ምህረት ሞገስ
በ1945 ዓ.ም በሐረር የተወለዱት ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ዘካርያ፤ እድገታቸው አዲስ አበባ በመሆኑ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በቀድሞ አጠራሩ ወሰንሰገድ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና በልዑል መኮንን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡ በ1964 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት የታሪክ ትምህርትን አጥንተዋል፡፡ ወደ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ በማቅናት በሙዚየም ትምህርት ዘርፍ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ሰርተዋል፡፡
ከ1973 ዓ.ም ጀምረው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ ጥናት ምርምር ተቋም ውስጥ ከባለሙያነት እስከ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ሙዚየም ዳይሬክተርነት ድረስ አገልግለው የአርባ ዓመታት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቆይታቸውን ጨርሰው በጡረታ ተገልለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በእርቅ ሰላም ኮሚሽን የሀገር ሽማግሌ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ። ከአዲስ ዘመን ዝግጅት ክፍል ጋር በወቅታዊ አገራዊ የፖለቲካ ጉዳይ፣ ከጎረቤት አገር ጋር ባለን ግንኙነት እና በምሥራቅ አፍሪካ ወቅታዊ ፖለቲካ ዙሪያ ቆይታ አድርገዋል፡፡ እንደሚከተለው አሰናድተነዋል።
አዲስ ዘመን፡– ከለውጥ በፊት የነበረውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ እንዴት ይገልፁታል?
ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ፡– ሁሉም አዲስ ነገር ሲመጣ የትናንትናውን መውቀስ ይፈልጋል:: ነገር ግን ሕይወት ተያያዥ ናት:: ተበጥሶ እንደአዲስ የሚጀመር ነገር የለም:: ስለዚህ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሥርዓቱ እና ሂደቱ ተያያዥ ነው:: ከመሰረቱ ጀምሮ ሲታይ እንደሰንሰለት የተያያዘ ነው:: በሰንሰለቱ ውስጥ እያንዳንዱ ቀለበት ደካማ ወይም ጠንካራ ሊሆን ይችላል:: ጠንካራ ሰንሰለት ሲኖር መተሳሰሪያውም ይጠነክራል:: ደካማ ሲሆን ደግሞ መተሳሰሪያውም የላላ ይሆናል:: ነገር ግን ሰንሰለቱን የሚያያይዝ ቀለበት መኖሩ መረሳት የለበትም:: ቀለበት ከሌለ እና ከተበጠሰ አዲስ አገር አዲስ መንግሥት ተፈጠረ ማለት ነው:: ስለዚህ አመለካከታችንን ማስተካከል አለብን:: ትናንት ሁሉ ነገር መጥፎ ነው ማለት አይቻልም:: ትናንት መጥፎም ጥሩም ነገር ነበር:: ዛሬም እንደዚያው ነው:: ጥሩ ብቻ የሚባል ነገር የለም::
የሰው ልጅ የመልአክ እና የሰይጣን ቁራጭ ነው:: መልአክ አያጠፋም ይባላል:: ሰይጣን ደግሞ አጥፊ ነው:: ስለዚህ ሰው የሁለቱንም ወስዷል:: በዚህ ግንዛቤ ሥርዓታችንንም ሆነ ታሪካችንን መተንተን ከቻልን ጤናማ ይሆናል:: በማመስገን እና በመሳደብ ብቻ የምንሄድ ከሆነ የአመለካከት ጉድለት ይኖራል:: የአመለካከት ጉድለት ከኖረ ደግሞ የአስተሳሰባችንን ቀና መንፈስ ያናጋዋል:: ሁሉም ሥርዓት የራሱ ዓላማ ይኖረዋል:: አንዳንዱ ሥርዓት እኔ በበላሁት አንተ ተፈወስ ዓይነት ይሆናል:: አንዳንዱ ደግሞ ሕዝቡን ያማከለ ዓይነት ይሆናል::
ለውጥ ሲባል ከየትኛው እንጀምር? ያለፈው 30 ዓመት ነው? ያለፈው 30 ዓመት ከሆነ ሁለት ነገር አለ:: በግሌ እንደማምነው ያለፈው ሥርዓት የወታደር መንግሥት ነው:: ከዚያ በፊትም የነበረው የወታደር መንግሥት ነው:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኮሎኔል ናቸው:: ስለዚህ የሲቪል ስሜት አሁንም ገና አልመጣም:: ኢህአዴግም ሆነ ህወሓት አመሠራረታቸው ከወታደር የመጡ ስለነበሩ የወታደር መንግሥት ነበሩ ማለት ነው:: እርሱን እንዴት እናስተናግዳለን? የሚለው ጥያቄ መነሳት አለበት:: አሁንም ያው ነው::
ወደ ፊት የሲቪል መንግሥት የሚመሰረት ከሆነ ሲቪሉ ራሱን አዘጋጅቷል ወይ? የፓርቲ ሂደቱ ምን ይመስላል? ከተባለ እዚያም ላይ ችግር አለ:: ስለዚህ ከሥርዓት አንፃር ከተነጋገርን ገና መስቀለኛ መንገድ ላይ ነን:: የኢኮኖሚው፣ የፖለቲካው እና የማህበረሰቡን ሁኔታ ስናይ ባለፉት 27 ዓመታት ሁሉም የአካባቢው ንጉስ ይሆናል የሚል ስሜት ነበረ:: ያ የፈጠረው አዲስ ስሜት ሲነሳ ንግስናው ምን ዓይነት ነው? የሚሰራው ምንድን ነው? ንግስናው ሥራ ላይ የሚውለው እንዴት ነው? የሚለው ላይ ማጥናት አልተጀመረም::
መጀመሪያም ቢሆን በመሰረቱ የተሞከረው አስቸጋሪ ነገር በመሆኑ በሂደት እያመረቀዘ ማስተናገድ የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል፤ ዛሬም ያው ችግር አለ:: ዛሬም የፖለቲካ ልሂቃን ኢትዮጵያን እንዴት እናስተዳድራት የሚለውን ጥያቄን አስመልክቶ ማሰብ አለባቸው:: ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ጥያቄ የተከማቸበት ምክንያት የሥልጣን ሥርዓት ጥያቄ ትርጉም ባለው መልክ ባለመመለሱ ነው:: ይህ ጥያቄ መመለስ አለበት:: ልሂቃኑ ቁጭ ብለው የኢትዮጵያ የሥልጣን ፍልስፍና ምን መሆን አለበት? የሚለውን ረጋ ብሎ በጥናት መመለስ ይጠበቅባቸዋል:: አሁን የተቸገርነው አንድ የሚያደርገንና የሚያይዘንን ነገር በማጣታችን ነው:: ኢትዮጵያዊነታችንን የሚገልፅልን አንድ ነገር ማስቀመጥ ያስፈልጋል::
ባለፉት መንግሥታት ጠቃሚም ሆነ አልሆነ ሥልጣን የሚገኝበት (የሚያዝበት) ግልፅ መንገድ ነበረ:: ሥልጣን ለመያዝ የሰለሞንና የሳባ ዘር መሆን ይገባ ነበር::
አዲስ ዘመን፡– ሥልጣን በደም ውርስ ማለት ነው?
ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ፡– አዎ! (blue blood) የሚባለው ማለት ነው:: በደም ሥልጣን ይያዝ ነበር:: ከዚያ ማርክሲዝም መጣ:: ማርክሲዝም ላይ የመደብ ጉዳይ ነበር:: ቀጠለና ብሔር ብሔረሰብ ተከተለ:: የመደብ ልዩነቱ ተፈልጎ ታጣ:: አሁን ደግሞ ብሔር ምንድን ነው? ብሔር ብሔረሰብ ማን ነው? ሕዝብስ የትኛው ነው? ትርጉም ሳይሰጠው እየተሰቃየን እንገኛለን:: መብትስ የአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው? ወይስ ተለይቶ የተሰጠው ለብሔሮች ነው? የሚል ጥያቄ እየተነሳ እንደገና ሕገመንግሥቱ የሚታይበትን ሁኔታ እንዲፈጠር አስገድዶናል:: ሕገመንግሥቱ አተገባበር ላይ ደግሞ የራሱ ሌላ ችግር አለ:: ያለፈው መንግሥት በአጠቃላይ የወታደር መንግሥት በመሆኑ አካሄዱ ወታደራዊ ነው:: ሲቪል ነን ስለተባለ ሲቪል መሆን አይቻልም:: በግብፅም ባለፉት 60 ዓመታት ወታደራዊ መንግሥት ነበረ:: በኢትዮጵያም እስካሁን ባለው ተመሳሳይ ይመስላል::
መንግሥቱ ኃ/ማርያም ወታደር እንደነበር ግልፅ ነው:: መለስ ዜናዊም ከወታደር ብዙ የራቀ አይደለም:: የዶ/ር ዓብይ አህመድም ተመሳሳይ ነው:: አገርን ለማዳን ሁሉም ዘብ ሆኖ ሊሰለፍ ይችላል:: ነገር ግን ሥርዓት ይዞ መከላከያ ውስጥ የሚያገለግል ከሲቪሉ የተለየ ነው:: ይህ እንደጥያቄ ሊነሳ የሚችል ነው:: በአጠቃላይ ምንጮቹን እያጠሩ መነጋገር እንጂ የትናትናውን መጥፎነት እና የዛሬን ጥሩነት ብቻ መነጋገር አይገባም:: ከትናንትናውም ሆነ ከዛሬው ከሁለቱም ጥሩነትም ሆነ መጥፎነት አለ:: በኃይለሥላሴም ዘመን ጥሩም ሆነ መጥፎ ነገር ነበር:: በደርግም ሆነ በኢህአዴግ ጊዜም ጥሩም መጥፎም ነገር አለ:: በለውጡ ዘመንም በተመሳሳይ መልኩ ጥሩም መጥፎ ነገርም አለ:: መሠረታዊ የሆኑ ጥያቄዎችን ለመመለስ በእኔ በኩል የምለው የእኔ ፍልስፍና መነሻው ሰላም ነው::
ዛሬ አንፃራዊ ሰላም በመኖሩ ቁጭ ብለን እንነጋገራለን:: ይህ አንፃራዊ ሰላም በኢትዮጵያ በሌሎች አካባቢዎች የሌለበት ሁኔታ አለ:: ያው በቅርቡ የመን ላይ በስደት ላይ ያሉ በመቶ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሞተዋል:: ይህ በጣም የሚዘገንን ነው:: ‹‹ለዚህ ስደት ያበቃን ምንድን ነው?›› ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል:: አገሪቱ ጥሩ ከሆነች ‹‹ኢትዮጵያውያን ለምን ተሰደው ይሞታሉ?›› ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው:: አንፃራዊ ሰላም መኖሩ የሚያስመሰግን ቢሆንም ሙሉ ሰላም እንዲኖርም እንደሚያስፈልግ መረሳት የለበትም::
ሰላም ለሰው ልጅ የኦክሲጅን ያህል አስፈላጊ ነው:: አየር ከሌለ የሰው ልጅ አይኖርም:: ግን ደግሞ ሰው በአየር ብቻ አይኖርም ውሃ ያስፈልገዋል:: ውሃው ኢኮኖሚ ነው:: ኢኮኖሚው ሥርዓት መያዝ አለበት:: ያለአየር ለደቂቃዎች መቆየት አይቻልም:: ያለ ውሃ ለቀናት መቆየት ይቻል ይሆናል:: ነገር ግን ብዙ ቀን መቆየት አይቻልም:: ያለ ምግብ ደግሞ ለወራት መቆየት ይቻል ይሆናል:: ነገር ግን ምግቡም ከሌለ ሰው መኖር አይችልም:: ፖለቲካውም እንዲሁ ሥርዓት ሊኖረው ይገባል:: አየሩ፣ ውሃው እና ምግቡ መያያዝና በአግባቡ መኖር አለበት:: ኢትዮጵያ ውስጥ እነዚህ ነገሮች አልተመጣጠኑም:: ግብፆች ከእኛ ጋር የሚጣሉት በውሃ እና በአፈር ነው:: እኛ ግን ረሃብተኛ ሆነን እንለምናለን:: ይህንን የምናርቀው እንዴት ነው? ይህንን ማንኛውም ዜጋ የሚጠይቀው ነው? እኔም ይህንን ጥያቄ እጠይቃለሁ::
በእኔ ግምት በኢትዮጵያ 120 ሚሊየን ሕዝብ አለ:: ከዚህ መሃል ያለው አብዛኛው ደግሞ ወጣት በመሆኑ ከታሰበው ጊዜ ቀድሞ በቅርብ ጊዜ ውስጥ 200 ሚሊዮን ይደረሳል:: ለ120 ሚሊየን ሕዝብ መቀለብ ያቃተው አገር፤ ነገ 200 ሚሊዮን ሕዝብ እንዴት መቀለብ ይችላል? ይህ አጠያያቂ ነው:: ዛሬ የሚነገረው መልካም ነገር እንደተጠበቀ ሆኖ ያሉ ችግሮችን በግልፅ መወያየት ያስፈልጋል::
ከመሬት ጋር የተያያዙ ችግሮች ዛሬም አልተፈቱም:: ዛሬም በአዲስ አበባ ሁሌም የሚሰማው የቤት እጦት ሮሮ ነው:: ስለመሬት ወረራ በተደጋጋሚ ይሰማል:: በገጠርም ገበሬው ባለመብት አይደለም:: ሰርተፍኬቱ አልተሰጠውም:: እዚያ ላይ መሰራት አለበት:: የመሬት ስሪት ሥርዓቱ በደንብ ካልተፈተሸ ቴክኖሎጂ ቢገባም ሆነ ልማት ቢዘረጋ ገበሬው ‹‹የኔ ነው›› ብሎ ካልተቀበለው ያስቸግራል የሚል እምነት አለኝ:: በኪራይ የሚኖር ሰው ቤቱን አያድስም ምክንያቱም ነገ ትቶት ይወጣል:: ባለቤት የሆነ ሰው ግን ቤቱን ሁሌም ይጠግናል:: ምክንያቱም ቤቱ ዛሬ ብቻ ሳይሆን ነገም የእርሱ ነው:: ስለዚህ የቤት ባለቤትነት ጥያቄ መፍትሔ ማግኘት አለበት::
እኔ ሳስበው ከተማ ላይ መሬት የግድ ላያስፈልግ ይችላል:: በላፕቶፕ እየሰሩ ብዙ ገንዘብ እያገኙ ሆቴል መኖር ይቻላል:: በአውሮፕላን መንቀሳቀስ አይከብድም:: አሁን ላይ በከተማ ትልቁ ሀብት አንጎል ነው:: በፊት መሬት ነበር፤ ከዚያ ፋብሪካ ሆነ በኋላ ዳግሞ ወደ አንጎል ዞረ:: በገጠር ግን ገበሬው ሕይወቱ ከመሬት ጋር የተያያዘ ነው:: የኢትዮጵያ አንደኛው ችግር ደግሞ ከመሬት ጋር የተያያዘ ነው:: ስለዚህ የብዙኃኑን ጥያቄ መመለስ ያስፈልጋል::
በቂ መሬት አለ:: ውሃው፣ አፈሩ እና ጉልበቱ እያለ ለምን እንለምናለን? የሚለውን ጥያቄ መመለስ ይገባል:: ያለውን ደግ ደግ ነገር ብቻ ማውራት ቀላል ነው:: ነገር ግን ችግሩ እያፈጠጠ ይመጣል:: ስደት አለ:: የሰው ቁጥር ሲበዛ ሌላ ተስፋ ያስፈልጋል:: እዚህ ተስፋ መስጠት የምንችልበት መላ ካለ ስደቱ ይቀንሳል:: ስለዚህ ትልቁ ፈተና ያለውን ፀጋ መጠቀም አለመቻል ነው:: ላለው ልማት እያመሰገንኩ፤ ነገር ግን አሁንም ችግሩ አልተፈታም የሚል እምነት አለኝ:: ችግሩ ካልተፈታ አንድ ያሰረው ነገር አለ:: ከለውጡ በፊት የነበረው መንግሥት ሲታይ ገንዘብ የተሰራበት አንደኛው መንገድ መሬት ነው:: ዘረፉ፣ ሰረቁ ሲባል የነበረው በመሬት እና በባንክ ነው:: አሁንም ከለውጡ በኋላ የማዘጋጃ ቤት ሰዎች እንደሚናገሩት የመሬት ጉዳይ ትልቅ ጩኸት አለበት:: ስለዚህ የችግራችን ምንጭ መሬት ነው:: ሌላውን ወርቅም ሆነ ማዕድን እንዲሁም ነዳጅም ቢኖር መንግሥት ይቆጣጠረዋል::
መሬቱ ሁሉንም ይመለከታል:: መሬቱ ቢለማ አግሮ ኢንደስትሪው ይመጣል:: የአገልግሎት ዘርፉ ያድጋል:: ቱሪዝም ብለን እንጮሃለን፤ ነገር ግን ድሃ አገር ላይ ቱሪዝም ብዙም አይኖርም:: ምክንያቱም ቱሪስቱ ድሃ አገር ላይ የማይመጣው መሠረተ ልማት ይፈልጋል:: በኢኮኖሚ ዘርፍ ላይ ያሉ ሰዎች የበለጠ ሊተነትኑት ይችላሉ:: ነገር ግን ኢኮኖሚው እየሰበረን ነው:: ነፃነት አንድ ነገር ነው:: ነገር ግን ደግሞ ኢኮኖሚውም ደግሞ ሌላ ነገር ነው:: በነፃነነታችን ብንኮራም ራሳችንን ባለመቻላችን ደግሞ አፍረን አንገታችንን እንሰብራለን:: ስለዚህ እነዚህ ጥያቄዎች ያለውም ሆነ የሚመጣው መንግሥት ሊያያቸው ይገባል:: ይህንን ደብቀን ልማት ልማት ብቻ ማለት በፊትም እንደነበሩት መንግሥታት የማይጨበጥ ከሆነ ዋጋ አይኖረውም::
አዲስ ዘመን፡– ለ50 ዓመታት የኢትዮጵያ መንግሥታት የአሁኑን ጨምሮ ወታደራዊ ይመስላሉ ብለዋል:: በሌላ በኩል ደግሞ ባለፉት ጊዜያት ሁሉም የአካባቢው ንጉስ ነበር:: የሚል ነገር ጠቅሰዋል:: የፖለቲካ አደረጃጀቱ ላይ የነበረውን ችግር በደንብ ቢያብራሩት?
ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ፡– ሁሉም መንግሥታት ለመግዛት የራሱ አቀባበል እና አጀንዳ ይዞ ይነሳል:: ህወሓት ከትንሽ ጫካ ተነስቶ አዲስ አበባ ሲገባ ከ70 ሚሊዮን በላይ አልፎ ተርፎ 100 ሚሊዮን ሕዝብ እንዴት እንደሚያስተዳደር አስቦበት አልመጣም:: ስለዚህ ያኔ የችግር ምንጮች ናቸው ተብለው የሚታሰቡ ከ30 በላይ የነፃነት አውጪ ድርጅቶች ተብለው የሚታሰቡት ሁለት ሰው ያለው ድርጅትም ተቆጥሮ ማለት ነው፣ የእነርሱ ጉዳይ ነበር::
ቀድሜ እንዳነሳሁት ኢትዮጵያ ውስጥ የሥልጣን አስተዳደር ሥርዓቱ በግልፅ አልተቀመጠም:: በደርግ ጊዜ የተሞከረው የመደብ ጉዳይ ተነሳ፤ ነገር ግን ኢትዮጵያ ውስጥ እንደፈረንጅ አገር ዓይነት ኢኮኖሚ ባለመኖሩ ጨቋኝ ተጨቋኝ የሚለው ነገር አልነበረም:: የመደብ ልዩነት ሳይኖር ያ በኢትዮጵያ ትርጉም የሌለው መስመር ተቀመጠ:: ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው በግብርና ምርት ላይ ባላባት የነበረው ሰው ያስገብራል፤ በዓመት ግብር እያበላ ያችኑ ይበትናት ነበር:: ልዩነቱ ሰፊ አልነበረም:: ምናልባት ልዩነቱ ባላባቱ ጠጅ ሲጠጣ ገበሬው ቤት ጠላ ይጠጣ ነበር:: አለባበሳቸውም አኗኗራቸው ይህን ያህል ሰፊ ልዩነት ያለው አልነበረም:: ጨቋኝ የሚያስብል ነገር ሳይኖር መጽሐፍ ላይ ያነበብነውን የመደብ ሁኔታ በተግባር መኖር አለመኖሩን ሳናረጋግጥ በመሞከራችን ተጨራረስን፤ እርሱ ብዙ ጎዳን::
በእርግጥ በደል አልነበረም ማለት አይደለም:: በደሎች ይኖራሉ:: ነገር ግን የመደቡን ትምህርት ተማርን ባዮቹ እነርሱም ዞረው በመበደላቸው ደግሞ እንደገና ሕዝቡ ጮኸ:: መጽሐፉን ስላነበቡ መፍትሔ ያመጣሉ ማለት አይደለም:: የኢትዮጵያን ተጨባጭ ባህል እና ታሪክ አለማወቃችን ትልቅ ችግር ፈጠረ:: ስለዚህ ህወሓት ጫካ ሆኖ ያሰበው ስለመንገጠል ነው:: አሁንም አዝማሚያው እንደዚያ ይመስላል:: ነገር ግን የወርቅ እንቁላል የምትጥለዋ ዶሮ ካለች ወርቁ አለ፤ ያለበለዚያ አበቃ:: ዶሮዋን ካረድናት የምትሆነው ብልት ብቻ ነው:: ብልት ደግሞ ለጭልፊት ይመቻል::
ከባለፉት 40 እና 50 ዓመታት አንፃር የአፍሪካ ቀንድን ስናስበው የችግር እና የጦርነት ቀጣና ነበር:: ኢትዮጵያን ስናስብም የውጭ እና የውስጥ የራሳችንን ግጭት በአግባቡ ማየት አለብን:: ስትራቴጂክ ቦታ ስለሆንን የውጭ ግፊቶች ይኖራሉ:: እርሱንም ሳንክድ፤ አመጣጥነን ማሰብ አለብን:: ጠንካራ ሰውን በሽታ ብዙ ላይጎዳው ይችላል:: ነገር ግን የደከመ ሰው ትንሹ ቫይረስ በጣም ይጎዳዋል:: ስለዚህ የውስጥ ጥንካሬ ለውጭ ጠላት መግቢያ ቀዳዳ ይከለክለዋል:: የውስጥ ድክመት ለውጭ ጠላት በር ይከፍታል:: ባለፉት 50 ዓመታት የአፍሪካ ቀንድ የተረጋጋ አልነበረም:: በኢትዮጵያም የዩጎዝላቪያ ዕጣ ታይቷል:: ኤርትራን ገነጠልን፤ ሶማሌያን በታተንን፤ ሱዳንን ከፈልን አሁን ደግሞ የሚፈለገው ምንድን ነው? የሚለው ትልቅ ጥያቄ ነው:: የበለጠ የዶሮ ብልት የመሆን ጥያቄ ነው? ወይስ ፈጣሪ የሰጠንን ፀጋ ተጠቅመን ሕዝቡም በፍትሃዊነት ተጠቅሞ የተሻለ ሕይወት እንዲመራ ነው? ይህ የሚታሰብበት ደረጃ ላይ ተደርሷል::
ከውጭ በሚመጣ መሣሪያ ወንድም ከወንድሙ ጋር ቢጨራረስ ምንም ትርጉም የለውም:: ጥይት እና ጠመንጃውን፣ ታንክና አውሮፕላኑን የምንሰራው እኛ አይደለንም:: ይሄ ምን ትርጉም አለው? ስንጨራረስ ለጠላት ደስታው ነው:: ስትራቴጂክ ጥቅማቸውንም ሆነ የተፈጥሮ ሀብታችንን ይጠቀሙበታል:: ኢትዮጵያ ውስጥ ትግራይ ላይም ሆነ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ላይ በአፍሪካ ትልቅ ወርቅ ቢገኝ ትርጉም የለውም:: ገና ሳናየው መጨራረስ ይኖራል:: ቤኒሻንጉል ላይ ማን ለምን ግጭት ይፈጥራል? የሚለው ግራ ያጋባል:: የሚቆሰቁሰው የውጭ እጅ ነው? ወይስ የራሳችን ድክመት ነው? ጋምቤላ ላይ ነዳጅ ቢገኝ መጨራረስ ይኖር ይሆን? እርግጥ በአፍሪካ ምድር የተፈጥሮ ሀብት ርግማን ነው ይባላል:: ምናልባት ርግማን እየመጣብን ይሆን? ብዬ እጠይቃለሁ::
የመንግሥት ሥርዓት ሕዝብን ለማስተዳደር ብሔር፣ ብሔረሰብ ሕዝብ ብሎ ሲነሳ፤ የአንዱ ባህል በሌላው ባህል ላይ ሥርዓት ይመስርት ብሎ መጀመር ነገር ያበላሻል:: ኢትዮጵያ ብዝሃ ባህል ያላት አገር ናት:: ያንን ታስተናግድ ትክክል ነው:: ነገር ግን ረጋ ተብሎ ሲታሰብ በሁለት መልኩ ሊታይ ይችላል:: ፖለቲካ ሁሉን አቀፍ ነው:: የመብት ጥያቄ ነው፤ የኢኮኖሚ ፍትህ ነው፤ የሕግ ጉዳይ በሙሉ በፖለቲካ ማዕቀፍ ውስጥ መካተት ያለበት ነው:: በባህል ዘርፍ ውስጥ ያለው ግን በግል የሚገኝ መብት ነው:: ስታሊን ቋንቋ ፖለቲካ ውስጥ መግባት የለበትም ይላል:: አንድ ሰው ክርስቲያን እና አማራ ቢሆን፤ ይህ ይከበርለታል:: ነገር ግን የፖለቲካ አጀንዳ መሆን የለበትም:: ብሔር የሚለው ነገር እኔን አይገባኝም:: እኔ ብሔር የሚለውን የማየው እንደባህል ነው:: ደግሞም ማስተናገድ አለባት:: የፖለቲካ አጀንዳ ካደረግነው ፖለቲካው ራሱ ከአካታችነት ይልቅ አግላይ ሆነ ማለት ነው:: ወገንተኛ ሲሆን ደግሞ ማፅዳት አይቻልም::
አማራ ወይም ክርስቲያን እሆናለሁ ብሎ ማንም አልተወለደም:: ስለዚህ አንዱ የሌላውን ማክበር አለበት:: መጀመሪያ መደብ ነበረ:: በዚያ አንድ ትውልድ ባከነ:: አሁን ደግሞ በዚህ አንድ ትውልድ ሊያልቅ ይችላል:: ተቃቅፈን ተጋብተን ብዙ ወንዞች አቋርጠናል:: ሁሉም ቅይጥ ነው:: ንፁህ ነኝ ብሎ የሚናገር ካለ ራሱን ያታልላል:: ትግራይ ሰላም በነበረበት ጊዜ አንድ የማውቀው ምሁር ጥናት አጥንቶ እዚያ ከነበሩ የትግራይ ሹሞች ከአማራ እና ከኦሮሞ ያልተወለደ አለመኖሩን ገልፆልኛል:: የትም ቢኬድ በተለይ ከተማ ላይ ለንግድና ለሥራ በመገናኘት ብዙኃኑ ይጋባል፤ ይቀየጣል:: ያንን ተፈጥሯዊ ሂደት የፖለቲካ አጀንዳ በማድረግ መሣሪያ መሆን የማይችለውን በግድ መሣሪያ እናድርገው ስንል የመጣው ጣጣ መጥቷል:: ባህል እና ሃይማኖት ቢነካ ፍርድ ቤት ቀርቤ የመክሰስ መብቴ የተጠበቀ መሆን ይገባዋል:: ይህንን መብቴን መንግሥት ማስከበር አለበት::
የፖለቲካ ጥያቄ ሁሉም የሚጋራው ነገር ላይ መሆን አለበት:: ሁሉም ይርበዋል፤ ሁሉም ይጠማዋል:: ፓርቲዎች ሥራ እንፈጥራለን፤ ፍትህ እናመጣለን፤ የአስተዳደር በደል እንከላከላለን ማለት አለባቸው:: እኛ ንጹህ ደም አለን፤ የእነንትና ደም ቆሻሻ ነው ብለው መምጣት የለባቸውም:: መጀመሪያም ሥልጣን የሚያገኘው የከተማ ምሁርም ቢሆን ሥራ ላይ የሚውል ጥያቄን ብቻ ነው መመለስ ያለበት:: ሰውን ከተወለደበት ካደገበት ቦታ ‹‹ተነቀል ቦታው የተደነገገው በኔ ስም ነው፤ አፅመ ርስቴ ነው›› የሚል ጥያቄ የመጣው የፖለቲካ አቀራረባችን ችግር ስለነበረበት ነው::
ይህም መታረም ካለበት በጊዜ መታረም አለበት:: ይሄ ጋጥ የወጣውን የፖለቲካ ሂደታችንን ማስተካከል አለብን:: ከፊታችን ምርጫ ነውና እነዚህን ዝርዝር ነገሮች ተናግረን አንጨርሰውም፤ ከምርጫው በኋላ ነቅሰን አውጥተን እንነጋራለን የሚል ተስፋ አለኝ:: ዛሬ ማፅዳት ስለማይቻል የሚቀጥለው መንግሥት ይህንን ኃላፊነት ወስዶ ነገ የተሻለ አገር ለመገንባት ምክንያት ይሆናል የሚል ተስፋ ይዘን እንጂ ብዙ ችግር አለ:: በኢኮኖሚ ብዙ ችግር አለ:: የመሬት ጥያቄ ገና አልተመለሰም:: በፖለቲካም ቢሆን ብሔር ብሔረሰብ ሕዝቦች የሚለውን ጉዳይ መብት የሚያስከብር ሕገመንግሥት ኖሮ በፖለቲካ ላይ የሚኖራቸው ድርሻ በውል መለየት አለበት::
አዲስ ዘመን፡– እዚህ ላይ ብሔር ብሔረሰብ ሲሉ መከፋፈልን እንዴት ያዩታል? ስለአንድነትስ ምን ያስባሉ?
ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ፡– እምነቴን ከጠየቅሽኝ መሃል ሰፋሪ ነኝ:: በሁለቱም መንገድ ለየብቻ መቅረብ ልክ አይደለም ባይ ነኝ:: በኢትዮጵያዊነትና በአንድነት ብቻ እንቀጥል ከተባለ ምንን በመመርኮዝ ነው? የሚል ጥያቄ አቀርባለሁ:: ልዩነትን ማየት አልፈልግም ማለት በራሱ ችግር ነው:: ተፈጥሮ በራሷ ልዩነትን ታስተናግዳለች:: ልዩነት የለም አይስተናገድም ማለት ምን ማለት ነው:: እኔና ወንድሜ አንድ አይደለንም:: የእናት ሆድ ዥንጉርጉር ይባላል፣ እኛም ዥንጉርጉሮች ነን:: በፊት የነበረው አንድ ብሔር፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንድ ቋንቋ የሚለውን ስሜት ያመጣል::
አንድነት በሚለው ላይ የበፊቱ የሚመጣበት ሁኔታ ማምጣቱ ጣጣ ነው:: በሌላ በኩል ደግሞ የእኔ መብት ብቻ ነው፤ ሌሎችን አላስተናግድም፤ የሚል ከሆነ ትልቋን ኢትዮጵያ መርሳት ይሆናል ማለት ነው:: ሁለቱም ፅንፍ የወጡ ከሆኑ መሃል ላይ ማስታረቂያውን መንገድ መነጋገር ነው:: ለውይይት፣ አዲስ ሃሳብ ለማምጣትና ነገር ለማብላላት ፅንፍ ጥሩ ነው:: ነገር ግን ፅንፍ አብሮ ለመኖር አያመችም:: ስለዚህ ወደ መሃል መምጣት ያስፈልጋል::
ኢትዮጵያ የሁላችንም መሰባሰቢያ ናት:: እዚህ ላይ መግባባት ያስፈልጋል:: ሁሉም ቁስል አለበት:: አንድነት በሚባልበት ጊዜ እኔም ያሳለፍኩት ቁስል አለ:: ቁስሉን አስመልክቶ ይቅር ማለት ይቻላል:: መርሳት ግን አይቻልም ምክንያቱም ጠባሳው አለ:: ቁስሉም ከአንዱ የአንዱ የተለየ ሊሆን ይችላል:: ምክንያቱም የመወጋቱ መጠን የተለያየ ይሆናል:: ጠባሳ አለብኝ ካለ አይ ጠባሳ የለብህም ማለት አይቻልም::
አዲስ ዘመን፡- ምንም አልተጎዳህም ብሎ መካድ አይቻልም?
ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ፡- አዎ! መካድ አይቻልም:: ጎጂው የኔ አባትም ሆነ አያት ብቻ ጉዳት ነበረ:: ነገር ግን ጠባሳ ቢኖርም ደግሞ ይቅርታ ማለት ማንንም አልገደለም:: ሰለጠኑ የሚባሉት እነ አሜሪካ የባሪያ ንግድ ሥርዓታቸውን አልኮነኑትም ስለዚህ ዛሬም ዴሞክራሲ አለ ቢባልም ጥቁሩን እንደውሻ ይገድሉታል:: ስለዚህ መጀመሪያ አስተሳሰቡ መፅዳት አለበት:: አንድነት ሲባል ኢትዮጵያን የመሰረትኳት እኔ ነኝ፤ ዳር ድንበሯን የጠበቅኳት ጀግና የሆንኩት እኔ ብቻ ነኝ፤ ብሎ አንተ ምን አደረግክና የሚል ካለ ግን ችግር ነው::
ለምሳሌ ከ25 ዓመታት በፊት ጀምሮ የተከታተልኩትን ዓድዋን እንደምሳሌ ላንሳ፡- በቅድሚያ ብሔራዊ እንዲሆን ታስቦ ነበር:: ነገር ግን ገመድ ጉተታ ውስጥ ተገባ:: በፊት የአማራ እና የትግሬ ልሂቃን ሁለቱም ኢትዮጵያን እንወክላለን ይላሉ:: ነገር ግን ተፈልፍሎ ሲታይ የዮሐንስ ድል ነው የምኒልክ ድል ነው እያሉ ልሂቃኑ ሲጣሉ ውጪ ሌላው ሰው ረስቶት ነበር:: ቀስ በቀስ ሕዝባዊ ሆነ:: በተለይ የዛሬ ስምንት ዓመት ወጣቶች የተለያየ ምክንያት ቢኖራቸውም የእግር ጉዞ መጀመራቸው አንድ ስሜት ፈጠረ:: እዚያ የወደቀው ጀግና የተባለው አርበኛ ብቻ ሳይሆን ተራው ሰውም ጭምር መሆኑን አመለከቱ:: ሁሉም አካባቢ የደስታ ስሜት ፈጠረ::
አሁን በዓሉ የእኛ አይደለም የሚሉ ሳይቀሩ ሂደቱ ላይ ችግር ቢኖርም ተቀላቀሉ:: ሂደቱም ወደ ፊት ይስተካከላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ:: መቀላቀላቸው ትልቅ ነገር ነው:: ቤተሰብ ሆነዋል ማለት ነው:: እዚያ ላይ ፀሎት ያደረገውም፣ አዝማሪውም፣ የፎከረውም የተጋደለውም ኢትዮጵያን ለማዳን አገልግሏል:: ስለዚህ መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም የሚመሰገን ነው:: ማር የሚሰራው በንግስቷ ንብ ብቻ አይደለም:: ንግስቲቷም ሥራ አላት፤ አበባ የሚቀስመውም ውሃ የሚሰብስበውም ሁሉም የየራሳቸው ድርሻ አላቸው:: ድምር ውጤት ላይ መስማማት አለብን::
ሁሉንም ነገር ለእርሱ ከሰጠነው ጥሩ አይመጣም:: አመራር ሥራው ማስተባበር ነው:: ለውጥ ለማምጣትም የሕዝብ ንቅናቄ ነው:: ለማስተባበር ለውለታው ምስጋና እናቀርባለን:: ነገር ግን የምንሰራው ሁላችንም ነን:: የፖለቲካ ሂደታችንም ላይ የነበረው አንድነት የሚለው ስሜት ሁሉም ሲፈለፍለው የሚለው የትናንትናው እንዳይመጣ እየፈራ ነው:: አንድነት የሚይዘው አማራነትን ክርስቲያንነትን ነው ብሎ ሊሰጋ ይችላል:: ይህንን የሚለው ከመሬት ተነስቶ አይደለም:: ትናንት ችግር ስለነበር ነው:: ስለዚህ አንድነትን ይፈራል::
በሌላ በኩል ከኢትዮጵያ ተነስቶ አሜሪካ ገብቶ ስንት ዓመት ከቆየ በኋላ ‹‹አፅመርስቴ ነው›› የሚል ዓይነት ጨዋታ የሚያዋጣ አይደለም:: ኬኩን መብላት ወይም መያዝ እንጂ ሁለቱንም ማድረግ አይቻልም:: ኢትዮጵያ አሁን ላይ 100 ሚሊዮን ገበያ እና የሚሰራ እጅ አላት::
ይህንን በሥርዓቱ መጠቀም ከቻልን ከችግራችን ቶሎ እንወጣለን:: ቻይና ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት አላት:: ስለዚህ የዓለም የሥልጣኔ ጫፍ ላይ ለመድረስ እየቻለች ነው:: ቻይና ሕዝቧ በዝቶ ችግር አልሆነም:: ሕዝቦቿ የሚያሰራ ሥርዓት ተፈጥሮላቸዋል:: ሁሉም የየድርሻቸውን ስለሚሰሩ አድገዋል፤ ተመንግደዋል:: በ50 ዓመት ውስጥ እጅግ ልቀዋል:: ስለዚህ ፖለቲካው ላይ ፅንፍ የተያዘበትን ሁኔታ ወደ መሃል ማምጣት ሲቻል ለውጥ ይመጣል:: እኔ በበላሁ አንተ ትፋ የሚለው ማታለያ እስከተወሰነ ጊዜ ሊያስኬድ ቢችል እንጂ ዘላቂ አይሆንም::
አዲስ ዘመን፡– ለውጡ ይዞ የመጣው አዲስ የፖለቲካ ባህል እና ተስፋን በሚመለከት ምን ይላሉ?
ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ፡– የሰው ልጅ ያለ ተስፋ አይኖርም:: ተስፋ አለ:: ነገር ግን ስጋትም አለ:: 120 ሚሊዮን ሕዝብ ካልበላ እና ካልጠጣ በሰላም ወጥቶ መግባት አይቻልም:: አንዱ በልቶ ሌላው ተርቦ በሰላም መኖር አይቻልም:: የኢኮኖሚው ጉዳይ ሥርዓት መያዝ አለበት:: የፖለቲካ ልሂቃን ሥርዓት ካላስያዙት ማስተዳደር አይቻልም:: አሁን ባለው ሁኔታ ብዙ ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉ:: እንዲሁ ስለተስፋ እና ስለተስተካከለ ሜዳ ብቻ ማውራት ውጤት የለውም:: ታሪክ የሚጠቅመው ከትናንትናው ለመማር ነው:: ተስፋው ቢኖርም ስጋት መኖሩ መካድ የለበትም::
አዲስ ዘመን፡– ለሰዎች የሚያስፈልጉ በአየር፣ በውሃ እና በምግብ ተመስለው በእርሶ የተጠቀሱት ጉዳዮች እንዳይገኙ የሚያደርጉ ለለውጡም እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮች ምንድን ናቸው?
ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ፡– እንደኔ አስተሳሰብ ትልቁ ችግር እልኸኛነት ነው:: የተራራ ሰው እልኸኛ ነው:: ለውጭ ጠላት እና ለድህነት እልኸኛ መሆን ጥሩ ነው:: ነገር ግን ወንድም ወንድሙን ለማጥፋት እልኸኛ መሆን የለበትም:: ለውጥ አለ:: ነገር ግን ለመስራት አስቸጋሪ ይሆናል:: ትልቁን ስዕል ለማየት ከእልህ መውጣት ያስፈልጋል:: የተስፋዊቷን ኢትዮጵያ ለማየት እልሃችንን በአግባቡ ማስተናገድ አለብን:: እንዴት እናስተናግድ ከተባለ ብዙ ውይይት እና ክርክር ያስፈልጋል:: የእልህ መፍቻ መንገዱ ላይ መግባባት ከተቻለ ከባድ አይሆንም::
እኔ ደጋግሜ የማነሳት ስዊዘርላንድን ነው:: ስዊዘርላንድም እንደኢትዮጵያ ሕዝቦቿ የተራራ ሰዎች በመሆናቸው እልኸኞች ናቸው:: ስዊዘርላንዶችም ድብቅ፣ ምስጢረኞች እና እልኸኞች ናቸው:: የእነርሱ አስተዳደርም በጎጥ ነው:: ይህን ያደረጉት እልሃቸውን ለማስተንፈስ ነው:: ሕዝባቸው 7 ሚሊዮን ቢሆንም 26 አስተዳደር አላቸው:: የአዲስ አበባን ማህበረሰብ ለሚያክል ሕዝብ 3ሺ ገደማ ማዘጋጃ ቤት አለ:: ሀብታም በመሆናቸው ይችላሉ:: ብዙ ጊዜ ስለማይስማሙ በዓመት ሁለት ጊዜ ሪፈረንደም ያደርጋሉ:: ድምፅ እየሰጡ እልሃቸውን ይወጣሉ:: እኛ አገር ግን እልሃችንን የምንወጣው በመቆሳሰል ነው:: ከእነርሱ የምንማረውን ተምረን ለእኛ በሚመች መልኩ እልህ ማስተንፈሻ መላ ያስፈልገናል እላለሁ::
ትልቁ ችግር ጠቃሚ እልህ ቢኖርም የማይጠቅም እልህ አለ:: የማይጠቅመው እልህ እንዴት ይስተናገድ? ብለን ማስቀመጥ አለብን:: ያለበለዚያ የለውጥ ሂደት በጣም ይደናቀፋል:: ኑሯችንም አስቸጋሪ ይሆናል:: ብዝሃነታችንን የሚያስተናግድ አስተሳሰብ ካላዳበርን ይበልጥ አስቸጋሪ ይሆናል:: አንዱ የጀመረውን እያፈረሰ፤ ሁሉም ጀማሪ ነኝ ካለ ከባድ ነው:: የኃ/ስላሴ መንግሥት የጀመርኩት እኔነኝ ሲል ነበር:: ደርግም በተመሳሳይ መልኩ የጀመርኩት እኔነኝ ሲል ቆይቶ ኢህአዴግም የጀመርኩት እኔነኝ ሲል ነበር:: የአሁኑን የለውጡን መንግሥት ጊዜው አጭር በመሆኑና ሽግግር ላይ ስላለ ለመውቀስ ቢከብድም የጀመርኩት እኔነኝ ከማለት ይልቅ የእልሁን ጉዳይ በአግባቡ የሚስተናገድበትን መንገድ ማመቻቸት ይሻላል:: ስለዚህ የለውጡ ፈተና እና የፈተና ምንጭ በእኔ እምነት እልህ ነው::
አዲስ ዘመን፡– የህወሓት ፅንፈኛ ቡድን መከላከያን አጥቅቷል:: መንግሥትም ሕግ የማስረከበር እርምጃ ወስዷል:: ይህንን እንዴት አዩት?
ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ፡– በእኔ እምነት መንስኤው እልህ ነው:: ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ ጦርነት ይጠቅማታል ወይ? ብሎ ከተጠየቀ ኢትዮጵያ አሁን ጦርነት አትፈልግም፤ ጦርነት አይጠቅማትም:: ወደዚህ የተገባው በእልህ ነው:: ብዙ ሰው ተጎዳ:: አሁን ትልቁ ፈተና ይህንን ማስታመም ነው:: እንዴት አስታመን ወደተለመደው ሥርዓት እንመለስ የሚለው ፈተና ነው:: በእርግጥ ሕግ ማስከበር ያስፈልጋል:: አንድ ሎሌ ለሁለት ጌታ አይገዛም:: በአንድ አገር ሥርዓት መኖር አለበት:: ያ ሥርዓት ተናግቷል::
የዶሮ ብልት መሆን ይቻላል:: ነገር ግን ሁላችንም ወደ ቀልባችን ተመልሰን ሰፊ ሀገርና ሕዝብ በቂ የተፈጥሮ ሀብት በመጠቀም ወርቅ የምትጥለዋን ዶሮ መጠበቅ ይሻላል:: ጥፋተኛ ማን ነው? የሚለው ውስጥ መግባት አልፈልግም:: የአገር ሽማግሌ በመሆኔ ተዉ እላለሁ:: በእርግጥ አገር ጠባቂ ዘብ በማይሆን መልኩ መጎዳቱ የሚያማርር ነው:: የተጠቁት ብዙ መሆናቸው ብቻ አይደለም፤ አንድ የመከላከያ አባል ላይም ቢሆን ይህ መፈፀሙ የሚኮነን ነው:: ከዚያም በኋላ የመጣው ሁኔታ ሲታይ ብዙ ሰው ተበድሏል:: ያ በደል እንዳይቀጥል ማድረግ ነው::
ጦርነት የእራት ግብዣ አይደለም:: የሰው ሕይወት ያጠፋል:: መፈናቀል ይኖራል:: በሽታ እና ረሃብ አለ:: ምንም ያላጠፋውም ሰው ሊጎዳ የሚችልበት ሁኔታ ይኖራል:: ማንም አልተጎዳም ማለት አይቻልም:: ይህ ጉዳት ለማንም የምንመኘው አይደለም:: ያጠፉት ጥቂት ግለሰቦች ናቸው:: ነገር ግን የሽማግሌ ሥራው ሌላ ጥፋት እንዳይመጣ ያጠፋውንም ቢሆን ማስታረቅ ነው:: ጦርነት ለኢትዮጵያ በምንም መልኩ ተመራጭ አይደለም:: ነገር ግን ያለንበት ስትራቴጂክ ቦታ ከጦርነት ነፃ አያደርገንም:: በመሆኑም የግድ መዘጋጀት አለብን:: የውጭው ጠላት የውስጡንም አካል ይጠቀማል:: በውስጥም መቸገራችን አይቀርም:: ዓለም ወደ አንድ መንደር እየተቀየረች ነው በሚል እኛንም ካልተቀበላችሁን የሚል ወዳጅ መሳይ ጠላትም ይኖራል:: እነዚህን ሁሉ ማየት ያስፈልጋል:: የሚጣላው ማን ነው? የሚጣላን ለምንድን ነው? የሚለውንም ማየት ያስፈልጋል::
አዲስ ዘመን፡– በእርግጥ በጦርነት ብዙ ሕይወት እና ንብረት ይወድማል:: ከዚህ ባሻገር የህወሓት ፅፍኛ ቡድን ድርጊት በአገር ሉአላዊነት ላይ ጥሎት የሄደው አደጋን እንዴት ይገልፁታል?
ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ፡– ቀድሜ እንደገለፅኩት ያለንበት ቦታ የችግር ቀጣና ነው:: ስትራቴጂክ ችግራችን ቦታው ነው:: አልተከፋፈልንም ብንልም ተከፋፍለናል:: ኢትዮጵያ ተገንጥላለች:: ኤርትራ ሄዳለች:: ሱዳንም ቢሆን ዘመዶቻችን ናቸው:: ከእኛ ጋር አንድ አገር መሆን ነበረባቸው:: የአፍሪካ ቀንድ አንድ አገር መሆን ነበረበት:: አውሮፓዎቹ ስንት ዓመት ሲዋጉ ቆይተው አንድ ሆነናል እያሉ ነው:: ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ እንደልብ መንቀሳቀስ ይቻላሉ:: ገንዘባቸው አንድ ነው::
እኛም ከእነርሱ መማር አለብን:: ትልቅ በሆንን ቁጥር ጠንካራ እንሆናለን:: የሚለው አስተሳሰብ ካለ ችግሩ ይቀላል:: የውጭው አካል የሚስብልን ምንድን ነው? እንድንበታተን ነው? ለምን? የሀብት ጉዳይ ነው ወይስ ሌላ የሚለውን መለየት ያስፈልጋል::
ሀብት ከሆነ ካላገኙ አይተኙም:: ኮንጎ ብዙ ሀብት አላት ግን ጦርነት ላይ ናት:: እኛም የምንፋጀው በሀብት ምክንያት ይሆን ብዬ እጠይቃለሁ:: እርሱ ከሆነ ኢትዮጵያ ነፃ አገር በመሆኗ ለአፍሪካዎቹ አዲስ መንገድ በመቅረፅ ተምሳሌት ትሆናለች የሚል ተስፋ ስላለኝ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ ዲፕሎማሲያችንን ተጠቅመን መንገድ ማስያዝ መቻል አለብን እላለሁ:: እልኸኞች ስለሆንን ነፃነታችንን አንተውም::
የአሜሪካውም ሆነ የሌላ አገር ተፅዕኖ ቢኖር ለነፃነታችንና ለክብራችን በመሆኑ መዘጋጀት እንጂ አንንበረከክም:: በድህነትም ቢሆን እንታገላለን:: ጣሊያኖችም ቢሆን መሣሪያ ብቻ ሳይሆን የመርዝ ጪስ እና አውሮፕላን እያላቸው አምስት ዓመት ኢትዮጵያ ውስጥ በሰላም አልኖሩም:: ምንም ቢሆን በጦርነት አያሸንፈንም:: ነገር ግን እርስ በእርስ ያራቁቱናል:: ማራቆቻ መሣሪያው የማህበራዊ ድረ ገፅ ነው:: ይህ ማህበራዊ ድረገፅ ለግለሰብ ነፃነት ቢሰጥም ግዴታ የሌለበት ነውና በዓለም ደረጃ ጂኒው ከጠርሙሱ ወጥቷል::
ዲያስፖራውም ሁለት ልብ ነው:: አገሩን ቢወድም አሜሪካዊ፣ ካናዳዊ ወይም እንግሊዛዊ ነው:: ውጪ ያለውም ኢትዮጵያዊ 10 ሰው አይደለም ወደ 3 ሚሊዮን ሰው ነው:: ይህ በራሱ የችግር ቀዳዳ ሊሆን ይችላል:: ችግሮቻችን እንደበዛ የማሰብ አቅማችንም መዳበር አለበት:: በጣም ብዙ ችግሮች አሉ:: ድሃ ነፃ ሲሆን ሁሉም ለመኮርኮም ይሞክራል:: የመኮርኮሚያ መሣሪያው የተለያየ ይሆናል:: ስለዚህ ራሳችንን ከቻልን እና አቅማችንን ካጎለበትን ኩርኩሙን መከላከል ይቻላል::
አዲስ ዘመን፡– እርሶ እንዳሉት ጂኒው ከጠርሙሱ ወጥቷል:: በማህበራዊ ድረገፁ በተጨማሪ በዋናነት ደግሞ በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ስለሕግ ማስከበር ዘመቻውም ሆነ ስለትግራይ ተጨባጭ ሁኔታ የሚዘገቡ ዘገባዎችን እንዴት ያዩዋቸዋል? ከጀርባቸው ምን አለ?
ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ፡– ዓለም አቀፍ ሚዲያው ላይ የሚስተጋባው ቀድሞ የተዘጋጀ ጉዳይ ነው:: ስለዚህ ብዙ አስገራሚ አይደለም:: አረቦች ‹‹መታኝ እና አለቀሰ ቀድሞኝ ከሰሰ›› ይላሉ:: የህወሓት ፅፍኛ ቡድን ቀድሞም ቢሆን የተዘጋጀበት ነው:: በእኛ በኩል አንድ አገር ነን በሚል ያን ያህል አላሰብነውም:: እነሱ ግን እራሳቸውን እንደአገር እያሰቡ ነበር:: ገና ከአነሳሳቸው አፈጣጠራቸውም ለብቻ አገር እንሆናለን የሚል ስለነበር በደንብ የሚሄዱበትን መንገድ ተዘጋጅተውበታል:: በዓለም አቀፍ ደረጃ የነበራቸው ተሰሚነት ከፍተኛ ነበር:: እነርሱን የሚረዳቸው ግንኙነት እና ገንዘብ ሌሎችም ብዙ ነገሮች አሏቸው:: እኛ ከድህነት ለመውጣት እያሰብን እነርሱ በሄዱበት ርቀት ያህል አስቦ ለመሄድ ጊዜውም አልነበረም:: ነገር ግን የተፈጥሮ ፀጋ ጥሎ አይጥልምና አልወደቅንም::
በህዳሴው ግድብ ድርድር ላይ ትራምፕን ‹‹ተው›› ያሉት ጥቁር የኮንግረስ አባላት ናቸው:: ዛሬም እነርሱን ማንሳት ይቻላል:: አሁንም የመላው የጥቁሮች የነፃነት አርማና ምልክት የሆነችውን ኢትዮጵያን ሊያፈርሷት ነው በሚል ሥርዓት ባለው መልኩ ቢጮህ ብዙ ሰሚ ይኖራል:: ጥቁሮች ደግሞ የነፃነት ምልክት የሆነችው ኢትዮጵያ እንድትፈርስ አይፈልጉም:: አፍሪካውያን መሪዎችም ቢሆኑ የውስጥ ችግሮችን ፍቱ ብለው ይቆጣሉ እንጂ ተገነጣጠሉ አይሉም::
አሁን ጦርነቱ አልፏል:: ተባራሪ ነገሮች ይኖራሉ:: እርሱም በሂደት ይረጋጋል:: ድህነታችን እንጂ ገንዘብ ቢኖር ሕዝቡ በጦርነት ያጣውን ወዲያው መተካት ቢቻል ሕዝቡን ማረጋጋት ከባድ አይሆንም ነበር:: ያንን ማድረግ ባለመቻላችን ልመና ውስጥ ገብተናል:: አሁን እየለመንን ጫናቸውን እንዴት እናስተናግድ የሚለው ላይ ማሰብ ነው:: ነገሩ ‹‹ላም ወለደች እሳት›› ዓይነት ፈተና ነው::
ነገር ግን የአብረሃምም ሆነ የኢብራሂም ልጆች ያሉባት፤ ሃይማኖቶች ሁሉ የሚያከብሯት አገር የነፃነት ምልክቷን እናድን የሚል ዘመቻ ቢጀመር ጥሩ ነው:: አሜሪካን አገር አንዳንድ እንቅስቃሴ አለ:: ነገር ግን እንደተደራጀው ኃይል አይደለም:: እኛ የምንነቃው ካለፈ በኋላ ነው:: ያንን ክፍተት መሙላት አለብን:: ትግራዮች አካላችን ናቸው:: እልሃቸውን የሚያስተናግዱበትን ሁኔታ ማመቻቸት ያስፈልጋል:: ሕዝቡ ላይ ችግር የለም:: በእልህ የሚረብሹት ትንሽ ናቸው:: እነርሱን መገሰፅ፣ ማባበል ይሻላል:: ጎራ ለይቶ ጠላት ናቸው ብሎ ጦርነት ውስጥ መግባቱ ለአገር አይጠቅምም:: በመገናኛ ብዙኃንም ሆነ በማህበራዊ ድረገፅ ድልድይ ሆነው የሚሰሩ መፈጠር አለባቸው:: የነፃነት ተምሳሌት የሆነችውን አገር ልትደመሰስ ነው ብሎ ሁሉም ቢነሳ እልኸኛውም ይረጋጋል ለምን ይህን አደረግኩ ብሎ ይፀፅተዋል::
አዲስ ዘመን፡– የተባበሩት መንግሥታት የውሳኔ ሃሳብን አስመልክቶ ምን ይላሉ? ሩሲያ እና ቻይና መቃወማቸውን እንዴት አዩት?
ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ፡– በዓለም ደረጃ በቀዝቃዛው ጦርነት ጊዜ ሁለት ኃይሎች ስለነበሩ አንዱ ጋር መደበቅ ነበር:: አሁን ላይ ያ ዘመን አለፈ እና አሜሪካን በትራምፕ ጊዜ ብዙ ችግሮች ተነስተውበታል:: አሁንም አዲሱን አስተዳደር አናውቀውም:: በሌላ በኩል የሚገዳደሩ ኃይሎች እየመጡ ነው:: ቻይናም ከድህነት ወጥታ ልዕለ ኃያል አገር እየሆነች ነው:: ራሺያም ብትሆን የምዕራቡ ጫና ስለሚያሰቃያት ወገን ትፈልጋለች፤ ስለዚህ እሱ ላይ ዲፕሎማሲው ቢሰራ፤ አዲስ ወዳጅ መፍጠር ወዳጅ ማስፋት ጥሩ ነው:: ዲፕሎማቲክ ሂደቱ እንደቀጠለ ሕዝባዊ ንቅናቄ ከተፈጠረ አሜሪካ ላይም ቢሆን ጫና ማሳደር ይቻላል:: የግድ ቻይናን እና ሩሲያን ከመጠበቅ ይልቅ አሜሪካም ውስጥ ቢሆን እንቅስቃሴ ቢጀመር ተፅዕኖ መፍጠር ይቻላል:: ኢትዮጵያ ያላትን ፀጋ የበለጠ መጠቀም የነፃነት አርማነቷ አደጋ ውስጥ መሆኑን በማስተጋባት መዳን ይቻላል:: የእነርሱ ወዳጅነት እንደተጠበቀ ቢሆንም በራስ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል::
አዲስ ዘመን፡– የምሥራቅ አፍሪካን የፖለቲካ ሁኔታ እና ግብፅ በፖለቲካው ውስጥ እጇን በስፋት ማስገባቷን በሚመለከት ምን ይላሉ?
ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ፡– ይሄ አዲስ ነገር አይደለም የቆየ ነው:: አዲሱ ነገር የሕዝብ ብዛት እያስፈራራን ነው:: የተፈጥሮ ሀብት እየቀነሰ መምጣቱ ለሁላችንም ስጋት ነው:: ዛሬ ግድብ ብንልም ነገ ውሃውን ልንል የምንችልበት ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል:: ስለዚህ የሕዝብ ብዛት ላይ መነጋገር፤ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምን የበለጠ ማዘመንና የምንጠቀምበትን መላ መፍጠር የግድ ነው:: ኢትዮጵያ በውሃ አጠቃቀም አሁን ያለችበትን ሁኔታ ስንመለከት ከዓለም የመጨረሻዋ ናት:: በተቃራኒው የውሃ ማማ ናት:: ብዙ ተቃራኒ እና የማይመስሉ ነገሮች አሉ:: እነዚህን ነገሮች ማስታረቅ ያስፈልጋል::
ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገሮች ጋር በውሃ ተያይዛለች:: ከሱዳን ጋር አባይ፤ ከኬንያ ጋር በቱርካና ከኤርትራ ጋር በመረብ ከሌሎችም ጋር የጋራ የተፈጥሮ ሀብት አለን:: ተራራ ማማ ላይ በመሆናችን ውሃው እንዳለ ወደ ጎረቤት አገር ይፈሳል:: ነገር ግን እኛ የምንጠቀመው በነፍሰ ወከፍ በቀን 2 ነጥብ 5 ሊትር ውሃ ብቻ ነው:: ሌሎች ደግሞ ይንበሸበሹበታል:: በሌላ በኩል አባይ እስራኤል መድረሱም ሌላው ችግር ነው:: እነዚህን ነገሮች በሙሉ በማየት የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምን አስመልክቶ መነጋገርና አጠቃቀማችንን ማዘመን ያስፈልጋል:: እርሱ ላይ መሰራት አለበት::
ግብፆች አፈር በቃን እስከሚሉ ድረስ ተራራችን ተግጦ አፈር ጠግበዋል:: እኛ በየዓመቱ አፈር እያጣን እነርሱ ነገ ከነገወዲያ አፈሩን ሊሸጡት ይችላሉ:: ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ላይ እስከዛሬ አላሰብንም:: ከአሁን በኋላ ግን እያሰብን ይሆናል ማለት ነው:: ባለፉት 50 ዓመታት ምግብ ከውጭ መምጣቱ ብዙ ጎድቶናል::
ሌላው ጉዳይ ኢጋድ አለ:: በኢጋድ በኩል የሰላም፣ የተፈጥሮ ሀብቱንና የአየር መዛባትን አስመልክቶ ብዙ ይወራል:: ስለዚህ ያ ሥርዓት እንዲይዝ ማድረግ ያስፈልጋል:: ኢጋድ መፈጠሩ አባል አገሮቹ ተነጋግረው ችግር እንዲፈቱ በመሆኑ ጅማሮ አለ:: ነገር ግን ከእነርሱ ውጪ ያሉ አገሮችን ጫና እንዴት እናስተናግዳለን የሚለው ራሱን የቻለ ስትራቴጂ ይጠይቃል:: አገሮች ምን ይፈልጋሉ:: የሚቆጣጠሩን በምንድን ነው? የሚለውን መመካከር እና ማወቅ ይጠይቃል::
አዲስ ዘመን፡– በእርግጥ ኢጋድ መስራት አለበት:: ነገር ግን ግብፅ በተለይ በምሥራቅ አፍሪካ እጇን በስፋት ማስገባቷን በሚመለከት ምን ይላሉ?
ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ፡– እኛ ለአባይ ሩቅ ነን:: አባይን አስመልክቶ ከመዝፈን ውጪ የምንጠቀምበት በጣም ጥቂት ነው:: የፈውስ መድኃኒት ነው ፀበል ነው ብለን እንጠቀምበት ይሆናል:: ከዚያ ውጪ ሸለቆ ሲገባ ይርቀናል:: አባይ ከችግር ውጪ ምንም አላተረፈልንም ነበር:: ዝናብ ሲዘንብ በወንዙ ምክንያት ሰዎች አይገናኙም ነበር::
እነርሱ አባይን በቅርበት ያዩታል፤ ይሳፈሩበታል፤ ይዋኙበታል:: ሕይወታቸው ነው:: አሁን ደግሞ ጊዜው ለማገዶነት እንጨትን ሳይሆን ኃይልን መጠቀም አስፈለገ:: አሁን ኢትዮጵያ መጠቀም አለብኝ አለች:: ለ100 ሚሊዮን ሕዝብ የማገዶ እንጨት ማቅረብ አይቻልም:: ስለዚህ ታዳሽ ኃይል ያስፈልጋል:: ታዳሽ ኃይል ደግሞ በቅርብ አለ:: እኛ ከግብፅ ጋር ተመካክረን እንጠቀም አልን:: እነርሱ ግን በምንም መልክ በጋራ መጠቀሙ አይጥማቸውም:: የለመዱትን ማግኘት ብቻ ይፈልጋሉ:: ምንም ቢባል ግብፆች ምክንያታዊነት አይገባቸውም::
እነርሱ ‹‹የፈጣሪ ፀጋ ነው:: ከፈርኦን ጀምሮ የሚታወቅ ነው:: አሳልፈን ለእስራኤል ሰጥተናል ምንም አንደራደርም›› ባዮች ናቸው:: ከእኛ የሚጠበቀው የምንችለውን መስራት ብቻ ነው:: ግብፆች የሚሰሩት ለእነርሱ የሚያሳምን ነው:: እኛ ግን ሥራችንን አናስተጓጉልም:: ግብፅን ለመጉዳት አናስብም:: ግብፅን እስካልጎዳን ድረስ ተጠያቂ አንሆንም:: ነገር ግን የተፈጥሮ ሀብትን በሥርዓት ካልተጠቀምን አደጋ አለው:: ይህ በዓለም ደረጃ ብዙ ውይይት እየተካሄደበት ነው::
ኢትዮጵያ ዛፎቿን ሁሉ አጥፍታ ብትቀመጥ፤ ግብፅ ውሃ ታጣለች ኢትዮጵያም ድሃ ትሆናለች ማለት ይቻላል:: ውሃው እንዲኖር ዛፍ ያስፈልጋል፤ ዛፍ እንዳይጨፈጨፍ ታዳሽ ኃይል መጠቀም ያስፈልጋል:: ለታዳሽ ኃይል ኢትዮጵያ ግድቡን መገንባት አለባት:: ቢረዱን ጥሩ ነው:: ባይረዱንም ግን መቀጠላችን አይቀርም::
ከሱዳን ጋር ተያይዞ ቀድሞ እንደገለፅኩት ወታደራዊ አገዛዝ ነው:: ወታደር ለጦርነት ቅርብ ነው:: ነገር ግን ጦርነቱ ካለቀ በኋላ ማን ምን ይጠቀማል? ብለን ብንነሳ ሕይወት ይጠፋል፤ ንብረት ይወድማል፤ ሱዳንም ሆነች ኢትዮጵያ በጦርነቱ ምክንያት የበለጠ ድሃ ይሆናሉ:: አሁን ደግሞ ከሱዳን መልካም ዜና እየተሰማ ነው:: የሱዳን ሕዝብ ወደ ጦርነት አታስገቡን በማለት ለተቃውሞ መውጣቱ ተሰምቷል:: ይህ ጥሩ ነው:: እኛ ወሰናችንን በሥርዓቱ እንወስን:: ግብፆቹ ግድቡ ካለቀ በኋላ ይተነፍሳሉ:: እዚያ እስኪደርስ እሰጣገባው ይቀጥላል::
አዲስ ዘመን፡– የኢትዮጵያ መንግሥት አካባቢው የግጭት ቀጣና እንዳይሆን ምን መስራት አለበት?
ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ፡– በተቻለ አቅም ከጦርነት መታቀብ ጥሩ ነው:: ነገር ግን ጦርነት ከመጣ ይቀጥላል:: የሞተው ሞቶ የሚሆነው ይሆናል:: ያው ጦርነት በአጭር ጊዜ ማለቅ እንደሚችል በቅርቡ ታይቷል:: ከሱዳን ጋርም የሚካሄደው ጦርነት ቢኖር፤ በአጭር ጊዜ ያልቃል:: ነገር ግን አጠያያቂው ነገር ይጠቅማል ወይ? የሚለው ነው:: እዚያ ላይ ምሁራንም ማሰብ አለባቸው:: በዚም በኩል ሁሉም ላለመጎዳዳት ቀልባቸውን መሰብሰብ አለባቸው::
አዲስ ዘመን፡– ስለነበረን ቆይታ በዝግጅት ክፍሉ ስም በጣም አመሰግናለሁ::
ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ፡– እኔም በጣም አመሰግናለሁ::
አዲስ ዘመን መጋቢት 7/2013