
አዲስ አበባ፦ በሶስተኛው ቢግ 5 ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን 250 የሚጠጉ ኩባንያዎች ምርትና አገልግሎታቸውን እንደሚያቀርቡ ከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሶስተኛው ቢግ 5 ዓለም አቀፍ ኤግዚቢሽን ከዛሬ ሰኔ 19 እስከ 21 የሚካሄድ መሆኑን አስመልከቶ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ በሰጡት መግለጫ እንደተናገሩት ፤ በኤግዚቢሽኑ ከ20 ሀገራት የተውጣጡ 250 የሚጠጉ ኩባንያዎች ምርትና አገልግሎታቸውን ያቀርባሉ።
ባለፉት ሰባት ዓመታት የኮንስትራክሽን ዘርፉ እድገት እያሳየ እንደሚገኝ ያነሱት ሚኒስትሯ፤ የኮሪዶር ልማቱን ጨምሮ የኮንስትራክሽን ሥራ ትልቅ መነቃቃት አሳይቷል። ከዚህ አንፃር በዘርፉ ያለው የልምድና እና የእውቀት ፍላጎት እያደገ መምጣቱን ገልፀዋል።
እንደ ሀገር የኮንስትራክሽን ዘርፍ አጠቃላይ ለሀገር ውስጥ ምርት 19 በመቶ የሚሆነውን ሚና እንዳለው አመልክተው፤ ነገር ግን ከአሠራር ጀምሮ አዳዲስ ቴክኖሎጂ ከመጠቀም፤ በቂ ባለሙያዎችን ከማፍራት፤ እና ከግብዓት ዋጋ መወደድን ጨምሮ ክፍተቶች እንደሚስተዋሉበት ተናግረዋል።
ክፍተቶቹን ለመሙላት እና በዘርፉ ልምዶችን ለማግኘት ከምርምር ጀምሮ አጠቃላይ በዘርፉ ከሚገኙ ባለድርሻ አካላት ጋር መወያየት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፤ ከዚህ አንፃር እንደ ቢግ 5 አይነት ኤግዚቢሽኖች ጉልህ አስተዋጽኦ አላቸው ሲሉ አስረድተዋል።
ወይዘሮ ጫልቱ እንደተናገሩት፤ ኤግዚቢሽኑ የቴክኖሎጂ እና የእውቀት ልውውጥ በማድረግ ለፖሊሲ ግብዓት የሚሆኑ ልምዶችን ለማግኘት ያስችላል።
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ዮናስ አያሌው በበኩላቸው እንደገለፁት፤ ያለፉት ሁለት ኤግዚቢሽኖች በኮንስትራክሽን ዘርፍ አቅም የፈጠረ ሲሆን፤ የዘንድሮ ኤግዚቢሽን ዘርፉን በማዘመን ኢትዮጵያ ዓለም የደረሰበት የኮንስትራክሽን ደረጃ እንድትደርስ የሚያስችል ነው።
በዚህም ባለፈው ዓመታት የተካሄዱት ኤግዚቢሽኖች በዘርፉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ወደ ሥራ ለማስገባት ያገዙ መሆናቸውን በመግለፅ፤ በዘንድሮው ዓመት ኤግዚቢሽን መሠረተ ልማት ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
በዝግጅቱ ምርትና አገልግሎታቸውን ከሚያቀርቡ ተሳታፊዎች በተጨማሪ፤ ዓለም አቀፍ ሰርተፊኬት የሚያሰጡ ስልጠናዎች የተዘጋጁ በመሆኑ በዘርፉ የሚገኙ አካላት እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።
ዓመለወርቅ ከበደ
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 19 ቀን 2017 ዓ.ም