ውብሸት ሰንደቁ
ኅብረት ሥራ ማህበራት በሌሎች ሀገራት ብዙ ዜጎችን ከድህነት ማጥ ያወጡ ተቋማት ናቸው፡፡ የገበያ ሁኔታውን በማረጋጋትና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል በመፍጠር የሚስተካከላቸው እንደሌለም ይነገራል፡፡
በኢትዮጵያ በተለይ ተገቢ ባልሆነ የዋጋ ንረት እና የሸቀጦች መጥፋት የዜጎቿ ኑሮ የተናጠበት ይቆጠር ቢባል ያታክታል፡፡ ይህን ይፈቱታል ተብለው ከሚጠበቁ ማርከሻዎች መካከል የኅብረት ሥራ ማህበራት ቀዳሚ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ሆኖም ችግሮቹ ሥር የሰደዱ እና ራሳቸው የኅብረት ሥራ ማህበራቱም ድጋፍ የሚሹ በመሆናቸው ተሳካላቸው የሚባል ደረጃ አልደረሱም:: ለእሳት ማጥፊያ የሚሆን አቅም ግን የተቸራቸው ይመስላል፤ ምክንያቱም ብዙ ጊዜ ሌላው ቢቀር በሕዝቡ ዘንድ የሚከበሩ በዓላትን ተንተርሶ ለሚፈጠር የዋጋ ንረት ተደጋጋሚ የማረጋጋት ሥራዎችን ከውነዋል፡፡
የፌዴራል ኅብረት ሥራ ማህበራት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዑስማን ስሩር እንዳሉት፤ ኅብረት ሥራ ማህበራት አንዱ ተልዕኳቸው የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ነው፡፡ ይህን ለማሳደግ ደግሞ የግብርና ቴክኖሎጂዎችን ለአርሶ አደሩ፣ አርብቶ አደሩና ከፊል አርብቶ አደሩ ቀዬው ድረስ በተመጣጣኝ ዋጋና በትክክለኛው ጊዜ ማቅረብ ተገቢ ነው፡፡ ይህን በማድረግ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ይቻላል፡፡ ከዚያ ቀጥሎ የሚሆነው ለአደገው ምርት ገበያ መፈለግ ነው፡፡ የኅብረት ሥራ ማህበራት ሌላው ተልዕኳቸው አምራቹን ከሸማች ወይም ባለ ኢንዱስትሪ ጋር ያለምንም ተጨማሪ የዕሴት ሰንሰለት ሁለቱም ወገኖች ተጠቃሚ የሚሆኑበት ዕድል መፍጠር በመሆኑ አምራቹ ማህበረሰብ በለፋበት ልክ ፍትሃዊና ትክክለኛ ዋጋ እንዲያገኝ የሚያስችል ሲሆን ኢንዱስትሪያሊስቱና ሸማቹ ማህበረሰብ ምርቶችን በአጠረ የዕሴት ሰንሰለት በትክክለኛ የገበያ ዋጋ እና በትክክለኛ ልኬትና ጥራት ማገናኘት ላይ አልሟል፡፡
በሌላ በኩል በፌዴራል ኅብረት ሥራ ማህበራት ባዛር ሲቀርብ ኅብረተሰቡ ኅብረት ሥራ ማህበራት በገበያ ላይ በትክክለኛ ዋጋና ጥራት ምርት እንደሚያቀርቡ እንዲያውቅ ማድረግ ነው፡፡ የክልል እና የዞን ከተሞችም መሰል ኤግዚቢሽኖችን እንዲያካሂዱ ይጠበቃል፡፡ ይህን ኤግዚቢሽን ኦሮሚያ ክልል በክልል ደረጃ ማዘጋጀት እንደጀመረ እንዲሁም በአማራ ክልልም በስፋት እየተካሄደ መሆኑን ገልጠዋል፡፡ በተለይም አማራ ክልል ከክልል ደረጃ ባለፈ በዞን ደረጃ ኤግዚቢሽን ማዘጋጀት ጀምሯል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ዝግጅቶች ተጠናክረው ከቀጠሉ ኅብረተሰቡ አምሥት ስድስት ጊዜ አማራጮች ስለሚኖሩት ሰው ሠራሽ የሆኑ የአቅርቦት ችግሮች እና ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የሌላቸው የዋጋ ንረቶች ይጠፋሉ::
የኅብረት ሥራ ማህበራት ሚዛን ማስጠበቅ እንጂ ሁሉንም የንግድ ሥራ እንዲሠሩት እንደማይጠበቅና ማህበራቱ አንድ የቢዝነስ ተቋም እንጂ ብቸኛ ሊሆኑ አይችሉም ያሉት ዳይሬክተሩ በቂ ምርት በማቅረብ ረገድ ችግር እንደሌለ እና በጠቅላላ ሀገሪቱ ያሉት የኅብረት ሥራ ማህበራት በሰጡት መረጃ መሠረት የአቅርቦት ችግር እንደማይኖር ተረጋግጧል ብለዋል፡፡ የኅብረት ሥራ ማህበራት ከአራት ሺህ እስከ አምስት ሺህ ኩንታል ምርት በቦታው መከዘን የሚችሉ ሲሆን በአቅራቢያ የሚገኙ ማህበራት ደግሞ ሲያልቅባቸው እያስመጡ ይሸጣሉ ተብሏል፡፡ የእንስሳትና እንስሳት ተዋፅዖ ምርትም በተመሳሳይ በጨረሱ ጊዜ እያስመጡ ይሸጣሉ፡፡
አቶ ኡስማን የኑሮ ውድነቱ ጉዳይ የገበያ ሥርዓቱ የጤንነት ጉድለት ነው ያሉ ሲሆን በመደበኛው አካሄድ የማምረቻ ወጪ በተለየ መንገድ ከጨመረ እና ከፍ ያለ ፍላጎት የሚያመጣ ነገር ከተፈጠረ ኑሮ ውድነት ሊመጣ እንደሚችል አብራርተው ሆኖም እንደ ኅብረት ሥራ ማህበራት ያለውን ምርት ለተፈጠረው የኑሮ ውድነት ምክንያት ሊሆን የሚችል ችግር አልተፈጠረም ብለዋል:: የተለየ የማምረቻ ወጪ የሚጠይቅም ሆነ ፍላጎት እንዲጨምር የሚያደርግ ነገር ስላልተፈጠረ የኑሮ ውድነቱ ጤናማ ካልሆነ የገበያ ሥርዓት የመነጨ ነው እንላለን ሲሉ አክለዋል፡፡
ኅብረት ሥራ ማህበራት ዋናው ሥራቸው በአጠረ የእሴት ሰንሰለት በግብይት ሥርዓት ውስጥ ያሉ ተዋናዮችን ማገናኘት ነው፡፡ ይህ አምራቹ ለምርቱ ፍትሃዊ የገበያ ዋጋ እንዲያገኝ ያስችለዋል፤ ሸማቹም በቀጥታ ወይም በአጭር የእሴት ሰንሰለት ከአምራቹ ጋር በመገናኘቱ ምክንያት በተገቢ ዋጋ ተገቢውን ምርት የሚያገኝበት ዕድል እንደሚፈጠርና ሁለቱም ወገኖች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በመጥቀስ የኤግዚቢሽኑ መካሄድ የዋጋ ንረቱን ለመቀነስ የበኩሉን አስተዋፅዖ እንደሚያበረክት ጠቁመዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ ከዚህ ቀደም በነበሩ ልምዶች የኅብረት ሥራ ማህበራት ለሽያጭ የሚያቀርቧቸው ምርቶች በትንሹ ከ20 እስከ 30 በመቶ ቅናሽ እንደነበራቸው ያስታውሳሉ:: ኅብረት ሥራ ማህበራቱ በተቻለ መጠን የተጋነነ ዋጋ እንዳይኖር በማድረግ ምክንያታዊ የሆነ የትርፍ ህዳግ ይዘው እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል።
ዓመታዊውና 8ኛው ሀገር አቀፍ የኅብረት ሥራ ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየም ዝግጅት «የኅብረት ሥራ ግብይት ለዘላቂ ሰላም» በሚል መሪ ቃል ከመጋቢት 9 እስከ 13 2013 ዓ.ም ድረስ መዲናችን አዲስ አበባ ላይ በልዩ ልዩ ኩነቶች በታላቅ ድምቀት ይከናወናል ሲሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ነግረውናል፡፡
የኅብረት ሥራ ማህበራት ልምድና ተሞክሮዎች መጋቢት 9 ቀን 2013 ዓ.ም ላይ ሲምፖዚየም የሚቀርብ ይሆናል፡፡ ይህ ሲምፖዚየም ኅብረት ሥራ ማህበራት በዋናነት ያላቸውን ምርጥ ተሞክሮ እና በተሰማሩባቸው የሥራ መስኮች ያሳኳቸው በማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ፣ በሰላም ግንባታና በሀገር ግንባታ ያበረከቷቸው አስተዋፅዖዎች ላይ ያላቸው ምርጥ ተሞክሮዎች ለመሰል የኅብረት ሥራ ማህበራት ልምድ እንዲቀስሙ በሚል የተዘጋጀ ነው፡፡ በዚህ ሲምፖዚየም ላይ ከ300 በላይ ታዳሚዎች ይገኛሉ፡፡ አራት ኅብረት ሥራ ማህበራትም የተመረጡ ልምዶቻቸውን ያቀርባሉ፡፡
በተመሳሳይ አንድ ዞን በኅብረት ሥራ ማህበር ያለውን ምርጥ ተሞክሮ ያቀርባል፡፡ ይህ የሚቀርብበት ምክንያትም የሚቀርበው ልምድ ተቀምሮ ቢሰፋ መልካም ነው በሚል እሳቤ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ተሞክሮዎችን ሚዲያዎችም ተሳትፈውበትና እዚህ ውስጥ ላልታደመው የማህበረሰብ ክፍል ማስፋፋት ቢቻል ኅብረት ሥራ ማህበራት በአጠቃላይ በተጨባጭ በሀገር ግንባታ፣ በሕዝቦች ትብብር፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮችን በመፍታት እንዲሁም የሥራ ዕድል በመፍጠር ዜጎችን በዘላቂነት ከድህነት ከማውጣት አልፈው አካባቢዎችን እርስ በእርስ በኢኮኖሚም በማህበራዊ ግንኙነትም ትስስር በመፍጠር ጠንካራ መስተጋብር እንዲኖር በማድረግ ረገድ ያላቸውን ሚና ይዳስሳል፡፡
የዚህ መርሀ ግብር ሁለተኛው ኩነት የኅብረት ሥራ ማህበራቱ ኤግዚቢሽንና ባዛር ነው፡፡ የዚህ ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየም ዋና ዓላማው አምራቹ በቀጥታ ከሸማቹ ጋር የሚተሳሰርበት ዕድል መፍጠር ነው:: በተለይ የግብርና ኅብረት ሥራ ማህበራት ምርትና አገልግሎታቸውን በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚሸጡበትን መፍጠር እንዲሁም ከረጅም ጊዜ አንፃር ደግሞ ዘላቂ የገበያ ትስስር ፈጥሮ መውጣት ዋና የኩነቱ ትልም ነው፡፡ በተጨማሪም የኅብረት ሥራ ማህበራቱ አንዱ ተልዕኳቸው የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ከመሆኑ አንፃር በኤግዚቢሽንና ባዛሩ በርካታ የግብርና ግብዓቶችን የሚያቀርቡ ትልልቅ ኩባንያዎች ይሳተፋሉ፡፡ በተለይ የግብርና ሜካናይዜሽን መሣሪያዎችን የሚያመርቱ ወደ ሀገር ውስጥ የሚያስገቡና የሚሸጡ ድርጅቶች ከኅብረት ሥራ ማህበራት ጋር የገበያ ትስስር የሚፈጥሩበት መድረክ ነው የሚሆነው፡፡
በኤግዚቢሽኑ ወደ 66 አካባቢ የኅብረት ሥራ ማህበራት እንዲሁም ከ10 በላይ የተለያዩ የግል ኩባንያዎች፣ የግብርና ግብዓት አቅራቢዎችና ባለ ኢንዱስትሪዎች ይሳተፋሉ፡፡ እነዚህ የህብረት ሥራ ማህበራት ከ500 በላይ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን ይዘው ይቀርባሉ፡፡ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርቶችን በማቅረብ በመዲናችን ላይ የሚታየውን ያልተገባ የኑሮ ውድነትም በተጨባጭ ለማረጋጋትም የድርሻቸውን ያበረክታሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የኅብረት ሥራ ማህበራቱ ከመላው የሀገራችን አካባቢዎች ማለትም ከሁሉም ክልሎችና ከሁለቱ ከተማ መስተዳድሮች የሚሳተፉ ነው የሚሆኑት፡፡
የኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየም መርሀ ግብሩ የግብርና እና የኢንዱስትሪ ምርት መገበያያ ብቻ ሳይሆኑ የሀገራችን ሕዝቦች የሀገሪቱን ህብረ ብሔራዊ ውበትና ባህላዊ ትውፊቶች ከአለባበስና ከአነጋገር በማቆራኘት የሕዝቦች መስተጋብር እና የእርስ በእርስ ትስስርን የሚፈጥር ነው፡፡
«የኅብረት ሥራ ግብይት ለዘላቂ ሰላም» መሪ ቃል የተመረጠበት ዋናው ምክንያትም ኅብረት ሥራ ማህበራት የሚደራጁት በሰዎች፣ የሚሠሩት ለሰዎች እና የሚሠሩትም ከሰዎች ጋር በመሆኑ ማኅበራቱ ዘር፣ ቀለም፣ ብሔር፣ ኃይማኖትና የመሳሰሉትን ሳይመርጡ ሁሉንም አካታች እሴት ያላቸው የቢዝነስ ሞዴሎች በመሆናቸው ነው፡፡ ኅብረት ሥራ ማህበራት ፍትኃዊ በሆነ መንገድ የሚደራጁና ፍትኃዊነትን የሚያረጋግጡ፤ ዜጎች በተሳትፏቸው ልክ እንዲጠቀሙ የሚያደርጉ ማህበራት ናቸው፡፡
ገጠርን ከከተማ በቀጥተኛ የኢኮኖሚ ትስስር የሚፈጥሩና ትስስሩም አንዱ ለሌላው ዋስትና እንደሆነና አንዱ ያለ ሌላው መኖር እንደማይችል የሚያሳይና በዚህ መካከል የሚፈጠረው ትብብር ሰላምን ለማስፈን ሚናቸው የላቀ መሆኑን ማሳያ በመሆኑ ነው፡፡ የኅብረት ሥራ ማህበራት ግብይት ለሰላም ግንባታ ሲባልም ኅብረት ሥራ ማህበራቱ ካሏቸው መርሆዎችና እሴቶች አጠቃላይ መስተጋብር የሚመነጭ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ይህን ሃሳብ ታሳቢ በማድረግ ነው መሪ ቃሉ የተቀመጠው፡፡
ከዚህ ኤግዚቢሽንና ባዛር በህብረት ሥራ ማኅበራት ደረጃ አንዱ ለሌላው ልምድ የሚያካፍልበት፤ በሲምፖዚየም ታዳሚዎች ማለትም የኅብረት ሥራ ማህበራት ባለቤቶች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የዘርፉ ምሁራን እና ባለድርሻ አካላት የበለጠ መነሳሳት የሚፈጥሩበት እና በቀጣይነት ኅብረት ሥራ ማህበራትን ለመደገፍም ይሁን ለማጠናከር መነሳሳትና ቁጭት ይፈጠራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየሙ ከመላው ሀገሪቱ ከሚቀርቡ ጤፍ፣ የስንዴ ዱቄት፣ ቅመማ ቅመም እና ሌሎችም በቀጥታ ግብይት ከ4 እስከ 5 ሺህ ኩንታል፤ የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም ከ20 ሺህ ኩንታል በላይ እንዲሁም ከ30 ሺህ ኩንታል በላይ የሚገበያዩ ደግሞ ውል የሚዙበት ነው፡፡ በተጨማሪም ኅብረት ሥራ ማህበራቱ ከቴክኖሎጂ አቅራቢ ኢንዱስትሪዎች ጋር የገበያ ትስስር ፈጥረው ይወጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አጠቃላይ መዲናችን አዲስ አበባና በዙሪያዋ ያሉ ሸማቾች የሚታየውን የገበያ ዋጋ በማረጋጋት ጤናማ የዋጋ ሥርዓት ይፈጠራል ተብሎለታል፡፡ ገበያው እጅግ የተረጋጋ፤ ሁሉንም ያሳተፈ፤ ሁሉንም በተሳትፎው ልክ ተጠቃሚ የሚያደርግ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ከዚህ ቀደም የነበሩ ልምዶችና ተሞክሮዎች ውጤት የሚያሳየውም ይህንኑ ነው፡፡
ይህን ሁነት ለማድመቅ የአዲስ አበባ አስተዳደር ኅብረት ሥራ ኤጀንሲ መጋቢት 8 ቀን 2013 ዓ.ም ላይ የመኪና ትርኢት የሚከናውን ሲሆን የተዘጋጀውን የኅብረት ሥራ ማህበራት ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየም የበለጠ መረጃ ለመስጠት፣ የጎደለውን የመረጃ ክፍተት ለመሙላትና መነቃቃትና መነሳሳት ለመፍጠር ታስቦ የሚካሄድ ነው፡፡
ኤግዚቢሽንና ባዛር አምራችና ሸማች ፊት ለፊት የሚገናኙና በመካከላቸው እበላ ያለ ነጋዴና ላጭበርብር ያለ ደላላ የማይገባበት ነው፡፡ ይህ ደግሞ የግብይት ሰንሰለቱን ያሳጥረዋል፡፡ ወቅቱ የሸቀጦች ዋጋ የተሰቀለበት ነውና ለአጭር ጊዜ የሚቆይ እንኳን ቢሆን እነዚህ የኅብረት ኢንቨስትመንቶች የሸቀጦችን ዋጋ ቁልቁል መሳብ ይችሉ ይሆን? ለሚለው ጥያቄ መጪዎቹ ቀናት መልስ ይኖራቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 08/2013