አሮጌ መጽሐፍትን በቅናሽ ዋጋ ከሚያዞሩት “አዳፍኔን” ገዝቼ መግለጥ በጀመርኩበት አንድ ወቅት ነበር ቀልብና ጆሮዬን እንድሰጠው የሚያስገድድ ቃለ ምልልስ ላይ ትኩረቴ ያረፈው። ቃለምልልሱን በኢትዮጵያ ሬዲዮ እየሰጡ የነበሩት ደግሞ ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ነበሩ። ፕሮፌሰሩ በነበራቸው ቆይታ ቁጭትና ኀዘን የተጫነውን ገጠመኛቸውን በትውስታ አካፈሉ፤ እኔም ለአሁኑ ትውልድ ይበጃልና የሞራል ስንቅ ይሆን ዘንድ የጽሑፌ ምሰሶ አደረግሁት።
ፕሮፌሰሩ ለሥራ ኬንያ በሄዱበት አጋጣሚ በአንድ የመዝናኛ ሥፍራ ያዩት ክስተት ክፉኛ አስቆጣቸው። አንድ ጥቁር ኬንያዊ ጥግ ይዞ ሲያለቅስ ያዩትና ምን እንደሆነ በጠየቁት ጊዜ ቆዳው ነጭ ወደ ሆነ ሠው እየጠቆማቸው ሚስቱን ነጥቆ እንደወሰደበት ቢነግራቸው ወገባቸውን ይዘው ወዲያ ወዲህ እየተንቆራጠጡ ደማቸው ፈልቶ ከጆሯቸው የደረሰውን ስንኝ ቀለቡት፡፡
ከቅቤው ከሆነ ከቅቤው ስጧቸው፣
ከማሩ ከሆነ ከማሩ ስጧቸው፣
ይችን የደም አጥር እንዳታስነኳቸው፡፡
“ጥቁር እንቁነታችንን በደም ያተምነው ሰውነትን አስቀድመን ነው” አሉና እብሪት የወጠረውን ፈረንጅ በጥፊ አላሱት። መደፈሩ አብግኖት ሲተናነቃቸው ቁልቁል ደፈቁትና እርካሽ ድርጊቱን ኮንነው ሚስቱን በማስመለስ የጥቁር ኬንያዊውን እንባ አበሱለት። ኬንያዊውም በደስታ ተውጦ “አፍሪካውያን ተስፋችን ኢትዮጵያ ናትና ለአፍታም ቢሆን እንዳትዘነጉት” አላቸው ማመስገኛ ቃል ቸግሮት።
እውነት ነው ይሄን መሰል ልብን የሚያሞቅ ታሪክ መስማት ብኩርናየን ላቀለልኩትና የክብርን ትርጉም ከፀጉሬ ላቀጠንኩት ለእኔ አይነቱ የዛሬ ሰው ብርቱ ተግሳጽ ነው። “ችግር መፍትሔ መውለዱን መልካም ምላስ ቁጣ ማብረዱን” እያሰብኩ ሀገሬን እንዲህ እላታለሁ፤
ልብ ብል ኖሮ ወዲያ ማዶ ያለው አስረሽ ምቺው ቀልቤን አሸፍቶት የወጣሁበት ማህጸንሽን ባልረገምኩት ነበር። ለውጭ ሰው አልጋ ለውስጥ ሰው ቀጋ የሆነው አመሌ ክብርሽን ሲያጎድፈው ሀገሬ ምን ብለሽኝ ይሆን? ቢሆንም ግን ስለክብርሽ ብለው በተዋደቁ ልጆችሽ አጥንት ይዤሻለሁ… ማሪኝ ኢትዮጵያዬ? ለነገሩ አንቺ ምን ታደርጊ… እንዳትይዥኝ ምግባር አጣሁ፤ እንዳትተይኝ ስጋሽን ነሳሁ፤ ቢጨንቅሽ “ልቦና ስጠው” አልሽ እንጂ። አዎ ልክ ብለሻል ሀገሬ…በክፉ ቀን ሊደገፉት የማይችል ልፍስፍስ ሙጃነቴን ጥዬ ከጣና እርጋታና ስክነትን፣ ከአባይ ረዥም ተስፋን፣ ከመቅደላ እምነት ጀግንነትን፣ ከዓድዋ ህብረትንና ከካራ ማራ ፅናትን ተምሬ ከህሊናው ጋር ታርቆ እራሱን የገራ በትረ-ዘንግሽ ልሆን በአንድ የመድረክ አጋጣሚ ጋሼ አያልነህ ሙላቱ ስለሀገር ፍቅር የተናገሩትን ዳገት መውጫ ምርኩዜ አደረግሁት፡፡
አበባው አበበ ንቡ ገባልሽ፣
እንግዲህ ሀገሬ ማር ትበያለሽ።
ብሎ መዝፈን እየከጀለኝ “ባለወር ባለሳምንት” ሲባል መደናገሬ አይሎ የፀፀት ጅራፍ እንዳይገርፈኝና “ሞቴ ይሙት” እያለች ፈጣሪዋን የምትማፀነው ኢትዮጵያ ከሀረግ የረዘመ ህልሟን እንድትኖር በመሻት የበኩሌን ሃሳብ ለማዋጣት የትናንት ስህተቴ ለዛሬ ማንነቴ እርማት ሰጥቶ ለነገ እኔነቴ እርሾ ጣለበትና ማስተዋልን ተጎናጽፌ የጋሼ አያልነህን ምክር በልቦናየ ፃፍኩት፡፡
ፀሐፈ-ተውኔት ገጣሚና መምህር አያልነህ ሙላቱ የያኔውን ሁነት ማሰቡ ቢያንገሸግሻቸውም እንቅፋት ሲመታ ወደፊት እንጂ ወደኋላ እንደማይጥል ትውልዱ ይገነዘብ ዘንድ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ውሉን የሳተ መረዳት የፈጠረባቸውን ቅሬታ ይገልፃሉ። “ዶን ኦፍ ሆፕ” የተሰኘ ፊልማቸውን ለመቅረጽ ሀገረ እንግሊዝ በከተሙበት ጊዜ ነው። ወጪ ለመቆጠብ ኮርን ፍሌክስ እየተሻሙ ሲበሉ የተመለከቱት የቤት አከራያቸው እንግሊዛዊት ባልቴት “መቼ ይሆን ከርሀብ የምትላቀቁት?” አሏቸው በትካዜ። የተፈጥሮ ሀብታችን ከራሳችን አልፎ ለሌላም እንደሚተርፍና የዓድዋን ገድል ቢያስረዷቸውም ባልቴቷ ግን እውነታውን ከመቀበል ይልቅ “እኔ የማውቀው በየአሥር ዓመቱ ርሀብ እንደሚጎበኛችሁ ነው!” ብለው ጡረታቸውን ለኢትዮጵያ ድጋፍ ማድረጋቸውን ነገሯቸው። ከሴትዮዋ ምጸት ጋር ተዳምሮ ኦክስፎርድ መዝገ-ቃል እንኳን ሳይቀር ኢትዮጵያን የርሀብ ምሳሌ ማድረጉ የከነከናቸው ጋሼ አያልነህ ፈር የሳተ መረዳታቸውን ለማረቅ ያረገዙትን “የሕዝብ ለሕዝብ” ሃሳብ ሀገራቸው እንደተመለሱ ወለዱትና የዓለምን ሕዝብ እጁን በአፉ ያስጫነ የኪነ-ጥበብ መድረክ አዘጋጁ፤ ይህ ጀግንነታቸውም የሞራል ስንቅ ሆኖን በመልካም ሥራ የሀገር ገጽታን ለመገንባት የየድርሻችንን አበርክቶ እንድንወጣ ለእኔ ዘመን ትውልድ ጥሪያቸውን አስተጋባሁ፡፡
“እስከ ዛሬ ድረስ የሰው ውሃ ጠጣሁ፣
ከእንግዲህ ሀገሬ ተቀበይኝ መጣሁ”።
እንዳለው ዘፋኙ ሰውነትን በሚያስሱ ህሊናን በሚያድሱ እሴቶቻችን ተጠልለን እንደ ብቅል በባዕዳን ደጅ ፈቅደን ያሰጣነውን የተበተነውን ሃሳባችንን ሰብስበን ለራስ መግዢያ ፍቱን መድኃኒት ማድረግ ይኖርብናል። ጣሊያኖች ጦርነቱ ሲከብዳቸው አለን የሚሉትን ሥልጣኔ በወሬ አስውበው የበላይ ዘለቀን ሠራዊት ቅርብ አስንቀው ሩቅ አስናፍቀው ልቦናቸውን በመስለብ ከብረት የተጠነከረ ሞራላቸውን ለማሽመድመድ ጣሩ፤ ሙሉ በሙሉ ባይሳካላቸውም ግን አልፎ አልፎ ከሠራዊቱ መሀል
“አትሄድም በቦላሌ፣
ግዛላት ካቻማሌ”፡፡
በማለት የዘፈኑም አልታጡም። “እፍ እሳትን ያነዳል ያጠፋልም” እንደሚባለው ጀግናው አርበኛ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ሁነኛ መላ ነው ያሉትን ስልት በመገንዘብ ለተከታዩቹ “በራሳችን ያልተቃኘ አስኳላ ልጆቻችንን በላ” ሲል የኮበለለ መንፈሳቸውን ከጭፍን ጉዞ በመጠበቅ አትኩሮት ጨመረበትና የሚያምሳቸውን የሃሳብ ማዕበል ማስቆም ቻለ፡፡
እናም ጎበዝ…ሀገርና ትውልድ የቅብብሎሽ ውጤት በመሆኑ በእንዲህ መልኩ የተሠራችን ሀገር ዘመን ለማሻገር ስለምን አቅም ይከዳናል? ምን አገባኝ የወለደው ስሜት የዛለ ወኔ አላብሶ ለሞራል ስብራት ይዳርጋልና ለመጠገን የተውሶ እጅ ሳናይ ለብዙ ችግሮቻችን ወጌሻ ሆነው ያገለገሉንን መልካም እሴቶቻችንን የወረሳቸውን አቧራ አራግፈን ልንጠቀምባቸው ይገባል። ስለዚህ “ሰው ከመከረ ልቦና በጠነከረ” ነውና ከተራራ የገዘፈ ሞራል በመታጠቅ እምነት የሚጣልብንና ለአደራ የምንበቃ የዘመን ድልድዮች እንሆን ዘንድ በይርዳው ጤናው ሙዚቃ መልዕክቴን አሳፈርኩላችሁ፡፡
“ከምንሰማው ከምናየው፣
ጥሩውን ከመጥፎ እንድንለየው፣
ሁሌም እንድናስብ ቀና፣
ፈጣሪ ይስጠን ልቦና”።
ሀብታሙ ባንታየሁ
አዲስ ዘመን ህዳር 4/2017 ዓ.ም