በላንዱዘር አሥራት ጋዜጠኛና ከፍተኛ የኮሚዩኒኬሽን ባለሙያ
ግራዝማች ዮሴፍ ንጉሤ የውጫሌ ውልን ወደ አማርኛ የተረጎሙና በውሉ ላይ በአማርኛና በጣሊያንኛ በተጻፈው መካከል ያለውን መሰረታዊ ልዩነት ያጋለጡና ለንጉሰ ነገስቱ በጥልቀት ያስረዱ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ሊቅ ነበሩ፡፡
ግራዝማች ዮሴፍ ንጉሤ ውልደታቸውና እድገታቸው ትግራይ የነበረ ሲሆን በኤርትራም የወቅቱን የቀለም ትምህርት ተከታትለዋል፡፡
ኢትዮጵያ አንቀጽ 17 የውጫሌው ስምምነት ላይ፤ በጣሊያንኛ ቋንቋ የተጠቀሰውን የኢትዮጵያ ንጉስ ከውጭ አገራት ጋር የሚያደርጋቸውን ማናቸውንም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶችን ሁሉ፤ በጣሊያን በኩል ማድረግ ይኖርበታል የሚለውን ኢትዮጵያ ሉአላዊነቴን አሳልፌ አልሰጥም በሚል አልተቀበለችውም፡፡
ኢትዮጵያ ምስራቅ አፍሪቃን የመቀራመት ፍላጎታቸው ላይ ውሃ በሚቸልስ አኳኋን ስምምነቱን አሻፈረኝ በማለቷ፤ ጣሊያን የቅኝ ግዛት፤የመስፋፋትና የበርሊን ኮንፈረስ አፍሪካን የመቀራመት አጠቃላይ ምኞት በወታደራዊ መንገድ ብቻ ለማሳካት ወሰነች፡፡
በዚህም መነሻ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የሚገኙ የግዛት አስተዳዳሪዎችን በልዩ ልዩ ገፊ አኳኋኖች በመተንኮስ ከባአታ ሃጎስ ጋር ኤርትራ ውስጥ በፈረንጆች ሕዳር 1894 በመግጠም እየገፋች ወደ ትግራይ አድዋ የመዝልቅ ሙከራ አድርጋለች፡፡
የጣሊያን ወታደር ከጊዜ ወደ ጊዜ በማን አለብኝነት ድንበር እየጣሰ ወደ ውስጥ በመዝለቁ ምክንያት በፈረንጆች ህዳር (7, 1895) ራስ መንገሻ ዮሐንስ፤ራስ ዎሌ ብጡልና ራስ መኮንን ወ/ሚካኤል በጋራ ጥምረት ፈጥረው ጣሊያንን በመውጋት አምባላጌ ተራራ ላይ በተደረገው አውደ ውጊያ ጣሊያንን አይቀጡ ቅጣት ቀጥተው ድል አድርገዋል ፡፡
በዚህም ሳቢያ ከፍተኛ የሞራልና ሰብዓዊ ኪሳራ የደረሰበት የጣሊያን ወታደር ትንሽ ፋታ ያደርግና ኢትዮጵያን በአራት አቅጣጫ ለመውጋት ይዘጋጃል፡-
ዘመናዊ የጦር መሳሪያ እስከ አፍንጫው የታጠቀው የጣሊያን ሰራዊት በወቅቱ የጦር አዛዥ በጀነራል ባራቲዮሪ እየተመራ ኢትዮጵያውያንን ቅኝ ተገዥ አድርጎ ለማንበርከክ ኢትዮጵያን ጠንቅቆ ካለማወቅ በመነጨ ድፍረት ቆርጦ ይነሳል፤ ዓላማውንም ለማሳካት ከሃያ ሺ በላይ ሰራዊቱን በአራት ብርጌድ አሰልፎ ተራራና ሸለቆውን እያቋረጠ ገስግሶ አድዋ ከተማ ከተተ፡፡
የጣሊያንን የጦር ዝግጅት ሲከታተሉ የቆዩት የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ አጼ ምኒልክም ልዩ ልዩ እርምጃዎችን መወሰድ ይጀምራሉ፡-
ንጉሰ ነገስ ምኒልክም ፈርጀ ብዙ ዲፕሎማሲያዊ ሙከራዎች መክሸፋቸውን ካረጋገጡ በኋላ፤ ታላቁ የአድዋ ጦርነት አይቀሬ መሆኑን ተገንዝበው በመላ አገሪቱ የጦር ክተት አዋጅ ወረኢሉ እንገናኝ ብለው ያስነግራሉ፡፡
አገር በባዕድ ተወራለች የሚለውን የጦር ክተት አዋጅ የሰሙት ኢትዮጵያውያን በአራቱም አቅጣጫ ተመው ወረኢሉ ከተሙ፤ በወቅቱ በተሰናዳው መረጃ መሰረት 120,000 ገደማ የሚሆኑ ጦረኞች ፤ወንዶች ፤ሴቶች፤ህጻናት፤አርሶ አደሮች፤አርብቶ አደሮች እና አካል ጉዳተኞች በነቂስ ካለ አንዳች ልዩነት ረጅሙን መንገድ በጽናት ተጉዘው እንደ አንድ ልብ መካሪ፤ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ጠላትን ለመመከትና ለመደምሰስ በቆራጥነት ተነስተው ለአድዋ ዘመቻ ወረኢሉ ተገናኙ፡፡
ንጉሰ ነገስት ዳግማዊ አጼ ምኒልክም ከስፍራው ገስግሶ የደረሰውን የኢትዮጵያ የጦር ኃይል በሚከተሉት የጦር መሪዎች ስር ከፋፍለው ለታላቁ የአድዋ ጦርነት አሰናዱ፤ ንግስት ጣይቱ ብጡል፤ራስ ዎሌ ብጡል፤ራስ መንገሻ አትቅም፤ራስ መንገሻ ዮሐንስ፤ራስ አሉላ እንግዳ አባ ነጋ፤ራስ ሚካኤል፤ራስ መኮንን ወ/ሚካኤል፤ፍታውራሪ ገበየው እና ንጉስ ተክለ ሃይማኖት ተሰማ ስር አድርገው በመደልደል በተጨማሪም የጦር ካምፕ አካባቢ ሆነው በቅርበት የጦር መሳሪያ ቶሎ ቶሎ ለሰራዊቱ የሚያቀብሉ ሰዎችን አድርገው መደቡ፡፡
ንጉሱም ባሰናዱት የጦር ኃይልና የጦር መሪዎች በመታገዝ የማይቀረውን የአድዋ አውደ ወጊያን በፈረጆች 1896(1888) የጣሊያንን ወራሪ ኃይልን ገጥመው በሁለት ቀናት ጦርነት ብቻ በጠቃላይ አውሮፓውያን ቅኝ ገዥዎችን አንገት ባስደፋ መልኩ በዓለም ታሪክ የመጀመሪያ የሆነውን አንጸባራቂ የመላ ጥቁር ሕዝቦች ድልን በጣሊያን ላይ ተጎናጸፉ፡፡
በውጊያው ወቅት ከቅድመ አያቶቻችን መካከል አንዳቸው ጎድለው ቢሆን ኖሮ ዛሬ አድዋም፣ የአድዋ ልጅነትም ከእናካቴው ባልኖሩ ነበር። የሀገርን ብሔራዊ ጥሪ እኩል ሰምተው በጋራ ባይዘምቱና አድዋ ላይ የድል ሰንደቅ ባይተክሉ ኖሮ፤ ዛሬ የምናከብረው የድል ቀን መሆኑ ቀርቶ እንደሌሎች አፍሪካውያን የነጻነት ቀን በሆነ ነበር። አድዋ ከእኛ የድል ሰንደቅነት አልፎ ተርፎ ለብዙ የነጻነት ትግሎች እንደ መነሻ ሆኖ ያገለገለም የአጠቃላይ ጥቁር ሕዝቦች የነጻነት ምልክት ለኢትዮጵያውያን ደግሞ በአንድነት ምንም የማይቻል ነገር እንደሌለ ያሳየ ድል ነው፡፡
ኢትዮጵያ በጣሊያን ላይ በተጎናጸፈችው አንጸባራቂ ድል ምክንያት በዓለም ላይ የሚከተሉት የፖለቲካ ለውጦች ተከናውነዋል፤ ለዘመናት በዓለም ፖለቲካ ላይ የተጫነው የነጮች የበላይነት ዳግም ላያንሰራራ ተንኮታኮተ፤በመላ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ተሞክሮን በመውሰድ በይቻላል ስሜት የጥቁሮች የነጻነት ትግል ተቀጣጠለ፤በእስያ፤ በአውሮፓ እና በአፍሪቃ የአንገዛም ባይነት ሕዝባዊ እምቢተኝነቱ የትጥቅ ትግልን አካቶ በርትቶ ቀጠለ፡፡
እልፍ የሕይወት መስዋዕትነት ተከፍሎ ከ1960 በኋላ አብዛኞቹ የአፍሪቃ አገራት ከነጭ ቅኝ ግዛት ነጻ መውጣት ችለዋል ፡፡
ዓለም ላይ የተከሰተው የፖለቲካ ለውጥ በጣሊያንም ቀጥሎ ምኒልክ ለዘላለም ይኑር የሚሉ ሰልፈኞች አደባባዮችን ዘግተው አንለቅም በማለታቸው ምክንያት የሚከተሉት ለውጦች ጣሊያን ውስጥም ተደረጉ፤ጠቅላይ ሚኒስትሩና አጠቃላይ የአድዋን ጦርነት የመሩ ጀነራሎች ማእረጋቸው ተገርስሶ ከስራቸው ተባረሩ ፤ የጣሊያን ጋዜጦችም በወቅቱ በፊት ለፊት ገጻቸው የምኒልክንና የጣይቱን ፎቶግራፍ ተጠቅመው ቪቫ ምኒልክ ቪቫ ጣይቱ በሚል በዓለም አደባባይ የኢትዮጵያን ድል አስተጋቡ፡፡
አድዋ የእርቅንና የይቅርታን ኃይል ያሳየም ጭምር ነው። በአካባቢ ግጭቶች የተቀያየሙ የግዛት መሪዎች፤ በንጉሱም ላይ ያኮረፉ የወላይታና የአንዳንድ አካባቢ ገዥዎችም፤ ቂምና ቁርሾን በእርቅ ሳይውል ሳያድር ሽረው ለአንድ አገራዊ ዓላማ በአንድነት እንዲቆሙ ያስቻለ የትውልዱ ዘመን ተሻጋሪ ታላቅ በድል የተጠናቀቀ ደማቅ የታሪክ ምዕራፍም ነው፡፡
ጣልያኖችም እነዚህን ቅያሜዎች አስፍተው ኢትዮጵያውያንን ማንበርከክ እንደሚችሉ የተሳሳተ ስሌት አስልተው ነበር ወደ ኃይል እርምጃ የገቡት፡-
ሆኖም ስሌታቸው የተሳሳተ መሆኑን የተረዱት ለሰላምና እርቅ ቅድሚያ ሰጥተው በትዕግስት ጉዳዩን ሲመለከቱ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ተቆጥተው ልክ እንደ አንደ ሰው መቆማቸውን ሲመለከቱ ነበር ከእንቅልፋቸው በትክክል መንቃታቸውን ያረጋገጡት ።
ኢትዮጵያውያን ቅሬታቸውን በእርቅ፣ ቅያሜያቸውን በይቅርታ በፍጥነት ሽረውት፤ ‹ሁሉም ከሀገር አይበልጥም› በሚለው የኢትዮጵያውያን የቆየ ሀገር በቀል ቢህል መሠረት፤ ከመንግሥት ጋር ልዩ ልዩ ግጭት ውስጥ የገቡ ሁሉ ሳይቀሩ ለሀገራቸው ለመሞት ቆርጠው ተነሱ ።
ዘወትር አገር ከሚያልፍ መንግሥታዊ ስርዓት እንደምትበልጥ አስቀድመው ጠንቅቀው ከማንም በላይ የሚያውቁት ኢትዮጵያውያን፤ሀገር ሁል ጊዜም የምትድነው በእርቅና በይቅርታ መሆኑን አምነው ልዩነቶቻቸውን አጥብበው በአንድነት መቆም ቻሉ። በተለያዩ አካባቢዎች አኩርፈው የሸፈቱም ሳይቀሩ እርቅና ሰላም እያወረዱ ከአድዋው ዘማች ጋር አብረው ዘመቱ።
አድዋ የኢትዮጵያውያን የአመራር ጥበብ የታየበት ድልም ነው። ዳግማዊ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ በአራት መንገድ ሠራዊቱን አደራጅተው፤ ጠላት የውሃና የስንቅ አቅርቦት እንዳያገኝ መስመሩን በጀግንነት አቋርጠውበት፤ ዕውን ያደረጉት ድል እንጂ በአንድ ጀንበር የመጣ አልነበረም።
በተጨማሪም በሁለቱ በብስለትና በዕውቀት የታገዘ አመራርና ማስተባበር ሀገር ወዳድ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች በተለያዩ ዘዴዎች መሣሪያ በማሰባሰብ፤ ስንቅ በማዘጋጀት፤ ጥቂት ጊዜ መግዛት የሚያስችል የዲፕሎማሲና የቅድመ መረጃ ሥራዎችን በማከናወን እና ሠራዊቱን በአንድነት አደራጅቶ በማዝመት የተቀዳጁት የመላ የጥቁር ሕዝቦች ድልም ጭምር ነው።
የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ታጋይ የነበረው አሜሪካዊው ማርክስ ጋርቬይ ስለ ታላቁ የአድዋ ድል የሚከተለውን ብለው ነበር ‹‹የአድዋ ድል የአፍሪካን ጥንታዊ ክብርና የወደፊት ተስፋ ከጥቁር ህዝቦች ጋር ያገናኘ የመላው የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ተምሳሌት ማሳያ ድልድይ ነው››::
ድሉ ለጥቁር ህዝብ የነጻነት ታጋዮች ለእነ ማርክስ ጋርቬይ፤ ጁሊየስ ኔሬሬ፤ ኩዋሜ ንኩርማህ፤ስቲቭ ቢኮ፤ ሳንካራ እና ለሌሎች የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ትግሎች፤ ለደቡብ አፍሪቃ የጸረ አፓርታይድም ሆነ ለሌሎች ለጸረ ቅኝ ግዛት ትግሎች ጉልበት መሆን መቻሉን የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ታቦ ኢምቤኪ ‹‹የአድዋን ጦርነት እኛ ሰለባ አይደለንም ነገር ግን እኛ አሸናፊዎች ነን›› በሚል ገልጸውትም ነበር፡፡
በአንድ ወቅት አንዲት የታሪክ ተመራማሪ ሚዲያ ላይ በእንግድነት ቀርበው ፤የአድዋ የድል በዓል አከባበርን አስመልክቶ በሰጡት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፤ የአድዋ ድል የመላ ጥቁር ህዝቦች ድልና ኩራት ከመሆኑ አንጻር ላለፉት ዓመታት አድዋ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የሚገባውን ትኩረት እንዳላገኘ እንዲያውም አብዛኞቹ አፍሪካውያንና ጥቁር ህዝቦች እንኳን የአድዋን ድል በደንብ እንደማያውቁ የሚያሳዩ ግኝቶች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡
ይሄንን እውነታ ለመለወጥና ኢትዮጵያን እና አዲስ አበባን በአዲስ መንገድ ለማስተዋወቅ ተገቢ እና ደረጃውን የጠበቀ አካባበር እንደሚያስፈልግ አክለው መናገራቸውን አስታውሳለሁ፡፡
በዚህም ኢትዮጵያ የመላ አፍሪካውያንና በዓለም የተገፉ ህዝቦች የነጻነት ተምሳሌት ሆና እንድትቆጠር ጥንታውያን የሁላችንም ቅድም አያቶች አሻራቸውን በደምና አጥንታቸው አኑረዋል፡፡
የዓድዋ ድል የዛሬውም ትውልድ ለአገር ቅድሚያ ሰጥቶ ተፈጥሮአዊ ልዩነቶችን እንደ አምላክ ፀጋ ተቀብሎና በፖለቲካ ልዩነቶችም ቢሆን መቻቻልን መርሕ አድርጎ፤ አካታች ለሆኑ የፖለቲካ ሀሳቦች ቅድሚያ ሰጥቶ በአንድነት ከተነሳ ከመንገዱ የሚያስቆመው ምንም አይነት ምድራዊ ኃይል እንደማይኖር አብነት የሆነ ታሪካዊ የአንድነት ድርና ማግ ነው ፡፡
የነጌ ማንነት በዛሬ ላይ መሰረት ተጥሎ እንደሚሰራ የተገነዘበ ትውልድ ስለመፈጠሩም ምስክር የማይሻ አቢይ ማሳያ ነው፡፡ያንን ዘመን አይሽሬ ድል በጥልቀት የተረዳ ትውልድ ዛሬም እጅ ለእጅ ከተያያዘ ተመሳሳይ ዘመን ተሻጋሪ ድል እያስመዘገበ መሄድ እንደሚችል ዳግም ምስክር አይሻም ፡፡
ለዚህኛውም ትውልድ የድል ጅማሬ ማሳያ፤ በሀገራችን እየተገነቡ ከሚገኙት ግዙፍ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ነው፡፡ በአድዋ ዘመቻ ላይ ያሳየነውን የአብሮነታችንን ጥብቀት፤ የአንድነታችንን ውህደት እና ዘመን ተሻጋሪ የኢትዮጵያዊነት ቅርጽና ቀለም ለሚጠራጠሩም የትላንቱ አንድነታችን በብዙሀነታችን የደመቀ ቀለም መሆኑን በእያንዳንዱ ተግባራችን ወደፊትም ለጠላትም ለወዳጅም እያሳየን እንዘልቃለን፡፡
የአባይን የዘመናት ቋጠሮ መፍታት የአንድን አካባቢ ወንዝ ጠልፎ የጓሮ አትክልት እንደማልማት ቀላል አይደለም፡፡አይችሉምን የቻልንበት፤ ትላንት በአንድነታችን ጸንተን በአድዋ ያስገኘነውን ድል፤ በድጋሚ ያስመሰከርንበት፤ የትላንት ታላቅነታችን ማሳያ የውሀ ሐውልታችን ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ በላይ፤ በአገር ውስጥና በውጭ የሚኖሩ ፤በሚቻላቸው ሁሉ በአንድነት ቆመው ለኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ብሄራዊ ጥቅም ዲፕሎማሲያዊ ትግል በጋራ የሚያደርጉበትና በብሔራዊ ጥቅማችን ላይ የሚቃጡ ዓለም አቀፍም ሆነ አህጉራዊ ጫናዎችን የሚመክቱበት ትክክለኛ ጊዜ አሁን ነው፡፡
አገር ከሚያልፍ መንግሥታዊ ስርዓትና በየጊዜው ከሚለዋወጥ የፖለቲካ አስተሳሰብ የምትልቅ ስለሆነች ፤አንዳችን የሌላኛችንን ተፈጥሯዊም ይሁን ቀለም ውላጅ ልዩነቶች እክብረን በማስተናገድ፤ልክ እንደ አባቶቻችን ሁሉ እጅ ለእጅ ተያይዘን ሆ ብለን ለጋራ አገር ግንባታ ልክ እንደ አንድ ሰው የምንቆምበት እንዲሁም ይመለከተኛል የሚል ዜጋ ሁሉ ዳር ቆሞ መመልከትንና በረባ ባረባ ሁሉ ላይ ተችት ማብዛትን ተሻግሮ፤ የድርሻውን በታሪክ የሚታወስ አሻራ እንዲያኖር የአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ የሚያመላክት ይሆናል፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 7/2013