ እንዲሁም እንደልባቸው ተንቀሳቅሰው አቅማቸው የፈቀደውን እንዳይሰሩም የነርቭ ህመምተኛ የሆነችውን ልጃቸውን በቅርብ በመሆን መንከባከብ ስላለባቸው ተስፋቸውን ጥለው የተቀመጡት በፍቅር ለህጻናትና ቤተሰብ ልማት በጎ አድራጎት ድርጅት ላይ መሆኑንም ይናገራሉ።
በተመሳሳይ ወጣት ቤተልሄም አንተነህ መካኒሳ ቆሬ አካባቢ ሁለት ቁጥር ማዞሪያ ነዋሪ ስትሆን የአንዲት ሴት ልጅ እናትም ናት። የቤተልሄም ልጅ በልጅነቷ በገጠማት የጤና እክል መናገርና መስማት፤ መንቀሳቀስም ሆነ ምንም ነገር ራሷን ችላ ማድረግ አትችልም። እናም በየቀኑ የልጇን ጤና ለመጠበቅ ከፓምፐርስ ጀምሮ ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቁ በርካታ ወጪዎች ይጠብቋታል። ከግዜ በኋላም ከባለቤቷ ጋር ባለመስማማት የተለያዩ በመሆናቸው የልጇ ኃላፊነት በሙሉ የወደቀው እሷው ላይ ነው። እንደዚች አይነት ልጅ እቤት ውስጥ አስቀምጦ ስራ ውሎ መግባት የማይታሰብ በመሆኑም ወጣት ቤተልሄም ልጇን ለመንከባከብ የእለት ድጋፏን እያገኘች ያለችው ከዚሁ ድርጅት መሆኑን ትናገራለች።
ለመሆኑ «ፍቅር ለህጻናትና ቤተሰብ ልማት በጎ አድራጎት ድርጅት» ማነው ስንል የድርጅቱን ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳለ አሰፋን አነጋግረን አመሰራረትና ጉዞውን በተመለከተ የሚከተለውን አጫውተውናል ። ዘነበወርቅና ቆሬ የሚባሉት አካባቢዎች በከፍተኛ ችግር ውስጥ ያሉ የማህበረሰብ ክፍሎች ያሉባቸው ከመሆናቸው በተጨማሪ አካባቢው በርካታ የአካል ጉዳተኞችና የሥጋ ደዌ ህመምተኞች የሚኖሩበት በመሆኑ በከፍተኛ ድህነት ውስጥ የሚኖሩት ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ ነው። በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎችም የኑሯቸውን መሰረት የጣሉት ከከተማዋ ተስብስቦ ከሚደፋው ቆሻሻ በሚወጡ ምግቦችን በመመገብና ሌሎች ቁሳቁሶችን በመሸጥ ነው።በዚህም የተነሳ አብዛኞቹ ራሳቸውን ችለው ልጆቻቸውን ለማስተማርና ለማስተዳደር በቂ አቅም ያልነበራቸው በመሆኑ እነሱን በመደገፍ ለጥሩ ነገር ለማብቃት የተቋቋመ ድርጅት ሲሆን ቻይልድ ፈንድ ኢትዮጵያ ከሚባል ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በጋራ የሚሰራ ነው ።
ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ እና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሁለት ላይ ህጻናትንና እናቶችን መሰረት ያደረጉ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል። ድርጅቱ በዋነኛነት ህጻናትንና እናቶችን መሰረት ያደረጉ ድጋፎችን የሚያከናውን ሲሆን ይህንንም ዘላቂ እንዲሆን ለማስቻል በተለያዩ መንገዶች ቤተሰቦቻቸውን በማቋቋምና በመደገፍ ራሳቸውን እንዲችሉ በማድረግ ልጆቻቸውን በጤናና በፍቅር እንዲያሳድጉ እያበቃ ይገኛል። ለዚህም ከገንዘብና ብድር ቁጠባ ተቋማት ጋር በመሆንና እንዲደራጁ በማድረግ በተለያዩ የገቢ ማስገኛ ስራዎች እንዲሳተፉ እያደረገ ይገኛል። በዚህም አይነት እ ኤ አ ከ2010 ጀምሮ የተለያዩ ህጻናት ሴቶችና ቤተሰብ ተኮር ስራዎችን እያከናወነ ሲሆን ተቋሙ ዋና መነሻ አድርጎ የሚሰራው በከፍተኛ ድህነት ውስጥ ያሉትን በወረዳ ሴቶችና ህጻናት ቢሮ በኩል እየመረጠ በማስመጣት ቢሆንም አብዛኛዎቹ ችግረኞች ከመሆናቸው ባሻገር ልጆቻቸውን ብቻቸውን የሚያሳድጉ እናቶች መሆናቸውን አቶ እንዳለ ይናገራሉ።
ዳይሬክተሩ ጨምረው እንዳብራሩት ምንም እንኳን ድርጅቱ ሲቋቋም በተለይ ህጻናት ላይ ትኩረት የሚያደርግ ሲሆን እነዚህን ህጻናት ያለ ቤተሰቦቻቸው ጥበቃ ሊደረግላቸው የሚችለው ድጋፍ ውጤታማ የመሆኑ ጉዳይ አጠራጣሪ በመሆኑ አብዛኛው ክትትልና ድጋፍ የሚደረገው ቤተሰቦቻቸውንም ባካተተ መልኩ ነው። በተጨማሪ ልጆች የትኛውም አይነት ፍላጎቶቻቸው ቢሟሉላቸው ከቤተሰብ ጋር ሲኖሩ ሊያገኙት የሚችሏቸውን ሥነልቦናዊና ማህበራዊ ጥቅሞች ያለወላጆች ሲኖሩ ሊያገኙ ስለማይችሉ ድጋፉና ክትትሉ እንዲደረግላቸው የሚመረጠው ከቤተሰብ አልያም ከቅርብ ዘመዶቻቸው ጋር ሆነው ነው።
በዚህም መሰረት ድርጅቱ ለህጻናት የሚያደርገውን ድጋፍ በሶሰት አይነት መልኩ የሚከውን ሲሆን ዋናው ዓላማውም ህጻናትንና ልጆችን በመንከባከብ እድሜያቸው ሲደርስ ከቤተሰብ ጥገኝነት ተላቀው ለተለያዩ ሱሶችና ማህበራዊ ችግሮች ተጋላጭ ሳይሆኑ ጤናማ፤ ብቁ፤ አምራች ዜጋ ሆነው ለራሳቸው፤ ለቤተሰባቸውና ብሎም ለሀገራቸው እንዲተርፉ ለማብቃት ነው። ይህንንም ከግብ ለማድረስ በቀዳሚነት እናቶችን በቅድመ ወሊድ ወቅት አስፈላጊውን እንክብካቤ እንዲያገኙ ክትባት፤ የቤተሰብ ምጣኔና ሌሎች የምክርና የግብዓት አገልግሎቶችና አቅርቦትና እንዲሁም ተመሳሳይ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛል። እነዚህ አገልግሎቶችም ተደራሽ የሚደረጉት እንደ ቤተሰብም እንደ ማህበረሰብም ነው።
በድህረ ወሊድ ደግሞ በተለይ ከአምስት አመት በታች ለሆኑት ልጆች ይሄ አገልግሎት ተደራሽ የሚደረግ ሲሆን በየሶስት ወሩ ኪሏቸውን ከመመዘን ጀምሮ አስፈላጊውን ምርመራ በማድረግ የተመጣጠነ ምግብ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመቻች ይደረጋል። ከምግብ አዘገጃጀት፤ ከልጅ አያያዝና አጠባበቅ እንዲሁም አስተዳደግና ቤት ውስጥ ለትምህርት ማዘጋጀትን ስልጠና እንዲያገኙ ይደረጋል። ይህም ድርጅቱ በአካባቢው ለሚገኙ የመንግሥት ትምህርት ቤቶችና የጤና ተቋማት ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ ማለት ነው። በሌላ በኩል አስገዳጅ ሁኔታ ውስጥ ካልሆኑ በቀር እናቶች እቤት እንዳይውሉ ለማድረግ የሥራ እድል ፈጠራ ላይ የሚሰራ ሲሆን እንጀራ በመጋገር፤ በጉሊትና በችርቻሮ ንግድ እንደየ ፍላጎታቸውና ብቃታቸው እንዲሰማሩ ከብድር አቅርቦት ጀምሮ ሁኔታዎች ይመቻቹላቸዋል።
በሁለተኛ ደረጃ ከስድስት እስከ አስራ አራት ዓመት ለሆናቸው ተማሪ ልጆች በየትኛውም የትምህርት ደረጃ ቢሆኑ በራሳቸው የሚተማመኑ ሆነው እውቀት እንዲገበዩ ለማስቻል በትምህርት ሂደት ውስጥ የሚያስፈልጉ ነገሮች ሊሟሉላቸው ይገባል። በዚህም ከችግረኛ ቤተሰብ ለሚመጡት የደንብ ልብስ የምግብ የትምህርት ቁሳቁስ አቅርቦት የሚሟላ ሲሆን። ለየቤተሰቦቻቸውም ፓረንቲንግ ኤዱኬሽን (የልጅ አስተዳደግ አዋዋል ትምህርት ክትትልና የልጆችና የቤተሰብ ግንኙነትን) የሚመለከቱ ነገሮችን በማስተማር ቤተሰብ ልጆችን በጥሩ ሥነ ምግባር የማሳደግ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ለመወጣት እንዲችሉ የማብቃት ስራ ይሰራል። እነዚህ ልጆች በትምህርት ቤት የሚኖራቸውም ቆይታ የተስተካከለ ሊሆን ስለሚገባ ከትምህርት ቤቶችና ከመምህራንም ጋር በተመሳሳይ የሚሰሩ ሥራዎች አሉ።
በሶስተኛ ደረጃ ደሞ ከአስራ ስድስት እስከ ሀያ አራት ዓመት ለሚሆናቸውና በተለይ በሁለተኛ ደረጃ ለሚማሩ ተማሪዎች የሚደረግ ድጋፍና እንክብካቤ ሲሆን እነዚህንም በትምህርት ወቅት ከሚደረግላቸው ድጋፍ ባለፈ ነጥብ መጥቶላቸው ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገቡ ከሆነ ለእነሱ ቤተሰብ ሊያደርግላቸው ያልቻላቸውን ድጋፍ በማሟላት ትምህርታቸውን እንዳያቋርጡ ብቻ ሳይሆን ውጤታማም እንዲሆኑ ክትትልና ድጋፍ። ነጥብ ያልመጣላቸው ከሆኑ ደግሞ ስራ ፈት በመሆን የቤተሰብ ሸክም ሆነው እንዳይቀሩ በተለያየ መልክ ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ አልያም የሙያ ስልጠና እንዲወስዱ በማድረግ የስራ እድል ተፈጥሮላቸው ወደስራ እንዲገቡ። አንዳንዶቹም በበጎ ፈቃድ አገልግሎት እንዲሳተፉ ከማድረግ ጀምሮ ሁኔታዎች እንዲመቻቹላቸው ይደረጋል። በተለይም ወጣቶች በትምህርት ወቅትና ከትምህርት በኋላ ካለ እቅድ በማርገዝ በቤተሰባቸው ላይ ጥገኛ በመሆን ራሳቸውንም ቤተሰባቸውንም ለተለያዩ ችግሮች እንዳይዳረጉ ድርጅቱ በተለያየ መንገድ የስነተዋልዶ አገልግሎት እንዲያገኙ ያደረጋል።
ቤተሰብ ባለበት እንዲቀጠል ችግረኛ ወላጆች የብድር አገልግሎት በማመቻቸት ተደራጅተው እንዲቆጥቡ የሚደረግ ሲሆን አብዛኛው የድርጅቱ አባል የዚሁ አካል መሆኑን የሚናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ እንዳለ ። በአሁኑ ወቅት ቻይልድ ፈንድ ኢትዮጵያ ከሁለት ሺህ አምስት መቶ በላይ ህጻናት ድጋፍ የሚደረግላቸው ሲሆን በዩአኤስ አይዲ በኩል ደግሞ አስራ ሁለት ሺህ ህጻናት አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል እየተደረገላቸው ነው፡፡ በቀጣይም በተለየ ድጋፍ የገቢ ምንጫቸው ዝቅተኛ የሆነባቸውን ቤተሰቦች በቋሚነት የስራ እድል እንዲፈጠርላቸው በማድረግ ራሳቸውን ችለው እንዲኖሩ ለማስቻል እየተንቀሳቀሱ መሆኑንም ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 08/2013