ፍሬህይወት አወቀ
ድሮ ድሮ እናቶች በሚሰጡት ምክር ህጻናት ልጆችን ከቤት ውጭ ሲወጡ ሸፈን ማድረግ የተለመደ ነበር፡፡ እንዲያውም ሳይሸፋፈኑ ተይዘው ከተመለከቱ ‹‹ምነው ነጠላ ጣል አታደርጊበትም›› በማለት ሲገስጹ ይደመጣሉ:: ምክንያቱን በግልጽ አይናገሩት እንጂ መልዕክቱ አይን ውስጥ ይገባል፤ ይታመማል፤ የሚል እምነት ስላላቸው መሆኑ እኔም፣ አንተም፣አንቺም፣ እሱም፣ እሷም ሁላችንም ይገባናል፡፡ እናም ለህጻናቱ ጤናና ሰላም ስንል አብዛኞቻችን እናቶቻችንን አምነን ምክራቸውን ተግባራዊ ስናደርግ ኖረናል፡፡
አሁን አሁን ግን የእናቶቻችን እምነት በሳይንስ ያልተረጋገጠ በመሆኑ ይሁን ነጠላ ጠፍቶ፤ አልያም አይን የሚገባ ልጅ ጠፍቶ፤ ወይስ ከህጻናቱ ይበልጥ አይን የሚገቡ ውድ ነገሮች በዝተው ባይታወቅም ዘንድሮ ህጻናቱ ሁሉ ከአለባበሳቸው ጀምሮ አሻንጉሊት መስለው የሚያማምር እምቡጥ ገላቸው ከሽፍንፍን ውጭ ሆኖ መመልከት የተለመደ ሆኗል፡፡ የህጻናቱን ከሽፍንፍን ውጭ መሆን እዚህ ጋር ገታ ላድርግና ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝን ‹‹አይን እንዳይገባብሽ ሸፈን አድርገሽ ያዥው›› የሚለው የእናቶቻችን አባባል ከሰሞኑ እንዴት እየተጠቀምንበት እንደሆነ ላውጋችሁ፡፡
መቼም ሁልጊዜ ኑሮ ተወደደ የኑሮ ውድነቱ ጣራ ነክቷል አይደል የሚባለው፤ የዘንድሮውማ የባሰ ሆኗል ምን ጣራ ብቻ ሰማይ ደርሷል እኮ እንደምትሉ አምናለሁ፡ ፡ ምክንያቱም ከማመን አልፈን እየኖርነውም አይደል፤ እናላችሁ ከሰሞኑ የሚታየው አጠቃላይ የዋጋ ንረትን በዝርዝር ብናነሳው ጊዜ የሚበቃው አይደለምና ወደ ቀደመው ነገሬ ልመለስ፡፡ እንዳልኳችሁ የቀደመው ነገሬ የነዳጅን ያህል ተፈልጎ የሚገኝና ሲገኝም በውድ ዋጋ የምንገዛው የምግብ ዘይት መንግስት በጥብቅ ከሚፈልጋቸው ቀሪ የጁንታ አካላት ባልተናነሰ መልኩ ከአይናችን ርቆ ሰነባብቷል፡፡ ይህ ማህበረሰቡ በጥብቅ የሚፈልገው ዘይት ታድያ ቢገኝም አይን እንዳይገባ ተፈርቷል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡
ሴትየዋ፤ በጥብቅ ከሚፈለገውን እና ከየሱቁ ደጃፍ ለአይን የጠፋውን ባለ አምስት ሊትር ዘይት ገዝታም ይሁን በስጦታ አግኝታ ባይታወቅም ይዛ መንገዷን ታቀናለች፡ ፡ ቦታው ሜክሲኮ አካባቢ ነው፡፡ የበርካታ ሴቶች አይን ከሴትየዋ ዘይት ላይ አርፏል፡፡ እረ ወንዶችም ያስተውሉት ነበር፡፡ ታድያ እንዳልኳችሁ እኔን ጨምሮ አይናቸውን ካሳረፉት ሴቶች መካከል በዕድሜ ጠና ያሉቱ ‹‹የኔ ልጅ ይህን ዘይት የት አገኘሽው እባክሽ›› አሉ ልክ የጠፋ ንብረታቸውን አልያም ለረጅም ጊዜ የተለዩትን ዘመድ ያገኙ ያህል ልባቸው በደስታ እየዘለለ፡፡ ሌላኛዋም ቀጠል አድርጋ ‹‹ከየት ነው የገዛሽው›› አለች ስጋት በተሞላው ድምጽ፤ ላላገኘው ምን አስጠየቀኝ አይነት ስሜት እየታየባት፤ ብርቅ የሆነችው ባለ አምስት ሊትር ዘይት ባለቤት ግን ከመስሪያ ቤት ነው አለች እንደዘበት፡፡
አይናቸውን ያሳረፉት በሙሉ ‹‹ይህ መስሪያ ቤት የቱ ይሆን›› የሚል ጥያቄ የፈጠረባቸው ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለኝም፡፡ ይሁንና ውስጣቸው ለተፈጠረው ጥያቄ ምላሽ ያላሻቸው ጠና ያሉት እናት ‹‹በይ ሸፈን አድርገሽ ያዥው አይን እንዳይገባብሽ›› በማለት መልዕክት አዘል ቅኔ ተናገሩ::
መቼም የቅኔው ሰምና ወርቅ ለሁላችንም በግልጽ የሚታይ ለመሆኑ ምስክር አያሻንም፡፡ ምክንያቱም ለአይን የጠፋ ነገር ሲገኝ አይን ይበዛበታል፡፡ አለፍ ሲልም ከየት አገኘሽው፤ አገኘኸው የሚሉ ጥያቄዎች ይበረክታሉ:: ታድያ ለጠየቀ ሁሉ ምላሽ በመስጠት የሚባክን ጊዜና ጉልበት መኖሩን ለመጠቆም የተሰነዘረ ሰምና ወርቅ አይነት ቅኔ አይመስላችሁም? መልሱን ለናንተው ልተውና እንደው ይህ የኑሮ ውድነት ውሎ ሲያድር ምን ሊያደርገን ይሆን? ብዬ ሌላ ጥያቄ እራሴን ጠየኩ፡፡
የዘይቱማ ነገር እጅግ አሳሳቢና አንገብጋቢ ከመሆኑ የተነሳ ከመስሪያ ቤትም ይሁን በኩዊንስ ሱፐር ማርኬት ደጅ ላይ ዘይቱ ከውጭ ሀገር እስኪገባ የሚወስደውን ያህል ጊዜ ወስደው በመሰለፍ ያገኙትን ባለ አምስት ሊትር ዘይት ሸፈን አድርጎ መያዝ ተገቢ ነው፡፡ የቱንም ያህል ጊዜ ወስደን ብንሰለፍም ለጊዜው ዘይቱ እየተገኘ ያለው በዚሁ ሱፐርማርኬት ነውና ሊመሰገኑ ይገባል፡፡
እርግጥ ነው የመንግስት አካል የሆነው የማዕከላዊ ስታስቲክስም በዘንድሮ ዓመት ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት መታየቱን በሚያወጣቸው መረጃዎች አመላክቷል፡፡ ዳሩ ምን ዋጋ አለው ሕዝብ የሚያውቀውንና የሚታገለውን እውነት መልሰው መላልሰው ቢነግሩት መች መፍትሔ ይሆነውና፡፡ ሕዝቡ የሚፈልገው የዋጋ ግሽበቱን የሚተርክለት ሳይሆን ዋጋውን የሚያረጋጋለት፤ አቅርቦቱን የሚያሰፋለትና በቀላሉ ተንቀሳቅሶ መሸመት የሚችልበት መንገድ እንዲመቻችለት ነው፡፡
አሁን እየታየ ያለው የዋጋ ግሽበት ፍጥነት እና መጠን ከዚህ ቀደም ታይቶ እንደማይታወቅ በተደጋጋሚ ተገልጿል። ታድያ ይህ በፍጥነት እየጨመረ ያለው የዋጋ ግሽበት ህብረተሰቡን ምን ያህል እየተፈታተነውና ሊገላገለው ያልቻለው ምጥ እንደሆነበት መገመት አያቅትም፡፡ ለዚህም ነው የኑሮ ውድነቱ በተለይም በአሁን ወቅት ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ የታየበት የምግብ ዘይት ከገበያው መሰወሩ ዋነኛ የህብረተሰቡም ሆነ የሚዲያ አጀንዳ ሆኗል፡፡ ከአጀንዳነቱ ሲያልፍም እንዳልኳችሁ አይን እንዳይገባ ተፈርቷል።
ይሁንና በተደጋጋሚ የሚዲያ አጀንዳ የሆነው አጠቃላይ የኑሮ ውድነት መፍትሔው ምን ይሆን እያለ ዕለት ዕለት ለሚጠይቀው ሕዝብ የመንግሥት መልስ ሁልጊዜም ተመሳሳይ ነው፡፡ ‹‹የኑሮ ውድነቱ ለማረጋጋት እየሰራሁ ነው››፤ ‹‹ያለምክንያት ዋጋ በጨመሩ ድርጅቶች ላይ እርምጃ እየወሰድኩ ነው››፤ ‹‹ምርቶችን ከውጭ ለማስገባት እየተሞከረ ነው›› ወዘተ… የሚሉ የተለመዱ ምላሾች ቢሰጡም ዘላቂ መፍትሔ ሲሆኑ ግን አይታዩም፡፡
እርግጥ ነው መንግስት የሚሰጠው ምላሽ ዘላቂ መፍትሔ አይሁን እንጂ፤ በተለይም የኮሮና ቫይረስ ወደ ሀገሪቱ መግባቱን ተከትሎ ህብረተሰቡ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫናው እንዳይበረታበት የወሰዳቸው የመረዳዳት እርምጃዎች የሚበረታቱ በመሆናቸው የኑሮ ውድነቱ አሁን ካለው በላይ እንዳይባባስ ሆኗል፡፡ ይህንንም መንግስት ነግሮናል፡፡ ባይነግረንም ብዙዎቻችን ተረድተነዋል፡፡
የሆነ ሆነና ማህበረሰቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች በሙሉ የሚያነጣጥሩት ወደ መንግስት በመሆኑ ኃላፊነት እንዳለበት ዕሙን ነው፡፡ ለዚህም የአጭር ጊዜ ሳይሆን የረጅም ጊዜ መፍትሔ ለመስጠት ስትራቴጂ ነድፎ መስራት እንዳለበት ይታመናል፡፡ ከዚህም በላይ ለኑሮ ውድነት ቅድሚያ ሰጥቶ በመስራት ህብረተሰቡ ዕለት ተዕለት በልቶ ለማደር የሚፈተነውን ፈተና ማቃለል ይኖርበታል፡፡ ይህ ካልሆነ ግን ቀውሱ አሁን ከምንለው በላይ በርትቶ ያጠፋን ይሆናል፡፡
በርግጥ ሀገሪቱ አሁን ባለችበት ሁኔታ የተረጋጋ ሰላም የላትም፡፡ ሰላም ሲደፈርስ ደግሞ ሁሉም ነገር አብሮ ይደፈርሳል፡፡ በሰላም እጦት በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በርካቶች ተፈናቅለዋል፡፡ ሕግ የማስከበር ስራው በራሱ የሚጠይቀው ከፍተኛ ወጪ ለኑሮ ውድነቱ ድርሻ ይኖረዋል:: በተጨማሪም የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እያስከተለ ያለው ጫና የኑሮ ውድነቱን አባብሶታል፡፡ እነዚህና መሰል ጉዳዮች እየተባባሰ ለመጣውና ህብረተሰቡን እያማረረ ላለው የኑሮ ውድነት አይነተኛ ምክንያት ሆነዋል፡፡
‹‹ግርግር ለሌባ ያመቻል›› እንደሚባለው አነዚህን ምክንያቶች አስታኮ የራሱን ጥቅም ለማሳደድ የሚሮጥና በግርግሩ ለመጠቀም እንቅልፍ አጥቶ በነደፈው ስትራቴጂ ሕዝቡ ላይ የኑሮ ጫና የሚፈጥር አለ፡፡ ምንም ይሁኑ ምን አሁን መንግሥት አንገቱን ወደ ሕዝቡ ዘንበል በማድረግ ከሁሉ አስቀድሞ የኑሮ ውድነቱን ማረጋጋት የሚያስችል ስራ መሥራት ይኖርበታል፡፡ በተለይም ገበያውን በማረጋጋት ነጋዴው የሸቀጦችን ዋጋ እንደፈለገ እንዳይሰቅለውና እንዳያወርደው ዘርፉን በሥርዓት መምራትና መቆጣጠር ያስፈልጋል ፡፡ በተለይም የአዲስ አበባ አስተዳደር የሸማቹን መብት ማህበር መመስረቱ እንደልባቸው ዋጋ የሚቆልሉ ነጋዴዎችን አደብ ለማስገዛት ይጠቅም ይሆናል፡፡
ከሁሉም የሚቀድመው ነገር ግን ሰላም ነውና ሰላምና የሕግ የበላይነትን በማስከበር ዜጎች የማይፈናቀሉባት፣ የማይሞቱባትና በመረጡት አካባቢ ያለስጋት መኖር የሚችሉባትን ሀገር መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ይህም መንግሥት ብቻውን የሚሰራው ሥራ ሳይሆን፤ እያንዳንዱ ዜጋ ለራሱ የሰላም አምባሳደር በመሆን ለሰላም ዘብ መቆም ይገባዋል፡፡ ሀገር ሰላም ከሆነ መንግሥት የሚጠመድበት ትልቁ የቤት ሥራ የሚቃለልለት በመሆኑ ለዜጎች ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥበትን ሰፊ ጊዜና ዕድል ያገኛል፡፡ ስለዚህ በሰላም ዙሪያ ዜጎች ትልቅ ኃላፊነት ያለብን በመሆኑ
አዲስ ዘመን መጋቢት 08/2013