
ሰኔ 16/2017 ዓ.ም (አዲስ አበባ) የኢፌዴሪ የስራና ክህሎት ሚኔስቴር በውጭ ሀገራት የሚሠሩ ኢትዮጵያውያንን መብት፣ ደህንነት እና ዘላቂ ጥቅም ለማስጠበቅ ያለመ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ አቅርቧል።
ረቂቅ አዋጁ ግንቦት 21 ቀን 2017 ዓ.ም ለሚኒስትሮች ምክርቤት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ መወሰኑ ይታወቃል።
ይህን ተከትሎ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ረቂቅ አዋጁን መርምሮ ሰኔ 5 ቀን 2017 ዓ.ም ለሰው ኃይል፣ ስራ ስምሪትና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቶታል። ረቂቅ አዋጁ አስፈላጊውን የሕግ ሂደት አልፎ ሲፀድቅ በስምሪቱ የዜጎችን መብት፣ ደህንነትና ዘላቂ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የሚያስችል ነው።
የስራና ክህሎት ሚኒስቴር በስራ ዕድል ፈጠራ መስኩ ለሀገር ውስጥ የስራ ዕድል ፈጠራ ስራው ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል። ከዚህ ባሻገር ዓለም አቀፍ የስራ ገበያው ለስራ ዕድል ፈጠራ ያለውን እምቅ አቅምም አሟጦ ለመጠቀም፣ ሕጋዊ የስራ ስምሪቱን ለማበረታታትና የዜጎችን መብት ደህንነትና ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እንዲሁም ሀገር ከዘርፉ የምታገኘውን ጥቅም ለማሳደግ የውጭ ሀገር ስራ ስምሪቱን ለማዘመን በትኩረት እየሠራም ይገኛል። ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ሀገራት በተለይም በመካከለኛው ምስራቅ የሚገኙ ዜጎቻችን ከፍተኛ እንግልት ሲደርስባቸው እንደነበር የሚታወስ ነው።
በስራ ላይ የሚገኘው የሕግ ማሕቀፍ (አዋጅ ቁጥር 923/2008 በኋላም የተሻሻለው አዋጅ 1246/2013) ካለው ነባራዊ ሁኔታ በተለይም የዜጎችን መብት፣ ክብርና ደህንነት ከማስከበር አንጻር በርካታ ክፍተቶች የሚስተዋልበት ነው። አብዛኛው ኤጀንሲዎች የዋስትና ገንዘብ ሕጉ በሚፈቅደው መልኩ ስለማያስቀምጡ ለስራ ያሰማሯቸው ዜጎች ችግር በሚገጥማቸው ጊዜ በወቅቱ ተገቢውን ምላሽ እንዳያገኙ ተግዳሮት ሆኖ መቆየቱን እንደ አብነት ማንሳት ይቻላል።
በዘርፉ የተደረገውን ሪፎርም ተከትሎ መንግስት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በልዩ ትኩረት ሲሠራ ቆይቷል። በዚህም ዜጎችን ወደተለያዩ ሀገራት በሕጋዊ መንገድ ለመላክ የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነቶችን ከመፈራረም እና የመዳረሻ ሀገራት ከማስፋት ጀምሮ ሀገር ውስጥ ያሉ የሕግ እና የአሠራር ክፍተቶችን ለመሙላት በሚኒስቴር መስሪያ ቤታችን በኩል የተለያዩ ስራዎች እየተሠሩ ቆይቷል። የዚህ ስራ መሰረት፤ መነሻ እና መድረሻም የዜጎችን ክብር፣ ደህንነትና ዘላቂ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ነው።
በቅርቡ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ ለተከበረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመራው ኢትዮጵያ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ረቂቅ አዋጅም ግብና ዓላማውም ይሄው ነው። የዜጎችን መብት፣ ደህንነት፣ ክብር እና ዘላቂ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ፤ በዘርፉ የሚስተዋሉ ሕገወጥነቶችን መግታት እና ሀገራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ የረቂቅ አዋጁ ዋና ዋና ዓላማዎች ናቸው።
የረቂቅ አዋጁ ቁልፍ ማሻሻያዎች
ደረጃ ያለው የፍቃድ አሰጣጥ ስርዓት – አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ኤጀንሲዎችን በአምስት ደረጃዎች ይከፍላቸዋል። ደረጃው ኤጀንሲዎች በሚያሰማሩት የሰው ኃይል ብዛት፣ ክህሎት፣ የሙያ ዘርፍ፣ መነሻ ካፒታል እንዲሁም ተያያዥ መስፈርቶችን ታሳቢ ያደረገ ነው። ነባሩ የሕግ ማሕቀፍ ግን ሁሉንም በአንድ ምድብ የሚመለከት ነበር።
- የተቀነሰ የገንዘብ ዋስትና
- አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ኤጀንሲዎች በባንክ ዝግ አካውንት
- እንዲያስቀምጡ የሚገደዱት ዝቅተኛ ገንዝብ ከ100 ሺህ ወደ 50 ሺ ዶላር ዝቅ እንዲል አድርጓል።
- ጥብቅ የፋይናንስ ቁጥጥሮች ኤጀንሲዎች ለዋስትና የሚያሲዙት ገንዘብ በካሽ በባንክ እንዲቀመጥም ያስገድዳል።
ይህ ገንዘብ የዜጎችን ደህንነት ለማስከበር የሚውል ሲሆን ኤጀንሲዎች ለላኳቸው ዜጎች ተገቢውን ኃላፊነት እንዲወስዱ እና ዜጎችም ችግር ውስጥ ከገቡ ያለ ምንም ውጣ ውረድ ወደ ሀገራቸው ክብራቸው ተጠብቆ እንዲመለሱ ሙሉ ወጪን ለመሸፈን የሚውል ነው።
ግልጽና ከሰው ንክኪ ነፃ የሆነ የአሠራር ስርዓት – በዘርፉ የሚደረገው የስራ ስምሪ፣ የስልጠና ምደባ፣ የብቃት ምዘናና የአየር ትኬት መቁረጥን ጨምሮ ሁሉም አገልግሎት ዲጂታል በሆነ ስርዓት እንዲሰጥ የሚያደርግ ነው። ለዚህም የኢትዮጵያ የስራ ገበያ መረጃ ስርዓት ለውጭ ሀገር ስራ ስምሪቱ አገልግሎት የሚሰጥበት ብቸኛው ስርዓት ነው።
የስራ እና ክሕሎት ሚኒስቴር አሁን ለውይይት የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ሲያዘጋጅ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላትን ለማሳተፍ ጥረት አድርጓል። በተለይ የውጪ ስራ አገናኝ ኤጀንሲዎች የስራና ክሕሎት ሚኒስቴር ሚኒስትር እና ሚኒስትር ዴኤታዎች በተገኙበት ሁለት ጊዜ ውይይት አድርገውበታል። በቀጣይም አዋጁ ከመጽደቁ በፊት ከሕዝብ የሚሰበሰብ ጥያቄን ጨምሮ በተከበረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሰፊ ውይይት የሚደረግበት በመሆኑ ሁሉም የዘርፉ ተዋንያንና ሕብረተሰቡ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ይጠበቃል።
እንደ አጠቃላይ ረቂቅ አዋጁ በዜጎች መብት፣ ክብርና ደህንነት ላይ በመደራደር ሀብት ያጋብስ የነበረውን ኃይል የሚገታ ብቻ ሳይሆን በየደረጃው የዜጎችን እና የሀገርን ጥቅም ሲጎዱ የነበሩ ሕገወጥ የጥቅም ማጋበሻ ሰንሰለቶችን በመበጣጠስ ሕጋዊ አሠራርን የሚያሰፍን ነው። ይህ በመሆኑ ሰሞኑን የተለያዩ ረቂቅ አዋጁን በተመለከተ ተገቢነት የሌላቸው መረጃዎች በተለያዩ የመገናኛ ብዘሃን አውታሮች እየተሠራጩ እንደሆ አስተውለናል።
የስራና ክሕሎት ሚኒስቴር አዋጁን ከማሻሻሉ በፊት በትግበራ ሂደት የተገኙ ክፍተቶችን ብቻ ሳይሆን ከኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ፊሊፒንስ ምርጥ ተሞክሮዎች ወስዶ በዝርዝር ተመልክቷል።
በዚህ መነሻነትም ረቂቅ አዋጁ የዜጎችን መብት፣ ደህንነት፣ ክብርና ዘላቂ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንዲሁም ሀገራችን ከዘርፉ ማግኘት ያለባትን ጥቅም ለማስጠበቅ የሚያስችል እንዲሆን ተደርጎ የተዘጋጀ መሆኑን በአጽኖት ለመግለጽ እንወዳለን።
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም
በስራና ክህሎት ሚኔስቴር
አዲስ ዘመን ረቡዕ ሰኔ 18 ቀን 2017 ዓ.ም