መንግስትም ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የተቸገሩትን በማብላትና ቤታቸውን በመጠገን ውጤታማ ስራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ወጣቱ ማህበረሰባዊ ተሳትፎ እያደረገ፤ ማህበራዊ አገልግሎትም እየሰጠ ሲሆን፤ በተለይም አቅመ ደካማዎችን በማገዝ ረገድ ከፍተኛ ሚና በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህል እየተጠናከረ የመጣ ሲሆን በተለይ በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ወገኖችን በመርዳት በኩል ወጣቱ ግንባር ቀደም ተሳታፊ ነው፡፡ ይህን ማህበራዊ አገልግሎት የበዓላት ወቅትን በመጠበቅ ብቻ ማከናወኑ ተገቢም፣ በቂም ሆኖ ባለመገኘቱ በሌሎችም ወቅቶች ሊሰራ የሚገባው ሰፊ ማህበረሰባዊ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የበርካታ በጎ አድራጎት ተቋማትን መኖርና የእነሱንም ያልተቋረጠ ተሳትፎ ይፈልጋል። በመሆኑም፣ የሲቪክ ማህበራት አዋጅ ከተሻሻለ በኋላ በሁሉም ቦታዎች በጎ አድራጎት ማህበራት እየተበራከቱ ይገኛሉ፡፡
በተለይም ማህበራዊ ችግሮችን ከስራቸው ከመፍታት አኳያ ውጤታማ ስራዎችን በማከናወን ላይ ናቸው። ለዛሬ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ በተማሪነት ወቅት በጀመሩት የሰብአዊ አገልግሎት ተግባር ቀጥለው ዛሬ ለተማሪዎች፣ ለአረጋውያንና ለህፃናት ድጋፍ በማድረግ ላይ ስለሚገኙት ኢትዮ አምባ በጎ አድራጎት ማህበር እንቃኛለን፡፡ ከማህበሩ መስራቾች አንዱ ከሆነው ዶክተር ደሞዝ ታደሰ ጋርም ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
የማህበሩ አመሰራረት
ማህበሩ 2002 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ የተመሰረተ ሲሆን ማህበሩን ለመመስረት ምክንያት የነበረው በወቅቱ በከፍተኛ ህመም ትሰቃይ የነበረች ተማሪን ለማሳከም የነበረው እንቅስቃሴ ነው፡፡ ልጅቷ ወደ ውጪ ሄዳ እንድትታከም የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ በወቅቱ ለልጅቷ የሚያስፈልጋትን ገንዘብ በማሰባሰብ ወደ ህክምና እንድትገባ ለማድረግ
ተሞክሯል፡፡ ይህ ስራ መልካም ጅምር በመሆኑ በቀጣይ ስራውን በማስፋት የበጎ አድራጎት ስራ መከናወን አለበት የሚል ሀሳብ መጣ፡፡ ከዚም በኋላ ማህበር መስርቶ መንቀሳቀስ አስፈላጊ መሆኑ መግባባት ላይ ተደረሰበት፡፡ በወቅቱ ማህበሩን ለመመስረት ያሰቡት አባላት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ነበሩ፡፡
ይህ በአባላቱ የሚመሰረተው ማህበርም አላማና ግብ ኖሮት የሚንቀሳቀስ መሆን እንዳለበት ተስማሙ፡፡ ማህበሩን ሲመሰርቱ የህክምና እርዳታ ፈልጋ የነበረችው ልጅ ስም ሕይወት ነበር፡፡ ስለዚህ የማህበሩን ስም አዲስ ህይወት የሚል ስም እንዲኖረው ተደረገ፡፡ አዲስ ብሩህ ተስፋ በመያዝ የተቸገሩ ሰዎችን ለመርዳት አላማ አድርጎ መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ ልጅትዋ ህክምና እንድታገኝ ወደ ታይላንድ እንድትሄድ ተደረገ፡፡ ህክምናውን ተከታትላ ከህመሟ ድና አሁን በመልካም ጤንነት ላይ ትገኛለች፡፡
ማህበሩ ያከናወናቸው ተግባራት
ማህበሩን ለማጠናከር የሚያስችሉ ስራዎችን ለማከናወንና የአባላቱን ቁጥር ለማሳደግ ስራዎች ተጀመሩ፡፡ ማህበሩ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህክምና ትምህርት ቤት ስር ሆኖ የተለያዩ ስራዎችን ለማከናወን እቅድ ይዞ ተነሳ፡፡ የመጀመሪያ ተግባር የነበረው የደም ልገሳ ነበር፡፡ በወቅቱ ደም መለገስ ትኩረት ያገኘበት ሁኔታ ስላልነበረ በየሩብ ዓመቱ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ህብረተሰቡ ደም እንዲለግስ ተደረገ፡፡ በሌላ በኩል የተቸገሩ አረጋውያንንና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችን በዓላትን በማስመልከት የአልባሳት እደላና የምገባ ስራ ይከናወን ጀመር፡፡ ስድስት ለሚሆኑ ህፃናት ከአረጋውያን ቤተሰቦቻቸው ጋር እየኖሩ ድጋፍ የሚፈልጉትን በመለየት የመደገፍና የማስጠናት፤ እንዲሁም የመንከባከብ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው፡፡
በአሁን ወቅትም ልጆቹ ድጋፍ እያገኙ ያለበት ሁኔታ አለ፡፡ ለአስራ አንድ አመት ያክል ልጆቹን የመንከባከብ ስራ እየተከናወነ ነው፡፡ በተመሳሳይ ሀኔታ ወደ ውጪ ሄዳ መታከም የነበረባት ልጅም ማህበሩ ከሚመለከታቸው ጋር ተነጋግሮ በውጪ የሚገኙ ሀኪሞች ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት በአገሪቱ የማይሰጡ የቀዶ ጥገና ህክምናን ያከናውኑ ነበር፡፡ ለልጅትዋም ከጎን አጥንቷ ላይ አጥንት በመወሰድ ስብራት የደረሰበትን እግሯን እንዲጠገን ተደረገ፡፡ ከዛም ሰላማዊ ኑሮዋን እንድትቀጥል ተደርጓል፡፡ በዩኒቨርሲቲው በነበራቸው ቆይታ ጥቅም እየሰጠ ያልሆነን ቦታ በመረከብ የወጣት ማዕከል እንዲገነባ ተደርጓል፡፡
በማህበሩ ውስጥ የሚገኙ የህንፃ ዲዛይን ተማሪዎች የማዕከሉን ዲዛይን እንዲሰሩ የተደረገ ሲሆን፤ ሌሎችም የምህንድስና ተማሪዎች ስራዎችን እንዲያግዙ፤ ዩኒቨርሲቲውም አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ በማድረግ የተገነባ ሲሆን ማዕከሉ የራሱ የሆነ የማንበብያ ቦታ እንዲኖረው ተደርጓል፡፡ ተማሪዎችም በቀን አንድ ብር እየከፈሉ መፅሀፍ ተከራይተው እንዲያነቡ የሚደረግ ሲሆን፤ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ የሚደረግበትም ጂም አለ፡፡
የተለያዩ አካላት ለማእከሉ የመፃህፍት ድጋፍ ከማድረጋቸውም በተጨማሪም ማእከሉ የተለያዩ ፕሮግራሞች የሚካሄዱበት በመሆኑ እስካሁንም ድረስ ከሚገኘው ገቢ ማህበሩ እንዲደገፍ ከመደረጉም በላይ ዩኒቨርሲቲውም እንደ ገቢ ምንጭ እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡ ማህበሩ ይህንን ማበርከት ችሏል፡፡ ከነዚህ ውጪ እስካሁን ድረስ ያልተቋረጡ፣ ተከታታይነት ያላቸው፣ ማህበረሰቡን በተለይ የስምንተኛና የአስረኛ ክፍል ተማሪዎች ላይ ከትምህርት ቤታቸው ጋር በመነጋገር የክለሳ ትምህርቶችን እንዲማሩና ለፈተና እራሳቸውን እንዲያዘጋጁ የማድረግ ስራዎች ተከናውኗል፡፡
በዓላትን በማስመልከት በማህበሩ አባላት አማካኝነት በሆስፒታሎች ተኝተው የሚታከሙ ሰዎችን በቦታው ተገኝቶ የመጠየቅ ስራዎች የተከናወኑ ሲሆን የመስራት አቅም ላላቸው ልጆችም የሊስትሮ እቃ በመግዛት፤ ሱቅ በደረቴ፣ ሚዛን እንዲሁም ሌሎች ስራዎችን በማከናወን እራሳቸውን እንዲደግፉ እየተደረገ ነው፡፡ ማህበሩ ህጋዊ እውቅና ለማግኘት ባደረገው ሂደት “አዲስ ሕይወት” የሚለው ስም በሌሎች ቀደም ብሎ በመያዙ ወደ “ኢትዮ አምባ በጎ አድራጎት ማህበር” እንዲቀየር ተደርጓል፡፡
በአገሪቱ የነበረው የሲቪክ ማህበራት አደረጃጀት አሰሪ ባለመሆኑ ምክንያት ማህበሩን ህጋዊ ለማድረግ በተደረገው ስራ ላይ እንቅፋት የፈጠረ ሲሆን፤ በተለይም “ፕሮጀክት ማዘጋጀት” የሚል ስለነበር በዚህ መልክ መደረጀትን አስቸጋሪ አድርጎት ነበር፡ ፡ የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋለ ህፃናቱን የመደገፍ ስራ ባለበት የቀጠለበት ሁኔታ ነበር፡፡ ሆስፒታል ውስጥ ደግሞ ከህሙማን ጋር በተገናኘ እንክብካቤዎች የማድረግ፣ በዓላትን ምክንያት በማድረግ ገንዘብ በማሰባሰብ የተቸገሩ ሰዎች የመጠየቅና የመጎብኘት፤ እንዲሁም የአልባሳትን የማደል ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
የማህበረሰቡ አቀባበል
ስራው በአምስት ተማሪዎች የተጀመረ ሲሆን ስፍራውም በህክምና ትምህርት ግቢ ውስጥ ነበር፡፡ ከዛም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስር ወደሚገኙ የተለያዩ ካምፓሶች እንዲስፋፋ ተደረገ፡፡ የህክምና ትምህርት ኮሌጅ – ቴዎድሮስ፣ ማራኪ፣ ፋሲልና ፀዳ ካምፓሶች ውስጥም ስራው እንዲጀመር ተደረገ፡፡ በሂደቱም ብዙ ተማሪችን ወደ ማህበሩ ማንቀሳቀስ ተችሏል፡፡
ከማህበሩ አገልግሎት አኳያ በተለያዩ ደባል ሱስ ውስጥ የነበሩና ጭንቀት የነበረባቸውን ሰዎች ከነበሩበት ሁኔታ አውጥቶ አሁን ላሉበት ጥሩ ደረጃ እንዳደረሳቸው ይናገራሉ፡፡ በማህበሩ ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች የሚወያዩት ስለ መረዳዳትና ስለ ቅንነት በመሆኑ አባላቱ በጥሩ መንገድ ተሰባስበው እራሳቸውን ከነበሩበት መጥፎ ሁኔታ መታደግ ችለዋል፡፡
ሌላውን ለመርዳት በሚደረጉ መስተጋብሮች ውስጥ ሁሉም የማህበሩ አባል ተሳታፊ ነው። የተለየ ህብርና ቀለም ያለው አንድነት መፍጠር ተችሏል፡፡ አንዳንዱ አባላት ምንም ሳይታወቅ ሰውን ለመርዳት ብለው ቅድሚያውን ወስደው ድጋፍ እየሰጡ በስተመጨረሻ ህይወታቸው ሲጠና እነሱም በተመሳሳይ ህይወት ውስጥ ያለፉ ሆነው ይገኛሉ፡፡ በዚህም አዕምሯዊ ጥቅም የተገኘበት የበጎነት ስራ ተደርጓል ማለት ይቻላል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጥሩ ድጋፍ ያደርግ ነበር። ከአመራሩ ጀምሮ ሁሉም አስፈላጊ ድጋፎችን ያደርጋሉ፡፡ በብዙ መንገዶች ከማህበሩ ጎን በመሆን ስራዎችን ይሰራሉ፡፡ ይህ ሲባል ግን እንደ ችግር የተከሰቱ ነገሮች አሉ፡፡ ማንኛውም ስራ ሲሰራ ከየትኛውም አቅጣጫ ይሁን በትክክለኛ መንገድ ያለማየት ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ የማህበሩን ሀሳብ ያለማመንና ጫና የመፍጠር ሁኔታዎች ነበሩ፡፡
በአሁኑ ሰአት የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን የአካባቢውም ማህበረሰብ ለማህበሩ የተለየ ፍቅር ያለው ሲሆን አሁንም ድረስ በዓላት ሲደርደሱ ማህበረሰቡ በያገባኛል መንፈስ እየተንቀሳቀሰ ነው ያለው፡፡ የአልባሳት ድጋፍን፣ የገንዘብ መዋጮዎችን እንዲሁም የጉልበት ተሳትፎ ያደርጋል፡፡ ማህበረሰቡ ለበጎ አድራጎት ማህበራት ያለው ተባባሪነት አስደሳች ነው፡፡ የማህበሩ አላማና ተግባሩ ጥሩ ስለሆነ ወደ ሌሎች ተቋማት የሚስፋፋበት ሁኔታ እንዲመቻች ሁል ጊዜ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ጥያቄ ይቀርባል፡፡ በመዚሁ መነሻነትም በቀጣይ የማህበሩን ተሞክሮ ወደ ሌሎች ተቋማት የማስፋፋት እቅድ አለ፡፡
ማህበሩን ያጋጠሙ ችግሮች
ማህበሩ ከተመሰረተ በኋላ በጣም ከባድ የነበረው መልካም ለማድረግና በጎ ለመስራት እንቅስቃሴ ሲደረግ የብሄር ተዋጽኦ የሚለው ነገር ነው፡፡ ይህ ሁኔታ የማህበሩን እውቅና አግኝቶ በፍጥነት እንዳይሰራ እንቅፋት ፈጥሮ ነበር፡፡ ማህበሩን የመሰረቱት አባላት ከልብ በመነጨ ሰብዓዊነት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ስውር በሆነ መንገድ ስለላ ይካሄድ ነበር፡፡ ስራዎች ለመስራት እንቅስቃሴ ሲጀመር ሆን ብሎ የማደናቀፍ ሁኔታዎች ነበሩ፡፡ ይህ ሁኔታ ከማህበሩ 0አባላትም ውስጥ ይስተዋል ነበር፡፡ በተለይ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ቡድኖች ማህበሩ ላይ እንቅፋት ይፈጥሩ ነበር፡፡ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ማህበሩን በመደገፋቸው ችግሩ ሊቀረፍ ችሏል፡፡
ሌላው ህጋዊነት ይዞ ለመደራጀት ስራዎች ሲጀመሩ ህጋዊ ለመሆን የተቀመጡት ቅድመ ሁኔታዎች ከማህበሩ አቅም በላይ ነበሩ፡፡ በተለይ ትልቅ የሆነ ፕሮጀክት መቅረፅ እንደ ግዴታ መቀመጡ እክል ነበረው፡፡ ለምሳሌ በህፃናትና ወጣቶች ላይ እሰራለው የሚል ማህበር የግድ ስለ ህፃናትና ወጣቶች የሚሰራ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ማየት አለበት ይባላል፡፡ ወደ መስሪያ ቤቱ ሲኬድ የሚተባበር አካል አይገኝም፡፡ እናም አላስፈላጊ አሰራሮችን በመፍጠር የሚመጣው ሰው ተስፋ ቆርጦ ነገሮችን እንዲያቆምና ወደ ፊት እንዳይኬድ የሚያደርግ አሰራሮች ነበሩ፡፡
በዚህ ሁኔታ በተማሪነት መንፈስ የእውቀትና የክሂሎት እጥረት ተደምሮበት ማህበሩን ህጋዊ ለማድረግ አስቸጋሪ ነበር፡፡ የአሰራር ሁኔታው በመንዛዛቱ የታሰበውን ያህል መስራት አልተቻለም፡፡ በተጨማሪም ያልታሰቡ ክትትሎች መደረግ፣ በተለይም የተማሪ ፖሊስ የሚባለው የሚፈጥረው ችግር ነበር፡፡ በዩኒቨርሲቲው ቅን አመራር ምክንያት ማህበሩ እስካሁን መዝለቅ ችሏል፡፡
የማህበሩ ቀጣይ እቅድ
አብዛኛው የማህበሩ አባላት በአሁን ወቅት በስራ ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ ሁሉም በየራሱ የተለያዩ ትምህርቶችን እራስን የማብቃት ሁኔታ አለ፡፡ ለታሰበው ትልቅ ህልምና ራዕይ መሳካት የሚያግዙ ነገሮች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው፡፡ በቀጣይ ትልቅ መንደር በመመስረት ከፍተኛ የጤና እክል የገጠማቸውን ሰዎች መርዳት ነው፡፡ ማህበሩም ሲመሰረት በዋናነት አላማ አድርጎ የተነሳው ወደ ውጪ ሄደው የሚታከሙ ሰዎችን በአገር ውስጥ እንዲታከሙ ማድረግ ነው፡፡ አሁን ላይ ከፍተኛ ህክምና የሚፈልጉ ሰዎች በገንዘብ እጥረት ምክንያት በየቦታው ወድቀው ይገኛሉ፡፡ ይህን የሚያስቀር መንደር በመመስረትና በውስጡም ሆስፒታል በመክፈት ከፍተኛ የህክምና ስራ ለማከናወን እቅድ አለ፡፡ ለዚህም በማሰብ አባላቱ እራሳቸውን በትምህርት እያገጎለበቱ ነው፡፡
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 26/2013