ጌትነት ተስፋማርያም
በኮቮድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት የአንድ ዓመት የስራ ዘመን የተራዘመለት አምስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የሥራ ዘመኑ ሊያልቅ ጥቂት ወራቶች ብቻ ቀርተዋል። ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ እስኪከናወን ድረስም የተለያዩ ሕጎችን እና አዋጆችን እያወጣ እና ሥራ አስፈጻሚዎችን እየተከታተለ ስራውን እያከናወነ ይቀጥላል። እኛም በቀጣዩ ምርጫ በአርባ ምንጭ ከተማ ብልጽግና ፓርቲን ወክለው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከሚወዳደሩት እና ከወቅቱ የምክር ቤት አፈጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ጋር ከለውጥ በፊት እና በኋላ ስለነበረው የምክር ቤት አሰራር ሁኔታ ላይ በማተኮር ቆይታ አድርገናል፡፡ የምክር ቤቱ የሪፎርም ስራዎች ውጤት፣ ስለፓርላማ ዲፕሎማሲ እና ቀጣዩ ፓርላማ ምን መምሰል እለበት በሚሉ እና በሌሎችም ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ከአቶ ታገሰ ጫፎ ጋር ያደረግነውን የቃለ ምልልስ ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
አዲስ ዘመን ፦ በምክር ቤቱ የተከናወኑ የሪፎርም ሥራዎች ምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ? ምንስ ውጤት አስገኝተዋል?
አቶ ታገሰ፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሕገመንግስታችን አንቀጽ 50 መሰረት የኢትዮጵያ ከፍተኛው የሥልጣን አካል ነው። ሕግ አውጪውም አካል በመሆኑ ትልቁ ሥራው ሕግ ማውጣት ነው። በሌላ በኩል አስፈጻሚዎችን የማደራጀት እና የመቆጣጠር ኃላፊነት አለበት። በዋናነት ደግሞ የሕዝብ ውክልና ስላለው የሕዝብን ጥያቄዎች ያነሳል።
በዚህ አግባብ እንደ አገር ከመጣው ለውጥ በኋላ በርካታ የለውጥ (ሪፎርም) ሥራዎች ተከናውነዋል። ምክር ቤቱ ቀደም ሲል የወጡ እና የልማት ሥራውም ሆነ የአስተዳደር ሥራው በተገቢው መንገድ እንዳይፈጸሙ አፋኝ የሆኑና አስረው የያዙ ሕጎችን ለማስተካከል ጥረት ተደርጓል።
ከሕግና ፍትሕ ጋር የተያያዙ ሕጎች፤ ከሰላምና ደህንነት እንዲሁም ከማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ሕጎች እንዲስተካከሉ ተደርጓል። ሁላችንም እንደምናውቀው የፀረሽብር አዋጁ፣ የበጎ አድራጎት ልማት ድርጅቶች አዋጅ ፣ የመገናኛ ብዙሃን አዋጅ፣ የጦር መሳሪያ ቁጥጥር አዋጅን ለአብነት ብንመለከት ለሀገሪቷ ቀጣይ እድገትና ሰላማዊ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር እጅግ አስፈላጊ ናቸው።
በኢኮኖሚውም የንግድ፣ የፋይናንስና ባንክ ስርዓት እንዲሁም ሌሎች አዋጆችም እንዲስተካከሉ በመደረጋቸው በሕግ ደረጃ ትልቅ ስራ ተከናውኗል። በዚህ ሂደት የሕጎቹን ጥራት፣ ተፈጻሚነትና ተደራሽነት ጭምር የሚጎዱ እና የተሟላ እንዳይሆን የሚያደርጉ ሳንካዎችን በመለየት የኢፌዴሪ የሕግ አዘገጃጀት እና ረቂቅ ማንዋል ተዘጋጅቷል። ስለዚህ ሕግ ከሚረቅበት ተነስቶ እስከሚጸድቅበት ያለው በተናበበ መልኩ እየተሰራበት ይገኛል።
በሌላ በኩል የተበተነ የነበረውን የምክር ቤቱ ክትትል እና ቁጥጥር ስራ የቋሚ ኮሚቴዎችንም አደረጃጀት በማስተካከል የለውጥ ሥራ ተከናውኗል። በምክር ቤቱ 10 ቋሚ ኮሚቴዎች እና በስራቸው 33 ንዑስ ኮሚቴዎች በማደራጀት በተናበበ መልኩ የቁጥጥር ሥራውን መስራት እና ማሰራት የሚችል አደረጃጀት እንዲፈጠር ጥረት ተደርጓል።
በቋሚ ኮሚቴዎች አማካይነት የአስፈጸሚ አካላት ተቋሞችን በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ክትትል እንዲያደርጉ ተደርጓል። ለአብነት ውሃን በተመለከተ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ምን ያክል ተፈጽሟል የሚለውን በተጨባጭ ሁኔታ ለማየት ተሞክሯል። በምክር ቤት ደረጃ የሚደረጉ ውይይቶች የሕዝቡን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ እንዲሆን እና የክትትል ስራውም ከዝርዝር ጉዳይ ይልቅ በወሳኝ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር ጥረት ተደርጓል።
አሁን ላይ የፓርላማው የውክልና ሥራው እንዴት መሆን አለበት የሚለው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን እንዲጠና ተደርጓል። ለአብነት በየካቲት ወር እና ክረምት ወቅት ላይ ምክር ቤቱ ዝግ በሚሆንበት ሰዓት አባላቱ ወደመረጣቸው ሕዝብ ወርደው ያወያያሉ፤ ይገናኛሉ። በጥናቱ መሰረት ይህ ግን በቂ አይደለም።
በየጊዜው የሕዝቡን ጥያቄ ለማቅረብ በወቅታዊነት ከሕዝብ ጋር መገናኘት የሚችሉበት አማራጭ መፈጠር አለበት የሚል የጥናት ውጤት አለ። የፓርላማ አባላት ከመረጣቸው ሕዝብ ጋር በቴሌ ኮንፈረንስ እንዴት መገናኘት ይችላሉ የሚለው ቴክኖሎጂ አዘል አካሄድ እየታየ ነው። የወረዳ እና የክልል ምክር ቤት ተመራጮች ጋር በቀጥታ በመገናኘት የፓርላማ አባላት በቂ መረጃዎች እንዲያገኙ እና የውክልና ሚናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አማራጮች ቀርበዋል።
እነዚህን ታሳቢ ያደረጉ የአሰራር ሥርዓቶች ተዘርግተዋል። በቀጣዩ ፓርላማ ዘመን የጥናቱ ውጤቶች በሥራ ላይ ሊውል ይችላል። ጥናቱን መሰረት አድርጎ የምክር ቤቱን አሰራር እና አባላት ሥነምግባር ደንብ ተሻሽሏል፤ ጉዳዩም ወደመጽደቁ እየሄደ ነው።
አንዱ የለውጥ አጀንዳ የሆነው የምርምርና ጥናት ዘርፍ እራሱን ችሎ በፓርላማው ስር እንዲደራጅ ተደርጓል። በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያውን የፓርላማ ምርምር ኮንፈረንስም በማካሄድ በምክር ቤት ጉዳዮች ላይ በርካታ ጥናትና ምርምሮች እንዲቀርቡ ተደርጓል።
በዋናነት ደግሞ ምክር ቤቱ በራሱ የለውጥ ሥራዎች ጽሕፈት ቤት በኩል ምን ለውጦች ያስፈልጋሉ?፤ ምንስ ተከናውኗል የሚለው በዝርዝር ይታያል። በአጭር እና በረጅም ጊዜ እቅድ ተለይቶ የትኞቹ ሕጎች፣ አሰራሮች እና ሥርዓቶችን በምክር ቤቱ አሻሽሎ መሄድ ይገባል፣ የእስካሁኑስ አፈጻጸም ምን ያሳያል፣ የሚለውን በመለየት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል።
አዲስ ዘመን፦ ከሪፎርሙ በፊት የነበረው ጣልቃ ገብነት እና ጫና እንዴት ይገለጻል?
አቶ ታገሰ፦ ምክር ቤቱ ውስጥ ለሚነሱ ሃሳቦች አባላት ተጠያቂ አይሆኑም። ከለውጡ በፊት ግን በተጨባጭ ይህ አልነበረም። በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ለምን ይህን አይነት ውሳኔ ያዛችሁ ተብለው ይጠየቃሉ። የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ ከኦዲት ጋር ተያይዞ በሚመጡ መረጃዎች ከተቋማት ጋር ከፍተኛ ክርክር ያደርጋል።
ለአብነት ከስኳር ኮርፖሬሽን አፈጻጸም፣ ከኢትዮጵያ ብሮድካስት የዲጂታላይዜሽን ስራዎች ጋር በተያያዘ እና በሌሎችም ተቋማት ላይ ቋሚ ኮሚቴው ጥልቅ ምርመራ ያካሂድ ነበር። በዚህ ወቅት ግን የቋሚ ኮሚቴውን አባላት ሃሳብ ለማስቀየር ከቦታው ማንሳት እና ቶሎ ዞር ማድረግ እንዲሁም መረጃዎችን ደብዛ የማጥፋት ሴራ ይፈጸማል። በምክር ቤቱ ስራ የተለያዩ አካላት ጣልቃ ይገቡ ነበር።
ጣልቃ ገብነቱ ገዥው ፓርቲም እራሱ እንዲጠፋ ስለሚያደርገው በመሰረቱ ገዥውን ፓርቲም የሚጠቅም አልነበረም። በምክር ቤቱ የሚደረጉ ግምገማዎች እና ክርክሮች ስህተቶችን ለማስተካከል እና የሚታረም አስፈጻሚ ካለ ጠቃሚዎች ናቸው።
ቀደም ሲል የነበረው አንዱ ችግር ለማዳመጥም ዝግጁ አለመሆን ነው። ሕዝብ የሚያነሳው ምንድን ነው? ምክር ቤቱ የሚወያይበት ጉዳይ ምንድን ነው? ብሎ ለማዳመጥ ዝግጁነት አልነበረም። በሌላ በኩል መረጃዎች ከተገኙ በኋላም ማድበስበስ እና ጉዳዩን ማጥፋት ነው የሚፈለገው። መረጃዎቹን ለምክር ቤቱ ያመጣ ሰው ከስራው እንዲነሳ አሊያም እንዲጠፋ ይደረጋል። ዘርፈ ብዙ ጫናዎች በምክር በቤቱ ላይ ደርሰዋል። በፍርድ ቤቶች ጉዳይ ጣልቃ ይገባል፤ የሰብዓዊ መብት ሪፖርት ዝግጅት ላይ ጭምር ጣልቃ ገብነት ነበር። እነዚህ ጉዳዮች ተደማምረው ሀገራዊ ለውጡ እንዲቀጣጠል አድርገዋል።
አስፈጻሚዎች ቢችሉም ባይችሉም ከነችግራቸው ይቆዩ ነበር። እኛ አገር ሥራ ካልቻለ በገዛ ፍቃድ መልቀቅ መለመድ አለበት። ይህ ባህል እንዲጎለብት እንጂ ችግሮች ተድበስብሰው እንዲያልፉ ማገዝ አይገባም። ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፕሮጀክቶች በአግባቡ የማያከናውኑትን መንግስት ነፃ በሆነ መንገድ ማስተካከያ መስጠት አለበት። ቀደም ሲል በምክር ቤቱ የነበረው አፈናና ጣልቃ ገብነት ከለውጡ በኋላ በከፍተኛ ሁኔታ ቀንሷል፤ ይህን ልምድ እያጎለበቱ መሄድ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡- ከለውጥ በፊት በነበረው ጊዜ በርካታ ፕሮጀክቶች ቢዘገዩም ሆነ ዘረፋዎች በአስፈጻሚ ተቋማት ላይ ሲታይ ምክር ቤቱ ዝምታን መርጦ ነበር በሚል ይተቻል፤ ከለውጡ በኋላ ላይ ግን አባላቱ ሳይቀየሩ ፓርላማው ሞጋች ወደመሆን መሸጋገሩ ይነገራል፡፡ በዚህ ደረጃ እንደ ምክር ቤትም ሆነ እንደ አባላቱ ለውጡ እንዴት ሊመጣ ቻለ?
አቶ ታገሰ፡- ቀደም ሲል በነበረው አሰራር የምክር ቤት አባላት ጥያቄ ለማንሳት ብዙ ፍላጎት አላቸው፤ ግን ከሰዓት በፊት ያነሱትን ጥያቄ መነሻ በማድረግ ከሰዓት በኋላ ይጠየቁበት ነበር። ይሄ በምክር ቤቱ የፈለጉትን ሃሳብ እንዳያንሸራሽሩ እና አቋም እንዳይዙ ሥርዓቱ እንዲሁም አጠቃላይ ተቋማዊ አሰራሩ ጫና ፈጥሮባቸው ነበር።
እንደሚታወቀው የምክር ቤት አባላት ለሕገመንግሥቱ፣ ለሕዝቡ እና ለህሊናቸው ታማኝ መሆን አለባቸው። ስለዚህ አባላት በምክር ቤቱ ውይይት ወቅት በሚያነሱት ሃሳብ አይጠየቁም። ነገርግን በተጨባጭ የነበረው አሰራር አባላት ውሳኔያቸውን እንዲቀይሩ እንጂ በነጻነት እንዲነጋገሩ አይደረግም። ከለውጡ በኋላ ዴሞክራሲያዊ አካሄዶችን በመከተል የምክር ቤቱ አባላት በመሰላቸው ሃሳብ ላይ ጊዜ ወስደው እንዲከራከሩ እና የእራሳቸውን አቋምም እንዲወስዱ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት ተኩል ጊዜ ውስጥ አባላቱ ጫና ሳይሆን ለምክክር በቂ ጊዜ እንዲወስዱ ነው የሚደረገው። ለአብነት የተሳሳተ መረጃ ሲኖራቸው የተሳሳተ ነገር ሊያነሱ ይችላሉ፤ ይህ ግን ችግር አይደለም፤ ሌላኛው የምክር ቤት አባል ደግሞ ያን ስህተት በማረም በመረጃ ያስደገፈ ንግግር ሊያደርግ ይችላል። በተጨማሪ በሀገራችን በሚከሰቱ ግጭቶች ላይ ሀሳብ አንስቶ በመወያየት ችግሩን ለማቅረብ ይሞከራል።
ለሀገር ደህንነት ሲባል ፣ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ምክር ቤቱ ምን አቋም መያዝ አለበት የሚለው በምክክር ነው የሚፈጸመው። እንደስሙ ምክር ቤት በመሆኑ ምክክር ዋነኛው ተግባር ሆኗል። በነፃነት መምከር፣ መወያየትና አቋም መያዝ እየተለመደ መጥቷል። ከዚህ ቀደም ይህን ለማድረግ ምክር ቤቱ አባላት ስላልፈለጉ አልነበረም ያላደረጉት። ይልቁንም ነጻነቱ እና ውይይት እንዲደረግ ስላልተፈለገ ነው ያልነበረው፤ ችግሩ የተፈጠረው የወቅቱ ሥርዓት ቀፍድዶ ስለያዘ ነው።
የምክር ቤት አባላት በነፃነት የመወያየቱ ጉዳይ በውስጣቸው ስለነበረ እድሉን ሲያገኙ ተጠቅመውበታል። ለውጡ በሕዝብ ፍላጎት የመጣ ስለሆነ የምክር ቤቱ አባላትም የሕዝብ ፍላጎትና ጥያቄ ምንድነው የሚለውን እየለዩ በግልጽ መወያየትንና እርምት የሚያስፈልጋቸው የኢኮኖሚም ሆነ የፖለቲካ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ ይሄ ይሄ ትክክል አይደለም በማለት አቋም ይይዛሉ። በአጠቃላይ በምክር ቤቱ ሃሳብን በነጻነት የመግለፅና በተረዱት ልክ ያሻቸውን አቋም የመያዝ እድል በመፈጠሩ አባላቱም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በግልጽ መነጋገር ችለዋል።
ምክር ቤቱም ሲቋቋም ከማህበረሰቡ የወጡ ተወካዮች በበሰለ ሁኔታ ምክንያታዊ በሆነና መረጃ ላይ መሰረት አድርገው መነጋገር እንዲችል ነው። ከዚያ በኋላ ያለው ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ አብላጫ ድምጽ ያላቸው ውሳኔዎችን እየተከተሉ መሄድ ነው የሚያስፈልገው። ባለፉት ሁለት ዓመት ተኩል ጊዜያት መሰረት ለመጣል የሞከርነው ዴሞክራሲያዊ ክርክር እና ግልጽ ውይይት እንዲኖር ማድረግ ነው።
ያልሰራ ተቋም ከመጣ ለምሳሌ አንዳንድ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ሪፖርት ሲያቀርቡ የእናንተ ስራ ሪፖርት ብቻ ነው ወይ ሌላ ስራ የላችሁም ወይ እስከማለት የደረሰ ጥያቄ ጠይቋል። ቀድሞ ይህ አይነት ነገር ቢነሳ እያሳጣችሁን ነው ይባላል፤ ስለዚህ ደግሞ የሚያነሳ የለም። አሁን ግን ተቋማቱን በሚያርም ሁኔታ ጭምር መነጋገር ተጀምሯል። ይህ ልምድ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል፤ ሊበረታታም ይገባል።
እኛ አገር እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን የሚል ጸረ ዴሞክራሲ እና አፈና አይሰራም። ሕዝቡ የሚወስደው አቋም እና የሚፈልገው ነገር ነው መደመጥ ያለበት። ያንን ታሳቢ ያደረገ ሥራ ነው በምክር ቤቱ ለመጀመር የፈለግነው። የፓርላማው ልምድ ወደወጣቶችና ወደሌሎች ማህበራዊ አደረጃጀቶች በማውረድ ምክንያታዊነትን የተከተለ ውይይት ለማድረግ ትልቅ ትምህርት ይሆናል።
አዲስ ዘመን፦ ፓርላማው የአንድ ፓርቲ አባላት ብቻ የሚሳተፉበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ምን አይነት ተጽእኖ አድሮበታል ብለው ያስባሉ፤ በቀጣዩ ፓርላማ ከገዥው ፓርቲ አስተሳሰብ ውጪ የሆነ እይታ ያላቸው ሰዎችን ለማሳተፍ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
አቶ ታገሰ፦ እንደተባለው አሁን ያለው ምክር ቤት የአንድ ፓርቲ አባላት ያሉበት ምክር ቤት ነው። የትኛው ትክክል ነው የትኛው አይደለም፤ የትኛው መሆን አለበት የትኛው መሆን የለበትም በሚሉ ጉዳዮች ላይ ግን ክርክር እንዲኖር ነው ጥረት የተደረገው። በተመሳሳይ መልኩ ሕጎችም ሲወጡ፣ የተቋማት ሪፖርቶች ሲቀርቡም ሆነ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አካሄዱ ያው ነው።
በአንድ ጉዳይ ላይ ከ150 በላይ ሰው ሊቃወም ይችላል። አሊያም 30 እና 40 ሰው ድምጸ ተአቅቦ ያደርጋል። የምክር ቤት አባላት በፓርቲ ደረጃ አንድ ወጥ ሆነውም ሲያበቁ በተቻለ መጠን በጉዳዮች ላይ ለህሊናቸው ተገዥ ሆነው በመምከር የሚጠበቅባቸው ለማድረግ ጥረት አድርገዋል።
የተለያየ ሃሳብ ያላቸው ሰዎች ቀርበው ደግሞ የሕዝብ ድምጽ በተሻለ መንገድ እንዲሰማ ማድረግ ያስፈልጋል የሚለው ጥሩ ነገር ነው። የተለያዩ ድምጾች በምክር ቤቱ ውስጥ መሰማት ይኖርባቸዋል፤ በእርግጥ ይህን የሚወስነው ግን የሚመርጠው ሕዝብ ነው። የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃንም ሆነ የተለያየ የሃሜት ጉዳዮች ብቻ አንስቶ የሚሻኮቱበት ሳይሆን በበቂ ሁኔታ ክርክር አድርጎ ችግሮች የሚፈቱበት መንገድ ያስፈልጋል። ትክክለኛ ክርክር ቢደረግ በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን የሚለቀቅ ውዥንብር እየደረቀ ይሄዳል፤ ሰውም በሃሜትና በጥርጣሬ አይተያይም።
የተለያዩ ድምጾችና አመለካከቶች ሁሉ ለሀገር ግንባታ እስከሆኑ ድረስ እና ሰላማዊ መንገድን እስከተከተሉ ድረስ ያስፈልጋሉ። ተገቢ በሆነ መንገድ ድምጾች ያስፈልጋሉ። ገዥው ፓርቲም ይሁን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ዞሮ ዞሮ ለሀገር ግንባታ እንሰራለን ብለው ነው የተነሱት። ይህ እስከሆነ ድረስ ሁሉም ምክር ቤት ገብተው በልማት ስራዎችም ሆነ፣ በሕገመንግስት ጉዳዮች ላይ የሕዝብ ድምጽ የሚሰማበትን መንገድ በምክክር ማምጣት ይችላሉ።
ሕገመንግስቱ የሚደግፈውም የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ነው። መድብለ ፓርቲ ሥርዓት ደግሞ የተለያየ አመለካከት እና ሃሳብ እንዲካተት ያግዛል። አንዱ የተሳሳተውን አንዱ እያስተካከለ ወይም በተለየ መንገድ ጉዳዩን ለማስተካከል በሚሞክርበት ጊዜ ሕዝቡም የትኛው ነው ትክክል የሆነው? የትኛው ነው ትክክል ያልሆነው? የሚለውንም ለመመዘን እድል ያገኛል።
በአጠቃላይ የተለያዩ ድምጾች የክልል ምክር ቤቶች ላይም ሆነ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ላይ የሚሰሙበት ሁኔታ ቢኖር አስፈላጊ ነው። ዞሮ ዞሮ ግን ይህን መወሰን የሚችለው መራጩ ሕዝብ ነው።
አዲስ ዘመን፦ ፓርላማው አስፈጻሚዎችን የመከታተል እና አንዳንዶችንም ከኃላፊነት የማስነሳት ኃላፊነት አለበት። ከዚህ ቀደም ግን የዋና ኦዲተር ግኝቶችን ተከትሎ ኃላፊዎችን ሲያስነሳ አልተስተዋለም፤ በአግባቡም ቁጥጥር አላደረገም የሚል ትችት ይደርስበታል፤ ይህ ችግር ከምን ጋር ተያይዞ የተፈጠረ ነው?
አቶ ታገሰ፦ እኛ አገር ያለው ትልቁ ችግር ብዬ የማስበው የተቋም ግንባታ ላይ ነው። ተቋም ሲገነባ የሚይዛቸው መሰረታዊ ነገሮች አሉት፤ ከዚህ ውስጥ አንዱ ሥርዓት (ሲስተም) የሚሉት ነው። ሲስተሙ /ሥርዓቱ/ የሚመራበትን አደረጃጀት ይይዛል። ብቁ የሰው ኃይል መኖሩን ያረጋግጣል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ አስረጂ የሚሆን አንድ ጉዳይ ለማንሳት ያክል እኛ ጋር ስለመልካም አስተዳደር ይነሳል። መልካም አስተዳደር እንዲረጋገጥ የሚያደርገው ደግሞ ሰው ነው። ያንን የሚሰራ ብዙ ሰው በእያንዳንዱ ተቋም ውስጥ አለ ወይ? አብቅተናል ወይ? ነው ጥያቄው። እናም ተቋሙን ተጠያቂ የሚሆንበትን ተገቢ ሥርዓት መዘርጋት ይጠይቃል።
ምክር ቤቱ ደግሞ ሕዝብ የመረጠው አካል ቢሆንም፤ ዋና ኦዲተር፣ ሰብዓዊ መብት፤ ፍርድ ቤት አደረጃጀቱን፤ ሰው ሃብቱን አሰራሩን የተመቸ ተቋም ከፈጠርንና ተጠያቂነትን የሚያመጣ አሰራር ከዘረጋን በኋላ ነው ተጠያቂነትን ማስፈን የሚቻለው።
ምክር ቤቱ እኮ አስፈጻሚዎችን አቋቁሞ ተቆጣጠሩልኝ ብሎ ይሰይማል። ስለዚህ ተቋማቱ ገለልተኛ ሆነው እንዲቆጣጠሩ ያስፈልጋል፤ ተቋም ግንባታ በዚህ ረገድ ወሳኝ ነው። ከዚያ በኋላ ነው ተጠያቂነት በየተቋማቱ ሊረጋገጥ ይገባል። በመጀመሪያ ተቋማቱ ሳይጠናከሩ ተጠያቂነት ማረጋገጥም ይከብዳል።
ተቋም ገንብተን ተቋሙ የተቀመጠለትን አሰራር ተከትሎ እንዲፈጽም ካደረግን ተጠያቂነትን ማረጋገጥ እየቀለለ ነው የሚሄደው። በዓለም ላይ ወደእድገት ገብተው የቆሙ ሀገራት ወይም ወደኋላ የተመለሱ ሀገራት ትልቁ ችግር ተቋም አለመገንባታቸው ነው። ሀብትን በተገቢው መንገድ የሚያስተዳድሩበት እና ተጠያቂነትን የሚያረጋግጡበት አሰራር ወሳኝ ነው።
የተለያዩ የመቆጣጠሪያ ሥርዓቶች ደግሞ ስራ ላይ አሉ። በዚህ ረገድ ለአብነት ብሔራዊ መታወቂያ በሀገር ደረጃ ተግባራዊ በማድረግ ሌብነት እና እዚም እዛም እያሉ የሚዋሽላቸው እየፈጠሩ በወንጀል የሚደበቁ ሰዎችን ለመቆጣጠር ይቻላል። ተጠያቂነትን ግልጽ በሆነ መንገድ ለማስፈጸምም ይረዳል።
እኛ አገር ያለው ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳየው ተቋም እራሱ በአግባቡ አለመገንባታችንን ነው። በአግባቡ ሳይገነቡ ደግሞ ተጠያቂ ማድረግ አይኖርብንም። ለምሳሌ ዋና ኦዲተር በየጊዜው የየተቋማቱን ጉድለቶችን ያወጣል።ተቋማቱ ስራን በአግባቡ የሚመሩበት ሁኔታ ሳንፈጥር፣ ተጠያቂነትን በአግባቡ የሚያረጋግጡበት መንገድ ሳይተገበር ወደውሳኔ እና ቅጣት መሸጋገሩ አስፈላጊ አይሆንም።
ኦዲተር በሚያቀርባቸው መረጃዎች በየዓመቱ የተወሰኑ ማስተካከያዎች ለማድረግ ጥረት ይደረጋል። ባለፈው ዓመት በተለይ በአፈጉባኤው በሚመራ ኮሚቴ አማካኝነት ልዩ ክትትል ለማድረግ ተሞክሯል። የተወሰኑ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመግፋት ጥረት አለ፤ ይህ ግን ጅምር ነው። ከዚህ አኳያ ብዙ ይቀረናል፤ ብዙ ስራ ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን፦ የፓርላማ አባላት በተገቢው መንገድ አቋም ይዘው ቁጥጥር እንዳያደርጉ እና ስራ አስፈጻሚው ላይ የተንጠለጠሉ እንዲሆኑ ያደረጋቸው በኢኮኖሚ አለመጠናከራቸው ነው የሚል ሃሳብ የሚያነሱ አሉ፤ ይህ ምን ያክል አሳማኝ ነው?
አቶ ታገሰ፦ አቋም ለመያዝ ዋናው ኢኮኖሚ ብቻ አይደለም፤ ህሊናም ወሳኝ ነው። የምክር ቤት አባላት አቋም ለመውሰድ እንደማይቸገሩ ባለፉት ሁለት ዓመታት ታይቷል። የሃገርን እና የሕዝብን ጥቅም የምናስቀድም ከሆነ ዋጋ የሚያስከፍል ነገር ቢኖርም እንኳን በየትኛውም ቦታ ላይ አቋም መውሰድ አያስቸግርም።
በአንጻሩ የምክር ቤቱ አባላት የኢኮኖሚ እና መሰል ጉዳዮች መሻሻል አለበት የሚለው ትክክል ነው፤ የአገሪቷ አቅም በሚፈቅደው ሁኔታ በሀገር አቀፍ መንገድ ልክ እንደሲቪል ሰርቪሱ ሰራተኛ መሻሻል አለበት የሚለው ያስኬዳል። በሀገር ጉዳይ ግን የተለያዩ ፈተናዎችና ችግሮች የኢኮኖሚ ችግር ቢኖር እንኳን አቋም ለመያዝ መታገል ያስፈልጋል።
ለአብነት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ይሄን ሁሉ በእብሪት ተወጥሮ ሀገር ሊበትን የተነሳውን ኃይል የተጋፈጠው ሀገርና ሕዝብ በማስቀደም እንጂ ደመወዙን አሊያም የተለየ ጥቅም እንደሚያገኝ አስቦ አይደለም። ሀገር ሲኖር ነው እኔም ያለሁት ብሎ አቋም በመያዝ ነው ለሰንደቅ ዓላማው ታማኝ የሆነው። ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን ለመጠበቅ ሁሉነገር ተሟልቶላቸው አይደለም የተዋጉት በባዶ እግራቸው እና ኋላቀር መሳሪያ ይዘው ነው።
ከሁሉም በተሻለ ሁኔታ ደግሞ ሀገር ያለችበትን ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማህበራዊ ሁኔታ የሚረዳው በምክር ቤት ያለው ሰው ነው። ስለዚህ ሀገርን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ ዋጋ ከፍሎም ቢሆን ሀገርን ለማሻገር መስራት ያስፈልጋል። ይህ ተግባር በሁሉም ማህበረሰብ ዘንድ ሊተገበር የሚገባው ጉዳይ ነው። ስለዚህ በተሰማራንበት ሃሳብ ሁሉ ከግል ጥቅም ይልቅ ለሀገራችን ምን ማድረግ ይጠበቅብኛል የሚለውን ነው ማሰብ የሚያስፈልገው።
አዲስ ዘመን፡– ከምክር ቤቱ ሥራዎች መካከል አንዱ የፓርላማ ዲፕሎማሲ ነው። በፓርላማ ዲፕሎማሲ በወቅታዊ እና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ምን ውጤት አስገኛችሁ?
አቶ ታገሰ፦ አብዛኛው የውጭ ግንኙነት እና የዲፕሎማሲ ስራ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ነው የሚከናወነው። እኛም በበኩላችን ደግሞ የምናግዛቸው ጉዳዮች አሉ። ባለፈው አንድ አመት የኮሮና በሽታ ተጽእኖ ቢያሳድርም በቪዲዮ ኮንፈረንስ ጭምር እየተሳተፍን የሀገራችንን አቋም የምንገልጽባቸው ትላልቅ መድረኮች ላይ ተሳትፈናል።
የፓን አፍሪካ ፓርላማ፤ የዓለም ፓርላማ ህብረት እና የተለያዩ መድረኮች ላይ በመሳተፍ የኢትዮጵያን አጀንዳዎች ለዓለም ፓርላማ አባላት ለማስተዋወቅ ጥረት ተደርጓል።
እንደፓርላማም ህዳሴው ግድብ ድረስ ሄደንም ሆነ ችግር ያጋጠመባቸው አካባቢዎች ላይ ያለውን እውነታ ሄደን እናያለን፤ ያን መረጃ ይዘን ደግሞ በተገኘው ዓለም አቀፍ መድረክ ላይ የኢትዮጵያን እውነታ በማሳወቅ ረገድ የዲፕሎማሲ ስራውን እያገዝን ይገኛል። ኢትዮጵያ ምን ጊዜም ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ወዳጅነት መስርታ መጓዝ እንደምትፈልግ ለዓለም የፓርላማ አባላት መረጃ ተሰጥቷል።
ከጎረቤት ሀገራት ፓርላማዎች ጋር መልካም ግንኙነት በመፍጠር የሀገርን አቋም ለማስረዳት በየጊዜው ጥረት ይደረጋል። ከጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ኬንያ ፓርላማዎች ጋር ውይይት ተደርጓል። ሱዳን በሽግግር መንግስት ሂደት ላይ በመሆኗ ፓርላማዋ ተበትኗል በዚህ ምክንያት ከጎረቤት ሀገራት መካከል በፓርላማ ደረጃ ግንኙነት ማድረግ አልተቻለም። ከዚህ ባለፈ ከአፍሪካ እና ሌሎች አህጉራት ጋር ቀና ግንኙነት በመፍጠር በቴክኖሎጂ የታገዙ ውይይቶች እያደረግን ይገኛል።
የትግራይን ሕግ ማስከበር እርምጃ በተመለከተም ለአውሮፓ ህብረት ጭምር በቂ መረጃ እንደሌላቸው በማሳወቅ የተፈፀመውን ጉዳይ ከመነሻው ጀምሮ በዝርዝር አስረድተናል። በክልሉ የነበረውን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መንግስት በትዕግስት መከታተሉን እና በመጨረሻ ሕገመንግሥቱን የተፃረረ እና የሀገር አንድነትን አደጋ ላይ የጣለ ጥቃት ሲፈፀም እርምጃ መወሰዱን በማብራራት እውነታው እንዲያውቁ ተደርጓል። በኢትዮጵያ ላይ የሚወስዱትን አቋም እንዲያስተካክሉ በግልጽ የማስረዳት ስራ ተሰርቷል። በዚህም የኢትዮጵያ አጀንዳዎች በሚገባ የተረዱት የበርካታ ሀገራት ፓርላማ አባላት ቀድሞ የነበራቸው የተሳሳተ አመለካከት እንዲቀየር ምክንያት መሆኑን በግልጽ ታይቷል።
አዲስ ዘመን፦ የተለያዩ ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያራምዱት የተሳሳተ አመለካከት በማየት ብቻ የተጠናከረ ዲፕሎማሲያዊ ስራ በፓርላማውም ሆነ በእያንዳንዱ ዜጋ አያስፈልገንም?
አቶ ታገሰ፦ በእርግጥ አንዳንድ አገሮች ኢትዮጵያን በተመለከተ የሚያራምዱት የተሳሳተ አቋም እና እሳቤ የዜጎችን ስነ ልቦና ካለማወቅ የመነጨ ነው። የሕዝቡን ስሜት ስለማያውቁት በኢትዮጵያ አገራዊ ጉዳዮች ላይ የተሳሳተ አቋም ሲወስዱ ይታያል። ኢትዮጵያዊ በቅኝ ግዛት ያልተያዘ እና ነፃነቱን አስከብሮ የኖረ ሕዝብ በመሆኑ ቁጣው ከባድ ነው። ኢትዮጵያውያን ሀገር እና ሕዝብን በሚመለከቱ ጉዳዮች ላይ በጋራ የመቆም ልምድ አላቸው።
በእራሱ ማንነት የሚኮራ እና የእርሱን ማንነት ፈፅሞ የማይጥል ሕዝብ መሆኑን ያልተረዱ ሃገራት ጫና ለማሳደር ሲጥሩ ይስተዋላል።በዚህ ረገድ ብዙ አገሮችም የኢትዮጵያን ሕዝብ በአግባቡ አያውቁት ብዬ አስባለሁ።
በግድቡ ጉዳይም ሆነ በድንበር ጉዳዮች ላይ ያለውን የኢትዮጵያን አቋም የመንግሥት ብቻ አድርገው የሚያዩ የውጭ አገራት የሕዝቡም ስሜት ጭምር ያለባቸው የሕዝቡ አጀንዳዎች መሆናቸውንም ይረሱታል። ሀገራቱ ያልገባቸው እውነታው ግን ኢትዮጵያውያን ያላቸው እሴት ትልቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በሃሳብ የሚለያዩባቸው ጉዳዮች ቢኖሩ እንኳን በሀገር ጉዳይ ላይ አንድ ሆነው መነሳትን እንደሚያውቁበት ነው።
ኢትዮጵያውያን ከተደማመጡ እና በሀገራዊ ጉዳይ ላይ አንድ ሆነው ሲቆሙ ብዙ ፈተናዎችን ማለፍ እንደሚችሉ በተደጋጋሚ ጊዜ በተግባር አሳይተዋል። በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የነበረውን እብሪተኛ ኃይል መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ከፈጸመ በኋላ ኢትዮጵያውያን በአንድነት ሁኔታውን መልክ ለማስያዝ የተነሱበት መንገድ ለዚህ አመላካች ነው። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጫፍ ጫፍ እንዴት ተቆጥቶ እንደተነሳ በወቅቱ የታየ ሃቅ ነው።
በኢትዮጵያ ያለውን እውነታ ካለመረዳት የተለያዩ የሃሰት መረጃዎች መውጣታቸውን ሲታይ የተሻለ ዲፕሎማሲ ስራ መስራት እንዳለብን ያሳያል። በሌላ በኩል ደግሞ የሞተ እና የማይንቀሳቀስ አገር ብንሆን ኖሮ እንዲህ ከሁሉም አቅጣጫ ትኩረት አይኖርም ብሎ ማሰብ ይገባል።
ኢትዮጵያ ወደፊት የተሻለ ለመጓዝ ተስፋ ያላት ሀገር በመሆኗ ታላላቅ የሚባሉ ሀገራት ሳይቀሩ በውስጥ ጉዳዩዋ እየገቡ ነው ፣ ሀገሪቱ ወደፊት የመሄድ ተስፋ ባይኖራት እና ሀገራትም ከእርሷ ጋር በጋራ መስራት እንችላል የሚል ተስፋ ባይኖራቸው በዓለም ያሉ ኃያላን ሀገራት እና መገናኛ ብዙሃን ጭምር ይህን ያክል አይረባረቡም ነበር። ተፈላጊ በመሆናችን የመነጨ ጥያቄም እንዳለ እና ሙሉ በሙሉ ማስቀረት ሳይሆን ማለዘብ የምንችላቸው ጉዳዮች መኖራቸውን ማሰብ ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡– ቀጣዩ ፓርላማ ወደስራ ሲገባ የትኞቹ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ ቢሰራ የተሻለ ይሆናል ብለው ያስባሉ?
አቶ ታገሰ፦ የአገርን ወቅታዊ እና ሀገራዊ አጀንዳዎች በይበልጥ ለዓለም ሕዝብ ማስተዋወቅ ይገባል። ከዚህ ባለፈ ግን ስለሕግ እና አዋጆች ወጥነት የተጠናከረ ስራ ያስፈልጋል። በአሁኑ ወቅት በምክር ቤቱ የወጡ ሕግና አዋጆችን ኦዲት እያደረግን ነው። የትኞቹ ሕጎች ወጥተው የትኞቹ ተፈጻሚ ሆነዋል የሚለውን እያየን ነው።
ቀጣዩ ፓርላማ ሲመጣ ጥራት ያላቸው ፣ በዋናነት ተፈጻሚ የሚሆኑ ሕጎችን ማውጣት ላይ ቢያተኩር ብዬ እመኛለሁ። በተለይ ሕዝብ የተሳተፈበት ሕግ አስፈላጊ ነው። የሕግ ዝግጅቱ ጥራት ያለው ፣ ተፈጻሚ የሚሆን እና ተደራሽነት ያለው ሊሆን ይገባል።
የክትትል እና ቁጥጥር ሥራው በደንብ ሊያረጋገጥ ይገባል። ምክር ቤቱ ባልተፈፀመ ሥራ እና ፕሮጀክት እንዲሁም በባከነ ሃብት ላይ ተጠያቂ የሚሆኑትን መለየት ያስፈልጋል። እያየ እንዳላየ የሚያልፍ ሳይሆን የሚጠይቅ መሆን አለበት። በዚህ ረገድ ትልቅ ለውጥ ያስፈልጋል።
በሌላ በኩል ምክር ቤቱ ሕዝቡን የወከለ ስለሆነ ሕዝብን መሽተት አለበት። የሕዝብን ስሜትና መንፈስ ማወቅ ብሎም ያንን ማንጸባረቅ ነው የሚያስፈልገው። ጥሩ ክርክርና የሃሳብ ፍጭት የሚካሄድበት ምክር ቤት መሆን ይኖርበታል። መረጃን ማዕከላዊ በማድረግ ምክንያታዊ ሆኖ ውይይት ማካሄድ ተገቢ ነው። እኔ ያልኩት ካልሆነ ብቻ ማለት ስለማያስፈልግ ከእኔ የተሻለ ሃሳብ ሲቀርብ መቀበልን የለመደ ምክር ቤት እንዲሆን እመኛለሁ።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ አመሰግናለሁ፤
አቶ ታገሰ፦ እኔም ከልብ አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 08/2013