ውብሸት ሰንደቁ
በህንፃዎች ግንባታ ዙሪያ በርካታ ሕፀፆች ይነሳሉ:: ግንባታ በጥራት፣ በጊዜ እና በተገቢው ሁኔታ አለመጠናቀቁ አንደኛው ውዝፍ ዕዳ ሳይቀር ሀገር ላይ እየጣለ ያለ ችግር ነው:: በሌላ በኩል ሕንፃዎች ተገንብተው ተጠናቀቁ ተብሎ እንኳን ከአካባቢ ጋር ስምሙ አይሆኑም አሊያም ለማህበረሰብ አገልግሎት ዴንታ የሌላቸው ይሆናሉ:: የጥራትም ሆነ የግንባታ ወጪ ቁጥጥር፤ የዲዛይንም ይሁን የአጨራረስ ጊዜ ክትትል የመጨረሻ ግቡ ግንባታዎች ለሰው ልጆችና ለአካባቢው ምቹ መገልገያዎችና አሉታዊ ተፅዕኖዎች የሌላቸው ማድረግ ነው::
የኮንስትራክሽን ሥራዎች ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን በ2013 ዓ.ም ስድስት ወር አከናውኛቸዋለሁ ያላቸው በርካታ ተግባራት በግማሽ ዓመት ሪፖርቱ ላይ
አካትቷል:: ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዋጋ ጥናት፣ ቀመር ዝግጅት፣ የዲዛይን ግምገማ ሥራዎች ውስጥ አንዱ የሆነውን በፌዴራል መንግሥት ባለቤትነት የሚገነቡ የግንባታ ፕሮጀክቶች ዲዛይን የመገምገም ሥራ ለመስራት በዕቅዱ በተያዘው መሠረት ከ10 የፌዴራል ተቋማት 13 የዲዛይን ይገምገምልኝ ጥያቄ ቀርቦ 11 የሚሆኑ ዲዛይኖች የተገመገሙ ሲሆን ቀሪ ሁለት ዲዛይኖች በግምገማ ሂደት ላይ ናቸው:: ለግንባታ ፕሮጀክቶች የሚተከሉ ዋጋዎች ከመገምገም አንጻር በፌዴራል የመንግሥት ተቋማት አማካኝነት የሚገነቡ የ14 ፕሮጀክቶች የዋጋ ቀመራቸውን ለመገምገም ችሏል::
ወቅታዊ የሆኑ የኮንስትራክሽን ግብዓቶች ማለትም የጉልበት፣ የፋብሪካ ውጤቶች፣ የአካባቢ ግብዓቶች፣ የማሽነሪና መሳሪያዎች ወ.ዘ.ተ የዋጋ መረጃ በመሰብሰብ እና በማቀናጀት ለፈላጊ አካላት ተደራሽ ለማድረግ ታስቦ የበጀት ዓመቱን የኮንስትራክሽን ዋጋ አሰባሰብ የድርጊት መርሐ ግብር በማዘጋጀት በግማሽ ዓመቱ ሁለት ጊዜ መረጃውን ሰብስቧል:: ከግንባታ ፕሮጀክቶች ዲዛይን እና የዋጋ ግምገማ ሥራ ጋር በተያያዘ በስታቲካል ሪፖርት መካተት የነበረባቸው ዳታዎች ያለመካተታቸው እና የመሬቱ የመሸከም አቅም ያለመገለጽ ችግሮች ከተገመገሙት ዲዛይኖች በሦስቱ ላይ የታየ ሲሆን የጽሑፍ ግብረ መልስ ለተቋማት በመስጠት እንዲታረም በመደረጉ የጥራት ደረጃቸውን እንዲጠብቁ ተደርጓል::
በግንባታ ተቋራጮች በኩል አዲሱን ኮድ ያለመጠቀም፣ የአፈር ጥናት ሪፖርት፣ ያላለቀ የሳኒቴሪ ዲዛይን ሪፖርት፣ የሳኒቴሪ ዝርዝር ዲዛይን ያለመካተት፣ የውሃ አቅርቦት ዲዛይን በአግባቡ አለማዘጋጀት፣ የፍሳሽ ቆሻሻው አወጋገድና የዝናብ ውሃ አወጋገድ ሲስተም ሳያካትቱ የቀረቡ አምስት ዲዛይኖች ግብረ-መልስ ተሰጥቶባቸው እንዲታረም በመደረጉ የጥራት ደረጃቸውን እንዲጠብቁ ተደርጓል::
ቦታ አለመታየት ወይም የሥራ ዝርዝርና የሥራ መጠን ሰነድ ያልቀረበባቸው አራት ዲዛይኖች የጽሑፍ ግብረ መልስ ለተቋማት በመስጠት እንዲታረም በመደረጉ የጥራት ደረጃቸውን እንዲጠብቁ ተደርጓል:: ከዋጋ ቀመር ግምገማ አንጻርም ባለፉት ስድስት ወራት የግንባታ ፕሮጀክቶች ዋጋ በመገምገም ሂደት ፕሮጀክቶች ጥራታቸውን ጠብቀው እና ዋጋቸው ያልተጋነነ እንዲሆኑ በተሰራ ሥራ ከቀረቡት 14 ፕሮጀክት ሰባቱ በዋጋ ቀመር ላይ የተቀመረው ዋጋ ከውል ሰነድ ነጠላ ዋጋ ጋር ባለመጣጣሙ፣ የድንጋይ ግንብ ሥራ ዋጋ ቀመርና የተተከለ ነጠላ ዋጋ ያልተጣጣመ በመሆኑ እና ሌሎች የተጋነኑ ዋጋዎች እንዲታረሙ በማድረግ ብር 19 ሚሊዮን የሚጠጋ በፕሮጀክቶቹ ላይ ሊታይ የሚችለውን አላስፈላጊ ወጪ ማስቀረት ተችሏል:: በጥቅሉ ዋጋ ጥናት፣ ቀመር ዝግጅት እና የዲዛይን ግምገማ ሥራዎች ጋር ተያይዞ በግማሽ ዓመቱ ለማከናወን የታቀዱ ግቦችና ተግባራት አማካይ አፈጻጸም 94 ነጥብ 87 በመቶ የተፈጸሙ መሆናቸውን የተቋሙ ሪፖርት ያመላክታል::
ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በአገር ውስጥ በሚመረቱና ከውጭ በሚገቡ አስገዳጅ ደረጃ በተሰጣቸው በመጀመሪያ ግማሽ ዓመት 32 ያክል የግንባታ ግብዓቶች ላይ የቁጥጥር ሥራ ማከናወን ችሏል:: በበጀት ዓመቱ 50 የግንባታ ግብዓት አቅራቢዎች ላይ የገበያ ክትትል እንዲሁም በ71 የማምረቻ ቦታዎች ላይ የሠራተኛ ጤንነትና ደህንነት እና የአካባቢ ደህንነት ስጋት ለመቀነስ የሚያስችል ቁጥጥር ማድረግ ችሏል::
አዲስ ለሚመዘግቡ እና ዓመታዊ ዕድሳት ለሚያደርጉ 5ሺህ600 እንዲሁም ከዚህ ውስጥም በግማሽ ዓመቱ 2ሺህ700 የኮንስትራክሽን መሣሪያዎች የቴክኒክ ብቃት ምርመራ በማድረግ ብቁነታቸውን ለማረጋገጥ አቅዶ 1702 መሳሪያዎች ላይ ብቻ የቴክኒክ ምርመራ የተደረገ መሆኑ ተመዝግቧል::
በአጠቃላይ የግንባታ ግብዓቶች እና ማሽነሪ ቁጥጥር ሥራ ጋር በተያያዘ በመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ለማከናወን በዕቅድ የተያዙ ሥራዎች 82.04 በመቶ ያክሉ የተፈጸመ ሲሆን በበጀት ዓመቱ ለማከናወን ከተያዘው ጋር ሲነጻጸር 42.49 በመቶ ያክሉን ማከናወን እንደተቻለ ተቀምጧል::በእርግጥ የተቋሙ ሪፖርት በርካታ ተግባራትን የዳሰሰ ነው:: እኛም የወሰድነው በጥቂቱ ለማሳየት ያህል እንጂ የዘርፉን አጠቃላይ የስድስት ወር ሪፖርት ለመዳሰስ አይደለም:: በባለሥልጣኑ እንደዚህ ዓይነት ክንውኖች ይመዝገቡ እንጂ ዘርፉ ገና ብዙ ሥራ የሚጠይቁ ችግሮች የተጋረጡበት የግንባታ ኢንዱስትሪ ነው::
የኮንስትራክሽን ዘርፉ ላይ የሚሠሩ ሥራዎች በተለይ ለታዳጊ ሀገራት የህልውና ጉዳይ እየሆኑ ነው:: አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ ነውና በዘርፉ የሚካሄደው ቁጥጥር ወሳኝ
ነው:: በዘርፉ ስላሉ ተግዳሮቶችን በክንውን ወቅት ስላስተዋሏቸው ችግሮች የተቋሙን የሥራ ኃላፊዎች አነጋግረናል::
አቶ መስፍን ነገዎ የኢፌዴሪ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ናቸው:: አቶ መስፍን በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለፁት፣ በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚታዩት ችግሮች ከሕግ ማዕቀፉ ምልዑ አለመሆን
ይጀምራል:: በተጨማሪም የሕግ ማዕቀፉ አንዳንድ ክፍሎች ያረጁና አሁን ያለውን ፍላጎት የማያሟሉ እንዲሁም የኢንዱስትሪውን ዕድገት የሚመጥኑ አይደሉም ሲሉ በዘርፉ ላይ የሚታየውን እንከን ይናገራሉ:: በዘርፉ የሚቆጣጠር አካል ለረጅም ጊዜ ስላለነበረ ተጠያቂነትን እያረጋገጡ መሄድ ላይ ችግር ነበር::
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ የኢፌዴሪ የኮንስትራክሽን ሥራዎች ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የኮንስትራክሽን ሕጎችን የሚያከብር፤ በተቀመጠለት ዋጋ የሚጨርስ፤ በተያዘለት ጊዜ የሚያጠናቅቅ፤ በሚፈለገው ጥራት የሚሠራ እና የአካባቢንና የሕዝብን ደህንነትና ምቾት የሚጠብቅ ኢንዱስትሪ እንዲፈጠር እየሠራ ይገኛል::
ባለሥልጣኑ በአጠቃላይ በሦስት ደረጃ የሚከፈሉ ችግሮችን አይቷል:: የመጀመሪያው ቅድመ ግንባታ ላይ የሚታይ ችግር ነው:: ዲዛይናቸው ብቻ ተነጥሎ ሲታይ ያለቀለትን ዲዛይን ይዘው የሚጀመሩ እምብዛም ናቸው:: ሆን ተብሎ ዲዛይናቸው ከነብዙ እጥረቶች ይሠሩና ግንባታው ከሚያስፈልገው በላይ ተጨማሪ ወጪ በመጠየቅ ለሙስና የተጋለጡ አሠራሮች
ይታያሉ:: በተጨማሪም በግንባታው ዘርፍ የሚታዩት የተበላሹ የጨረታ አሠራሮች የዘርፉ አንድ ችግሮች ናቸው:: በግንባታ ወቅት የሚታዩት ችግሮች ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ በተለይ በግንባታው በጥራት ያለመገንባት፤ በተያዘለት ጊዜ አለመጠናቀቅ የመሳሰሉት ችግሮች አሉ:: በሦስተኛ ደረጃ የሚታዩት ደግሞ የሕንፃዎችን ችግሮች ለማረም የሚሠራ አለመኖሩ ነው:: በተለይ በዩኒቨርሲቲዎች ያሉ ፕሮጀክቶች በዚህ የተጠቁ ናቸው::
ዋና ዳይሬክተሩ እንዲህ ይላሉ እንደዚህ ዓይነት ፕሮጀክቶች ሲገጥሙን በመጀመሪያ የምናደርገው የሦስትዮሽ ውይይት ማካሄድ ነው:: በዚህም ባልተገባ ጥራት የተሠሩ ህንፃዎችን እስከማፍረስና መጠነኛ ችግሮች የታየባቸውን በራሳቸው ወጪ እርማት እንዲያደርጉባቸው እስከማድረግ ደርሰናል:: የተዛቡና የተጋነኑ ዋጋዎችንም እንዲሁ እንዲስተካከሉ አድርገናል:: በአጠቃላይ በእነዚህ ሥራዎች ረገድ ከአንድ ፕሮጀክት እስከ 60 ሚሊዮን ብር ማስመለስ የቻልንበት አጋጣሚ አለ::
ማህበረሰብን ያላማከለና ለማህበረሰብ አገልግሎት ዴንታ የሌለው የህንፃ ግንባታ መገንባቱ ፋይዳ አይኖረውም፤ ስለዚህ ግንባታዎች ከመገንባታቸው በፊት የአካባቢና የማህበረሰብ ተፅዕኖ ግምገማ ሊደረግባቸው ይገባል ሲሉ የሚያስረዱት ደግሞ አቶ በረከት ተዘራ ናቸው:: አቶ በረከት ተዘራ በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ የሕንፃ ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ናቸው:: በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ትልቁ ነገር ግንባታው ተገንብቶ የሚያመጣው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው እና ለማሕበረሰብ አገልግሎት ጤናማ አድርጎ ማስቀጠል መቻሉ ላይ ነው:: የግንባታ ሥራዎችን የዲዛይን ጥራት፣ ከግንባታ ጊዜና በዋጋ ስንቆጣጠር የመጨረሻው ግቡም ይሄው ነው ይላሉ አቶ በረከት:: የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ በየጊዜው ራሱን በመለወጥ ላይ የሚገኝ ኢንዱስትሪ ስለሆነ ይህንን ያማከለ የህግ ማዕቀፍ መደንገግ ያስፈልጋል:: የሕንፃ አዋጆቻችንም ኢንዱስትሪውንና ማህረሰቡን ሊያጣጥም በሚችል መልኩ ሊቀረፁ ስለሚገባ አሁን ላይ ያሉትን ለአሰራር የማያመቹ አዋጆችን በመቀየር ላይ እንደሚገኙም ይናገራሉ:: በርካታ ግንባታዎች መጠናቀቅ ከሚገባቸው ጊዜ እየተጓተቱ በመሆኑ ይህን እየተከታተሉ በማረም ላይ ይገኛሉ:: አብዛኞቹ ሕንፃዎች ማህበረሰቡን ተደራሽ ማድረግ ስላለባቸው የአካል ጉዳተኞች ተደራሽ ያልሆኑ ሕንፃዎች የዲዛይን ማስተካከያ እንዲያደርጉ በዲዛይን ደረጃ ሳያካትቱ የመጡት ደግሞ መጀመሪያውኑ አሟልተው እንዲመጡ እየተደረገ ነው::
አቶ በረከት እንደሚሉት የግንባታ ሥራ ተሳታፊዎች ሕጉን አክብረው መሄድ የሚችሉ ከሆነ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው አንድ እርምጃ ወደፊት መሄድ
ይችላል:: በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በየዓመቱ እስከ 150 ሺህ የግንባታ ፈቃድ ይሰጣል:: ሆኖም የግንባታ ሥራዎች እየተሠሩ ያሉት ግን በተወሰኑ አካላት
ነው:: በከተማዋ የሚገነቡ ግንባታዎች በአብዛኛው ፈቃድ ያላቸው ወይም በሙያው የሠለጠነ አካል እየተገነቡ አይደለም:: አብዛኞቹ በአሠሪና በገንቢ መካከል በሁለትዮሽ ድርድር የሚሠሩ ናቸው:: ይህ መንግሥት ከዘርፉ የሚያገኘውን ጥቅም ከማሳጣቱም በላይ የጥራት ጉድለት የመድረስ ዕድሉም ከፍተኛ
ነው:: እነዚህን ችግሮች በጠንካራ አመራር በመሻገር ነው የግንባታ ኢንዱስትሪውን ማዘመን
የሚቻለው:: ወደ ኢንዱስትሪው መቀላቀል የሚገባቸው ተምረው ሥራ ያጡ ዜጎችም ወደዘርፉ በመቀላቀል ዘርፉን በተማረ ሰው ኃይል እንዲመራና የሥራ አጥ ቁጥር እንዲቀንስ ማድረግ ይቻላል::
አንድ አማካሪ የግንባታ ሥራዎች ድርጅት በዩኒቨርሲቲ ግምባታዎች ውስጥ ብቻ 147 ፕሮጀክቶችን ይዞ መገኘቱን አቶ በረከት በትዝብታቸው ገልፀዋል። ይህ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሱፐርቪዥን የተባለው የመንግሥት ድርጅት እነዚህን ያህል ቢይዝም ሁሉም ግንባታዎች በሚፈለገው ጊዜ እየተጠናቀቁ አለመሆኑንም እንዲሁ:: አጠቃላይ በኢትዮጵያ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችን የ2013 ዓ.ም የግንባታ ሥራ በጀት 7 ኮንትራክተሮች 25 በመቶ ያህሉን ይዘውታል:: እንደዚህ ዓይነት ነገሮች በአዋጅ ተደግፈው መስተካከል ይኖርባቸዋል:: እንደዚህ ዓይነት አሠራሮችን የሚገድብ መመሪያ እስከሌለ ድረስ ኢንዱስትሪውን ከእንከን የጸዳ ማድረግ አይቻልም:: የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ማነቆ ሆነው አላሠራ ያሉ እንዲህ ዓይነት የሕግ ክፍተቶች መታረም ይኖርባቸዋል::
አዲስ ዘመን መጋቢት 7/2013