ማህሌት አብዱል
የተወለዱት በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ወልቂጤ በሚገኘው ሥላሴ በተባለ ትምህርት ቤት የተከታተሉ ሲሆን፤ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ ያበሩስ በተባለ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ በፉድ ኤንድ ባዮ ኬሚካል ኢንጅነሪንግ መስክ አግኝተዋል። ወደ ትውልድ ቀያቸው ተመልሰው ለስምንት ዓመታት በውሃ መምሪያ የሥራ ሂደት አስተባባሪ ሆነው የሠሩ ሲሆን፤ በመቀጠልም በወጣት አደረጃጀት ላይ በመሳተፍ የተለያዩ በጎ ተግባራት ሲያከናውኑ ቆይተዋል። ከዚሁ ጎን ለጎንም በክልል ታዳጊ ክለቦች ታቅፈው እግር ካስ ተጫውተዋል። የዞኑ ወጣቶችና ስፖርት ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ሆነው ለአራት ወራት አገልግለዋል። ለዘጠኝ ወራትም የወልቂጤ ከተማ ከንቲባ ሆነው ሠርተዋል። ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ደግሞ የጉራጌ ዞን አስተዳደሪ ሆነው በማገልገል ላይ ነው የሚገኙት። ዝግጅት ክፍላችንም ከዛሬው የዘመን እንግዳችን ከአቶ መሐመድ ጀማል ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ቃለምልልስ አድርጓል። እንደሚከተለው ይቀርባል።
አዲስ ዘመን፡– ወደስልጣን ከመጡበት ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የዞኑን ነዋሪዎች የልማት ጥያቄ ለመመለስ ምንያህል ጥረት አድርጊያለሁ ብለው ያምናሉ?
አቶ መሐመድ፡– እንደሚታወቀው እኛ የመጣንበት ወቅት አስቸጋሪ በመሆኑ እድለኞች አልነበርንም ማለት ይቻላል። የለውጡን መምጣት ተከትሎ በአገር አቀፍም ሆነ በዞን ደረጃ አለመረጋጋቶች ነበሩ። ብዙ ዋጋም የከፈልንባቸው ችግሮች ነበሩ። በዚህ ምክንያት ብዙ ልንሠራበት የሚገባው ጊዜ የሰላምና ፀጥታ ሥራ በማከናወን ነው ያሳለፍነው። የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ፣ የሕዝቦችን አንድነት ለማጠናከር፣ ከሌሎች አካባቢዎች የተፈናቀሉ የዞኑ ተወላጆችን የመመለስ ሥራ ላይ ነበር ተጠምደን የቆየነው። በተለይም ዞናችን በኦሮምያ ዞኖች የተከበበ እንደመሆኑ ብዙ ፈተናዎችን አሳልፈናል። በመሆኑም ባለፉት ሁለት ሦስት ዓመታት በምንፈልገው ደረጃ የልማት ሥራዎችንም የመሥራትም ሆነ ህዝቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት አልቻልንም። ግን ደግሞ የዞኑ ህዝብ በሰላም እጦት የበለጠ ፈተና ውስጥ እንዳይገባ የሠራነው ሥራ በጥሩነት የሚወሰድ ነው።
ከዚሁ ጎን ለጎንም ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው የተለያዩ ጥያቄዎች አሉ። እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ህብረተሰቡን በማስተባበር በአካባቢው ያሉት የጉራጌ፣ የቀቤና እና የማረቆ ማህበረሰቦች የሚያነሷቸው የልማት፣ የአደረጃጀት የዴሞክራሲ ጥያቄዎች አሉ። ባለፉት ዓመታት ትግል እያደረገባቸው ያሉ ጥያቄዎችን ወደ መሬት ለማውረድ በተለያየ ጊዜ ከባለድርሻ አካላት ጋር ሠርተናል። በዋናነት ግን ጊዜው በሚፈለገው ደረጃ የሕዝቡን ጥያቄ የምትመልሺበት አልነበረም። አገርአቀፍም ሆነ ክልላዊ ተፅዕኖው ከባድ ስለነበር የልማት ሥራዎች ላይ ወደኋላ እንድንል አድርጎናል። በአጠቃላይ ሙሉ ጊዜያችንን የአካባቢያችንን ሰላም የመመለስ ሥራ ላይ አተኩረን ነው የነበረው።
አዲስ ዘመን፡– በተያዘው በጀት ዓመትስ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ምን ደረጃ ላይ ይገኛሉ?
አቶ መሐመድ፡– በነገራችን ላይ አሁን ባለው ሁኔታ በመንግሥት የሚበጀተው ገንዘብ አዳዲስ የልማት ፕሮጀክቶችን ለመተግበርም ሆነ የህዝቡን ጥያቄ የሚመልስ አይደለም። በአንፃሩ ደግሞ ብዙ ለውጥ እንዲመጣ የደም ዋጋ የከፈለ ማህበረሰብ ነው። ለውጡም ችግር ውስጥ እንዳይገባ ብዙ ጥያቄዎቹ ሳይመለሱለትም ችሎ ያደረ ማህበረሰብ ነው። በሌላ በኩል ይህ ማህበረሰብ በብዙ አካባቢ የተበተነ እንደመሆኑ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች መመለስ የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመሥራት የበጀት ውስንነት አለብን። ህብረተሰቡ ከሚያነሳቸው ጥያቄዎች መካከል በዋናነት የአደረጃጀት ጥያቄ ነው። ይህ ጥያቄ በፌዴራል መንግሥቱ የሚመለስ ነው። በተመሳሳይ ትልልቅ ኢንቨስትመንት እንዲመጣ ይፈልጋል። ለአዲስ አበባ 150 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ እንደመሆኑ መጠን ከአጎራች የኦሮምያ ዞኖች ጋር በሰላምና በፀጥታ፣ በዴሞክራሲ፣ በልማቱ በጋራ እንዲሠሩ ይፈለጋል። የመንገድ ጥያቄዎች ቢኖሩትም ትላልቅ የመንገድ ፕሮጀክቶች በፌዴራል መንግሥቱ እየተሠራለት አይደለም። የኢንዱስትሪ ፓርክ ጥያቄዎች አሉት። ወጣቱን አቅፎ ሊሠራ የሚችል የመሰረተ ልማት ሥራዎችም አልተሠሩለትም።
በክልሉ መንግሥት የሚያዙ ፕሮጀክቶችም ቢሆን በፍትሐዊነት ከማግኘት አንፃርም ሰፊ ችግር አለበት። በዚህ ምክንያትም ዞኑ ለዓመታት ወደኋላ የቀረ ነው ማለት ይቻላል። እነዚህን ሁሉ ጥያቄዎች ህዝቡ ለዓመታት በምሬት ነው ሲያነሳ የቆየ ከመሆኑም ባሻገር አሁንም ያልተመለሱ ጥያቄዎች ናቸው። እኛም እንደአመራር ሌሎች ቦታዎች ላይ የሚሠሩ ሥራዎች በፍትሐዊነት ወደ ዞናችን እንዲመጡ እንሻለን።
ለምሳሌ ያህል ባነሳልሽ ከቱሉ ቦሎ አጨበር ኬላ መንገድ ወደ ገደባ ጉታዘር ወረዳ ለመግባት ሰባት ኪሎ ነው የሚቀረው። ግን የእኛን ወረዳ አልፎ የተሠራ መንገድ አለ። ይህችንም ሰባት ኪሎ ሜትር መንገድ ለማሠራት ብዙ ዓመታት ፈጅቷል። ከእነሞር ሆሳዕና 13 ኪሎ ሜትር መንገድ ማግኘት አልቻልንም። በእነዚህ ምክንያቶች ህብረተሰቡ በመንግሥት አመራር ከፍተኛ የሆነ ምሬት ነው ያለው። ፌዴራል መንግሥቱ ተረድቶ የህዝባችንን ጥያቄ ከመመለስ አንፃር ፍትሐዊ አይደለም የሚል ቅሬታ አለው። ህዝቡ መሰል ትልልቅ ፕሮጀክቶች በአካባቢያችን እንዲሠሩ ከመፈለግ አንፃር ጥያቄ ያነሳል። በዞኑ ልማት ላይ የሚያሳትፍና ወጣቱን ሊያቅፍ የሚችል ሁኔታ ባለመፈጠሩ ብዙ የተማረው ወጣት ሥራ ፍለጋ ይሰደዳል።
በሌላ በኩል ግን ዞናችን ለአዲስ አበባም በቅርብ ርቀት ላይ እንደመገኘቱ መጠን ልክ እንደሌሎቹ አካባቢዎች ልማት እንዲመጣለት የተሻለ ነገር ከመንግሥት ይጠብቃል። በፊትም ብዙ ቃል የተገባለት ነገር ነበር። በተገባለት ቃል መሰረት ሥራዎች ባለመሠራታቸው ልማት አሁንም የጉራጌ ዞን ነዋሪዎች አንገብጋቢ ጥያቄ ነው። በሌላ በኩል የሕዝቡን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችል አቅም የለንም። የሚበጀተው በጀትም ከደመወዝ አያልፍም። በመሆኑም ህብረተሰቡ ለዓመታት ያነሳቸውን ትልልቅ ጥያቄዎች መሬት ላይ ማውረድ አልተቻለም። አሁን ካለው አገራዊ ችግር አንፃር ተጨማሪ ፈተና ለመንግሥት እንዳንሆን፤ ወጣቱን እያሳመንን ብዙ ጥያቄዎች ቢኖሩትም ለሰላም ሲል በይደር ይዞት ነው ያለው። ሌላው ይቅርና ይሄነው የሚባል የፌዴራል ተቋም የሌለበት ዞን ነው። ምንአልባት አለ ሊባል የሚችለው የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ብቻ ነው። በሀገሪቱ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ካምፓስ የሌለው ዩኒቨርሲቲ የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ነው። ስለዚህ በእነዚህ ድምር ችግሮች ምክንያት ህብረተሰቡ ከፍተኛ የሆነ ምሬት አለው። ከዚህ ባሻገርም በማይታወቅ አካል ብዙ ጥቃት የደረሰበት ማህበረሰብ ነው።
አዲስ ዘመን፡– ይህንን ሲሉ ምን ማለትዎ ነው?
አቶ መሐመድ፡– እንደሚታወቀው ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት የጉራጌ ማህበረሰብ በየአካባቢው በተፈጠሩ ግጭቶች ሁሌም ሰለባ ሆኖ ነው የቆየው። ለምሳሌ በሻሸመኔ፣ በዝዋይ፣ በአጋርፋና በሌሎችም አካበቢዎች በተከሰቱ ግጭቶች ዋነኛ ተጎጂ ነበር። ምንአልባትም የራሳችን ሚዲያ ባለመኖሩ ምክንያት ልክ እንደሌላው ማህበረሰብ አልተለቀሰለት ይሆናል እንጂ የጉራጌን ያህል ብዙ ዋጋ የከፈለ አለ ለማለት አልችልም። በየቀኑ ተሰዶ የሚመጣው የሕዝብ ቁጥር በጣም ከፍተኛ ነው። የእኛን ሰዎች ለመጠበቅ ሲሉ ደግሞ ዋጋ የከፈሉ አሉ። በእኛ ማህበረሰብ ላይ ጉዳት እንዳይደርስና ቤቱ እንዳይቃጠል እገዛ ያደረጉ የሌላ አካባቢ ነዋሪዎች አሉ።
በአዲስ አበባም ቢሆን ባለፉት 27 ዓመታት የጉራጌ ማህበረሰብ በተጠና መንገድ ከንግዱ እንዲወጣ ተደርጓል። ነገር ግን በፊት የነበሩትን ክፍተቶች አርሞ ይህንን ማህበረሰብ በደንብ አቅፎ ይዞ ለአገር ፋይዳ እንዲኖረው አልተደረገም። ይህ ቅሬታ አሁን ያለውን መንግሥትንም ሆነ የዞኑን አመራሮች የሚገዳደር ነው ብዬ ነው የማስበው። ሌሎች ቦታዎች ላይ የምናያቸው መሰረተ ልማቶች ለጉራጌ ዞን አልተሠራም። እስከአሁንም የተሠሩት ሥራዎች ህብረተሰቡን በሚያረካ ደረጃ ተሠርቷል ብዬም አላምንም። እንደአጠቃላይ እንደ ሌላው ዜጋ ሁሉ የጉራጌ ህዝብ በለውጡ ተስፋ ያደረገ አንጂ ተጠቃሚ የሆነ አይደለም ማለት ይቻላል። ደግሞም በጣም ቁጥ ቁጥ በሆነ መልኩ የሚመደበው በጀት ይህንን ማህበረሰብ የሚመጥን ሥራ ለመሥራት አያስቻልም። ከዚህ ባሻገር ግን በግላቸው ተነሳሽነት መንገዶችን፣ ሆስፒታሎችንና ትምህርት ቤቶችን የሚገነቡ ባለሀብቶች ያሉበት ዞን ነው። በዚህ ደረጃ የመንግሥት ድጋፍ ቢታከልበት ኖሮ በተሻለ ፍጥነት የህብረተሰቡን ጥያቄ በጥቂቱም ቢሆን መመለስ በቻልን ነበር።
አዲስ ዘመን፡– ከዚህ አንፃር የዞኑ የመንገድ መሰረተ ልማት ተደራሽነት ምን ደረጃ ላይ ነው የሚገኘው ?
አቶ መሐመድ፡– የሚገርምሽ በእኛ ዞን በአብዛኛው መንገድ የሠሩት የእኛ አባቶች ናቸው። ትልቅ ድርጅት አቋቁመው ከቡታጀራ እስከ ሆሳዕና፣ ከዓለምገና እስከ ሆሳዕና ከእያንዳንዱ ቤት ገንዘብ ተሰብስቦ መንገድ ተሠርቷል። እናም ይህ ማህበረሰብ ከመንግሥት ሳይጠብቅ የመንገድ መሰረተ ልማትን ቀድሞ የጀመረ ቢሆንም የተጨመረለት አዲስ መንገድ የለም። ይህም ባለንበት እንደመርገጥ ይቆጠራል። ልክ ኢህዴግ ሲገባ ያንን የጉራጌ መንገዶች ሥራ ድርጅት በጠላትነት ፈርጆ ዜሮ ነው ያስገቡት። አሁን ላይ በጉራጌ ዞን ባለሀብቱ ከፍተኛ በሚባል ደረጃ መዋለንዋዩን እያፈሰሰ ያለው መንገድ ላይ ነው። ለምሳሌ ብጠቅስልሽ የዛሬ ዓመት ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ አቅደን እስከ 60 ሚሊዮን ብር በመንገድ ልማት ላይ ባለሀብቱ አስተዋፅኦ አድርጓል። ዘንድሮ እስከ 200 ሚሊዮን ብር እናገኛለን ብለን ነው የምንገምተው። እናም አብዛኛው መንገድ በማህበረሰቡ የተሠራ ነው። አብዛኛው የፌዴራል መንገድ ግን ሌሎች ቦታዎች አቋርጦ ከሚሄደው በስተቀር የተሠራ ነገር የለም። እርግጥ ነው በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሰላኝ ዘመን ጉብሬ ቡታጀራ መንገድ ተሠርቶልናል። በአጠቃላይ ግን ባለፉት 27 ዓመታት ውስጥ ይሄነው የሚባል የመንገድ ሥራ አልተሠራም። አስቀድሜ እንዳልኩሽ በመንግሥት የሚወጣው ትንሽ በጀት የህዝብን ጥያቄ የሚመልስ አይደለም። በጥቅሉ ይህንን ማህበረሰብ የሚመጥን አይደለም። እኛ የብልጽግና አመራሮች እንደመሆናችን መጠን ይህንን ህዝብ በብልጽግና ማዕቀፍ ውስጥ ይዞ ለመቀጠል ከባድ የቤት ሥራ ነው ያለብን።
አዲስ ዘመን፡– በዚህ ዞን ከስምንት ያላነሱ የማዕድን ውሃ ምርቶች ይወጣሉ። ነገር ግን የዞኑ ህዝብ ከፍተኛና አሳሳቢ የሚባል ንፁሕ የመጠጥ ውሃ ችግር አለበት። ይህ የሆነበትስ ምክንያት ምንድን ነው?
አቶ መሐመድ፡– እንዳልሽው የውሃ ችግር የዞናችን አንዱና መሰረታዊ ችግር ነው። ከዚህ በተጨማሪም የዞናችን አብዛኛው አካባቢ የኤሌትሪክ መሰረተ ልማት ያልተዘረጋለት በመሆኑ አሁንም ማህበረሰቡ በኩራዝ ነው የሚጠቀመው። እንደጠቀሽው ዞናችን ከፍተኛ የሆነ የከርሰ ምድር ውሃ ሀብት አለ። ከስምንት ያላነሱ የውሃ አምራቾች አሉ። ይሁንና የዞናችንም የንፁሕ መጠጥ ውሃ ሽፋን 39 በመቶ ብቻ ነው። ይህንንም የምልሽ በግርድፍ መረጃ ማለት ነው። ወልቂጤ ላይ ከፍተኛ የሚባል የውሃ እጥረት አለ። በዚህ በኩል ህብረተሰቡን ተደራሽ ማድረግ ያለመቻሉ የተለያዩ ምክንያቶች ቢጠቀሱም በዋናነት ግን የአመራሩ ድክመት ነው ባይነኝ። የማይካደው ግን ውሃ ሀብቱ ቢኖረንም ማልማቱ በራሱ ከፍተኛ መዋለንዋይ የሚፈልግ ነው። ለአንድ ቀበሌ ውሃ ለማዳረስ ከ10 እስከ 15 ሚሊዮን ብር ይፈልጋል። በዚህ የተነሳ ህብረተሰቡ በጣም ምሬት ውስጥ ገብቷል። የመጀመሪያውም፤ የመጨረሻውም ጥያቄ ውሃ ነው። በነገራችን ላይ የጉራጌ ዞን ህዝብ የቅንጦት ጥያቄ ጠይቆ አያውቅም። የሚያነሳቸው ጥያቅዎች ሁሉ ትክክለኛና ህገመንግሥታዊ መብት ናቸው። ልክ አንደሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ የመልማት፣ የመጠቀም፣ የለውጥ ጥያቄ ነው እያነሳ ያለው። አንድ መንግሥት እያስተዳደረ እስከሆነ ድረስ መጠየቅ ያለበትን ጥያቅ ነው ይህ ህዝብ የሚያነሳው። ደግሞም መንግሥት የማይመልሰውንና ከአቅሙ በላይ የሆነ ጥያቄ አንስቶ አያውቅም። ስለዚህ ይህንን ጊዜ ወስዶ መፍታትና መተማመን ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡– አደረጃጀቱ ቢኖርም የአመራሩ ችግር እስካለ ድረስ እንዴት ሊፈታ ይችላል ተብሎ ይታመናል?
አቶ መሐመድ፡– ለምሳሌ የፖሊሲ ጥያቄዎች አሉ። አንድ መሬት የምናስተላልፍበት መንገድ በክልሉ ማዕቀፍ የታሰረ ነው። እኛ እና ኮንሶ አንድ ዓይነት ነው መመሪያችን። እኛ እና ከፋ የም እኩል ነን። ይሄ ዞን ለአዲስ አበባም ሆነ ለክልሉ ርዕሰ ከተማ ቅርብ ነው። ይህንን ዞን የሚመስሉና የሚመጥኑ መመሪያዎች የሉም። ይህም ህዝቡ ወጥሮ የሚያነሳውን ጥያቄ በራሳችን አቅም እንኳን ለመፍታት አዳጋች ሆኖብናል። ሌላ ምሳሌ ላንሳልሽ፤ በክልሎች ደረጃ የውሃ ሥራዎች ድርጅት አለ፤ ነገር ግን በዞን ደረጃ ይህንን ድርጅት ማቋቋም አትችይም። ይህም የህዝብን ጥያቄ መመለስ የሚያስችል አሠራር አንድንዘረጋ እንቅፋት ሆኖብናል። መብራት ኃይልም በተመሳሳይ በጉራጌ ዞን ቅርጫፍ ፅህፈት ቤት የለውም። ነገር ግን እኛን አልፎ ሄዶ ሆሳዕና ዲስትሪክት ነው ያለው። ከአምስትና ስድስት ዓመት በላይ ብር የከፈልንባቸው ትራንስፎርመሮች ምንም እንኳን ከሜቴክ ጋር ቢያያዝም አሁንም ያልተፈታ ችግር ነው። አሁን ላይ በእኛ ዞን ለጤና ጣቢያ ትራንስፎርመር ለማገናኘት ዛሬም ሆሳዕና ድረስ ነው የምንሄደው። እርግጥ ነው በዞን ደረጃ ህዝቡ ራሱን እንዲያስተዳድር ዕድል ቢሰጠውም ነገር ግን የበለጠ የመንግሥት አቅምና ኃይል ከመስጠት ባለፈ ለህዝቡ ትክክለኛ መፍትሔ ማምጣት የሚያስችል አቅም የለውም። የሚገርምሽ አንድ ሠራተኛ ቅሬታ ቢኖረው ቅሬታውን ማቅረብ የሚችለው ዛሬም ክልል ድረስ ሄዶ ነው። ይህ ግን ከእኛ አቅም በላይ አይደልም። ከታመነበት የዞኑ አስተዳደር ብቻውን መወሰን የሚችለው ጉዳይ ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ሌላ አንድ ምሳሌ ላንሳልሽ በዞናችን በርካታ ቁጥር ያለው የቀበሌ ቤት አለ። ይህንን ወደ ግል ማዞር አንችልም። ምክንያቱም የክልሉ መመሪያ ይከለክላል። ስለዚህ አካባቢሽን የሚመስሉ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች አውጥተሸ እንዳትሄጂ ያደርግሻል። አርብቶአደር አካባቢ የሚኖር ማህበረሰብና የጉራጌ ዞንን በአንድ መመሪያ ማስተዳደር ፍትሐዊ አይደለም። ወደኦሮምያ ክልል አንዱ ዞንላይ ብትሄጂ ከሠራተኛ ጥቅማጥምም ሆነ ከመሬት አስተዳደር ጀምሮ ያሉ አሠራሮች ከእኛ ጋር ልዩነት አላቸው። ለምሳሌ ወሊሶ ከተማ ከእኛ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የምትገኘው። በእኛ ዞንና ወሊሶ ከተማ ላይ እኩል የተማሩ ሁለት ግለሰቦች እኩል ቢቀጠሩም ደመወዛቸው በጣም ልዩነት አለው። ኑሮ እዚህ ዞን ላይ በጣም ውድ ነው። ከተማ የሚያለሙበት መንገድ ከእኛ በጣም ይለያል። እኛ ከተሞቻችንን እንደፈለግን እንዳንቀይር የሚይዘን መመሪያ አለ። ምክንያቱም ለ56 ብሄረሰብ የወረደው መመሪያ ነው ለእኛ የሚሠራው።
በነገራችን ላይ መቶ ካሬ ሜትር መሬት ለማስተላለፍ ሃዋሳ ልከን ነው የምናፀድቀው። በዚህ ምክንያት ባለሀብቱ እየሸሸብን ነው ያለው። በውጣ ውረድ ብቻ የሚያሳልፈው ጊዜና የሚያባክነው ገንዘብ ተስፋ አስቆራጭ ነው የሚሆንበት። በእነዚህ ችግሮች ምክንያት ህብረተሰቡ የአደረጃጀት ጥያቄ የመመለሱ ነገር የሞት የሽረት አድርጎ እንዲጠይቅ ገፍቶታል። ይህ እንዳለ ሆኖ በአመራር እንዝላልነት በወቅቱ ሥራዎችን ከመሥራት አንፃር ችግር አለ። ለምሳሌ የተረፈሽ ሃምሳ ብር ቢሆንም እንኳን በሚፈለገው ቦታና ጊዜ ከመሥራት አንፃር ይሄ የለም ብለን የምንከራከርበት ሁኔታ አይኖርም። በአጠቃላይ ሥራ ይፈልጋል።
አዲስ ዘመን፡– በትምህርት ተደራሽነት በኩልስ ህብረተሰቡ ምን ያህል ተጠቃሚ ሆኗል ማለት ይቻላል?
አቶ መሐመድ፡– ከዚህ አንፃር ዞናችን ትምህርት ላይ ወደኋላ ተመልሷል። በጥራትም በብዛትም። ይህም ማለት ትምህ ርትን ዘልቆ የሚጨርሰው የህብ ረተሰብ ክፍል እየቀነሰ ነው የመጣው። ትምህርትን አጠናቆ ዩኒቨርሲቲ ከሚገባ ይልቅ በግሉ ተንቀሳቅሶ የሚያገኘውን አስልቶ ትምህርቱን የሚያቋርጠው የህብረተሰብ ክፍል በርካታ ነው። ኑሮውን ለመለወጥ የሚያስችለውን አማራጭ ነው የሚይዘው። ሴቶቻችን ወደ ስደት የመሄድ ዝንባሌ ነው ያላቸው። ለምሳሌ ለአረፋ ወይም ለመስቀል የሚመጣ አንድ የክልሉ ተወላጅ ሁለት ሦስት ሰው ይዞ ነው የሚሄደው። ስለዚህ ባለፉት ጊዜያቶች በትምህርት ላይ እያመጣን የነበረው ውጤት በጣም ዝቅተኛ ነበር።
በርግጥ ትምህርት ቤት በመገንባት ረገድ ብዙ ችግር የለም። ይህንን የትምህርት ጥራት ችግር ለመቅረፍ ከገመገምን በኋላ በሁለት ስትራቴጂዎች ነው የዘረጋነው። አንደኛ ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤት ያስፈልጉናል ብለን ከአምና ጀምሮ አቅደን ዘንድሮ ግንባታው የጀመረ ከ103 ሚሊዮን ብር በላይ በዞኑ በጀት የሚሠራ አዳሪ ትምህርት ቤት አለ። ከወልቂጤ አስር ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ነው የሚገኘው። ይህ ልዩ አደሪ ትምህርት ቤት 400 ተማሪዎችን የሚይዝ ሲሆን፤ ከ8ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ተማሪዎችን የሚቀበል ነው። ይህም በትምህርት ጥራት ላይ ራሳችንን ገምግመን የጀመርነው ፕሮጀክት ነው። ግንባታው በተያዘው በጀት ዓመት ያልቃል።
በዚህ ትምህርት ቤት በጉራጌ ዞኑ ካሉት ከ21ዱም ወረዳዎች የተውጣጡ ተማሪዎችን ነው የሚያስተናግደው። ጥሩ ውጤት ያላቸውን ወንድና ሴት ተማሪዎችን በእኩል መጠን ይቀበላል ተብሎ ነው የሚጠበቀው። በምዕራፍ ሁለት ግንባታውም የመምህራን መኖሪያ፣ ላብራቶሪና ሌሎችንም ሁሉ ግንባታዎች ያካትታል። ይህ ትምህርት ቤት አገልግሎት ማዕከሉ ከፍተኛ ነው። እዚያ የሚገቡ መምህራንም ጭምር አቅማቸው ተፈትሾ ነው የሚገቡት። ከዚሁ ጎን ለጎን ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ጋር ትስስር በመፍጠር ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲደገፍ የሚደረግ ነው የሚሆነው።
በነገራችን ላይ በዞናችን 11 ቴክኒክና ሙያ እንዲሁም ሁለት ፖሊ ቴክኒኮች አሉ። እነዚህ ተቋማት ከ8ኛ እና ከ10ኛ ክፍል የሚወድቁ ተማሪዎች ብቻ የሚማሩበት ሳይሆን ውጤት ኖሯቸው ነገር ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰልጥነው ሥራ መፍጠር የሚችሉ ወጣቶችን የሚያወጡ ናቸው። ይህም ሆኖ ግን ከእነዚህ ተቋማት የሚወጡ ተማሪዎች ቁጥር ገበያው ከሚፈልገው አንፃር ውስንነት አለው። በመሆኑም በርከት ያሉ ተማሪዎች ገብተው የሚሰለጥኑበትን ስትራቴጂዎች ነድፈናል።
በመሆኑም ከአዳሪ ትምህርት ቤቱ ባሻገር መምህራን ኮሌጆች የመገንባት እቅድ አለን። ይህም በተለይ በዞኖ የአካበቢው ተወላጅ የሆኑ መምህራን እምብዛም የሉም፤ አብዛኞቹ ደግሞ ከሌሎች አካባቢዎች የመጡ ናቸው። እነዚህ መምህራን አብዛኞቹ ወደአካበቢው የሚመጡት የሥራ ልምድ ለማግኘት እንጂ በእኔነት ስሜት በዘላቂነት ትውልድ ለመቅረፅ በመትጋት ረገድ ውስንነት ይታይባቸዋል። በዚህ ምክንያት ከፍተኛ የሆነ የመምህራን እጥረት አለብን። በሌላ በኩል የአካባቢውን ማህበረሰብ ቋንቋና ባህልም አለማወቃቸው በራሱ የሚፈጥረው ተፅዕኖ አለው። የሚገርምሽ የመምህራን ኮሌጅ የመክፈት ስልጣን የክልል ነው። ይህም ማነቆ ሆኖ ቆይቶብናል። በአሁኑ ወቅት ግን ጥናት አስጠንተን በክልሉ ካቢኔ ፀድቆልናል። በመሆኑም በቀጣይ ዓመት የመምህራን ኮሌጅ ለመክፈት በዝግጅት ላይ ነው ያለነው። በዚህ ረገድ የባለሀብቱ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነው። በዞናችን 10 ሚሊዮን ብር አውጥተው ትምህርት ቤት የገነቡ ባላሀብት አሉ። በአጠቃላይ የዚህ አካባቢ ማህበረሰብ ለትምህርት የሚያደርገው አስተዋፅኦ ከመንግሥት የሚበልጥ እንጂ የሚያንስ አይደለም። በዞናችን ያለውን ከፍተኛ የሰው ኃይል ፍልሰት ለማስቆምና የተማረ ማህበረሰብ እያጣን እንዳንሄድ ከወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር እየሠራን ነው።
አዲስ ዘመን፡– የዞኑን ማህበረሰብ ከንግዱ ማህበረሰብ ባሻገር በትምህርት የሚያምን ከማድረግ አንፃር የአመለካከት ቀረፃ ላይስ ምን ያህል ውጤታማ ሥራ ሠርታችኋል?
አቶ መሐመድ፡– የዚህ አካባቢ ማህበረሰብ በግድ ትምህርት ተማር የምትይው አይደለም። ይማራል። ግን በሙሉ ቀልቡ ነው ወይ የሚማረው? ብትይኝ እርግጠኛ አይደለሁም። አብዛኛው ተማሪ ትምህርቱን ይጨርሳል። ነገር ግን በውጤት ስትመዝኚው ስኬታማ ነን ለማለት አልችልም። ጥራትም ሆነ ውጤታማነት ረገድ ብዙ ይቀረናል። አብዛኛው የተማረ የምትይውም ኃይል ሥራ ፍለጋ ይሰዳደል። ሴት ተማሪዎችም በብዙ ኃላፊነት ውስጥ ሆነው የሚማሩ በመሆናቸው በውጤት ደረጃ አመርቂ አልነበሩም። በመሆኑም የምናሳልፈው ተማሪ መጠን 48ና 50 በመቶን መሻገር ካልቻለ ደንገጥ ማለት ይገባናል። በዚህ ረገድ ይህ ለምን ሊሆን እንደቻለ ለማጥናት ሞክረናል። ይህንን የአመለካከት ችግር ለመቅረፍ እየሠራን ነው።
አዲስ ዘመን፡– በዞኑ የጤና ተቋማት ተደራሽነትስ ምን ደረጃ ላይ ነው ያለው?
አቶ መሐመድ፡– ከጤና ተቋማት አንፃር የጎላ የሚባል ችግር የለብንም። በዞናችን የመጀመሪያ ደረጃ ፣ ሪፈራልና ቲቺንግ ሆስፒታሎች አሉን። ነገር ግን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የለንም። በቅርቡ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ መጥተው ነበር። ያለውን ችግር ተመልክተዋል። ባሉት አጠቃላይ ሆስፒታሎች ላይ በተሻለ መንገድ ተደራሽ ለመሆን ቃል ገብተውልናል። በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሆነ የአምቡላንስ ቁጥር አለ። በፊት ግን በአንድ ወረዳ አንድ አምቡላንስ ብቻ ነው የነበረው። ሪፈርም ወለሶ ነበር የሚኬደው አሁን ግን ይህ ቀርቷል። በአጠቃላይ በቅርብ ርቀት የጤና ተቋማት ከማግኘት አንፃር በብዙ መልኩ መሻሻሎች አሉ። የመንግሥትም የትኩረት አቅጣጫ በመሆኑ አስፈላጊው ድጋፍ እየተደረገ ነው ያለው።
አዲስ ዘመን፡– ከዚህ ጋር ተያይዞ በዞኑ የኮረና ወረርሽኝን ለመከላከል የሚደረገው እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ መምጣቱን አስተውለናል። በተለይ ህብረተሰቡ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ጥንቃቄ እያደረገ አይደለም። ከዚህ አንፃር ያለውን ችግር ለመፍታት ምንአስባችኋል?
አቶ መሐመድ፡– በዚህ ረገድ ያለው ችግር በዋናናት የእኛ ነው። እኛ ለማህበረሰቡ ምሳሌ መሆን ባለመቻላችን ነው በዚህ ደረጃ ህብረተሰቡ እየተዘናጋ ያለው። በርካታ ቁጥር ያለው ህዝብ ሰልፍ እያስወጣን፣ በልቅ ሁኔታ ህዝብ እየሰበሰብን ከእኛ ምን ሊማር ይችላል?። በመሆኑም እኛ አርዓያ መሆን ያለመሆናችን ውጤት ነው ባይ ነኝ። በመሆኑም ይህ ችግር እያለ ህብረተሰቡ ላይ መፍረድ አይቻልም። በዓለምአቀፍ ድረጃ ጥንቃቄው አንዳለ ነው። እኛ ግን በሽታው ጠፋ የተባልን ያህል ከላይ ጀምሮ መዘናጋታችን ዋጋ እያስከፈለን ነው ያለው። በተለይም የወጣውን አዋጅ ማስተግበር አልቻልንም። ምንም እንኳ እስከአሁን በዞናችን ቦኮቪድ ያጣነው ሰው ሁለት ብቻ ቢሆንም የሚያዘው ሰው ቁጥር እያደገ ነው ያለው። የእምነት ተቋማትም ህብረተሰቡን ወደአልሆነ መንገድ ነው እየመሩት ያሉት። አንድ ቀብር ላይ እንዳውም የመጡትን ሰዎች ሁሉ ማስክ መንጠቃቸውን ሰምተናል። ይህም ከፍተኛ የሆነ የግዛቤ ችግር መኖሩን ያስገነዝባል። እርግጥ ነው ኢትዮጵያ የአማኞች አገር ናት። ነገር ግን የሃይማኖት አባቶች ልቅ መሆንና የመሪዎች ሚናቸውን በበቂ ሁኔታ አለመወጣት ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ነው። በመሆኑም ከሁሉም አመራር አዋጁን በተጨባጭ ሥራ ላይ አንዲውል ኃላፊነታችንን መወጣት ይገባል። በመንግሥት ተቋማትም ያለማስክ አገልግሎት እንደማይሰጥ ለህብረተሰቡ ማስገንዘብና በአግባቡ መተግበርም ይገባናል። ያልሽው ችግር ግን ትክክል ነው። መንግሥት የመሪነት ሚናውን መወጣት መቻል አለበት።
አዲስ ዘመን፡– በአጠቃላይ የዞኑ ማህበረሰብ የሚያነሳውን ጥያቄ በሚመለከት ከክልሉ መንግሥት ያገኛችሁት ምላሽ ምንድን ነው?
አቶ መሐመድ፡- የደቡብ ክልል አሁን ያለበት ሁኔታ የሚታወቅ ነው። አሁን ላይ አመራሩ በአጠቃላይ የአደረጃጀት ጥያቄ ለመመለስ እየጣረ ነው ያለው።
በእርግጥ ከዚህ ቀደም በክልሉ መረጃ የምናደርስበት፣ እቅዶችን የምናቀርበበት ስርዓት ጠንካራ ነበር። አሁን ላይ ግን ሁሉም እሳት ማጥፋት ዘመቻ ላይ ነው ያለው። እያንዳንዱ አመራር ሩጫ ላይ ነው። በፊት ግን በየጊዜው ከአመራር ጋር የምትገናኚበት መንገድ በጣም ጥብቅ ነበር። አመራሩን በቅርበት አግኝተሽ ቅሬታ የምታቀርቢበት እድል ነበረው። አሁን ያ ስርዓት የለም። ችግር ካልተፈጠረ በስተቀር ሰላማዊ አካባቢዎች ላይ ትኩረት እየተሰጠ አይደለም። ሌላው ይቅርና ከዚህ ቀደም ተሠርተው የነበሩና የወደሙ ብዙ ንብረቶች እንኳን አልተጠገኑም። እነዚህ ድምር ችግሮች በምንፈልገው ደረጃ ኃላፊነታችንን እንዳንወጣ አድርጎናል። ግን አስቀድሜ እንዳልኩት ለአገራዊ ሰላም ተጨማሪ ችግር ላለመፍጠር በዝምታ ችሎ ነው ያለው።
አዲስ ዘመን፡- በዞኑ ቀቤና አካባቢ ተፈጥሮ የነበረው ችግር በዘላቂነት ከመፍታት አኳያ ምን እየተሠራ ነው?
አቶ መሐመድ፡- እንደሚታወቀው በዞናችን ሦስት ብሄረሰቦች አሉ። ጉራጌ፣ ማረቆና ቀቤና ማህበረሰብ አለ። በማረቆና በመስቃን አካባቢ የተፈጠረ ችግር አለ። የሰው ህይወት አጥተናል። የህይወት ዋጋ ተከፍሏል። ብዙ ተፈናቃዮች አሉ። የክልሉ መንግሥት አቅጣጫ አስቀምጦ አሁንም ሥራ ላይ ነው ያለው። በህብረተሰቡ መካከል ሰላማና አንድነት ለማምጣት ብሎ በዞኑ የተፈጠሩ ችግሮችን ሙሉ ለሙሉ ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው። በዚህ አካባቢ ያሉትን ጥያቄዎች በፌዴራል መንግሥቱ የሚመለሱ ቢሆንም ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በአሀገር ሽማግሎዎችና በዞኑ አመራር ትብብር ሥራዎች እየተሠሩ ነው ያሉት።
አዲስ ዘመን፡– የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ቡታጀራ ካምፓስ ለመክፈት እያደረገ ላለው ጥረት የዞኑ አስተዳደር ምንዓይነት ድጋፍ አድርጓል?
አቶ መሐመድ፡– በነገራችን ላይ የዞን አስተዳደሩ የዩኒቨርሲቲው ምክትል የቦርድ ሰብሳቢ ነው። እንዳልሽው በቡታጀራ ካምፓስ ለመክፈት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያ ደሳለኝ ቃል ገብተው ነበር። ያኔ የተገቡ ቃሎች ናቸው አሁን ላለው አመራር ፈተና እየሆኑ ያሉት። ይህ ጉዳይ የእኛም ጥያቄ ነው። የዚያ አካባቢ ማህበረሰብ እንደማንኛውም ኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት አገልግሎት ሊያገኝ ይገባዋል። ይህ ህገመንግሥታዊ መብቱ ነው። እዚያ ያለው ማህበረሰብ ግን አሁንም በጉጉት ነው እየጠበቀ ያለው። ነገር ግን በትምህርት ሚኒስቴር በኩል በቂ ጥኩረት ሳይሰጠው ነው የቆየው። በቦርድ ደረጃ በተደጋጋሚ ውይይት አድርገንበታል። ነገር ግን ይህ ጉዳይ ከእኛ አቅም በላይ ነው። ቃል የተገባው ነገር ወደ መሬት አንዳይወርድ በአሠራር የተዘጋ በመሆኑ ነው።
አዲስ ዘመን፡- በዞኑ በሶዶና ቡታጀራ አካባቢ ያለው ማህበረሰብ ከሌላው የዞኑ ወረዳዎች አንፃር ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በተደጋጋሚ ያነሳሉ። ይህንን የፍትሐዊነት ጥያቄ ከመመለስ አንፃር የዞኑ አስተዳደር ምን ያህል ጥረት አድርጓል?
አቶ መሐመድ፡– እንዲህ ዓይነቱ የፍትሐዊነት ጥያቄ ሁሉም ቦታ ያለነው። በነገራችን ላይ ትክክለኛ ፍትህ ከፈጣሪ ነው የሚገኘው። በአሠራር የተፈጠሩ ችግሮች እንዳሉ እሙን ነው። ያም ቢሆን ግን ለምሳሌ የቡታጅራና የወልቂጤ ከተማ እድገት ተቀራራቢ ነው። ፍትህ ማምጣት በመሪ ደረጃ ከባድ ነው። ምክንያቱም ፍትህ የሚያዛባውም አመራር በመሆኑ ነው። በዞኑ ምክር ቤት የሁሉም ወረዳ ተወካዮች ያሉበት በመሆኑ የወከለውን ህዝብ ጥያቄ ማቅረብ ይገባዋል የሚል እምነት አለኝ። በእኛ ደረጃ እንደገመገምነው በዞናችን የመልካም አስተዳደር፣ የፍትህና የሰላም ጥያቄዎች መመለስ አለባቸው። የፌዴራል መንግሥቱም ሆነ የክልሉ መንግሥት የፍትሐዊነት ጥያቄ አንዳለባቸው ሁሉ ዞኑም ፍፁም ሊሆን የሚችልበት እድል የለም። ወረዳም ብንወርድ ተመሳሳይ ችግር አለ። አመራሩ የራሱ ቀበሌ፣ የራሱን መንደር ነው የሚያለማው የሚሉ መሰል ጥያቄዎች ይነሳሉ። ይህ በአመራር ስርዓት ውስጥ ያለ ማነቆ ነው። በዚህ ረገድ በቀጣይ ሊፈታ ይገባል የሚል አቅጣጫ አስቀምጠናል። እንደአጠቃላይ ግን ዞኑ በራሱ አስቀድሜ አንዳልኩሽ በፍትሐዊነት የልማት ተጠቃሚ ባለመሆኑ የክልሉን ተወካዮች የሚመደበው በጀት ምን ላይ እንደዋለ መጠየቅ ይገባል።
አዲስ ዘመን፡- የዞኑ ማህበረሰብ በሌሎች ከተሞች ላይ ያበረከተውን አስተዋጥኦ ያህል ለዞኑ ልማት የበኩሉን ሚና እንዳይጫወት ያደረገው አብይ ምክንያት ካለ ይጥቀሱልኝ?
አቶ መሐመድ፡– እንዳልሽው የእኛ ማህበረሰብ በሌሎች አካባቢዎች ላይ በርካታ ልማቶችን አምጥቷል። በእኛም ዞን ላይ ከመንግሥት መፎካከር የሚችል አስተዋፅኦ እያደረገ ነው። ይሁንና ይህ በተናጠል ባለሀብቱ የሚያደርገውን አስተዋፅኦ በጋራ የማስተባበር ሥራ ሠርተናል ለማለት አልችልም። ጠንካራ ማህበርም አልፈጠርንም። ልማት ማህበር መንግሥት በተቀያየረ ቁጥር የሚቀያየር ነው። የልማት ማህበሩ ያለመጠናከሩ ደግሞ ውጤታማ የሚባል ሥራ እንዳይሠራ አድርጎታል ባይ ነኝ። በሚፈለገው ደረጃ ባለሀብቱንም ሆነ ሌላውን የክልሉ ተወላጅ አቀናጅተን መሥራት ባመቻላችን ነው እዚህ ግባ የሚባል እድገት በዞናችን መምጣት ያልቻለው። በመሆኑም በቀጣይ በርካታ የቤት ሥራዎች አሉብን። እዚህ ላይ ትኩረት አድርገን መሥራት ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን፡– ለሰጡን ሰፊ ማብራሪያ በአንባቢዎቼና በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።
አቶ መሐመድ፡– እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን መጋቢት 4/2013