የኮፕ29 አጀንዳ ክርክሮች ከተደረጉ በኋላ ፋይናንስ እንዲሆን ስምምነት ላይ ተደረሰ

በጉባዔው ላይ ከ198 ሀገራት የተውጣጡ የሀገራት መሪዎችን ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እየተሳተፉ ይገኛሉ የኮፕ29 አጀንዳ ክርክሮች ከተደረጉ በኋላ ፋይናንስ እንዲሆን ስምምነት ላይ ተደረሰ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የአየር ንብረት ጉባዔ ወይም ኮፕ29 የአየር ንብረት ለውጥ ቀውስን ለማስወገድ መላው ዓለም የተውጣጡ በሽዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች በተገኙበት በደቡብ ካውኳሷ ሀገር ባኩ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

የዚህ ጉባዔ ቁልፍ አጀንዳ ክርክሮች ከተካሄዱ በኋላ የፋይናንስ ጉዳይ እንዲሆን ተወስኗል።

“የፋይናስ ኮፕ” የሚል ስያሜ የተሰጠው ጉባዔው የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ ለታዳጊ ሀገራት የሚሰጠውን ርዳታ መጨመር በሚቻልበት ሁኔታ ይመክራል።

ታዳጊ ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ከፍተኛ ተጎጂ በመሆናቸው ድጎማ ሊደረግላቸው ይገባል የሚለው ጥያቄ ከአየር ንብረት ጋር በተያያዘ በተደረጉ ጉባዔዎች ሁሉ ሲነሳ ቆይቷል።

የኮፕ28 ጉባዔ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሱልጣን አል ጃቢር የአረብ ኢምሬትስን ፕሬዚዳንትነት ለአዘርባጃን በይፋ ባለስተላለፉበት ከትናንት በስተያ እንዳሉት የፓሪሱን የአየር ንብረት ለውጥ ግቦችን ለማሳካት ፋይናንስ ወሳኝ ነው።

በአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ መሻሻሎችን ለማምጣት ፋይናንስ ወሳኝ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር ጃቢር ሁሉም የመንግሥት እና የግል የፋይንስ ምንጮች እንዲለግሱ ማበረታት ይገባል ብለዋል።

ዶክተር ጃቢር ዓለም የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት አንድ የጋራ ግብ እንዲያስቀምጥ እና የዓለም የሙቀት መጠን ከ1 1/2 በታች ዝቅ እንዲል እንደሚፈልጉም ገልጸዋል።

በዱባይ በተካሄደው የኮፕ28 ጉባዔ ሀገራት ታዳሽ ያልሆኑ የኃይል ምንጮች ለመቀነስ እና ታዳሽ ኃይሎች ለማብዛት ታሪካዊ የተባለውን “የኢምሬትስ ስምምነት” መድረሳቸው ይታወሳል።

ተመድ እንዳስጠናው ጥናት ከሆነ በ2030 የሙቀት መጨመርን ማስቀረት የሚቻለው በፍጥነት እያደጉ ያሉ ሀገራት ቻይናን ሳይጨምር ከ2 ትሪሊዮን ዶላር በላይ በየዓመቱ ኢንቨስት ማድረግ ሲችሉ ነው።

በ2009 ሀብታም ሀገራት በማደግ ላሉ ሀገራት የአየር ንብረት ፋይናንስ 100 ቢሊዮን ለመስጠት ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም ማሳካት የቻሉት ሁለት ዓመት ዘግይተው ነበር። ደሃ ሀገራት በየዓመቱ ለአየር ንብረት ለውጥ ቅነሳ ፕሮጀክት የሚውል አንድ ትሪሊዮን ዶላር እንዲሰጣቸው ጥሪ እያደረጉ ነው።

በዓለም ቁጥር አንድ በካይ ጋዝ የምትለቀው ቻይና እና ከፍተኛ የነዳጅ አምራች የሆነችው አረብ ኢምሬትስ እስካሁን በማደረግ ላይ ያሉ ሀገራት ተብለው ቢመደቡም ለአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ የሚያዋጡ ናቸው።

ከ198 ሀገራት የተውጣጡ የሀገራት መሪዎችን ጨምሮ ከ32 ሺህ በላይ እየተሳተፉበት የሚገኘው ከትናንት በስተያ የተጀመረው የባኩ የአየር ንብረት ጉባዔ በቀጣይ ሳምንት ይጠናቀቃል።

በጋዜጣው ሪፖርተር

 አዲስ ዘመን ህዳር 4/2017 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You