በስልሳ ስድስት ሚሊዮን ብር የመዝናኛና ወጣቶች ማረፊያ እየተገነባ ነው

መተሀራ፦ በሰቃ ሃይቅ ዳርቻ በ66 ሚሊዮን ብር ወጪ የመዝናኛና የወጣቶች ማረፊያ እየተገነባ እንደሚገኝ የምስራቅ ሸዋ ዞን መተሀራ ከተማ ከንቲባ አቶ አዲሱ ዋቆ ገለፁ። የፕሮጀክቱ ግንባታ አፈጻጸም 75 በመቶ መድረሱንና ወጪውም ሙሉ በሙሉ በአስተዳደሩ የተሸፈነ እንደሆነ አመልክተዋል።

የመተሀራ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደተናገሩት፤ ከተጀመረ ሁለት ወራት ያስቆጠረው የመዝናኛና የወጣቶች ማረፊያ በቀጣዩ 45 ቀናት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። በበሰቃ ሀይቅ ዳርቻ እየተገነባ ያለው ፕሮጀክት ወጣቶች ተደራጅተው መኪና የሚያጥቡበት፣ የፓርኪንግ አገልግሎት የሚሰጡበት፣ በመግቢያው ላይ ደግሞ ዘመናዊ የዓሳ ርባታ የሚካሄድበት ሰፋፊ ግንባታዎችን ያካተተ ነው ብለዋል።

በተንጣለለው ጊቢ ውስጥም የህፃናት መጫወቻ፣ ዘመናዊ ካፍቴሪያ፣ የሀይቁን ዳርቻ የሚያሳይ እና የጀልባ ጉዞን የሚያካትት ግንባታዎችን የያዘ እንደሆነ አስረድተዋል።

በተጨማሪ በመዝናኛ ስፍራው ለሚመጡ ተጠቃሚዎች የእግር ጉዞ የሚሆን አንድ ነጥብ አምስት ኪሎ ሜትር መንገድ እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

‹‹የፕሮጀክቱ አካል የሆነው የዓሳ ርባታ ከዓሳ ሽያጭ ባሻገር ለጎብኚዎች እይታ ማራኪ የሆነ እና ለቱሪስቶች ተመራጭ እንዲሆን ተደርጎ እየተገነባ ነው›› የሚሉት ከንቲባው አቶ አዲሱ ዋቆ፤ በግንባታው ውስጥ ለዓሳ ርባታ ምቹ የሆኑ ትልልቅ ሰው ሰራሽ ኩሬዎች እየተገነቡ መሆኑን ተናግረዋል።

በዓሳ ርባታ ላይ ትኩረት ያደረግነው የፕሮጀክቱ አካል የሆነው በሰቃ ትልቅ ሀብት መሆኑን ጠቁመው፤ የከተማዋ ነዋሪም ዓሳን እንደ ባህል የሚጠቀም ሲሆን በጉብኝትና በሥራ የሚመጡ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ዜጎች ጥራት ያለው የዓሳ አቅርቦት እንዲያገኙ እንደሚረዳ አስረድተዋል።

በርካታ መኪኖች ከተማው ላይ አርፈውና አድረው ይሄዳሉ የሚሉት ከንቲባው፤ የፓርኪንግ አገልግሎቱ በፕሮጀክቱ መካተቱን ያነሳሉ፤ ግንባታው ሲጠናቀቅም ለተጠቃሚዎቹም ሆነ ተደራጅተው አገልግሎቱን ለሚሰጡ ጉልህ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል።

እንደ ከንቲባው ገለፃ፤ የወጣቶች ማረፊያና መዝናኛ ፕሮጀክቱ ወጣት ተማሪዎች የንባብ ባህላቸውን የሚያዳብሩበት አራት ብሎኮች ያሉት 24 ክፍሎችን ያካተተ ነው። በተጨማሪ ሁለት ትላልቅ ካፍቴሪያዎች በበሰቃ ሃይቅ ዳርቻ እየተዝናኑ ጊዜያቸውን እንዲያሳልፉ በማሰብ እየተገነባ ነው። በተለይ የመተሀራ ከተማ የበረሃማነት ፀባይ ስላለው ከሃይቅ ዳርቻው እና በመዝናኛ ስፍራው ከሚተከሉ ዛፎች ነፋሻማ የአየር ፀባይ ይፈጠራል። የመዝናኛ እና የወጣቶች ማረፊያ ግንባታው የአካባቢውን ባህል የከተማዋን ማህበረሰብ እሴት በሚያንፀባርቅ መልኩ እየተገነባ እንደሆነ ተናግረዋል።

‹‹ሙቀቱን ለማብረድ የሚዋኙ የከተማ ነዋሪዎች በበሰቃ ሃይቅ ውስጥ ባለው አዞ ጥቃት እየደረሰባቸው ነው›› የሚሉት ከንቲባው አቶ አዲሱ፤ ይህንን ለማስቀረት ህጻናት፣ ወጣቶች እና የከተማዋ ነዋሪ የሚዝናናበትና ሙቀቱን ለመቋቋም የሚታጠቡበት ሁለት ገንዳዎች ግንባታ የፕሮጀክቱ አንድ አካል መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ ተጠናቅቆ ወደ ሥራ ሲገባ በጥቅሉ ለ100 ወጣቶች ሥራ እድል የሚፈጥር መሆኑን አመልክተው፤ ከሥራ ፈጠራ ባሻገር የከተማዋን ገፅታ በመቀየር እና የቱሪስት ፍሰቱ እንዲጨምር ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል ነው ያሉት። በተለይ በበሰቃ ሃይቅ ላይ የሚገነባው ፕሮጀክት በትልቅነቱ የመጀመሪያው ነው፤ የሚሉት ከንቲባው፤ እንደ መንግሥት ተነሳሽነቱን ወስደው መሥራታቸውን ይገልፃሉ። መሰል ፕሮጀክቶቸን ሎጆችን እና ሆቴሎችን በግል ባለሀብት ለማሠራት ትልቅ ፍላጎት አለ። ደረጃውን የጠበቀ ሆቴል በግል ባለሀብት እየተሠራ መሆኑን ገልፀዋል።

ለቱሪዝም እና ለመዝናኛ አገልግሎት የሚውል ለግል ባለሀብቱ ክፍት የሆኑ ሰፋፊ ቦታዎችን የከተማ አስተዳደሩ ማቅረብ ይችላል ያሉት ከንቲባው፤ ለወጣቱ የስራ እድል የሚፈጥር ተግባር ለማከናወን ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። አንዳንድ ወጣቶች በሱስ ይጠመዳሉ የሚሉት የከተማዋ ከንቲባ ፤ይህ እንዳይሆን በሥራ ፈጠራ በመዝናኛ ቦታ ግንባታ ላይ ሰፊ ፕሮጀክቶች ለመሥራት መታቀዱን ተናግረዋል። በቅርብ ግንባታው የሚጀመረው ስታዲዮምም የዚሁ አካል እንደሆነም አመልክተዋል።

ዳግም ከበደ

አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 19 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You