ራስ ገዟ ሶማሊላንድ በዛሬው ዕለት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ታካሂዳለች።
የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ በሚገኝበት በዚህ ወቅት ራስ ገዟ ሶማሊላንድ በዛሬው ዕለት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ልታካሂድ ነው፡፡
አሁናዊውን ፕሬዚዳንት ሙሴ ቤሂ አብዲን ጨምሮ ሶስት ተፎካካሪዎች ሀገሪቱን ለመምራት እጩ ሆነው ቀርበዋል፡፡
ከ2017 ጀምሮ በሥልጣን ላይ የነበሩት እና ለሁለተኛ ጊዜ የሥልጣን ዘመን የሚወዳደሩት ሙሴ ቤሂ የሶማሊላንድን ዴሞክራሲ ለማጠናከር፣ የኢኮኖሚ እድገትን ለማሻሻል እንዲሁም የሀገርነት እውቅናን ለማረጋገጥ እንደሚሠሩ ቅስቀሳ ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡
ከአሜሪካ ድምጽ ጋር በነበራቸው ቆይታም ፕሬዚዳንት ሆነው የሚመረጡ ከሆነ ከኢትዮጵያ ጋር የተፈረመውን የወደብ የመግባቢያ ስምምነት ወደ ተግባራዊነት እንደሚያስገቡ ተናግረዋል፡፡
“በእኛ በኩል ስምምነቱን ለመተግበር ነጻ እና ዝግጁ ነን፤ እየተጠባበቅን የምንገኘው ከኢትዮጵያ በኩል የሚመጣውን ምላሽ ነው፤ እርሱን ካገኘን ወደ ትግበራ የማንገባበት ምክንያት አይኖርም” ብለዋል።
አብዱራህማን መሀመድ አብዱላሂ ከዋዳኒ ፓርቲ፣ ፋይሰል አሊ ዋራቢ ከፍትህ እና እድገት ፓርቲ ለፕሬዚዳንትነት የሚወዳደሩ ሌሎቹ ዕጩዎች ናቸው።
ሃርጌሳ የራሷ ፓስፖርት፣ የመገበያያ ገንዘብ፣ የጸጥታ ሃይሎች፣ በተፎካካሪ ፓርቲዎች ዘንድ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር የሚያስገድድ የፖለቲካ ሥርዓት ብትከተልም ለ33 ዓመት ሙሉ የሀገርነት እውቅና ሳታገኝ ቆይታለች።
ይህ በእንዲህ እያለ አሁንም ጋዜጠኞች እና ማህበራዊ አንቂዎች ከባለሥልጣናት ጫና ይደርስባቸዋል፤ አናሳ ጎሳዎች ለፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መገለል የተጋለጡ ሲሆኑ በሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃትም ቢሆን አሳሳቢ ችግር ስለመሆኑ ይነገራል፡፡
የዋዳኒ ፓርቲው እጩ አብዱራህማን መሀመድ ሥልጣን የሚይዙ ከሆነ ከሶማሊያ መንግሥት ጋር እንደሚደራደሩ ቃል ገብተዋል። ባለፉት 11 ዓመታት በታችኛው ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሆነው ያገለገሉት አብዱራህማን ከሶማሊያ ጋር ለመደራደር ተሞክረው የከሸፉ ድርድሮችን ዳግም አስጀምራለሁ ነው ያሉት፡፡
ከፍትህ እና እድገት ፓርቲ ሶስተኛው እጩ ዋራቤ በበኩላቸው በሶማሊላንድ ብሔራዊ አንድነቱ የተጠበቀ መንግሥት በመመሥረት የሀገርነት እውቅናን አስገኛለሁ ብለዋል፡፡
የዚያድ ባሬ መንግሥት በ1991 መውደቅን ተከትሎ ከሰሜን ምዕራብ ሶማሊያ ክፍል የተገነጠለችው ሶማሊላንድ ዘንድሮ የምታደርገው ምርጫ ለአራተኛ ጊዜ የሚካሄድ ነው፡፡
የምርጫ ኮሚሽኑ ይፋ ባደረገው መረጃ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ዜጎች ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት የሚያስተዳድሯቸውን መሪዎች ለመምረጥ ወደ ምርጫ ጣቢያዎች ያቀናሉ፡፡
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ህዳር 4/2017 ዓ.ም