ዋጋ እያስከፈለ የሚገኘው የአበረታች ንጥረ-ነገሮች ተጠቃሚነት ጉዳይ

በዓለም አቀፍ ደረጃ አበረታች ንጥረ ነገሮችን (ዶፒንግ) የሚጠቀሙ አትሌቶች ጉዳይ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መሄዱን ተከትሎ የሚሰጠው ትኩረትና የክትትል ደረጃውም እየጠነከረ መጥቷል። በአትሌቲክስ ውጤታማ የሆኑ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራትም በዓለም አቀፉ ፀረ አበረታች ንጥረ ነገሮች ተቋም (ዋዳ) ትኩረት ያደረገባቸው ናቸው። ኢትዮጵያ እየተስተዋለ ካለው ችግር አንፃር ጥንቃቄ እንድታደርግ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣትም ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ በመላ ሀገሪቱ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫና ሌሎች በርካታ ሥራዎችን እየሠራ ይገኛል። ለዚህም ዓለም አቀፉ ተቋም የኢትዮጵያን ተሞክሮ ለሌሎች እስከ ማጋራት እንደደረሰ ይታወቃል። ይሁን እንጂ የዘርፉ ተዋናዮች በርካታ ከመሆናቸውና ቁጥጥሩም አስቸጋሪ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሊቀረፍ አልቻለም።

በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ከነበረው በከፍተኛ ሁኔታ እየተስፋፋና ታዋቂ አትሌቶችንም ጭምር እየጎዳ ይገኛል። ይህንን ተከትሎም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጉዳዩ ከአቅሙ በላይ መሆኑንና ስፖርቱን በበላይነት እየመራ ባለው ተቋም ድጋፍ እንዲደረግለት ከወራት በፊት በይፋ መጠየቁ አይዘነጋም። ያም ሆኖ የችግሩ አሳሳቢነት ቀጥሏል። ለዚህም የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን በዶፒንግ የሕግ ጥሰት በፈፀሙ አትሌቶች ላይ የቅጣት ውሳኔ መተላለፉን ከትናንት በስቲያ ይፋ ያደረገው መረጃ ማሳያ ነው።

ተቋሙ ቅጣት እንደተላለፈባቸው ይፋ ካደረገው አትሌቶች መካከል ታዋቂዋ አትሌት ፀሀይ ገመቹ ከበድ ያለውን ቅጣት አስተናግዳለች። በቶኪዮ ኦሊምፒክ በ10ሺ ሜትር እንዲሁም በ2023ቱ የቡዳፔስት ዓለም ቻምፒዮና በማራቶን ኢትዮጵያን የወከለችው አትሌት ቅጣት የተላለፈባት ከአበረታች ቅመሞች ጋር በተያያዘ ምርመራዎችን የማድረግና ርምጃዎችን የመውሰድ ሥልጣን ያለው “Athletics Integrity Unit (AIU) ባደረገላት የባይሎጂካል ፓስፖርት ምርመራ ጉዳዩዋን ሲከታተል ቆይቶ ጥፋተኛ ሆና በመገኘቷ ነው።

በዚህም መሠረት እኤአ ከህዳር 30/2024 አንስቶ ለቀጣዮቹ አራት ዓመታት በየትኛውም የአትሌቲክስ ውድድሮች ላይ እንዳትሳተፍ እገዳ ተጥሎባታል። በተጨማሪም እኤአ ከመጋቢት 22/2020 እስከ ህዳር 30/2023 ድረስ ያስመዘገበቻቸው ውጤቶች በሙሉ እንዲሰረዙ ተወስኖባታል። ከእነዚህም መካከል በ2023 የቶኪዮ ማራቶን ሁለተኛ ሆና ያጠናቀቀችበት ውጤቷ ተጠቃሽ ነው። የ25 ዓመቷ አትሌት ፀሀይ ገመቹ በማራቶን ምርጥ ሰዓቷ 2:16.56 ሲሆን ይህም በሴቶች ማራቶን ታሪክ ርቀቱን ከ2:17 በታች የገባች የዓለማችን 8ኛዋ ፈጣን አትሌት ያደርጋታል። አትሌቷ ከዚህ በተጨማሪ በ5ሺ ሜትር 14:29.60፤ በ10ሺ ሜትር 30:19.29 እንዲሁም በግማሽ ማራቶን 1:05.01 የግል ምርጥ ሰዓቶቿ ናቸው።

ሌላኛዋ እገዳ የተጣለባት አትሌት ህብስት ጥላሁን አስረስ ናት። የ24 ዓመቷ አትሌት እኤአ ጥቅምት 3/2023 በቻይና ናኒንግ ባደረገችው ውድድር በተደረገላት የሽንት ምርመራ “triamcinolone acetonide” የተባለውን የተከለከለ አበረታች ንጥረ ነገር መውሰዷ ተረጋግጧል። ካለባት የአስም ህመም ለማገገም በተወጋችው መርፌ ውስጥ ንጥረ ነገሩ ሳይኖር እንዳልቀረ ብትናገርም ጉዳዩን የሚያጣራው ዓለም አቀፍ ተቋም አትሌቷ “መርፌውን ተወግቻለሁ” ባለችውና በምርመራ የተረጋገጠው መድሃኒቱን ወሰዳበታለች የሚለው የምርመራ ጊዜ ሊገጣጠሙ ባለመቻላቸው ከቅጣት ልታመልጥ አልቻለችም። ስለዚህ እኤአ ከሰኔ 3/2024 አንስቶ የሚታሰብ የሁለት ዓመታት የእገዳ ቅጣት ተጥሎባታል። በተጨማሪም ለመጀመሪያ ጊዜ የሽንት ምርመራ ካደረገችበት እኤአ ጥቅምት 3/2023 አንስቶ በተወዳደረችባቸው መድረኮች በሙሉ ያገኘቻቸውን ሜዳሊያዎች፣ ሽልማቶች፣ የአሸናፊነትና የመግቢያ ክፍያዎች እንድትነጠቅ ተወሰኖባታል።

እነዚህ በዓለም አቀፉ ተቋም ቅጣት የተጣለባቸው ሲሆን የኢትዮጵያ ፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን በበኩሉ በአትሌት ሳሙኤል አባተ ዘለቀ ላይ የእገዳ ርምጃ መውሰዱን አስታውቋል። እንደ ባለሥልጣኑ መግለጫ ከሆነ አትሌቱ እኤአ ከየካቲት 29/2023 ከውድድር ውጪ በተወሰደለት የሽንት ናሙና EPO (Erythropoietin) የተባለው የተከለከለ ንጥረ ነገር በሰውነቱ ተገኝቷል። በመሆኑም የኢትዮጵያ ፀረ አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን በመጀመሪያ ደረጃ ዳኝነት ሰሚ ጉዳዩ ሲታይ ቆይቶ እኤአ ጥቅምት 11/2024 በተላለፈው ውሳኔ መሠረት ከእኤአ ከሚያዝያ 17/2024 ጀምሮ ለ2 ዓመት በማንኛውም ስፖርታዊ ውድድር እንዳይሳተፍ እገዳ ተጥሎበታል፡፡

አትሌቲክስ በብዙ ትግልና በተለያዩ አካላት ፍላጎት የተጠመደ መሆኑ ችግሩን የተወሳሰበ አድርጎታል። ዘርፉ በርካታ ተዋናዮች የሚሳተፉበት በመሆኑ አትሌቲክሱ በተፅዕኖ ስር እንደወደቀም ለስፖርቱ ቅርብ የሆኑ ሰዎች በተደጋጋሚ ተናግረዋል። በአትሌቲክስ የሚወሰዱና የሚከለከሉ ንጥረ ነገሮች ቢኖሩም መቼ፣ ማንና እንዴት የሚለው ጉዳይ አሳሳቢና ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑንም ገልጸዋል። ጉዳዩ እየሞቀና እየበረደ ስር ወደ መስደድ እየተጓዘ በመሆኑም ትኩረት ሊለየው እንደማይገባ የስፖርት ቤተሰቡ እምነት ነው፡፡

የአበረታች መድኃኒቶች ተጠቃሚነት እንዲባባስ የሚያደርጉ ብዙ ተዋናዮች ቢኖሩም አሁንም ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገባቸው አይገኝም። ችግሩን ለመቆጣጠር የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ቢወጣም በአግባቡ ሥራ ላይ ውሎ ችግሩን መቅረፍ አልተቻለም። ችግሩን ከሚያባብሱ አካላት ይልቅ የቅጣት ርምጃው አትሌቶች ላይ ብቻ የሚበረታ በመሆኑ ችግሩ አሳሳቢ ሆኖ እንዲቀጥል አስገድዷል። በዚህም ውስጥ ለአትሌቶች ድጋፍ በመስጠት ሽፋን የአትሌቶች ተወካዮች፣ ከውጪ የሚመጡ አሠልጣኞች፣ ደላሎች ነገሩን እያባባሱና ከቁጥጥር ውጪ እንዲሆን እያደረጉ መሆኑ ቀደም ሲልም ተጠቁሟል።

ይህ ሕገ ወጥ ሆነው የተገኙትን አትሌቶች ብቻ ሳይሆን በንፁህ ልፋታቸው ላባቸውን አፍሰው ውጤታማ የሆኑ በርካታ ከዋክብት አትሌቶች ያሉባትን ሀገር ስምና ዝና የሚያጎድፍ በመሆኑም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥተው ዘወትር በጋራ ከመሥራት ሊዘናጉ እንደማይገባም የስፖርት ቤተሰቡ እምነት ነው፡፡

ቦጋለ አበበ

አዲስ ዘመን ህዳር 4/2017 ዓ.ም

 

 

 

 

Recommended For You