ልጆች በወላጆቻቸው እቀፍ ማደጋቸው ለሚኖራቸው ሁለንተናዊ እድገት በምንም የማይተካ ሚና አለው። ነገር ግን በአንዳንድ ጉዳዮች ወላጆቻቸውን ሲያጡ አልያም ከወላጆቻቸው ሲነጠሉ ደግሞ የወላጅ ምትክ የሆነና የቤተሰብን ሚና የሚወጣ አቤት ባይ ያስፈልጋቸዋል። በተለይም ችግሩ የገጠማቸው ገና በህጻንነት እድሜያቸው ከሆነ ራሳቸውን ችለው የሚያስፈልጓቸውን መሰረታዊ ፍላጎቶች ማሟላት ስለማይችሉ የግድ አቤት ባይ ግለሰብ አልያም ተቋም ያሻቸዋል። በተለያዩ ቦታዎች እንደምንመለከተው ከቤተሰባቸው የተነጠሉና የእኔ ብሎ የሚቀበላቸው አካል ያጡ ህጻናት ለጎዳና ህይወት መዳረግ ቀዳሚ መዳረሻቸው ነው።
የጎዳና ህይወት ደግሞ እንኳን አጥንታቸው ላልበረታ አቅማቸው ላልጠነከረ ህጻናትና ልጆች ይቅርና ለአዋቂውም ቢሆን የመከራ የሰቆቃ ስፍራ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው። የጎዳና ህይወት በአንድ ወገን እንደ ምግብ መጠጥና ልብስ ያለው ስጋዊ የሆነው መሰረታዊ ፍላጎት የሚገኝበት ካለመሆኑ ባሻገር ነግቶ በጠባ ከድብደባ እስከ አስገድዶ መድፈር ያሉ ወንጀሎች የልማድ ያህል የሚፈጸሙበት ቦታ ነው። አዲስ አበባ ደግሞ ይህ ትእይንት በስፋት የሚከወንባት ከተማ ስትሆን በየቀኑም ከሌሎች ክልሎችም ሆነ ከጉያዋ የሚወጡ ልጆች የጎዳናን ህይወት ይቀላቀሉባታል።
ክበበ ጸሀይ ህጻነት እንክብካቤ ማእከል ከስልሳ ዓመታት በፊት የተቋቋመና በአዲስ አበባ ከተማ ከወላጆቻቸው የተነጠሉ ህጻናት ልጆችን እየተንከባከበ የሚገኝ መንግስታዊ ተቋም ነው። ተቋሙ ባሳለፈው ከግማሽ ምእተ ዓመት በላይ እድሜ በርካታ ህጻናትን በመታደግ ለቁም ነገር ማብቃት ችሏል። እኛም በዛሬው የቤተሰብ አምድ እትማችን ይህንን አንጋፋ የህጻናት መንከባከቢያ ማእከል የተቋሙን ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሀብታም ነጋሽን በማነጋገር የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል።
ዋና ስራ አስኪያጇ ወይዘሮ ሀብታም እንደሚያብራሩት ክበበ ጸሀይ ህጻነት እንክብካቤ ማእከል ተከትቦ የተቀመጠ ማስረጃ ባይገኝለትም በአስራ ዘጠኝ ሀምሳ ሁለት እንደተመሰረተ የሚያመላክቱ በርካታ ፍንጮች አሉ። በአሁኑ ወቅትም በተቋሙ ውስጥ አንድ መቶ ሃያ አምስት ህጻናትን ይዞ በመንከባከብ ላይ ይገኛል። ከእነዚህ መካከል ሰላሳ አምስት የሚሆኑት የልዩ ፍላጎት ውስጥ የሚካተቱ ናቸው። የየራሳቸው የሆነ የጤና እክል ያለባቸው በመሆኑ ከፍተኛ እንክብካቤና ክትትል የሚያስፈልጋቸው ናቸው። ብዙ ጊዜ በእንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ ያሉ ህጻናትን በጉድፌቻም ሆነ በአደራ ለመውሰድ ፈቃደኛ ቤተሰብ አይገኝም። ተቋሙ ባለው አቅም የሚያስፈልጋቸውን ለማሟላት እየሰራ ይገኛል። ነገር ግን በዘላቂነት መፍትሄ ለመስጠት ዛሬም ቢሆን ፈቃደኛ ሆኖ ወስዶ የሚያሳድጋቸው እስከዚያውም ድረስ የተለያዩ ድጋፎች የሚያደርግላቸው እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።
ወይዘሮ ሀብታም ጨምረው እንዳብራሩት ከላይ የተጠቀሰው የህጻናቱ ቁጥር ዛሬ ላይ በተቋሙ ያሉትን ህጻናት ቁጥር ብቻ የሚያሳይ ነው። ተቋሙ በዚህ አይነት ባሳለፈው ከግማሽ ምእተ ዓመት በላይ በርካታ ህጻናትን በጉድፈቻና በአደራ ቤተሰብና ሌሎች መንገዶች እያገናኘ ከማህበረሰቡ ጋር ሲያቀላቅል ቆይቷል። በተጀመረበት ወቅት የነበረው አካሄድ ተመዝግቦ ባይቀመጥም በአሁኑ ወቅት ህጻናቱ ማእከሉን የሚቀላቀሉት አንዳንዶቹ ወድቀው የተገኙ ሲሆን እነዚህም በማህበረሰቡ ጥቆማ በፖሊስና በሴቶች ጉዳይ በኩል አስፈላጊው ማጣራት ተደርጎላቸው ነው። በዚህ ሁኔታ አስፈላጊው እንክብካቤ እየተደረገላቸው በማእከሉ እንዲቆዩ ከተደረጉ በኋላ የሚወስዳቸው ቤተሰብ ሲገኝ ለአሳዳጊ ይሰጣሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንደ ጊዜ የህጻናቱ ወላጆች በወንጀል ተጠርጥረው በህግ ጥላ ስር ሲውሉ በቅርብ የሚንከባከባቸው ቤተዘመድ አልያም ጓደኛ የሌላቸው ህጻናትም ማእከሉን እንዲቀላቀሉ ይደረጋል። ከእነዚህ ውጪ ደግሞ ወላጆች አልያም አሳዳጊዎች የአእምሮ ህመምተኛ መሆናቸው ሲረጋገጥና ልጆቹ ያሉበት ሁኔታ አስቸጋሪ በሚሆንበት ወቅትም ወደ ማእከሉ የሚገቡ ህጻናት አሉ። በዚህ አይነት ማለትም በእስርና በህመም ከወላጆቻቸው የሚለዩት ህጻናት በማእከሉ የሚኖራቸው ቆይታ የሚወሰነው የታሰሩ ከሆነ ወላጆቻቸው ከእስር ነጻ እስከሚሆኑ የጤና እክል የገጠማቸውም ከሆነ ጤናቸው መመለሱ እስከሚረጋገጥ ብቻ ይሆናል።
ከላይ በተዘረዘሩት ሶስት መስፈርቶች ተቋሙን የሚቀላቀሉት ህጻናት በማእከሉ የሚኖራቸው ቆይታ እንደየሁኔታው የተለያየ ነው። ማእከሉ ህጻናቱን የሚቀበለው ከተወለዱ ጀምሮ ያሉ ጨቅላ ህጻናትን ስምንት ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ ያሉትን ብቻ ነው። ነገር ግን ህጻናቱ በማእከሉ ውስጥ ሆነው ስምንት ዓመት ከሞላቸው በኋላ በተለያዩ አግባቦች የሚወስዳቸው ቤተሰብ ካልተገኘ ወንዶች ከሆኑ ወደ ኮልፌ የወንዶች ህጻናት ማሳደጊያ ተቋም ፤ እንዲሁም ሴቶች ከሆኑ ደግሞ ወደ ቀጨኔ ሴቶች ህጻናት ማሳደጊያ ተቋም የሚዛወሩ ይሆናል። እነዚህ ሁሉም ተቋማት በአዲስ አበባ በሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ስር የሚተዳደሩ ሲሆን የመንግስት ተቋማት ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ሲገጥም ወደ ሌሎች የግል ድርጅቶችም ተዛውረው በአደራ እንዲቆዩ የሚደረግበት አሰራር አለ። ይህ ሲደረግም የአዲስ አበባ ሴቶችና ህጻናት ቢሮና ተቋሙ ልጆቹ ያሉበትን ሁኔታ በቅርብ ክትትል ያደርግላቸዋል።
በሌላ በኩል ህጻናቱ ስምንት ዓመት እስኪሞላቸው ድረስ በጉድፈቻ ለመውሰድ የሚመጡ ቤተሰቦች ሲኖሩ ባለው የህግ አግባብ መሰረት አዲሱን ቤተሰባቸውን እንዲቀላቀሉ የሚደረግ ይሆናል። በዚህ መልኩ የተወሰዱ ልጆችንም በአዲሱ ቤታቸው ውስጥ የተለያዩ በደሎች እንዳይደርሱባቸውና መብቶቻቸውን እንዳያጡ ተቋሙ ከሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ጋር በመሆን በተመሳሳይ የረጅም ጊዜ ያልተቋረጠ ክትትል የሚያደርግላቸው ይሆናል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ አሳዳጊዎችም በመመሪያው መሰረት በሚቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ልጆቹ ያሉበትን የደህንነት ሁኔታ በፎቶ የተደገፈ መረጃ የሚያቀርቡ ይሆናል።
በተጨማሪ ተቋሙ የራሱ የህግ ባለሙያ ያለው በመሆኑ ህጻናቱ በጉድፈቻም ሆነ በአደራ ቤተሰብ ተወስደው ተቋሙን ከለቀቁበት ጊዜ አንስቶ የመብት ጥሰትና አካላዊም ሆነ ስነልቦናዊ ጉዳት እንዳይደርስባቸው በእነዚህ የህግ አካላት ክትትል ይደረጋል። ከዚህ ውጪ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ የህጻነቱ ቤተሰብ ልጆቹ በተለያየ ምክንያቶች ጠፍተውባቸው አልያም ተለይተዋቸው ከነበረና አሁን ለመውሰድ ከፈለጉ በህጋዊ መንገድ አስመስክረው ሲመጡ ተቋሙ የማቀላቀል ስራ የሚሰራ ይሆናል።
ይህም ሆኖ ህጻናቱ ወደማቆያው የሚመጡበት ሁኔታ ከጤናቸው ጀምሮ የተለያየ ነው። በመሆኑም በተቋሙ በመሰረታዊነት ለሁሉም የመጠለያ፤ የምግብና መጠጥ የመሳሰሉት የቁሳቁስ ድጋፍ የሚደረግላቸው ሲሆን በተጨማሪ የህክምናና የስነልቦና ድጋፍም በባለሙያዎች የሚደረግላቸው ይሆናል። ለዚህም በተቋሙ የህክምና ማእከል ያለ ሲሆን ለዚህ ስራ የተመደቡ የህክምና ባለሙያዎችም ክትትል እንዲያደርጉላቸው ይደረጋል።
ተቋሙ እነዚህን ስራዎች ሲሰራ የሚገጥሙት አንዳንድ ችግሮች አሉ የሚሉት ዋና ስራ አስኪያጇ ወይዘሮ ሀብታም ማእከሉ ህጻናቱን የሚቀበለው የፍርድ ቤት የፍቃድ ወረቀት ሲያገኝ ነው። ነገር ግን ህጻናቱ የተገኙትና ወደማእከሉ የሚገቡት በስራ ቀናት ካልሆነ ተቋሙ ፍርድ ቤት ስራ ላይ ስለማይሆን የፍርድ ቤት ወረቀቱ እስኪመጣ ድረስ የሚቀበላቸው ይዘዋቸው በመጡት ፖሊሶች መታወቂያ ብቻ ይሆናል። በዚህ ሁኔታ ከገቡ በኋላ የፍርድ ቤቱን ወረቀት ለማምጣት መዘግየት ስለሚፈጠርና ማእከሉ አንዳንድ አገልግሎቶችን ለመስጠት በህጋዊ መንገድ ተቋሙን መቀላቀላቸው መረጋጋጥ ስላለበት መጉላላት ይፈጠራል። በመሆኑም በመታወቂያ የሚያስገቡበት አስገዳጅ ሁኔታ ስለሚኖር ይህንን ማድርጋቸው ተገቢ ነው ነገር ግን ይህን ካደረጉ በኋላ በፍጥነት የፍርድ ቤቱን ወረቀት ቢያቀርቡ ሲሉ ምክረ ሀሳባቸውን ሰንዝረዋል። በተጨማሪ ተጥለው የተገኙ ልጆችን በተመለከተ እናትና አባት እንዳልተገኘላቸውና ወደ ጉድፈቻ መዞር እንደሚችሉ የሚፈቅድ ሁለተኛ ደብዳቤ ስለሚያስፈልግ በተመሳሳይ ከፍርድ ቤት ለማግኘትም የመዘግየት ሁኔታ ይታያል። ይህ የተለያዩ በጉድፈቻና በአደራ ሊዛወሩ ይችላሉ የሚለውን ደብዳቤ ለማግኘት የሚወስደው ጊዜ መርዘም ህጻናቱን ለመውሰድ የመጡትን ቤተሰቦች እያጉላላ ይገኛል። በእርግጥ አፈላልጎ ቤተሰብ የላቸውም የሚለውን ውሳኔ ለመወሰን ረዥም ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም ከህጻናቱ ልዩ ጥቅም አንጻር በተቻለ ፍጥነት ቢጨረስ የተሻለ ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል።
በተጨማሪ ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት ለህጻናቱ ሰርተፍኬት ለመውሰድ ባለው ሂደት ወረዳው ልዩ ትኩረት በመስጠት ፈጣንና የተቀናጀ አገልግሎት የሚሰጥ ቢሆንም የአሰራር ክፍተት አለ። ይህም ህጻናት ወደ ማእከሉ ሲመጡ ስም ያልነበራቸው አንዳንዶቹም የማይታወቅ በመሆኑ ስማቸውን የሚያወጣው ማእከሉ ነው። በዚህ አይነት አካሄድ የሁሉም አባት ሰም የሚሆነው የማእከሉ መጠሪያ ክበበ ጸሀይ ነው። ነገር ግን በፖሊስ ተጣርቶ የመጡና የራሳቸውና የአባታቸው ሰም የታወቁ ከሆነ በዛው እንዲመዘገቡ ይደረጋሉ። በዚህ ሂደት ለገቡት የልደት ሰርተፍኬት ሲሰራ የአባት ስም ካለ አባትና እናት ካልቀረቡ የልደት ሰርተፍኬቱን መስራት አይቻልም የሚባል አሰራር አለ። ይህ አካሄድ ደግሞ አባትና እናት ቢታወቁም ማቅረብ ስለማይቻል የተቋሙ ስራ እንዳይቀላጠፍ ከማድረግ ባሻገር ለህጻናቱም ተገቢውን አገልግሎት በወቅቱ እንዳያገኙ መሰናክል እየፈጠረ ይገኛል። በተጨማሪ በተቋሙ ውስጥ የራሱ የህክምና ማእከል ያለው ቢሆንም ለተጨማሪ ሀክምና ህጻናቱን ወደ ሌላ ሆስፒታል መላክ ሲያስፈልግ የሚወስድ አምቡላንስ የለም። ይህ በፍጥነት ሊቀረፍ የሚገባው አንዱ የተቋሙ ችግር ነው።
እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ የጉድፈቻ አገልግሎቱ ዝቅተኛ ነበር በዓመት የጉድፈቻ አገልግሎት ሊያገኙ የሚችሉትም ልጆች ከአስር የዘለሉ አልነበሩም የሚሉት ዋና ስራ አስኪያጇ ወይዘሮ ሀብታም። በዚህ ዓመት ግን ተቋሙ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ከግንዛቤ ፈጠራ ጀምሮ በሰራው ስራ፤ እየተጠናቀቀ ባለው በጀት ዓመት ሁለት መቶ ልጆችን በጉድፈቻና በአደራ ከአሳዳጊዎች ጋር ማገናኘት መቻሉን ተናግረዋል።
ወይዘሮ ሀብታም ጨምረው እንደተናገሩት ተቋሙ በአሁኑ ወቅት ሁለት መቶ ለሚደርሱ ዜጎች የስራ እድል የፈጠረ ቢሆንም ከሚሰጠው አገልግሎት አኳያ ግን በቂ አይደለም። የእንክብካቤ ሠራተኞች መቶ ናቸው። በስታንዳርዱ መሠረት ከተሄደ አንድ የእንክብካቤ ሠራተኛ አገልግሎት (ማብላት፤ ማጠጣት፤ ማልበስና የመሳሰሉትን) መስጠት ያለበት ለሁለት ህጻናት ነው። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በተቋሙ አራት ፈረቃ ያለ ሲሆን በአንድ ፈረቃ የሚገቡት ሀያ አምስት ብቻ በመሆናቸው ከፍተኛ የስራ ጫና አለ። በተጨማሪ ጥቂት የማይባሉ ልዩ ፍላጎት ያላቸው ልጆች መኖራቸው ደግሞ የእንክብካቤ ሠራተኞቹ ላይ የሚፈጥረው ተጽእኖ አለ። ይህም ሆኖ እስካሁንም ስራውን በጫና ውስጥ ሆነው ሊሰሩት የቻሉት የእንክብካቤ ሠራተኞቹ በእድሜያቸው የገፉና ለልጆቹ እና ለተቋሙ ትልቅ አክብሮትና ፍቅር ስላላቸው ነው።
ትምህርትንም በተመለከተ ተቋሙ የራሱ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ያለው ሲሆን ትምህርት ቤቱ ከመደበኛ ትምህርት ባለፈም ህጻናቱ ከማህበረሰቡ ጋር ያላቸው ቁርኝት የተጠናከረ እንዲሆን እየሰራ ይገኛል። ለዚህም በራሱ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤት ከተቋሙ ልጆች በተጨማሪ የአካባቢውንም ልጆች ቀላቅሎ እያስተማረ ይገኛል። የተቋሙ ልጆች የቅድመ መደበኛ ትምህርታቸውን ከጨረሱም በኋላ ከአንደኛ ክፍል ጀምረው የሚማሩት ከሌሎች ልጆች ጋር ተቀላቅለው ነው።
ልጆች በተለያዩ ምክንያቶች ከወላጆቻቸው ሊነጠሉ የሚችሉበት አስገዳጅ አጋጣሚ ሊፈጠር ይችላል። ነገር ግን ዛሬ ዛሬ እየተደጋገመ የመጣው ልጅን ጥሎ የመሠወር ልማድ ሊቀረፍ የሚገባው አሳሳቢ ጉዳይ ነው የሚሉት ወይዘሮ ሀብታም። ይህ ተግባር በአንድ ወገን ከኢትዮጵያዊነት ባህል ያፈነገጠ ተግባር ነው። በሌላ በኩል ካለ እቅድና ዝግጅት ልጅ ላለመውለድ የሚደረገው ጥንቃቄ እንደተጠበቀ ሆኖ ነገሩ ከተከሠተ ግን የህሊና ጠባሳ የሚያስቀምጥና የአብራክን ክፋይ ለክፉ ነገር ከሚዳርግ ተግባር በመቆጠብ ሌሎች አማራጮችን ማማተር ያስፈልጋል። ተቋሙ እንዲህ አይነት ችግር የገጠማቸውን ረዳት በማፈላለግም ለመተባበር ዝግጁ በመሆኑ ተመሳሳይ ችግር የገጠማቸው በቅድሚያ ወደ ተቋሙ በመምጣት የምክርም ሆነ ሌሎች ድጋፎችን የሚያገኙበትን ሁኔታ መሞከር እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል። እንደ ግለሰብም ከገንዘብ እጥረትም ሆነ ቤተሰብ ምን ይለኛል የሚለውን የአንድ ሰሞን ወሬ መሆኑን በመገንዘብ በወቅቱ አስፈላጊውን ማድረግ አለባቸው። እንደ አጠቃላይ ማህበረሰቡም የጠቅላይ ሚንስትሩንና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች በቅርቡ እያደረጉት ያለውን ወላጅ አልባ ልጆችን የማሳደግ ተግባር ሊከተሉ ይገባል። ቀናነቱ ካለ ያለ ውጪ ድጋፍ እርስ በእርሳችን በመረዳዳት ብቻ ይህንን ችግር መቅረፍ ስለምንችል እያንዳንዳችን የአቅማችንን ለማድረግ መንቀሳቀስ ይጠበቅብናል ሲሉ ተናግረዋል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 5/2013