ባለፈው ሳምንት የቤተሰብ አምድ እትማችን በ-ያለእድሜ ጋብቻ የሚጣሱ መብቶችንና የሕጉን አግባብ የአማራ ክልልን እንደ መነሻ በማድረግ ከክልሉ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤት የፍትሐብሔር አቃቤ ሕግ የሆኑትን አቶ አማረ ሲሳይን አነጋግረን የመጀመሪያውን ክፍል ይዘን መቅረባችን ይታወሳል ። በዛሬው እትማችን ሁለተኛውንና የመጨረሻውን ክፍል ይዘን ቀርበናል።
የመማር መብት
በርካታ የዓለም ሀገሮች ለማሳካት የሚደክሙለት “ትምህርት ለሁሉም” የሚለው መሰረታዊ አላማ ወንዶችንም ሆነ ሴት ህጻናትን በእኩል ደረጃ ይመለከታል። ሆኖም ግን ህብረተሰባችን ከትምህርት ይልቅ ለጋብቻ የበለጠ ዋጋ ስለሚሰጥና ያለእድሜ ጋብቻ በስፋት በመፈጸም ላይ ስለሆነ ዓላማውን በማደናቀፍ ላይ ይገኛል ። ስለዚህ በመማር ላይ ሳሉ ያለእድሜ ጋብቻ የተፈጸመባቸው ሴት ህጻናት ከጋብቻው በኋላ በስራ ጫና፣ በወሊድና በቤተሰብ ግፊት ትምህርታቸውን ለመቀጠል አይችሉም ።
በተጨማሪ የመማር መብት በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሰነዶች ሁሉን አቀፍ ዕውቅና አግኝቷል ። በዚሁም መሰረት የሰብዓዊ መብቶች አለም አቀፋዊ መግለጫ በአንቀጽ 26 ንኡስ አንቀጽ (1) በግልጽ እንደሚለው ማንም ሰው የመማር መብት አለው ። የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባህላዊ መብቶች ስምምነትም በአንቀጽ 13 (1) እንደሚደነግገውም ማንኛውም ሰው ትምህርት የማግኘት መብት ያለው መሆኑን የስምምነቱ አባል አገሮች ሊያውቁ ይገባል ።
በተመሳሳይ የህጻናት መብቶች ስምምነት በበኩሉ በአንቀጽ 28 የህጻናትን የመማር መብት ደረጃ በደረጃና ለሁሉም እኩል እድል መስጠት በሚለው መርህ ላይ በመመስረት የስምምነቱ ተዋዋይ አገሮች ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው በማያሻማ ሁኔታ አስቀምጧል ። የአፍሪካ ህጻናት መብቶችና ደህንነት ቻርተርም በአንቀጽ 11 ማንኛውም ህጻን የትምህርት መብት አለው ሲል ይደነግጋል ።
የመማር መብት በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሰነዶች ብቻ ሳይሆን በኢ.ፌ.ዴ.ሪና በአማራ ክልል ሕጎችም ከፍተኛ ትኩረት ያገኘ ጉዳይ ነው ። ስለዚህ ሕገ-መንግስቶቹን ጨምሮ የመማር መብትን ለማስከበር የሚችሉ ብዙ ብዙ ፖሊሲዎች ጸድቀዋል፤ ሕጎችም ወጥተዋል ማለት እንችላለን ።
ሆኖም ግን ምንም የሰብዓዊ መብት ስምምነት ቢፈረም፣ ምንም ፖሊሲ ቢጸድቅና ምንም ሕግ ቢወጣ የሴት ህጻናትን ትምህርት የሚገታውን ያለእድሜ ጋብቻ ለማስቆም በሚችልበት አቅም ልክ አልደረጀም እየተተገበረም አይደለም ። በመሆኑም ሴቶች ልጆች ያለእድሜ ጋብቻ ሲፈጽሙ ከትምህርታቸው ጋር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተቆራርጠው ይቀራሉ ። ያልተማሩ ሴቶች ደግሞ ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን በገንዘብ ሊደግፉ አይችሉም። በተለይም ባሎቻቸው ሲሞቱባቸው፣ ሲተዋቸውና ሲፈቷቸው ቀጣይነት ላለው ድህነት ይጋለጣሉ።
መ. የጤና መብት
ካለእድሜ ጋብቻ በመፈጸሙ አማካኝነት ወደ ትዳር የሚገቡ ሴት ህጻናት በእድሜ ብዙ ከሚበልጧቸው ባሎቻቸው ጋር የግብረ-ስጋ ግንኙነት ለመፈጸም በአካልም ሆነ በስነ-ልቦና ብቁ አይደሉም ። በተጨማሪም ግንኙነቱን ተከትሎት ለሚመጣው እርግዝናና ወሊድ አካላዊም ይሁን አእምሯዊ ዝግጁነት የላቸውም ። ይህ ደግሞ በትንሹ ሽንትና ሰገራን መቆጣጠር እንዳይችሉ ስለሚያደርግ ፊስቱላ ለተባለ ከፍተኛ የህክምና ክትትልና ግዜ ለሚፈልግ ህመም ያጋልጣቸዋል ።
ከእርግዝና ጋር ተያይዘው ከሚያጋጥሟቸው ውስብስብ ችግሮች በላይ ያለእድሜ ጋብቻ የፈጸሙ ሴት ልጆችን ህይወት ይበልጥ የከፋ የሚያደርገው ለአባላዘር በሽታዎች የመጋለጥና በ ኤች አይ ቪ ኤድስ የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑ ነው ። ይህም ባሎቻቸው አስቀድሞ ከነበራቸው የግብረ-ስጋ ግንኙነት ጋር ይያያዛል ። የባሎቻቸው ጥገኛ መሆንና ያላቸው የእድሜ ልዩነት ደግሞ ስለጤናማ ወሲብ እንዳያስቡ እንዲሁም ስለታማኝነት እንዳይገነዘቡ ስለሚያደርጋቸው ቀጣይ ህይወታቸው በሙሉ የተስተካከለ የመሆን እድሉ በጣም ጠባብ ነው ።
በየጊዜውና በየወቅቱ የሚወጡት ዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች ሁሉ የጤና መብትን የተመለከተ ድንጋጌ የያዙ ናቸው ። ዋና ዋናዎቹን ስንመለከት የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባህላዊ መብቶች ስምምነት አንቀጽ 12 (1) “ማንኛውም ሰው ሊደርስበት ወደሚችል ከፍተኛ የአካልና የአእምሮ ጤንነት ወደተሟላበት የኑሮ ደረጃ የመድረስ መብት ያለው መሆኑን” ያውጃል። የአፍሪካ የሰዎችና የሕዝቦች መብቶች ቻርተርም በተመሳሳይ በአንቀጽ 16 (1) “ማንኛውም ሰው የአካልም ሆነ የአእምሮ ጤንነቱ በሚኖርበት ማህበረሰብ ሊደረግ በሚችልበት ደረጃ እንዲጠበቅለት የማድረግ መብት አለው” በማለት ደንግጓል ።
የአፍሪካ ህጻናት መብቶችና ደህንነት ቻርተርም በአንቀጽ 14 (1) “እያንዳንዱ ህጻን የላቀ የአካል፣ የአእምሮና የመንፈስ ጤንነት የማግኘት መብት” እንዳለው ሲደነግግ በሴቶች ላይ የሚደረግን ማንኛውንም አድሏዊ ልዩነት ለማስወገድ የተደረገው ስምምነት አንቀጽ 12 (1) ደግሞ ስምምነቱን የተቀበሉ አገሮች በጤና አገልግሎቶች እኩል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሴቶች ላይ የሚደረግን አድልዎና ልዩነት ለማስወገድ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ይገልጻል ።
ከዚህ በላይ የተጠቀሱት የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 9 (4) መሰረት የአገሪቱ የሕግ አካል ቢሆኑም ከስምምነቶቹ በተጨማሪ አንቀጽ 90 (1) ን መሰረት አድርገው ሁሉም ኢትዮጵያዊ የጤና አገልግሎቶች እንዲያገኝ በሚያስችል መልኩ በብዛት የተቀረጹ ፖሊሲዎችና የወጡ ህጎች አሉ ። እነዚህ ፖሊሲዎችና ሕጎች በአማራ ክልልም ተፈጻሚነት ያላቸው ሲሆን የጤና መብትም በክልሉ ሕገ-መንግሥታዊ ዋስትና ያገኘ መብት ነው ።
ይህም ሆኖ የእነዚህ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች ሁሉ መኖር፣ የብሔራዊና ክልላዊ ሕጎች መበራከት ያለእድሜ ጋብቻን ማስቀረት አልቻለም ። በመሆኑም በያለእድሜ ጋብቻ ምክንያት ሴት ህጻናት ከእርግዝና ጋር ተያይዘው ለሚከሰቱ ውስብስብ ችግሮች ይጋለጣሉ፤ በአካል ሳይደረጁና በአእምሮም ሳይበስሉ ያለእድሜያቸው ልጅ ይወልዳሉ ። ይህም የራሳቸውንም ሆነ የልጆቻቸውን ህይወት አደጋ ላይ ይጥላል ብሎም ለሞት ይዳርጋቸዋል ። ከዚህም ሌላ ከላይ እንዳስቀመጥነው ፊስቱላን ጨምሮ በአባላዘር በሽታዎችና በኤች አይ ቪ ኤድስ ስለሚያዙ ጤናማ ህይወት የመምራት ተስፋቸው ይጨልማል ።
ሠ. ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የመጠበቅ መብት
በሀገራችን ከ140 በላይ የሚሆኑ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መኖራቸውን በዚህ ጽሑፍ መጀመሪያ ላይ ተመልክተናል ። በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶቹ የሚጠቁት ደግሞ ሴቶችና ህጻናት መሆናቸው የማይታበል ሀቅ ነው ። ለዚህም ነው አብዛኞቹ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች ሴቶችና ህጻናት ከማንኛውም ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት የመጠበቅ መብት አላቸው ሲሉ በግልጽ የሚደነግጉት ።
ከብዙዎቹ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች ጥቂቶቹን ስናይ የህጻናት መብቶች ስምምነት በአንቀጽ 24 (3) ተዋዋይ አገሮች ለህጻናት ጤና ጠንቅ የሆኑ ባህላዊ ልምዶችን ለማስወገድ ተገቢና ውጤት ሊያስገኙ የሚችሉ እርምጃዎችን ይወስዳሉ ሲል በአስገዳጅነት ደንግጓል ። የአፍሪካ ህጻናትና ደህንነት ቻርተርም ጎጂ ከሆኑ ማህበራዊና ባህላዊ ልምዶች መጠበቅ በሚል ርዕስ ስር በአንቀጽ 21 የቻርተሩ ተዋዋይ አገሮች በህጻናት ደህንነት፣ ክብር፣ ጤናማ እድገትና ጉልምስና ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ጎጂ ማህበራዊና ባህላዊ ልማዶችን ለማስወገድ ማናቸውንም ተገቢ እርምጃዎች መውሰድ እንዳለባቸው ይገልጻል ።
ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የመጠበቅ መብት ከፍ ሲል በተጠቀሱት ስምምነቶች ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም ። የኢ.ፌ.ዴ.ሪና የአማራ ክልል ሕገ-መንግስቶችም ተመሳሳይ ድንጋጌ ይዘዋል ። ይሄውም ሴቶች ከጎጂ ባህል ተጽዕኖ የመላቀቅ መብታቸውን መንግሥት ማስከበር እንዳለበት በአንቀጽ 35 (4) በአስገዳጅ መልኩ ተደንግጎ ይገኛል ።
ሆኖም ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የመጠበቅ መብት የተለያዩ ኃይማኖታዊና ባህላዊ ሰበቦች እየተጠቀሱበት ከሚከበርበት ይልቅ የሚሻርበት ጊዜ ይበዛል ። በተለይ ደግሞ ያለእድሜ ጋብቻ እንዲህ አይነት ምክንያቶችን በማቅረብ ከሚፈጸሙት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ግንባር ቀደሙ ነው ። ከዚህም አኳያ ያለእድሜ ጋብቻ አለማቀፍ ስምምነቶቹንና ብሔራዊ ሕጎቹን ዋጋ እያሳጣ ለዘመናት ሊዘልቅ ችሏል።
ያለ እድሜ ጋብቻ መፈጸም የሚያስከትለው የህግ ተጠያቂነት
ያለ እድሜ ጋብቻ ዘመናትን ያስቆጠረ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት መሆኑ አስረጅ አያሻውም ። ተፈጽሞም ሲገኝ ሁለት አይነት የሕግ ኃላፊነቶችን ያስከትላል ። የመጀመሪያው የፍትሐብሄር ሲሆን ሌላኛው የወንጀል ተጠያቂነት ነው ።
የፍትሐብሄር ተጠያቂነቱን የሚያስከትሉት የኢ.ፌ.ዴ.ሪና የአማራ ክልል የቤተሰብ ሕጎች ናቸው ። የወንጀል ኃላፊነቱ ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ ተፈጻሚነት ባለውና በ1997 ዓ.ም ተሻሽሎ በወጣው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ በግልጽ ተመልክቷል።
የቤተሰብ ሕጎቹ በአንቀጽ 17 እና 28 እንደቅደም ተከተላቸው ጋብቻ ለመፈጸም አስፈላጊ የሆነ ሁኔታ አልተሟላም በማለት ሊፈጸም የታሰበ ጋብቻ እንዳይፈጸም ተቃውሞ ማቅረብ እንደሚቻል ሲደነግጉ በአንቀጽ 18 እና 29 ደግሞ ጋብቻ እንዳይፈጸም መቃወም የሚችሉ ወገኖችን ለይተው አስቀምጠዋል ። በዚህም መሰረት በእድሜ ምክንያት ሲሆን ወላጆች፣ አቃቤ ህግ ወይም ሌላ ማንኛውም ያገባኛል የሚል ሰው መቃወሚያውን ለጋብቻ አስፈጻሚው አካል በማቅረብ ያለእድሜ ጋብቻው እንዳይፈጸም ማድረግ ይችላል ።
በሌላ በኩል ተቃውሞ ሳይቀርብበት ቀድሞ የተፈጸመ ያለእድሜ ጋብቻም ቢሆን የሚጸና አይደለም ። ይህም በተጠቃሾቹ የቤተሰብ ሕጎች አንቀጽ 31 እና 42 በማያሻማ ሁኔታ ተገልጿል። ስለሆነም እድሜአቸው ከአሥራ ስምንት አመት በታች በሆኑ ሰዎች መካከል የተፈጸመ ጋብቻ በማንኛውም ሰው ወይም በአቃቤ ሕግ ለወረዳ ፍ/ቤት በሚቀርብ ጥያቄ እንዲፈርስ መደረጉ አይቀሬ ነው ።
ያለእድሜ ጋብቻ ላይ የሚወሰደው እርምጃ ጋብቻው እንዲፈርስ በማድረግ ብቻ የሚቆም አይሆንም ። ይልቁንም ከጋብቻው መፍረስ በኋላ የወንጀል ተጠያቂነት ይከተላል ። ይሄውም በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 647 ስር በተደነገገው አግባብ በሕግ የተከለከለ ጋብቻን ያስፈጸመ፣ የፈጸመና ለዚህ ዓይነቱ ጋብቻ ምስክር የሆነ ሰው ከሦስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከአምስት ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ እንዲቀጣ ይወሰንበታል።
በተለይ ደግሞ የወንጀል ሕጉ በአንቀጽ 648 ስለ ያለእድሜ ጋብቻ ወንጀልነት ይደነግጋል ። በመሆኑም አግባብ ባለው የቤተሰብ ሕግ ከተፈቀደው ውጭ ማንም ሰው አስቦ ዕድሜዋ አስራ ሶስት ዓመት ወይም ከዚያ በላይ የሆነችን ልጅ ካገባ ከሶስት ዓመት በማይበልጥ እስራት፤ ወይም ዕድሜዋ ከአስራ ሶስት ዓመት በታች የሆነችን ልጅ ካገባ ከሰባት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ይቀጣል ። ይሁንና ጋብቻው የፍትሐብሄር ክስ ቀርቦበት አስቀድሞ ካልፈረሰ በቀር ከፍ ሲል በተጠቀሱት አንቀጾች መሰረት የወንጀል ክስ ሊቀርብ አይችልም ።
እንደማጠቃለያና የመፍትሔ ሀሳብ
ያለእድሜ ጋብቻ ጎጂነት፣ አጥፊነትና አስከፊነት በድፍን አለም ይታወቃል። ስለዚህን በሁሉም አለማቀፋዊ፣ አህጉራዊና አገራዊ ሕጎች መወገዙ ቢያንስበት እንጂ አይበዛበትም ። ሆኖም ግን ውግዘቱ ጎልብቶ ያለእድሜ ጋብቻን ማስቆም ይቅርና መቀነስ አልቻለም ።
በዚህም ያለእድሜ ጋብቻ ገፈት ቀማሾቹ ብዙን ጊዜ ሴት ህጻናት ሲሆኑ ወንዶች ልጆችም አልፎ አልፎ በድርጊቱ ሲጠቁ ይስተዋላል ። ያለእድሜ ጋብቻን ለመቀነስ ብሎም ለማስቀረት በሚደረገው ጥረት የአንበሳውን ድርሻ መያዝ ያለበት ህብረተሰቡ ነው ። ነገር ግን ህብረተሰቡ ዛሬም ድረስ ያለእድሜ ጋብቻውን በመፈጸም አለያም በማስፈጸም የራሱን እጅ ስለሚያስገባ ድርጊቱ ለዘመናት ሊዘልቅ ችሏል ።
ስለሆነም ይህን ስር የሰደደ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ቢቻል ለማስወገድ ካልሆነም ለመቀነስ መንግሥትም ሆነ መላው ህብረተሰብ ያላሰለሰ ርብርብና ትብብር ማድረግ ይጠበቅበታል ። እንደዚሁም የባህል ጠባቂዎችና የሀይማኖት አባቶች ያለእድሜ ጋብቻን ጎጂነት ተረድተው ለተከታዮቻቸው ማስተማርና መስበክ ይኖርባቸዋል ። ከሁሉም በላይ ደግሞ በየደረጃው ያሉ የሕግ አስከባሪ አካላት ለችግሩ አሳሳቢነት ትኩረት በመስጠትና በመከታታል በአንድ ወገን የወንጀሉን ተሳታፊዎች ለሕግ በማቅረብ ተገቢውን ውሳኔ እንዲያገኙ በማድረግ፤ በሌላ በኩል የሚያስከትለውን የሕግ ተጠያቂነት በማስተማር ግለሰቦችም ሆኑ ማህበረሰቡ ከዚህ ተግባር እንዲቆጠብ ማድረግ የሚጠበቅባቸው ይሆናል ።
በሌላ በኩል ሕጋዊ ጋብቻ ለመፈፀም ወንዶችና ሴቶች ዕድሜያቸው 18 ዓመት መድረስ እንዳለበት የሚደነግጉት ሕጎች መሬት ላይ ወርደው ሊፈጸሙ ይገባል ። ከዚህም ባሻገር ያለእድሜ ጋብቻ በብዛት በሚፈጸምበት በገጠር አካባቢ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ስለነዚህ ሕጎች በቂ ግንዛቤ እንዲይዙ ማድረግ ያስፈልጋል።
በተለይ የአማራ ክልል በአገር ደረጃ ቀዳሚ ስፍራ የያዘበትን ያለእድሜ ጋብቻ ለማስቆም የማያዳግም እርምጃ መውሰድ አለበት ። ይህንንም ለማሳካት በክልሉ ባለዕድሜ ጋብቻ ዙሪያ የሚሰሩ የፍትህ አካላት፣ የህክምና ተቋማት፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውጤት አምጪ የተቀናጀ ሥራ ሊሰሩ ይገባቸዋል ።
ራስወርቅ ሙሉጌታ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 28/2013