ተገኝ ብሩ
ጎበዝ ወዴት ይሆን እየሄድን ነው? እ… ምን? ወደ ቤት፤አልያም ወደ ስራ ነው ያላችሁኝ? ኧረ ወገን እኔ ወዲህ ነኝ። እየሄዳችሁ ስላላችሁበት ቦታ አልያም መድረሻችሁ አይደለም ጥያቄዬ። አጠቃላይ ሁኔታችን ነው፣ስርዓትና ህግ አተገባበራችን፣ ሰብዓዊ ግንባታችንና አጠቃላይ ማህበረሰባዊ ገፅታችን ላይ ነው ትኩረቴ።
የእኛነታችን መለያ የሁኔታችን መቀያየር አንድ ማሳያን ጠቅሼ ወዴት እየተጓዝን እንደሆነ እናንተንም እራሴንም መጠየቅ ፈለኩ። ታክሲዎች ናቸው የዛሬ ወጌ መዳረሻ። የሚያመላልሱን እነሱ አይደሉ፤ እኛም በሀሳብ እንመላለስባቸዋለን። አንዳንዴ የራሳችንን ስህተት እንላመደውና ስህተታችን ትክክል ይመስለናል። መዛነፋችንን ፍፁምነት መሳታችንን ደግምሞ ግብ እናደርገዋለን።ለዚያም ነው የሰሞኑ የታክሲ አገልግሎት ሰጪዎች ሁናቴ ለመታዘብ ያበቃኝን ጉዳይ ማንሳቴ።
እኔ ምለው ጓዶች! ታክሲዎች ግን ህግ ተላለፉብን ነው ወይስ እነሱ ህግን ጣሱ ነው የሚባሉት። ለነገሩ መጋጨት ስለሚያበዙ ህግን ገጩ ቢባል ነው የሚሻል። ሰሞኑን እንዳደረጉት በድሎ ማልቀስ፤ተሳፋሪን እየቀጡ ቆይተው ተቀጣን ዘራፍ ማለታቸው አያስገርምም? በሞቴ ወገን። እስኪ ወደ ሁዋላ መለስ ብላችሁ የታክሲ ላይ ሁነትን አጢኑ። ከእነሱ በላይ እዚች ከተማ ላይ ህግን የሚጥስና እንዳሻው የሚሆን ማን አለ? እንጃ።
አንድ ማሳያ ገጠመኜን ላንሳና ላውጋችሁ ወዳጆቼ። አንድ ጉዳይ ገጥሞኝ ጓደኛዬ ቤት አምሽቼ ወደ ቤቴ ለመሄድ ወጣሁ። ሰአቱ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ከ20 ደቂቃን ያመለክታል።ድሮ ቢሆን አዲስ አበባ ላይ ገና ጊዜ ነው። ዛሬ ላይ ግን ሰው ሁሉ ፀሀዩ ለአይን ያዝ ማድረግ ሲጀምር ጀምበርዋ ለመጥለቅ ስትቃረብ ወደቤቱ ይተማል። ይሄኔ ጭር ያለ ጎዳናና ቀን በመንገድ መዘጋጋት ታስረው የዋሉ መኪኖች የቀኑን እስራት ቂም ለመወጣት በሚመስል መልኩ ሲከንፉ ነው የሚታዩት።
ቄራ አካባቢ ነኝ። ታክሲ እየጠበቅሁ። ከአፍታ በኋላ ታክሲው እኔ ወዳለሁበት ተጠግቶ “አጎና አጎና” ብሎ መጣራትና መጫን ጀመረ ። ለእግር መንገድ ለዚያውም በምሽት ጥሩ ስላልሆነ እንጂ ከቄራ አጎና ግማሽ ፌርማታ ነው። ለምን ላንቻ አትጭንም? ብዬ ጠየኩት። ካልፈለክ ተወው ፤ላንቻ አልደርስም አለኝ። አማራጭ ስለሌኝ እኔም ወደ በሩ ለመሳፈር ተጠጋሁ። ረዳቱ ወደ በር ለተጠጋው ተሳፋሪ ጠጋ ብሎ “5 ብር ነው አውቃችሁ ግቡ” ሲል ሰማሁት።
ወይ ጉድ በትክክለኛው ታሪፍ ከቄራ ላንቻ 2 ብር ብቻ ነው። ግማሹን ተጉዞ ሊጥለን ነው “5” ብር እያለ ያለው። ገብቼ መብቴን አስከብራለሁ ብዬ ገባሁ። ከኋላ ወንበር ነበር የጠቀመጥኩት ተሳፋሪው ያለምንም ማመንታት የተጠየቀውን ይከፍላል። አንድም ሰው ለምን ከታሪፍ በላይ ያለ የለም። ተለምዷል ማለት ነው አልኩ በልቤ። እኔ ከተቀመጥኩበት ወንበር ፊት ላይ አንዱ “ከታሪፍ በላይ” አልከፍልም የሚል ቅሬታ ሲያቀርብ በሱ ተፅናናሁ እንጂ በሌሎች ተሳፋሪዎች አዝኜ ነበር። የሚያሳዝነው ግን ከረዳቱ ይልቅ የጮኸበት ከፊት የነበሩ ተሳፋሪዎች ናቸው።
ተሳፋሪዎች መብታችን ማለታቸው ሳያንስ እነሱ የተነፈጉትን መብት ሌላው ሲጠይቅ “ተስማምተህ አይደል እንዴ የገባኸው ምን ትጨቃጨቃለህ” እያሉ የረዳትና ሹፌሩ ጠበቃ ሆነው አረፉት።
ወይ ጉድ እኛ ማለት እንዲህ መገለጥ ጀምረናል። የሚያገባንን ባንጠይቅ በማያገባን ባንገባ ግን ምን አለ? ወገን ወዴት ነው ግን ጉዟችን? አንዴ ቆም ብለን እራሳችንን ማየትማ ይገባናል። እናም ሰውየው ሁሉም ሲረባረብበት እኔ ዝም ብዬ ማለፍ አቃተኝ። እኔም እንደሱ ነኝ ከታሪፍ በላይ ለዚያውም ግማሽ ፌርማታ ነው እሄዳለሁ ያልከው አልከፍልም፤ ተሳፋሪዎች ስለራሳችሁ ብቻ አውሩ፤ ሰው መብቱን ሲጠይቅ አትጋፉ” አልኩና የራሴን ድርሻ በታሪፉ መሰረት አውጥቼ ሰጠሁት።ረዳቱ አያያዜን አይቶ መሰለኝ አጉተምትሞ ዝም አለ። ከሁለታችን በቀር ሁሉም የተጠየቀውን ከፈለ።
የሚገርመው ግን ላንቻ አልሄድም ያለው ታክሲ አጎና ጋር ሁሉንም ተሳፋሪ አራግፎ በድጋሚ ላንቻ ላንቻ “5” ብር ማለት ጀመረ። ተመሳሳይ ንትርክና ሙግት ሊገጥመኝ ነው። በትክክለኛው እሱ 10 ብር እየተቀበለበት ያለው መንገድ 2 ብር ነው። 8 ብር ከአንድ ሰው ላይ ትርፍ መቀበሉ ምን ያህል ህገወጥነት እንዳለ ያሳያል። ደግሞ የተሳፋሪው መብት አለማስከበር ሳያንስ መብቱን ለማስከበር የሚነሳውን ሰው አትናገር ብሎ ያልተገባ መናገር አይይ… ጎበዝ ምን ሆነናል።
የዚያን ቀኑን የታክሲዎች ሰሞንኛ ህገወጥነት እያሰብኩ እቤቴ ደረስኩ። በንጋታው የሰማሁት እና ያየሁት ግን “እራሱ በድሎ እራሱ አለቀሰ ፤ ባሉቧልታ ፈረስ አገር አዳረሰ ” የሚለውን ዜማ ይሁን ተረት አስታወሰኝ። ታክሲዎች ተደጋጋሚ ክስ ተመሰረተብን ትራፊክ ገላመጠን ብለው አድማ ሊመቱ ሞከሩ።አያችሁ ወገን እዚህ ላይ ነው ወዴት እየተጓዝን ነው ማለቴ።
ተሳፋሪውን በሚፈልጉት መልኩ እያንገላቱ ታሪፍ እንዳናውቅ ተመን እንዳንለይ በፈለጉት ዋጋ ደራርበው ጭነውን በፈለጉት መንገድ አስኪደው ያሻቸው ቦታ የሚጥሉን ታክሲዎች አልፎ አልፎ ለምን ተገቢ ያልሆነ ስራ ላይ ተገኛችሁ ተብለው ሲጠየቁ ለምን ተጠየቅን ብለው ለአመፃ መነሳታቸው አይገርምም?
ለነገሩ ይሄ በየቦታው ሲያንገላቱት የነበረው ተሳፋሪ አቂሞባቸው ኑሮ አመፁ፤ አንሰራም አሉ መባሉን ሲሰማ ሲያፌዝባቸው ዋለ አሉ። “ተዋቸው ሲርባቸው ከሰዓት በራሳቸው ጊዜ ይወጣሉ” እያለ። ተሳፋሪ ላይ ሙድ ሲይዙ የነበሩት ታክሲዎች በተራቸው ሙድ ሲያዝባቸው ተዋለ። ወይኔ ሲያሳዝኑ የምርም ተሳፋሪው ያለው አልቀረም። ከሰዓት ላይ በራሳቸው ወጥተው አገልግሎት ሳይሆን ሰውን ማንገላታቱን ቀጥለውበታል።
በነገራችን ላይ በከተማችን ላይ ያሉ አማራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎችና አውቶቡሶች ተግባር የሚደነቅ ነበር።ለተሳፋሪው እየሰጡ ያሉት አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻለ ያለና የሚደነቅም ነው። ያኔ ታክሲዎች በራሳቸው ህግ ጥሰት ታውረው ካላመፅን ብለው በራሳቸው ላይ ያመፁበት ቀን የታክሲዎች ጠቀሜታ እስኪረሳ ድረስ ሽር እያሉ እንደውም ጎዳናው ሰፍቷቸው መንገዱ ነፃ ሆኖላቸው ህዝቡን በተቀላጠፈ መልኩ ሲያገለግሉ ነበር የዋሉት።
አዲስ ዘመን መጋቢት 5 ቀን 2013 ዓ.ም