አስናቀ ፀጋዬ
በዓለም አቀፍ ደረጃ የትምህርቱ ዘርፍ አሁን ለደረሰበት የእድገት ደረጃ በየዘመኑ ጥቅም ላይ ሲውሉ የነበሩ ቴክኖሎጂዎች የራሳቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል:: ተማሪዎችንም ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል:: ብራና፣ ጥቁር ሰሌዳና መጽሐፍት በጊዜያቸው የትምህርት ዘርፉ የተጠቀመባቸው አዲስ ቴክኖሎጂዎች ነበሩ:: ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ እንደ ሬዲዮ፣ ካሴቶች፣ ፊልሞች፣ ፕሮጀክተሮችና መሰል የቴክኖሎጂ ግኝቶች ትምህርቱን ለማገዝ ሥራ ላይ ውለዋል:: በኢትዮጵያም ተግባራዊ ሲደረጉ የቆዩት ትምህርት በሬዲዮና በቴሌቪዥን እንዲሁም የፕላዝማ ትምህርቶች ለዚህ ጥሩ ማሳያ ናቸው::
በአሁኑ ዘመን ደግሞ ኮምፒዩተሮች፣ ላፕቶፖች፣ ታብሌቶች፣ ተንቀሳቃሽ ስልኮችና የመሳሰሉት የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንደ ትምህርት አጋዥ መሣሪያዎች ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ:: በተለይ ደግሞ የኮሮና ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተከሰተ ወዲህ ተማሪዎች በቤታቸው እንዲውሉ በማስገደዱ የዲጂታል ቴክኖሎጂ ጠቀሜታ በእጅጉ ጎልቶ ታይቷል:: ተማሪዎችም ከዲጂታል ሚዲያ ጋር ያላቸው ትስስር ጨምሯል:: ዲጂታል ቴክኖሎጂውም የተማሪዎችን መማርና ለትምህርታቸው ኃላፊነት ወስደው መከታተልን የመሳሰሉ አወንታዊ ባህሪዎቻቸውን አሳድጓል::
በተመሳሳይ በኢትዮጵያ የኮሮና ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ ትምህርት ቤቶች በመዘጋታቸው አብዛኛዎቹ ማህበራዊ ድረገፅና የቴሌግራም ቻናል በመጠቀም ለተማሪዎቻው አጋዥ ትምህርታዊ መረጃዎችን ሲያጋሩ ቆይተዋል:: ይህም ተማሪዎች በቤታቸው ሆነው ትምህርታውን እንዲከታተሉ ዕድል ሰጥቷቸዋል:: በወረርሽኙ ምክንያት ሊያመልጣቸው የነበረውን ትምህርትም እንዲያገኙ አስችሏቸዋል::
ከዚሁ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ትምህርትና ፈተናን ለተማሪዎች ገፅ ለገፅ መስጠት ባለመቻሉ መንግሥት ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂው ፊቱን በማዞር የ10ኛ እና 12ኛ ክፍል ተማሪዎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ፈተናቸውን በታብሌት እንዲወስዱ ከጫፍ ደርሶ እንደነበርም ይታወሳል:: ይህም የዲጂታል ቴክኖሎጂው በተለይ በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ምን ያህል አስፈላጊ እንደነበር አመላክቷል::
ከዚህ ሁኔታ በመነሳትና እያደገ የመጣው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ለትምህርቱ ዘርፍ ያለው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን በመረዳት ‹‹ለርን 365›› የተሰኘው የቴክኖሎጂ ተቋም ለተማሪዎች በዓይነቱ የተለየ አጋዥ የቪዲዮ ማቴሪያል ይዞ ብቅ ብሏል::
የ‹‹ለርን 365›› ቴክኖሎጂ ተቋም መስራችና የትምህርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ ሰብስቤ እንደሚናገሩት ተማሪዎች እውቀት እንደልብ ያለበት ዓለም ላይ ያሉ ቢሆንም በአስተማሪያቸው ወይም በአስጠኚያቸው ብቻ ይገደባሉ:: ከዚህ አኳያ ተማሪዎች እውቀትን በራሳቸው እንዲያገኙ የሚያስችል የለርን 365 አጋዥ የተማሪዎች የቪዲዮ ትምህርት መርጃ መሣሪያ የመጀመር ሃሳብ ከአምስት ዓመት በፊት ተፀነሰ::
የትምህርት መርጃ መሣሪያው ለተማሪዎች ሲቀርብ ላልተፈለገ መረጃ ተጋላጭ እንዳይሆንም የሀገሪቱን ሥርዓተ ትምህርትና የተማሪዎችን መጻሕፍት ይዘት በተከተለ ሁኔታና ተማሪዎች በሚወዱት መልኩ ለማዘጋጀት ተወሰነ:: ተቋሙም በትምህርቱና በሚዲያው ዘርፍ በተሰማሩ ኢትዮጵያውያኖችና ሕንዶች ከአምስት ዓመት በፊት ተመሰረተ:: በዘርፉ ከፍተኛ የትምህርት ዝግጅትና ልምድ ያላቸውን ባለሞያዎች በመመልመልና ጠንካራ ቡድን በማደራጀት ወደ ሥራ ገባ::
በቡድኑ ውስጥ የሥርዓተ ትምህርት ባለሞያዎች፣ አስተማሪዎች፣ የሶሻል ሚዲያ አማካሪዎች፣ የካሜራ ባለሞያዎች፣ ግራፊክ ዲዛይነሮች፣ የአኒሜሽን ባለሞያዎች፣ ሶፍትዌር አበልፃጊዎች፣ ፕሮዳክሽን አስባባሪዎች፣ የማርኬቲንግ ባለሞያዎችና ሌሎችም እንዲካተቱ ተደርጓል:: በዚህ ሂደትም ተማሪዎችን፣ የተማሪ ወላጆችን፣ ትምህርት ቤቶችን፣ ባንኮችንና ሌሎችም ተቋማት እንዲሳተፉ በማድረግ እገዛዎችን ማግኘት ተችሏል::
ከዓመታት ጥረት በኋላም ‹‹ለርን 365›› የተሰኘው አጋዥ የተማሪዎች የቪዲዮ ትምህርት መርጃ መሣሪያ ተማሪዎች ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ወደውና ፈቅደው እንዲማሩ በቅርቡ ሥራ ላይ ውሏል::
እንደ ኃላፊው ገለፃ በታብሌት ኮምፒዩተሮችና በስማርት ተንቀሳቃሽ ስልኮች የቀረበው አጋዥ የቪዲዮ የትምህርት መርጃ መሣሪያው በጊዜያዊነት ከ7ኛ እስከ 10ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች የእንግሊዝኛ፣ ሂሳብ፣ ፊዚክስ፣ ኬሚስትሪና ባዮሎጂ ትምህርቶችን አካቷል::በቀጣይም ሌሎች ክፍሎችንና የትምህርት ዓይነቶችን የያዘ አጋዥ የቪዲዮ ትምህርት መርጃ መሣሪያ ለተማሪዎች ተደራሽ ይሆናል::
በቪዲዮ የተደገፈው የትምህርት መርጃ መሣሪያው በኢንተርኔትና ያለ ኢንተርኔት ዳታ መስራቱ ለተማሪዎችም ሆነ ለወላጆቻቸው እጅግ ተስማሚ የሚያደርገው ሲሆን እያንዳንዱ ትምህርት ከፍተኛ ብቃትና ልምድ ባላቸው አስተማሪዎች በቪዲዮ፣ በግራፊክስና በምስል በመታገዝ ቀርቧል:: ከእያንዳንዱ ትምህርት በኋላም ተማሪዎች ግንዛቤያቸውን እንዲገመግሙ የሚሰሯቸው ጥያቄዎችንም አካቷል:: በእያንዳንዱ ክፍለ ትምህርት መጨረሻም ከአምስት ዓመት አገራዊና ክልላዊ ፈተናዎች የተውጣጡ ጥያቄዎች ቀርበውበታል::
በተጨማሪም በትምህርት መርጃ መሣሪያው የተማሪዎች ጥያቄዎች ከፍተኛ ብቃት ባላቸው የመምህራን ቡድን ሁሌም .ይስተናገዱበታል:: በሌላ በኩል ደግሞ ወላጆች ልጆቻቸው ምን ትምህርት እንዳጠኑ፣ ለምን ያህል ጊዜ እንዳጠኑ፣ ጥያቄዎችን መስራታቸውን ወይም አለመስራታቸውን የሚከታተሉበትና የሚያግዙበት ገፅታንም ተላብሷል::
መርጃ መሣሪያው በቪዲዮ መልክ መቅረቡ ደግሞ ወላጆች ትምህርቱን በቀላሉ እንዲያስታውሱትና እንዲረዱት በማስቻል ለልጆቻቸው የሚያደርጉትን እገዛ ያቀልላቸዋል:: ሥነ ልቦናዊ ጠቀሜታውም የላቀ ሲሆን በተለይ ተማሪዎች ከመርጃ መሣሪያው ጋር ያላቸው ቀጥታ ግንኙነት ለጥናታቸው ኃላፊነት መውሰድና ሂደቱን መቆጣጠር መቻላቸው ከዚህ አልፎ ይህን አጋዥ የትምህርት መርጃ መሣሪያ በመጠቀም በትምህርታቸው ውጤታማ መሆናቸው፣ በራስ መተማናቸውን በማሳደግ የትምህርት ፍላጎታቸውን ይጨምራል::
ኃላፊው እንደሚሉት የትምህርት መርጃ መሣሪያው በተማሪው ፍላጎት፣ አቅምና ፍጥነት ልክ የተዘጋጀና ተማሪ ተኮር መሆኑ ልዩ ያደርገዋል:: ይህም ተማሪ መማሩን መምራት መቻሉ ተማሪውን ያነቃቃዋል::ዘመኑ የዲጂታል ተማሪዎች ከመሆኑ አኳያም የዚህ ትምህርት አሰጣጥ በዚህ መንገድ መሆኑ ለአብዛኞቹ ዲጂታል ተማሪዎች ምላሽ ይሰጣል::
አጋዥ የትምህርት መርጃ መሣሪያው ተማሪዎች ትምህርታቸውን በሚወዱት መልኩ እንዲማሩ ታልሞ የተጀመረ ቢሆንም በተለይ የኮሮና ወረርሽኝ ያስከተለው ዓለም አቀፍ የጤና ቀውስ ተማሪዎች ቤት እንዲውሉ ሲደረግና አሁንም በፈረቃ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ባሉበት በአሁኑ ጊዜ፤ የተሸራረፈ የትምህርት ጊዜያቸውን ለማካካስና እቤት ሲውሉ ትምህርታቸውን በማስቀጠል ረገድ እንደግል አስጠኚ በማገልገል፣ ለተማሪዎች፣ ለወላጆችና ለትምህርት ቤቶች ትልቅ እገዛ ያደርጋል::
በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንም በሀገር ውስጥ ያሉ ዘመዶቻቸውን በገንዘብ ደግፈው በተለይ ታብሌት በመግዛት የመርጃ መሣሪያው አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ
ይጋብዛል:: በቀጣይም አሁን ያለውን ልምድና ተሞክሮ በመያዝ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመሆንና ግብረመልሶችን ከተጠቃሚዎች በመቀበል ይበልጥ ለማሳደግና ለማስፋት አቅድ ተይዟል::
አጋዥ የትምህርት መሣሪያው ሥራ ላይ ውሎ ከሚመጣው ግብረ መልስ በመነሳትም በቀጣይ መሻሻል የሚገባቸውን ነገሮች በማስተካከል በተሻለ መልኩ ለተማሪዎች አገልግሎት እንዲሰጥ ነው የሚደረገው:: በየደረጃው ላሉ የትምህርት ደረጃዎችም የማስፋት ዕቅድ አለው።
ቴክኖሎጂና ትምህርት እየተደጋገፉ እዚህ ደረጃ ላይ ከመድረሳቸው አኳያና ዘመኑም የዲጂታል ቴክኖሎጂ ከመሆኑ አንፃር ተማሪዎችን በመጻሕፍትና በፊት ለፊት ማስተማሩ ብቻ በቂ ባለመሆኑ መንግሥት ለዲጂታል ቴክኖሎጂ ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል::
የለርን 365 ቴክኖሎጂ ተቋም ጄነራል ማኔጀር አቶ ቢኒያም መርሻ በበኩላቸው እንደሚገልፁት፣ አጋዥ የቪዲዮ ትምህርት መርጃ መሣሪያው ሥራ ላይ የሚውለው የዲጂታል ሚዲያ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሲሆን ተማሪዎች በመጀመሪያ ለዚሁ አላማ የተዘጋጀውን መተግበሪያ ከተቋሙ በመውሰድ አስፈላጊውን ሁሉ ያሟላሉ::
በኢትዮጵያ ብዙ ጊዜ የኢንተርኔት ችግር የሚያጋጥም ከመሆኑ አኳያም መተግበሪያው በኢንተርኔትም ሆነ ያለ ኢንተርኔት እንዲሰራ ሆኖ ተዘጋጅቷል:: መተግበሪያው ያለኢንተርኔት የሚሰራ መሆኑ ደግሞ ተማሪዎች በኢንተርኔት ወደሚሰሩ ሌሎች ጉዳዮች ገብተው ከትምህርታቸው እንዳይዘናጉ ያደርጋል::ወላጆችም ልጆቻቸው ወደ ሌላ ነገር ይገባሉ ብለው አይሰጉም:: ኢንተርኔት በሌላቸው ገጠር አካባቢዎች ላይም ተማሪዎች ታብሌትና ስማርት ተንቀሳቃሽ ስልክ እስካላቸው ድረስ በቀላሉ እንዲጠቀሙ ያስችላቸዋል::
ተማሪዎች ታብሌቶች በመግዛት አልያም በስማርት ተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው አማካኝነት መተግበሪያውን ጭነው ከከፈቱ በኋላ የሚፈልጉትን የትምህርት ዓይነት መርጠው የመጀመሪያውን ምዕራፍ በቪዲዮ በታገዘ መልኩ በሕንድ መምህራን ትምህርታቸውን ይከታተላሉ:: አንደኛውን ምዕራፍ አጠናቀው ወደ ሁለተኛው ምዕራፍ የሚሸጋገሩትም በመጀመሪያው ምዕራፍ መምህራኖቹ የሚሰጧቸውን ፈተናዎች ሰርተው ካጠናቀቁ በኋላ ይሆናል:: ይህም ተማሪዎች ወደቀጣዩ ምዕራፍ ለመሸጋገር በየትምህርት ዓይነቱ ያሉ ምዕራፎችን በሚገባ ተከታትለው እንዲያጠናቅቁና ፈተናዎችንም በብቃት እንዲሰሩ ያደርጋል::
ጄነራል ማኔጀሩ እንደሚሉት ሕንዶች በሳይንስና ቴክሎጂ ጥሩ ተሞክሮ ያላቸው ከመሆኑ አኳያ የቴክኖሎጂና የእውቀት ሽግግር እንዲኖር ከማድረግ አንፃርም የትምህርት መርጃ መሣሪያው ትልቅ አስተዋፅኦ ያበረክታል:: አጋዥ የትምህርት መርጃ መሣሪያው ሲዘጋጅ የመጀመሪያ ከመሆኑ አኳያ በቀጣይ በተለያዩ የትምህርት ዓይነቶችና ክፍሎች እያደገና እየሰፋ ሲሄድ የተሟላ አገልግሎት ይሰጣል:: በተመሳሳይ የዲጂታል ላቦራቶሪ እንዲኖርም ይደረጋል::
በቀጣይ የትምህርት መርጃ መሣሪያው እንዲያድግና እንዲሰፋ ይሰራል:: በአጋዥ የትምህርት መርጃ መሣሪያ ውስጥ የተካተቱ ቪዲዮዎች እንዳሉ ሆነው ተጨማሪ ቪዲዮዎች እንዲካተቱም ይደረጋል:: ሕንዶቹ እያስተማሩበት ያለውን መንገድ በማየትም በሂደት ለተማሪዎች ቀላል የትምህርት ማስረጃ ቴክኒኮችን በመጠቀም ትምህርት እንዲያገኙ ይሞከራል::
ለሰባተኛና ስምንተኛ ክፍሎች በቶሎ መድረስ ስላለበትና ክፍተቱን ለመሙላት በአሁኑ ወቅት አጋዥ የቪዲዮ ትምህርት መረጃ መሣሪያው ተዋውቆ ሥራ ላይ መዋል ጀምሯል:: ከአስተዳደሮችና ከሚመለከታቸው አካላት ጋርም ውይይትና ስለ መርጃ መሣሪያው ገለፃ ተደርጓል:: በየደረጃው ካሉ ትምህርት ቤቶች ጋርም ተመሳሳይ ንግግር መደረጉን ነው ያስረዱት::
አጋዥ የትምህርት መርጃ መሣሪያውን በአሁኑ ወቅት ተማሪዎች መጠቀም የጀመሩ ሲሆን በቀጣይ ይበልጥ እየተዋወቀ ሲሄድ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ይደርሳል ተብሎ ይጠበቃል:: ወላጆች ከተቋሙ ጋር እየተገናኙም ስለ አጋዥ የቪዲዮ ትምህርት መርጃ መሣሪያው ገለፃ ከተደረገላቸው በኋላ መተግበሪያውን ይወስዳሉ::
በክልል ደረጃም መቅረብ ሲጀምር ተማሪዎች በስማርት ተንቀሳቃሽ ስልኮቻቸው አማካኝነት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስችላቸዋል:: በቅርቡም አዲስ አበባ የሚገኙ ሁለት ትምህርት ቤቶች እንዲያዩት ተደርጎ ለመጠቀም ፍላጎታቸውን አሳይተዋል::
ጄኔራል ማኔጀሩ እንደሚገልፁት ታብሌቶችን በሚመለከት ከተቋማት ጋር በተለይ ከንስር ማይክሮ ፋይናንስ ጋር በመሆን ተማሪዎች ታብሌቱን ወስደው የሚከፍሉበትን መንገድ እያመቻቸ ይገኛል:: በተመሳሳይም ተቋሙን ያግዛሉ ተብለው ከሚታሰቡና ንግድ ባንክን ከመሳሰሉ የፋይናንስ ተቋማት ጋር አብሮ ለመስራት ጥረት እየተደረገ ይገኛል::
በቀጣይም ተቋሙ ከመንግሥት ጋር በመነጋገር የትምህርት መርጃ መሣሪያው ለብዙኃን ተማሪዎች የሚቀርብበትን ሁኔታ ያመቻቻል:: ይህን ሥራ ተቋሙ ለብቻው ሊያከናውነው የማይችለው በመሆኑ ባለሀብቶችና መንግሥት ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል:: ይህን ማድረግ የሚቻል ከሆነም የትምህርት መርጃ መሣሪያውን በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች ለሚገኙ ተማሪዎች ማዳረስ ይቻላል:: ይህንንም ለማሳካት ተቋሙ በግሉ የራሱን ጥረት በማድረግ ላይ ነው::
እንደ ኢንቨስትመንት ሲታሰብ ሥራው ለመንግሥት ቀላል ከመሆኑ አኳያም ተማሪዎች ታብሌቶችን አንዴ ካገኙ የተለያዩ የክፍል ደረጃዎችን መማር ስለሚያስችላቸው ታብሌቶች ለተማሪዎች የሚቀርቡበትን መንገድ ማመቻቸት ይኖርበታል:: በውጭ ሀገር የሚኖር እያንዳንዱ ሰው ለዘመዱ አንድ ታብሌት በላከ ቁጥርም ለመንግሥት የውጭ ምንዛሬ የሚያድን በመሆኑ ይህን ማበረታታት ይገባል:: በትምህርት ላይ የሚደረገውን ኢንቨስትመንት መደገፍና ማበረታታት ከመንግሥት ይጠበቃል::
አዲስ ዘመን መጋቢት 7/2013