አስናቀ ፀጋዬ
በኢትዮጵያ የማእድን ዘርፉ የሚጠበቅበትን ኢኮኖሚያዊ አስተዋፅኦ እያበረከተ እንዳልሆነ በተለያዩ ግዜያት የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ። የማእድን ዘርፉ የኢትዮጵያን ግብርና መር ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ እንዲያሸጋግር የታለመ ቢሆንም በተለይ ባለፉት አመታት ከዘርፉ የወጪ ንግድ የሚገኘው ገቢ እየቀነሰ መጥቷል።
ከቅርብ አመታት ወዲህ ደግሞ ዘርፉን ለማሳደግ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ቢገኙም ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ከማሳደግ አኳያ አሁንም አርኪ ውጤት አልተገኘም። ለዚህም በሀገሪቱ የሚገኙ ማእድናትን በጥናት ለይቶ የማወቅና የታወቁትንም ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውሉ የማድረግ ችግሮች መሆናቸው በዘርፉ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ይጠቀሳል።
በሀገሪቱ በርካታ የማእድን ሃብቶች እንዳሉ የሚገመት ቢሆንም ሃብቱ በትክክል በጥናት ባለመረጋጋጡ ጥቅም ላይ ማዋል አልተቻለም። የማእድን ሃብት በስፋት ይገኝባቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ የሀገሪቱ ክልሎች ውስጥ አንዱ በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል የሚገኘው የደቡብ ኦሞ ዞን ቢሆንም በቂ ጥናት ባለመደረጉ ሃብቱን ጥቅም ላይ ማዋል እንዳልተቻለ ከክልሉ ማእድንና ኢነርጂ ኤጀንሲ የወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የደቡብ ኦሞ ዞን ውሃ፣ማእድንና ኢነርጂ መምሪያ ሃላፊ አቶ ወርቅነህ ቀርማ እንደሚገልፁት በዞኑ በጥናት የተረጋገጡ አጌት፣በሪሊየምና አማዞናይት ማእድናት ይገኛሉ። የአጌት ማእድን ሜትር አካባቢ እንዲሁም ማሌ ወረዳ ኮይዴ አካባቢ ይገኛል። አማዞናይትና ብሪሊየም የተሰኙት ማእድናት ደግሞ በማሌ ወረዳ ኤርቦ ቀበሌና ጎሎ ቀበሌዎች ይገኛሉ።
ይሁንና የማእድናቱን የክምችት ሁኔታ ይበልጥ ለማረጋገጥ ዝርዝር ጥናቶችን ማካሄድ ያስፈልጋል። በማሌ ወረዳ ኤርቦ ቀበሌ እንደሚገኝ የታወቀው በርሊየም ማእድንም ወደ ማምረት ሂደት እየተገባበት ነው። አንድ ኩባንያም ማእድኑን በማምረት ወደ ውጪ ሀገር ለመላክ ፍላጎት አሳይቷል። ሆኖም ሌሎቹ ማእድናት በቂ ጥናት ስላልተደረገባቸው ጥቅም ላይ እየዋሉ አይደለም።
እንደ ሃላፊው ገለፃ በዞኑ ብሪሊየም፣አጌትና አማዞናይት ማእድናት እንዳሉ ቢታወቅም አጠቃላይ ያለው የማእድን ሃብት ግን በጥናት ተረጋግጦ አልታወቀም። የፌደራል መንግስትም በዚህ ዓመት በዞኑ በሚገኙ አስር ወረዳዎች ላይ ዝርዝር ጥናት ለማካሄድ ፕሮግራም ቢይዝም እስካሁን ድረስ ወደተግባር አልገባም።
በዞኑ እምቅ የማእድን ሃብት እንዳለ ቢታወቅም እስካሁን ድረስ ዝርዝር ጥናት ባለመካሄዱ ማእድኑን ጥቅም ላይ ማዋል አልተቻለም። የዞኑ ውሃ፣ ማእድንና ኢነርጂ መምሪያም በዘርፉ የሰለጠነ ባለሙያ፣ በቂ ሃብትና ጥናት ለማጥናት የሚያስችል በቂ መሳሪያ የሌለው በመሆኑ የዞኑን ማእድን ሃብት በጥልቀት አጥንቶ ማወቅ አልቻለም።
በመሆኑም መምሪያው በቀጣይ ዓመት ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት በዞኑ ያሉ የማእድን እምቅ ሃብቶችን የመጠቀም ሃሳብ አለው። ለዚህም የተለያዩ ዝግጅቶችን እያከናወነ ይገኛል። ጥናት ላይ በማተኮርም በጥናቱ ውጤት መሰረት ወደማምረት ለመግባት አቅዷል።
በዞኑ የብረት ማእድን ክምችት በሰላማጎ ወረዳ ዴሮ በሚባል አካባቢ እንዳለም የሚነገር ሲሆን ዝርዝር ጥናት እየተካሄደበት ይገኛል። ዝርዝር ጥናቱ ከተጠናቀቀ በኋላም ወደማምረት ይገባበታል ተብሎ ይጠበቃል።
ሃላፊው እንደሚሉት በዞኑ በርካታ የማእድን ሃብቶች እንዳሉና ነዳጅም ጭምር እንደሚገኝ ቢታሰብም ዝርዝር ጥናት ባለመደረጉ በተለይ የከበሩ ማእድናትን አውጥቶ በስፋት ጥቅም ላይ ማዋል አልተቻለም። በአሁኑ ግዜ ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉት ማእድናትም በአብዛኛው ለኮንስትራክሽን ግብአትነት የሚውሉ አሸዋና ድንጋይ ናቸው።
የዞኑ ውሃ፣ማእድንና ኢነርጂ መምሪያም በዚሁ የማእድን ጥናት ላይ አተኩሮ እየሰራ ይገኛል። ጥናት የማጥናት ፍላጎት ያለው ማንኛውም አካልም ሆነ ባለሞያ ካለም ገብቶ እንዲያጠና ይጋብዛል።
የኮንስትራክሽን ማእድናት በተለይ አሸዋና ድንጋይ ከሁለት ወረዳዎች በስተቀር በሁሉም የዞኑ አካባቢዎች ላይ የሚገኙ ሲሆን በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ ያሉት ግን በከተማ አካባቢዎች ያሉት ናቸው። በእነዚህ የኮንስትራክሽን ማእድናት ማውጫ አካባቢዎች ላይም ወጣቶች በማህበር ተደራጅተው እየሰሩባቸው ይገኛሉ።
በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ሰፊ የማእድን ሃብት ክምችት እንዳለ በተደጋጋሚ ቢነገርም ክምችቱ በጥናት ተለይቶ ባለመረጋገጡ ጥቅም ለይ ማዋል እንዳልተቻለ ከዚህ ቀደም አዲስ ዘመን በሰራቸው የተለያዩ ዘገባዎች ለማረጋገጥ ተችሏል።
አዲስ ዘመን መጋቢት 6/2013