ከመኰንን አበበ ተሰማ
የኢትዮጵያን ጥልቅ ምስጢር ካለፈጣሪ አምላክ በስተቀር ማንም ፍጡር አጠናቆ አያውቅም፤ አይደርስበትም፡፡
ኢትዮጵያ ከዓለም ሀገራት ነጭና ጥቁር ሳይባል በተለይም ከጥቁር ሀገራት በቅኝ ያልተያዘች ንጹህ ሀገር ናት፡፡ አሜሪካን የሚያክል የዘመናችን ግዙፍና የተንኮል ማህደር፤ የምስረታው ዕድሜ አነስተኛ የሆነው ሀገር በቅኝ ከሁለት መቶ ዓመታት በላይ ስትገዛ፤ ኢትዮጵያ የራሷን አስተዳደር የዘረጋችና በነፃነት የኖረች ሀገር ናት፡፡ ምዕራባውያንን ይህም ይከነክናቸዋል ያስቆጣቸዋል፡፡ኢትዮጵያ በየጊዜው በሚመጡባት ጠላቶች ተሸንፋ አታውቅም፡፡
ኢትዮጵያ የጀግኖች ሀገር ናት ብዙውን ባንጠቅስም የዓድዋ ድል ብቻ በቂ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ያሳየችውና ያገኘችው የአትሌቲክስ ድልም የዚሁ አንድ ማሳያ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በራሷ ፊደል የመጠቀምና የራሷ የሆነ የጽሑፍ ሥነሥርዓት ግኝት አላት፡፡ – ኢትዮጵያ የራሷ ቀመርና ግኝት የሆነ ከሌሎች የተለየ ውብ የዘመን አቆጣጠር አላት፡፡
– ኢትዮጵያ በምርት አመራረቷና ዘዴዋ ሌላው ያላመረተውን ያመረተች ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ ከሣይንስ ቀመርና ግኝት ያልተናነሰ የባህል ጤና መጠበቂያ መድሐኒቶችን ትቀምማለች፤ ተሠርቶበት የማዳን ውጤትም ታይቶበታል፡፡ – ኢትዮጵያ የብዙ ሃይማኖቶች ሀገር ከመሆኗም በሃይማኖቶች ውስጥም ብዙ ምስጢራት አሏት ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡ -ኢትዮጵያ የሊቃውንትና ሊህቃን አገር ናት በተለይ በሊቃውንት ዘንድ ብዙ ምስጢራት ይገኛሉ፡፡
-ኢትዮጵያ ዘመን አመጣሽ፤ ጊዜ ዘራሽ ትውልድ በወያኔ አባትነት በምዕራባያውያን አያትነት ጉትጉታ ባህልና ወጓን ሊያበላሹ ብዙ ቢታትሩም ባህሏን ጠብቃ እየኖረች ያለች ሀገር ነች፡፡ ከሰማንያ በላይ ብሔርና ጐሣ እርስ በእርስ ተደጋግፎ ተቻችሎ ተዋህዶ፣ በስምምነት፣ የሚኖሩባት ሀገር ነበረች፡፡ – ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ ሀገር ናት ይህ ትልቁ የምዕራባውያን ሀገራት ራስ ምታት በሽታ ነው፡፡ -ኢትዮጵያ መልከአ ምድር አቀማመጧና አየር ጠባይዋ ደጋ ቁር በጣም ቀዝቃዛ ወይን፣ ደጋ፣ ቆላና በረሃ፣ ጋራና ሜዳ ሽንተረርና ሸለቆ፣ ጫካ ያላት ሀገር ናት፡፡
ኢትዮጵያ የተለያዩ የዱርና የቤት እንስሳት አዕዋፋት ለጉብኝት የሚመቹና ለዓይን ስበት ያላቸው ፍጥረታት የሞሉባት ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ በዓመት ውስጥ የተለያዩ አራት የወቅቶች ጊዜ አላት፡፡ በጋ፣ ክረምት በልግና መኸር፣ ጸደይ በሌሎች ሀገራት ተሟልተው የማይገኙ፣ ኢትዮጵያ ከሌሎች በተለየ 13 የፀሐይ ወራት አላት፡፡ በዚህንም ወራት ፀሐይና ዝናብ ይፈራረቁበታል፡፡ ሌሎች ሀገራት የዚህን ፀጋ አያገኙም፡፡
ኢትዮጵያ የብዙ ወንዝ ሀገር ነች፡፡ በዓለም ረጅሙ ወንዝ መነሻም ኢትዮጵያ ናት፡፡ ኢትዮጵያ የሕዝቦቿ ቀለም በዓለም የሚደነቁ ልዩ ውብ የሆነ የተፈጥሮ ቅብ ወዛማ ቀይ ጥቁር፣ ጠይም፣ ቢጫ፣ ቀይ ዳማ የሆነ ተፈጥሮ የሰጣትና ያደላት የቆንጆዎች ሀገር ናት፡፡ ኢትዮጵያ ሰው ሠራሽ ሳይሆን የተፈጥሮ ዴሞክራሲም ነበራት፡፡ በመሪዎች የዕኩል መስተዳደር ፍላጐት ሲኖር፣ በተከታዮቻቸውና ጋሻ ጃግሬዎች የሥልጣን ሹክቻና የጥቅም ስግብግብነት ምክንያት አንዳንዴ ተበላሽቶ ይገኛል እንጂ፡፡ እዚህ ላይ የገዳ ሥርዓትንና ሌሎች ከ130 በላይ የዕርቅ ሥርዓቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡
ኢትዮጵያ የዓለም ሀገራት በተለይ ምዕራባውያን በከፋ ሁኔታ የሚረባረቡባት ይህ ሁሉ የበላይነት ምስጢር ስለአላት እና በብዙ ነገር ለምን በለጠችን ለምን ልዩ ሆነች የማለትም አንዱ ፈተናዋና የጫናዋ መነሻ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያ ላይ የችግር ክምር ይጭኑባታል የውሸት ናዳ ይለቁባታል ይጠሉታል ይናደዱበታል፣ ያስጨንቋታል፡፡
በየጊዜው ዓለም ላይ በሚታዩት ተለዋዋጭ ሁኔታዎችና ድርጊቶች፤ በአሁኑ ጊዜ የዓለም ሽብርተኞች የሚባሉት፤ እነ አልቃይዳ፤ አልሸባብ፣ ኢዝቦላ፣ ቦኮሃራም፣ እና ሌሎችም ይሁኑ፤ ተራው ግን የአሜሪካና አውሮፓ ፍርደ ገምድል መሪዎችና ጋሻ ጃግሬዎቻቸው ሆኖ ይታያል፡፡
በዚህ ዘመናችን እንደ ዓለም ድንቃ ድንቅ ጎልቶ የሚታየውና በዓለም ላይ እስካሁን በአገራት ላይ በአንድ ወቅት ያልተፈጸመ ግፍ የ2ኛ ዓለም ጦርነትና ሁከት እንኳን የማይመጥነው የዓለም ሀገራት በተለይም ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ እንደ ከባድ ክረምት የበረዶ ውርጅብኝ በመጥፎ አመለካከት በከባድ ጫና በውሽት የዜና አዋጅ የመረባረባቸው ምስጢር ከኢትዮጵያ አልደፈርም ባይነት ጋር ተያያዘ ነው፡፡ ይህም ያልፋል ብሏል ጸሐፊው፤ ጉድ አንድ ሰሞን ነው ብሏል ዘፋኙም፡፡ ግን ይህ ጊዜ ያልፍና ያስተዛዝበን ይሆናል፡፡
የአውሮፓ ሀገራትና አሜሪካ የህሊና ቁስለኞች ናቸው፤ በአፍሪካና በተቀሩት የዓለም ሀገራት በሰሩት ደባና በአፈሰሱት የሰው ልጅ ደም የተነሳ ሁልጊዜ የተሳከረ አካሄድ ይታይባቸዋል፤ መልካም የሰሩ መሰሏቸው፣ ውሸታሙን በመደገፍ እውነተኛውን በመጣል የሰከረ አካሄዳቸውን ቀጥለውበታል፡፡
ምዕራባውያን በተለይ አሜሪካ እንግሊዝ፣ ፈረንሣይ እና አንዳንድ የምሥራቅ አውሮፓ ሀገራት ኢትዮጵያ ከባድ የተፈጥሮ ችግር እንደ ደረሰባት ያህል የሃሳብ ወረራ እና የውሸት ውርጅብኝ ወቀሳ እያደረጉባት ነው፡፡ ኢትዮጵያን ሊቦጫጭቋት የተመኙ ብዙ ጠላቶች ቀርበው ይታያሉ፡፡ ችግርም እየፈጠሩብን ነው፡፡
በነጭ ወራሪ ጠላት በ1888 ዓ.ም ተሞከረች በ1928 ዓ.ም እንደገና ተሞከረች፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጥቁር ወራሪ ጠላት በ1969 ዓ.ም ተሞከረች እንደገና በ1991 ዓ.ም ተሞከረች፡፡ ኢትዮጵያ በምዕራባውያን ፕሮፓጋንዳ ወረራ በ2013 ዓ.ም ተሞከረች ሁሉም አልተሣካላቸውም፤ ወደፊትም ለማንም አይሣካም፡፡
ምዕራባውያን በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ ላይ በመጥፎና ተንኮል መረባረብ ወቅታዊ ዕብደታቸውንና ትዕቢታቸውን የሚያሣይ ነው፡፡ በተለይ ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ ምርጫ ውስጥ በንቃት በመሳተፍ የአሁኑን ፕሬዚዳንት በማስመረጥ ረገድ የበኩላቸውን ሚና ተጫውተዋል፡፡ ሆኖም ግን አሜሪካ በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ውስጥ እጇን በማስገባት ያሻትን ለማድረግ በመቋመጥ ላይ ትገኛለች፡ ፡አንድ ጊዜ የኤርትራ ሰራዊት ይውጣ በሌላም ጊዜ የአማራ ልዩ ኃይል ቦታውን ይልቀቅ በማለት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ሲዳፈሩ ይታያሉ፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም የዓለም አሻንጉሊት ሆኖ አጫዋች ከመሆን ያለፈ ዓለምን የረዳው ሁኔታ የለም ወይም አልቢትሮ ሆኖ አገራትን ከማጋጠም በስተቀር ለተጠቁና ዕውነተኛ ፍርድ ለሚጠይቁት ሀገራት ምንም ፋይዳ አልሰጠም:: ያለመኖሩ ይሻላል፡፡
በአጠቃላይ የሰው የውሸት ፍርድ እየሣሣ ይሄዳል፡፡ የአምላክ ዕውነተኛ ፍርድ ግን እየጠነከረ ይሄዳል፡፡ በዓለም ላይ ሃሰት እየፋፋ ቢገኝም በመጨረሻ ዕውነት አሸናፊነትን ታገኛለች፡፡ ኢትዮጵያም እንደሁልጊዜው ሁሉ ታሸንፋለች፡፡
አዲስ ዘመን መጋቢት 7/2013 ዓ.ም