ሕጎች ሲወጡ ሕገ-መንግሥትን መሠረት አድርገው ነው። ሕገ-መንግሥቱን የሚቃረኑ የሕግ ድንጋጌዎች በየትኛውም መንገድ ተግባራዊ የሚሆኑበት አግባብ የለም። ይህም ሆኖ ግን በታክስ አስተዳደር አዋጅ ለታክስ ይግባኝ ኮሚሽን እና ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ስለማቅረብ በሚሉት የተቀመጡ አንቀጾቹ (አንቀጽ 56 እና 57) ዙሪያ ሕገመንግሥቱን ጠቅሰው ጥያቄ የሚያነሱ አሉ።
በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ አቶ አያሌው ቢታኒ እንደሚሉት፤ አንድ ነጋዴ በታክስ ሰብሳቢ መሥሪያ ቤት የተጣለበት ግብር ላይ ቅሬታ ቢኖረው ለታክስ ይግባኝ ኮሚሽን ቅሬታውን ለማቅረብ በታክስ አስተዳደር አዋጅ መሠረት የግድ ቅድሚያ 50 በመቶ መክፈል ይጠበቅበታል ።
የገቢ ግብር አዋጅ 979/2008 በመግቢያው ላይ የሀገራችን የኢኮኖሚ ዕድገት ከደረሰበት ደረጃ ጋር የተጣጣመ እና የኢኮኖሚውን ዕድገት የሚያግዝ ዘመናዊና ቀልጣፋ የግብር ሥርዓት መዘርጋት በማስፈለጉ፤ የግብር አከፋፈሉ ሥርዓት ፍትሐዊነት ያለው እንዲሆን አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የወጣ መሆኑን አቶ አያሌው አዋጁን ጠቅሰው ይናገራሉ።
አቶ አያሌው አዋጁን ሲያብራሩ፤ ሕጉ በመጀመሪያ ያስፈለገበት ምክንያት የኢኮኖሚ እድገቱ ከደረሰበት ጋር ለማጣጣም እና እድገቱን ለማገዝ ግብር ከፋዩ ወይም ነጋዴው ማኅበረሰብ ግብሩን በአግባቡ መክፈል አለበት ከሚል እሳቤ በመነሳት ነው ይላሉ። ግብሩን በአግባቡ ካልከፈለ ደግሞ ተቆጣጣሪ አካል ማለትም ጉምሩክ ወይም ገቢዎች ሚኒስቴር ኃላፊነታቸውን ባልተወጡ ግለሰቦች ላይ ርምጃ ይወስዳሉ፤ እንዲከፍሉም ያደርጋሉ።
የሕግ አማካሪው እንደሚናገሩት፤ የግብር አከፋፈል ሥርዓቱ መሆን ያለበት ፍትሐዊ እና ግብር የማይከፈልባቸው ገቢዎች በግብር መረብ ውስጥ እንዲገቡ ማድረግ መሆኑም ተደንግጓል። ፍትሐዊ
የሚለውን ከአዋጁ ላይ በመውሰድ ስናየው፤ አንድ ግብር ከፋይ እንዲከፍል የተጠየቀው ግብር ፍትሐዊ ነው? ወይስ አይደለም? የሚለው ጉዳይ በአግባቡ ሊታይ ይገባል።
ፍትሕ የማግኘት መብት የዜጎች መሠረታዊ መብት መሆኑን የሚናገሩት አቶ አያሌው፤ ይሄውም በሕገ-መንግሥቱ ውስጥ እና በዓለም አቀፍ የቃልኪዳን ስምምነቶች ውስጥ የተደነገገ መሆኑን ያብራራሉ። የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት፣ አንቀጽ 37 እንዳስቀመጠው ማንኛውም ሰው በፍርድ ሊወሰን የሚገባውን ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይም ለሌላ በሕግ የዳኝነት ሥልጣን ለተሰጠው አካል የማቅረብና ውሳኔ ወይም ፍርድ የማግኘት መብት አለው።
የገቢ ግብሩ ላይ የተቀመጠውን ‹‹ፍትሐዊ እንዲሆን›› የሚለው ሃሳብ ፍትሕ የማግኘት መብትን በማይጥስ መልኩ መሆን እንዳለበት ከግምት ውስጥ ሊገባ እንደሚገባም የሕግ አማካሪው ይጠቅሳሉ። ይሄ ሲወሰድ ሕገ-መንግሥቱ ላይ የተቀመጠው ፍርድ ሊሰጥ የሚገባው ጉዳይ ለፍርድ ቤት ወይንም የዳኝነት ሥልጣን በተሰጠው አካል ፍርድ የማግኘት መብት መሠረታዊ የሆነ የማይገረሰስ የዜጎች መብት መሆኑንም ያብራራሉ።
አንድ 20 ሚሊዮን ብር ግብር የተጣለበት ዜጋ ፍርድ ለማግኘት 10 ሚሊዮን ብር ክፈል የሚባል ከሆነ ለማንኛውም ዜጋ ሕገ-መንግሥቱ የሰጠውን መብት አጣብቦታል ማለት እንደሚቻልም አቶ አያሌው ይናገራሉ። ከዚህ አንጻር የግብር ይግባኝ ኮሚሽን ጋር ለመሄድ 50 በመቶ፤ ኮሚሽኑ ውሳኔውን ቢያጸና ደግሞ 25 በመቶ ተጨማሪ ክፍያ በመክፈል 75 በመቶ የተጣለበትን ግብር ግለሰቡ ይከፍላል። ይህ ማለት ደግሞ ቅድመ ዳኝነት ተወስኖበታል።
ከዚህ በኋላም ተመልሶ ገንዘቡን የማግኘት ሁኔታውም ጠቧል። በዚህ ሁኔታም አዋጁ ቅሬታ ለማቅረብ እና ውሳኔ ለማግኘት የሚያስችል ነው ለማለት አያስደፍርም ወይም አዳጋች ነው ባይ ናቸው። ስለዚህ ከዜጎች ሕገ-መንግሥታዊ መብት ጋር የሚጣጣም አዋጅ ሊወጣ ይገባል ይላሉ።
ግለሰቦቹ ገንዘቡን እንዲከፍሉ የሚደረጉት እንዳይጠፉ በሚል ከሆነም መንግሥት ትልቅ አቅም ያለው በመሆኑ ከኢሚግሬሽን እና ከሌሎች መሥሪያ ቤቶች ጋር በመነጋገር ሌሎች አማራጮችን መውሰድ ይችላል። ካልሆነም በካሽ ብቻ እንዲከፍሉ እና እንዲከራከሩ ከማድረግ ንብረታቸውን ማስያዝ የሚችሉበት አሠራር ሊመቻች እንደሚገባም የሕግ ባለሙያው ይገልጻሉ።
ዜጎች መንግሥት እና ሕግን ሊያከብሩ ይገባል፤ በሕገ-መንግሥቱ መሠረትም ጉዳያቸው ሊፈጸምላቸው ይገባል፤ እንጂ እንደ ቀንበር ሊጫንባቸው አይገባም። ግብር እና ታክስ ከማናቸውም ዕዳ ቀዳሚ ዕዳ ስለሆኑ ነጋዴዎቹ ቢጠፉ እንኳን ያሏቸውን ንብረቶች በመሸጥ ገንዘቡን ማግኘት ይቻላል። በመሆኑም ቅድሚያ ክፍያ ለመጠየቅ እንደ መነሻ ሊሆን አይችልም የሚል እሳቤ አላቸው።
ሀገሪቱ ካለችበት የገንዘብ እጥረት ‹‹የሊኪዩዲቲ እጥረት›› አንጻር ክፍያው በሙሉ በካሽ የሚሆን ከሆነ ዜጎች ያሏቸውን አንጡራ ሃብቶች ሁሉ ሊያጡ እና ከንግድ ሥርዓት ውስጥ ሊወጡ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ይናገራሉ።
ብዙ ሀገራትም የፍትሕ ሥነ-ሥርዓት ሕጉን የሚከተሉ ናቸው። የዳኝነት አከፋፈል ሥርዓትን ይከተላሉ። አቶ አያሌው ባሏቸው፤ መረጃም ሌሎች ሀገራት ላይ ያለው አካሄድ የቁርጥ ክፍያን የሚጠይቅ እንጂ እንደኛ ሀገር ዓይነት አካሄድ የሚከተሉ እንዳልሆኑ ይጠቅሳሉ።
ዜጎች መንግሥትን እና ሥርዓትን የሚፈሩ ማድረግ ሳይሆን ግብር ማለት ዕዳ አለመሆኑን እንዲገነዘቡ ማድረግ ያስፈልጋል። ተቋማትም የሚገነቡት ከግብር ከፋዩ በሚሰበሰቡ ክፍያዎች መሆናቸውን ማስታወቅ ይገባል። የግብር አከፋፈል ሥርዓቱ ዜጎች የሚፈሩት እና የሚደነግጡበት ከማድረግ ይልቅ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ሊሠራ እንደሚገባ አመልክተዋል።
አሁን ያለው የአከፋፈል ሥርዓት ዜጎች ለሙስና እና ብልሹ አሠራሮች እንዲጋለጡ የሚያደርግ መሆኑን አቶ አያሌው ይገልጻሉ። ለዚህም እንደምክንያትነት የሚጠቀሰው ነጋዴው የግብሩን 50 በመቶ እና 75 በመቶ ከፍሎ ይግባኝ ከመከራከር ይልቅ በቀላሉ ጉቦ በመክፈል
ግብሩን ለማስቀነስ እንዲሞክር ያደርገዋል። በተጨማሪም መክፈል የሚያቅተው ነጋዴ ሥራውን እንዲተው እና ከጫወታው እንዲወጣ ይሆናል፤ ይሄም ለሀገር፣ ለዜጋው እና ለቤተሰቡ ጎጂ ይሆናል ይላሉ።
ጠበቃ እና የሕግ አማካሪ አቶ አደራው አዲሱ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ የዜጎች ቅሬታ ሲኖራቸው ከመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጀምሮ እስከ ላይኛው ድረስ ቅሬታቸውን የማቅረብ መብት አላቸው። ነገር ግን በታክስ አከፋፈል ሥርዓት የይግባኝ ቅሬታ አቀራረብ ላይ የሚጠየቀው ክፍያ አንድ ሰው ገና ቅሬታ እያለበት ከፍርድ አሰጣጡ በፊት ፍርድ ወይም ውሳኔ የተሰጠበት ነው።
በሁለቱ ተከራካሪዎች መካከልም ሁለት የዳኝነት ካስማ ውስጥ በማስገባት በእኩልነት የመዳኘት መብትን ያሳጣል። ማለትም አንዱን ወገን በማመን 50 በመቶ ክፈል ማለት ውሳኔው በ50 በመቶ ትክክል ነው እንደማለት ይቆጠራል ሲሉ ይገልጻሉ።
ቅሬታ አቅራቢዎችም ሁለት ዓይነት ናቸው የሚሉት የሕግ ባለሙያው፤ አንዳንዶቹ ብዙ ተወስኖብኛል ይቀነስልኝ ሲሉ ሌሎቹ ደግሞ ጭራሽ ያልሠራሁበት ነው የሚሉ ናቸው። ይሄ በሚሆንበት ጊዜም ምንም የሌላቸው ዜጎች ተበድረው ለመክፈል ይገደዳሉ። በዚህም በግብር ዜጎች እንዲማረሩ ዕድል ይፈጥራል። በግብር ሥርዓቱም ላይ ታማኝነትን ይቀንሳል። የመንግሥት ካዝና ውስጥ የገባ ብርም ተመላሽ ካልሆነ መንግሥት ከዜጋው እንደተበደረ ይቆጠራል፤ በዚህም ዜጋው ችግር ውስጥ ይገባል ብለዋል።
ግብር የአንድ ሀገር ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ነው የሚሉት አቶ አደራው፤ የክትትል እና የቁጥጥር ሥራውን ማዘመን ተገቢ መሆኑንም ይናገራሉ። የግብር አከፋፈል ሥርዓትም የዜጎችን መብት ሊጥስ አይገባም ይላሉ። ከዳኝነት በፊትም ገንዘብ መጠየቅ ፍትሕ የማግኘት መብት ላይ ኬላ ማበጀት ነው። ይሁን ቢባል እንኳን 50 በመቶ ክፍያ ከመጠየቅ የዋስትና እና የማስያዢያ አማራጭ ሊቀርብ እንደሚገባም አመላክተዋል፡፡
መክሊት ወንድወሰን
አዲስ ዘመን ሐሙስ ሰኔ 19 ቀን 2017 ዓ.ም