ተወዳጁ ጋዜጠኛ

ጋዜጠኝነት ከባድ ኃላፊነትን የተሸከመ ባለአራት ዓይና ሙያተኛ ይፈልጋል። እንደ ጋዜጠኛ ወይም ዘጋቢ ያገኘውን መረጃ እውነትነቱንና ፍትሃዊነቱን ደግሞ ደጋግሞ ማጣራትና መመርመር ይገባል። የሰማውን፣ ያየውንና ያነበበውን ሁሉ እንደትክክለኛ መረጃ ከወሰደው በመጨረሻ የከፋ ስህተት ሊፈጥር ይችላል። ጋዜጠኝነት በሥነ ምግባር የሚገዛና ኃላፊነትን የሚጠይቅ ጠበቅ ያለ ብርቱ ሥራ ነው።

ውድ አንባቢያን ዛሬ ጋዜጠኝነትን ማንሳታችን ያለ ምክንያት አይደለም። በተሰማሩበት ሙያ ወይም ኃላፊነት ያለመታከት ለሀገርና ሕዝብ የሠሩ ባለውለታዎች ታሪካቸው ቀርቦ በሚመሰገኑበት በዚህ የባለውለታዎቻችን አምድ ሥራዎቹን አንስተን የምናመሰግነው አንጋፋውን የሬዲዮ ጋዜጠኛና ደራሲ ዜናነህ መኮንንን በመሆኑ ነው።

ዜናነህ ወደዚህች ምድር የመጣው በ1945 ዓ.ም ጎንደር አዘዞ በምትባል ከተማ ውስጥ መስከረም ወር ላይ አደይ አበባና አዲስ ዓመቱን ተከትሎ ነበር። ውልደቱ አዘዞ ይሁን እንጂ በቤተሰቦቹ የሥራ ፀባይ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ የመጣው በልጅነቱ ነበር። በመቀጠልም ወደ ጂማ ሄዶ “ቆጪ” ሰፈር ይኖሩና ፃዲቁ ዮሐንስ ይማር ነበር።

ጂማ እስከ 3ተኛ ክፍል ድረስ ከተማረ በኋላ ወደ ጎንደር በመሄድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ጨርሶ የሁለተኛውንም አጋምሷል። ከዚያም ወደ ድሬዳዋ በመጨረሻም ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ የሙዚቃ ፍቅር ስለነበረው በ60ዎቹ ገደማ ያሬድ ት/ቤት ሙዚቃን ለመማር ገብቶም ነበር። የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱንም የጨረሰው እየሠራ በመማር ነበር።

የጋዜጠኝነት ሕይወት

ዜናነህ ለመጀመሪያ ጊዜ ፖለቲካን የተለማመደው በጄኔራል ዊንጌት የ2ተኛው ዙር የፖለቲካ ተማሪ ሳለ ነበር። በዚሁ አጋጣሚ በጣም ተከራካሪ እና ላመነበት ሟች መሆኑን ያዩ ወዳጆቹ ማስታወቂያ ሚኒስቴር እንዲቀጠር ይገፋፉት ነበር። ከዚያ 1968 ገደማ በሬዲዮ ሪፖርተርነት ተቀጠረ።

የመጀመሪያው ንባቡ ‹‹የአብዮት መድረክ›› የሚባል የኢህአፓ እና የሜኤሶን የግጭት ሁኔታ የሚገልፅ በርካታ አድማጮች የነበሩት መሰናዶ ነበር። እነ አሳምነው ገብረወልድ፣ እነዘውዱ ታደሰ፣ እነመሐመድ እንድሪስ፣ እነንጉሴ ተፈራ እና እነአብዱ ሙዘይን በኢትዮጵያ ሚዲያ ላይ ትልቅ አበርክቶ ያደረጉና የእኔም ሞዴል የምላቸው ናቸው ሲል በተለያዩ ሚዲያዎች ቃለ-መጠይቅ ሲያደርግ ተደምጧል።

በዋነኛነት ግን ወደ ጋዜጠኝነት ሞያ እንዲገባ አርአያ የሆነው አሳምነው ገብረወልድ እንደሆነ ይናገራል። ሌላው ደግሞ ጎንደር ትምህርት ላይ እያለ ሰኞ ሰኞ የጀርመን ሬዲዮ ድምፅን አዘውትሮ ያደምጥ ስለነበር ያን ይዞ ሰልፍ ላይ ሰንደቅ ዓላማ ሲሰቀል ለመላ ተማሪዎቹ ያነብ ነበር። ይህም በኋላ ለነገሰበት የጋዜጠኝነት ሙያ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደነበረው ይናገራል።

ለመጀመሪያ ጊዜ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ አዘጋጅ የነበሩት አቶ ማዕረጉ በዛብህ ግጥሞቹን በጋዜጣ ላይ ያወጡለት አጋጣሚ ጥሩ መነቃቃትና የእችላለሁ መንፈስ እንዲያድርበትም ያደረገው እንደነበር ገልጿል።

አንዳንዴም ስምን መልዓክ ያወጣዋል እንዲሉ ዜናነህ ዜናን ሲያነብ አድማጮቹን የሚያከብር፤ ለማህበረሰቡ ቅርብ የሆኑ ጉዳዮችን አድኖ የሚዘግብ ጎበዝ ጋዜጠኛ ነበር። መንግሥትን የሚቃወሙና በመንግሥት ያኮረፉ ሰዎች የዜናነህን ዜና አድማጮች ነበሩ። የዜና አቀራረቡ፣ አከፋፈትና አዘጋጉ ላይ የሚያሳየው ትህትና ዜናነህን አይረሴ አድርገውታል።

የማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ ሲቀጠር ዘመኑ ቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር ይካሄድ የነበረበት ወቅት ነበር። በዚህ ጊዜ ከሬዲዮ ወደ ቴሌቪዥን ገብቶ ዜናን እና ከየአቅጣጫው የሚባል ፕሮግራም ተሰጠው። ይህ ወቅት ጥሩ መለማመጃ ሆኖለትም አለፈ። በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ታሪክ ለሰባት ዓመታት ያህል እንቁጣጣሽን አንባቢ የነበረውም ይሄው ዜናነህ ነበር።

በጊዜው በነበረው ትእዛዝ መሠረት የቲቪ ወይም የሬዲዮ አንከሮች እንኳን አደረሳችሁ ማለት አይፈቀድላቸውም ነበር። ይልቁንም እንኳን አደረሳችሁ ብቻ እንዲሉ ይገደዱ ስለነበር ነው። ምክንያቱም ያኔ የነበረው የሶሻሊዝም አስተሳሰብ በእግዚአብሔር መኖር ወይም ሃይማኖት ላይ ጥብቅ ተቃውሞ ስለነበረው ነው። ዜናነህ ግን አልፎ አልፎ አውቆ እንኳን አደረሳችሁ በማለት ተመልካችን ሰላም የሚልበት ጊዜ ነበር።

አንድ ወቅት ጄኔራልን ኮሎኔል ብሎ ዘግቦ በመሪዎች ዘንድ በእኩይ ዓይን ታይቶ እንደነበር ይታወሳል። ዜናነህ ዜና ማንበብ ሲጀምር “ይህ የኢትዮጵያ ድምፅ ነው” ብሎ መጀመሩን ሳይቀር እንዲያቆም የተከለከለበት አጋጣሚም ነበር። ዜናነህ በኃላፊው ተፈርሞ ያልተሰጠውንና እርሱ ያላመነበትን ጉዳይ የማይዘግብ፤ የራሱን ስሜት፣ አመለካከትና አተያይ በፍፁም በሚያነበው ዜና ውስጥ ጨምሮ አድማጭን የማያደናግር ሰው ነበር፡፡

በ1967 ዓ.ም በማስታወቂያ መምሪያ ጋዜጠኝነትን “ሀ” ብሎ የጀመረው ባለ ነጎድጓዳማው ድምፁ አንጋፋው ጋዜጠኛ ዜናነህ ሃሳቡን ያለ ይሉኝታና ፍርሃት በነፃነት መግለጽ መቻል ባህሪው ነው። ይህንንም የማይወዱለት ታዲያ ብዙ ዋጋን አስከፍለውታል።

የኢህአፓ አባል ነህ በሚል የክስ ጭብጥ አስረውት ይህ አላስኬድ ሲላቸው ደግሞ የልዑል መኮንን ልጅ ነው በሚሉ አሉባልታዎች ከከፍተኛ አንድ ማዕከላዊ እስከ ዓለም በቃኝ ድረስ እሥር ቤቶቹን አፈራርቋል። ከእስሩ ሲፈታ ሶስት ዓመት ያህል ያለ ኪራይ ከመምሪያው ኃላፊ ጎን ብስራተ ወንጌል ውስጥ ቤት ተሰጥቶት በነፃ እንዲኖር በማድረግ የሞራል ካሣም ተከፍሎት ነበር፡፡

ዜናነህ በሙያው በትላልቆቹ ዘንድ ትልቅ ከበሬታ ያገኘ ሰው ነው። አብዬ መንግሥቱ ለማ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲያስተምሩ “ዜና ዜናነህ አነበበ ሲባል ዘመዳዊ ተሳቢ ነው” እያሉ ስሙን ይጠሩትና ያደንቁትም ነበር። ዜናነህ “ነፃነት” የተሰኘ በ5 ዓመቱ የጣሊያን ጦርነት የኢትዮጵያ ጀግኖች የከፈሉትን መስዋዕትነት የሚዘክር ታሪካዊ ልቦለድና በአዲስ አበባ ሕይወት ላይ የሚያጠነጥን የማህበረሰቡን አኗኗር ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ በእውነተኛ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የተጻፈ “ከጣሪያው ስር” የተሰኘ ልቦለድን ለአንባቢያን እንካችሁ ብሏል።

እ.ኤ.አ 1999ዎቹ አሜሪካን ሀገር ያሳተመውና ወደ 30 የግጥም ስብስብን የያዘ “በረከተ መርገም”ን የሚሞግት “በረከተ ራዕይ” በሚል ርዕስ የግጥም ሲዲ አውጥቷል። “የመንገድ ላይ ወግ” ኢትዮጵያን ወደኋላ ከሚጎትቷት ባህርያት መካከል ቅናት ላይ የተሰራ ትያትርም ፅፏል። ዜናነህ በድርሰቶቹ ሃይማኖታዊ ፖለቲካዊ እና የፍትህ ጥያቄዎችን ይጠይቃል፡፡

በ1975 ላይ ቤተሰብ ለመጠየቅ ከአዲስ አበባ ወደ ጎንደር ተጉዞ ነበርና የተወለደባት አዘዞ መብራት ስላልነበራት በወቅቱ ከነበሩ ሻለቃ መላኩ ተፈራ ጋር ተነጋግሮ መብራትም አስበርቶ ዜናነህ መብራት አስበራልን ተብሎ ይነገር ነበር። ዓለም በቃኝ በእስር ላይ እያለም ስፖርቱ ላይ ጥሩ እንቅስቃሴዎች ያደርግ ነበር።

ሕይወት ከሀገር ውጭ

አንተ ከሀገርህ ልትወጣ ትችላለህ ፤ ሀገር ግን ካንተ ውስጥ አትወጣም ! … እናም ኢትዮጵያ ፤ ሀገሬ ሳልገባ አምላክ አይግደለኝ! ሲል ይደመጣል። ዜናነህ መኮንን ከሀገሩ ወጥቶ ወደ እስራኤል ሀገር የተጓዘው በ1984 ዓ.ም አጋማሽ ነበር።

ወደ እስራኤል ሀገር ከሄደ በኋላ ትምህርታዊ ፊልሞችን ዳይሬክት በማድረግ ሠርቷል። ለመጀመሪያ ጊዜ የ24 ሰዓት የግል ሬዲዮ ጣቢያ መስርቶ ይሠራ ነበር። በርካታ ሬዲዮ ጣቢያዎችን በማቋቋምና ወጣቶችን በማሰልጠን ዛሬ ትልቅ ደረጃ ላይ የደረሱ ወጣቶችንም ማፍራት ችሏል።

በኋላም በ1991 ዓ.ም አካባቢ ወደ አሜሪካም አቅንቶ ነበር። አሜሪካንም እንዳሰበውና እንደጠበቀው ስላላገኘው ዘጠኝ ወር አካባቢ እንደተቀመጠ ወደ ኖርዌይ ሄዶ በሊደር ሺፕ ተምሮ ተመርቋል። ከዚያ ወደ ልጆቹ ወደ እስራኤል ሀገር ተመልሷል። እስራኤል ሀገርም በርካታ ኮርሶችን ወስዷል።

እስራኤል ሀገር መኖሬ ምርጫ ሳይሆን የፈጣሪ ፍቃድ ነው ብሎ ያምናል። እስራኤል የዓለም ማዕከል ነችና በየጊዜው ሕይወት አለ ፤ ዜና አለ፤ የፈጣሪን መኖር እንዳረጋግጥ አድርጎኛልና እስራኤል ለእኔ መማሪያ ትምህርት ቤቴ ነች ይላል።

እስራኤል ሀገር ከገባ በኋላ ከ10 ሺህ በላይ የሚሆኑ አካዳሚክ የሆኑና የፍልስፍ እና መጻሕፍትን ማንበቡን የሚያስታውሰው ዜናነህ በሳምንት አንድ ቀን ቅዳሜን ጠብቆ ከልጆቹ ጋር የሚወያይበትና መጽሐፍ ቅዱስን የሚያነብላቸው ቀን እንዳለው ይናገራል። ዜናነህ በዚህ በ30 ዓመት ጉዞ ውስጥ በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ በርካታ የሬዲዮና የቴሌቪዥን አስተማሪ ፕሮግራሞችን መሥራት የቻለ ጠንካራና ተወዳጅ ጋዜጠኛ ነው። “ጋዜጠኛ ጡረታ አይወጣም” በሚል ንግግሩ የሚታወቀው ዜናነህ በጀርመን ሬዲዮ ጣቢያ (ዶቼዌሌ) የመካከለኛው ምሥራቅ ዘጋቢ በመሆን ሲያገለግል ነበር ።

የቤተሰብ ሕይወት

ዜናነህ ትዳር የመሠረተው ከእስር ቤት ከወጣ በኋላ ነው። ከወይዘሮ አልማዝ ጥላሁን ጋር ትዳር መሰረተ። ገና ሚስት ሳያገባ ልጆች ብወልድ ስማቸውንም “ቢታንያ (ከሞት መዳን) እና ነፃነት (የመጽሐፌን ስያሜ) ለልጆቼ እሰጣቸዋለሁ ብሎ ያልም የነበረውን ለልጆቹ ስያሜ አድርጓል።

ከትዳር አጋሩ ጋር ለ5 ዓመት ያህል አብረው ከቆዩ በኋላ፤ በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ትኩሳት ወደ አሜሪካ ሄዳ እንድትኖር አደረገ። ከባለቤቱ ጋርም ርቀት ለያያቸው። በአንድ ሰው ደመወዝ የልጆችን ፍላጎት አሟልቶ ማስተማሩ እየከበደው ሲመጣ፤ ከሀገር መውጣት ግዴታ ሆነበት። ደርግ ወድቆ ኢህአዴግ ቦታውን ሲቆጣጠረው ወደ እስራኤል ሀገር ሄደ። እናታቸው ጥላቸው የሄደችው ልጆቹ ገና የ2 እና የ3 ዓመት ሕፃን ሳሉ ነበር። እነርሱ ዛሬ የደረሱበት እንዲደርሱ ትልቅ ሥራ ነበረበት።

ጋዜጠኛ ዜናነህ አሜሪካን ሀገር፣ ጀርመን ከዚያም ወደ ስዊድን፣ ኖርዌይ ተዘዋውሯል። ኖርዌይ በነበረበት ጊዜም ሊደርሺፕን ተምሯል። ልጆቹንም በእነዚህ ሀገራት ልኮ ማስተማር ይችል ነበር። ስብዕናቸው ላይ መሥራት እና በእንክብካቤው ስር እንዲያድጉ በመፈለጉ በእስራኤል እንዲያድጉ ወደደ።

ዜናነህ ትምህርት ቤቱን ብቻ አምኖ የሚተው አባት ሳይሆን የልጆቹን የቀን ተቀን ሕይወት የሚከታተልና ስለ ልጆቹም አብዝቶ የሚጨነቅ አባት ነበር። በጣም አስቸጋሪ የፈተና ጊዜንም አሳልፏል። ልጆችን ያለ እናት ብቻውን የማሳደጉ ኃላፊነትም በጫንቃው ላይ አርፏል። ሌላ ማግባት ሳያምረው ልጆቹን በኢትዮጵያዊ ሥነ ምግባር አንጾ ያሳደገና የልጅ ልጅ ለማየትም የበቃ ጠንካራ ኢትዮጵያዊ አባትም ነው።

ጋዜጠኛ ዜናነህ አንጋፋዎቹ መገናኛ ብዙሃን የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን በ70ዎቹ እና 80ዎቹ ሲታወሱ ዛሬም ድረስ ስሙ በጉልህ ይነሳል። የታሪክ ተመራማሪ፣ የመካከለኛው ምስራቅ የፖለቲካ ተንታኝ የጀርመን ድምፅ ሬዲዮ ልዩ እና ተወዳጅ ዘጋቢ ነበር፡፡

ዜናነህ መኮንን ከጋዜጠኛነቱ በተጨማሪ ደራሲ፣ ገጣሚና ሃያሲም ነው። ከግርማ ሞገሱ ጋር ግርማ ሞገስን የሚያላብስ ልብስ ለብሶ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከምሸቱ ሁለት ላይ “ጤና ይስጥልኝ እንደምን አመሻችሁ ከሰዓቱ ዜና ጋር ዜናነህ መኮንን ነኝ” በማለት እጅ ሲነሳ የብዙዎች ትዝታ ሆኖ አልፏል።

በበርካታ የቲቪ እና የሬዲዮ ተከታታዮች ዘንድም የሚወደድ ነው። የጀርመን ድምጽ (ዶቼ ዌሌ ሬዲዮ) የጣቢያው መክፈቻና መዝጊያ ድምፅ የዚሁ አንጋፋ ጋዜጠኛ ነው። ባለወርቃማ ድምጹ ዜና አንባቢና ደራሲ ዜናነህ መኮንን በተወለደ በ72 ዓመቱ ባሳለፍነው ሳምንት ከዚህ ዓለም በድካም አርፏል። እኛም ይህንን አንጋፋ የሚዲያ ባለሙያ ነፋስ ይማር እያልን ለወዳጅ ዘመዶቹ መፅናናትን እንመኛለን! ለዚህ ጽሑፍ በምንጭነት የተወዳጅ ሚዲያ ድህረገጽን ተጠቅመናል።

ክብረአብ በላቸው

 አዲስ ዘመን ህዳር 4/2017 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You