ዳግም ከበደ
ሥራ ከጀመርኩ ዕለት አንስቶ ያልተለየኝ ችግር የትራንስፖርት እጦት ነው። ከቤት ወደ ሥራ ከሥራ ወደቤት ያለው ጊዜ እንጂ በቢሮ ውስጥ የማከናውናቸው ጉዳዮች ሥራ ሆነውብኝ አያውቁም። አንድ ሰዓትና ከዚያ በላይ ለሚሆኑ ጊዜያት አስፋልት ዳር ላይ ተገትሮ ታክሲ መጠበቅ የዕለት እንጀራዬ ከሆነ ሰነባበተ፤ ኧረ ምን መሰነባበት፤ ከረመ እንጂ፡፡ እንዲያውም አስፋልት ላይ ለብዙ ሰዓት ቆሜ ትራንስፖርት ከመጠበቄ የተነሳ በቆሎ ማሳ ውስጥ እንደሚቆም የወፍና አውሬ ማስፈራሪያ ሰው መሰል አሻንጉሊት ጋር የሆንኩ ያህል እንዲሰማኝ አድርጎኛል።
በዚያ ላይ ደግሞ “እድል” የለኝም፤ ለአንድ ሰዓት ቆሜ ትራንስፖርት ስጠበቅ የነበርኩት ሰውዬ ከደቂቃዎች በፊት አጠገቤ ያልነበረ ጠብደል ድንገት መጥቶ አይሆኑ አገፋፍ ገፍቶ አሽቀንጥሮ ጥሎኝ ይገባና ጉዞውን ይቀጥላል። ይሄ እድል ሲያመልጥ ደግሞ ሌላ ተጨማሪ ረጅም ጊዜ ለመጠበቅ መገደድ ይሉታል ይሄ ነው።
ዛሬ ግን ነገሮች የተገላቢጦሽ ሆነውልኛል። እድል ፊቷን ወደ እኔ ያዞረች ነው የመሰለኝ። ገና ከቤት ወጥቼ አስፋልት ላይ ከመቆሜ አንድ ሚኒባስ መጥቶ ፊት ለፊቴ ቆመ፤ በሩ ተከፈተ። ዓይኔን ሳላሽ ተንደርድሬ ገብቼ ቁጭ አልኩ። ሎተሪ የደረሰኝ ነው የመሰለኝ። ታክሲ ውስጥ ገብቼ ጥቂት እንደተረጋጋሁ የታክሲው ረዳት ቁና ቁና ስተነፍስ አይቶኝ “ቻንስህ ነው” ሲል ጭንቅላቴ ላይ የደወለች አንድ ቃል ወረወረብኝ።
እኔና ረዳቱ በዓይን ተግባብተናል። በዚህ ቅጥ አንባሩ በጠፋው ወቅት ውስጥ ገና ከቤት ሲወጡ ሚኒባስ አፉን ከፍቶ ሲጠብቅህ ማግኘት ሎተሪ ከመድረስ በላይ ቢሆን አይገርምም። ጥቂት ታክሲው እንደሄደ ረዳቱ በመስኮቱ አሻግሮ ያማትር ጀመር። ቆየት ብሎም አንገቱን ወደ ውስጥ አስገብቶ በመገረምና በማዘን ስሜት ጭንቅላቱን ወዘወዘ። “ምነው ስል” ጠየቅሁት። “አይ በዚህ በፆም ለዚያውም የክርስቲያን ስጋ ቤት ብሎው እንዴት ስጋ ቤት ይከፍታሉ ብዬ ነው” በማለት ምላሹን ሰጠኝ።
እኔም ፈገግ እያልኩ “እሱስ ልክ ነህ፤ ዋናው የሚያስገርመው በዚህ ወቅት ስጋ ቤት መከፈቱ ሳይሆን ይሄን ሁሉ ብር አውጥቶ ስጋ ገዝቶ የሚበላ መገኘቱ ላይ ነው” ስል በምፀት መለስኩለት። አሁንም ተግባብተናል፤ መሳሳቅ ጀመርን። አሁንም “ቻንስ ነው” የምትለዋን ቃል ወረወረብኝ። በእርሱ ንግግርና በእኔ ምላሽ ጆሮውን ሰቅሎ ሲያዳምጥ የቆየው ተሳፋሪ ሁሉ ጥሩ ርእሰ ጉዳይ አገኘ መሰል ወሬያችንን ነጥቆ መንግሥትን፣ ነጋዴን ሲረግም የሚያምነው አምላኩ ደግሞ ፍትህ በመለኮታዊ መንገድ እንዲያሰፍንለት መለማመጡን ተያያዘው።
አንዱ “ምርጫው እየደረሰ ነው። ግዴለም እንቀጣቸዋለን” በማለት ሰሚ እንደሚፈልግ በሚያሳብቅ ከፍ ያለ ድምፅ ይናገር ጀመር። ቀጠል አድርጎም “ምርጫ ሲደርስ ብትመርጡን ይህን እናደርግላችኋለን የሚሉንን ያህል ተፈጥሯዊ ባልሆነ መንገድ የኑሮ ውድነቱን የሚያንሩብን ስግብግቦች አንድ ቢሉልን። ይሄን ቢያደርጉልን እኮ በደስታ እንመርጣቸዋለን” ሲል “የልቡን ሲነግሩት የኮረኮሩት ያህል ይስቃል” እንደሚባለው ተሳፋሪው በአንድ የመስማማት ድምፅ ለሰውዬው ትችት ፈገግታውን ለገሰው። እኔና ረዳቱ የርእሰ ጉዳያችን መስፋት እና የሁሉም ሃሳብ መሆኑ ገርሞን እየተያየን እንሳሳቃለን።
የልጁን ሃሳብ መጨረስ ያስተዋሉ በእድሜ ጠና ያሉና ጨዋታ የሚያውቁ አንድ እናት ደግሞ ቀጠሉ፤ “ባለፈው ሰሞን ጎረቤቴ ተጨማሪ መኖሪያ ቤት መስራት ይጀምራል” ሲሉ ጀመሩ፤ በዚህ የኑሮ ውድነት ጣሪያ በነካበት ሰሞን ሰውዬው ቤት መስራት መጀመሩን እሳቸው ከእብደት ጋር አመሳስለው በማየት ጨዋታውን አሟሟቁት። “ታዲያ ግንባታውን የሚያይ አላፊ አግዳሚ ልክ በስጋ ቤት እንደሚያልፍ ዓይነት በብሎኬቱ፣ በሲሚንቶው፣ በብረቱ፣ በአሸዋውና እየቋመጠ የሚሄድበትን ቦታ ሁሉ እየረሳ ቆሞ ሲመለከት ይውል ጀመር” በማለት ተሳፋሪውን በሙሉ በሳቅ እምባ ያራጩት ጀመር።
እኚህ ጨዋታ አዋቂ እናት በቀልድ መልክ ይሄን ይበሉ እንጂ ረዳቱ እንዳለው በአሁኑ ወቅት አይደለም ቤት መስራት ራስን ለማኖር፣ ታክሲ አግኝቶ ወደ ሥራ ቦታ ለመንቀሳቀስ እድል፤ አሊያም በፈረንጅኛው አፍ “ቻንሰኛ” መሆን ይጠይቃል። በዚህ ወቅት መኖሪያ ቤት እየገነባህ ከሆነ ወይ ባለስልጣን ነህ፣ አሊያም ስግብግን ነጋዴ ነህ። አስተያየቱ ጥረው ግረው በእውነት ፀጋን ያገኙትን ባያካትትም፣ በዚህ ሰሞን ግን ሰዉ ይሄን ቢያስብ አይፈረድበትም። ነገርዬው እስከዚህም ድረስ ያስጠረጥራላ።
የሰሞኑን ፖለቲካ የሚከታተል አንዱ ወጣት ደግሞ ከሌላኛው የሚኒባስ መቀመጫ ላይ ሆኖ ሌላ አስተያየት ሰነዘረ፤ በኑሮ ውድነቱና በአምባሳደሮቻችን የዲፕሎማሲ ውድቀት በግኗል፤ “አምባሳደርና ዲፕሎማቶቻችንን ካሉበት አገር መልሶ የሚከፈለውን ዶላር ለኑሮ መደጎሚያ ማድረግ ነበር” አለ።
ስለ ሲሚንቶና ብረት ሲያወሩ የነበሩት እናት ወሬውን ከአፉ ቀበል አድርገው “እውነት ነው ልጄ፤ ካልሰሩ እሰው አገር ተዘፍዝፈው እነሱን ማን ይቀልባል። ዶላሩ ለእነርሱ በብላሽ ከሚበትን መንግሥት ለዘይት መግዣ ለእኛ ለእናቶች ቢያከፋፍለን ጥሩ ነው። እኛም ኤምባሲዎች በር ላይ ተሰልፈን የነሱን ሥራ በእጥፍ እንሰራለን” ብለው በድጋሚ ተሳፋሪውን አስፈገጉት። የእውነቴን ነው ከእነሱ የዲፕሎማሲ ሥራ የእኛ ልጆች ሰልፍ እያስናቀ ነው:: የፈረንጆቹ ነገር ለዘብ ማለት ጀምሯል ሲባል የሰማሁ መሰለኝ፤ ይህ የሆነው በልጆቻችን አቤቱታ መሰለኝ አሉ፡፡
የታክሲ ውስጥ ጭውውቱ ሰሞኑን የተካሄደውን የቲውተር ዘመቻ መሰለ፤ አንድ ጎልማሳና ድምፁ ጎርነን ያለ ሰው የተሳፋሪውን እሮሮ ተቀላቀለ። የምጣኔ ሀብት እውቀት ያለው ይመስላል። ምፀት የተቀላቀለበትን ጨዋታ ምርር ወዳለ ጨዋታ ይወስደው ጀመር። መንግሥት የሸማቾች ማህበር እያለ ዋጋ ለማረጋጋት በየወረዳው ያቋቋመው የንግድ ስፍራ የኑሮ ውድነቱን እንደማያቃልለው ይልቁንም እንደሚያንረው ይነግረን ጀመር። ከዚያ ይልቅ ማህበራቱን በእርሱ ተፅእኖ ስር ከሚያደርግ ይልቅ ነፃ የሸማች ማህበራት እንዲኖሩ ፈቅዶ ኅብረሰሰቡ ራሱ መብቱን እንዲያስከብር ቢያድርግ መልካም ነው ሲል ጠቆመ።
“በአዲስ አበባ ሚኒባስ ታክሲዎች ሰሞኑን ነዳጅ ጨመረ፣ታሪፉ ይታይልን፣ ቅጣት በዛብን እያሉ ተጨማሪ ካላስከፈልን ብለው አድማ ሲመቱ ኅብረተሰቡ ግን ጫና በዛብኝ ብሎ አቤት አለማለቱ ይህን ሰው አስገርሞታል:: እሺ በዚህ ሀገር በብዙ ጉዳዮች በተወጠረችበት በእዚህ ወቅት አድማ አይምታ፤ በጨዋ ቋንቋ ለምን አቤት አይልም በማለት ሃሳቡን ሲደመድም ተሳፋሪው በግርምት በአንድነት ይተያይ ጀመር።
ሚኒባሱ እንደ ኤሊ እየተጎተተ መጨረሻው ተርሚናል ደረሰ። የኑሮ ውድነትና የትራንስፖርት እጦት ርእሰ ጉዳይ ቤተሰብ ያደረገን ተሳፋሪዎችም ከሚኒባሱ ወርዶ መለያየት ግድ አለን። ምንም ማድረግ አይቻልም! እንደ ረዳቱ አባባል ይሄም
“ቻንስ ነው” ።
በነገራችን ላይ እኔም በዚሁ አጋጣሚ “መንግሥት ሆይ የኑሮ ውድነቱ ጣሪያ እየነካ ነውና አንድ በለን” ስል በዛሬው የሚኒባስ ተሳፋሪዎች ስም ግልፅ ደብዳቤ ጽፌያለሁ። ቸር እንሰንብት!!
አዲስ ዘመን መጋቢት 08/2013