የተፈጥሮ አካባቢን ከጥፋት ለመታደግ

ከረጢቶች/ ቦርሳዎች በጥንቱ ዘመን ለሰው ልጆች አገልግሎት ይሰጡ እንደነበር የታሪክ መዛግብት/መረጃዎች ያመለክታሉ። ምግብን ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶች እና አዝዕርት እህሎች ለመያዧነት ያገለግሉም ነበር። ብዙ ጊዜም ከጥጥ፣ ከቆዳ፣ ከቀርቅሃ፣ ከዘምባባ ወይም ከሰሌን፣ ከቃጫ (ዘንቢል የምንለው ዓይነት) ይሰሩ ነበር። በግብፃውያን የቀብር ቦታዎች ቅድመ ልደተ ክርስቶስ (2686-2160) ይህንን የሚያጠነክሩ መረጃዎች ተገኝተዋል።

በግብፃውያን የቀብር ቦታዎች ከተገኙ ቦርሳዎቹ መካከል ከቆዳ የተሠሩ፤ ሁለት ማንጠልጠያ ያላቸው፤ እንደሁኔታው እና እንደ ሸክሙ ክብደት በሁለት ሰዎች ጫፍና ጫፍ ተይዘው ዕቃዎችን የሚፈልግበት ቦታ የሚያደርሱ ትላልቅ የቆዳ ከረጢት ቦርሳዎች ይገኙባቸዋል።

በእኛ ሀገር እስካለንበት ዘመን ድረስ ስልቻ በገጠር እህል በማጓጓዝ የሚያገለግል ነው፤ ረጅም ዘመን የሚያገለግል ጥንታዊ የብራና መጻሕፍትም የቆዳ ከረጢት/ስልቻ/ለረጅም ዘመን በሀገሪቱ የእህል ማጓጓዣ በመሆን ማገልገሉን ይመሰክራሉ።

ብዙዎቻችን ስልቻን የምናውቀው ጤፍ፤ ስንዴ እና የመሳሰለውን ሲይዝ ቢሆንም፤ በአንዳንድ የግብይት ቦታዎች ቅቤ፣ ማር እንዲሁም አይብ የመሳሰሉ በስልቻ ይዘው በመኪና ጭነው ለነጋዴዎች የሚሸጡ ገበሬዎች ብዙ ነበሩ፤ አሁንም አሉ።

ቀስ በቀስም በታሪክ ሂደት ውስጥ የሰው ልጅ የወረቀት ከረጢት /ቦርሶዎችን ወደ መጠቀም ተሸጋግሯል። በዓለም የመጀመሪያው የወረቀት ከረጢት ማሽንም እ.ኤ.አ በ1852 በፍራንሲ ዎሌ ተፈብርኳል። የወረቀት ከረጤቶች ለዘመናትም አገልግሎት ሰጥተዋል።

ከምዕተ ዓመት በኋላ የፕላስቲክ ከረጢት በመምጣቱ ሰዎች ከወረቀት ከረጢት ፊታቸውን አዙረዋል። በቀላሉ እጥፍጥፍ የሚለውና በኪስ የሚቀመጠው የመገበያያ ፕላስቲክ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሥራ የገባው በስዊድናዊው ኢንጅነር ስቴፍ ጉስታፍ ትሁሉን፤ እንደነበር ከዊኪፒዲ ድረ ገጽ የተገኘ መረጃ ያስረዳል።

እ.ኤ.አ. በ1960ዎቹ ወደ ዓለማችን የመጣው የላስቲክ ከረጢት በወቅቱ ሲመረት ቀላል ግን ጠንካራ ሆኖ ከፍተኛ ክብደት ያላቸውን ዕቃዎች መያዝ የሚችል እና በቀላሉ፤ ሳይቀዳደድ ለረጅም ጊዜ የሚገለገሉበት ነበር። ከ1980ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በሰለጠኑት ሀገራት የፕላስቲክ ቦርሳዎች በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎች መደበኛ መገልገያ ሆኑ።

በግሮሰሪዎች፣ በዕቃ መገበያያ መደብሮች፣ በግለሰቦች ጭምር የፕላስቲክ ከረጢት ተፈላጊነት እየጨመረ፤ ዘንቢል፣ የጨርቅ ከረጢት እና ሌሎችን ከገበያ ወጡ። ቀስ በቀስም የፕላስቲክ ከረጢቶች ገበያውን ተቆጣጠሩ፤ ይህን ተከትሎም ለአንድ ጊዜ የሚያገለግሉ የፌስታል ከረጢቶችን በገበያ ውስጥ ገዝፈው መታየት ጀመሩ።

ከረጢቶቹ ቅጥነታቸው በብዛት ከ50 ማይክሮንስ በታች መሆኑ በቀላሉ ከጥቅም ውጪ እንዲሆኑ ከማድረግ ባለፈ” በስፋት መመረታቸው፤ በተፈጥሮ አካባቢ ላይ ከፍተኛ ጥፋት እንዲያስከትሉ አድርጓቸዋል፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ የፈጠሩት አሉታዊ ተፅዕኖም ‹‹በቀላሉ የሚቀደድ የፕላስቲክ ከረጢት ይወገድ›› የሚል ዘመቻን አስከማስነሳት ደርሶ ነበር።

ችግሩን ለመከላከልም በዓለም በየዓመቱ ጁን 12 ቀን የዓለም የወረቀት ከረጢት ቀን ወይም የወረቀት ቦርሳ ቀን እንዲከበር አስገድዷል። ቀኑ የሚከበርበት ዓላማም ሕዝቡ ለአካባቢ ሥነምህዳር ምቹ የሆነውን የወረቀት ከረጢት እንዲጠቀምና የላስቲክ ከረጢትን ወይም ፌስታልን ከመጠቀም እንዲቆጠብ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው።

የዓለም ወረቀት ከረጢት ቀን ትኩረቱ፤ የወረቀት ከረጢት ለኅብረተሰቡ ያለውን አካባቢያዊ ጠቀሜታ እና የፕላስቲክ ከረጢት ለአካባቢ ሥነ-ምኅዳር ላይ ያለውን ተፅዕኖ በመግለጽ የኅብረተሰቡን ግንዛቤ በማስፋት፤ ቀኑን ለመዘከርና ለማክበር ነው።

ቀኑ ብዙ ትምህርት ቤቶችና ተቋማት የወረቀት ከረጢት የመሥራትና የመጠቀምን ክህሎት ለተማሪዎች እና ለተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በማስገንዘብ የራሳቸውን የወረቀት ከረጢት በመሥራት በሂደት እንዲገለገሉበት ለማስቻል ነው። በአጭር አማርኛ ኅብረተሰቡ የፕላስቲክ ከረጢት ጥሎ የወረቀት ከረጢት እንዲገለገል ለማድረግ ነው።

በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፕላሲክ ከረጢትን የሚያግድ አዋጅ ሲወጣ፤ የፕላስቲክ ከረጢቶች ሀገርን እንደሚጎዱ እስከ 100 ዓመት ድረስ እንዳማይበሰብሱ በአባላቱ ክርክር ላይ የተገለጸ ሲሆን ቅጣቱ ሀገርን ለማትረፍ ታስቦ እንደሆነ ተገልጿል። ፌስታሉ በተቀበረበት አካባቢ ደግሞ በመሬቱ ስር ውሃ ዝናብ እንዳይገባ በማገድ ሣርና ዕጽዋትና አታክልት እንዳይበቅሉ ከበቀሉም ሳይበስሉ ሳይደርሱ እንዲደርቁ ያደርጋል።

የተጠቀሰውን ችግር በመረዳት ስስ ፕላስቲክ ቦርሳዎችን ጠቅላላ በማገድ ረገድ በበርጉሃም ክሃሌዳ ዚያ የሚመራው የባንግላዴሽ መንግሥት እ.ኤ.አ. በ2002 ቀዳሚ ነበር። ይህንኑ ተከትሎ ከ2010-2019 ፕላስቲክ ከረጢት ከገበያ ያገዱ ሀገራት በሦስት እጥፍ ጨምረዋል። እ.ኤ.አ. በ2024 በ127 ሀገራት በፕላስቲክ ከረጢት ላይ የቁጥጥር ደንብ ያወጡ ሲሆን፤ 27 ሀገራት በፕላስቲክ ከረጢት ለሸማቾች ዕቃዎች እንዳይሸጡ፤ 30 ሀገራት ደግሞ፤ ለሸማቾች የፕላስቲክ ከረጢት ከሸጡ እንዲቀጡ የሚደነግግ ሕግ አጽድቀዋል።

ዘንድሮ የዓለም አካባቢ ቀን ግንቦት 28 ቀን 2017 ‹‹ ለፕላስቲክ ብክለት መቋጫ እናበጅለት›› በሚል መሪ ቃል ሲከበር፤ በዓለም በየዓመቱ 8 ሚሊዮን ቶን ፕላስቲክ ቆሻሻ ወደ ውቅያኖሶች እንደሚለቀቅ ተገልጿል። በዚህ መጠን በየዓመቱ የሚለቀቅ የፕላስቲክ ቆሻሻን ለማስቆም ዓለም አቀፍ ትብብር እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል።

”ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሔ ካልተወሰደ በፈረንጆቹ 2050 በባሕር ላይ ከዓሣዎች ይልቅ ብዙ የተወገዱ የፕላስቲክ ቆሻሻዎች ተጥለውበት እናገኛለን ”ሲልም በቀኑ የወጣው መረጃ አስጠንቅቋል።

በአንዳንድ የአፍሪካ ሀገራት ችግሩ አሳሳቢ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። ለምሳሌ በጋና ያለውን ብንመለከት፤ ሀገሪቱ ብቻዋን በዓመት 840 ሺህ ቶን የተወገደ ፕላስቲክ ‹ታመነጫለች› ከዚህ ውስጥ በዳግም ዑደት ለማምረት የሚሰበሰበው የወዳደቀ ፕላስቲክ 9 ነጥብ 5 በመቶው ብቻ እንደሆነ መረጃዎች ይናገራሉ።

በአፍሪካ ፌስታል በማገድና በማስወገድ ደረጃ ሩዋንዳ፣ ኬንያ ሞሮኮ፣ ታንዛንያ፣ ማሊ፣ ካሜሩን፣ ኢትዮጵያ፣ ሴኔጋል፣ ደቡብ አፍሪካ እና ቦትስዋና በቅደም ተከተል ይጠቀሳሉ። ሰሞኑን ፌስታልን አስመልክቶ የወጣው ሕግም የዚህ እውነታ ማሳያ ነው።

በሕጉ መሰረት የአንድ ብሩን ፕላስቲክ ከረጢት የያዘ ከ2ሺህ እስከ 5ሺህ ብር ያስቀጣል። ያከማቸ ደግሞ ከ50 ሺህ ብር በማያንስ ከ200ሺህ ብር በማይበልጥ እንደሚቀጣ ደንግጓል። በአዋጁ መውጣት አንዳንድ ግለሰቦችና የፕላስቲክ ከረጢት አምራች ድርጅቶች እየተበሳጩና እየተንጫጩ ነው። አዋጁ ለምን ወጣ የሚል ቁጣ መሆኑ ነው።

በሀገራችን ከኢመደበኛ ውጪ በመደበኛነት የተመዘገቡና የሚሠሩ 860 የፕላስቲክ አምራች ድርጅቶች አሉ፤ ጥቅል ካፒታላቸው 58 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር እንደሚገመት የፕላስቲክና ጐማ አምራቾች ማኅበር የወጣው መረጃ ያሳያል።

ማኅበሩ በተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ የጸደቀውን የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ አዋጅ በመቃወም በሰጠው መግለጫ፤ ከአዋጁ ረቂቅ ጀምሮ ባለድርሻ አካላትን የፕላስቲክ ውጤት አምራቾችን ሆኑ ማኅበራትን እንደማኅበር አላናገሩንም። የአሳታፊነት ችግር ነበረበት ብሏል። በፌስታል ምርት ጥቅል ሀገራዊ ጠቀሜታ 51 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር አስተዋጽዖ የሚያደርግ ኢንዱስትሪ እንደሆነም አመልክቷል።

አሁን ላይ 90 በመቶው የሚሆነው ፕላስቲክ (ፌስታል) የሚያሠራው በአካባቢያችን ከሚገኙ እና ሌሎች ኢንዱስትሪዎች ከሚያመነጩዋቸው እንደ ዘይት ጀሪካን እና የመዋቢያ (ኮስሞቲክስ) ዕቃዎች ከመሳሰሉ ደረቅ ቆሻሻዎች እንደሆነም ማኅበሩ ገልጿል።

ማኅበሩ በራሱና በገለልተኛ ቡድን አማካኝነት አሠራሁት ባለው ጥናት ኢንዱስትሪው በዓመት 441ሺህ 228 ነጥብ 8 ቶን ቆሻሻ በዳግም ዑደት (Recycling) ይጠቀማል። ፌስታል ከውጭ ይገባ ከነበረበት አሠራር ከማስቀረት በተጨማሪ ጥሬ ዕቃውን በሀገር ውስጥ መተካቱን እና ከውጭ ይገባ የነበረን ጥሬ ዕቃ በመተካት 350 ሚሊዮን ዶላር ማዳን እንዳስቻለ ተናግሯል።

በየአካባቢው በርካታ ወጣቶች በማዳበሪያ ላስቲክ እና ጀሪካን እየለቀሙ ለፋብሪካዎች በግብዓት ያቀርባሉ። በዳግም ዑደት ከፋብሪካ የወጡ ተረፈ ምርቶችን መጠቀምና ማምረት በመቻሉ ለአካባቢ ጥበቃ ያበረከተው አስተዋጽዖ ዕውቅና ሊሰጠው እንደሚገባ ማኅበሩ ይሞግታል።

ከማኅበሩ በተጨማሪ ብዙ ሰዎች የፕላስቲክ ከረጢት አገልግሎት በአዋጅ መታገዱ አልተዋጠላቸውም። ይህም ሰዎች ፌስታል ደረቅ ቆሻሻ ሆኖ አካባቢ በመበከል የሚያስከትለውን ተጽዕኖ ባለመገንዘብ ያለፈ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት ማድረጋቸው ሊሆን እንደሚችል ይሰማኛል።

የፌስታል አካባቢ በመበከል ረገድ የአዲስ አበባን ወንዞችና ጅረቶች ማየት በቂ ነው። ወንዛ ወንዙ ዳርቻ ወንዞቹ መሃል ፌስታሎች ተሰግስገው አንደ ባንዲራ ሲውለበለቡ ይታያሉ። በብዛት በክረምት ወንዞች ጅረቶች ሲሞሉ ፌስታሎች በብዛት ስለሚታዩበት፤ ከሰማይ እንደ በረዶ ፌስታል መዝነብ ጀመረ እንዴ ሊያስብለን ሁላ ይችላል።

በተጨማሪም አስፋልት ዳር እና በየመንደሩ ያሉ የፍሳሽ ቱቦዎች በእንዝህላል ሰዎች ሃይላንድና ፌስታል ቆሻሻ እየተጣለባቸው ፍሳሽ ማለፊያ አጥቶ በአስፋልት ላይ ኮለል እያለ ሲፈስና ብዙ ወጪ የወጣበት አስፋልትን ሲቦረቡር የምናየው እውነታ ነው።

ችግሩን ለመቅረፍ አንዳንዴ ትቦውን ቆፍረው የተሰገሰገውን የላስቲክ ቆሻሻ በብዛት ሲያወጡ ይታያል። ክስተቱ በየዓመቱ ተደጋጋሚ በመሆኑ ሥራው ‹‹ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ›› ይመስላል። ዘለቄታዊ መፍትሔ በየዓመቱ ትቦ መቆፈር ሳይሆን የላስቲክ ከረጢትን ማገድ ነው።

ከገጠር አካባቢ የመጡ አንድ ገበሬ በፌስታል ጨው ገዝተው ሲያበቁ ጨውን እቤት በዕቃ ገልብጠው ፌስታሉን ሲጥሉ የቀንድ ከብታቸው ፌስታሉ ጨው ስላለበት በልቶ ፌስታሉ አንጀቱ ላይ ተለጥፎ እንደሞተ ሲያወሩ ሰምቻለሁ። ችግሩ በመደጋገሙም የአካባቢው ገበሬዎች ፌስታል ወደ አካባቢው እንዳይገባ መወሰናቸውንም ሰምቻለሁ።

ብዙዎቻችን የላስቲክ ከረጢት ጉዳት በከተሞች ብቻ የተገደበ ይመስለናል። ከፍተኛ ችግሩ የሚታየው በገጠር አካባቢዎች ነው። ከከተሞች ወጣ ባሉ አካባቢዎች ሰዎች ለሥራም ሆነ ለልዩ ልዩ ጉዳዮች ሲሄዱ ውሃ በፕላስቲክ ይይዛሉ። ውሃውን ከተጠቀሙ በሁዋላ ከአስፋልት ዳር ባሉ የገበሬ ማሳዎች ላይ መጣል የተለመደ ነው።

በግጦሽ መስክና በእርሻ ማሳ ቦታዎች ፌስታልና ሃይላንድ መጣል እንዲሁ፤ ይህም የመሬቱን ምርታማነት ከመቀነስ ባለፈ፣ የእርሳ መሬቶችን ለተጨማሪ ስጋት የሚዳርግ እንደሆነ የተለያዩ ጥናቶች ያመለክታሉ። ከቆሻሻነት አልፎ ለግብርና ልማት ተግዳሮት ይሆናል። ይህንን እና ሌሎች በዚሕ ጽሁፍ ያላነሳኋቸውን ችግሮች ታሳቢ በማድረግ ፌስታልን በማገድና ላለመጠቀም በመወሰን የተፈጥሮ አካባቢን እንጠብቅ፤ ከጥፋት እንታገድ።

ይቤ ከደጃች ውቤ

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You