ይቅርታ በተፈጥሮ ባህሪው ስህተት የማያጣው የሰው ልጅ ከመሰሉ ጋር ለሚኖረው አብሮነት ወሳኝ አስተዋጽኦ አለው። በምድር ላይ ፍጹማዊ የሆነ፤ ከስህተትና ተገቢ ያልሆኑ ነገሮችን ከመከወን አልያም ከመናገር የጸዳ ሰው ስለማይኖር እያንዳንዱ ሰው በተለያዩ አጋጣሚዎች ለሰራቸው ስህተቶች በይፋም ሆነ በስውር የሌሎችን ይቅርታ መቸሩ የግድ ነው። አንዳንድ ግዜ ደግሞ የሚጠፉት ጥፋቶች አልያም የሚሳሳታቸው ስህተቶች የሚጎዱት ወይንም የሚያጎሉበት የራሱን ጉዳይ ብቻ ይሆንና ሌሎችን ባያስቀይምም «ራስ አይቀጡ» የሚለውን ብሂል ተከትሎ ለራሱ ይቅርታ ማቅረቡም መስጠቱ አይቀርም።
ይቅር ባይነትም ሆነ ይቅርታ መጠየቅ ለስህተት ፈጻሚው የሚሰጠው ትልቅ የህሊና እረፍት መኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ ይቅርታ ለሚቀርብለትም ሰው የሚያጎናጽፈው ትልቅ የሞራል ልዕልና ይኖራል። በተለይም ይቅርታ የተጠየቀው አልያም ጥያቄው የቀረበለት ሰው ከበዳዩ ወይንም ከስህተት ፈጻሚው ጋር የቀረበ ግንኙነት ያለው ከሆነ ደግሞ መሳሳትን ማመን ብቻ ሳይሆን ለሚቀርቡት ወዳጅ ያለንም ክብር የሚያሳይ ይሆናል። ለመሆኑ በትዳር ግንኙነት ውስጥ ለሁለቱ ጥንዶችና አጠቃላይ በቤተሰብ ግንኙነት ወስጥ የይቅርታ ፋይዳ ምን ይመስላል። ስንል የማህበረሰብ ሳይንስ ባለሙያ የሆኑትን አቶ ቴዎድሮስ ይርጋን አነጋግረን የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል።
አቶ ቴዎድሮስ እንደሚያብራሩት ስህተት ከሰው ልጅ የተፈጥሮ ባህሪያት መካከል እንደ አንድ የሚወሰድና በማንኛውም ሰው ላይ በተለያዩ ግዜያቶችና ምክንያቶች የሚከሰት ነው። የሰው ልጅ አንዳንድ ስህተቶችን ባለማወቅ፤ ከመረጃ እጦት ወይንም በወቅቱ በትክክል መደረግ ያለባቸው ሆነው አግኝቷቸው ሊፈጽማቸው ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ የሚሰራው ስራ አልያም የሚናገረው ነገር ስህተት መሆኑን እያመነ በተለያዩ እንደ ንዴት፤ ግብታዊነትና አልሸነፍ ባይነት ባሉ ስሜቶች በመገፋፋት ሊፈጽመው ይችላል።ስህተቶቹ በየትኛውም መልኩ ቢፈጸሙ በትክክለኛው አካሄድ ባለመከወናቸው የሚያስቀይሙት፤ የሚያስከፉት ወይንም ጫና የሚፈጥሩበትና ለችግር የሚዳርጉት ሌላ አካል መኖሩ አይቀርም።
በተሰራው ስራ ቅር የሚሰኝ ሁለተኛ ወገን ሰው ባይኖር እንኳን ፈጻሚው ራሱ ላይ የሚፈጠር ስሜት (ጸጸት) መኖሩ አይቀርም። በመሆኑም ስህተቶች መፈጸማቸው ከታወቀ ወደ ግጭት፣ አላስፈላጊ ጭቅጭቅና ጸብ ከመቀየራቸው በፊት ባሉበት እንዲቀጩ የሚያደርግ ዋንኛው መንገድ ይቅርታ ነው። በተለይም ይቅርታ ጠያቂውና ይቅርታ ተጠያቂው ያላቸው ቀረቤታ ጠንካራ ከሆነ ይቅርታ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ ይሆናል። በዚህ አይነት ጠንካራ ትስስር ከሚፈጠርባቸው ማህበራዊ ግንኙነቶች መካከል ደግሞ ቀዳሚው የትዳርና የቤተሰብ ግንኙነት ነው።
ቤተሰብ በትዳር አማካይነት በሁለት ጥንዶች የማህበረሰብ አንድ ክፍል የሆነ እንደ ተቋም የሚወሰድ በስጋ ግንኙነት ትስስር ጭምር የሚመሰረት ነው። በትዳር ወስጥ የሚኖሩ ግንኙነቶችም ከሌሎቹ የሰው ልጅ የእለት ከእለት ግንኙነቶች ፈጽመው የተለዩ ናቸው። አንድ ግለሰብ ከትዳር አጋሩና ከቤተሰቡ ጋር የሚኖረው አይነት ግንኙነት በሌሎች ጉዳዮች ከሚያገኛቸው ሰዎች ጋር ተመሳሰይ ሊሆን አይችልም። ለምሳሌ አንድ ሰው በጓደኝነት የሚቀርበው ወዳጅ ቢኖረው ደረጃው ቢለያይም የሚኖራቸው ግንኙነት በሁለት ሰዎች መካከል እንደሚኖር የጓደኝነት ትስስር ብቻ ነው። በተመሳሰይ በስራ ምክንያት፤ በሀይማኖት ክዋኔዎች እንዲሁም በተለያዩ ማሀበራዊና ፖለቲካዊ ስብስቦች የሚገናኘው ሰው ቢኖረውም ግንኙነቱ በዋናነት የሚወሰነው የጋራ በሆናቸው ጉዳይ ላይ ብቻ ተንተርሶ ይሆናል። በትዳርና በቤተሰብ ግንኙነት ወስጥ ግን ሁሉን ተሳታፊዎች አንዳቸው የአንዳቸው ጉዳይ ሙሉ ለሙሉ የሚመለከታቸው ይሆናል። በመሆኑም ሰዎች በእለት ከእለት የሚከውኗቸው ነገሮችና የሚወስኗቸው ውሳኔዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከቤተሰባቸው ጋር ግንኙነት ይኖረዋል፤ እነሱን ይመለከታል ማለት ነው።
በትዳርና በቤተሰብ ውስጥ የሚፈጠረው ግንኙነት ወሰን አልባ ከመሆኑ ባሻገር በአብዛኛው በህሊና ዳኝነት ላይ የተመሰረተም ነው። የህሊና ዳኝነት በሌሎቹ የሰው ልጅ የእለት ከእለት ግንኙነቶች መካከል ያለ ቢሆንም በቤተሰብ ውስጥ እንዳለው ጠንካራና ወሳኝ ሊሆን ግን አይችልም። ሁለት ጓደኛማቾች የማያስማማቸው ነገር ቢገጥማቸው በቀላሉ ግንኙነታቸውን ሊያቋርጡት ይችላሉ አልያም በህግና በሽማግሌ አልያም በመራራቅ የተፈጠረውን ችግር መቋጫ ሊያበጁለት ይሞክሩ ይሆናል። በቤተሰብ መካከል የሚፈጸም ስህተት አልያም ጥፋት ግን በዚህ መልኩ በሚገኝ ውሳኔ የሚፈታበት አካሄድ አዋጭ ሊሆን ስለማይችል ይቅርታ ትልቅ ቦታ ይኖረዋል። በቤተሰብ ውስጥ የሚኖር ግንኙነት ደግሞ ቀጣይነት ያለው፤ በግዜና በቦታ የማይገደብ በመሆኑ የሚቀርበው ይቅርታ ያለፈውን ስህተት በስምምነት ለማለፍ ብቻ ሳይሆን ለሚቀጥለውም ግንኙነት አመኔታን ለማስቀመጥ የሚረዳ ነው።
ይቅርታ ማድረግ ምን ማለት ነው? ይቅርታ ማድረግ ማለት አንድ ቅሬታ የሚፈጥር የሚጎዳ ነገር ደርሶ ያንን መተው፣ የተፈጸመውን አልያም የተነገረውንና አንድን ሰው የጎዳውንና ያስቀየመውን ነገር እንዳልተከሰተ መቁጠር፣ መርሳት፣ መሰረዝ፣ ማለት ነው፡፡ ይህ ማለት ግን የሆነው ነገር ሁሉ ከአእምሮ ተፍቆ ይወጣል ይሰረዛል አልያም ማስወገድ ይቻላል ማለት ሳይሆን እንዳልተፈጸመ እንዳልተከሰተ አድርጎ መተው ይቻላል ማለት ነው። ይቅርታ ችግርን ለመፍታት፣ በደልን ለመሻር፣ ያንን ተከትሎ የሚፈጠርን አካላዊ ቁሳዊም ሆነ ስነ ልቦናዊ ጉዳት ለመቀነስ እና ህመሙን ለማከም የሚጠቅም መድሃኒት ነው፡፡
ይቅርታ ጥላቻንና በቀልን ማዳከሚያ መሳሪያ ሲሆን እርቅ፣ ሠላምና ፍቅር በሰው ልጅ ህሊናና ተግባር ውስጥ እንዲወለድ የማድረግ ትልቅ አቅምም ያለው ነው፡፡ ይቅርታ ሰው ከተበደለ በኋላ ከደረሰበት ቅሬታ ወይም ሃዘኔታና የልብ መሰበር ለመዳን ወይም ለመውጣት ዋነኛ መፍትሔ ነው፡፡ ይቅርታ የራስን ጥቅም አስቦ የሚደረግ ሳይሆን ከራስ በፊት ለእርስ በእርስ ግንኙነት ትልቅ ቦታ ከሚሰጥ ልብ የሚፈልቅም ነው፡፡
ይቅርታ ሲጠይቅ ተበዳዩንና ከእርሱ ጋር ያለውን ትስስር ምን ያህል የክብር ቦታ እንደተሰጠው የሚያመላክትም ነው፡፡ ይህም ሆኖ በርካታ ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ጥፋት ፈጽመው ቤተሰባቸውን ይቅርታ ከመጠየቅም ሆነ ተበድለው ይቅርታ ሲጠየቁ ይቅር ከማለት ሲከለከሉ ማየት የተለመደ ተግባር እየሆነ መጥቷል።
የሰው ልጅ ይቅርታ ለመጠየቅ ለምን ይፈራል? ለዚህ ዋነኛው ምክንያት በአብዛኛው ሰው ዘንድ ይቅርታ መጠየቅ የደካማነትና የተሸናፊነት ምልክት ተደርጎ ስለሚወሰድ ነው። ይህ የሚመነጨው አንድ ግለሰብ ሰው መሆኑንና ስህተት መፈጸምም የሰው ልጅ አንዱ የባህሪይ መገለጫው መሆኑን ካለመገንዘብ ነው። የዚህ አይነት ስሜት በሰው ወስጥ ሲኖር ጥፋቱን እሱ ብቻ የፈጸመው ስለሚመስለውና ሌሎችን ፍጹማዊ አድርጎ ስለሚመለከት ጥፋቱንም ይፋ ከማድረግ ይቅርታም ከመጠየቅ ይገደባል። ሌላው ይቅርታ ለመጠየቅ የሚያስፈራውና እንቅፋት የሚፈጥረው ነገር ከይቅርታ ለጥቆ የሚመጣውን ነገር ምላሽ በመፍራት ጉዳዩ ያልታወቀ ከነበረ ሲታወቅ ምን ሊከሰት እንደሚችል በመገመት ሊያቀርብ ያሰበውን ይቅርታ ሊሰርዝ ይችላል።
የይቅርታ ማድረግ እንደ ግንኙነቱ መሰረት በሁሉም ቦታ በሁለቱም ወገን የራሱ የሆነ የህሊና እረፍትና ጥቅሞች ያሉት ቢሆንም በትዳር አለም የሚኖረው ፋይዳ ግን እጅግ ከፍተኛ ነው። ዛሬ እንደ ቀልድ በየቀኑ ከምንሰማቸው የትዳር መፍረስ ዜናዎች መካከል አብዛኞቹ ይቅርታ ሊታደጋቸው የሚችሉ መሆናቸውን በድፍረት መናገር ይቻላል። የትዳር ግንኙነት በሁለቱ ጥንዶች (ባልና ሚስት) ግንኙነት ላይ የተመሰረተ ቢሆንም ተዋናዮቹ ግን በርካቶች ናቸው። እናም አንዳንድ ግዜ ቅያሜ የተፈጠረበት ሰው የደረሰበትን ትቶ ይቅር ለማለት ፍላጎቱ ቢኖረው እንኳ ምን ይሉኛል የሚለው ነገር ሊያግደው ይችላል። ነገር ግን የይቅርታ መጠየቅንም ሆነ ይቅርታ ማድረግን ፋይዳ በግዜ የተረዳ ካለ ከሰው ሀሜት ይልቅ ትልቁን ተቋሙን ቤተሰቡን ለመታደግ ሲል እንደ ቀላል ሊያደርገው የሚችለውና ትልቅ ፋይዳ ያለው ተግባር ነው።
በተለይ በደል የተፈጸመበትና ቅሬታ ያለው ሰው የተፈጸመበትን ነገር ደጋግሞ ማስታወስ ከጀመረ፤ ለደረሰበት ነገር በቀል አልያም አጸፋ የመስጠት ሀሳብ ከመጣበት፤ የተደፈርኩ አልያም የተናቅኩ አይነት ስሜት ከተፈጠረበት፤ ልንረሳው ይገባል ወይም ማንንም የሚገጥም ጉዳይ ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ይቅር በማለቴ የምታደገው መላው ቤተሰቤን ነው ብሎ በመረዳት ይቅር ባይ ሊሆን እንደሚገባ ለራሱ መንገር አለበት፡፡ ይህንንም ለማድረግ ይቅር ማለት የምንችለው ይቅር ማለት ምን ትርጉም እንዳለው ማስታወስ፤ ይቅርታ በአብሮነት ለመቀጠል ያለውን ጥቅም ማሰብ፤ ራስን በሌሎች ቦታ በማስቀመጥ ስህተት መቼም በማንም ሊፈጠር እንደሚችል ማሰብ፤ ምክንያታዊ መሆንና ነገሮችን አሁን ካሉበት ነባራዊ ሁኔታ አሻግሮ ማየት ሲቻል ነው።
ለዚህም አንደኛ ፍርሃትን መቀነስ፤ አብዛኞቻችን ይቅርታ ለመጠየቅ ፈቃደኛ የማንሆነው ይቅርታ መጠየቃችን ስህተት ነው ብለን ስለምናምን ሳይሆን ይቅርታ በመጠየቃችን የሚፈጠርብንን ጫና በመፍራት ነው። ነገር ግን እያንዳንዱ በትዳር ወስጥ ያለ ግለሰብ ሊገነዘበው የሚገባው ትንንሽ ችግሮችን በሆድ ይዞ መቀጠል ለትዳር ግንኙነት እንቅፋት ከመሆኑ ባሻገር በቤተሰብ ውስጥ ያለ ሰላምን የሚያደፈርስም ይሆናል። ሁሌም ቢሆን በትዳር ግንኙነት ውስጥ ትንንሽ አለመግባባቶችና ስህተቶች በወቅቱ በይቅርታ ስሜት እየተቀነሱ ካልሄዱ ተደራርበው አንድ ትልቅ ችግር የመፍጠር አቅም ይኖራቸዋል።
እነዚህን ምን አልባትም ስህተት ፈጻሚው ትልቅ አድርጎ ያላሰባቸው ክስተቶች ደግሞ በተበዳይ ዘንድ በትልቁ ሊመዘገቡ ይችላሉ። በመሆኑም ይሄ እኮ ምንም ማለት አይደለም፤ ይህ እኮ ቀላል ነው ከማለት እሳቤ በመውጣት ለተፈጠረው ስህተት በሙሉ ይቅርታ ማቅረብ ተገቢ ሲሆን ለዚህም ኢምክንያታዊ ፍርሀትን ማስወገድ ተገቢ ይሆናል። ይቅርታ ለመጠየቅ ስንል የሚፈጠርብንን የፍርሀት ስሜት ለማስወገድ ደግሞ በአንድ ወገን በውስጣችን የያዝነው ነገር ውሎ ባደረ ቁጥር የራሳችንን ሰላም እየነጠቀን እንደሚሄድ መገንዘብ፤ በሌላ በኩል ይቅርታ ስንጠይቅ የኛ ለምንለው ሰው የምንፈጥርለትን ደስታና ለሱ ያለንን ፍቅር እንደሚያጎላ መገንዘብ አለብን። ይህንን ማድረግ ስንችል የበደልነውን ይቅርታ ለመጠየቅ ምላሹ ምንም ቢሆን ምን ድፍረት እናገኛለን፤ ተበድለንም ከሆነ ለሚቀርብልን ይቅርታ በደሉ ምንም ያህል ቢያበሳጨን ይቅር ለማለት ልቦናችን ክፍት ይሆናል።
በሌላ በኩል ይቅር ለማለት በቅድሚያ ራስን ማወቅና መሰልጠን የሚጠበቅ ይሆናል። ለዚህም ለራስ ጊዜ በመስጠት ራስን ከሁሉም በመለየት ከራስ ጋር በመነጋገር ራሳችንን ለማወቅ ስንዘጋጅ የችግሩን መነሻና ገጽታ እየለዩ ለማወቅ ይረዳናል፡፡ እንዲሁም ራሳችንን ስናውቅ እኛም የምንሳሳት መሆናችንንና አሁን ደግሞ ተራው የሌሎች ሆኖ እንደተሳሳቱ እንድንረዳና ይቅር እንድንል ከማስቻሉ ባለፈ ራሳችንን ስናውቅ ስህተታችንን እንድናውቅ እድሉን ይሰጠናል፡፡ በዚህም ለሌሎች እንድናዝን (እንድንራራ) ከማስቻሉም በላይ ጨክነን ከመፍረድ እንድንቆጠብ ያግዘናል፡፡ ይህም የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ግማሽ መንገድ እንደመሄድ ከመቆጠሩ በተጨማሪ ይቅር ባይ እንድንሆን ስለሚረዳን ይቅርታ ለመጠየቅም ሆነ ለመቀበል አቅም ይሆንልናል፡፡
በተጨማሪ የቤተሰብ አባላትን በተለይ ልጆችን የይቅርታው አካል ማድረግ፤ እንደየጉዳዩ ክብደትና ቅለት ይቅርታ የምንጠይቀው ሰው ጉዳዩ የሚመለከተው እሱን ብቻ ቢሆንም ሌሎቹንም የቤተሰብ አካላት ማካተት ይመከራል። ይህ ሊደረግ የሚገባበት ዋነኛው ምክንያት በአንድ በኩል ጉዳዩ የማይመለከታቸው የቤተሰብ አባላት በቤተሰቡ ውስጥ ያለውን መተሳሳብ እንዲገነዘቡ ለማድረግ ሲሆን፤ በሌላ በኩል እነሱም በተለያዩ ግዜያት ምንም አይነት ስህተት ቢፈጽሙ ያለ ማመንታትና ያለ ፍራቻ ይቅርታ ለማቅረብ፤ ተበድለውም ከሆነ ከማንኛውም ወገን ለሚቀርብላቸው ይቅርታ ተገቢ ምላሽ ለመስጠት ነጻ እንዲሆኑ የሚያስችላቸው ይሆናል።
ሁለተኛ ቤተሰብ የሚለው ተቋም ከቁሳዊ ግንኙነቶች ባለፈ በህሊናና በስነ ልቦና የተገናኘ እንደሆነ መገንዘብ። የአንድ ቤተሰብ አባላት የሚኖራቸው ግንኙነት በጣም ጠንካራና ክፍተት የሌለበት ሊሆን ይገባል። በቤተሰብ ግንኙነት ውስጥ የቦታ ርቀት ወይንም የግዜ ርዝማኔ ግንኙነትን ያጠናክረዋል እንጂ አያላላውም። በተመሳሳይ በቤተሰብ ወስጥ ለቅያሜ ለበደል የሚቀርብ የይቅርታ ጥያቄ የቤተሰቡን ቀጣይ ህይወት የሚያጠናክር እንጂ የሚያላላው የሚያደፈርሰው አይሆንም። በመሆኑም የተፈጠረውን ነገር ተበዳዩ ቢያውቀውም ባያውቀውም ይቅርታ ማቅረቡ ተአማኒነትን ለማስቀመጥ ቁልፍ መሳሪያ ይሆናል።
ይቅርታ እንዴትና መቼ መቅረብ እንዳለበት መለየት፤ የተሳሳተው ሰው አልያም የበደለ ሰው ይቅርታ ለማቅረብ ከወሰነ በኋላ እንደየሁኔታው ግዜውን መምረጥ ይጠበቅበታል። ግዜ የሚመረጥበት የመጀመሪያው ምክንያት ይቅርታ የሚቀርብለት ሰው ከጉዳዩ ጋር በተያየዘ ያለውን ስሜት ለመረዳት ነው። አንዳንድ ግዜ ይቅርታው የሚቀርበው ነገሮች በተጋጋሉበት ሰአት የደረሰው ጥፋት አልያም በደል የፈጠረው ንዴት ባልበረደበት ወቅት ከሆነ ይቅርታ የቀረበለት ሰው የሚሰጠው ምላሽ ከስሜት የመነጨ ሊሆን ይችላል። በመሆኑም በዚህ አይነት ሁናቴ (ሙድ) ውስጥ ላሉ ሰዎች በፍጥነት ሳይረጋጉ የሆነውን ሁሉ ነገር ከመንገር መቆጠብ ይገባል። ይህን ለማድረግ ሁኔታዎች ምቹ ካልሆኑ ደግሞ በዳዩ አልያም ጥፋት የፈጸመው ሰው የይቅርታውን ጥያቄ ራሱ ከማቅረብ ይልቅ በሌላ በሶስተኛ ወገን ለሁለቱም ቅርብ በሆነ ሰው ቢያስነግር የተሻለ ምላሽ ለማግኘት በር ይከፍታል። በአንጻሩ የተፈጸመውን ድርጊት ተበዳዩ ካላወቀውና ሊያውቀው የሚችልበት አጋጣሚ ካለ ቀድሞ ሁሉንም ነገር ግልጽ ማድረጉ ትልቅ ፋይዳ ያለው በመሆኑ በማንኛውም ሁኔታ ወስጥ ቢሆን የይቅርታው መቅረብ የሚመከር ይሆናል።
ሁለተኛው ይቅርታ ለማቅረብ ግዜ የሚመረጥበትና ሁኔታዎች ቀድመው እንዲመቻቹ የሚደረግበት ምክንያት የተፈጠረው ጉዳይ የሚያስከትለው ውጤት የማይቆም ሲሆን ነው። ለምሳሌ አንድ አባት ከሚስቱ ውጪ ሌሎች ልጆች ወልዶ ከሆነ ያደረገውን ነገር በመናገር ከባለቤቱ ይቅርታ ማግኘት ቢፈልግ ከችግሩ ጠንካራና አስደንጋጭነት አንጻር በቅድሚያ ለሚመጡ ምላሾች ራሱን ማዘጋጀት ይጠበቅበታል። እንደዚህ አይነት ክስተቶች ሲኖሩ ይቅርታ ከቀረበላት የትዳር አጋርም ይሁን ከሌሎች የቤተሰቡ አባላት ያልተጠበቀና ጥሩ ያልሆነ ምላሽ ሊኖር ስለሚችል የብዙዎች ተሳትፎ የሚኖርበት በእቅድ የተመራ እንቅስቃሴ ያስፈልጋል። ለዚህም ይቅርታ ጠያቂው ከፍተኛ ቦታና ክብር የሚሰጣቸውን ሰዎች የሀይማኖት አባቶችን ጨምሮ ማካተት ይገባል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ችግር በራሱ የችግሩ ፈጣሪ አቅም ሊስተካከል የሚችል ሆኖ ሲገኝም ይቅርታውን ሲያቀርብ ለስህተቱ ማረሚያ የተቀመጠውንም መንገድ እዛው ማሳወቅ ቀና ምላሽ እንዲኖር በር ይከፍታል። ለምሳሌ የተቀመጠ ገንዘብ ያጠፋ ሰው ካለ ይህንን ገንዘብ በስህተት አልያም በዚህ ምክንያት አጥፍቼዋለሁ ከማለት ተሻግሮ በዚህ አድርጌ ይህንን ለማስተካከል ዝግጁ ነኝ ማለትም ያስፈልጋል። በመሆኑም ትዳርን ለሚያክል በሁለንተናዊ ግንኙነት ለተሳሳረ ህብረት ይቅርታ መጠየቅም ሆነ ይቅርታ መቀበል ያለውን ፋይዳ በመረዳት ልብን ለይቅርታ ክፍት ማድረግ ይጠበቃል።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 19/2013