ራስወርቅ ሙሉጌታ
የዘንድሮ ትምህርት ዘመን ተማሪዎች በሚቀጥሉት ስድስት ወራት የዓመቱን ሙሉ ትምህርት ተከታትለው ማጠናቀቅ ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ ዛሬም ድረስ መድኃኒት ያልተገኘለት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የፈጠረው ተጽእኖ ተማሪዎችን በፈረቃ እንዲማሩ ያደረጋቸው ሲሆን በተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጠሩ የብዙ ንጹሀንን ህይወት የቀጠፉት ግጭቶችና መጪው ምርጫ ደግሞ በመማር ማስተማሩ ሂደት የየራሳቸውን ተጽእኖ የሚያሳድሩና በተማሪዎች እንቅስቃሴም ላይ የስነ ልቦና ጫና የሚፈጥሩ ናቸው። ለመሆኑ እነዚህ ድርብ ድርብርብ አጋጣሚዎች በተማሪዎች ላይ እና በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ ምን ጉዳት ሊፈጥሩ ይችላሉ በምን መልኩስ እነዚህን አስቸጋሪ ሁኔታዎች መቆጣጠር ይቻላል ስንል በኢምፓክት ኢትዮጵያ የሳይኮሎጂካል አገልግሎቶችና የማኅበረሰብ ጤና ማማከር ማኅበር የሥነልቦና አማካሪና የማኅበረሰብ ጤና የሆኑትን ወይዘሮ ሙሉ መኮንን አነጋግረን የሚከተለውን ይዘን ቀርበናል።
እንደ ባለሙያዋ ማብራሪያ በመደበኛው የትምህርት ዘመን በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቁ የነበሩ ትምህርቶችን በስድስት ወር ለመጨረስ መሞከር በተማሪውም ሆነ በአጠቃላይ በመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ የሚፈጥረው የራሱ የሆነ ተጽእኖ አለው። በመጀመሪያ በተማሪዎቹ ረገድ ከላይ የተቀመጡት ችግሮች እንኳን በተደራራቢነት ተከስተው በተናጠልም ቢሆኑ የሚያሳድሩት የየራሳቸው ጠንካራ ተጽእኖዎች አሉ ። በመጀመሪያ ደረጃ ድሮ ሊያስመዘግቡት የሚችሉትን ውጤት እንደማያስመዘግቡ ድሮ ሊያገኙ የሚችሉትን ያህል አውቀት ሊያገኙ እንደማይችሉ ስለሚገነዘቡ በተማሪዎች ላይ የሚፈጥሩት የድካም፤ የመሰላቸት፤ ያለመረጋጋትና የመጨናነቅ ስሜቶች ሁሉንም ተማሪዎች ባይሆንም የስነ ልቦና መቃወስ የሚፈጠርባቸው ይኖራሉ።
በተለይም እስካሁን በነበረው የትምህርት ሂደታቸው ዝቅተኛ ውጤት የነበራቸውና በትምህርት ሂደት ለመማርም ለማጥናትና ለማንበብም ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስድባቸው ደግሞ ለችግሩ የበለጠ ተጋላጭ የመሆን እድላቸው ሰፊ ነው። በሁለተኛ ደረጃ እንደ መማር ማስተማር ሂደት ሲታይም በጥልቀት ትምህርቱን ከማካሄድ ይልቅ በጊዜ እጥረቱ ምክንያት ብቻ ከላይ ከላይ ወይንም ዋና ዋናውን ብቻ በመነካካት ለማለፍ የሚያስገድዱ ሁኔታዎች መፈጠራቸው አይቀርም። በተጨማሪ በየአካባቢው እየተፈጠሩ ያሉት ግጭቶች እንዲሁም እስካሁን በሀገሪቱ የነበረውን ልምድ በመውሰድ በምርጫ ወቅት ይፈጠራሉ ተብለው የሚሰጉ ነገሮች ሁሉ ለተማሪዎች ጭንቀት አማጭ ናቸው። እነዚህ ችግሮች ተማሪዎች ነገን የተሻለ ሀይወት ለመኖር የሚሰንቁት ተስፋ ላይም የሚያሳድሩት የየራሳቸው ተጽእኖዎች ይኖራቸዋል። ከነዚህም ውስጥ ድባቴ አንዱ ነው በተጨማሪ ትምህርት ለማቋረጥ አልያም ሌሎች ተገቢ ያልሆኑና የወደፊት ህወታቸውን የሚያቃውሱ ውሳኔዎችንም ለመወሰን ሊገደዱ ይችላሉ።
በሌላ በኩል ምንም እንኳን የችግሩ መነሾ ለሁሉም አንድ አይነት ቢሆንም ከሚያስከትለው ተጽእኖና ከሚያመጣው ጉዳት አንጻር ግን የተለያየ ነው። ለምሳሌ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ ያሉ ተማሪዎች የሚማሩት በትውልድ አካባቢያቸው አልያም ቤተሰቦቻቸው ባሉበት አካባቢ ከሆነ ሊፈጠርባቸው የሚችለው ጫና ዝቅተኛ ሲሆን በአንጻሩ ከትውልድ ቀዪአቸው ርቀው በሚማሩት ላይ የሚፈጠረው ተጽእኖ የበረታ ይሆናል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ችግሩ በሁሉም ላይ የተከሰተ ሀገራዊ ከማድረግ ይልቅ ከራሳቸው ግላዊ ችግር ጋር የሚያይዙት ደግሞ ለበለጠ ጭንቀትና ተስፋ መቁረጥ የሚዳረጉበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል።
የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚያስቀምጠው አንድ ሰው ሙሉ ጤነኛ ነው ሊባል የሚችለው የአካል ጤንነቱ ፤ የስነ ልቦና ጤንነቱ ፤ የአእምሮ ጤንነቱ እንዲሁም የማህበራዊ ተጋብሮቱና መንፈሳዊ ሁኔታው የተስተካከለ ሲሆን ነው። ከእነዚህ መካከል አሁን ባለው የሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ ግን በማህበራዊ ተጋብሮት ረገድ ከዘርና ከጎሳ ጋር በተያያዘ በዩኒቨርሲቲ ያሉ ተማሪዎች ግንኙነት የላላና የራሱ ችግርና ስጋት ያለበት ነው። ከደህንነት ጋር በተያያዘም በስነ ልቦናቸው ያለመረጋጋት ይፈጠርባቸዋል፤ በየወቅቱ የሚሰሙት አሰቃቂ ዜናዎችም መንፈሳዊ መረጋጋታቸውን የሚያደፈርሱ ናቸው። ከአካላዊ ጤንነትም ጋር በተያያዘ የኮሮና ቫይረስ ራሱን የቻለ ስጋት ነው።
በመሆኑም መንግሥት እነዚህ ሁሉ ጫናዎች በአንድ ጊዜ ተማሪዎች ላይ መውደቃቸው ሊያስከትል የሚችለውን ተጽእኖ በመረዳትና ባለሙያዎችን በማማከር ሌሎች አማራጭ መንገዶችን ማማተር ይጠበቅበታል። ተማሪዎችም ምንም አንኳን ችግሩ ለሁሉም በተመሳሳይ መልኩ የሚገጥማቸው ቢሆንም ምላሽ የሚሰጡት በየግል ራሳቸው ያሉበትን ሁኔታና የአካባቢያቸውን ነባራዊ ሀኔታ ከግምት በማስገባት መሆኑን መገንዘብ አለባቸው። በመሆኑም ተማሪዎች በቅድሚያ ራሳቸውን ከተፈጠረው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ለማስማማት ለማላመድ መዘጋጀትም መንቀሳቀስም ይጠበቅባቸዋል። ከዚህ ባለፈም የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎችም ሆኑ የሚወስዷቸው ውሳኔዎች ነገን ከግምት ያስገቡና ቀጣይ ህይወታቸው ላይ መጥፎ ተጽእኖ ሊፈጥሩ በማይችል መልኩ መሆን አለበት።
አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በጣም ዝቅተኛ ውጤት ካስመዘገቡ ወይንም በዩኒቨርሲቲ ሊያቆያቸው የማይችል ሁኔታ ከተፈጠረ በግላቸው አልያም ከቤተሰብና ከመምህራን እንዲሁም ከባለሙያዎች ጋር በመምከር አማራጭ መንገዶችን መፈለግ ይጠበቅባቸዋል። ቤተሰቦችም በየወቅቱ ልጆቻቸውን በተለያየ መንገድ በማግኘት ችግሮቻቸውን መከታተል በጣም አስጊ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ ብለው ከሰጉ ደግሞ ቅድሚያ ለደህንነታቸውና ለጤናቸው በመስጠት ከተጋረጠባቸው ነገር ማሸሽ ይጠበቅባቸዋል ሲሉ ባለሙያዋ ምክራቸውንም አስተላልፈዋል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 7/2013