
ሰላም በሰው ልጆች መካከል መተኪያ የሌለው የሕልውና መሰረት ነው። ከተሰጡን ስጦታዎችም ሁሉ በላጩ ነው። በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የጋራ ታሪክ ሰንደው ለሚኖሩ ሀገራት ትርጉሙ ለየት ይላል። አሁን አሁን የዘመናዊነት መለኪያ እየሆነ መጥቷል። አንድ ሀገር ከቴክኖሎጂና ከግዙፍ ኢኮኖሚው ባለፈ የሰላም ዋስትናው ላለበት የዘመናዊነት ቁመና ሚዛን የሆነበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።
ሰላማዊነት ሀገር የምታድግበት፣ ሕዝቦች የጋራ እሴቶቻቸውን በመከባበር እና በመቻቻል የሚጠቀሙበት ከፍ ሲልም ለልማት እና ለመሰል አስፈላጊ ሁነቶች ላይ የሚሳተፉበት ነው። እንደ ሀገር በርካታ የተፈጥሮ ሀብቶች ተሰጥተውናል። ሀብቶቻችንን ወደልማትም ሆነ ወደ ኢኮኖሚ ለመቀየር አስተማማኝ ሰላም ያስፈልገናል።
ተነጋግሮ መግባባትም ሆነ ተግባብቶ አብሮ መኖር እጅግ አስፈላጊ በሆነበት ጊዜ ላይ ነን። በሀገራችን የተለያዩ ቦታዎች የሚነሱ ግጭቶች እና አለመግባባቶች ምክንያታቸው ብዙ ቢሆንም ወደ መፍትሄ ለመምጣት ተነጋግሮ መግባባት ያስፈልጋል። ችግሮቿን በውይይት የማትፈታ ሀገር ጫንቃዋ ላይ ቀንበር የወደቀባት ናት። ቀንበሩ የድህነት፣ የኋላቀርነት፣ የጥላቻ እና የዘረኝነት ነው። ይሄ ቀንበር ከሀገራችን ጫንቃ ላይ እንዲነሳ ውይይትን ያስቀደመ የፖለቲካ ልዩነት ያስፈልገናል።
ልዩነቶቻችን ለመገዳደል ጽንፍ ካስረገጡን ሀገራችን የእኛ አትሆንም እኛም የሀገራችን አንሆንም። ሀገርና ሰው ውሀ የሚያነሱት በሰላማዊነት በኩል ነው። ድህነት ባደቀቃት እና የዜጎቿ መሰረታዊ ፍላጎት ያልተመለሰባት ሀገር ላይ ጦርነት ሌላ መዘዝን ከመፍጠር ባለፈ ለጥያቄዎቻችን መልስ አይሰጠንም።
ሀገርን ሜዳ አድርጎ የይዋጣልን ትግል ለማንም አይጠቅምም። ሀገርን ሜዳ አድርጎ መወያየት እንጂ የይዋጣልን ነጋሪት አያስፈልግም። የሰላም ነጋሪቶች በጥይት አረር ከወንድሞቹ ጋር ለሚጋፋው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ወሳኝ ነው። ተታኩሰን፣ ተጋድለን፣ ገለንና ሞተን ወደ አዘቅት ከመውረድ ባለፈ የመለስነውም ሆነ ያስመለስነው ጥያቄ የለም። በአፈሙዝ የሚመለስ ጥያቄ እንደሌለ እና እንደማይኖር ያለፉ ታሪኮቻችን መስካሪዎች ናቸው።
ሀገር ከሰጡን ቀደምት የታሪክ ውርስ መሀል ባሕላዊ የእርቅ አፈታት ሥርዐታችን አንዱ ነው። በእቅፎቻችን በሸንጎና በዋርካ ጥላ የሚጠሩ በርካታ የእርቅ ልማዶች አሉን። ከእሴቶቻችን አፈንግጠን እንቢተኝነትን ወረስን እንጂ ሥርዐቶቻችን እኛን ለማረቅም ሆነ ለመግራት አቅም ያላቸው ነበሩ።
ተፈጥሮ ሰላም ትሻለች። የሰው ልጅ ካለሰላም ሕይወትን መድፈሪያ አንዳች ኃይል አልተሰጠውም። ሰላም ሰው እና ተፈጥሮ የተሳሰሩበት ገመድ ነው። ገመዱ ሲላላ ሀገር ታዘማለች። ሀገር ስታዘም ታሪክ እና ሉአላዊነት ጥያቄ ውስጥ ይገባሉ። ከዚህ በኋላ የሚመጣው ሁሉ የጋራ ጠላታችን ሆኖ በአንድ የሚጠራ ይሆናል።
ሁልጊዜ አንድ አይነት ተረት ተረት ጥሩ አይደለም። ተረት ቢኖር እንኳን” አፌን በዳቦ አብሱ ”የሚል መቋጫ ያስፈልገዋል። ማን እንደፈጠራቸው፣ በማን እንደተተረቱ በማናውቃቸው እና አፌን በዳቦ አብሱ በሌላቸው የሞት ትርክቶች መገዳደል ይበቃል። ሰማያችን ጉም አትኖ ደም አርግዟል። ቀዬው የአበቦች ሽታን አስወግዶ የጥላቻ መርዶን ታቅፏል። በላይ እና በታች ሰፈር ቡና ሲጠራሩ የነበሩ ጎረቤታሞች በዘረኝነት ተራርቀዋል። እናስ አልታመምንም? መድሀኒት ያስፈልገናል። ከተቻለ ቅድመ መከላከያ ካልተቻለ ደግሞ በበሽታችን ላይ ማገገሚያ ግድ ይለናል።
በሳቅ ስም የሚጠሩ በገጻችን ላይ የተሳሉ የንጋት ጮራዎች በሰላም በኩል ያገደሙ ናቸው። ሀገራችን ሰላም ጠምቷታል። ሰው በሚለው የተፈጥሮ ስማችን እንጠራራ፣ እንጠያየቅ። ብሄርተኝነት ፖለቲካ ወለድ ነው። ሰውነት ግን የተፈጥሮ መልክ ነው። ተፈጥሯችንን ሽረን በሰውኛ ስለተጠራን ነው ያጎነበስነው። ወደ ሰውነት እንመለስ።
ሰው ሀገር ሲያጣ..ሀገር ሰው ሲያጣ እኛን እየመሰለ ነው..አዎ እኛን ሀገር አጽኚዎቹን እኛን። በዚህ ልክ ወደኋላ መመለስ ይቻላል? ከከፍታ በመውረድ በዚህ ልክ ወደኋላ መመለስ እንደሚቻል አላውቅም ነበር። አትጠራጠሩ ሀገር ሰው ከሌለው የመቃብር ቦታ ነው። መቃብርን ማን ይደፍረዋል? ንጋትን ያበሰሩልንን እልፍ ጸሀዮቻችንን ቀብረን፣ ሕይወት ያለመዱንን የፍቅር ቀንበጦቻችንን ገንዘን እንኳን የማንደርስበት ቦታ አይደል? መቃብር በአበባዎች እና በባለመዐዛ ዛፎች ቢሞላ ምንድነው ትርጉሙ? ሀገር የሌለው ሰው..ሰው የሌለው ሀገርም እንዲሁ ነው።
ሀገር ማንነት እንደሆነ እናውቃለን። የአንተና የኔ፤የዚህኛው እና የዛኛው። ይሄኛው እና ያኛውስ ምንድነው ለሚለው ይሄኛው እኔ እና የፊቱ ነን፣ ያኛው ደግሞ እኔና አባቶቼ ናቸው። ይሄኛው ሕልሜ፤ ክብሬ እና ታሪኬ ያለበት ነው። ነገዬ እና ከነገዬ ጋር የሸከፍኩት እኔና እኔን መሳዬ ነው። ይሄኛው የሕልውናዬ መደብ ነው..የኑባሬዬ ሀሌታ። ያኛውስ? ዛሬን የሰጠኝ ተስፋ ላደረኩት ነገ ያጸናኝ መነሻዬ ነው። ሀገር ማንነት ነጭ ማለት ይኸው ነው።
ሀገር መጠበቅ ማንነትን መጠበቅ ነው። አሁን ላይ እንደዘር ብዙ ነውረኛ ትርክቶች ተዘርተውብናል። እነዚህ ዘሮች አድገው የባሰ ችግር ከመፍጠራቸው በፊት መቀንጨር አለባቸው። ብዙሀኑ ኢትዮጵያዊ ተከባብሮ እና ተሳስሞ የሚኖር የልብ ወዳጅ ነው። ክፋትን አያውቀውም። ጥላቻውን አለመደም። ሲበድል ወደፈጣሪው ይቅር በለኝ የሚል ሲበደል ደግሞ ለፈጣሪ የሚናገር ሕዝብ ነው።
ዋቃ፣ ረጲ፣ ማጋኖ፣ ጦሳ የመሳሰሉት የፈጣሪ ስሞች ብዙ ብሄረሰብ ከፈጣሪ ጋር ሕብረት ያበጁበት የእምነት ድልድይ ነው። እያየናቸው ያሉ መከፋፈሎች እግዚአብሄር ከሌላቸው ልቦች ቢኖራቸው እንኳን እንደቃሉ ካልቆሙ ልቦናዎች መሀል የሚፈልቁ ስለመሆናቸው አያጠራጥርም።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ብሄር ሳይጠይቅ እና ሀይማኖት ሳይል አንዱ ከሌላው የተሳሰረ ነው። ትስስሩ በመከባበር በመቻቻል እና በመፈቃቀር መሆኑ ደግሞ አይካድም። በዚህ ማንነቱ መሀል ፈርሀ እግዚአብሄርን አኑሯል..እናስ ይሄ ሕዝብ ዘረኛ ነው ማለት ይቻላል? የኢትዮጵያ ሕዝብ ነውርን የሚጠየፍ ሕዝብ ነው።
አይደለም እርስ በርስ ሊገዳደል ጠመንጃ ሊወለውል ቀርቶ ለእንስሳ የሚራራ ነፍስ ያለው ነው። ግን ከኋላ ይገፋል። ወዳጁ የሆነው እና ብዙ ዘመናትን አብሮት ያሳለፈው ጎረቤቱ ጠላቱ እንደሆነ በክፉ ፖለቲከኞች ይነገረዋል። እንደዛም ሆኖ የሚጨክን ልብ የለውም።
አህያ ከእንስሳት ሁሉ በራስ ወዳድነቷ ትመሰላለች። ለዚህ ግብሯም እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል አይነት ብሂል ሰጥተዋታል። ልክ እንደ አህያዋ ራስ ተኮር ፖለቲከኞች ተፈጥረዋል፣ እየተፈጠሩም ይገኛሉ። ልክ እንደ እንስሳዋ ከሰውነት ግብራቸው አንሰው እንስሳዊ ባህሪን የተላበሱ ጥቂቶች አይደሉም።
ያበላሹን እኔ ከሞትኩ ሰርዶ ለምኔ እንዳለችው አህያ ያሉ ፖለቲከኞች ናቸው። ፍቅራችንን በጥላቻ የመነዘሩት እነዛ..አዎ እነዛ በተሳሳሙ ጉንጮች መሀል ጎጠኝነትን ያተሙት እነሱ ናቸው። እንዴት ሕዝብ በግለሰብ ይለወጣል? እንዴት ብዙሀነት በአንድ ራስ ይቀየራል? አንዳንዶች ኢትዮጵያን በራሳቸው ቀይረዋታል።
ሰፊውን ሕዝብ በግለሰብ ለክተውት ራስ ተኮር ፖለቲካ እና መንደር ተኮር ፍልስፍናን እያራመዱ ይገኛሉ። ለዚህ እኮ ነው የራስ ሀገር፣ የራስ ክብር ያጣነው። በዚህ እኮ ነው የሉአላዊነት ካቦቻችን ተንደው ከመሬት የወደቀን ተባብሮ ማንሳት ያቃተን። ለዚህ እኮ ነው..ለዚህ እኮ ነው..።
በእኔ በአንተ እጣ ተጣጣልንባቸው እንጂ ታሪኮቻችን የጋርዮሽ ናቸው። ትውልድ በትውልድ ሲበለጥ ምሳሌ የሚያደርገው እኛን ነው። በፊተኞቻችን ተበልጠናል። እነሱ ስለሀገር ሲሞቱ እኛ ስለብሄር እንሞታለን። እነሱ ስለ ኢትዮጵያ ሲወድቁ እኛ ስለክልል እንወድቃለን። እነሱ ስለሰብዐዊነት ሲደክሙ እኛ ስለእኔነት እንደክማለን።
በሥርዐት የተሰደሩን ጡቦች በአይነልቦናችሁ እስኪ አስቡ! እነዚህ ጡቦች በብዙ ክንዶች በኩል ያማረ ቤት ሰርተዋል፣ ያማረ ሕንጻ ማግረዋል። ከጡቦቹ መሀል አንድ ብትመዙስ? ሁሉም ነገር እንዳልነበረ ይሆናል፤ ኢትዮጵያ ያማረችው እንደጡቦቹ በብዙ ክንዶች በኩል በሥርዐት ስለጸናች ነው። አሁን ላይ በእኔ በአንተ ክፍፍል ከጡቡ ላይ የየድርሻችንን እያነሳን ነው።
ጆንያ ያለ እህል መች ይቆምና? ሀገርስ ያለሰው ምን ውበት አላት? ውበቶቻችን የተውናቸው እና የረሳናቸው አልፎ ተርፎም በጥላቻ የመነዘርናቸው እሴቶቻችን ናቸው። ድምቀታችን በሰብዐዊነት የተገነቡ ራሮቶች ሰው ከሚለው ስም ጋር የተሰጡን የጸጋ መጠሪያዎቻችን ናቸው። እኚህ ስሞች ከየትኛውም ሀገርና ሕዝቦች በላይ እኛጋ ዋጋ ያላቸው ናቸው።
ሰፊ ሰማይ ነን። ሰማያችን ለብዙ ከዋክብት ይበቃል። ለሁሉ በሚበቃ ሰፊ ግዛት ላይ እኔ ብቻ ካልበራሁ፣ እኔ ብቻ ጨረቃን ካልሆንኩ ማለት አይሰራም። እንዲህ ያሉ ንትርኮች ብርሀን አልባ ሰማይን ከመስጠት ባለፈ ትርጉም የላቸውም። ሰፊ ሰማይ አለን አብረን በርተን አብረን መድመቅ እንችላለን።
ሀገራችንን በወዛችን መፍጠር አለብን። በዚህ ዘመን ላይ በይቅርታ ተሟሽቶ በጥላቻ የጎሸ ልብ የሁላችን ሆኗል። ተቃቅፈን እንኳን እንፈራለን። የተቃቀፈ መች ፈርቶ ያውቅና ፈራን? የተሳሳመ መች ሰግቶ ያውቅና ይሰጋል? ቀፏችን ውስጥ ማር ሳይኖር ባለማር እንደሆንን በሚነግሩን ሰዎች መሀል ነን። አበባችን ፍሬ ሳያፈራ ፍሬአማ እንደሆንን በሚዋሹን ፖለቲከኞች ጥላ ስር ነን። ለራሳቸው ሲሉ በሚያታልሉን ተከበናል።
ለጦርነት ያሰላናቸው ካራዎች ክቡር ያደረግንውን የሰው ልጅ ከማድማት በስተቀር ትርጉም የላቸውም። ቀስቶቻችን አልመው ከመግደል ባለፈ ትርፍ የላቸውም። ግድግዳዎቻችን ማሲንቆና ክራር አውርደው መሳሪያ ሰቅለዋል። ድብኝት እና ቡሀቃችን ዱቄት እና ጥሪታቸውን ትተው መሳሪያ ማከማቻ ሆነዋል።
ሰፊ ሰማይ ነን..ሰማያችን ላይ ተባብሮ ከማብራት ውጪ ምንም አማራጭ የለንም። ምርጫችን ሀገር ናት። ምርጫችን ሕዝብ ነው። ይሄ ሁሉ ደግሞ በአብሮነት ይጸናል። እኔ ከእናንተ ነኝ እናንተም ከኔ ናችሁ። ሀገር ማንነት ናት ስል እናንተን ተመልክቼ ነው። ያለእናንተ እኔ ማነኝ..? ምንስ መሆን ይቻለኛል? ያለእኔስ እናንተስ ምንድናችሁ? ምንስ መሆን ይቻላችኋል?
ከእኛ በስተቀር ወደኋላ መቅረት ማንን ይመስላል? የጦርነት እስክስታዎች እያጎደሉን ነው። ከማንም በፊት ቀድሞ በመንቃት ላንቀላፋው ዓለም ብስራት የሆነ ማንነታችን ወዴት ተሰወረ? ቀድሞ በመንቃት የክብር ባለቤቶች ነን። የዛሬ መጠሪያችን ግን ድህነት፣ ኋላቀርነት፣ ጦርነት ሌላም ሌላ ነው.. እና ይሄ አያሳፍርም? ከከፍታ ወደዝቅታ ማለት ይሄ አይደል? ከአሳዳጅ ተሳዳጅነት መመለሻችን መቼ ይሆን?
በትረ ሙሴ (መልከ ኢትዮጵ)
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም